Wednesday, 28 April 2021 00:00

አቡነ ዮሐንስ ዘውራ ኢየሱስ

Written by  ቀሲስ ዐብይ ሙሉቀን

Overview

ትውልድ ጻድቁ አቡነ ዮሐንስ የአባታቸው ስም የማነ ብርሃን የእናታቸው ስም ሐመረ ወርቅ ይባላል። የተወለዱበት ቦታ አክሱም ጽዮን ነው። እናቱን ሐመረ ወርቅን ያለ ፈቃዷ ለአንድ ሀገረ ገዥ ሊያጋቧት ሲሉ የአባታችን የጻድቁን የአቡነ ተክለ ሃይማኖትን እና የሌሎችን ቅዱሳን መቃብር ሳልሳለም አላገባም። ፍቀዱልኝና ተሳልሜ እመጣለሁ አለቻቸው። ይህን ጊዜም ከብዙ ሠራዊትና ከብዙ ገንዘብ ጋር ሰደዷት።  ቅድስት ሐመረ ወርቅ ደብረ ሊባኖስ የእመቤታችን የሥጋዋ ፍልሰት በሚከበርባት በነሐሴ ፲፮ ቀን ደረሰች። በዚያችም ሌሊት አባታችን ተክለ ሃይማኖትን በሕልሟ አየችው። የብርሃን ምሰሶም ከፊቷ አየች። ጻድቁም ይህ የብርሃን ምሰሶ ለአንቺና ለባለቤትሽ ለየማነ ብርሃን ነው አላት። ይህንም በገዳሙ ሱባኤ የገቡ መነኰሳት ለሰባት ተከታታይ ቀናት ያህል አዩ። ያዩትንም ለገዳሙ አበ ምኔት ለአባ ዳንኤል ነገሩት። እርሱም እኔም እንደናንተ አይቻለሁ አላቸው። የአባቱ የየማነ ብርሃን ቤተሰቦችም እንዲሁ ደጋግና እግዚአብሔርን የሚፈሩ ለተራበ የሚያበሉ፣ ለተጠማ የሚያጠጡ ነበሩ፣ በመጋቢት ሃያ ሰባት ቀን እመቤታችን ተገለጸችላቸውና ከልጃችሁ ከየማነ ብርሃን የብዙዎች አባት የሚሆን ደግ ልጅ ታገኛላችሁ ከጻድቁ ከተክለ ሃይማኖት በቀር የሚበልጠው የለም እናቱ ሐመረ ወርቅም በደብረ ሊባኖስ ገዳም ትገኛለች  አሏቸው። ስለዚህ የየማነ ብርሃን እናትና አባት ከልጃቸው ከየማነ ብርሃን ጋር በምልክት ይፈልጓት ዘንድ ወደ ደብረ ሊባኖስ ሄዱ።

 

የገዳሙ አበ ምኔት አባ ዳንኤልም ለነሐሴ ሃያ አራት ለጻድቁ ለአቡነ ተክለ ሃይማኖት በዓል ከአራቱም ማዕዘን የተሰበሰቡትን ስማችሁን ጽፋችሁ አምጡ አሏቸው። የሁሉንም ስም ሰብስበው ከጸለዩበት በኋላ የማነ ብርሃን እና ሐመረ ወርቅ በተክሊል እንዲጋቡ ነገሯቸው። ሐመረ ወርቅም ፈቃዳችሁ ፈቃዴ ነው ነገር ግን እናትና አባቴ ለማያውቁት ሰው ሚስት እሆን ዘንድ እናትና አባቴ አልፈቀዱልኝም አለቻቸው። አባ ዳንኤልና መነኰሳቱም ሐመረ ወርቅ ሆይ ክርስቶስ መረጠሽ፤ እመቤታችን ድንግል ማርያም ለየማነ ብርሃን ሚስት ትሆኚ ዘንድ አጨችሽ፤ እሺ በዪ አሏት። በዚህ ጊዜ እርሷም ፈቃደኛ ሆነች። በዚህም ዕለት በሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን ተጋቡ። ሥርዐቱ ከተፈጸመ በኋላ በጾምና በጸሎት ተወስነው ለሁለት ሳምንት በደብረ ሊባኖስ ተቀመጡ።

