Friday, 04 September 2020 00:00

ክብረ ክህነት (ክፍል ሁለት)

Written by  ዲ/ን ዐብይ ሙሉቀን

Overview

 ክህነት እንዴት ይሾማል   ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ “ኢኀደጋ ለምድር እንበለ ካህናት ወዲያቆናት፣ እምቅድመ ዓለም ወእስከ ለዓለም፤ ቸሩ አምላክ እግዚአብሔር ለዘለዓለም እስከ ለዓለም ምድርን ያለ ካህናትና ዲያቆናት አልተዋትም’’ (ዚቅ ዘኅዳር ጽዮን) በማለት እንደገለጸው ክህነት ከጥንት ከአዳም ጀምሮ እንደነበረ በክፍል አንድ ተመልክተናል፡፡ በዚህ ክፍል ደግሞ ክህነት እንዴት ይሾማል የሚለውን እንመለከታለን፡፡ የክህነት አሿሿም ሥርዓት በየዘመናቱ ይለያያል፡፡ ሿሚው ራሱ እግዚአብሔር ሁኖ የሚሾምበት ሥርዓት ግን እንደዘመናቱ ነባራዊ ሁኔታ የተለያየ እንደነበር መገንዘብ ይገባል፡፡ ለምሳሌ አዳምን በቀጥታ እግዚአብሔር ሾመው፤ መልከ ጼዴቅንም እንዲሁ በቀጥታ እግዚአብሔር ሾመው፡፡ አሮንና ከእርሱ በኋላ የነበረውን የክህነት አሿሿም ስንመለከት ደግሞ በሙሴ አማካኝነት ተሾሙ:: ከዚያ በኋላ በዘር ማለትም ከሌዊ ወገን የሆነውን በዘመኑ የሚኖረው ሊቀ ካህን ሲሾም ኖሯል፤ ሐዋርያትን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሾማቸው፤ ከእነርሱ በኋላ ደግሞ ተከታዮቻቸውን እነርሱ እንዲሾሙ ታዝዘዋልና ሐዋርያት ሲሾሙ ኖረዋል፤ የእነርሱ ተከታዮችም እንዲሁ እየሾሙ ኖረዋል፡፡ የሐዲስ ኪዳኑ አማናዊ ክህነት ከሐዋርያት ጀምሮ ሐዋርያዊ ቅብብሎሹ ሳይቋረጥ እየተላለፈ ዛሬ ላይ ደርሷል፡፡

 

ይህ ሐዋርያዊ ቅብብሎሹን ሳያቋርጥ ዛሬ ላይ የደረሰው የክህነት አሿሿም በአንብሮተ እድ ይከናወናል። በሐዋርያት ዘመን እንዴት እንደቀጠለ የሐዋርያት ሥራን የጻፈው ቅዱስ ሉቃስ “ወንድሞቻችን ሆይ ከእናንተ ወገን በመልካም የተመሰከረላቸውን መንፈስ ቅዱስና ጥበብ የሞላባቸውን ሰባት ሰዎችን ምረጡ፤ ለዚህ ሥራም እንሾማቸዋለን” (ሐዋ.፮፥፫) በማለት እንደነገረን ሐዋርያት እነርሱን በክህነት አገልግሎት እንዲያግዟቸው በሕዝብ ዘንድ የተመሰከረላቸውን፣ በመንፈስ ቅዱስና በጥበብ የተሞሉትን ካስመረጡ በኋላ እንደሾሟቸው ያስረዳናል። የአሿሿም ሥርዓቱንም “በሐዋርያትም ፊት አቆሟቸው፤ ጸልየውም እጃቸውን በራሳቸው ላይ ጫኑ” (ሐዋ.፮፥፮) በማለት በምን ሥርዓት እንደተሾሙ ያስረዳናል።

ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ በመንፈስ ቅዱስ የወለደውን ጢሞቴዎስን “ስለዚህም ምክንያት እጄን በአንተ ላይ በመጫኔ ያገኘኸው የእግዚአብሔር ጸጋ ይታደስልህ ዘንድ አስብሃለሁ፤ የእግዚአብሔር የኃይልና የንጽሕና፣ የፍቅርና የጥበብ መንፈስን እንጂ የፍርሀት መንፈስን አልሰጠንምና” (፪ጢሞ.፩፥፮-፯) በማለት በምን ዓይነት ሥርዓት እንደሾመው ያስረዳናል። ይህ አማናዊው የሐዲስ ኪዳን ክህነት በክርስቶስ ተጀምሮ ወደሐዋርያት ተላልፎ ሐዋርያዊ ቅብብሎሹን ሳያቋርጥ እስከዚህ ዘመን ደርሷል በዚህ መንገድ እስከ ዓለም ፍጻሜም ይቀጥላል፡፡ የሐዲስ ኪዳን ክህነት በክርስቶስ መሥራችነት ከሐዋርያት የቀጠለና ሐዋርያዊ ለመሆኑ ተጨማሪ ማስረጃ እንመልከት፡፡

