Thursday, 21 January 2021 00:00

የጮቢ መካነ ሕይወት  በዓታ ለማርያም የአንድነት ገዳም

Written by  ዲ/ን ደረጄ ጋረደው

Overview

መግቢያ በቅዱስ መጽሐፍ “እግዚአብሔር አምላክም ሰውን ወስዶ ያበጃትም ይጠብቃትም ዘንድ በኤዶም ገነት አኖረው” (ዘፍ.፪፥፲፭) ተብሎ እንደተጻፈ ሰው ቦታን ይቀድሳል። በአንጻሩም ሰዎች በቦታ ይቀደሳሉ። ይልቁንም የቅዱሳን የጸሎት በዓታቸው  የእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ያለበት፣ የቅዱሳኑ አጽማቸው የረገፈበት ስለሆነ  በረከተ ሥጋን በረከተ ነፍስን ያድለናል። ይህንም መሠረት በማድረግ የጮቢ መካነ ሕይወት  በዓታ ለማርያም የአንድነት ገዳም ከምሥረታ አስከ አሁን ያለውን ታሪክ ለአንባብያን ልናስተዋውቃችሁ ጀመርን መልካም ንባብ፡፡ ፩. የገዳሙ መገኛ ቦታ፡- መካነ ሕይወት ጮቢ በዓታ ለማርያም አንድነት ገዳም የሚገኘው በምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት በዱግዳ ቦራ ወረዳ ሀርቦ አቡኖ ቁሙሮ ቀበሌ ገበሬ ማኅበር ነው፡፡ በመካከለኛው ምሥራቅ አቅጣጫ ከአዲስ አበባ እስከ ኬላ ከተማ ድረስ ፻፲፫ ኪሎ ሜትር ርቀት ያለው ሲሆን፤ ከኬላ ከተማ ገዳሙ ድረስ ደግሞ ያለው ጥርጊያ መንገድ ፲፭ ኪሎ ሜትር ይሆናል፡፡  "ጮቢ" ማለት በኦሮሚኛ በረከት ማለት ሲሆን፤ የገዳሙ አካባቢ ደግሞ አቡኖ በመባል የሚጠራ ነው፡፡ ይህንንም ስያሜ ያገኘበት ምክንያት በጥንት ጊዜ ቦታው ላይ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ እና አቡነ ተክለ ሃይማኖት ያረፉበት በመሆኑ እንደሆነ የገዳሙ አባቶች ያስረዳሉ፡፡ ከገዳሙ በስተ ምዕራብ አቅጣጫ በተራራ የተከበበ እና የተለያዩ ዕፅዋቶች የሚገኙበት ሲሆን፣ ሰፋፊ የእርሻ መሬት ያለበት ሜዳ እና ገደላማ ነው፡፡ በገዳሙ አካባቢ የሚኖሩ ምዕመናን የሶዶ ጉራጌ ሲሆኑ፤ መለያ ስማቸው ግን ሶዶ ክስታኔ በመባል ይታወቃሉ፡፡ ይህንንም ስያሜ ያገኙት በጣሊያን ጊዜ በመስቃን ጦርነት ከአርሲ ሙስሊሞች ጋር ተዋግተው ብዙዎች ሰማዕትነት ተቀብለዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በግራኝ አሕመድ ወረራ ጊዜም ሃይማኖታቸውን ሳይቀይሩ ፀንተው የቆዩ ክርስቲያኖች በመሆናቸው ነው፡፡

 

