Saturday, 27 February 2021 00:00

የጮቢ መካነ ሕይወት በዓታ ለማርያም የአንድነት ገዳም ክፍል ሁለት

Written by  በዲ/ን ደረጀ ጋረደው

Overview

፮. በገዳሙ የተከናወኑ ገቢረ ተአምራት  በገዳሙ ለረጅም ጊዜ ያስቆጠረ የአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ  ጠበል የሚገኝበት ሲሆን፤ በተጨማሪ ከቅርብ ዓመታት በፊት የበዓታ ለማርያም ጠበል ፈልቋል። አሁን ሁለቱም ጠበሎች በአንድ ላይ የሚፈሱ ሲሆን፤ ከጥንት ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁንም ድረስ ብዙ ድውያን ተፈውሰዋል እየተፈወሱም ይገኛሉ   ጠበሉ ፈዋሽ እንደመሆኑ መጠን አላግባብ ለሚጠቀሙበት ሰዎችም ደም በመሆን ተአምራቱን ገልጿል።  በጥንት ጊዜ ጫካው የሚጠበቀው በዳልጋ አንበሳ እንደ ነበር አባቶች ያስረዳሉ። ፯. በገዳሙ ተሠርተው አገልግሎት እየሰጡ ያሉ የልማት ውጤቶች  ፯.፩.የእናቶች እና አሳዳጊ የሌላቸው ሕፃናት ማደሪያ አንድ እናት ፭ እጓለ መውታ (የሙት ልጅ) ሕፃናትን በመንከባከብ እንዲያሳድጉ በማሰብ ፲፮ ክፍሎች ያሉት ባለ አንድ ፎቅ (G+1) ዘመናዊ ሕንጻ ተገንብቶ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጁ ሲሆን የተለያዩ ቁሳቁሶች፣ የገላ መታጠቢያ እና መጸዳጃ ቤቶችም የተሟሉለት ነው። እጓለ ማውታ (የሙት ልጅ) ሕፃናት ገብተው አገልግሎቱ መሰጠት ባይጀምርም ሕንጻው መናንያን እናቶችን በጊዜያዊ በዓትነት እያገለገለ ይገኛል።

 

፯.፪. ዘመናዊ የእህል ማከማቻ ጎተራ

የገዳሙ ዋና የገቢ ምንጭ እርሻ ነው። ከእርሻው የሚሰበሰበውን ምርት በጥንቃቄ ለማስቀመጥ ባለ አንድ ፎቅ (G+1) ዘመናዊ ሕንጻ ጎተራ ተገንብቷል። ጎተራው ፰ ክፍሎች ሲኖሩት እህሉ በላይኛው ፎቅ ይጨመራል። ለአገልግሎት ሲፈለግ በታችኛው ወለል በእያንዳንዱ የእህል ዘር ማስቀመጫ ቀዳዳ ክዳን በመክፈት በቀላሉ መውሰድ ይቻላል። ገዳሙ የተለያዩ የእህል አይነቶችን ማለትም ስንዴ፣ ጤፍ፣ ባቄላ፣ አተር፣ ገብስ፣ ሽንብራ፣ እና በቆሎ የሚያመርት ሲሆን ፲፬ ጥማድ የእርሻ በሬዎችም አሉት። በተጨማሪም ሰብሉን ከአውድማ ወደ ጎተራ የሚያመላልስ ፩ ትራክተር አለው።

፯.፫. የውኃ ማጠራቀሚያ ገንዳ እና ቤተ መጻሕፍት

የገዳሙ ዋና ችግር የመጠጥ ውኃ ነው። ችግሩ ከፍተኛ በመሆኑ ውኃ ይቆነናል። ችግሩን ለማቅለል የተወሰደው እርምጃ ከጠበሉ ጎን የሚመነጭ ውኃ በማጠራቀም አገልግሎት ላይ እንዲውል ይደረጋል። ይህንንም የሚያግዝ ፴፼ (ሦስት መቶ ሺህ) ሊትር የሚይዝ የውኃ ማጠራቀሚያ ገንዳ በግንብ መሬት ላይ ተገንብቶ ሥራ ጀምሯል። ከውኃ ማጠራቀሚያው ላይ የተገነባው የላይኛው ቤት ፶ ሰዎችን በአንድ ጊዜ የሚያስተናግድ ዘመናዊ ቤተ መጻሕፍት እና ለገድል ማንበቢያ እንዲሆን ታስቦ የተሠራ ነው። ቤተ መጻሕፍቱም መናንያን፣ የአብነት ተማሪዎች ጠበልተኞች እና የዕረፍት ጊዜያቸውን በገዳም የሚያሳልፉ ምእመናን፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ኦርቶዶክሳውያን ተማሪዎች የሚገለገሉበት ይሆናል።  