ሐዋርያት ከራሱ ከሊቀ ካህናት ከኢየሱስ ክርስቶስ የተቀበሉትን ክህነት እነርሱም በሰጣቸው በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ፈቃድ ለተከታዮቻቸው አስተላልፈዋል፡፡ ይህ የሐዋርያት ክህነት ከእነርሱ ወደ ተከታዮቻቸው እንደተላለፈ በመጽሐፈ ዲዲስቅልያ እንዲህ ተገልጾ እናገኘዋለን፡፡ “በእኛም ዘንድ የተሾሙ ስማቸው ይህ ነው፡፡ መጀመሪያ በኢየሩሳሌም የተሾመ የጌታችን ወንድም ያዕቆብ ነው፡፡ ከእርሱም ቀጥሎ የቀለዮጳ ልጅ ስምዖን ነው፡፡” በማለት የሁሉንም ስም ይዘረዝርና በመጨረሻም “በኢየሩሳሌም አምነን የሾምናቸው በየሀገራቸው ይሰብኩ ያስተምሩ ዘንድ የላክናቸው እሊህ ናቸው፡፡ የእነዚህን ድካማቸውን አስቡ፤ ምክራቸውንም ተቀበሉ፤ ቃላቸውንም ጠብቁ፤ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ይሁን፤ ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዘለዓለሙ” (መጽሐፈ ዲዲስቅልያ አንቀጽ ፵፫) ተብሎ ተጽፎ እናገኘዋለን፡፡

ዲያቆን ያረጋል አበጋዝ መድሎተ ጽድቅ በተባለው መጽሐፉ በቅጽ ሁለት ሐዋርያዊ ክህነትን በተመለከተ በስፋት አስረድቷል፡፡ ከመጽሐፉ መመልከቱ የተሻለ ግልጽ እንደሚያደርገው የታመነ ቢሆንም ለማሳያ ያህል እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡ 

ሁሉም ምሥጢራት የሚፈጸሙት በካህናት ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደሯም ሳይቀር ሐዋርያዊ እንጂ በሙያቸው ወይም በሌላ መለኪያ ተወዳድረው ሥራ እንደሚቀጠሩባቸው እንደ ሌሎች ወይም ተቋማት አይደለም፡፡ ቤተ ክርስቲያን በአስተዳደሯም ሐዋርያዊት ናት፡፡ ሁል ጊዜም የምትመራው የሐዋርያት ተከታዮች (ወራሾች) በሆኑ ጳጳሳት ነውና፡፡ 

ስለሆነም ክህነት ለቤተ ክርስቲያን ህልውና ቍልፍ (ጉዳይ) ነው። እንዲህ ከሆነ ይህ ቤተ ክርስቲያን የምትገለገልበት ክህነት ከቤተ ክርስቲያኗ መሥራችና ባለቤት ከጌታ የተገኘ ሊሆን የግድ ነው። ከጌታ የተገኘ ለመሆኑ ማረጋገጫው እና መለኪያው ምንድን ነው? ከተባለ ይህን የክህነት ጸጋ ከሊቀ ካህናት ከኢየሱስ ክርስቶስ ከተቀበሉ ከሐዋርያት እና እነርሱ ከሾሟቸው አባቶች ባልተቋረጠ ቅብብሎሽ የተገኘ ወይም የመጣ መሆኑ ነው።

ይህ ሐዋርያዊ ቅብብሎሽ የሆነ ቦታ ላይ ከተቋረጠ ‘ክህነቱ’ የሊቀ ካህናት የኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑ ቀረ ማለት ነው። እንዲህ ከተቋረጠ ደግሞ ማንም የክርስቶስ ክህነት ሊል አይችልም። አይሁድ ፋሲካቸው ከእግዚአብሔር የተሰጣቸው ስለነበረ ከእርሱ በተሰጡበት መንፈስና መንገድ ሲያከብሩ ሳለ “የእግዚአብሔር ፋሲካ” ተብሎ ይጠራ ነበር፡፡ (ዘፀ.፩፥፩፤ ዘሌ.፳፭፥፭፤ ዘኍ.፳፰፥፲፮) ከዚያ መንፈስና መንገድ ወጥተው በራሳቸው ስሜትና መንገድ ፋሲካን በማድረጋቸው “የአይሁድ ፋሲካ” ተባለባቸው፡፡ (ዮሐ.፪፥፲፫) እንደዚሁም ሁሉ ባልተቋረጠ ሐዋርያዊ ቅብብሎሽ ከመጣው ክህነት ውጭ “ክህነት አለኝ” የሚል ቢኖር ይህ ክህነት “የእገሌ ክህነት” ነው የሚባለው፡፡ 