፪. የገዳሙ አመሠራረት

መካነ ሕይወት ጮቢ በዓታ ለማርያም አንድነት ገዳም የተመሠረተው በእግዚአብሔር መልካም ፈቃድ በ፲፱፻፺፫ ዓ.ም. ነው፡፡ መሥራቹም የምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል የሆኑት ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ሣልሳዊ ናቸው፡፡ አሁን እየተጠራበት ያለውን ስያሜ ያገኘው ግን ሰኔ ፬/፲፱፻፺፰ ዓ.ም ነው፡፡ ዛሬ የሚታየው ልማት ከመምጣቱና ከመስፋፋቱ በፊት ቦታው ጠፍ እና ምንም የሌለበት የእርሻ መሬት ነበር፡፡ በወቅቱ ፭ እናቶች እና ሁለት አባቶች በጊዜው ቡታጅራ ማረሚያ ቤት ለእስር ከተዳረጉ እና የእስር ጊዜቸውን ጨርሰው በነጻ ከተለቀቁ በኋላ ወደ ሥፍራው በማቅናት አከባቢውን ሲቃኙ አስቀድሞ ቦታው ለእግዚአብሔር ማደሪያ የተመረጠ መሆኑን በመረዳት በእኒሁ አባቶች እና እናቶች ተነሣሽነት በብፁእ አቡነ ጎርጎርዮስ ሣልስ የምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ መልካም ፈቃድ የመሠረት ድንጋይ ተቀመጠ፡፡ ለሐሳቡ እውን መሆን አቶ አማረ ዱቤ የሚባሉ የአከባቢው ነዋሪ እና የሀገር ሽማግሌ የሆኑ የአባቶችን ሐሳብ በመቀበል የራሳቸውን የእርሻ መሬት ለቤተ ክርስቲያኑ በመስጠት አሁን ያለችው የቤተ ክርስቲያን መቃኞ ሰኔ ፲፭/ ፲፱፻፺፭ ዓ.ም. ተጀምሮ በ፮ ወር ታንጾ ታኅሣሥ ፫ ቀን ፲፱፻፺፮ ዓ.ም. ተጠናቆ ቅዳሴ ቤቷ ተከበረ፡፡

በተለይ አሁን ያሉት የገዳሙ አበ ምኔት መ/ር አባ ተ/ሥላሴ በሳል የአመራር ሰጪነት በአባ ገ/እግዚአብሔር እና አባ ኃ/ገብርኤል አጋዥነት የመጀመሪያ ተግባር የነበረው የገዳሙን ይዞታ ማስፋፋት ስለነበር እስከ ፲፱፻፺፰ ዓ.ም. ይህን ዐቢይ ተግባር በሰፊው ቀጥለውበታል፡፡ የገዳሙ ይዞታ ፹፩.፸፱ (ሰማንያ አንድ ነጥብ ሰባ ዘጠኝ) ሄክታር ሲሆን የይዞታ ማረጋገጫ ደብተርም ተሰጥቶታል፡፡ ወደ ፊትም ይዞታን የማስፋቱ ሥራ የሚቀጥል ይሆናል፡፡ የእኒህ አባቶች ምኞት እና ራእይ ለትውልዱ አርዓያ የሚሆንና ለችግረኞች መጠጊያ ሊሆን የሚችል ገዳም መመሥረት በመሆኑ  ከሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ጎን ለጎን ተግባር ቤት እና የእናቶች ማደሪያ ሠሩ፡፡ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ገዳሙ፣ የገዳሙ መናንያንና  ልማት የማይነጣጠሉ የአንድ ሳንቲም ገጽታ ሆኑ፡፡

፫. የገዳሙ ሥርዓተ አበው

፫.፩. አንድነት

ገዳሙ የአንድነት ገዳም በመሆኑ ጠንካራ የአንድነት ሥርዓት አለው፡፡ በዚህ ገዳም ቁሪት (የግል ሀብት) አጥብቆ የተከለከለ ነው፡፡ በገዳሙ በምናኔ የሚኖርም ሆነ በእንግድነት የመጣ ማንኛውም ሰው የገዳሙን የአንድነት ስርዓት የማክበር ግደታ አለበት። ምዕመናን ወደ ገዳሙ ሲመጡ በመናንያን ላይ መሰናክል እንዳይሆኑ ክትትል ይደረግባቸዋል፡፡ የጠበልተኞች ማረፊያ ለብቻ የተዘጋጀ ሲሆን ወደ እናቶች ገዳም መግባት በጥብቅ ይከለከላል፡፡ ማንኛውም የማኅበር አባል ለግል ጉዳይ በልዩ ልዩ ምክንያትና ችግሮች ወደ ሌላ ቦታ ደርሶ ለመመለስ ያሰበ እንደሆነ አስቀድሞ መምህሩን ወይም መጋቢውን ወይም ሊቀ አርድዕቱን ማስፈቀድ ይኖርበታል፡፡  መናንያን ፫ ዓመት እና ከዚያ በላይ ገዳሙን ካገለገሉ በየዓመቱ በገዳሙ ወጪ ተሸፍኖላቸው ታሪካዊ ገዳማት በመጎብኘት ከበረከት እንዲሳተፉ ይደረጋል፡፡ ለእናቶችም ወርኃዊ የንጽሕና መጠበቂያ በወቅቱ ይሟላላቸዋል፡፡  ከአቅም በላይ ከሆነ ግን ወደ ገዳሙ አስተዳደር ቀርቦ ውሳኔ ይሰጥበታል፡፡ 

