Tuesday, 25 August 2020 00:00

“ ክፉውን ከእናንተ አርቁ ” (፩ኛ ቆሮ. ፭፥፲፫)

Written by 
ኢትዮጵያ ጥንታዊት ሐዋርያዊት ርትዕት የሆነችው የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ሀገር ናት፡፡ ኢትዮጵያ ሀገረ እግዚአብሔር መባልዋም እግዚአብሔርን በብሉይ ኪዳን የአመለከች፣ በልደቱ ቤተ ልሔም ድረስ አምኃ ይዛ የሄደችና ሰግዳ መባዕ ያቀረበች (መዝ. ፸፩፥፱-፲፩)፣ በስደቱ ጌታን ከእናቱ ጋር የተቀበለች፣ በጃንደረባው አማካይነት በመጀመሪያው ምዕተ ዓመት ወንጌልን ተሰብካና አምና በሐዋርያት እጅ ተጠምቃ ክርስትናን የተቀበለች (ሐዋ.፰፥፳፯-፵) ሀገር በመሆኗ ነው፡፡ ወደ ፈጣሪዋ የተዘረጉት እጆቿ በዘመነ ብሉይም ሆነ በዘመነ ሐዲስ ከማንም አገር በተለየ ሁኔታ መንፈሳዊ ስጦታዎችን ከእግዚአብሔር ተቀብለዋል፡፡ ለአብነትም በዘመነ ብሉይ ታቦተ ጽዮን ከብዙ ንዋያተ ቅድሳት ጋር፣ በዘመነ ሐዲስ ኪዳን ደግሞ  ግማደ መስቀሉንና የመሳሰሉትን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ይህ ሁሉ የሆነው አባቶቻችን በሃይማኖታቸው ጸንተው በጎ ምግባር ሠርተው እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ መኖር በመቻላቸው ነው፡፡    በዚህም አባቶቻችን ሃይማኖታቸውን ከአገራቸው አልፈው በኢየሩሳሌምና በሌላውም ዓለም አስፋፍተዋል፡፡ የእግዚአብሔር ቅዱሳንም ኢትዮጵያን በመንፈስ ተረድተው ከሀገራቸው ተሰደው ተሸሽገውባታል፤ ሃይማኖትንም ሰብከውባታል፡፡ ለአብነትም ዘጠኙ ቅዱሳንንና አቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስን መጥቀስ ይቻላል፡፡  በዚህም ቤተ ክርስቲያን አገሪቱን በታሪክ በቅርስና በጀግንነት  ማማ ላይ ሆና ከፍ ብላ እንድትታይ አብቅታለች፡፡  የክርስትና ሃይማኖት  በሌሎች አገሮች የተሰበከው በብዙ የደም ሰማዕትነት ነው፡፡ በሀገራችን ኢትዮጵያ ግን በእግዚአብሔር ቸርነትና ፈቃድ ሃይማኖት ከቤተ መንግሥቱ ጀምሮ ወደ ሕዝቡ ስለተሰበከ የክርስትናው ሃይማኖት በሰላም እንዲሰበክ ጥሩ ዕድል ፈጥሯል፡፡  ይሁንና ይህን የሰላምና የጥበብ ጉዞ ለማደናቀፍ ጠላት ተኝቶ አያወቅም፡፡ ከምንጩ ቀድታ በሰላም ስትመራው የኖረችውን ክርስትና ከምንጩ ያልቀዱት በተንሸዋረረ መንገድ የተሰበኩት ምዕራባውያኑ ግን መስመሯን ሊያስቱ ሲታገሏት ሲፈታተኗት መኖራቸው የማይዘነጋ ሐቅ ነው፡፡ ጥቂቶቹን ብናይ በአፄ ሱሱንዮስ ዘመን፣ በፋሽሽት ጣሊያን ወረራና በየጊዜው ነገሥታቱን በመሣሪያና በመሳሉት በመደለል ቤተ ክርሰቲያንን ለመከፋፈል የተከናወኑ ተግባራት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ጴጥሮስን አንተ ዐለት ነህ ባንተ ዐለትነት ቤተ ክርስቲያንን እሠራታለሁ፡፡ የገሃነም ደጆችም አይችሉአትም፡፡ (ማቴ.