Wednesday, 24 March 2021 00:00

የክርስትናችንን እንቅፋት ከፊታችን እናስወግድ

Written by  በዝግጅት ክፍሉ

Overview

ኢትዮጵያ ሀገራችን ልዩ ልዩ መልክ ባህልና ቋንቋ ያላቸው ሕዝቦች የሚኖሩባት ታላቅ ሀገር ስትሆን  ከ፹ በላይ ቋንቋዎችም ይነገሩባታል። ከነገድ እና ከወገን የሚበዙት የሚኖሩባት ሁሉንም አቅፋ የያዘች እጀ ሰፊ ሀገር ናት። የረጅም ዘመን ታሪኳም የሚያሳየው ሕዝቦቿ ተፋቅረው እና ተከባብረው እንደ አንድ ልብ አሳቢ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ሆነው መኖራቸውን ነው። ለዚህም በተለያየ ጊዜ ሊወራት የመጣውን የጣሊያን ወራሪ ኃይል መክታ ከሀገር ያስወጣችበት ታሪክ ቋሚ ምስክር ነው። ሕዝቧ እንደዛሬ የዘር ቋጠሮ ሳይፈታ ፤ በወንዝ እና በድንበር ሳይወሰን  ከአራቱም አቅጣጫ በመትመም የጣሊያንን ሠራዊት ድል አድርጎ በዓለም ላይ ኢትዮጵያ የሚለው ስም ከፍ ብሎ እንዲጠራ ኃይል እና ብርታት ሆኖ ነበር።   የዚህ ሁሉ ማጥበቂያው ድር እና ማግ ሀገራችን ከጥንት ክርስትናን መቀበሏ እና የክርስቲያን ሀገር መሆኗ፣ ሕዝቡም ሆነ ነገሠታቱ ፈሪሃ እግዚአብሔር ያደረባቸው ሆነው መገኘታቸው ነው። ቃለ ወንጌልን በተግባር ሲፈጽሙ ለመኖራቸው ሌላው ምስክር ዘጠኙን ቅዱሳን መቀበላቸው፣ ከመካ መዲና የተሰደዱ ሙስሊሞችን ማስጠጋታቸው ነው። ሀገር በሰላም እና በአንድነት ተጠብቆ  እንዲኖር፤ ሕዝቦቿ  በፍቅር ተጋብተው እና ተጋምደው እንዲኖሩ ያደረጋቸው ብሎም ኢትዮጵያዊነት እንዲጠነክር በማድረግ የአንበሳውን ድርሻ የሚወስደው የክርስትናው አስተምህሮ ነው።  ዛሬ ከዘመን ብዛት ይህ የመከባበር እና አብሮ የመኖር ውል ጠፍቶ፣ በጠንካራ ዓለት ላይ የተመሠረተው አንድነታችን ተሸርሽሮ ዥንጉርጉርነቱና መለያየቱ በቤተ ክርስቲያን ላይ ሳይቀር አጥልቶ እናያለን። በክርስቶስ ደም አንድ የሆኑ ክርስቲያኖች በዘር ተለያይተው  እና ጎራ ለይተው ሲፋለሙ ማየት ቀስ በቀስ እየተለመደ መጥቷል። ከራስ አልፎ ሌሎችን የተቀበለ ክርስቲያናዊ ሰብእናችን ጠፍቷል፤ ሁሉን አንድ አደርጎ የሚያየው ዓይነችን ተንሸዋሯል። ሁሉም በየቤቱ በክርስቶስ ስለዳነው የሰው ልጅ ሳይሆን ስለጎጥ እና ስለዘር ሲያወራ ይውላል። ጾታና ዕድሜ ሳይለይ ከሊቅ እስከ ደቂቅ፤ ከምእመን እስከ መነኲሴ በዘረኝነት አዙሪት ውስጥ ገብቶ ሲባዝን ይውላል። ግዴለም ወደሌሎች ማየት እና መጠቆም አያስፈልገንም ሁላችንም ከእነዚህ እንደ አንዱ ሆነናል፤ ግን እስከ መቼ? ቤተ ክርስተያን ሄዶ የቅዱስ ወንጌልን ቃል ከመስማት ይልቅ ስለዘረኝነት መስማት የወንጌል ቃል ያህል እየተለመደ ነው። በእግዚአብሔር ስም ተሰብስቦ ሀገርን ስለማይጠቅም፣ ክርስትናን ስለማያንጽ ተራ ጥላቻ እና ወሬ መስማት ከክርስትናው ተርታ የሚያስወጣ ነው። እኔ ክርስቲያን ነኝ ከሚለው ይልቅ እኔ የዚህ ዘር ነኝ፣ እከሌ የዚህ ዘር ነው ብሎ ማውራት እጅግ የሚያሳፍር ነው። መጽሐፍ ቅዱስ  ‹‹የእግዚአብሔርን ቃል እንደሚሸቃቅጡት . . . ›› ፪ኛ ቆሮ ፪፥፲፯  እንዳለው