ከዚህ በኋላ ወደ ትውልድ ቦታቸው ወደ አክሱም ተመለሱ። በአክሱምም እንግዳ እየተቀበሉ፣ ለተራበ እያበሉ በመልካም ምግባር ሲኖሩ ነሐሴ ሃያ አራት ጻድቁ አባት ዮሐንስ ተፀነሰ፤ ግንቦት ሃያ አራት ቀንም ተወለደ፤ ስሙንም ዮሐንስ አሉት ትርጓሜውም ፍጹም ደስታ ማለት ነው።    

 ዕድገትና ትምህርት

እናት አባቱ ቅዱሳት መጻሕፍትን፣ የቤተ መንግሥትንም ሥርዐት እያስተማሩ አሳደጉት። ዮሐንስም ለአባቱ የማነ ብርሃንና ለእናቱ ሐመረ ወርቅ በነግህም በሠርክም ይታዘዝ ነበር። በተወለደ በሰባት ዓመቱም ይህን ኃላፊውን ዓለም ናቀ። ኅልፈት ውላጤ ከሚስማማው ዓለም ኅልፈት ውላጤ የማይስማማውን ሰማያዊውን ዓለም መረጠ። የተክለ ሃይማኖት ሁለተኛ ልጅ ወደሆነው ጸጋ ኢየሱስ ሄደ። በዚያም ከጸጋ ኢየሱስ ጋር ለአምስት ዓመት ያህል ቆየ። ዐሥራ ሁለት ዓመት ሲሞላውም የምንኵስናን ሥርዐት በጸጋ ኢየሱስ ተቀበለ።

የአገልግሎት ሁኔታ

ገና በዐሥራ ሁለት ዓመቱ የመነኰሰው ተጋዳይ አባት በዋልድባ ገዳም ገባ። በዚህም መነኰሳቱ በመዓልትም በሌሊትም ያገለግለው ዘንድ በሥጋው ቁስል ሁለንተናው የተላና የተበላሸ በጸባዩም እጅግ የከፋ ሰው ርዳው ብለው ሰጡት። ያም መነኵሴ ይረግመዋል፤ የሚማታበት ጊዜም ነበር። ጻድቁ ዮሐንስ ግን ፈጽሞ ይደሰት ነበር። ሥራው የከፋ የዚያን መነኵሴ ፈቃድ በገዳሙ የሚኖሩትን የመነኰሳትንም ፈቃድ እጅግ ደስ እያለው ያገለግል ነበር። በየዕለቱ ሰባት መሥፈሪያ ይፈጭ ነበር። እንጨት ለቅሞ ሰባት ጎልማሶች የሚያመጡትን ያህል ያመጣ ነበር። በምድረ በዳም ቋርፍ ይምስ ነበር። ከሰንበት ዕለት በቀር እህል ውኃ አይቀምስም ነበር።

እንዲህ እያደረገ ሰባት ዓመት ኖረ፤ የአርድእትንም በረከት ተቀበለ። የጻድቁ ድንቅ ሥራ ከተገለጠ በኋላ በእግዚአብሔር መልካም ፈቃድ ወደ ኢየሩሳሌም ሄደ። ከጌታ መቃብርም ተሳለመ። ከዚህ በኋላ ታቦተ ኢየሱስን፣ ታቦተ ኪዳነ ምሕረትንና ታቦተ ጽዮንን እየጠበቀ ሁለት መቶ ዓመት በዚያ የኖረ ሁለተኛው  እንጦንስን አገኘው። በእመቤታችን ፈቃድ ለእርሱ እንድተሰጠው የተነገረው ይህ አባትም ሦስቱን ታቦቶች ሰጠው። አባ ዮሐንስም ይጠብቀው ከነበረው አባት የተቀበላቸውን ሦስት ታቦታት ተቀብሎ ወደ ኢትዮጵያ ተመለሰ። 