፯.፬. ለሕሙማን አገልግሎት የሚሰጥ ጠበል

ቀደም ሲል ከተለያዩ ቦታ የሚመነጩ የአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ እና የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጠበል የነበረ ሲሆን ኃይል ከማጣቱ የተነሣ ሕሙማን በሚገባ መጠበል አይችሉም ነበር። ይህንንም ችግር ለመቅረፍ ጠበሉን ከዋናው ምንጭ በማቆር እና በማጠራቀም በኃይል እንዲወርድ ተድርጓል። አሁን ምእመናን ሳይሳቀቁ በኃይል የሚወርድ ጠበል ይጠበላሉ። ሕሙማን ከተጠበሉ በኋላ በፍሳሽ መልክ የሚወርደው ማይ አይባክንም። በውኃ ማስተላለፊያ ቧንቧ ተጠልፎ ለግንባታ አገልግሎት ይውላል። በገዳሙ ውስጥ የተገነቡ እና በመገንባት ላይ ያሉት ሕንጻዎች በሙሉ በዚሁ ከጠበል በሚወርደው ውኃ በመጠቀም ነው።  

፯.፭.ዘመናዊ የወተት ላም ፕሮጀክት

ዘመናዊ የወተት ላም እርባታ በገዳሙ በጥቂቱ የተጀመረ ሙከራ ያለ ሲሆን ይህን ተሞክሮ ለማስፋት ቅድመ ዝግጅት ተጠናቋል። በዚህም ፴ የፈረንጅ ላሞችን የሚይዝ ዐሥራ ዐራት በሃያ ካሬ ዘመናዊ ቤት ተገንብቶ ለአገልግሎት ዝግጁ ሆኗል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ የወተት ማቀነባበሪያም ለመገንባት በረጅም ጊዜ ዕቅድ ተይዟል። ከእነሱ በሚወጣው እበት የባዮ ጋዝ ቴክኖሎጂም የሚሠራ ይሆናል። ለዚህ ዕቅድ መሳካት ዋነኛው በቂ የውኃ አቅርቦት ሲኖር ነው። ይህንንም  ችግር ለመፍታት ገዳሙ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ይገኛል።  

፯.፮.የተግባር ቤት

ገዳሙ ሲመሠረት አብሮ የተገነባው ተግባር ቤት ብዙ ዓመታት አገልግሎት በመስጠቱ አርጅቶ ወደ መፈራረስ ተቃርቧል። አስቀድሞ ሲሠራም አካባቢውን ያገናዘበ ባለመሆኑ በጪስና በሙቀት በመታፈኑ ለተግባር ቤት አገልጋዮች ፈተና ነው። የአካባቢውን የአየር ንብረት ያገናዘበ፣ ብዙ አገልጋዮች ማስተናገድ የሚችል፣ መናንያን የአብነት ተማሪዎችንና ወደ ገዳሙ የሚመጡ ምእመናን የሚያገለግል አዲስ ተግባር ቤት መሥራት አስፈልጓል። ይኅንንም ታሳቢ ያደረገ ተገንብቶ ለአገልግሎት ዝግጁ ሆኗል።

፰. ግንባታቸው ያልተጠናቀቁ ሕንጻዎች

ገዳሙ ብዙ የልማት ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል። ይኽም ከላይ ያየናቸው የተለያዩ ግንባታዎች ዋናዎቹ ሲሆኑ ወደፊት የሚጠናቀቁ ግንባታዎች የሚከተሉት ናቸው።

፰.፩. የእናቶች በዓት

ገዳሙ የአንድነት ገዳም ቢሆንም የእናቶች እና የአባቶች በዓት መለያየት እንደሚገባ የገዳሙ መተዳደሪያ ደንብ የሚያስቀምጥ በመሆኑ ፲፰ ክፍላትን የያዘ ሙሉ መገልገያ የሚሟላለት ሕንጻ በመገንባት ላይ ይገኛል።

