Wednesday, 07 April 2021 00:00

አባ ተከሥተ ብርሃን

Written by  ቀሲስ ዐቢይ ሙሉቀን

Overview

ልደት አባ ተከሥተ ብርሃን ከአባታቸው መልከ ጼዴቅ እና ከእናታቸው ድል በኢየሱስ በሰሜን ሸዋ አካባቢ የተወለዱ በ፲፫ኛውና በ፲፬ኛው  ክፍለ ዘመን የነበሩ አባት ናቸው። አባ ተከሥተ ብርሃን የቀድሞ ስማቸው በኪሞስ ይባል የነበረ ሲሆን የደብረ ሊባኖሱ የእጨጌ ፊልጶስ ደቀ መዝሙርም ነበሩ።  ሥርግው ሐብለ ሥላሴ ባዘጋጁት የአማርኛ የቤተ ክርስቲያን መዝገበ ቃላት ግን ልደታቸው በ፲፬ኛው ክፍለ ዘመን እንደሆነ ተጽፏል።  የአገልግሎት ሕይወት አባ ተከሥተ ብርሃን ከደብረ ሊባኖስ ገዳም ወደ ጎጃም በመሄድ፣ ወንጌልን አስተምረዋል። በዚያም ድንቅ ድንቅ ተአምራትን አድርገዋል። በርካታ ምእመናንን በማሳመንና በማጥመቅም ዕድሜያቸውን ሙሉ እግዚአብሔርን አገልግለዋል። ከደብረ ሊባኖስ ወደ ጎጃም የሄዱበት ምክንያትም ንጉሡ አፄ አምደ ጽዮን የእንጀራ እናቱን ማግባቱን እጨጌ ፊልጶስ ስለተቃወሙት እርሳቸው ማለትም አባ ተከሥተ ብርሃንም ደግሞ በወቅቱ የእጨጌ ፊልጶስ ደቀ መዝሙር ስለነበሩ የንጉሡ ሰዎች የእጨጌ ፍልጶስ ተባባሪ ናችሁ ብለው ካደረሱባቸው መከራ የተነሣ በስደት ነበር። አፄ አምደ ጽዮን መነኰሳቱን ሲያሳድዳቸው አባ ፊልጶስ አባ በኪሞስን አንተ ወደ ምድረ ጎጃም ሂድ እኔ ክፍሌ በመንዝ አካባቢ በምትገኘው ደብረ ዕንቍ ነው” ብለዋቸው ወደ ጎጃም እንዲመጡ ሆኗል።

 

አባ ተከሥተ ብርሃን ገና ደብረ ድማኅ ከመድረሳቸው በፊት በስደት እያሉ ደብረ ዕንቍ በምትባል ዋሻ ሱባዔ በመግባት የመምህራቸውን የእጅ መስቀል ለምልክት በቦታው ትተው በመምጣት በሞጣ አድርገው ወደ ዲማ በመግባት በዚያ ዐረፉ። በዚህም ቦታ በዲማ ማለት ነው ‹‹ወረከበ ዐቢየ ጾላዕተ በውስተ አሐቲ ሀገር እንተ ይእቲ ደብረ ድማኅ ይላል፤ ዲማ በምትባል ሀገር ውስጥ ትልቅ ዋሻ አገኘ።›› በዚህም ዋሻ ውስጥ በእመቤታችን ስም የተቀረፀች የሰማዕታት አለቃ ቅዱስ ጊዮርጊስ በሕይወተ ሥጋ ሳለ ‹‹ደምርኒ እሙ ምስለ ፍልሰትኪ›› እያለ ይጸልይባት የነበረችውን ታቦትና ንዋየ ቅድሳት አገኙ። በዚያም የእመቤታችንን ጽላትና ንዋየ ቅድሳቱን በክብር አስቀምጠዋል። እርሳቸውም አብረዋቸው ከሚኖሩ መንፈሳውያን ልጆቻቸው ጋር በጎጃም አውራጃ ሁሉ እየወጡና እየወረዱ ወንጌልን አስተምረዋል። 