አባ ዮሐንስ ከኢየሩሳሌም ያመጣቸውን ታቦታት በእግዚአብሔር መልካም ፈቃድ እየተመራ ታቦተ ኢየሱስን በሜጫ ወረዳ አንድ ውሮ የሚባል ባላባት ተቀብሎ ቦታ ሰስለሰጠው በዚያ ተከለ። የገዳሙንም ስም በባላባቱ ስም ውራ ኢየሱስ ብሎ ሰየመው። ገዳሙንም አከበረ፣ ከፍ ከፍም አደረገ። ከዘጠኝ ዓመት በኋላ መልአኩ ቅዱስ ዑራኤል እየመራው ወደ ዘጌ መጣ፤ በእርሷም  ታቦተ ኪዳነ ምሕረትን ተከለ። የገዳሙንም ስም ዑራ ኪዳነ ምሕረት ብሎ ሰየመ። ከዚያም በኋላ ታቦተ ጽዮንን በአዴት አካባቢ ተከለ። ከንጉሡ ከኢያሱ ጋር እየተወያየ የገዳማቱን ርስት ጉልት በማስፋፋት በጎ አገልግሎት ሲያገለግል ኖረ። 

ተአምር

ጻድቁ አባ ዮሐንስ በርካታ ተአምራትን አድርጓል ከብዙዎችም መካከል 

፩. በዋልድባ ገዳም ሳለ በአንድ ወቅት ከባድ ሕመም ተነሥቶ አንድ የገዳሙ መነኵሴ ሞተ፣ ሰው ሁሉ ፈርቶ ሳለ አበ ምኔቱ ብቻውን ሊከፍን ሲሄድ እርሱም አብሮ ሄደ። አበ ምኔቱ እንዳይሄድ ቢከለክለው አባታችን ዮሐንስም በለመለሙ ከንፈሮቹ ስለት በሆነው አንደበቱ አንተ ስትሞት እኔ አልቀርም አለ። ያን ጊዜም ወደ ሞተው ቀረበ፤ አቀፈውም ደም የተነከረ ልብሱንም ያዘ፤ ያን ጊዜም የሞተውን እንደ ጴጥሮስ፣ እንደ ጳውሎስና እንደ ሐዋርያት በጥላው አስነሣው። ያ ሙቶ የነበረውም ከሞትሁ ዛሬ ሦስተኛ ቀኔ ነው አይቶ የጎበኘኝ አልነበረም፤ ዛሬ ግን የእግዚአብሔር ሰው የገዳማቱ ኮከብ የቅድስት ውራ ገዳም መነኰሳት አባት የማይጠልቅ ፀሐይ፣ የማይጠፋ ፋና፣ ወደ ሰባቱ ሰማዮች ወጥቶ ዐርጎ ከሃያ አራቱ ካህናተ ሰማይ ጋር የሥላሴን ዙፋን የሚያጥን አባታችን ዮሐንስ በአቀፈኝ ጊዜ ነፍሴ ከሥጋየ ፈጽማ ተዋሐደች በማለት በወቅቱ የተፈጸመውን ድንቅ ተአምርና ወደፊት አባ ዮሐንስ የውራ ገዳም አባት እንደሚሆንም  ትንቢት ተናገረ። 

፪. በንጉሥ ኢያሱ ዘመን በንጉሡ ጠላት ተነሥቶበት የንጉሡን የሠራዊት አለቃ አገኘውና የንጉሡን ጠላት ድል ታደርጋለህ፤ ነገር ግን ንጉሡን ለኪዳነ ምሕረት ርስት እንዲሰጠኝ ጠይቅልኝ አለው። እርሱም እሺ ብሎ ከሄደ በኋላ ጠላቶቹን ድል ነሥቶ ሲመለስ ረሳው በመንገድ ላይ ግን ፈረሱ ከወንዝ ዳር ተኝቶ ከሦስት ሰዓት በላይ እንቢ አለ። ከወንዙ ዳር እያሉ ውኃ እንዲያጠጡት አገልጋዮቹን ጠየቃቸው በዚህ ጊዜ አባ ዮሐንስ ለምልክት ትሁንህ ብሎ በሰጠው ቅል አመጡለት፤ ቅሏን ሲመለከት ትዝ አለው በዚህ ጊዜ መልእክቱን ሊያደርስ ወደ ንጉሡ ሲመለስ ፈረሱ ተነሣለት።   