፰.፪. የስብከተ ወንጌል አደራሽ

ለገዳሙ ከሚያስፈልጉት መሠረተ ልማቶች መካከል የስብከተ ወንጌል አዳራሽ አንዱ ነው። የስብከተ ወንጌል አዳራሽ ዘርፈ ብዙ አገልግሎት ይሰጣል። ለስብከተ ወንጌል አገልግሎት፣ ለሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች መማሪያ ለመንፈሳዊ ጉባኤያት፣ ለእንግዶች መቀበያ እና ማረፊያ ያገለግላል። ገዳሙም ችግሩን ለመፍታት በማሰብ በአንድ ጊዜ ፲፻ (አንድ ሺህ) ምእመናንን ማስተናገድ የሚችል አዳራሽ እያስገነባ ይገኛል። 

፰.፫. ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን     

አሁን ያለው ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ገዳሙ ሲመሠረት የተገነባ ሲሆን ከዕድሜ መጨመር እና የአካባቢው ማኅበረሰብ እየበዛ መሄድ በተፈለገው መጠን ምእመናኑን ማስተናገድ አልተቻለም። የገዳሙ አስተዳደር አዲስ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን መገንባት አስፈላጊ መሆኑን ካመነበት በኋላ ፲፱ ሚሊየን የሚገመት አዲስ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን መገንባት ተጀምሯል።

፱. የገዳሙ ቋሚ እና ተንቀሳቃሽ ንብረቶች

ገዳሙ ከመናንያኑ ጀምሮ በርካታ ቋሚ እና ተንቀሳቃሽ ንብረቶች ያሉት ሲሆን ዋና ዋናዎቹን ለመጥቀስ፡-

 የይዞታ ማረጋገጫ ያለው ፹፩.፸፱ (ሰማንያ አንድ ነጥብ ሰባ ዘጠኝ) ሄክታር የእርሻ መሬት

 በናፍታ የሚሠራ ሁለት የእህል ወፍጮ

 ሰዎችን፣ እቃንና ምርትን ከቦታ ቦታ የሚያመላልስ ትራክተር

 የብሎኬት ማምረቻ ማሽን

 የሲሚንቶ ማቡኪያ ሚክሰር

 አርማታ ማዋሐጃ ቫይብሬተር

 ከሙአለ ሕጻናት እስከ ፬ኛ ክፍል አገልግሎት እየሰጠ ያለ ት/ቤት

 ፳፰ የእርሻ በሬዎች

 ፶፪ የሐበሻ እና የፈረንጅ ላሞች

 ፯ አህዮች

 ተገንብተው የተጠናቀቁ እና በመገንባት ላይ ያሉ ሕንጻዎች ዋና ዋናዎቹ ናቸው።

፲. ገዳሙ ለአከባቢው ማኅበረሰብ እየሰጠ ያለው አገልግሎት

በማንኛውም ደዌ ተይዘው ወደ ገዳሙ ለሚመጡ ምእመናን የጠበል አገልግሎት የሚደረግባቸው ሲሆን ጠበልተኞች የማረፊያ ቦታ ይመቻችላቸዋል በቆይታቸውም መቁነንት ከመናንያን ጋር ይጣሰቸዋል።

ለአከባቢው ማኅበረሰብ በተለይ በገዳሙ ዙሪያ ለሚኖሩ ምእመናን ማንኛውም ችግር ሲገጥማቸው ገዳሙ ይደርስላቸዋል። ለአብነት ያህልም ዘር ሲያጥራቸው ዘር ይሰጣል፣ ከገዳሙ የእርሻ መሬት በየዓመቱ በቂ ምርት የሚሰበሰብ በመሆኑ ከአካባቢው ማኅበረሰብ ባሻገር ለተለያዩ ገዳማትም የቀለብ እገዛ ይደረጋል። በገበያ ቀን ከገዳሙ እስከ ዋናው መንገድ ፲ ኪ.ሜ. በእቃ ማጓጓዣ ትራክተር የትራንስፖርት አገልግሎት ይሰጣል፣ በበጋ ወቅት የውኃ እጥረት ሲኖር የመጠጥ ውሃ ያከፋፍላል፣ የወፍጮ አገልግሎት በቅናሽ ዋጋ፣ አቅም ለሌላቸው ደግሞ በነጻ ይፈጫል፣ በኬላ ከተማ ከሙአለ ሕፃናት እስከ ፬ኛ ክፍል በከፈተው ት/ቤት በአከባቢው ካሉ የግል ት/ቤቶች በተሻለና ዝቅተኛ ክፍያ ማለትም በአንድ ተማሪ ፻፶ ብር በማስከፈል ያግዛል፤ እጓለ ማውታ (የሙት ልጅ የሆኑ) ሕጻናትን ያሳድጋል።

