Friday, 04 September 2020 00:00

 ሱባኤ

Written by  አባ ፍቅረ ማርያም መኩሪያ

Overview

ሱባኤ ቃሉ የግእዝ ሲሆን ሰባት ቁጥር ማለት ነው፡፡ ሰባት ቁጥር ደግሞ በዕብራውያን አቆጣጠር ፍጹም ቁጥር ማለት ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ብዙ በሰባት በሰባት የተጠቀሱ ነገሮችን ተጽፈው እናገኛለን፡፡ ለምሳሌ፡- አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር ሥነ ፍጥረትን በስድስት ቀን ፈጥሮ በሰባተኛው ቀን አርፎአል (ዘፍ.፪፥፪) ፡፡ ሰው ማለትም ሕያውነት፣ ለባዊነት ነባቢነት እና አራቱ ባሕርያተ ነፍስ ማለትም ነፋስ፣ እሳት፣ ውኃ፣ መሬት የተስማሙለት ማለት ነው፡፡ ሌላም በመጽሐፈ ምሳሌ ላይ ጠቢቡ ሰሎሞን ‹‹ጥበብ ቤትን ሰራች ሰባት ምሶሰዎቿን አቆመች›› (ምሳ.፱፥፩)  በማለት ተናግሯል። ጥበብ የተባለው ወልድ እግዚአብሔር ነው፡፡  ቅዱስ ዲዮስቆሮስ በቅዳሴው ‹‹ጥበብሰ መድኃኒነ ውእቱ፤ ጥበብ ግን መድኃኒታችን ነው›› እንዲል። ቤት የተባለች ቤተ ክርስቲያን ናት ሰባት ምሰሶዎች ተብለው የተነገሩት በቤተ ክርስቲያን የሚፈጸሙ ሰባቱ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን ናቸው፡፡ ይህ ብቻ አይደለም የሰባትን ፍጹምነት የሚያስረዱ ሌሎችም አሉ፡፡ ሰባቱ የጸሎት ጊዜያት “ስለ  እውነት  ፍርድህ በቀን ሰባት ጊዜ አመሰግንሃለሁ፡፡” (መዝ.፻፲፰፥፻፷፬)  ሰባቱ ሊቃነ መላእክት (ራእ. ፰፥፪) በእግዚአብሔር ፊት የሚቆሙትን ሰባቱን መላእክት ተመለከትኩ እንዲል። እነዚህ ከላይ የተመለከትናቸው የሰባት ቁጥርን ፍጹምነት የሚያስረዱ ለምሳሌነት የተጠቀሱ ናቸው፡፡  ሌላው ሱባኤ ማለት በጾም፣ በጸሎት፣ በስግደት፣ በምጽዋት፣ ወዘተ… ወደ እግዚአብሔር ለመቅረብ በቁርጥ ኅሊና፣ በተዘጋጀ ልቡና፣ በቤት፣ በገዳም ወደ እግዚአብሔር የምንቀርብበት ነው፡፡ ሰባቱን ዕለታት አንድ እያለ በመቍጠር ሰው እንደ ፍላጐቱ አንድ ሱባኤ ሰባት ቀን፣ ሁለት ሱባኤ ዐሥራ አራት ቀን፣ ሦስት ሲባኤ ሃያ አንድ ቀን… እግዚአብሔርን ደጅ ለመጽናት በጾም፣ በጸሎትና በስግደት ሳምንቱን በመንፈሳዊ ትሩፋት የሚጠመድበት ማለት ነው፡፡ 

 

ሱባኤ በስንት ይከፈላል?

ሱባኤ በሦስት ይከፈላል እነርሱም  ፩ የግል፣ ፪.የማኅበር፣ ፫.የአዋጅ በመባል ይታወቃሉ፡፡ ከዚህ በታች በጥቂቱ ለመመልከት እንሞክራለን፡-