፫.፪. ሥርዓተ ምንኵስና

ወደ ገዳሙ  ለመግባት የሚፈልጉ መናንያን በገዳሙ ሕግና ሥርዓት መሠረት የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አማኝ ሆኖ በሃይማኖቱ ሕጸጽ የሌለበት፣ በገዳሙ ደንብ ለመተዳደር ፈቃደኛ የሆነ፣ ከመጣበት አካባቢ ማንነቱን የሚያስረዳ በቂ ማስረጃ ያለው መሆን አለበት፡፡ ከሌላ ገዳም የሚመጣ መናኒ የማኅበሩ አባል ለመሆን ሲያመለክት ከመጣበት ገዳም በቂ ማስረጃ ማቅረብ ይኖርበታል፡፡ አንድ የማኅበር አባል የገዳም ኗሪነቱን የሚገልጽ መታወቂያ ወረቀት ሚያገኘው በገዳሙ ውስጥ አባል ሆኖ ቢያንስ አንድ ዓመት የቆየ እንደሆነ ነው፡፡ በአሁ ጊዜ በገዳሙ ተገኝተን በተመለከትነው መረጃ  በገዳሙ ውስጥ የሚገኙ መናንያን አባቶች ፲፱ እናቶች ፲፮ በአጠቃላይ   ፴፭ ናቸው፡፡

፫.፫. ሥርዓተ ጸሎት

 በገዳሙ የጸሎት ሥርዐት በቀን ሰባት ጊዜ የሚጸለይ ሲሆን፤ እነዚህም በመዓልት በ፫፣ በ፮፣ በ፱፣ በ፲፩፣ በሌሊት በ፫፣ በ፮፣ በ፱ ናቸው፡፡

 ዘወትር በጠዋት ኪዳን ይደረሳል፡፡

 መነኰሳይያት የማታ ጉባኤ እና ትምህርት አላቸው፡፡

፫. ፬. አመጋገብ እና የአለባበስ ሥርዐት

በገዳሙ መናንያን ከሰኞ እስከ ዓርብ በሁለት ቀን አንድ ጊዜ በ፱ ሰዓት፣ ቅዳሜ እና እሑድ በ፫ ሰዓት አንድ ዳቤ የሚሰጣቸው ሲሆን፣ በሥራ ላይ ለሚሰማሩት ግን በየቀኑ ምሳ ላይ እንጀራ ይሰጣቸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ለአብነት ተማሪዎች በቀን ሁለት ጊዜ እንጀራ ይሰጣቸዋል፡፡ መናንያኑ የሚለብሱት ሁሉም አንድ አይነት የሆነ እና በገዳሙ መናንያን ከቅጠላቅጠል በሚዘጋጅ ቀለም የሚነከር ቀይ ቡኒ ቀለም ያለው አቡጀዲ ሲሆን፤ አሰፋፉም የገዳማውያንን ሥርዓት የተከተለ ነው፡፡

፫.፭. የቅጣት ሥነ ሥርዐት

በአጋጣሚ በመናንያን መካከል አለመግባባት ቢፈጠር በራሳቸው እንዲፈቱ ይደረጋል፡፡ ነገር ግን ከገዳሙ ሥርዐት የወጣ መናኒን እንደ ጥፋቱ መጠን የተለያዩ ቅጣቶች ይሰጡታል፡፡ እነዚህም የጉልበት ሥራ (እንጨት ለቀማ፣ ፅዳት እና የመሳሰሉት)፣ ስግደት፣ በእግር ብረት መታሰር ሲሆኑ፣ ከነዚህም ቅጣቶች ጎን ለጎን ተግሣፅ እና ምክርን ያካትታል፡፡