ሐዋርያዊ የሆነው ክህነት ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ከሐዋርያትና ከክርስቶስ ጋር በቀጥታ የሚያገናኛት መስመር ነው። ይህ የቤተ ክርስቲያን ከሐዋርያት እና ከክርስቶስ ጋር ያላት ቀጥተኛ ግንኙነትም አሳባዊ አንድነት ወይም የማይታይ ዓይነት አንድነት አይደለም። እንዲሁ በመጻሕፍት እና በታሪካዊ ኵነቶች ያለ ዕውቀት ብቻም አይደለም። በምሥጢረ ክህነት አማካኝነት ቀጥተኛ የሆነ ሕያው ግንኙነት ነው እንጂ። በዚህ ምሥጢር አማካኝነት ዛሬ ያለችው ቤተ ክርስቲያን ሐረጓ ሲሰላና ሲመዘዝ ከሐዋርያት እና ከራሱ ከክርስቶስ ጋር ቀጥተኛ በሆነ ሕያው መስመር ያገናኛታል። ቤተ ክርስቲያንን ሐዋርያዊት ከሚያሰኛት አንዱ ይህ ነው” (ያረጋል.፳፻፲፪ ገጽ ፬፻፸፱)። 

ከላይ በሰፊው የቀረበው የዲያቀን ያረጋል ሐሳብ የሐዲስ ኪዳን ክህነት መሠረቱ ክርስቶስ ሆኖ በሐዋርያት ተቀባይነት ሐዋርያዊ ቅብብሎሹን ያላቋረጠ ይህን ሐዋርየዊ ቅብብሎሽ ካቋረጠ ደግሞ የግለሰቦች ክህት እንጂ የክርስቶስ ክህነት ሊባል እንደማይችል ያስረዳናል፡፡ ክህነት ይህ ዓይነት ቅብብሎሽ ስላለው ሀገራችን ኢትዮጵያ ከ፲፮፻ ዓመታት በላይ በቅርብ ሆኖ ጳጳሳትን፣ ካህናትን፣ ዲያቆናትን፣ የሚሾም፣ ቢያስፈልጋትም ሐዋርያዊ ቅብብሎሹን ላለማቋረጥ በእስክንድርያ ሥር ቆይታለች፡፡ በሁለቱ ሀገር መካከል ፖለቲካዊ ግጭት ሲፈጠር፣ የአሕዛብ ነገሥታት ሲነግሡና ጳጳስ ወደኢትዮጵያ እንዳይላክ ሲከለክሉ እስከ ሦስታና አራት መቶ ዓመታት ድረስ እየታገሠች ቆይታለች፡፡ ይህ ሁሉ ጥረት ሐዋርያዊ ቅብብሎሹ እንዳይቋረጥ ነው፡፡ ደግሞም ክህነቱ አማናዊ የሚሆነው ሕጋዊ የሆነ ሿሚ ሲኖረው ነው፡፡ ክህነት እንደፖለቲካ ሹመት ተሰብስቦ በድምጽ ብልጫ፣ በብዙኃን ይሁንታ  የሚሾሙት ሹመት አይደለም፡፡ 