ሀ/ የግል ሱባኤ፡- ይህ በግል የሚደረገው ሱባኤ በምክረ ካህን በፈቃደ እግዚአብሔር የሚከወን ነው ለምሳሌ፡- አንድ ሰው ኃጢአት ሠርቶ ኃጢአቱን ለመምህረ ንስሓው በተናዘዘ ጊዜ መምህረ ንስሓው የሚሰጠው ቀኖና በሱባኤ ሊወሰን ይችላል ይህንን ሱባኤ በግል ተነሳሒው እና የንስሓ አባቱ ብቻ የሚያውቁት ። ሌላው በዚህ በግል ሱባኤ አንዳንድ በገዳም ያሉ አባቶችና እናቶች እንዲሁም የበረቱ አንዳንድ ምእመናን በተለያዩ የአጽዋማት ጊዜ በግላቸው ከሰው ተለይተው በቦታ ተወስነው ዋሻ ወይም ቤት ዘግተው በጾም፣ በጸሎት በስግደትና በአርምሞ የሚያሳልፉ አሉ፡፡ ይህም የሚቻል እና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነው፡፡ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቅዱስ ወንጌል ‹‹አንተ ግን ስትጸልይ ወደ እልፍኝህ ግባ መዝጊያህንም ዘግተህ በስውር ላለው አባትህ ጸልይ በስውር የሚያይ አባትህም በግልጥ ይከፍልሃል›› (ማቴ.፮፥፮) በማለት እንደተናገረ  ፡፡ 

ለ/ የማኅበር ሱባኤ፡- ይህ ሱባኤ በተለይ በገዳማት የሚኖሩ አባቶች መነኮሳትና እናቶች መነኮሳይያት የሚጠቀሙበት የሱባኤ ዓይነት ነው፡፡ ይኸውም በሚኖሩበት ገዳም የተነሣ ፈተና ካለ ያንን ልዑል እግዚአብሔር እንዲያርቅላቸው ገዳማቸውንም እንዲጠብቅላቸው በማኅበሩ አበምኔት ወይንም እመ ምኔት በመታዘዝ የማኅበር ሱባኤ በኅብረት በመሆን በጾም፣ በጸሎትና በስግደት ሊገቡ ይችላሉ፡፡ ቅዱስ ዳዊት ‹‹ ወንድሞች በኅብረት ቢቀመጡ እነሆ መልካም ነው እነሆም ያማረ ነው›› (መዝ. ፻፴፪፥፩)  ብሎ እንደተናገረ ገደማውያኑ የያዙትን ሱባኤ ተቀብሎ እግዚአብሔር ገዳምን ይጠብቃል። የመጣውን ፈተና ይመልሰዋል፡፡ መነኮሳትና መነኮሳይያት ስለ ገዳማቸው ብቻ ያይደለ ስለ ሀገርም ስለ ቤተ ክርስቲያንም ስለ ሕዝቡም መጠበቅ ጭምር ሱባኤ ሰለሚይዙ በእነርሱ ልመና ልዑል እግዚአብሔር ይጠብቀናል። የማኅበር ሱባኤ በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት የሆኑት ቅዱሳን ሐዋርያት ናቸው፡፡ የሐዋርያትን ሥራ የጻፈልን ቅዱስ ሉቃስ የሐዋርያትን ስም ይዘረዝርና ‹‹እነዚህ ሁሉ ከሴቶች እና ከኢየሱስ እናት ከማርያም ከወንድሞቹም ጋር በአንድ ልብ ሆነው ለጸሎት ይተጉ ነበር›› (ሐዋ.፩፥፲፪-፲፬) ይላል፡፡ ሐዋርያት ድንግል ማርያምን በመካከል አድርገው ይዘውት የነበረው ሱባኤ በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት አግኝቶ ጌታ በዐረገ በዐሥረኛው ቀን ከሞት በተነሣ በሃምሣኛው ቀን መንፈስ ቅዱስ ወርዶላቸው በአገሩ ሁሉ ቋንቋ ተናግረዋል፡፡ ዙረው ወንጌልን አስተምረዋል፡፡ መከራውን ሁሉ ታግሰው አገልግለዋል፤ በስተመጨረሻም በፍጹም ጽናት በሰማዕትነት አርፈዋል፤ የክብር አክሊል ተሸልመዋል፡፡ ዛሬም በሰማያት ስለ እኛ እየማለዱ አሉ ይሄ ሁሉ ጸጋ እና ክብር የተገኘው በማኅበር ሱባኤ ነው፡፡ 

