Friday, 04 September 2020 00:00

ቶማስ ዘመርዓስ

Written by  ቀሲስ ዘክርስቶስ ጸጋዬ

Overview

በቶማስ  ስም የሚጠሩ በኦርቶዶክሳዊት  ቤተ ክርስቲያን የሚታወቁ በርካታ ቅዱሳን ቢኖሩም የዚህ  ዓምድ ዋና ትኩረቱ የክርስቶስ ምስክሩና ሐዋርያው የሆነ የመርዓስ ኤጲስ ቆጶስ ተጋዳይ ቶማስ ላይ አድርጎ ዘመናችንን ይፈትሻል፡፡ የቅዱስ ቶማስ ዘመርዓስ ትሩፋትና ገድሉን ሰው ተናግሮ ሊፈጽመው አይቻልም እርሱ አስቀድሞ ከልጅነቱ ቅዱሳት መጻሕፍትን የተማረ፣ ገና በወጣትነቱ መንኖ  ገዳም የኖረ፣ በጾም፣ በጸሎት፣ በሰጊድ፣ ቀን እና ሌሊትም በመትጋት ለድኆችና ለምስኪኖችም በመራራት ተጠምዶ የኖረ ነበር፡፡ ቅዱስ ቶማስ "መርዓስ" በምትባል አገር የወጣ የንጋት ኮከብ፣ ጻድቅ፣ ገዳማዊ፣ ጳጳስ፣ ሐዋርያ፣ ሰማዕትና ሊቅ ነው፡፡ የእርሱ ሕይወት ኦርቶዶክሳዊ የክርስትና ሕይወትና የጵጵስና የሹመት ሕይወት ምን እንደ ሆነ በትክክል የሚያሳይ ነው፡፡ መርዓስ በምትባል ሀገር ጳጳስ ሆኖ ተሹሞ በእረኝነት ያገለገል ዘንድ የክብር ባለቤት ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መረጠው መንጋውንም እንደ ሐዋርያት ጠበቀ፡፡ በሹመት ዘመኑ በሰላሙም በመከራውም  ዘመን ‹‹ መኑ ያኀድገነ ፍቅሮ ለክርስቶስ ፤ ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል?›› (ሮሜ ፰፥፴፭-፴፯) እንዳለ ቅዱስ ጳውሎስ ለክርስቶስ ያለውን ፍቅር መከራ፣ ጭንቀት፣ ስደት፣ ራብ፣ ራቁትነት፣ ፍርሃት፣ ሰይፍ ሳይለየው ለአርባ ዓመታት ስለ ክርስቶስ ቀኑን ሁሉ እንደሚታረድ በግ ሆኖ እግዚአብሔርን በመንፈስ ቅዱስ ኃይል አገለገለ፡፡ 

 

ቅዱስ ቶማስ ዘመርዓስ በሐዋርያዊ አገልግሎቱ ብዙ አሕዛብን ወደ ክርስትና የመለሰ እና በዘመነ ሰማዕታት ብዙ መከራን የተቀበለ አባት ነው፡፡ ጨካኞቹ ቅዱሱን ለ፳፪ ዓመታት አካሉን እየቆራረጡ ለጣዖታቸው ያጥኑ ስለ ነበር ፪ እግሮቹ፣ ፪ እጆቹ፣ ፪ ጀሮዎቹ፣ ፪ አፍንጫዎቹ እና ፪ ዐይኖቹ አልነበሩም:: ነገር ግን እንዲህም ሆኖ አልሞተም እግዚአብሔርንም ማገልግለ አልተወም ነበር፡፡ በመጨረሻም በዘመነ መናፍቃን አርዮስን ካወገዙት ፫፻፲፰ቱ ሊቃውንት አንዱ ለመሆን የበቃ ነበር ፡፡

 የስንክሳር አርኬ ደራሲው አርከ ሥሉስም ስለ ቶማስ ዘመርዓስ ለሌሎቹ ቅዱሳን እንደጻፈላቸው ሁሉ ‹‹ሰላም ለቶማስ  ዘአባላቲሁ ግሙድ፣ እስከ አስተርእየ ኅብሩ አምሳለ ውዑይ ጕንድ፣ ለዝ መዋዒ በነጽሮ ገድሉ ፍድፉድ፣ ወሰላም ለእለ ምስሌሁ ሙቁሐነ እድ፣ አእላፈ ክርስቶስ ተስዓቱ እልፍ በፍቅድ፤ ሰውነቱ እንደደረቀ ግንድ እስኪመስል ደድረስ አካላቱ ለተቆረጡ ለቶማስ ሰላምታ ይገባል። የዚህን የአሸናፊ ቶማስን የበዛ ገድሉን በማየት በፈቃድ ከእርሱ ጋር ለታሰሩትና የክርስቶስ ወገኖች ለሆኑ ለዘጠኝ እልፍም ሰላምታ ይገባል።›› በማለት አርኬ ደርሶለታል፡፡ 

