Friday, 04 September 2020 00:00

ነፍሴን የት ልውሰዳት? 

Written by  ዲ/ን አሸናፊ ደሳለኝ

Overview

  “አጥብቄ ፈለግሁ . . . ደከምሁ፤ እጅግም ባዘንሁ፤ ዙሪያ ገባውን ሁሉ እየቃኘሁ የዓለምን ዳርቻዎች ሁሉ አማተርሁ፤ . . . ነገር ግን ነፍሴን እፎይ ብየ አሳርፋት ዘንድ እሸሸግበት ጥግ አጣሁ የደከመ መንፈሴን ሰላም አሰፍንበት ዘንድ ማረፊያ ወደብ አጣሁ . . አዎ እጅግ ባተትሁ ነፍሴን ከደካማው ሥጋየ እሥር አላቅቄ ነጻነትን አጎናጽፋት ዘንድ  ማረፊያው የሥጋ ሸክም ማራገፊያው ከቶ ወዴት ነው? “ሰው ዓለምን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱን ግን ቢያጎድል ምን ይጠቅመዋል” (ማር. ፰፥፴፮) እንዲል ቅዱስ መጽሐፍ በዚህ ምድራዊ ዓለም የሚዳሰስ፣ የሚላስ፣ የሚቀመስ ይጣፍጥ ዘንድ ግን ከቶ በማይቻለው የዓለም ግሳንግስ የተወረረችና ዝላ የደከመች ነፍሴን ምኞት፣ ዝሙትና ፍቅረ ንዋይ የተሰኙ  ወንበዴዎች ደብድበው ያቆሰሏትን ድኩም ነፍሴን ዘይቱን አፍስሶ ቁስሌን ወደሚያክምልኝ ያ ደግና ርኅሩኅ ሳምራዊ  አደርሳት ዘንድ ከቶ የት ልሂድ፡፡” (ሉቃ. ፲፥፴፫) እያሉ አባ ሞገሴ ረዘም ባለ ንግግራቸው ድምፃቸውን ጎላ አድርገው ያወራሉ፡፡  አባ ሞገሴ ከሰው ጋር ያሉ መስሎኝ ትቻቸው ልሄድ ስል ብቻቸውን ናቸው። አመማቸው እንዴ ብየ ልጠይቃቸው ስል ዐይናቸውን ወደሰማይ ቀና አድርገው ከነበሩበት ስሜት ማንም የሚያናውጻቸው ያለ አይመስልም። አባ ሞገሴ በአንድ ታዋቂና ታላቅ ደብር ጸሎት  አሳራጊ አባት ናቸው። በዚህ ታላቅ ደብር ቄሰ ገበዝ ሆነው  ለረጅም ጊዜ ካገለገሉ በኋላ የጸሎት አሳራጊ አባት እንዲሆኑ በካህናቱ ፈቃድ ከሰሞነኛነት ተለይተው የሚኖሩ አባት ናቸው። ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ቅዱስ አባት ለአርባ ዓመት ቆመው የጸለዩበት ቦታ ነው ከሚባል ጫካ ቆመው እየጸለዩ ነው። እኔም ስሜታቸውን ከምረብሽ በጽሞና ማዳመጡና ከጸሎታቸው በረከት መቀበሉ የተሻለ ነው ብየ ማዳመጥ ጀመርሁ። አባ ከብሉያት ከሐዲሳት እየጠቃቀሱ ልመናቸውን ቀጠሉ።

 

ሰው መሆንን እና የሰውነትን ልክ በሚበላና በሚጠጣ በሚግብሰበስ ከንቱና ሕይወት የለሽ በድን በሆነ መስፈሪያ የሚመዝን ዓለም የታከተች ብኩን ነፍሴን አሳርፋት፤ ሰላም እሰጣት ዘንድ የት ልሂድ የት ልድረስ ፡፡ ታላቁን ቅዱስ መጽሐፍ ባገላበጥሁ ጊዜ እናንተ “ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም አሳርፋችኋለሁ . . .  . ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ” (ማቴ፲፩፥፳፰-፳፱) ያለውን መንፈስን የሚያድስ ልብን የሚያበረታ ቅዱስ ቃል ዓይኖቼ ተመለከቱ ትንሽ አለፍ ብየ ቅዱሱን መጽሐፍ በትኩረት ሳገላብጥ ሌላ ለጥያቄየ ምላሽ ፍንጭ የሚሆነኝን አጽናኝ ቅዱስ ቃል አስተዋልኩ “ሰላምን እተዉላችኋለሁ፡ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ። እኔ የምሰጣችሁ ዓለም እንደሚሰጣችሁ አይደለም” (ዮሐ.፲፬፥፳፯)፡፡  እያሉ ከእግዚአብሔር ጋር ያላቸውን የቅርብ ግንኙነት ስሰማ እኔም ወደ ኅሊናየ ተመለስሁ።