ሐ/ በአዋጅ አጽዋማት የሚያዝ ሱባኤ፡- ይህ ሱባኤ ክርስቲያኑ በሙሉ በአዋጅ አጽዋማት ማለትም በሰባቱ አጽዋማት የሚይዘው ሱባኤ ነው በአዋጅ ጾም ለምሳሌ የነነዌ ሰዎች እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ሆነው ወደ እግዚአብሔር በመመለሳቸው ተጠቅመውበታል። ሊመጣባቸው ከነበረው የእሳት መቃጠል በአዋጅ በያዙት ጾምና ጸሎት (ሱባኤ) በሦስት ቀን ልዑል እግዚአብሔር የምሕረት ፊቱን መልሶላቸው ከመቅሰፍት ድነውበታል፡፡ (ዮና. ፫ እና ፬) እንደዚሁም በአስቴር ዘመን እስራኤላውያን ‹‹ሃማ›› ከተባለ ጠላታቸው እና ከተመከረባቸው ክፉ የመጥፋት ምክር የዳኑት በአዋጅ በያዙት ሱባኤ ነበር፡፡  

በመጽሐፈ አስቴር ተመዝግቦ እንደምናገኘው  ችግር በመጣ ጊዜ በአዋጅ  መጾም መጸለይ (ሱባኤ መግባት) ከመጣ መከራ ያድናል። ‹‹አስቴርም እንዲህ ብሎ ለመርዶክዮስ እንዲመለሱ አዘዘችው ሄደህ በሱሳ ያሉትን አይሁድ ሁሉ ሰብስብ ለእኔም ጹሙ ሦስት ቀን ሌሊቱን እና ቀኑን አትብሉ፤ አትጠጡም፤ እኔና ደንገጡሮቼም ደግሞ እንዲሁ እንጾማለን ምንም እንኳ ያለ ሕግ ቢሆን ወደ ንጉሡ እገባለሁ፤ ብጠፋም እጠፋለሁ መርዶክዮስም ሂዶ አስቴር እንዳዘዘችው ሁሉ አደገ፡፡›› (አስ.፬፥፲፭)  እንዲል። ይህንንም የእስራኤልን ሱባኤ ተቀብሎ ልዑል እግዚአብሔር ሃማን በራሱ ምክር ባዘጋጀው ግንድ ተሰቅሎ እንዲሞት አድርጐታል፡፡ (አስ. ፯፥፩-፲) 

ሱባኤ ለምን እንገባለን?

ሱባኤ የምንገባባቸው ምክንያቶች ብዙ ቢሆኑም ከዚህ በታች ግን ጥቂቶችን እንመለከታልን፡፡ ፩/ ልዑል እግዚአብሔርን ለመለመን፡- ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቅዱስ ወንጌል ለምኑ ይሰጣችሁማል፤ ፈልጉ ታገኙማላችሁ፤ መዝጊያ አንኳኩ ይከፈትላችኋል፡፡ (ማቴ.፯፥፯) ባለው አምላካዊ ቃል መሠረት ሱባኤ የምንገባው ልዑል እግዚብሔርን ለመለመን ነው፡፡ በልመናችን ጊዜ ግን በማስተዋል መለመን ይገባል፡፡ በቅዱስ ወንጌል የዘብዴዎስ ልጆች ያዕቆብ እና ዮሐንስ እንዲሁም እናታቸው ማርያም ባውፍልያ የምትለምኑትን የማታውቁ ተብለዋል፡፡ (ማቴ. ፳፥፩)

፪/ ከቅዱሳን በረከት ለመሳተፍ፡- በረከትን የሚያድል እግዚአብሔር ቢሆንም ቅዱሳን ለእግዚአብሔር ካላቸው ቅርበትና ከተሰጣቸው ቃል ኪዳን የተነሳ በረከትን ከእግዚአብሔ እየለመኑ ያሰጡናል፡፡

