Friday, 04 December 2020 00:00

የተከዜ ምዕራፈ ቅዱሳን ቅድስት ኪዳነ ምሕረት እና መድኃኔዓለም ዘአቡነ ሐዋርያ ክርስቶስ አንድነት ገዳም ክፍል ሁለት

Written by  ወግደረስ አዳል

Overview

ውድ አንባብያን ባለፈው ዕትማችን በእናስተዋውቃችሁ ዓምዳችን “የተከዜ ምዕራፈ ቅዱሳን ቅድስት ኪዳነ ምሕረት እና መድኃኔዓለም ዘአቡነ ሐዋርያ ክርስቶስ አንድነት ገዳምን ከአመሠራረቱ ጀምሮ በርከት ያሉ ጉዳዮችን ማቅረባችን ይታወሳል። ቀሪውንና ክፍል ሁለትን በዚህ ዕትማችን እናቀርባለን። መልካም ንባብ። ፫. ገዳሙ ካለፉት ፳ ዓመታት ጀምሮ ያሉ እንቅስቃሴዎች ገዳሙ ከተዳከመበት ተነሥቶ ዳግም በ፲፱፻፺፪ ዓ.ም. ከቀናበት ዓመት ጀምሮ እስካሁን እጅግ አርአያ  የሚሆን ፈጣን ዕድገት ላይ ያለ ገዳም ነው። በገዳሙ ውስጥ የአባቶችን የገዳማዊ ሕይወት አጥብቆ በመያዝ አሁን ላይ ያሉ የዘመኑ ፈተናዎችን ለመቋቋም የሚያስችል አሠራርን የሚከተልና ገዳማዊ ሕይወት እውነትም በጸሎትና በሥራ የሚገለጽ መሆኑን ተመጽዋችነት የገዳማውያን ባህል አለመሆኑን የሚያሳይ አርአያ ገዳም ነው። በዚህም ጠንካራ የሥራና የጽኑ አንድነት ሥርዓት በ፲፱፻፺፪ ዓ.ም. ከሦስት ወደ ፲፬ ከፍ ያደረጋቸውን የመነኰሳት ቁጥር በ፳፻፲፩ ዓ.ም. ፮፻፲፮ መናንያንና ከ፴ በላይ የአብነት ተማሪዎች እንዲኖሩት አስችሎታል።

 

ከ፲፱፻፺፭ ዓ.ም. ጀምሮ በማኅበር “ልመና እስከ መቼ?“ በሚል መሪ ቃል ሁሉም በአንድነት ቃል ከገቡ በኋላ ብዙ ፈተናዎችን ተቋቁመው ራሳቸውን ከመቻል አልፈው ሌሎችን እየደገፉ ይገኛሉ። 

፫. ፩. የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ዘርፉ የሥራ እንቅስቃሴ

በዚህ ዘርፍ የሚመራው የገዳሙ አገልግሎት በሦስቱም የገዳሙ አብያተ ክርስቲያናት ስብሐተ እግዚአብሔር ሳይቋረጥ እየተገለገለ ይገኛል። ለገዳማውያኑና በገዳሙ ዙሪያ ባሉ ፲፬ አጥቢያዎች በቋራ የገዳሙ የእርሻ ልማት ኢንቭስትመንት ባለበት አካባቢ ባሉ አድባራት የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ይሰጣል። ለ፲፫ አድባራት ለእያንዳንዳቸው በዓመት የሁለት ሰው ኮታ አዘጋጅቶ ሙሉ ወጪአቸውን ሸፍኖ ከንባብ እስከ ምስክር ጉባኤ ድረስ እንዲማሩ ያደርጋል። በዚህም ገዳሙ ከአካባቢው ማኅበረሰብ ዘንድ ጥሩ ግንኙነትና ተቀባይነት እንዲኖረው አስችሎታል። የውስጥ አገልግሎትም እንዳይስተጓጎል ተተኪ አገልጋዮችን ለማፍራት በመንፈቅ ፯ መናንያንን ከየትኛውም የገዳሙ ሥራ ነጻ አድርጎ የአብነት ትምህርት ብቻ እንዲማሩ ያደርጋል። የነገውን የገዳሙን አገልግሎት በማሰብም አንድ የቅዳሴ መምህር እንዲያስመሰክሩ ወደ ደብረ ዓባይ ሌላ የቅዳሴ መምህር መጻሕፍት እንዲማሩ ወደ መጻሕፍት ቤት ልኳል። 