ምንም እንኳን በአቡነ ተክለ ሃይማኖትና በቶማስ ዘመርዓስ የዕረፍት ቀን  በመካከላቸው የ ፩ሺህ ዓመት ልዩነት ቢኖርም የአቡነ ተክለይማኖት መልክእ ደራሲው ዮሐንስ ከማ ሁለቱ ቅዱሳንን በማነጻጸር ‹‹ሰላም ለጸአተ ነፍስከ  በስብሐተ አእላፍ እንግልጋ፣ ለዓለመ ዛቲ እም ግብርናቲሃ ወጹጋ፣ ተክለሃይማኖት ቶማስ ለመርአስ ዐቃቤ ሕጋ ለእመ ገብሩ ተዝካረከ እለ ሀለዉ በሥጋ ፣ ሀቦሙ እግዚእየ ሞገሰ ወጸጋ፤ የመርዓስ የሕጓ ጠባቂ ቶማስ ተክለ ሃይማኖት ሆይ ከዚች ዓለም ሥራና ድካም  በአእላፍ መላእክት ምስጋ ለነፍስህ መውጣት ሰላምታ ይገባል፡፡ በሥጋ ሳሉ ተዝካርህን ያደረጉትን ጌታየ ሆይ ሞገስንና ጸጋን ስጣቸው።›› በማለት ጽፏል፡፡

ከሃዲው ዲዮቅልጥያኖስ በነገሠ ጊዜ ክርስቲያኖቹን ሲያሰቃዩ በነበረበት ወቅት ከንጉሱ መኳንንት አንዱ ወደ መርዓስ ሄዶ ቶማስ ዘመርዓስን በጭፍሮቹ አስያዙት፡፡ እንደያዙት ደብድበው በምድር ላይ እየጎተቱት ደሙ እየፈሰሰ ወሰዱት፡፡

መኰንኑ ቅዱስ ቶማስን  ‹‹ለአማልክት ስገድ›› አለው፡፡ ቶማስ ዘመርዓስም ‹‹እኔ ከሕያው እግዚአብሔር ልጅ ከጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ በቀር ለረከሱ ጣዖታት አልሰግድም ለረከሱ ጣዖታት የሚሰግድ ሁሉ የተረገመ ነውና ከእግዚአብሔር በቀር የሚሰግዱለት አምላክ የለም ›› አለው፡፡ 

መኰንኑም እጅግ የብዙ ጽኑ ስቃዮችን አሰቃየው፡፡ የነዳጅ ድፍድፍ አፍልተው በሰውነቱ ላይ እንዲሁም በአፍና በአፍንጫው ውስጥ ጨመሩበት እስከ ብዙ ዘመናት ኖረ፡፡ እነዚህ ከሀድያን ልባቸው እንደ ደንጊያ የጸና ስለነበረ ቶሎ ብለው እንዲሞቱ ሳይሆን በሥቃይ ሆነው እንዲቆዩ በማድረግና ሌሎች ብዙዎች ሰዎችን ያስፈሩአቸው ዘንድ የክብር ባለቤት ክርስቶስን ይክዱ ዘንድ የሥቃዩን ዘመን አስረዘሙት፡፡

ቶማስ ዘመርዓስ ግን በጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ኃይል የጸና ነውና ማሰቃየቱን ከሃዲያን በደከማቸው ጊዜ ስለስሕተታቸው ይዘልፋቸው ስለ ነበር ወደ ጨለማ  ቦታ ጣሉት በዚያም ለ፳፪ ዓመታት በጨለማ ውስጥ አስረው አሠቃዩት፡፡ ከሀድያኑም  በየዓመቱ ወደ እስር ቤቱ እየገቡ አንድ አካሉን ይቆርጣሉ፡፡

‹‹መተሩ አንፎ፣ ወከናፍሪሁ፣ ወእዘኒሁ፣ ወእደዊሁ፣ ወእገሪሁ፣ ወመሰሎሙ ለመርዓቱ ዘአዕረፈ ወነበሩ እንዘ ይገብሩ ተዝካሮ ለለዓመት፤ አፍንጫውን ከንፈሮቹን ጆሮዎቹን እጆቹንና እግሮቹን ቆረጡ መንጋዎቹም ያረፈ መስሏቸው በየዓመቱ መታሰቢያውን ሲያድርጉ ኖሩ፡፡›› 

ከሃዲያኑ እጅና እግሩን በየተራ የቆራረጡትን የሰውነት አካላቱን አፍንጫውን፣ ከንፈሮቹን፣ ጆሮዎቹን ሁሉ በየተራ እየቆረጡ ለ ፳፪ ዓመታት ጣዖታቸውን ሲያጥኑበት ኖረዋል፡፡