ጠቢቡ ሰሎሞን በመጽሐፈ ምሳሌ ላይ ‹‹በረከት በቅዱሳን ራስ ላይ ነው››(ምሳ. ፲፥፯) ሲል እንደተናገረ የቅዱሳን በረከት ለማግኘት ሱባኤ እንገባለን ለምሳሌ የአቡነ ተክለሃይማኖት ስም የሚጠራበት ገዳም እና ቤተ ክርስቲያን ቢኖር የቅዱሱን በረከት በሱባኤ ማግኘት ይቻላል፡፡ አምላካችን ልዑል እግዚአብሔርም በነቢዩ በኢሳይየስ አድሮ ‹‹… በቤት እና በቅጥሬ የማይጠፋ ዘለዓለማዊ ስም እሰጣቸዋለሁ›› (ኢሳ.፶፮፥፬) ብሎ እንደነገረን በቅዱሳን መካናት በተለይም ስሙ የሚጠራው ቅዱስ ተጋድሎውን በፈጸሙበት ቃል ኪዳን በተቀበለበት ዐፅሙ ባረፈበት ቦታ የቅዱሳን በረከት ተሳታፊ ለመሆን ሱባኤ ይያዛል፡፡ 

፫/ የተሠወረ  ምሥጢር እንዲገለጽ፡- የተሰወሩ ምሥጢራት እንዲገለጹልን በሱባኤ እግዚአብሔርን መጠየቅ ይገባል፡፡ የግብፅ ንጉሥ ፈርኦን የተሰወረበትን ምሥጢር የእግዚብሔር ሰው ዮሴፍ እንደገለጠለት (ዘፍ.፵፩፥፲፬-፲፮) የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር እና ብልጣሶር የተሰወረባቸውን ምሥጢር ነቢዩ ዳንኤል እንደገለጠላቸው ( ዳን. ፬፥፱፤ ዳን.፭፥፬) እንደዚሁም በባቢሎን ምርኮ ጊዜ ተቃጥለው የነበሩ መጻሕፍት እንዲገለጡለት ነቢዩ ዕዝራ ሱቱኤል ወደ ልዑል እግዚአብሔር በጸለየው ጸሎት በጾመው ጾም በያዘው ሱባኤ የእግዚአብሔር መልአክ ቅዱስ ኡራኤል ወደ እርሱ መጥቶ ጠፍተው የነበሩትን ፵፮ የኦሪት መጻሕፍት እንደ ገለጠለት እና በስተ መጨረሻም ሞትን እንዳያይ እንዲሰወር አድርጐታል፡፡ (ዕዝ.ሱቱ.፩) እንዲህ ለአብነት ያህል እነዚህን ከላይ የተመለከትናቸውን ጠቀስን እንጂ ብዙ እንቆቅልሻቸው በሱባኤ የተፈታላቸው ቅዱሳን አባቶች እና እናቶች አሉ። እኛም በሕይወታችን እንቆቅልሽ የሆነብን ነገር ሁሉ እንዲፈታልን እና ለጥያቄያችን መልስ እንድናገኝ በሱባኤ ልዑል እግዚአብሔርን ደጅ መጽናት ይገባል፡፡ 

በሱባኤ የተጠቀሙ እነማን ናቸው?

በሱባኤ የተጠቀሙ እጅግ በጣም ብዙ ቢሆኑም በዚህ ጽሑፍ ግን እጅግ ጥቂቶችን ለአብነት ያህል እንመለከታለን፡፡ 

ሀ/ አዳም፡- አባታችን አዳም ከገነት በተሰደደ ጊዜ በበደሉ ምክንያት ገነትን ያህል ቦታ እግዚአብሔርን ያህል ቸር ጌታ በማጣቱ እጅግ አድርጐ አዘነ ስለዚህም ንስሓ ገብቶ ፈጣሪውን በሱባኤ ደጅ ጠና። ከደሙም ጋር የስንዴ መሥዋዕትን አቀረበ አምላካችን ልዑል እግዚአብሔርም የዛሬውን ተቀበልኩህ ዓለም የሚድነው በልጄ ደም ነው፡፡ አምስት ቀን ተኩል ሲፈጸም ከልጅ ልጅህ ተወልጄ በሜዳህ ድሄ፣ በመስቀል ተሰቅዬ፣ ቤዛ እሆንሀለሁ አለው፡፡ አምስት ቀን ተኩል በእግዚአብሔር አቆጣጠር ፭ ሺህ ፭መቶ ዘመን ነው የገባውንም ቃል ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ሰው በመሆን ፈጸመለት መ.ቀሌምንጦስ አንቀጽ፡ ፬ (ገላ.፬፥፬) ይህ የሱባኤው ውጤት ነው፡፡ 