፫. አንድ ሰው ጎሽ ሊገድል ፈልጎ ወደ ጫካ ሲሄድ አንድ ጎሽ አገኘችው። እርሱ ከማየቱ በፊት ቀድማ አየችውና ከፈረሱ ላይ ጣለችው። በዚህ ጊዜ በዮሐንስ አምላክ አምየሻለሁ እንዳትገድዪኝ ብሎ ተማጸናት። እርሷም ተወችው። እርሷ ከተወችው በኋላ ግን ሊገድላት ፈለገ፤ እርሷም እንደ እርሱ ሁሉ በዮሐንስ አምላክ ተማጽኘሃለሁ አለችው። አልሰማትም ወግቶም ገደላት። ምላሷን በክንዱ አስቀምጦ፣ ቀንዷን ይዞ ወደ አባ ዮሐንስ ሄደ። ቀንዷን ለአባ ዮሐንስ ሰጥቶ ሊባረክ ሲል ምላሷ ከክንዱ ላይ ወደቀችና የአባ ዮሐንስ ጥላ አረፈባት። በዚህ ጊዜ በሰው አንደበት ድምፅዋን አሰምታ ተናገረች። በሕያው እግዚአብሔር እማጸንሃለሁ፤ ነቢዩ ዳዊት “በጽድቅ ገሥጸኝ፤ በምሕረትም ዝለፈኝ፤ የኃጢአተኛ  ዘይትን ራሴን  አልቀባም” (መዝ.፻፵፥፭) እንዳለ በግፍ የገደለኝን የዚህን ዐመፀኛ ሰው እጅ መንሻ አትቀበል አለችው። 

አባታችንም ሰውየውን ይህ ነገር እውነት ነውን ብሎ ጠየቀው። ገዳዩም እውነት ነው በማለት መለሰ። በዚህ ጊዜ አንተ በእውነት ከእርሷ ታንሣለህን? ከእርሷ ብሰህ እንዴት ትበድላለህ? አለው ሰውየውም ጥፋቱን አመነ። ከዚህ በኋላ በመስቀል አማተበ፣ ሥጋዋንም ተቆራርጦ ከወደቀበት  ቦታ ሰብስቦ በስመ እግዚአብሔር አስነሣት፣ 

ጻድቁ አባ ዮሐንስ ሌሎች ድንቅ ድንቅ ተአምራትንም አድርጓል። ከእነዚህም መካከል ደዌያቸው ልዩ ልዩ የሆነባቸው ብዙ በሽተኞች ወደ እርሱ እየተሰበሰቡ ከበሽታቸውና ከደዌያቸው ይፈውሳቸው ነበር። 

ቃል ኪዳን

አገልግሎቱን በሰላም ከፈጸመ በኋላ ከዚህ ዓለም የሚለይበት ጊዜ ሲደርስ ሕይወቱን ሁሉ ከአገለገለውና ቸርነት የባሕርዩ ከሆነው ከእግዚአብሔር ጽኑዕ ቃል ኪዳን ተቀብሏል። ቃል ኪዳኑም ዝክርህን የዘከረ፣ በዓልህን ያከበረ፤ ገድልህን የሰማ፣ ያሰማ፣ መልክህን ጸሎት አድርጎ የደገመ፣ እባብ አይነድፈውም፤ መብረቅ አይገድለውም፤  በነፍሱ እስከ ዐሥራ አምስት ትውልድ ድረስ ይማራል። ከምትቀበርባት ውራ ኢየሱስ መብረቅ አይወርድም። የሚል ነው። 

በዓለ ዕረፍት

አባ ዮሐንስ መልካም የሆነውን ተጋድሎ ሲፈጽም ከኖረ በኋላ በሰማንያ ዓመቱ ጥቅምት ሃያ ሁለት ቀን አርፎ በውራ ኢየሱስ ተቀብሯል። የጻድቁ በረከት ይደርብን አሜን።

(ምንጭ ገድለ አቡነ ዮሐንስ ዘውራ ኢየሱስ)

 

Read 907 times