ፍትሕ መንፈሳዊ የክህነት አሿሿምን በተመለከተ በሰፊው ያትታል፡፡ ከሰፊ ሐተታው ውስጥ ግን ለዚህ ይሆናል ያልነውን እንደሚከተለው እንጠቅሳለን፡፡ “የሊቀ ጳጳሱ ሹመት የኤጲስ ቆጶሳትና የመጥሮጶሊሶች (ጳጳሳት) ጉባኤ ሳይሆን አይፈጸምም፡፡” (አንቀጽ ፬ ቁጥር ፶፯) ይህ የሊቀ ጳጳሱስ ሹመት የሚመለከት ሲሆን የኤጲስ ቆጶሱንም ከኒቂያ ጉባኤ ቁጥር ፱ በመጥቀስ እንዲህ በማለት ገልጸውታል፡፡ “አንድ ሰው ኤጲስ ቆጶስነትን ሊሾም ቢፈልግ ሕዝቡም ቢስማሙ ያገሩ ጳጳስ ግን ባይፈቅድ ያለ እርሱ ፈቃድ ኤጲስ ቆጶስነት መሾም አይገባውም፡፡ ይህን ቢያፈርስ ሲኖዶስ ያወግዘዋል፡፡ ኤጲስ ቆጶስነቱም ይቀራል፡፡ ስለ እርሱ የሚበዙት ቢስማሙ ግን ጳጳሳቱም ቢስማሙበት በድምፅ ብልጫ ይሹሙት” (አንቀጽ ፭፥ቁ፺፩)  “ያለ ኢጲስ ቆጶሱ ፈቃድ ቄስም ዲያቆንም አይሾም” (አንቀጽ ፭፥ቁ፻፲)  በማለትም በተዋረድ ሊቀ ጳጳሱን ለመሾም የኤጲስ ቆጶሳትና የጳጳሳት ጉባኤ፣ ኤጲስ ቆጶሳትን ለመሾም የሊቀ ጳጳሱ ፈቃድና የጳጳሳት ስምምነት ወይም ጉባኤ ቀሳውስትንና ዲያቆናትን ለመሾም ደግሞ የኤጲስ ቆጶሱ ፈቃድ እንደሚያስፈልግ ያስረዳል፡፡

ሐዋርያት በመጽሐፈ ዲዲስቅልያ “ቀሳውስት፡- ዲያቆናትንና ዲያቆናዊትን፣ አናጉንስጢስንም፣ መዘምራንንም በር ዘጊዎችንም እንዳይሾሙ እናዝዛለን፡፡ እነሆ አስቀድመን ነግረናቸው እንደዚህ የሚያደርጉ ሰዎች ከክርስቲያን ወገኖች የተለዩ ይሆናሉና ፡፡ (ዲዲስቅልያ አንቀጽ ፲፭፥፯-፲) በማለት ቀሳውስት እንኳንስ ከእነርሱ በላይ ያለ መዐርገ ክህነትን ከእነርሱ በታች ያሉ ዲያቆናትን እና አናጉንስጢሶችንም እንዳይሾሙ ተከልክለዋል፡፡ በቅዱስ ወንጌል ጌታችና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በንጉሥና በአገልጋይ መስሎ ባስተማረው ትምህርት ባለ አንድ፣ ባለሁለትና ባለ አምስት ብሎ በምሳሌ ያስተማረውን ትምህርት መምህራን ሲተረጉሙት ባላንድ ዲያቆን ግብሩ ተልእኮ ብቻ ነውና፣ ባለሁለት ቄስ ግብሩ ማጥመቅና ማቁረብ ነውና ባለአምስት ጳጳስ ግብሩ ማጥመቅ፣ ቀድሶ ማቁረብ፣ ካህናትን ዲያቆናትን መሾም… ነውና ብለው ተርጉመውት እናገኛለን፡፡ ስለዚህ ክህነትን ለመሾም የግድና የግድ ጳጳስ መኖር አለበት፡፡ የሚሾመው ጳጳስ ከሆነ ሦስትና ከዚያ በላይ ጳጳሳት፣ ቄስና ዲያቆን ከሆነ ግን እንድም ቢሆን ጳጳስ መኖር አለበት፡፡ 

በዘመናችን እንዲሁ በዘፈቀደ ጳጳስ ሹመናል፤ ፓትርያሪክ ሹመናል እየተባለ የሚወራው ወሬና እንቅስቃሴ ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሥርዓትና ከሐዋርያት ቀኖና እጅግ የማይገናኝ እንዲሁም የሐዋርያትንና የሊቃውንትን ቀኖና የጣሰ እንደሆነ ልብ ሊባል ይገባዋል፡፡ በቀሳውስት ተሾሙ እንዳይባል የቀሳውትን ድርሻ ግልጽ በሆነ መልኩ ያስቀምጥልናል፡፡ በፍትሕ መንፈሳዊ “ለቄስ አንድ ሥልጣን ብቻ አለው፡፡ ይኸውም ያስተምር ዘንድ፣ ያጠምቅ ዘንድ፣ ይቀድስ ዘንድ፣ ይባርክ ዘንድ ነው፡፡… አንዱን ስንኳ አይሹም፣ አይሻረውም” (አንቀጽ ፮ ቁጥር ፮፻፲፭) በማለት መሾም መሻር የቀሳውስት ድርሻ እንዳልሆነ ያስረዳናል፡፡ ስለዚህ እነዚህ ሰዎች በማን ተሾሙ የሚለውን መሠረታዊ ጥያቄ መመለስ ይኖርባቸዋል፡፡