፫. ፪. የቤተ እግዚአብሔር ዘርፍ የሥራ እንቅስቃሴ

ገዳምውያኑ በጽኑ የገዳም አንድነትና ሥርዓት መኖራቸውን፣ ሁሉም መናኝ ከገዳሙ ሊያገኝ የሚችለውን እንክብካቤ እያገኘ መሆኑን፣ አረጋውያንና ታማሚዎች በትክክል ድጋፍና እንክብካቤ እየተደረገላቸው መሆኑን እና ገዳሙን ብለው የመጡ እንግዶች በተገቢው ሁኔታ መስተናገዳቸውን እየተከታተለ ገዳሙን አሁን ካለበት ደረጃ ላይ አድርሶታል። ከዚህም በተጨማሪ ወላጅ አልባ ሕፃናትን በገዳሙ ወስጥ ከማሳደግ አልፎ በአካባቢው ለሚገኙ የድሃና የአቅመ ደካማ ልጆችን የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ በማድረግ ሀገራዊና ክርስቲያናዊ ግደታውን እየተወጣ ይገኛል። 

፫. ፫. የግብርና ልማት ዘርፉ እንቅስቃሴ

ገዳሙ ራሱን እንዲችል በቋራ አካባቢ በ፻፷ ሄክታር መሬት ላይ የእርሻና የእርባታ ሥራን ያከናውናል። በገዳሙ ክልልም ውስጥ በቀጭን አበባ ሥላሴ እና በመድኃኔዓለም የአባቶች ገዳም የአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም በሁሉም የገዳሙ ቅጽር ውስጥ የደን ልማት ሥራዎችን ይሠራል። በተለይ በዚህ ዘርፍ እጅግ የሚያስደንቀው የውኃ አጠቃቀሙ ነው። ምንም እንኳ ገዳሙ ከሥሩ የተከዜና የቀጭን አበባ ወንዞች የሚፈሱ ቢሆንም ከሸለቆው ጥልቅነት የተነሣ ለመጠቀም አስቸጋሪ ነው። ይሁን እንጂ ያሉትን የውኃ አማራጮች የሚጠቀምበት መንገድ ግሩም ነው። ተከዜ ገዳም ላይ ያለው የውኃ አጠቃቀም ለገዳማት ብቻ ሳይሆን ለመላው ዓለምም አስተማሪ ነው። በተራቆተው የተከዜ ተፋሰስ ላይ የገዳሙን ቅጽርና አካባቢ አረንጓዴ ለማልበስ የሚያደርገው ጥረት ይበል የሚያሰኝ ነው። 

፫. ፬. የግንባታ ዘርፉ የሥራ እንቅስቃሴ

በዚህ ዘርፍ ገዳሙ የራሱን የቅድስት ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን ሙሉ በሙሉ ከዲዛይን እስከ ኮንክሪት ሙሊት ግንባታ አንሥቶ የትኛውንም የገዳሙ ግንባታዎች በራሱ መነኰሳት ባለ ሙያዎችና የሰው ኀይል ያከናውናል። ከዚህም በተጨማሪ በግሸን ማርያም የአንቀጸ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤልን ቤተ ክርስቲያን በማስገንባት ላይ፣ በቋራ አካባቢ ፬ (ማር ውሃ ሚካኤል፣ ሰገነት ሚካኤል፣ አዲስ ዓለም ጊዮርጊስና ምርት ገለጎ ኪዳነ ምሕረትን) በላስታና በመቄት ወረዳዎች ፮ (ቂላ ሚካኤል፣ ወይጣ ዲባ ሚካኤል፣ ሻሎ ጊዮርጊስ፣ ዶሮ ላባ ማርያም፣ አሮጌ አምባ በዓለ እግዚአብሔር እና ዙፋን አምባ ማርያም) አብያተ ክርስቲያናት ሙሉ በሙሉ ወጫቸውን ሸፍኖ ገንብቶ እና ለአዋ ሚካኤል የግንባታ የገንዘብ ድጋፍ አድርጎ ለአካባቢው ምእመናን መገልገያነት አስረክቧል።