ከዚያም በኋላ ዐፄ ሰይፈ አርዕድ ከአካባቢው ስለ አሳደዳቸው ወደ በጌ ምድር ደብረ ግሸና በመሄድ በዚያ ወንጌልን በስፋት አስተምረዋል። ከዚያም ተመልሰው ሞጣ ደብረ ጦት በቅዱስ ሚካኤል ስም ቤተ ክርስቲያን ተክለው ዘጠኝ ዓመት አስተምረዋል። በተለያዩ ቦታ እየተዘዋወሩ ተቋርጦ የነበረውን ሐዋርያዊ ሥራቸውን በመቀጠል ምእመናንን በማጥመቅ እንደ ጮለሚት ማርያም (ብቸና አካባቢ ያለች ገዳምን) መሥርተዋል። በአዴት፣ በሳርካ፣ በአመዳሚት (ወሰንአም) እየተዘዋወሩ ሌሎች አብያተ ክርስቲያናትን እያነፁ ብዙ ሕዝብ አስተምረዋል። 

አባ ተከሥተ ብርሃን ከደብረ ሊባኖስ ወደ ዲማ ገዳም በሄዱ ጊዜ በአካባቢው ትመለክ የነበረች እመ ቡላድ የምትባል ሥጋ ለባሽ ሰይጣን ነበረችና ክርስቶስን ከሰይጣን ጋር ብርሃንንም ከጨለማ ጋር አንድ የሚያደርገው ማነው? ምእመናንን ከመናፍቃን ጋር ርስተ መንግሥተ ሰማያትን የሚያካፍላቸው ማነው? እያሉ በማስተማርና በመስበክ ሥጋ ለባሽዋ ሰይጣን እመ ቡላድ የነበረችበትን በረሃ የቅዱሳን ቦታ አደደረጉት። ክርስቶስ ባደረበት ሰይጣን፣ ብርሃን ባለበትም ጨለማ ሊኖር እንደ ማይችል ሁሉ ምእመናንም ባሉበት መናፍቃን ሊኖሩ አይችሉም በማለት ያችን ሥጋን የለበሰች ሰይጣን (እመ ቡላድ) በእግዚአብሔር ቸርነት ቀድሞ የግብር አባቷ ሳጥናኤል ከኢየሩሳሌም ሰማያዊት ተወርውሮ በተጣለበትና ድል በተነሣበት የብርሃን መስቀላቸው ከአካባቢው አስወጥተው እስከ ካራ ተራራ ድረስ (ዝሪም ይሉታል አዊ ሀገረ ስብከት ይገኛል) አባረዋታል። ከዚያም አልፎ እስከ ምድረ ሱዳን ሊያባርሯት ሲሉ እኔ የቤት እመቤት ‹‹ስሜ ማርያም›› ይባላል እያለች ሕዝቡን አሳተቻቸው። በዚህ ጊዜም ሕዝቡ የአባ ተከሥተ ብርሃንን ትምህርት መስማት ሲገባው የእሷን ነገር ተቀብሎ እኛ እንቀበላታለን ብሎ መልሷቸዋል። 

በዚሁ በአዊ አካባቢ ቡላድን ሲያባርሩ ያዩ ሰዎች እንዳያባሯት አንድ አርሶ አደር አባ ተከሥተ ብርሃንን በጅራፍ ገርፎ ሲያባርራቸው እሳቸውም ‹‹ተው ይህቺን ሰይጣን ላስወጣልህ እስከ ልጅ ልጆችህ ድረስ ስትገዛህ ትኖራለች›› ብለው ቢለምኑት ‹‹የለም እመቤቴንማ አላስወጣትም›› አላቸው። እሳቸውም በአካባቢ ያለውን ሕዝብ በማስተማር ወደ በአታቸው ዲማ ሲመለሱ ጉታ፣ ሜጫ፣ መርአዊ የሚባሉ አካባቢዎችን ሰብከዋል። ያቺ ቡላድ ዛር (ሰይጣን) ግን በአንዳንድ አካባቢዎች እስከ አሁን ድረስ እየተመለከች ትገኛለች። 