በራሳችን ተሾምን ካሉ ደግሞ በመጀመሪያ ደረጃ ራሳቸው መሾም አይችሉም በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ከላይ እየገለጽነው እንደመጣነው ሐዋርያዊ ቅብብሎሹን አቋርጧልና የክርስቶስ ክህነት ሊሆን አይችልም፡፡ ምክንያቱም የሐዲስ ኪዳን ክህነት እንደፖለቲካዊ ሥልጣን በሕዝበ ውሳኔ የሚሾሙት እንዳልሆነ መሠረቱ ክርስቶስ ሆኖ በሐዋርያት በኩል ዛሬ ላይ የደረሰ አማናዊ ክህነት መሆኑን በሰፊው ገልጸናል፡፡ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ እንዲሁ ተነሥተው ተሹሜያለሁ፣ ወይም ሾመናል የሚሉት እንዳልሆነ በሰፊው አይተናል፡፡ እንኳንስ እንዲህ ሊሉበት የራሱን ክብር ከመፈለግ አንጻር እኔ ሳልመጣ ለምን ሾማችሁ ብሎ ክህነቱን በያዘበት ጊዜ እንኳን ክህነቱን የያዘበትን አባት በምን መንገድ እንዳሸነፈው የሚያስታውሰን አንድ ታሪክ እንስታውስ፡፡  

አባ አትናስዮስ

ይህ ቅዱስ ከታናሽነቱ ጀምሮ መነኰሰ ባሕታዊም ሆኖ የሚያገለግል ቅን ትሑት በበጎ ሥራ ሁሉ ፍጹም ሆነ፡፡

ሊቀ ጳጳሳት አባ ሚካኤልም ካረፈ በኋላ ኤጲስ ቆጶሳት ሁሉም ተሰበሰቡ ይህንንም አባት ሊቀ ጵጵስና ይሾሙት ዘንድ መረጡት፡፡ ፈጥኖም እንዲመጣና ከእነርሱ ጋር ይህን አባት እንዲሾም ወደ ሀገረ ሰልቅ ሊቀ ጳጳስ ወደ አባ እልመፍርያን ላኩ፡፡ እርሱ ግን መምጣትን ዘገየ፡፡ እነርሱም ሃምሳ ቀኖች ያህል ጠብቀው አባ አትናስዮስን ሹመውት ወደየሀገረ ስብከታቸው ተመለሱ፡፡ ከዚህም በኋላ በላኩበት መሠረት ሊቀ ጳጳሳት አባ እልመፍርያን መጣ፡፡ ወደ ሶርያም ድንበር ሀገረ ዓምድ ደረሶ ከአንድ ጳጳስ ጋር ተገናኘ፡፡ ያም ጳጳስ እርሱ ከመምጣት በዘገየ ጊዜ አባ አትናስዮስን እንደሾሙት ነገረው በሰማም ጊዜ እጅግ ተቆጣ እንዲህም አለ በእኛና በእናንተ መካከል ያለውን ሕግ እንዲህ ትሽራላችሁን ይህንም ብሎ በቊርባንም ቢሆን ወይም በማዕጠንት የአባ አትናስዮስን ስም የሚጠራውን ሁሉ አውግዞ ወደ ሀገሩ ተመለሰ፡፡

አባ አትናስዮስም ይህን ነገር በሰማ ጊዜ እጅግ አዘነ ረዳቱንም ጠርቶ እንዲህ አለው ልቤ ትባርክህ ትመርቅህ ዘንድ ታዘዘልኝ ሕዝቡ የፈለጉኝ እንደሆነ በዋሻ ሱባዔ ውስጥ ነው በላቸው እኔ ወደአንድ ቦታ ሔጄ አንድ ዓመት ያህል እቆያለሁና አንተም ሊሆን በሚገባ ሥራ ሁሉ እዘዛቸው በእኔም ፈንታ እሰር ፍታ እረዳቱም እሺ አለው፡፡

ከዚህም በኋላ አባ አትናስዮስ የድሀ ልብስ ለብሶ በሥውር ወጣ በእግሩም ሔደ ወደ ሀገረ ሰልቅ ደረሰ፡፡ የሊቀ ጳጳስ አባ እልመፍርያንን ደጅ አንኳኳ በረኛውም ምን ትሻለህ አለው፡፡ ከሊቀ ጳጳሱ ቡራኬ እሻለሁ ብሎ መለሰለት ነግሮለትም አስገባው፡፡ አባ እልመፍርያን አንተ ከወዴት ነህ አለው፡፡ ከሶርያ ሀገር ነኝ የዕለት ሲሳይና ልብስ አጥቼ መጣሁ በጥላህም ሥር ሁኜ ላገለግል እሻለሁ ብሎ መለሰ፡፡