ለ/ ነቢያት፡- ቅዱሳን አባቶቻችን ነቢያት የጌታችንን ሰው መሆን እየናፈቁ በብዙ ሱባኤ ደጅ ይጠኑ ነበር።  ለምሳሌ ሙሴ፣ ኢሳይያስ፣ ኤርምያስ እና ዳዊት ተጠቃሽ ናቸው።  በተለይ ቅዱስ ዳዊት ‹‹በእውነት ወደ ቤቴ አልገባም ወደ ምንጣፌ አልጋም አልወጣም ለዐይኖቼ መኝታ ለሽፋሽፍቶቼ እንቀልፍ ለጉንጮቼም እረፍት አልሰጥም ለእግዚአብሔር ሥፍራ ለያዕቆብ አምላክ ማደሪያ እስካገኝ›› (መዝ.፻፴፩፥፫) ብሎ ጽኑዕ ምኞቱን ገልጾአል። ይህ በጊዜው ዳዊት ለእግዚአብሔር ታቦት ቤተ መቅደስ ለመሥራት ማደሪያውን ለማዘጋጀት የያዘውን ሱባኤ ያመለክታል፡፡ ምሥጢሩ ግን የያዕቆብ አምላክ እግዚአብሔር ማደሪያው የምትሆን ድንግል ማርያምን ለማየት አምላክ ሰው የሚሆንበትን ጊዜ የመናፈቅ ነው፡፡ ስለሆነም ሱባኤውን የተቀበለለት አምላክ መልስ ሲሰጠው ‹‹እነሆ በኤፍራታ ሰማነው በዱር ውስጥም አገኘነው›› (መዝ.፻፴፩፥፮) ብሎ ጌታ በኤፍራታ ቤተ ልሔም የሚወለድ መሆኑን በግዕዘ ሕፃናት ሲያለቅስ እንደሰማው ሁኖ በትንቢት መነፅር ተመለከተው፡፡ ይህ ሁሉ የሱባኤ ውጤት ነው፡፡ 

ሐ/ ሐዋርያት፡- ክቡራን አባቶቻችን ሐዋርያት በሱባኤ ተጠቅመዋል የተሰወረው ምሥጢር ተገልጾላቸዋል። በተለይ የአባቶቻችን የሐዋርያት ሱባኤ የሚጠቀሰው በድንግል ማርያም ምክንያት የገቡት ሱባኤና ያገኙት ውጤት ነው፡፡ ይኸውም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በዚህ ዓለም ፷፬ ዓመት በንጽሕና፤ በቅድስናና በድንግልና ኑራ ጥር ፳፩ ቀን ከዚህ ዓለም ድካም ባረፈች ጊዜ ማለትም ነፍሷ ከሥጋዋ በተለየች (በሞተች) ጊዜ አክብረው ገንዘው እያመሰገኑ ወደ ጌቴ ሴማኒ ለመቅበር ሲወስዷት አይሁድ የእመቤታችንን ሥጋዋን በእሳት ለማቃጠል መጡ፡፡ ከእነሱ መካከል ታውፋንያ የተባለው ደፋር የድንግል ማርያምን ሥጋዋን ወደ መሬት ለመጣል በቀረበ ጊዜ የአልጋውንም ሸንኮር በእጅ በያዘ ጊዜ ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክ እጆቹን በእሳት ሰይፍ ቆረጣቸው። ያን ጊዜ ወደ ልቡ ተመልሶ ይቅርታ ጠየቀ፤ ድንግል ማርያምም በኅቡዕ ተአምር ቅዱስ ጴጥሮስን አዝዛ የተቆረጠ እጆቹን መለሰችለት። ቅዱስ  ጴጥሮስም ለታውፋንያ በትር ሰጥቶ የኢየሱስ ክርስቶስን አምላክነት የድንግል ማርያምን አማላጅነት እንዲመሰክር አዘዘው። እርሱም በአይሁድ መካከል መስክሮ በድንጋይ ተወግሮ በሰማዕትነት አረፈ፡፡ (ምንጭ)