፲፮፥፲፰)  እንዳለው አጽራረ ቤተ ክርስቲያናት ምንም ቢጥሩ ቤተ ክርስቲያንን ሊያጠፉ አልቻሉም፡፡ እነርሱ እየጠፉ ቤተ ክርስቲያን ግን እያበበች፣ እያፈራችና እየተስፋፋች ኖረች እንጂ፡፡  ዲያብሎስ በየዘመናቱ በቤተ ክርስቲያን ላይ በውስጥም በውጭም ፈተና እያስነሣና የፈተናውን መልክ እየለዋወጠ ምእመናንን ሲያምስና ሲያውክ ኖሯል፡፡ በውጭ ካሉት የቤተ ክርስቲያን ጠላቶች በሚነሣ ፈተና ብቻ ሳይሆን በውስጥ ባሉ ሐሰተኛ መምህራንም ፈተናው እንደሚነሣ መረዳት ያስፈልጋል፡፡ በእኛ ዘመን ያለው ዋና ፈተና ደግሞ የዘረኝነትና የፖለቲካ መንፈስ ነው፡፡ ድንበር የለሽ የሆነውን ዋናውን የክርስትና ዓላማና ጉዞ ዘንግተን በዘር በጎሣ በቋንቋ በአካባቢ እየተከፋፈልን በመሆኑ ይህ ክፉ ሥራችን ቤተክስቲያንን ማዕበል ሆኖ እያናወጣት ይገኛል፡፡ ቤተክርስቲያን ሰማያዊት ናት፡፡ ቤተክርስቲያን አምነው የተጠመቁ ከእርስዋ ለተወለዱ ሁሉ እናት ናት፡፡ ዘር ቀለም ቋንቋ እውቀት ውበት ጉስቁልና ወንዝ መንደር አይወስናትም፡፡ ድንበር የለሽም ናትና በእኛ የአስተሳሰብ ልክ ልንወስናት አንችልም፡፡  አባቶቻችን  በእምነት ጉዞ ውስጥ አንዳንድ የአመለካከት መለያየቶች እንኳ ሲፈጠሩ ተረጋግተው ተወያይተው ተከራክረው ለመፍታትና ፍቅርና አንድነት ለመፍጠር ብዙ ጥረት ያደርጉ የነበረው ፍቅርን ማስቀደም ስለሚበልጥ ነው፡፡ ወደ መጨረሻው ውሳኔ የሚደርሱት አማራጭ ከጠፋና የሃይማት ልዩነት ሆኖ ሲገኝ ነው ፡፡ ያውም ቢሆን እንደዘመናችን ለግል ፍላጎትና ጥቅም ወይም የሥልጣን ፍላጎት ሳይሆን ቤተ ክርስቲያንንና መንጋውን ከአደጋ ለመታደግ ሲሉ ነበር የተፈለገውን መሥዋዕትነት ለመክፈል የሚተጉት፡፡ በዘመናችን ሕግና ሥርዓት በሰፈነበት ተወያይቶና ተመካክሮ ጉዳዮችን በሰላማዊ መንገድ መፍታት ሲቻል በሠለጠነ ዘመን የቤተ ክርስቲያንን አንድነት የአገርን ሰላማዊ ጉዞ የምእመናንን ፍቅርና አንድነት በሚያናጋ መልኩ ፅንፍ ይዞ ያለመንገዱ መሄድ ለማንም የማይጠቅም ነው፡፡ ይህን የሚያሰኘን በምሥራቅ ጎጃም ከቅባት ትምህርት ጋር በተያያዘ የተከሠተው የመለያየት አጀንዳ ነው፡፡ በመጀመሪያ በጥንቃቄ ማየት ያለብን መለያየት የመንፈስ ቅዱስ ሥራ አለመሆኑን ነው፡፡ ከወገኖቻችን እንደችግር የተነሡትም ጉዳዮች መፍትሔ የሚፈልጉ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ ቢሆኑም ለቀኖና እና በሕግ ጥሰት የሚዳርጉ ግን ሊሆኑ አይገባም፡፡ በአንዲት ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን ዶግማና