በዚህ ጊዜ ልቤ ሐሤት አደረገች መንፈሴም ደስታን ተመላ . . . ያች ከዐሥራ ሁለት ዓመት ጀምሮ ደም ይፈሳት የነበረች ሴት (ማቴ.፮፥፲፪) የጌታችንን የልብሱን ዘርፍ ስትዳስስ የተሰማት ዓይነት የፈወስ ተስፋ በውስጤ ለመለመ ደግሞም እንደ ሳምራዊቷ ሴት (የሐ. ፬፥፱) የማውቀውን ታሪኬን ነግሮኝ ለዘለዓለም እንዳልጠማ የሚያደርገኝን የነፍሴን እረፍት እንዳገኘሁት ተሰማኝ እናማ የእርሱን የአምላኬን የጌታየንና መድኃኒቴን ጥሪ ተቀብየ የከበደ ሸክሜን አራግፌ ዓለም እንደሚሰጠኝ ያልሆነውን የዘለዓለም ጥማቴን የሚያስወግድልኝን እረፍት አገኝ ዘንድ “ወደ እግዚአብሔር ቤት እንሂድ ባሉኝ ጊዜ ደስ አለኝ” (መዝ. ፻፳፩፥፩) እንዲል መዝሙረኛው ቅዱስ ዳዊት ማለዳ በትጋት ተነሥቼ የክርስቶስ ሙሽራ፤ የክርስቶስ አካል (ፊል. ፬፥፲፭) ክርስቶስ በገዛ ደሙ የዋጃት (ሐዋ. ፳፥፳፰) የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ የድሆች መጠጊያ ወደ ሆነች ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በፍቅር ገሰገስሁ፡፡  

እናም በዚህ ልዩ ቀን እግሮቸ በተስፋ ከቤቴ ደጅ ተነሥተው የማለዳውን ፀጥታና ሰላም እያጣጣሙ “ቅረቡ ኀቤሁ ወያበርህ ለክሙ ወኢይትኃፈር ገጽክሙ ወደ እርሱ ቅረቡ ያበራላችሁማል ፊታችሁም አያፍርም ይህ ችግረኛ ጮኸ እግዚአብሔርም ሰማው፤ ከመከራውም ሁሉ አዳነው” (መዝ. ፴፫፥ ፭) የሚለውን የቅዱስ ዳዊት ድንቅ መዝሙር በውስጤ እያዜምኩ ነፍሴን አሳርፋት ዘንድ በፍቅር እየተራመድኩ ወደ ቅዱስ ደጁ አመራሁ፡፡ እውነት እላችኋለሁ በማለዳ ከእንቅልፍ ድካም ተገላግለው በፀጥታው ጎዳና ወደ ደጀ ሰላሙ ሲያመሩ ያለው ጣዕም ያለው መንፈሳዊ እርካታ ከኅሊና በላይ ነው ፡፡

ወደ ቤተ ክርስቲያኑ ቅጽር አቅራቢያ በደረስኩ ጊዜ ኃጢአቴን እያሰብኩ ለመጸጸት . . . ልቤን አሰናዳሁ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ልዩ ሰማያዊ መዓዛ ለመመሰጥ ደካማ  ሥጋየን ጎስሜ እንግዲህ እግዚአብሔርን እሽ በሉት፤ ሰይጣንን ግን እንቢ በሉት፤ ከእናንተም ይሸሻል እግዚአብሔርን ቅረቡት ይቀርባችሁማል ተብሎ እንደተጻፈ ጥንተ ጠላቴን  እንቢ ብየ በተመስጦ ገሰገስኩ . . .  ያን ዕለት ደስታ ውስጤን እያረሰረሰኝ ነበር  . . . ሄደኩ ተራመድኩ ፡፡

ነገር ግን ምን ዋጋ አለው የካራን ኑሮየን ትቼ የሲናን በርሃ አቋርጨ ጉዞየን ፈጽሜ የተስፋይቱን ምድረ ከነዓንን  ሳልረግጥ . . . አንድ አስደንጋጭ ጆሮን በመውጋት  የሚያሳቅቅና ልብን  የሚያሰበረግግ ድምፅ ወደ ጆሮየ ገባ “ጧፍ ጧፍ . . . ሻማ፣ ነጠላ፣ ድስት፣ ብረት ድስት  በርካሽ ዋጋ  ይዉሰዱ … ቄጤማ ቄጤማ፣ ከኢየሩሳሌም የመጣች  ልዩ መስቀል በአባቶች የተባረከ. . . ወ ዘ ተ::”  