፫. ፭. የእደ ጥበብ ዘርፉ የሥራ እንቅስቃሴ

ይህ ዘርፍ የገዳሙ የልማት እንቅስቃሴዎች ሁሉ መነሻ መሠረት ነው።በ፲፱፻፺፮ ዓ.ም. በሁለት የሽመና እቃና በአንድ አሮጌ የስፌት ማሽን ሥራውን የጀመረው ይህ ዘርፍ በአሁኑ ሰዓት ገዳሙ ራሱ የሚሠራቸውን ጨምሮ በርካታ የሽመና የሹራብ፣ የስፌት ማሽኖችን የያዘ ሁለት ሸድ በገዳሙ ውስጥ ያለው ዘርፍ ነው። የተለያዩ የባህል አልባሳት በማምረትና በመሸጥ ከፍተኛ ዕድገት ላይ ነው። በወልዲያ ከተማ የፋብሪካ መትከያ ቦታ ተሰጥቶት የነበር ቢሆንም ከገዳማዊ ሕይወት ጋር አጣጥሞ ለመሄድ ፈተና ይሆንብኛል ብሎ ስለሰጋ ሳይቀበለው ቀርቷል። ከገዳሙ የተመረቱ አልባሳትን መሸጫ በወልዲያ ፪ በመቄት ፩ በላሊበላ ፩ በደሴ በቅርብ ሥራ የሚጀምር ፩ ሱቅ አለው። በየሱቆቹ በየ፬ ወር የጊዜ ሠሌዳ አስቀምጦ የሽያጭ ባለ ሙያዎችን ይቀይራል።  ከዚህም በተጨማሪ ለሌሎች ገዳማት የእደ ጥበብ ሥራ ሥልጠና በመስጠትና የመሥሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ በማድረግ ሌሎች ገዳማትን ራሳቸውን እንዲችሉ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ያለ ዘርፍ ነው። ይህንኑ አገልግሎት በጥቃቅን ተደራጅተው ለሚመጡ ሠልጣኞችም የገዳሙን ሕግ አክብረው እስከ ኖሩ ድረስ ሥልጠና ይሰጣል። ገዳሙ ምንም እንኳ በዚህ ዘርፍ የራሱን ጉድለቶች ለመሙላት እንጂ ‹እሸለማለሁ› ብሎ ባይሠራም በተለያዩ ጊዜያት በተደረጉ ሀገር አቀፍ ውድድሮች ላይ በመጋበዝ በሀገር ውስጥና በጎረቤት ሀገር ሱዳን ባዛሮችና ሲምፖዚየሞች በመገኘት ብዙ ሽልማቶችን፣ ዋንጫዎችን፣ ሜዳሊያዎችንና የምስክር ወረቀቶችን አግኝቷል። 

፫. ፮. የቴክኒክና የኢንዱስትሪ ዘርፍ የሥራ እንቅስቃሴ

ይህ ዘርፍ በገዳሙ የሚገኝን ምርት ወደ መሸጫ ቦታ በገዳሙ ተሽከርካሪዎች ያደርሳል፣ ጋራዡ ባለው አቅም ልክ የተሽከርካሬዎችን ጥገና ያደርጋል ። በገዳሙ ውስጥ ያለውን ወፍጮ ጨምሮ በገለሶት በወይጣ ድባ በምርት ገለጎ  ለማኅበረሰብ አገልግሎት የሚሰጡ ወፍጮዎችን ይሠራል ይጠግናል። የእደ ጥበብ ማምረቻ ማሽን ይሁን ሌላ ለገዳም አገልግሎት የሚውል  ማሽን በሱ አቅም የሚሠሩትን ያመርታል፤ ጥገናዎች ያከናውናል። ከእንጨትና ከብረት የሚሠሩ መገልገያዎችን፤ በርና መስኮቶችን፣ ወንበርና ጠረንጴዛዎችን  ያመርታል።