ሁለተኛም ቄስ ነህን ወይስ ዲያቆን አለው እርሱም አይደለሁም አለ፡፡ ሹሙንም ጠርቶ ከመነኮሳቱ ጋር እንዲአኖረው አዘዘው፡፡ አባ አትናስዮስም የሊቀ ጳጳሱን የቤት ውስጥ ሥራ የፈረሶችንና የበቅሎዎችን ፍግ  እስከሚጠርግ የሚሠራ ሆነ ይፈጫል ውኃ ይቀዳል እንጀራ ይጋግራል ወጥ ይሠራል ምንም ምን ሥራ አይቀረውም፡፡ እንዲሁም ለመነኰሳቱ ቤታቸውን ይጠርግላቸዋል ውኃንም ይቀዳላቸዋል እሳትንም ያነድላቸዋል እጅግም ስለወደዱት እንደ ሰማያዊ መልአክ አስመሰሉት፡፡

ከዚህ በኋላ አትናስዮስን ዲቁና ይሾመው ዘንድ ሊቀ ጳጳሱን መነኰሳቱ ማለዱት፤ በእሑድም ቀን አባ እልመፍርያን ወደ ቤተ ክርስቲያን ገብቶ ዲቁና ሊሾመው አባ አትናስዮስን ጠራው፡፡ እርሱም አባቴ ሆይ ተወኝ እኔ ድሀ ነኝና አለው ባልተወውም ጊዜ አባቴ ይቅርታ አድርግልኝ ይህስ ዲቁና አለኝ አለው፡፡ ሊቀ ጳጳሱም ከትዕግስሥቱና ከትሕትናው የተነሣ አደነቀ በዲቁናም እንዲአገለግል አዘዘው በዲቁና እያገለገለ ሰባት ወር ኖረ፡፡

ሊቀ ጳጳሱ አዋቂነቱን አይቶ ቅስና ሊሾመው ወደደ፡፡ በእሑድ ቀንም  ወደ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ጠርቶ መንፈስ ቅዱስ ቅስና ሊሾምህ መርጦሃል አለው፡፡ አባ አትናስዮስም ሰምቶ አለቀሰ እንዲተወውም ማለደው፡፡ ባልተወውም ጊዜ አባቴ ይቅር በለኝ እኔ ቄስ ነኝ አለ መነኰሳቱም ሁሉ አደነቁ በእርሱም ደስ አላቸው፡፡

አባ እልመፍርያንም አስተዋይነቱን የአንደበቱን ጣዕም የተደራረበ አገልግሎቱንም ተመልክቶ ጳጳሷ ለሞተባት ለአንዲት ሀገር ጵጵስና ሊሾመው ወደደ፡፡ ጳጳሳትንና ኤጲስ ቆጶሳትን ቀሳውስትንና ዲያቆናትንም በእሑድ ቀን ሰበሰባቸው አባ አትናስዮስንም አቅርበው እንዲህ አሉት ለእገሌ ሀገረ ስብከት ጳጳስ ልትሆን ዛሬ መንፈስ ቅዱስ ጠርቶሃል አሉት፡፡ እርሱም ሰምቶ አለቀሰ፡፡ እንዲተውትም አልቅሶ አማላቸው እንደማይተውትም በአወቀ ጊዜ እርሱ የአንጾክያ ሊቀ ጳጳሳት አትናስዮስ እንደሆነ ነገራቸው የአመጣጡንም ምሥጢር ገለጸላቸው፡፡

በዚያንም ጊዜ አባ እልመፍርያን ደነገጠ አክሊሉንም ከራሱ ላይ አውልቆ በምድር ላይ ወደቀ፡፡ ለረጅም ጊዜ እንደሞተ ሆነ በተነሣም ጊዜ እንዲህ ብሎ ጮኸ ወንድሞቼ የማደርገውን እስቲ ንገሩኝ ዛሬ እሳት ከሰማይ ወርዶ እንዳያቃጥለኝ ምድርም አፍዋን ከፍታ እንዳትውጠኝ እፈራለሁና ጌታየ የአንጾክያ ሊቀ ጳጳስ አትናስዮስ ውኃ እየቀዳ የፈረሶችና የበቅሎዎች ጉድፍ እየጠረገ በቤቴ ውስጥ እንደባርያ ሊያገለግል አግባብ ነውን ወዮልኝ ወዮልኝ፡፡

