Wednesday, 10 March 2021 00:00

የተቸገሩትን ለመርዳት የእግዚአብሔር እጆች እንሁን!

Written by  በዝግጅት ክፍሉ

Overview

ሀገራችን ኢትዮጵያ ከምን ጊዜውም በላይ በችግር ላይ የወደቀችበት ሰዓት ነው። ከከተማ ወጣ ብለው በሚገኙ አካባቢዎች እና በተለያዩ ክልሎች የሚኖሩ ዜጎች ወቅትን ተከትሎ በመጣው ግርግር ውስጥ የጥቃት ሰለባ ሆነዋል፤ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል፤ በእሳት ተቃጥለዋል፣ በሰይፍ ተገድለዋል፤ በአንድ ጀንበር ከባለንብረትና ከባለሀብትነት ማማ ላይ ወርደው የሰውን እጅ የሚጠብቁ ተረጂዎች ሆነዋል።  የመንግሥት ለውጥን ተከትሎ የመጣው ይህ ‹‹ሌሎችን›› የማጥቃት ሂደት ይበርዳል ሲባል እየጋለ፤ ይቀንሳል ሲባል እየጨመረ፣ መልኩን እየቀያየረ እዚህ ደርሷል። ዛሬም ንጺሐን ዜጎች ይገደላሉ፣ ይዘረፋሉ፣ እንዲሰደዱ ይደረጋሉ። አንድ ቦታ ቀዝቀዝ ሲል ሊላው ጋር እየሞቀ መላ ሀገሪቷን ያዳረሰው ይህ ክፉ ወረርሽኝ የእያንዳንዱን ቤት እያንኳኳ ‹‹ የነገ ተረኛ ማነው?›› የሚያስብል ደረጃ ላይ ደርሷል።  እንደ አየሩ ፀባይ የሚለዋወጠው ይህ የጥቃት ዒላማ ሲያሻው ፖለቲካዊ እየሆነ ፤ሲያሻው ብሔር ላይ እያተኮረ፤ አሊያም ጉዳዩን ሃይማኖታዊ አድርጎ ‹‹ከእኔ ውጪ ነው›› ከሚለው ሃይማኖት ተከታይ ላይ የጥፋት ቃታውን እየሳበ እዚህ ደርሷል። ከኢትዮጵያዊ ባህልና ወግ በተፋታ መልኩ የሞቱ በወግ ባልተቀበሩበት ቀዬ በሕይወት የተረፉቱ ለረኀብና ለእርዛት እንዲሁም ለመጠለያ እጦት ተዳርገው ይገኛሉ። ጉዳዩን በአንድ ሰሞን ሞቅታ ውስጥ ብቻ አይተን ሰሞነኛ ሐዘን እና ርዳታ ብቻ በማድረግ ሥራ ተጠምደን ስናበቃ በወረት የምንተወው የንፁሀን ሕይወት የሚገደን መቼ ነው? ለችግረኛ የሚዘረጋው ኢትዮጵያዊ እጅ ወዴት አለ? ያስብላል። ግማሽ አካላችን ለከፋ አደጋ ተጋልጦ ባለበት በዚህ ወቅት የእግዚአብሔር ልጆች ክርስቲያኖች ወዴት ናቸው? በየጊዜው እየጨመረ የመጣው ኦርቶዶክስ ተኮር የሆነው ጥፋት ከምእመን ወደ ቤተ ክርስቲያን እየተዛመተ የ፫ ሺህ ዘመን ታሪክ ያላትን ሀገር እንደ ሰደድ እሳት እየበላ ሲጨርስ ዝም ማለት ከታሪክ ተወቃሽነት አያድንም። ሀገርን እንደባላ አቁማ የያዘች ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ታሪክ አልባ ፣ ቅርስ አልባ እየሆነች ባለችበት በዚህ ሰዓት ምእመናንዋንም ሆነ አብያተ ክርስቲያን የሚጠብቅ፣ የሚንከባከብ እንዲሁም በፈረሰው በኩል የሚቆም ምእመን ዛሬ ያስፈልጋታል። ከሀገሪቱ ሕዝብ ከሃምሳ ፕርሰንት በላይ ምእመን ያላት፤ የሀገሪቱ ዋንኛ የቱሪስት መዳረሻ የሆኑ ቅዱሳት መካናት ባለቤት የሆነች ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሰው አልባ ፣ ምእመን አልባ አብያተ ክርስቲያናት እና ገዳማት አልባ እየሆነች እያደር እያነሰች እና ቀድሞ ከነበረችበት የልዕልና ማማ ላይ በፍጥነት እየወረደች መሆኑን በውል ተገንዝቦ ከሰሞነኛ ግርግርታ ወጥቶ በጽሞና ማሰብ ይጠይቃል። እንደ አንድ የቤተ ክርስቲያን ልጅ እየጠፉ ያሉትን የቤተ ቅዱሳት መካናት ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ፣ የተጎዱ ወገኖችን በማሰብ ፤ለርዳታ እጅን መዘርጋት እና ዘላቂ መፍትሔን በማፈላለግ የድርሻን መወጣት ወቅቱም ክርስትናችንም የሚጠይቀው ነው። በአርአያ ሥላሴ የተፈጠሩ ሰዎች በእርስ በርስ ግጭት፣ ዘርና ሃይማኖት ተኮር በሆነ ጥቃት ለስደት፣ ለመፈናቀልና ለሞት ሲዳረጉ እንደ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ከጎን ሆኖ የሚያጽናና፣ አይዞአችሁ ብሎ የሚያበረታታ ያስፈልጋል። ነፍስን ለመታደግ አስፈላጊውን ሰብአዊ ርዳታ ለማድረግ እጃችንን መዘርጋት ከእኛ ከክርስቲያኖች ይጠበቃል። ምክንያቱም እኛ ክርስቲያኖች የተጎዱትን ለማየት የእግዚአብሔር ዓይን፤ የተራቡትን ለማጉረስ የእግዚአብሔር እጅ፤ ለተሰደዱት ለማዘን የእግዚአብሔር ልብ ነንና ሊታሰብበት ይገባል።  ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደብረ ዘይት ስለ ዳግም ምጽአቱ በተናገረበት አንቀጽ ‹‹ተርቤ አይታችሁ አላበላችሁኝም፣ተጠምቼ አይታችሁ አላጠጣችሁኝም፣ ታርዤ አይታችሁ አላለበሳችሁኝም›› ማቴ ፳፭ በማለት የተናገረው አምላካዊ ቃል እኛን የሚመለከት የማይመስለን ብዙዎች ነን። ትናንት ባለቤት የነበሩ ኢትዮጵያውያን ይልቁንም ኦርቶዶክሳውያን ወገኖቻችን ለረኀብ ለስደት፣ ለእንግልት እና ለሞት ሲዳረጉ ቢቻል የሚደረገውን ግፍና ጭቆና በመቃወም ከፊት መቆም ፤አጋር መሆንም ተገቢ ነው። ስደተኞችን በመቀበል የሚታወቁት ኢትዮጵያውያን ይልቁንም ክርስቲያኖች የክርስትናው ትርጉም ሲዛባብን እንደማየት የከፋ ነገር የለም። ለዓለም የምትተርፈው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እንዴት ለገዛ ምእመናንዋ (አማኞችዋ) መሆን ያቅታታል? የመጀመሪያዎቹን ክርስቲያኖች ያበዛው፤ እንደ መልካም መዓዛ ሆኖ ለብዙዎች የተዳረሰው ‹‹ ከእነርሱም አንድ ስንኳ ችግረኛ አልነበረም፤ ቤትና መሬት ያላቸውም ሁሉ እየሸጡ ገንዘቡን ያመጡ ነበር። አምጥተውም በሐዋርያት እግር አጠገብ ያኖሩት ነበር፤ እነርሱም ለእያንዳንዱ እንደፍላጎቱ ያካፍሉት ነበር።›› ሐዋ.ሥ ፬ ፥ ፴፬-፴፭ በሚለው ቃል ብቻ ሳይሆን በተግባር የተገለጠው ክርስትና ዛሬ በእኛ ቸልተኝነት ጥያቄ ምልክት ውስጥ ነውና በእምነት ውስጥ ነን የምንል ሁሉ አጥብቀን ልናስብበት ይገባል።  ዛሬ ተደጋግፈን ያላቆምነው ወገናችንን ነገ አናገኘውምና ትኩረት ሰጥቶ መሥራት አስፈላጊ ነው። ዛሬ ያልተቆረቆርንላት ቤተ ክርስቲያን ፈርሳ እንድታልቅ ዝም ማለት ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ከታሪክ መዝገብ ለማጥፋት በሚደረገው ስውር ዘመቻ ውስጥ ተሳታፊ መሆናችንን መዘንጋት የለብንም። ቤተ ክርስቲያን ዛሬ በውስጥም ሆነ በውጭ ባሉ ፈርጣማ ጡንቻዎች እና መዳፎች ስትደቆስ ‹‹ለምን?›› የማይል የቤተ ክርስቲያን ልጅ ወደዚህ ዓለም የመጣበትን እንዲሁም ክርስትናው ከእርሱ የሚጠብቀውን ሥራ እየሠራ አይደለምና አጥብቆ ሁሉም ራሱን መፈተሸ ይገባዋል። ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ዛሬ ዘርፈ ብዙ ፈተናዎችን እየተጋፈጠች ትገኛለች። ይህንን ዘርፈ ብዙ ፈተና ልጆችዋ ተረዳድተው ከላይዋ ላይ ካላነሱላት፣ ወይም እንደ ሙሴ እጆችዋን መደገፍ ካልቻሉ ነገ የኔ የሚሉት ቤተ ክርስቲያንም ሆነ ምእመን ማግኘት ይቸግራልና በገዛ ሀገር ስደተኛ ከመሆን በፊት ዛሬ ላይ ቆም ብሎ መሥራት አስፈላጊ ነው። የቤተ ክርስቲያን ልጆች ዛሬ እየተገፉ እና እየሞቱ እንዲሁም በረኃብ በእርዛት እየተሠቃዩ ባሉበት አስቸጋሪ ወቅት አለንላችሁ ማለት የክርስቲያን ዋንኛ አላማ መሆን አለበት። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለተራቡት እንመጸውት ዘንድ እጆቹን አውሶናል፤ ድኃውን እናይ ዘንድ ዓይኖቹን ሰጥቶናል ፤ለተበደሉት እንራራ ዘንድ አዝዞናል። የክርስቶስ አምባሳደር ሆነን በተሾምንበት ሁሉ አውቀን እንተጋ ዘንድ ዘመኑ ከኛ ከክርስቲያኖች የሚፈልገው ዐቢይ ጥያቄ ነው።
Read 579 times