አባ ተከሥተ ብርሃን በደብረ ድማኅ እንዲህ ባለ ሐዋርያዊ አገልግሎት ወንጌልን በመስበክ እግዚአብሔርን ሲያገለግሉ ኖረዋል። በበአታቸው በዚሁ በደብረ ድማኅ በነበራቸው የ፲፭ ዓመታት አገልግሎትም ገዳሙን አጠናክረዋል። አባታችን በዚህ በአቋቋሙት ገዳም ወንዶች ከገዳሙ በስተምሥራቅ ሴቶች ደግሞ በስተምዕራብ አቅጣጫ መኖሪያቸውን አድርገው በአንድ በር እየገቡ በአንድ አዳራሽ እየተሰበሰቡ እንደ ማዕረጋቸው በቆብና በአስኬማ ተወስነው እየኖሩ የዕለት ምግባቸውን እንዲመገቡ የሚያደርገውን ሥርዐትም የሠሩት አባታችን አባ ተከሥተ ብርሃን ናቸው። 

አባ ተከሥተ ብርሃን ይህንን ሥርዓተ ምንኵስና ሠርተው ገዳም መሥርተው በገዳሙ ለ፲፭ ዓመታት በመንፈሳዊ ተጋድሎ መኖራቸውን ንጉሡ ዐፄ ዳዊት (፲፫፻፹-፲፬፻፲፪) ሰምቶ በመምጣት ዛሬ ገድእና ዝያ በሚባሉ ወንዞች መካከል ያለውን ርስት በጉልትነት በመስጠት በ፲፫፻፸፱ ዓ.ም አካባቢ ገዳሙን አጽንቶታል። ይህ የርስት ጉልት ቦታ በአሁኑ ጊዜ ተቆራርጦና ለኗሪው ተሰጥቶ የገዳሙ መሬት በጣም የተወሰነ ሁኗል። በእርግጥ ገዳሙ በፍጹም የለውም ባይባልም አስቀድሞ ከተሰጠው ይዞታ አንጻር ግን እጅግ የተወሰነና ይህን ያህላል የሚባል አይደለም።

ሥርግው ሐብለ ሥላሴ ባዘጋጁት የአማርኛ የቤተ ክርስቲያን መዝገበ ቃላት እንዲህ የሚል መረጃ ተጽፎ ይገኛል። 

አባ ተከሥተ ብርሃን ትሩፋታቸውና ገድላቸው ብዙ ነው። ከዚህም ውስጥ በጎጃም ክፍለ ሀገር እየተዘዋወሩ ብዙ አብያተ ክርስቲያናትን ተክለዋል። ከነዚህም ጥቂቶችን ለመጥቀስ ያህል ፩ኛ. ለመጀመሪያ ጊዜ ቀዳሚት ማርያም በዲማ፣ ፪ኛ ሞጣ ደብረ ሚካኤል፣ ፫ኛ ቢቸና ጨለሚት ማርያም ተጠቃሾች ናቸው። ከእነዚህም ሌላ ብዙ አብያተ ክርስቲያናትን አስተክለዋል። 

ከዚህ በኋላ የእግዚአብሔር መንፈስ አነሣሣቸውና ወደ ትግራይ ክፍለ ሀገር ሄደው በአድያቦ አውራጃ እየተዘዋወሩ ነገደ ኩናማዎችን አስተምረውና አሳምነው አጥምቀዋል። በአክሱም ጽዮን ንቡረ እድነት ተሹመው ጥንታዊት ጽዮንን አገልግለዋል። (የአማርኛ የቤተ ክርስቲያን መዝገበ ቃላት ገጽ ፺፱-፻፩)

