Monday, 09 November 2020 00:00

በአንድ ሐሳብ ለአንዲት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን መቆም ይገባናል

Written by  ዝግጅት ክፍሉ
በአንድ ሐሳብ ለአንዲት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን መቆም ይገባናል ቤተ ክርስቲያን በክርስቶስ ደም ከተመሠረተችበት ጊዜ ጀምሮ ፈተና ተለይቷት አታውቅም፡፡ በየዘመናቱ የሚነሡባት ዘርፈ ብዙ ችግሮችን ተጋፍጣ በጸሎት እየተጋች እዚህ ደርሳለች፡፡ ጠላት ዲያቢሎስ ለዘመናት የውስጥ እና የውጭ ጠላቶችን እያስነሣ፣ መሠረቶቿን ለማናጋት  ሲታገል ቆይቷል፡፡ ለዚህም ምስክሩ ደግሞ የታሪክ መዛግብቶቻችን ናቸው፡፡ ፈተናው እንደ የዘመኑ መልኩን ቀያይሮ ቢመጣም ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ላይ የሚያደርሰው ጥፋት ግን ዓላማው አንድ ነው፡፡ ጠላቶቿ መኖርዋን ነው የማይፈልጉት፣ ማደግዋን ነው የሚጠሉት ፣ ስምዋ ከመቃብር በታች እንዲሆን ነው የሚሹት፣ ጨለማቸውን ስለምታጋልጥ ብርሃንዋን ሊያጠፉ ነው የሚጥሩት፡፡ እነርሱ ቤተ ክርስቲያንን ለማጥፋት በአንድነት ሲቆሙ እኛ ግን ቤተ ክርስቲያንን ለመታደግ በአንድነት መቆም አልቻልንም፡፡ እነሱ ቤተ ክርስቲያንን ለማጥፋት አንድ ቋንቋ ሲናገሩ፣ እኛ ግን እንደ ባቢሎን ዘመን ሰዎች ቋንቋችን ተደበላልቋል፡፡ ከቤተ መቅደስ እስከ ዐውደ ምሕረት ፣ ሁሉም ባይሆን አንዳንዱ ከምእመን እስከ ጳጳስ አምላካዊውን ሥራ ሳይሆን የራሱን መሻት ለመፈጸም ይፈጥናል፤ አንዱ ሌላውን አይሰማም ይህ ደግሞ የቤተ ክርስቲያንን ስቃይ ዕለት ዕለት እንዲጨምር አድርጎታል፡፡ ራሱን በደገመው ታሪክ ውስጥ ሆነን የቤተ ክርስቲያን መከራ ከአፋችን አልወርድ ከዓይናችን አልጠፋ ብሎአል፡፡ በታሪክ እንደምናውቀው ትላንት ክርስቲያኖች ለአውሬ ሲጣሉ ነበር፡፡ ዛሬ ዓለም ሠለጠነ በተባለበት በሃያ አንደኛው መቶ ክፍለ ዘመን ክርስቲያኖች በሰው መሰል አውሬዎች ታርደዋል፣ በሰው መሰል አውሬዎቸ በገዛ ሀገራቸው ላይ ስደተኛ ሆነዋል፡፡ እኛም ቆመን ይህን ክፉ ድርጊት እናያለን። በእርግጥ በቦታው ስላልነበርን እንጂ የዚህ ክፉ ድርጊት ሰለባ አካል እንሆን ነበር፡፡  በክርስቲያኑ ላይ እየዘነበ ያለው የመከራ ዶፍ ዛሬም አላበቃም፡፡ በየዕለቱ  በክርስቲያኖች ላይ እየተፈጸመ ያለውን አዳዲስ ጥፋት እንሰማለን አሁን አሁን ሰቆቃውን የተለማመድን ይመስላል፡፡ አጀንዳውን ከማራገብ ውጪ ምንም መፍትሔ አላመጣንም፡፡ ከተሰጠን አጀንዳ ባሻገር ማየት ያቃተን ይመስላል ትላንትናም ዛሬም ነገም የምንሰማው ነገር አንድ ነው “ክርስቲያኖች ታረዱ” ከሚል ወሬ ውጪ መሬት የወረደ ፣ በተግባር የተገለጠ መፍትሔ ያስፈልጋል፡፡ ሥጋዊ ፍላጎቱን አሸንፎ ቤተ ክርስቲያንን እና ማዕተቤን እያለ አንገቱን እየሰጠ በአንድነት ለቆመ ክርስቲያን በአንድነት ቆሞ አርአያ መሆን ከአባቶች ይጠበቃል፡፡ መከራውን በድል እንሻገርም ዘንድ አባቶችን የሚያከብር፣ የሚፈራ እና የሚሰማ ትውልድ መፍጠር ራስን መለወጥ ይገባል፡፡ ዘመኑ አንዱ ሌላውን በመንቀፍና በማንቋሸሽ የሚተጋበት ፤ በዘርና በጎጥ ጎራ የሚለዩበት ሳይሆን ለቤተ ክርስቲያንና ለሀገር ሰላም በአንድነት የምንቆምበት ነውና፡፡ በየጊዜው ለሚወጡት መመሪያዎችና መግለጫዎች ተፈጻሚነት ከምእመኑ እስከ ቀዱስ ፓትርያርኩ ድረስ ‹‹እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ››  መሆንና እንደ ክርስቲያን መኖርን