የእግዚአብሔር መልአክ ቅዱስ ገብርኤል የድንግል ማርያምን ሥጋ ከቅዱስ ዮሐንስ ጋር ወደ ሰማይ አሳረገ፡፡ ሥጋዋንም በዕፀ ሕይወት ሥር አኖረው መላእክትም ሥጋዋን ያጥኑ ነበር፡፡ ነፍሷ ግን በልጇ ቀኝ በክብር ተቀመጠ (መዝ.፵፬፥፱) ወንጌላዊ ዮሐንስም ይህን አይቶ ተመልሶ መጥቶ ለሐዋርያት ነገራቸው እነርሱም ዮሐንስ እንዳየ ስላላዩ እንደሰማ ስላልሰሙ የድንግል ማርይምን ሥጋ ለማግኘት ከነሐሴ ፩-፲፬ ቀን ሁለት ሱባኤ ከጾሙ ከጸለዩ በኋላ ጌታ የእመቤታችንን ሥጋ አምጥቶ ሰጣቸው፡፡ እነርሱም ወስደው በጌቴ ሴማኒ ቀበሯት። በልጇ ሥልጣን ተነሥታ በዕዝራ መሰንቆ በዳዊት በገና በመላእክት እልልታ ስታርግ ቶማስ በደመና ሲመጣ ተመለከታት። እጅግ አዝኖ ከደመናው ሊወድቅ ወደደ ቀድሞ የልጅሽን ትንሣኤ አላየሁ አሁን ደግሞ ያንችን ብሎ እመቤታችንም አጽናንታ “ከአንተ በቅር ትንሣኤዬንም ዕርገቴንም ያየ የለም” ብላ ለበረከት እንዲሆናቸው ሰበኗን ሰጠችው። እርሱም ከእርሷ ተባርኮ ወደ ሐዋርያት መጣ፡፡ 

ሐዋርያቱም ተሰብስበው አገኛቸው የእመቤታችን ነገር እንዴት ሆነ? ብሎ ጠየቃቸው እነርሱም ሥጋዋን አግኝተን ወስደን ቀብርናት አሉት፡፡ እርሱም ‹‹ሞት በጥር በነሐሴ መቃብር›› እንዴት ይሆናል? አላምንም አላቸው፡፡  

ቅዱስ ጴጥሮስ ቀድሞም ተጠራጣሪ ነህና ተነሥ እናሳይህ ተጠራጥረህ ስታጠራጥር እንዳትኖር ብሎ ወደ ጌቴ ሴማኒ መቃብር ወስዶ መቃብሩን ቢከፍት የድንግልን ሥጋ አጣው። ቶማስም እመቤታችን ከሞት ተነሥታ ዐርጋለች። ይህው ሰብኗ ብሎ ለበረከት ሰጣቸው። ያንን ተከፋፍለው በዚያ ተአምራት ሲያደርጉበት ከኖሩ በኋላ ቶማስ ትንሣኤሽን ዕርገትሽን አይቶ እኛ እንዴት ይቀርብናል ብለው በዓመቱ ነሐሴ ፩ ጾም ጀመሩ ነሐሴ ፲፮ ቀን ሐዋርያትን ሁሉ ጌታ ወደ ሰማይ አውጥቷቸው የእመቤታችንን ትንሣኤዋን እና ዕርገቷን አሳያቸው። እርሷንም መንበር አድርጐ ቀድሶ ሥጋውን ደሙን አቀበላቸው። ለእመቤታችንም የከበረ ቃል ኪዳን ከሰጣት በኋላ  የእመቤታችን ትንሣኤዋን እና ዕርገቷን እንዲያስተምሩ ተዝካሯን እንዲያደርጉ ሐዋርያትን አዘዛቸው፡፡ እነርሱም የታዘዙትን ፈጸሙ፡፡ 

ይህ ከላይ የተመለከትነው ፍጹም የሆነ ሱባኤ የሚያስገኘውን ውጤት ነው፡፡ እኛም በሕይወታችን ሰለሚያስፈልገን ነገር ሃይማኖት ለማጽናት ምግባር ስለ ማቅናት በምንይዘው ሱባኤ መልስ እንድናገኝ የልዑል እግዚአብሔር ቸርነት የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት የቅዱሳን መላእክት ተራዳኢነት የጻድቃን የሰማዕታት የቅዱሳን ሁሉ ጸሎት ሁላችንን ይርዳን አሜን፡፡   

 

Read 1820 times