ጳጳሳቱ የተሰበሰቡት ሁሉ በሰሙ ጊዜ ከእግሩ በታች ወድቀው ሰገዱለት እጆቹንና እግሮቹንም ሳሙ ሊቀ ጳጳሱም ያማሩ የክህነት ልብሶችን ያለብሱት ዘንድ መስቀሎችንና አርዌ ብርቱን ያመጡ ዘንድ በመንበር ላይ ያስቀምጡት ዘንድ አዘዘ፡፡ 

ከዚህም በኋላ ጳጳሳቱ ከመንበሩ ጋር ተሸከሙት ሦስት ጊዜ አክዮስ አክዮስ አክዮስ እያሉ ይህም ይገባዋል ማለት ነው ቤተ ክርስቲያኑን አዙረው ወደ መቅደስ አስገቡት፡፡ ከዚህም በኋላ መቀደሻ ልብስ ለብሶ መሥዋዕቱን አክብሮ ቀድሶ አቆረባቸው እነርሱንም ሀገራቸውንም ባረከ ለዚያችም አገር ምንኛ መጠን የሌለው ደስታ ሆነ፡፡

በማግሥቱ አባ እልመፍርያን ተነሥቶ በቅሎ አስመጣ ለጒዞ የሚያሻውን ሁሉ አዘጋጀ አባ አትናስዮስንም በበቅሎ አስቀምጦ እርሱ በእግሩ ተከተለው ጳጳሳቱና ኤጲስ ቆጶሳቱ ሁሉም ከአባ እልመፍርያን ጋር አጅበው ወደ አንጾክያ ሀገር ወሰዱት፡፡ አባ አትናስዮስም አባ እልመፍርያንን አንተም በበቅሎ ላይ ተቀመጥና በአንድነት እንሒድ አለው፡፡ አባ እልመፍርያንም ጌታዬ ለእኔ አይገባኝም አንተ በእግርህ ወደ ሀገሬ እንደመጣህ እንዲሁ እኔም በእግሬ ወደ ሀገርህ አደርስሃለሁ አለው፡፡

የአንጾክያ ሀገር ጳጳሳትም የሊቀ ጳጳሳት አትናስዮስን መምጣት በሰሙ ጊዜ ከሕዝብ ሁሉ ጋር ሊቀበሉት ወጡ በታላቅም ክብር ተቀብለው ወደሹመቱ መንበር  አስገቡት፡፡ ለአባ እልመፍርያንም ሁለተኛ ወንበር አድርገው በክብር አስቀመጡት በዚያችም ቀን ፈጽሞ ደስ አላቸው ተሰናብተውትም ወደ ሀገራቸው በፍቅር በአንድነት ተመለሱ፡፡

ይህም አባት አትናስዮስ በጎ አኗኗርን ኖረ መንጋውንም በትክክል በእውነት ጠበቀ በጎ ጉዞውንም ፈጽሞ በሰላም አረፈ፡፡ (ምንጭ ስንክሳር ጥቅምት ዘጠኝ ቀን)  

ከዚህ ታሪክ የምንማረው ከሊቀ ጳጳሳት አባ አትናስዮስ ብቻ ሳይሆን ከሊቀ ጳጳሳት አባ እልመፍርያንም ነው፡፡ ምክንያቱም የአባ አትናስዮስን ትሕትና እና ትዕግሥት ባየ ጊዜ ራሱንም ዝቅ አድርጎ ላጠፋው ጥፋት ይቅርታ ጠይቋል፡፡ ለእኛም ከቅዱሳን አባቶች ከአባ አትናስዮስና እና ከአባ እልመፍርያን ረድኤትና በረከት የቅዱሳን አምላክ ያሳድርብን አሜን፡፡

ከላይ በቀረበው ታሪክ ግሩምና ድንቅ የሆነ የትሕትና ሥራ እንደምንማር ሁሉ በአንጻሩ ደግሞ ሥልጣነ ክህነቱ ሳይኖረው በድፍረት የክህነት አገልግሎት እያከናወነ የነበረውን ሰው ምን ዓይነት ቅጣት እንደደረሰበት እንመልከት፡፡