፫. ፯. የሥነ ጽሑፍና የቅንብር ዘርፍ የሥራ እንቅስቃሴ

በዚህ ዘርፍ ለገዳማውያኑ የሚሆኑ የምስል ወድምፅ ምርቶችን አቀናብሮ ለማስተማሪያነት እያቀረበ የሚገኝ ቢሆንም ከገዳሙ ውጭ በዓለም ላሉ ክርስቲያኖች ወንጌልን ለማዳረስ እንዲረዳው በቀረጻና በማቀነባበር የሚሠሩ ባለ ሙያዎችን ወደ ተቋማት ልኮ እያስተማረ ይገኛል። 

፫.፰.የሒሳብ አያያዝ

. ከዘርፍ አደረጃጀት ውጭ ያለው የገዳሙ የሒሳብና ኦዲት ክፍል በየ አራት ወሩ ቆጠራና ርክክብ ያካሂዳል በየሲሶ ዓመት የሒሳብ ሥራ ይሠራል። በዓመት አንድ ጊዜ ከሀገረ ስብከት በተላኩ ሦስት ኦዲተሮች ኦዲት ያስደርጋል።

በአጠቃላይ ሁሉም ዘርፎች የገዳሙ ገዳማዊ ሕይወትና ክርስቲያናዊ ተልእኮ በምንም ምክንያት ሳይስተጓጎል እንዲቀጥል በማድረግ በኩል የሚያሳዩት ትጋት ሁላችንም በገዳሙ ላይ ተስፋ እንድንጥል የሚያደርግ ነው።

፬. ገዳሙ እንዲሰፋና እንዲጠነክር አስተዋጽኦ ያደረጉ አካላት

ለገዳሙ መጠንከር ትልቁን ድርሻ የሚወስዱት ገዳሙ ወደ ቀድሞ ክብሩ እንዲመለስ ከ፲፱፻፺፪ ዓ.ም ጀምሮ ብዙ የደከሙት የገዳሙ አበ ምኔት አባ ኪዳነ ማርያምና የገዳሙ ሁሉም መነኰሳትና መነኮሳይያት ናቸው። ነገር ግን የእነሱን ትጋት በማገዝ በኩል ስንመለከት የገዳሙን ትጋትና የሥራ ባህል በተለያዩ ጊዜያት በየመድረኩ የሰሙት የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር የነበሩት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው መጋቢት ፯/፳፻፯ ዓ.ም ገዳሙን ጎብኝተው የገዳሙን ትጋት ካደነቁ በኋላ ከመንግሥት በኩል ምን እንዲደረግላቸው እንደሚፈልጉ ጠይቀው በተረዱት መሠረት የመንገድ፣ የውኃ፣ የመብራትና የተከዜ ወንዝ ድልድይ ጥያቄን  አብረዋቸው ለመጡት የክልሉ የሥራ ኃላፊዎች ትእዛዝ በመስጠት ሥራው እንዲጀመር አድርገው ታኅሣሥ ፳፻፰ ዓ.ም. ላይ የውኃው ብቻ ሲቀር መንገዱም፣ መብራቱም፣ የተከዜ ተንጠልጣይ ድልድይም ተጠናቀው አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል። በተለይ የተከዜ ተንጠልጣይ ድልድይ፣ የአባቶችንና የእናቶችን ገዳም ከማገናኘትም አልፎ ተከዜ ሲሞላ የሚለያዩትን የላስታና የመቄት ወረዳን ማገናኘት ተችሏል። ገዳማውያኑንም በክረምት በውሻ ፖስተኛ ከመገናኘት በአካል ወደ መገናኘት አሸጋግሯቸዋልና ትልቅ እገዛ ነው። በእደ ጥበብ በግብርና የሚያመርቱትን መርጠው የሚገዙም ደንበኞች ለገዳሙ ትልቅ እገዛ አድርገዋል። 