አካባቢው የገጠር ቀበሌ በመሆኑና ጥርጊያ መንገድ ባለመኖሩ አርሶ አደሩ ምርቱን ወደ ገበያ ለመውሰድ፣ ሰው ሲታመምበት ወደ ሕክምና ለማድረስ ከፍተኛ ችግር ነበር። ገዳሙም ይህን በመረዳት በራሱ ወጪ ፲ ኪ.ሜ. መንገድ በማስጠረግ እና ከዋናው መንገድ ጋር በማገናኘት የተጠቀሱ ችግሮችን መፍታት ችሏል።

፲፩. ወደፊት ሊሠሩ የታሰቡ ግንባታዎች

 እያንዳንዱ ፳፬ ክፍሎች ያሉት ባለ አንድ ፎቅ (G+1) የተለያዩ ፫ ሕንጻዎች የካህናት ቤት

 ዕቃ ቤት

 ምርፋቅ (የመመገቢያ አዳራቀሽ)

 የወንድ ተግባር ቤት

 የእደ ጥበባት ማእከል (የእንጨት ሥራ፣ የብረታ ብረት ሥራ፣ የሽመና ሥራ)

 የአብነት ትምህርት ቤት ግንባታ

 የከርሠ ምድር ውኃ ቁፋሮ 

 የባዮ ጋዝ ቴክኖሎጂ ዋና ዋናዎቹ ናቸው። 

፲፪.ገዳሙ ላይ ያለው ተግዳሮት

ገዳማዊ ሕይወት በራሱ ከፈተና ያልተለየ ሕይወት ቢሆንም ከላይ ካየናቸው ሰፋፊ የልማት ሥራዎች አንጻር የገዳሙ ዋና ፈተና የመናንያን ፍልሰት ነው። ወደ ገዳሙ ለሚመጡ መናንያን ልዩ አቀባበል ቢደረግላቸውም በገዳሙ ውስጥ ከሚከናወኑ በርካታ ተግባራት እና የጉልበት ሥራዎችን በመሰላቸት አብዛኛዎቹ መናንያን ለመቆየት ፈቃደኛ አይደሉም።

፲፫. መፍትሔ ሊሆኑ የሚችሉ

ለመናንያን ፍልሰት መፍትሔ ሊሆን የሚችለው በዋናነት አጽንኦ በዓት ሲሆን ይህም የሚሆነው አግዚአብሔር ሲፈቅድ እና ሲያጸና መሆኑ በእርግጥ ይታወቃል። ይሁን እንጂ እንደ ሰው ሰውኛ መናንያን በበዓታቸው እንዲጸኑ የተለያዩ ሥልጠናዎች መሥጠትም አንድ መፍትሔ ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ የምንኵስና ሕይወት ያሉት ፈተናዎች እና የሚየሰጠው ጸጋ፣ አጽንኦ በዓት እና ሌሎች ተዛማች ሥልጠናዎች ለመናንያን ቢሰጣቸው ያሉትን ችግሮች ሙሉ በሙሉ መፍታት ባይቻልም የመናንያንን ፍልሰት በትንሹ መቅረፍ ይቻላል። በተጨማሪም አዲስ ለሚመጡ መናንያን ከነባሩ ጋር መጓዝ ለማይችል አንድ ጊዜ ቀኖና ከመጫን ደረጃ በደረጃ እንደ ቆይታው መጠን እንዲለማመደው ቢደረግ እንዲሁም ተተኪ መናንያን ለማፍራት ሁሉም ገዳማት እና መናንን ዐቅደው መሥራት እንዳለባቸው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና መስጠት።  

ማጠቃለያ

በአጠቃላይ በምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት በዱግዳ ቦራ ወረዳ የሚገኘውን የመካነ ሕይወት ጮቢ በዓታ ለማርያም አንድነት ገዳምን ከሚገኝበት ቦታ በመነሣት መቼ እንደተመሠረተ፣ ከተመሠረተበት ጀምሮ ያከናወናቸውን ተግባራትና የገዳሙን ታሪክ በአሁኑ ሰዓት ገዳሙ ያለበትን ነባራዊ ሁኔታ ከረጅሙ በዐጭሩ አቅርበናል። እግዚአብሔር አምላክ ከገዳሙ በረከት ያድለን አሜን

Read 474 times