በአገልግሎት ዘመናቸው የደረሰባቸው መከራ

አባ ተከሥተ ብርሃን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ስብከቱ ‹‹ሊከተለኝ የሚወድ ሰው ራሱን ይካድ ጨክኖም የሞቱን መስቀል ተሸክሞ ዕለት ዕለትም ይከተለኝ›› (ሉቃ. ፱፥፳፫) በማለት ያስተማረውን ትምህርት በተግባር የፈጸሙና መልካሙን ገድል የተጋደሉ አባት ናቸው። ከበአታቸው ሁለት ሦስት ጊዜ ተሰደዋል፤ በሰዎች ተደብድበዋል፤ በዙ መከራና እንግልት ደርሶባቸዋል። ለማሳያ ያህልም በዚያን ዘመን ንጉሡ ዐፄ አምደ ጽዮን ብዙ ውጊያዎችን ከአረማውያን ጋር በማድረጉ ከእነርሱ የተማራቸው ብዙ ባህሎች ነበሩት። በዚህ ምክንያት የእንጀራ እናቱን እስከ ማግባት ደረሰ። ያን ጊዜ ዮሐንስ መጥምቅ ሄሮድስን እንደተቃወመው የደብረ ሊባኖሱ ፫ኛ እጨጌ አባ ፊልጶስ ፊት ለፊት ተቃወሙት። 

ንጉሡም ከስሕተቱ ከመመለስ ይልቅ እጨጌ አባ ፊልጶስን ወንጂ በተባለ ከተማቸው ደማቸው እንደ ውኃ እስኪወርድ ድረስ አስደብድቦ ወደ ትግራይ አጋዛቸው። በዚህም የተነሣ ከእርሳቸው ጋር ተባብራችኋል ተብለው አባ ተከሥተ ብርሃንም ተጋዙ። ለሁለተኛ ጊዜ ዐፄ ሰይፈ አርዕድ ከበአታቸው አሳድዷቸው በበጌምድር ደብረ ግሸና ተቀምጠዋል።

የአደረጓቸው ተአምራት

አባ ተከሥተ ብርሃን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ስብከቱ “ እውነት እውነት እላችኋለሁ በእኔ የሚያምን እኔ የምሠራውን ሥራ እርሱም ይሠራል፤ ከዚያም የሚበልጥ ይሠራል” (ዮሐ.፲፬፥፲፪) በማለት እንደተናገረ በርካታ ተአምራትን አድርገዋል። ከእነዚህም ውስጥ አንዱ እመ ቡላድን ከአካባቢው ማባረራቸው ነው። ከላይም እንደተገለጸው ይህቺ እመ ቡላድ የምትባለው ሥጋን የለበሰች ጋኔን  እየተገለጸች ልጃችሁን አሳድጋለሁ የተገዛ ከብታችሁን አረባለሁ፤ ቤታችሁንም እጠብቃለሁ እያለች ሕዝብን የምታስት ስትሆን ከዚህም የተነሣ በአካባቢው ሕዝብ ትመለክ ነበር። እርሷም ከገዳሙ በስተምዕራብ ጥልቀቱ ፭፻ ሜትር በሚሆን ገደል ላይ ተሠውራ ሰዎችን ስታስትና ስታስጨንቅ እስከ አባ ተከሥተ ብርሃን መምጣት ድረስ ቆይታለች። በዚያ በረዥም ገደል ላይ ተሠውራ ሕዝቡን ስታስት አባታችን አባ ተከሥተ ብርሃንም በበትር እየደበደቡ ከአካባቢው አስወጥተው አባረዋታል። 

ሁለተኛው ደግሞ ከዕለታት አንድ ቀን በጎጃም ክፍለ ሀገር ይኸውም እነሴና እነብሴ በሚባለው አካባቢ በሚገኘው ነድ አጹራ ማርያም በሚባለው ቦታ ያሉ ሰዎች የእጁን ተዓምራት የቃሉን ትምህርት ሰምተው ከማመናቸው የተነሣ በአንድ ቀን ፺፻፱፻፺፱ (ዘጠኝ ሺህ ዘጠኝ መቶ ዘጠና ዘጠኝ) ሕዝብ በማጥመቃቸውና ሕዝቡን ሳያቈርቡት ቀኑ መሽቶ ስለነበረ ብርሃን ስለወረደላቸው አባ ተከሥተ ብርሃን የሚል ስም ተሰጥቷቸዋል።

