Monday, 05 October 2020 00:00

መስቀሉን ዳግም መቅበር አይቻልም!

Written by  ማኅበረ ቅዱሳን

Overview

ለ፫፻፴ ዓመታት ያህል በአይሁድ ክፋት እና ጭካኔ ተቀብሮ ተራራ የሚያህል ቆሻሻ የተደፋበት  የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ክበቡር መስቀል በንግሥት ዕሌኒ አማካኝነት ከተቀበረበት ወጥቶ በከበረው ስፍራ እንዲቀመጥ ከተደረገ እነሆ ፳፻ ዓመታት በላይ ተቆጥረዋል፡፡ አይሁድ ሙት ያስነሣ ፣ ድውይ ይፈውስ የነበረውን ክቡር መስቀል ከኢየሩሳሌም የቆሻሻ መጣያ ወስደው ሲቀብሩ ፈዋሽነቱ እንዳይነገር ፣ አዳኝነቱ እንዳይመሰከር፣ ታሪኩ ተቀብሮ እንዲቀር አስበው እና አልመው ነበር፡፡ መስቀሉን በጊዜው ቆፍረው ማውጣት ያልቻሉ በአካባቢው የነበሩ ክርስቲያኖች ቦታውን ለይተው ቢያውቁም በ፸ ዓመተ ምሕረት በጥጦስ ወረራ ኢየሩሳሌም ስትጠፋ ከሀገር በመሰደዳቸው ቅዱስ መስቀሉ የተቀበረበትን ቦታ የሚያውቀው ሰው አልነበረም፡፡ የአይሁድ አላማም ይህ ነበረ ነገረ ድኅነቱ እንዲረሳ ከሰው ልብ እንዲወጣ ማድረግ፡፡ ለዚያም ነው ቅድስት ዕሌኒ  መስቀሉን ፍለጋ ወደ ኢየሩሳሌም ስትመጣ ኪርያኮስ የተባለ በዕድሜ የገፋ  የጥንቱን የሚያውቅ ሰው ያስፈለጋት፡፡  

 

 ክርስቶስን በመስቀል ከዚያም መስቀሉን በመቅበር የተጀመረው ፀረ ክርስትና እንቅስቃሴ ቀጥሎ ክርስቲያኖችን እና መምህራኑን በማሳደድ ክርስትናን ከምድረ ገጽ ለማጥፋት ብዙ ርቀት ተጉዟል፡፡ አይሁድ፣ አላውያን ነገሥታት፣ በየጊዜው የሚነሱ መናፍቃን ባጠቃላይ የእምነቱ ጠላቶች የመስቀሉ የድኅነት ታሪክ እንዳይነገር፣ ፈዋሽነቱ እንዳይዘከር፣ ለዓለም ይዞት የመጣው የመንግሥተ ሰማያት ጥሪ እንዳይመሰከር ያልፈነቀሉት ድንጋይ ያልቆፈሩት ጉድጓድ የለም፡፡ በዚህ ሁሉ ውስጥ መስቀልን መድኃኒቷ እና አርማዋ አድርጋ የተነሳቸው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ለዘመናት መከራን  ስትቀምስ ኖራለች፡፡

ብዙ ክርስቲያኖች በየዘመናቱ በተነሱ ዓላውያን (ከግለሰብ እስከ መንግስታት) መብታቸው ሲገፈፍ፣ በነፃነት እንዳያመልኩ ሲደረግ፣ በእምነታቸው ምክንያት ሲገለሉ፣ ሲሰደዱ እና ሲገደሉ ኖረዋል፡፡ ሐዋርያት በክርስቶስ ስም እንዳያስተምሩ ተገርፈዋል፣ በካህናተ ጣኦታት የሚመሩ ዓላውያን ነገሥታት ክርስቲያኖቹን ላቆሙት ጣዖት እንዲሰግዱ ካልሰገዱ ዳግም ሀገሩን ለቀው እንዲሰደዱ ተደርገዋል፡፡ ይህ በዓላዊው ንጉሥ በዲዮቅልጥያኖስ ዘመን በክርስትና እና በክርስቲያኖች ላይ የደረሰው የመብት ገፈፋ አንዱ ማሳያ ነው፡፡ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ የክርስቲያኖችን ልዩ ልዩ መብት እንዲከበርላቸው አዋጁን በአዋጅ እስከሻረበት ጊዜ ድረስ በዘመኑ የነበሩ ክርስቲያኖች በሀገራቸው እንደዜጋ እንዳይቆጠሩ፣ እርስ በርስ እንዳይገናኙ ፣ ንብረታቸው እንዲወረስ፣ በመንግሥት መስሪያ ቤት እንዳይቀጠሩ የመማሪያ ቅዱሳት መጽሕፎቻቸው እንዲቃጠሉ ትዕዛዝ ተላልፎባቸው ነበር፡፡  