፭. የገዳሙ የወደ ፊት ዕቅድ

ገዳሙ በ፳፻፴፪ ዓ.ም. ላይ ሊደርስበት ካሰበው ግብ ላይ ለመድረስ የሚያግዘው የ፳ ዓመት ዕቅድ አውጥቷል። በዚህ ዕቅዱ ውስጥ ከፍተኛ ትኩረት የተሰጠባቸው ዐበይት ጉዳዮቹን ብንመለከት 

. በአብነት ትምህርት በኩል ሁሉንም ጉባኤያት ያካተተ ት/ቤት ለመገንባትና አስፈላጊውን ግብአት ለማሟላት፤ የስብከተ ወንጌል ተልእኮ ተደራሽነትን ማስፋት፤

. በግንባታው በኩል በቀጭን አበባ የተጀመረውን የቤተ ክርስቲያን ዋሻ ፍልፈላና የመድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ግንባታ ማጠናከር፣ ከ፳፻፲፫ ዓ.ም. ጀምሮ የመነኰሳትና የተማሪዎች መኖሪያ በዓት ግንባታ፣ የመንገድ ሥራ ግንባታ፣ የመስኖና የመጠጥ ውኃ ግንባታ፣ የዓሣ ገንዳ ግንባታና የማምረቻ ቤቶች የማስፋፊያ ግንባታ እንዲሁም ለእንግዶች ማረፊያ አገልግሎት የሚሰጥ ከመናንያን በዓት የተለየ በገዳሙ መግቢያ አካባቢ የሚገነቡ  የቤቶች ግንባታ፤

. በእደ ጥበብ ዘርፍ የማምረት አቅምንና ጥራትን በማሳደግ የምርት ተፈላጊነትን በማሳደግ በገዳሙ የማምረቻ ማስፋፊያ ማድረግ፣ ሌሎችንም መደገፍ፤

. በግብርናው ዘርፍ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርትን ማሳደግና ማስፋፋት፣ የመደብ እርከን በመሥራት የደን ሽፋንን በሰፊው ማሳደግ፣ የዓሣና የዶሮ እርባታ መጀመርና ጥሩ ምርትን ለገበያ ማቅረብ፣ የቋራውን የእርሻ ፕሮጀክት በሰፊው ማጠናከር፤

. በቴክኒክና ኢንዱስትሪ ዘርፍ የዘርፉን ክፍሎች በማጎልበት የገዳሙን ማንኛውንም የማምረቻ መሣሪያ በራስ አቅም ማምረትና ጥገና ማካሄድ፤ 

. በቤተ እግዚአብሔር ዘርፍ የገዳሙን አንድነትና ገዳማዊ ሕይወት አጠናክሮ ለማስቀጠል በቅርብ የተከለሰውን የገዳሙን ሥርዓተ ገዳም ማሳተምና ማንኛውም ወደ ገዳሙ የሚመጣ አካል በዚህ እንዲመራ ለማድረግ ሥራው የተጠናቀቀ ቢሆንም በዚህ የዕቅድ ዘመን ለኅትመት ገብቶ ሥራ ላይ እንዲውል ማድረግ።  የገዳሙን አባቶችና እናቶች የማገልገሉ ተልእኮ ለምናኔ የሚመች አድርጎ አጠንክሮ ከማስቀጠል ባሻገርም የቤተ ክርስቲያን ተልእኮ የሆነውን የደከሙትን መርዳትን አጠንክሮ የሚያስቀጥልበትን መንገድ ማመቻቸት።