ይጠይቃል፡፡ ቤተ ክርስቲያኝ ለሀገር የምትተርፍ ቤተ ክርስቲያን ናትና  አጥብቀን ልንይዛት፣ በእውነት ልንመላለስባት፣ በአንድንት ልንቆምላት ያስፈልጋል፡፡ ቤተ ክርስቲያንን ለመታደግ መጀመሪያ ራሳችንን ልንታደግ ይገባል፡፡ ከውጭ ያለው በሰላም እንዲኖር  በውስጥ ያለው ሰላም ይሆን ዘንድ ግድ ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያን ክርስቶሳዊ ሰላም ለምእመናንዋ ብሎም ለሀገር የግድ ያስፈልጋል፡፡ በሰላም እጦት እየታወከ ላለው ምእመን መነሻው ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያለው ሰላም ነውና ከዚያ ሊጀምር ይገባል፡፡ የሀገር ሰላም መናጋት የቤተ ክርስቲያን ሰላም መናጋት ነውና ቅደስት ቤተ ክርስቲያን ሰላሙን ከቤትዋ መጀመር ይጠበቅባታል፤ ለዚህም ደግሞ  በክርስቶስ ክርስቲያን ተብሎ በአጸደ ቤተ ክርስቲያን የሚሰበሰብ ሁሉ የድርሻውን ሊወጣ ይገባል፡፡ እያንዳንዱ ክርስቲያን ወደ ገዛ መንገዱ ከመሄድ ተቆጥቦ መዋቅርዋ ባማረው ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ አሰላለፉን አሳምሮ ሊጓዝ ይባል፡፡ የቤተ ክርስቲያን መሠረት መናጋት የሀገር መሠረት መናጋት ነውና ፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ምንም ያልጎደላት ስንዱ እመቤት በመሆንዋ በተሰናዳው መዋቅር ውስጥ በፈሪሃ እግዚአብሔር በጸሎት መትጋት የዘመኑ ትልቅ መፍትሔ ነው፡፡ የሀገር አንድነትን ሆነ ሰላምን ለማምጣት የሰላማዊው ክርስቶስ ልጆች ለሰላም እና ለአንድነት በመቆም እየመጣ ያለውን የጥፋት እሳት ለማጥፋት በብርቱ ማገልገል ይጠበቃል ፤ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ቅዳሴዋ፣ ዝማሬዋ፣ ኪዳንዋና ሰዓታትዋ የሚነግሩን ይህንኑ እውነታ ነው፡፡ በተግባር የሚታይና የሚጨበጥ ለቤተ ክርስቲያን እና ለሀገር የሚጠቅም ሥራ ይሠራ ዘንድ በሚደረገው መንፈሳዊ ጉዞ ሁሉ  አባቶቻችን ከፊት ሆነው ሕዝቡን ሊመሩት ይገባል፡፡ መዋቅሩን በጠበቀ አደረጃጀት እንደ አባትና ልጅ በአንድ ላይ በመቆም አንደ ነነዌ ሰዎች ከልብ ሆነን እጃችንን ወደ እግዚአብሔር ልንዘረጋ ይገባል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ እጆችዋን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች›› መዝ.፷፯፥፴፩ የተባለላት ቅድስት ሀገር ናትና አምላከ ቅዱሳን ለጸሎትዋ መልስ አይነፍጋትም፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በየዕለቱ ስለ ሀገር ፣ ስለ ዓለም ሰላም የምትጸልይ እንደሆነች ቢታወቅም ዛሬ ሀገራችን እንዲህ ሰላም ባጣችበት ወቅት ደግሞ አብዝታ ወደ አምላክ ልታሳስብ ይገባል፡፡ ቅደስት ቤተ ክርስቲያን ስንል ምእመንዋን፣ ካህናትዋን፣ መነኮሳትዋን፣ ጳጳሳትዋንና ሊቃነ ጳጳሳትዋን እና በአፀደ ነፍስ ያሉ ቅዱሳንን ሁሉ ማለት እንደሆነ ሁሉም ልብ ሊለው ይገባል፡፡ ተደጋጋሚ ፈተና ሲፈራረቅባት እና የመከራ ዶፍ ሲወርድባት የከረመችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ለሰባት ቀን ባወጀችው ብሔራዊ ጾም ሁላችንም እንደ ነቢዩ ዕንባቆም ‹‹አቤቱ እኔ ስጮኽ የማትሰማው እስከ መቼ ነው?›› ዕን. ፩፥፪  በማለት ልንጸልይ ይገባል፤ ያኔ አምላክ መልስ ይኖረዋል  የቤተ ክርስቲያን መልስዋ ከላይ ነውና፡፡     
Read 704 times