፬. የገዳሙ አስተዳደራዊ መዋቅር

ገዳሙ መናንያን የሚመሩበት የራሱ የመተዳደሪያ የውስጥ ደንብ አለው፡፡ በመዋቅር ደረጃ ከገዳሙ አስተዳደር መምህር ጀምሮ የምርፋቅ አባቶች፣ ጸሐፊ፣ መጋቢ፣ ሒሳብ ሹም፣ ገንዘብ ያዥ፣ ኦዲተር፣ ዕቃ ግዢ ኃላፊ፣ ዕቃ ቤት ጠባቂ የሚል መዋቅር ተበጅቶለታል፡፡  የውስጥ ደንቡ የገንዘብ እና የዕቃ ወጪ አጠባበቅ፣ የገዳሙ ሥራና ሊቀ አርድዕቶች፣ ስለ ገዳሙ ፀጥታ አጠባበቅና ቅጣት፣ የአዲስ አባላት አቀባበል፣ ወደ ገዳሙ ስለሚመጡ እንግዶች፣ ስለ ሴቶች ገዳም፣ ስለ ገዳሙ አርድዕቶች፣ ስለ ሕመምተኞች፣ ደካሞችና ባሕታውያን፣ ስለ ውርስ ገንዘብ፣ ስለ ልማት፣ ስለ ትምህርት፣ ስለ መቁነንና የዓመት ልብስ፣ ስለ ስብሰባ፣ ስለ ፈቃድ፣ ስለ ጸሎተ ማኅበር፣ ስለ ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት፣ አቤቱታ ስለማቅረብ፣ ስለ ሥራና ዕቅድ ግምገማ፣ ስለ ሥራ ሪፖርት፣ ስለ ግል ቁሪት (የግል ሀብት)፣ ስለ ወንዶችና ሴቶች ገዳም ክልል፣ ስለ ገዳሙ ተጠሪነት በስፋት ያብራራል፡፡

፭. የአብነት ትምህርት ቤትና ስብከተ ወንጌል

የአብነት ትምህርት ቤቶች ለገዳማት ህልውና ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳላቸው በገዳሙ በመታመኑ ቀዳሚ ቦታም ተሰጥቶታል፡፡ የሁለት ጉባኤያት መምህራን የተቀጠሩ ሲሆን እነዚህም የአቋቋም እና የቅዳሴ መምህራን ናቸው፡፡ የቅዳሴ መምህሩ በማኅበረ ቅዱሳን አጋዥነት ከአካባቢው ሁለት ሰዎች በመላክ የደብረ አባይ ቅዳሴ አስመስክረው የመጡ ሲሆን አንደኛው በገዳሙ ወንበር ዘርግተው በርካታ የአካባቢውን ተማሪዎች እና መናንያንን እያስተማሩ ይገኛሉ፡፡ ገዳሙ እየታወቀ ሲመጣ የአቋቋም ተማሪዎችም እንደሚኖሩ ገዳሙ ተስፋ አለው፡፡ የአብነት ተማሪዎቹ ቀለብ በገዳሙ የሚሸፈን ሲሆን የማደሪያና የጉባኤ ቤት ችግር ግን አንዱ ፈተና ነው፡፡ ችግሩንም ለመፍታት ገዳሙ የተማሪዎች ማደሪያና የጉባኤ ቤት ዲዛይን ያሠራ ሲሆን በምእመናን ድጋፍም ግንባታው እንደሚሠራ ይታመናል፡፡

አንዳንድ የማኅበሩ አባላት የተሟላ ገዳማዊ ጠባይ እንዲኖረው ቅዳሜና እሑድ እንዲሁም በየዓመት በዓሉ ስብከተ ወንጌልና የመጻሕፍተ መነኰሳት ትምህርት በገዳሙ ውስጥ እንዲሰጥ ይደረጋል፡፡

 

Read 651 times