አንዲት ደግ ክርስቲያናዊት ሴት ቶማስ ዘመርዓስ የተጣለበትን ጉድጓድ አይታ ስለነበረ በድብቅ በሌሊት ተሰውራ እየሄደች ትመግበው ነበር፡፡ ደገኛውና ጻድቁ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ እስከ ነገሠና የቀናች የክርስቶስን ኦርቶዶክሳዊት ሃይማኖትን ክብር እስከ ገለጠበት ድረስ ቶማስ ዘመርዓስ ሲሰቃይ ቆየ፡፡ 

ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ በጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመታመኑ የታሠሩ እሥረኞችን ሁሉ በሀገሮች ሁሉ በወህኒ ቤት ያሉትን ይፈቷቸው ዘንድ አዋጅ አውጥቶ ሲያዝ ክርስቲያናዊቷ ሴት ሄዳ ስለ ቅዱስ ቶማስ ስለ እርሱ የሆነበትን ሃያ ሁለት ዓመት ተጥሎ እንደኖረ ለካህናቱ ነገረቻቸው በውስጡ ወደ ሚኖርበትም ቦታ መራቻቸው፡፡

ካህናቱም አንሥተው ተሸከሙት እየዘመሩና እያመሰገኑ ወደ ቤተ ክርስቲያን አደረሱት፤ በቤተ መቅደሱም ፊት ለፊት በወንበሩ ላይ አስቀመጡት፤ ምእመናንም ሁሉ ወደእርሱ እየመጡ ከእርሱ ይባረኩና የተቆረጡ አካላቱን ይሳለሙ ነበር፡፡

ቶማስ ዘመርዓስ ወደ ሠለስቱ ምዕት ጉባኤ ሲሄድ ዞሮ እንዳያስተምር እግሩን፣ ጽፎ መልእክታት እንዳይልክ እጁን፣ በሰማእትነት በሃያ ሁለት ዓመታቱ ሰማእትነት  አሰጥቶአቸው ስለነበር፤ ደቀ መዛሙርቱ በቅርጫት ውስጥ አድርገው በአህያ ጭነው ወደ ጉባኤ ኒቂያ ይዘውት ሄደዋል፡፡

በመንገድም ሳሉ ዐላውያን አግኝተዋቸው ጥቁርና ነጭ አህዮቻቸውን  ሌሊት ራስ ራሳቸውን ቆርጠው ጣሉባቸው፡፡ በማግስቱም ቶማስ ዘመርዓስም ራሳቸውን የተቆረጡትን አህዮች አምጡልኝ ብሎ የጥቁሩን አህያ ራስ ከነጩ፣ የነጩን አህያ ራስ ለጥቁሩ ገጥሞ ቢባርካቸው ሁሉም አህዮች ከሞት ተነስተዋል፡፡ የአህዮቻቸውም መልክ እጅግ ያማሩ ሆኑ፡፡

ንገሥ ቈስጠንጢኖስ የከበሩ የሦስት መቶ ዐሥራ ስምንት ኤጲስቆጶሳቱን በኒቂያ ሀገር እንዲሰበሰቡ ሲያደርግ ይህ የከበረ ቶማስ ዘመርዓስ ከሊቃውንቱ አንዱ  ነበር፡፡ ከጉባኤው ሲደርሱ ንጉሡ ቈስጠንጢኖስ ወደ ጉባኤው ገብቶ ለቅዱሳን ሊቃውንቱ ሰላምታ ሰጣቸውና ከሊቃውንቱ ቡራኬ ተቀበለ ፡፡  የዚህን ቅዱስ የቶማስ ዘመርዓስን ተጋድሎውን በነገሩት ጊዜ ወደ እርሱ ቀርቦ ሰገደለት፤ አካላቱም ከተቈራረጡበት ላይ ተሳለመው። ከዚያም አዝኖና አጅግም ተደንቆ አድንቆ አካላቱን ዳሠሠው ፊቱንና ዓይኖቹን አሻሸው ጽድቁንም ዐውቆ ‹‹ አባቴ በረከትህ ትድረሰኝ ›› በማለት ተባርኳል፡፡

ትምህርተ ሃይማኖትን፣ ሕገ ቤተ ክርስቲያንን ከሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ጋራ ካጸና በኋላ ወደ ሀገረ መንበረ ሢመቱ ተመልሶ ካህናቱንና መንጋዎቹን ሁሉ ሰብስቦ ጸሎተ ሃይማኖትን ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን አነበበላቸው ይኅን ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንም አጽንተው እንዲጠብቁት  አዘዛቸው፡፡ ጥቂት ዘመናትም ከኖረ በኋላ ቅዱስ ቶማስ ጵጵስና በተሾመ በ፵ ዓመቱ ነሐሴ ፳፬ አርፏል፡፡ የጻድቃንን፣ የሰማዕታትን፣ የሐዋርያትንና የሊቃውንትን አክሊልም ተቀብሏል፡፡ 

(ምንጭ ስንክሳር ዘወርኃ ነሐሴ)

      አምላከ ቅዱስ ቶማስ ዘመርአስ በረድኤቱ አይለየን!!!  

 

                                                                                                                                                                                        

 

Read 1666 times