በቤተ ክርስቲያን አውደ ምሕረት ላይ ወንጌልን ከፖለቲካ ጋር ቀላቅሎ መስበክም ሆነ መስማት የዘመኑ ፋሽን ሆኗል። ለዘመናት የተገነባው ማንነታችን ተሸርሽሮ  ክርስትናችንን እየፈተነው ይገኛልና አጥብቀን ልንቃወመው ይገባል። ሰዎች በደልና ግፍ ሲደርስባቸው፣ ከኖሩበት፣ ሀብትና ንብረት ካፈሩበት ቀዬ ሲፈናቀሉ፣  በጅምላ ሲታረዱና ሲገደሉ እንደ ዓለማዊ ሰው ማውራት ከጀመርን ቆይተናል። በእግዚአብሔር አርአያ ስለተፈጠረው ሰው ሳይሆን የኔ ስለምንለው ዘር ስንብከነከን ፀሐይ ወጥታ ትጠልቃለች። ሆኖም ግን ማዘንና ማልቀስ ያለብን የእኔ ስለምንለው ሰው ብቻ ሳይሆን  ለሰው ልጅ ሁሉ የሚገደን ልንሆን ይገባል። የሰው ልጆች ሁሉ ከአንድ አዳም ነው የመጡት ብላ በምትሰብከው ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያደግን የቤተ ክርስቲያን ልጆች ለሰው ልጅ ማዘንን በዘር መለካት ከጀመርን ሰነባበትን። ይህን ያህል ሰው ተሰደደ ወይም ሞተ የሚለው ሳይሆን የእንትን ብሔር ተገደለ ወይም ተሰደደ የሚለውን አግዝፈን መናገር የሚቀናን እኛው ክርስቲያኖች መሆናችን ያስገምታል። በእኛ ሐሳብ የእኛ ያልሆነ ብሔር ሲሞትና ሲሰደድ ዓይናችንን የምንጨፍን ጆሯችንን የምንደፍን በተቃራኒው የኔ ለምንለው ብሔር ጎራ ለይተን በየማኅበራዊ ሚዲያው ስንሳደብና ስንራገም የምንውል እኛው ነን እኛ የቤቱ ሰዎች። ‹‹ቀኖቹ ክፉዎች ናቸውና ዘመኑን ዋጁ›› ኤፌ ፭፥፲፰ የሚለውን የእግዚአብሔር ቃል ዘንግተነው አለዚያም ተራ ሆኖብን ዘረኝነትን ስናሳድድ ከክርስትና እየራቅን ነውና በጊዜ ልንመለስ ይገባል።   ቤተ ክርስቲያን በክርስትና ጉዞዋ ውስጥ ብዙ ታሪካዊ ሰቆቃዎችን አሳልፋለች፤ ለአብነትም የዘመነ ዮዲት ጉዲት፣ የዘመነ ግራኝ . . . በጥቂቱ ተጠቃሾች ናቸው። በእነዚህ ሰቆቃዎቿም የደረሰባትን መከራ በድል በማጠናቀቅ እዚህ ዘመን ላይ ደርሳለች። እኛ የዘመኑ ክርስቲያኖች ግን ከአባቶቻችን ጋር በምንም የማይገናኘውን ትንሹን ፈተና እንኳ ማለፍ አቅቶናልና ራሳችንን፣ እምነታችንን በደንብ ልንፈትሽ ይገባል። ሀገር ዛሬ ካለችበት እና ከገባችበት አዙሪት እንድትወጣ ሰላምን በመስበክ የምትታወቀው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን፤ በክርስቶስ አንድ የሆንን ክርስቲያኖች ተግተን ልንጸልይ ልንሠራ ይገባል።  ለሦስት ሺህ ዘመን ወንጌል የተሰበከልን ክርስቲያኖች እንዲሁም ለዚያን ያህል ዘመን  የተገነባ የእምነትና የአብሮነት ባህልን ያዳበርን የቤተ ክርስቲያን ልጆች ዛሬ ከእምነታችን እና ከአስተምህሮአችን ፈቀቅ የሚያደርግ የዘረኝነት ተራራ ከፊታችን ተገትሯል። በእምነታችን ጸንተን እንዳንኖር ፤በመንፈሳዊነትም እንዳንመላለስ የሚያደርገንን በክርስትናችን መንገድ ላይ ያለውን እንቅፋት ልናስወግደው ይገባል። በተለይም ለቤተ ክርስቲያን ቅርብ ነን ለምንል የቤቱ ሰዎች ክርስትናችንን የፈተነውን ይህን ክፉ ዘመን ተሻግረን ምእመናንንና ቤተ ክርስቲያንን ለማሻገር ከእኛ ብዙ ይጠበቃል።
Read 894 times