. የሥነ ጽሑፍና ቅንብር ዘርፉ እያሠለጠናቸው ያሉት የገዳሙ መናኝ ባለ ሙያዎች ከሥልጠና ሲመለሱ የስብከተ ወንጌል ተደራሽነቱን ለማስፋት ማደራጀትና የድምፅ፣ የድምፅ  ወምስልና የኅትመት ሥራዎችን በሰፊው መሥራት ላይ ትኩረት ያደርጋል።

በአጠቃላይ የገዳሙ የ፳ ዓመት ዕቅድ ሰፊ፣ የገዳሙን ገዳማዊ ሕይወት የሚያጠናክርና ለሌሎችም ገዳማት ምሳሌ የሚሆን ነው።

፮. ገዳሙ ሊያስተካክላቸው የሚገቡ ክፍተቶች

. የአገሬው መንገድ በገዳሙ ውስጥ ያውም በመነኰሳት መኖሪያዎችና በአብያተ ክርስቲያናቱ አጠገብ በመሆኑ ገዳማዊ ሕይወትን ከመረበሽ አልፎ ለሌሎች ግጭቶች በር የሚከፍት እንደሚሆን ታውቆ ለሁሉም የሚመች መንገድ ቢቀየስ ። 

. ከገዳሙ ውጭም ይሁን ከገዳሙ ውስጥ አቅጣጫ ጠቋሚና ገላጭ ምልክት ባለመኖሩ ወደ ገዳሙ ለመግባትም ይሁን በገዳሙ ወስጥ ሥርዓተ ገዳሙን ጠብቆ በሥርዓት ለመንቀሳቀስ አስቸጋሪ ስለሚያደርገው የአቅጣጫ ጠቋሚና ገላጭ ምልክቶች ጉዳይ ቢታሰብበት።

፯. ገዳሙ ገዳማት ላይ ለሚሠሩና ለሁሉም የቤተ ክርስቲያን አካላት ያስተላለፈው መልእክት

. በዐውደ ምሕረት ትምህርቶች፣ በሰንበት ት/ቤቶችና በግቢ ጉባኤያት ሥርዓተ ትምህርቶች፣ በክርስቲያናዊ ኮርሶች፣ በአብነት ት/ቤቶች እና በመሳሰሉት ላይ ስለ ገዳማዊ ሕይወትና ምናኔ ትምህርቱ ተካቶ ቢሰጥ፤

. ሕፃናትንና ወጣቶችን በመሰብሰብ የዕረፍት ጊዜያቸውን በገዳማት እንዲያሳልፉ በማድረግ ፍቅረ ገዳማዊ ሕይወት እንዲያድርባቸው ቢሠራ፤

. በገዳማት ዙሪያ ጥናት የሚሠሩ የቤተ ክርስቲያን ልጆች የእናቶችንም ችግሮች ቢያጠኑት መልካም ነው። 

ማጠቃለያ

የተከዜ ምዕራፈ ቅዱሳን ቅ/ ኪዳነ ምሕረት፤ አቡነ ሐዋርያ ክርስቶስ አንድነት ገዳም ብዙ ቅዱሳንን ያፈራ ታላቅ ገዳም ነው። ይሁን እንጂ በዘመናት ፈተና ተዳክሞ ለመበተን ደርሶ የነበረ መሆኑም ይታወሳል። ነገር ግን በእግዚአብሔር ቸርነት በቅዱስ አቡነ ሐዋርያ ክርስቶስ ረዳትነት በትጉሃን መነኰሳትና መነኰሳይያት ብርቱ ጥረት በ፳ ዓመት ውስጥ ጥሩ ደረጃ ላይ የደረሰ ለሌሎችም አርአያ የሚሆን ገዳም ነው።

እግዚአብሔር አምላክ ገዳሙን በረድኤት ይጠብቅልን።

በኢ/ኦ/ተ/ቤተ ክርስቲያን የሰ/ት/ቤቶች ማ/መ/ 

ማኅበረ ቅዱሳን 

የወልዲያ ማእከል ቅዱሳት መካናት ዋና  ክፍል ገዳማት ክፍል

 

Read 787 times