 የተሰጣቸው ቃል ኪዳን

አባ ተከሥተ ብርሃን እግዚአብሔር አምላክ በነቢዩ በዳዊት ላይ አድሮ “ከመረጥኋቸው ጋር ቃል ኪዳን አደረግሁ” (መዝ.፹፰፥፫) በማለት እንደተናገረ ጽኑ የሆነ ቃል ኪዳን ገብቶላቸዋል። ከገባላቸው ቃል ኪዳንም መካከል  እመ ቡላድን ከአካባቢው ከአስወጡበት ጊዜ ጀምሮ በአማላጅነታቸው አምኖ ጸሎት ላደረገ ሁሉ የልቡ መሻት እንደሚፈጸምለት፣ የታመመም ከደዌው እንደሚፈወስ ከተገባላቸው ቃል ኪዳኖች መካከል አንዱ ነው። እስከ ዛሬ ድረስም በተሰጣቸው ቃል ኪዳን አምነው ከአራቱም ማዕዘን የሚመጡ ሕሙማን ይልቁንም በእመ ቡላድ ስም ታመው የሚመጡት ሁሉ ገድላቸው እየተነበበላቸው ጠበላቸውን እየጠጡ እየተፈወሱ የሚሄዱ ሆነዋል። በስማቸው በፈለቀው ጠበልም በርካታ በሽተኞች በተለይም በእመ ቡላድ የሚሠቃዩት ይፈወሱበታል።  

ዳግመኛም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደመና ተገልጾ ጎጃምን ከዐባይ እስከ ዐባይ ታስተምር ዘንድ የመጀመሪያ አዲስ ሐዋርያ አድርጌሃለሁ ብሏቸዋል። በኋላኛው ዘመን መናፍቃን ይነሣሉ። ነገር ግን መካነ ዕረፍትህ የምትሆን ደብረ ድማኅን እስከ ዕለተ ምጽአት ድረስ የመናፍቃን እግር አይረግጧትም። ቢረግጧትም አያድሩባትም ብሎ ቃል ኪዳን ሰጥቷቸዋል። ይኸውም ሊታወቅ ከእርሳቸው ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ በእግዚአብሔር ቸርነት በሊቃውንት ብርታት ከደብረ ድማኅ የምንፍቅና ትምህርትም ሆነ እግረ ፍለጋቸው እንዳልደረሰ በቦታው የሚገኙ ሊቃውንትና ምእመናን ምስክር ናቸው። 

ዕረፍት

አባ ተከሥተ ብርሃን እንዲህ ባለ መንፈሳዊ አገልግሎት በበአታቸው ደብረ ድማኅ በሌሎችም አካባቢዎች ሁሉ እየተዘዋወሩ እግዚአብሔርን ሲያገለግሉ  ከኖሩ በኋላ በመጨረሻም ጊዜ ዕረፍታቸው እንደ ደረሰ ከእግዚአብሔር የተላከ መልአክ ነግሯቸው እግዚአብሔር አምላክም ለቅዱሳኑን የሚሰጠውን ቃል ኪዳን ሰጧቸው መጋቢት ፲ ቀን በሰላም ዐርፈዋል። ዕረፍታቸው እንደታወቀም ሱባኤ ይይዙበት በነበረው ዋሻ ውስጥ ተቀበሩ። በዓለ ዕረፍታቸውም በደብረ ድማኅ በየዓመቱ መጋቢት ዐሥር ቀን ይከበራል።

  

(ምንጭ በገዳሙ የተዘጋጀ የዲማ ቅዱስ ጊዮርጊስ አጭር ታሪክ እና ሥርግው ሐብለ ሥላሴ ያዘጋጁ የአማርኛ የቤተ ክርስቲያን መዝገበ ቃላት)

 

Read 792 times