ብህንሳ በምትባል ሀገር ይኖር የነበረ አንድ ሰው

ብህንሳ በምትባል ሀገር ከአንድ ገዳም  የነበረ አበ ምኔት በጽኑዕ ታሞ ሳለ አባ ለትጹን ወደ እርሱ ሲሄድ መነኮሳቱ በዙሪያው  ሲያለቅሱ አገኛቸው፡፡ መነኮሳቱን አስወጥቶ ብቻውን ሲጠይቀው እርሱ የሠራውን ኃጢያት ማንም እንዳልሠራው ነገረው፡፡ ከሠራቸው ኃጢያቶች የተወሰኑት ክህነት ሳይሾም እንደተሸመ ሆኖ የቅስና አገልግሎቱን ማገልገል፣ የጠላቸውን ሰዎች ደግሞ በቊርባኑ ላይ መርዝ እያደረገ መግደል፣ከእናቱ ጋር ግንኙነት መፈጸም፣በጸነሰች ጊዜ መርዝ አጠጥቶ ጽንሡን መግደል ወዘተ. የሚሉት ነበሩ፡፡ አባ ለትጹን የዚህን አበምኔት ኃጢያት ከሰማ በኋላ እግዚአብሔር ይቅር እንዲለው አብዝቶ መጸለይ ጀመረ፤ እግዚአብሔር ግን ኃጢያቱ እጅግ የከፋ ነውና ይቅር እንደማይለው በመልአኩም እርሱም ተገልጾ ነገረው፡፡ አባ ለትጹን ግን እርሱን ይቅር የማትለው ከሆነ እኔንም አብረህ ወደሲኦል አውርደኝ ብሎ ለመነ፡፡ ስለ አባ ለትጹን ቅድስና እና ትጋት የሰውዬውን ነፍስ እንዳልነበረች አደረጋት (ስንክሳር ፣ሰኔ ፲፯)

መቼም ስርየተ ኃጢያት የማይደረግለት ኃጢያት ከተሠራ እጅግ ከባድ ነው፡፡ ግን ሰውየው የፈጸማቸው ኃጢያቶች ለመስማትም ለመናገርም የሚዘገንኑ ናቸው፡፡ ከነዚህ ውስጥ በዋናነት ለክህነት የነበረው ድፍረት፣ ሳይካን አገልግሎት መፈጸም፣ ሰው አድንበታለሁ፣ እኔም እድንበታለሁ ብሎ በትሕትና በንጽሕና ማገልገል ሲገባው በድፍረት በሥጋ ወደሙ ላይ መርዝ እያደረገ ሰው መግደል፡፡ ክህነት አለኝ ብሎ በክህነት እያገለገለ ከእናቱ ጋር ዝሙት መፈጸም፣ ካህን የታመሙትን የሚፈውስ፣ ለሞቱት የሚጸልይ፣ የሕዝብ አገልጋይ ነው እርሱ ግን ነፍሰ ገዳይ በእነዚህ ሁሉ አገልግሎቶች የፈጸማቸው ኃጢያቶች የተደራረቡና በርከት ያሉ ናቸው፡፡ ይህም ሁሉ ክህነትን እንዴት በድፍረት እንደ ቀለደበት የሚያመለክት ነው፡፡ የዚህ የድፍረት ውጤቱ ደግሞ እንዲህ ዓይነት መዓትን አስከተለበት፡፡ 

ዛሬም ሰዎች ክህነትን እጅግ ከመደፋፈራቸው የተነሣ ሳይሾሙ ተሾመናል የሚሉ፣ ሹመታቸው በቅዱስ ሲኖዶስ ተይዞባቸውም በድፍረት የክህነት አገልግሎት እየሰጡ ያሉ ሰዎችን እያስተዋልን የምንገኝበት ዘመን ነው፡፡ መቼም የኃጢያት መጀመሪያ ባይሆንም በመደፋፈራቸው ቅጣት እንደደረሰባቸው፣ ባለመደፋፈራቸውና በትሕትና መንገድ በመጓዛቸው ደግሞ የትሕትና በረከትን ያገኙ ሰዎችን ታሪክና ሕይወት እየተማርን ከስሕተቱም ሆነ ከመልካም ሥራቸው የማንማር ከሆነ በአመፃችን የበለጠ ልንቀጣበት እንደምንችል መረዳት ይኖርብናል፡፡

በክህነት አገልግሎት እያገለገሉ ያሉት ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ በቤተ ክርስቲያን ሥርዓት አለመሾማቸውን እና ክህነታቸው ተይዞባቸው በድፍረት እያገለገሉ እንደሆነ እያወቀ በእነርሱ የሚገለገለው ምእመንም ከተጠያቂነት እንደማይድን፣ የጥፋተኞች የግብር አበር መሆኑንና ቅጣቱ እንደሚያገኘው መረዳት ይኖርበታል፡፡ ክቡርና ታላቅ የሆነውን የእግዚአብሔር ጸጋ በምንችለው መጠን ተረድተነውና አክብረነው በአግባቡ ተገልግለንበት የመንግሥቱ መውረሻ እንዲያደርግልን እግዚአብሔር ይርዳን አሜን፡፡ ይቀጥላል…

 

Read 1799 times