ይሁን እንጂ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ባሳለፈችው በዚያ የጨለማ ዘመን በምድር ላይ መኖርን ተነፍገው በግበብ ምድር እንዲኖሩ የተፈረደባቸው ልጆቿ መከራውን ተሰቅቀው ወንጌልን ከማስፋፋት፣ በክርስትናቸው ከመጽናት አላፈገፈጉም ይልቁንም በጽናታቸው ብዙዎችን የወንጌል ምርኮኛ እስኪያደርጉ ድረስ ክርስትና ለዓለም እንዲደርስ ፣ ጨለማው ዓለም እንዲበራ መስቀልን ምርኩዛቸው አድርገው እስከ ምድር ጫፍ ተጉዘዋል፡፡ በወገኖቻቸው ላይ በደረሰው አሰቃቂ ሞት ተሳቀው እምነታቸውን ርግፍ አድርገው ይተዋሉ ሲባል በተቃራኒው ሞትን ተጋፍጠው  የክርስትናውን አሸናፊነት አረጋግጠዋል፡፡ ኃላፊያኑን ሊተኩ ሌሎች የሃይማኖት  ጀግኖች ከሥር እንደ አሸን እየፈሉ በክርስትናው ስብከት እስከ  ምድር ዳርቻ ደርሰዋል፡፡

ለመስቀል ጠላት ሆነው የሚነሱ በየጊዜው ቢኖሩም ቅድስት ቤተ ክርስቲያን መስቀልን በጉልላቷ ላይ ተክላ ፣ በንዋየ ቅዱሳቷ አትማ በቅጽሯ ሳይቀር ተጎናጽፋው ኖራለች፡፡ በዘመናት ውስጥ መልኩን እየቀያየረ በሚነሣው ፀረ ክርስትና እንቅስቃሴ ውስጥ ልጆቿ በእጃቸው፣ በአንገታቸው፣ በልብሳቸው  ሳይቀር መስቀሉን አኑረው ይህ ነው እምነታችን ብለዋል፡፡ ከምኩራበ አይሁድ የተነሣው ጥላቻ ሁለት ሺህ ዘመን ዘልቆ ክርስትና ብዙ እንዳይነገር ከማድረጉም ባሻገር በክርስቲያኖች ላይ ታላቅ  መከራና ስደትን አስከትሏል፡፡ መስቀልን ጨምሮ ታላላቅ የክርስትና መገለጫዎችን ለማጥፋት ቢሞክርም ከበረሃው መኻል እየለመለመ፣ ከጭንጫው እየፈለቀ ፣ እየበዛ እዚህ ደርሷል፡፡ 

ይሁን እንጂ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በዮዲት ጉዲት ብዙዎቹን ልጆችዋን፣ ድንቅ የሆኑ ቅዱሳት መጻሕፍቷንና ንዋየ ቅድሳቷን እንዲሁም አብያተ ክርስቲያናቷን እንድታጣ ተደርጋለች፡፡ በግራኝ አህመድ ወረራ በጨለማ ውስጥ እንድትጓዝ ተገዳለች፡፡ በንጉሥ ሱስንዮስ ዘመን ከምእመናን አልፎ ቀዳሽ ናዛዥ ካህናቷን ተነጥቃለች፡፡ በዚህ ሁሉ መከራ ውስጥ እያለፈች ግን የየእለቱን መንፈሳዊ አገልግሎት ስትሰጥ ኖራለች፡፡ ታላላቆች በመከራው ውስጥ ይወለዳሉና ልጆቿ በሰማዕትነት ሲያልፉ ከሥር ሌሎች ሰማዕታት እየተነሡ እዚህ አድርሰዋታል፡፡ በቅዱሳን ደም የለመለሙ ልጆች አሉዋትና የክርስትናን ሥር ማድረቅ አልተቻለም፡፡

ዛሬም እንደ ዳክሲዮስ ዘመን የቤተ ክርስቲያኒቱን ልጆች ማሳደድና መግደል፣ በግድ እምነት እንዲቀይሩ ማድረግ፣ በገዛ ሀገራቸው እንደ ሁለተኛ ዜጋ እንዲታዩ ጫና ማሳደር እንዲሁም  ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ማቃጠልና መዝረፍ በዚህ ሁሉ መከራ እንድትጠፋ ማድረግ   ትላንት የነበረና ያልተሳካ ነገም የማይሳካ መሆኑን በክርስቶሰ ደም የተዋጁት ልጆቿ መሥዋዕትነት ከፍለው አሳይተውናል፡፡ አይሁድ ክርስቶስ የተሰቀለበትን ክቡር መስቀል አርቀው ቀብረው ለዘመናት ቆሻሻ በመድፋት እንዲረሳ ጥረት እንዳደረጉት ሁሉ ዛሬም መስቀሉን ከጉልላቷ ላይ አውርደው ቤተ ክርስቲያንን በማቃጠል እዚያ ቦታ ቤተ ክርስቲያን እንዳልነበረ ለማድረግ በዕቅድ ረጅም መንገድ ተሄዷል፡፡ ክርስቲያኖችን በመግደል፣ በማረድ እና ከቀዬአቸው  እንዲሰደዱ በማድረግ እዚያ ቦታ ያለው የክርስቲያኖች እና የክርስትና ታሪክ እንዲረሳ  ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴ ተደርጓል ፤ ሆኖም “ ዲያቢሎስ ዝናሩን ጨረሰ ቤተ ክርስቲያንን ግን አልጎዳትም ” እንዳለ ሊቁ መስቀሉን የመቅበር አላማው አልተሳካም፡፡