ቀኖና የሚመራ ማንኛውም ተከታይ የሐዋርያትን ዶግማና ቀኖና በግብታዊነት ሊንድ ሊሽር ፈጽሞ አይችልም፡፡ ማዕከላዊነትን ሳይጠብቁ በየፊናቸው የፈለጋቸውን የመሾም በፈለጉት መንገድ የመጓዝ አካሄድ የፕሮቴስታንቶች ባህል እንጂ የኦርቶዶክሳውያን ትውፊትም ባህልም አይደለም፡፡ ኦርዶቶዶክስ ተዋሕዶ ማእከላዊነትን የጠበቀ አሠራር ነው የምትከተለው፡፡ የምትመራውም ከፍ ባለ  ሐዋርያዊ ልዕልና በቅዱስ ሲኖዶስ ነው፡፡ ከቤተ ክርስቲያን እውቅና፣ ሕግና ቀኖና ውጭ ሊቀ ጳጳስ እስከ መሾም መድረስ አሳዛኝና አስደንጋጭ ኦርቶዶክሳዊ ያይደለ ምናልባትም ሁሉም ሰው ያልተገነዘበው ተቆርቋሪ መስሎ ቀርቦ የዋሁን ሕዝብ በማነሳሳት በኩል የጠላት እጅ ሊኖርበት የሚችል ባእድ ተግባር ነው፡፡  ቀደምት አባቶቻችን ሃይማኖቱን ብቻ ሳይሆን በእምነት ጉዞ ውስጥ የምንመራበትን ሕግና ሥርዓት ትልቅ መንፈሳዊና ተቋማዊ የመንፈስ ቅዱስ አሠራር ቅዱስ ሲኖዶስን መሥርተው አልፈዋል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊት በመሆኗ የትምህርት የቀኖና ሥርዓት አላት፡፡ ለመሾምም ለመሻርም ለማጥመቅም ለማውገዝም የራስዋ ሐዋርያዊ ቀኖና አላት፡፡ በቤተ ክርስቲያኒቱ ሥር ያሉ ተቋማትም የሚመሩት በቅዱስ ሲኖዶሱ ውሳኔ ነው፡፡ ከቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ የወጣ ነገር በሚኖርበት ጊዜ ጉዳዩን ለቅዱስ ሲኖዶስ አቅርቦ ሐዋርያዊ የሆነውን ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን ተከትሎ የሚስተካከል ጉዳይ እንጂ እከሌ ወእከሊት እንዲህ አለ እንዲያ አለ ተብሎ በወፍ በረር ወሬ ቤተ ክርስቲያንን የሚያክል ታላቅ ነገር የሚለያይ ሥራ መሥራት በምንም ሚዛን ትክክል ሊሆን አይችልም፡፡ ቆም ብሎ ማሰብ ማረምም ይገባል፡፡  የቤተ ክርስቲያንን ወገኖች አይጠቅምም፡፡ ከጀርባ ሆነው የቤተ ክርስቲያንን አንድነት ለማናጋት ለሚሠሩ አፅራረ ቤተ ክርስቲያን ለጥፋት ተልኮአቸው እድል መስጠት ነው፡፡ በአንዲት ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አባላት መካከል የቀኖና ወይም የዶግማ አረዳድና አተገባበር ላይ ልዩነት ከተፈጠረ በትምህርት የሚመለሰውን በትምህርት ፣ በውይይት የሚታረመውን በውይይት፣ በቀኖና ውሳኔ የሚፈታውን በውሳኔ ማስተካካል ተገቢ ነው፡፡ ከዚህ የወጣና የማይታረም ካለ አውግዞ እስከ  መለየት ሊዘልቅ ይችላል፡፡ የቤተ ክርስያንን ሐዋርያዊ ዶግማና ቀኖና የማስጠበቅ ኃላፊነት ደግሞ የቅዱስ ሲኖዶስ ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ልዩ ትኩረትና ጥንቃቄ የተመላው በጥበብና በመንፈስ ቅዱስ ኃይል የታገዘ አካሄድና ውሳኔ ሊሰጡበት ይገባል፡፡ አፅራረ ቤተ ክርስቲያን ሁልጊዜም ቤተ ክርስቲያንን ለማዳከም ምእመናንን ለመከፋል በየዘመናቱ የሚፈጥሯቸውን ተንኮሎች አባቶቻችን በጥንቃቄ ይዘው በምክርና በትምህርት እያከሙ ያቆዩትን ጉዳይ ምክንያት ፈልጎ በመቀስቀስ ከቤተ ክርስቲያን የመገንጠል፣ ሕዝብን የመከፋፈልና ለቤተ ክርስቲያን ጠላቶች መሣሪያ የመሆን አዝማሚያ ሊታረም ይገባል፡፡  ይህን የቤተ ክርስቲያንን ልዕልና ለማኮሰስ፣ ሰላሟን ለማደፍረስ ለሚሠሩ አካላት መሣሪያ መሆን ነው፡፡ ይህን ዝም ብለን የምንመለከተው ጉዳይ አይደለም፡፡ ቅዱስ ሲኖዶሱ በጉዳዩ ተወያይቶ አስተማሪ የሆነ በቤተ ክርስቲያን ዶግማና ቀኖና ላይ የተመሠረተ የእርምት ርምጃ ሊወስድበት በቦታውም ሄዶ ሕዝቡን ማወያየት ማስተማር ግልጽ ያልሆኑ ጉዳዮችን በትምህርት በሥልጠናና በውይይት መፍታት ያስፈልጋል፡፡  ቀኖናዊ ውሳኔዎች የሚያስፈልጉአቸውን ጉዳዮችን ደግሞ ለይቶ  መወሰን ይገባል፡፡ እንደዚህ በማድረግ ክፉ ልብና ሕሊናን በትምህርትና በንስሓ በተግሣጽም ጭምር ማስተካከል ካልተቻለ እሾሁ ካደገ መንቀል ይቸግራል፡፡ ጠላት በከፈተው በር ለመግባት ደግሞ ብዙ አሰፍስፎ የሚጠብቅ ወንበዴ ስላለ በዛ ቀዳዳና ክፍተት ገብቶ መንጋውን ይዘርፋል፡፡ ክፉውን ሕሊና አስወግደን  በጎ በሆነ ሕሊና ጠንክሮና ተግቶ አብሮ መሥራትን ይጠይቃል፡፡ ይህን ክፉ ሥራ ጠላት አደረገው እንዳለ ጌታ ሁልጊዜ የሚያለያይ የሚከፋፍል የቤተ ክርስቲያንን አንድነት የሚያናጋ ሥራ ከጠላት ከዳቢሎስ ነውና አውጥተን ልንጥለው በጎውን ቀናውን የፍቅር የሆነውን ልንይዘው ይገባል፡፡ ዓላማችን ቤተክርስቲያንን ማገልገል ፍጻሜያችንም መንግሥተ ሰማያትን መውረስ ከሆነ አማራጩ ክፉውን ነገር ከመካከላችን አውጥቶ ፍቅርና ሰላምን መመሥረት ብቻ ነው፡፡  በአጠቃላይ ለዚህ የመለያየትና የመጠላላት ከንቱ ፍላጎት ሲባል የቤተ ክርስቲያን አንድነትና የምእመናን ሰላም ፈተና ውስጥ መግባት የለበትም፡፡ ስለሆነም የሚመለከተን ሁሉ ደግ የሆነውን ነገር ከክፉው በመለየት እግዚአብሔር ለሚወደውና ለበለጠው ነገር መሣሪያና ምክንያት ለመሆን የምንተጋ እንጂ በተቃራኒው ሆነን ለቤተ ክርስቲያንም ለሀገርም የሚጎዳ ተግባርን እየፈጸምን የምንገኝ አንሁን፡፡ ክፉውን ሐሳብ የሚለያየንን፣ መንጋውን የሚበትነውን፣ ቤተ ክርስቲያናችንን የሚጎዳውን ለሀገር ለወገን የማይጠቅመውን ክፉ ሐሳብ አውጥተን እንጣለው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ደቀ መዛሙርቱ “ክፉውን ከመካከላችሁ አውጡት” እንዳለው እኛም ክፉውን አውጥተን መልካሙን ይዘን የመንግሥቱ ወራሾች እንድንሆን እግዚአብሔር ይፍቀድልን፤ አሜን፡፡  
Read 6398 times