በዚችው ቅጽበት ከነፍሴ ተፋትቼ ከከንቱ ሥጋዬ ጋር በድጋሜ ጋብቻ ፈጸምኩ፤ እናማ በልቡናዬ ሐሳብ ማውጠንጠን ጀመርሁ “አወ ስመለስ ቄጤማ እገዛና በጠዋት ቤቴን አጫጭሸ ሞቅ ሞቅ አድርጌ ቡናየን አፍልቼ ከጎረቤቶቼ ጋር ፈታ እላለሁ . .  .”  ብቻ ምን አለፋቹህ በዚያች ቅጽበት ከሰማያዊው ከፍታ ማማ እራሴን አውርጄ ስለ ማኅበራዊና ሥጋዊ ሕይወቴ ማሰላሰል እየጀመርሁ ዐውድ እየቀያየርሁ ከነፍሴ ተፋታሁ ዴማስን ሆነኩና የተሰሎንቄ ውበት ሳበኝ። ወደ ኋላ ዞሬ መንፈሳዊ የሕይወት ጉዞየ ተሰናክሎ የጨዉ ሐውልት ሆኜ ቀረሁ። 

 ትንሽ ከደካማው የሐሳብ ጉዞየ መለስ ስል ለካንስ ምእመናን “ለእግዚአብሔር በፍርሃት ስገዱ” ያለውን የሠራዒ ዲየቆኑን አዋጅ ሰምተው በፍርሃት ሰግደዋል . . . እግሮቼም እኔ ልብ ሳልላቸው ወደ ቤተ ክርስቲያኑ ቅጽር ዘልቀው ገብተዋል . . . በድርጊቴ በጣም ተሳቀቅኩ አፈርኩ ተሸማቀቅሁ  .  .  . እናም ከምእመናን ጋር ለመመሳሰል በአምልኮ እሰግድ ዘንድ  ጉልበቴን ሸብረክ ሳደርግ ምእመናን ሁሉ ከሰገዱበት “ተንሥኡ” ተብለው እየተነሡ ነበር፡፡ ከትንሽ የአስተውሎትና የተመስጦ ጊዜ በኋላ ይህ ከንቱ መርጦ አድማጭ ጆሮየ ተምዘግዝጎ ከደጀ ሰላሙ ቅጽር ግቢ አፈትልኮ ወጣ . . .ሄደ.. ገሰገሰ ወደ ኋላ ነጎደ . . . ለካስ የዓለም ሁካታ ሲከንፍ ከጀርባየ ተከትሎኛል . . .  አቤት . . የድምፁ መረበሽ  ቀጠለ ጫጫታው “የጭንቅ ደራሿ ማሠሪያ ነው  አምስት ዐሥር ያላቹህን …..የፈጥኖ ደራሹ  … ጣሪያው እያፈሰሰ ነው። ዐሥር ሺህ ብር ትኬቱን ለበረከት . . ወንድማችን እገሌ …በኩላሊት በሽታ ….ወደ ውጭ ሀገር ሂዶ እንዲታከም. . . ጧፍ በአንድ ብር በአንድ ብር: ልዩ ሎተሪ በጊዮርጊስ ቀን የሚወጣ፣ ትሪ፣ ሳሃን፣ ብረት ድስትም፣ አለ ወ ዘ ተ  ወ ዘ ተ”  ውይ …ሲያደክም  ተደበላለቀብኝ የትኛውን ትቼ የተኛውን እንደምሰማ ግራ ግብት አለኝ  ነፍሴን . . . እረሳኋት. . . . ተውኳት ጭራሽ ተሰናበትኳት . . .  በድንገት ስልኬን አወጣሁ፤ ሰዓቴንም በፍጥነት ተመለከትኩ፤  ሰዓቱ ሂዷል ራሴን ስለነፍሴ ሳይሆን ሰለ ሰዓቱ መሄድ ሲጨነቅ አገኘሁት …ይሄኔ ታዴያ ራሴን ታዘብኩት በመንፈስ ሳይሆን በሥጋ እንደነበርኩ ታወቀኝ፡፡

የሥርዓተ ቅዳሴውን መጠናቀቅ ሳይሆን የሰዓቴን ጉዳይ አስቀድሜ  ቅዱሱን ደጀ ሰላም በድፍረት ረጋግጨ በምእመናንና በቅዱሳን መላእክት ላይ ተረማምጀ ስከንፍና ስክለፈለፍ ወጣሁ . . . ከውስጥ ጆሮየን መስጦ ሲጠራኝ  ወደ ነበረው ጎትቶ ወደ አስወጣኝ ሁካታ በፍጥነት ተቀላቀልኩ …. የሥጋ ስሜቴን በመንፈሳዊ ገበያ ሸመትኩ …. ይህ ሁሉ ሁኖ ግን ነፍሴ አላረፈችምና ሰላም አላገኘሁም  . . .እንደገና ተጨነኩ እንደገና ውጥረትና መረበሽ  . . . ነፍሴ ታርፍ ዘንድ እድሉን የዕለት ቀለቧን የዘመናት ምግቧን ቃለ እግዚአብሔርን ታገኝ ዘንድ አለፈቀድኩላትምና ዕረፍት አላገኘችም ።

መለስ ብየ የአባ ሞገስን ተመስጦ አስተዋልኩ። ዕድሜ ልካቸውን በአገልግሎት ተጠምደው ኑረው አሁን ደግሞ የጸሎት ጊዜ ሲያገኙ ራሳቸውን እንደ ፍጹም ኃጢአተኛ ቆጥረው ማረኝ ማረኝ ይላሉ። እኔ ግን በአግባቡ ቅዳሴ ለማስቀደስ እንኳን አልበቃሁም። የአባ ሞገስን ጽናት እንደሳቸው ለመሆን ባልችልም ወደ እርሳቸው ሕይወት የሚወስደኝን መንገድ የሚዘጉብኝን ምክንያቶች እያሰብኩ እንዲህ ማለት ጀመርሁ። ደግሜ ደጋግሜ እጠይቃለሁ ዕረፍት ታገኝ ዘንድ ነፍሴን የት ልውሰዳት ፤ የነፍሴ ማረፊያ የልቤን ሰላም ሳዝን መጽናኛየን “ኢትግበሩ ቤተ አቡየ ቤተ ምስያጥ” (ማቴ. ፳፩፥፲፫) የተባለላትን እናቴን ቅድስት ቤተ ክርስትያንን የመሸጫ የመለወጫ የሌባና የቀማኛ ዋሻ ልታደርጉ በዙሪያዋ የከበባችሁ መንፈስ አልባ  ሥጋ ለባሶች  ከሰማያዊነቴ አርማና ምስከር ከቅድስት ቤተ ክርስትያን ትርቁ ዘንድ እለምናችኋለሁ።

አጥንትን የሚያለመልመውን ልቡናን  የሚመስጠውን ሰማያዊውን የቅዱስ ያሬድን ጥዑም ዜማ አፍናችሁ የምሕረቱን ዐውድ በገንዘብ ጉዳይና ጨረታ የከፈታችሁ የሥጋ ጠበቆች ከነፍሴ መሸሸጊያ ከማረፊያ ወደቤ ወግዱልኝ፡፡  “እስመ ቅንዓተ ቤትከ በልዓኒ ትዕይርቶሙ ለእለ ይትኤየሩከ ወድቀ ላዕሌየ  የቤትህ ቅናት በለታኛለችና የሚሰድቡህም ስድብ በላየ ወድቋል” (መዝ. ፷፰፥፱) እንዲል መዝሙረኛው ቅዱስ ዳዊት አቤቱ  የቤትህ ቅናት አቃጥሎኛል  ነፍሴን ታሳርፋት ዘንድ ጅራፍ አንስተህ ሻጭና ለዋጮችን ከቤተ ክርስቲያን፣ ማደሪያህ ከሆነው ቤተ መቅደስ ከተባለው እኔነቴ ደግሞ ከንቱ ዓለማዊ ሐሳብን አርቀህልኝ ትንሣኤ ልቡናን አድለህኝ  ምክንያተኝነቴንና ሰበበኝነቴን አሸቀንጥሬ ጥየ  የነፍሴን ዕረፍት አፋጥን ዘንድ ጣቶችን ወደ ሌሎች መቀሰር ብቻ ሳይሆን ወደ ራሴም ተመልክቼ በመንፈስ እበረታ ዘንድ እርዳኝ፡፡ የነፍስ ዕረፍት ከልቡና ከሐሳብ ይጀምራልና  ልቡናየን በምሕረት ከወደቀበት ታነሣልኝ ዘንድ እለምንሃልሁ አዎ ያኔ ነፍሴ ማረፊዋን ታገኛለች ፡፡

 

 

 

Read 1463 times