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በየዘመናቱ በተነሡ ሰማዕታት ጠፋች ሲባል እየበዛች በወንጌል የምድርን ዳር እያዳረሰች፣ ወደቀች ሲባል ጸንታ እየቆመች ፣ አበቃላት ሲባል በአዲስ ጉልበት እንደገና እየጀመረች እዚህ ደርሳለች፡፡ በቅርቡ በሊቢያ ማኅተመ ክርስትናችን የሆነውን የአንገታችንን ክር አንበጥስም ብለው የተሠዉ ወንድሞቻችን በክርስትናችን እንድንጸና በሰማዕትነት ጽናታቸው አርአያ ሆነውናል፡፡ ዛሬም ስለ ክርስትናቸው ዋጋ የከፈሉ ክርስቲያን ወገኖቻችን ቤተ ክርቲስያን እንድትቀጥል ክርስትናም እንዲስፋፋ ፣ ሰማዕት ሆነዋል.፡ እየሞቱ ፀንተዋል ፣ በጠፉ ቁጥር በዝተዋል ዓለም ያልተረዳው ይህን ታላቅ ምሥጢር ነው፡፡ ቤት ንብረት በማሳጣት ክርስቲያኖች በዚህ ዓለም የሀብት መስፈርት ብቻ ምንም ነገር እንዳይኖራቸው ማድረግ ይቻል ይሆናል ሰማያዊ የሆነውንና የክርስትና ሀብታቸውን መንጠቅ ግን አይቻልም፡፡ እየሞቱ መኖር እየተሰደዱ መስፋት፣ እየጠፉ መብዛት የነበረ ፣ ያለና  የሚኖር ነው፡፡ ከጥንት ጀምሮ የክርስትና ጉዞ የሚያረጋግጠው ይህንኑ ነው፡፡           

በዘመናት መሐል እንዲረሳ ለማጥፋት በተረባረቡበት መጠን ድንጋይ እንደተጫነው ተክል በየአቅጣጫው እያፈተለከ ፣ በተገኘው አቅጣጫ ሁሉ ክርስትና ተስፋፍቷል፡፡ ቃሉን ማሰር አይቻልምና፡፡ በጠንካራ መዳፍ ሊጨፈለቅ ቢሞከርም እንደ ሰናፍጭ ቅንጣት አድጎ ትልቅ ዛፍ ሆኗል፡፡ እውነቱ ይህ ነው በመከራ ውስጥም ቢሆንም የቤተ ክርስቲያን ጉዞ ለሰከንድ ቆሞ አያውቅም፡፡ ሁልጊዜ ቢሆን ክርስትናን መልሶ ለመቅበር የሚደረገው ትግል ከንቱ የሚሆነው ለዚህ ነው በተራራ ላይ ያለች ከተማን መሠወር አይቻልምና፡፡   

በርግጥ የክርስትና ሕይወት የመስቀል ጉዞ ነውና በመከራ ውስጥ ማለፍ የግድ ነው፡፡ በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ደም የተመሠረተችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በነበራት መንፈሳዊ አገልግሎት ውስጥ በልጆቿ መሥዋዕትነት እዚህ ደርሳለች፡፡ እውነት ነው ክርስትና እዚህ ዘመን ላይ እንዲደርስ ብዙ ቅዱሳን በእሳት ውስጥ አልፈዋል ፣ በመጋዝ ተሰንጥቀዋል ፣ ለአውሬ ተጥለዋል፣ በመንኰራኲር ተፈጭተዋል ፣ እነሱ በሥጋቸው ነደው እያለቁ ክርስትናው እንዲቀጥል ለሌሎች ብርሃን ሆነው አልፈዋል፡፡ በዚህ ታላቅ ገድል ውስጥ አልፎ የመጣውን ክርስትና ነው ዛሬም ብዙዎች ልክ እንደ መስቀሉ ሊቀብሩትና ሊያዳፍኑት የሚሞክሩት፡፡ በስደት ውስጥ ያለፈውን ክርስትና ነው ዛሬም በስደት እንዲጠፋ የሚጥሩት፡፡ በቅብብሎሽ እዚህ የደረሰውን ክርስትና ነው አማኙን በመግደል ሊያጠፉት የሚታትሩት፡፡ አዎን እንደ አይሁድ ዘመን በቅንአት ተነሣሥቶ ክርስቲያኖችን መግደል ማሳደድ ፣ መስቀሉን ከጉልላቷ ላይ ማንሳት ይቻል ይሆናል  መልሶ መቅበር ግን  አይቻልም፡፡ ምክንያቱም ቤተ ክርስቲያን በመከራ ደምቃ ፣ በመስቀል ከፍ ብላ ለእኛ ለክርስቲያኖች ለዘለዓለም ስታበራልን ትኖራለችና፡፡  

ወስብሐት ለእግዚአብሔር!  

 

 

 

 

 

 

 

Read 678 times