Wednesday, 28 April 2021 00:00

የፍስክ ብፌ

Written by  በደመላሽ ኃ/ማርያም

Overview

ብዙ ተማሪ ሲተራመስበት የነበረው ትምህርት ቤት ተማሪዎቹን በሆዱ ከቶ ጭጭ ብሏል፡፡ እስከ መጨረሻው ክፍት ብሎ የነበረው በር የሚያስፈልገውን ያክል ተማሪ ከቶ ተዘግቷል፡፡ ከአርፋጅ ተማሪዎች ጋር ሲሯሯጡ የነበሩት ዩኒት ሊደርና ጥበቃዎች እፎይ ብለዋል፡፡ ጥበቃው አለሁ ለማለት ያህል ትልቁን የወታደር ከስክስ ጫማቸውን በከፊል ከውጭ አድርገው ጋደም ብለዋል፡፡ ለዐይነት ያህል የተማሪዎቹን ጫጫታ ለመርሳት በብዛት እሽ የምትል ሬዲዮናቸውን ከጆሯቸው አፋፍ አስቀምጠው ይሰማሉ፡፡ ዩኒት ሊደሩ የብዙ ሴትና ወንድ ተማሪዎችን መቀመጫ የቸበቸበች አርጩሜያቸውን ጥለው ጣታቸውን ለብዕር ሰጥተዋል፡፡ ቅጥር ግቢው ውስጥ በየክፍሉ ዕወቀትን ለማጋባት ከሚውተረተሩት መምህራን ድምፅ ውጪ ዝም ብሏል፡፡        ሰሙነ ሕማማት በመሆኑና ኮሮና ቫይረስም በጋራ አልያችሁ ስላለ የከተማው ሰው ራሱን ከችግር ለመከላከል ከቤቱ ከቷል፡፡ ገሚሱ ከበሽታ ሽሽት፤ ገሚሱ ሥጋውን እየጎሰመ ፈጣሪውን ይቅር በለኝ ብሎ በስግደትና በጾም ለመለመን፡፡ በዚህ መካከል ታዲያ እውነትም የቫይረሱን አደገኛነት እና ገዳይነት ካልተረዱ ወጣቶች ውጪ እምብዛም የሰው ትርምስ አይታይም፡፡ 

 

ከሥራ መልስ አንድ ሁለት ብለው የሚገቡትም ባለትዳሮች ደረስኩ ደረስኩ እያለ በመጣው የትንሣኤ ወጪ ‹‹ቀሪ ሒሳብዎት አነስተኛ ነው፡፡ እባክዎን ከቤት ከመውጣትዎ በፊት ትንሽ ገንዘብ ይያዙ›› ብሎ መልእክት የሚያስተላልፍ የመሰላቸውን የኪስ ቦርሳቸውን አኩርፈው ቤት ውለዋል፡፡ ኑሮው ጣሪያ በመንካቱ ገና ዶሮና በጉ ሳይገዛ በጤፍና በሽንኩርት የአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ጎጆ ተፈትኗል፡፡ በዚህ ምክንያት “ሥጋ ድሮ ይበላ ነበር!” ብለን ለመተረክ እንዳንበቃ የሚሰጉም ጥቂቶች አልነበሩም፡፡ 

‹‹እኔ እምልህ ምነው ዛሬ በጊዜ ገባህ? አጣጮችህ በጠቅላላ ለሕማማቱ ገዳም ገቡ ወይስ መጨለጫችሁ ተዘጋ?›› አለች ወይዘሮ መሠረት ከሥራ ስትገባ ባሉዋ ያለወትሮው ቤቱ በጊዜ መግባቱ ገርሟት፡፡

‹‹እንዴ ምን ማለት ነው? አባወራ ቤቱ በጊዜ መግባት ነውር ሆነ እንዴ? … ወይስ እናንተ የከተማ ሴቶች ባል በጊዜ ሲገባ ያስጠላችኋል? አይዞሽ ቢራ ቢራ የሚል ትንፋሼን ናፍቀሽ ከሆነ ትንሽ ቀን ታገሽኝ እንጂ ጨልጨልሽ እመጣለሁ››

‹‹አ አ!! ደግሞ በአልኮል የተሟሸ ትንፋሽ ምኑ ይናፍቃል … ግዴታ ሆኖብኝ እንጂ አፍህን እዛው የጠጣህበት አስቀምጠህ ብትመጣ እንዴት በወደድኩህ … ግን አይቻልም ደግሞ ተቀያይሮ የባሰ ቢመጣ ምን ይውጠኛል!››

‹‹አቤት አቤት በእኔ በባልሽ የተጋባብሽን ሱስ በቀጥታ ላለማውራት “ዓሳ በለው በለው” ትጫወቻለሽ … ምን አለፋሽ ሚስቴ … ከኔ ባልተናነሰ አንቺም እራስሽ የቢራ ሱስ አናውዞሻል››

‹‹እኔ ልጅት አይነካካኝም … የማን ልጅ መሰልኩሀ … ጉሮሮዬን ከማንጎና ከብርቱካን ጁስ ውጪ ነክቶት እንደማያውቅ ታውቃለህ … ምን ያደርጋል አንተን ጠጃም ባል ካገባው በኋላ ጁስ በሥዕል እንጂ በግብሩ አጣሁት፡፡››

‹‹እሺ የኢትፍሩት ብቸኛ ልጅ  ያለ ጁስ ምንም ሳይቀምስ ያደገ ቁንጅናን ነዋ በቢራ አየር የምበክለው … ይቅርታ የኔ ሚስት … አሁን ይልቅስ ደሞዜም እንደምታውቂው ገና የቅርጫውን እንኳን ሳልከፍል ብን ብሏል፡፡ ሁለት መቶ ብር ስጪኝና አባሪኝ?››

‹‹ይኸው የጠረጠርኩት መች ቀረ! … ገብቶህ የአባወራነት ክብርን ናፍቀህ ሳይሆን ማጣት ጓዳኛው አርጎህ በጊዜ እንዳስገባህ መች አጥቼው … ለማንኛውም ለበዓል የምናወጣው ሁለታችንም መሰለኝ እንኳን ሁለት መቶ ብር ቤሳ ቤስቲን የለኝም! … ደግሞስ ምን አለ አሁን እንኳን በሕማማቱ መጠጣት ቢቀርብህ … ልጅ አይደለህ ምን አለ ትንሽ ብታሰተውል›› አለችው ነጠላዋን ከቁም ሳጥኗ አውጥታ ለመልበስ ሥራዋን ሳታቆም፡፡

“መቼ ጾሜ የማቀውን ነው ሚስቴ … ዛሬ ደርሰሽ ቄስ ልታደርጊኝ የምትሞክሪው?”

“ኧረ ባክህ አንተ ሰውዬ ቀዝቀዝ በል፡፡ እንዴ ነገረ ሥራህን እኮ ሲያዩት ገና የሃያ ዓመት ጎረምሳ ነው የምትመስለው፡፡ ትልቅነትህን አትዘንጋ እንጂ … ለስሙ ኦርቶዶክስ ነህ ግን ሕፃናት እንኳን ሊጾሙት የሚገባውን የአዋጅ ጾም አትጾምም፡፡” አለች ምርር ብሏት ነጠላዋን እያራገፈች

“ያለመደብኝን ምን ላርግ ሚስቴ”

“ምን ማለት ነው፡፡ በፊትስ ማስተዋል አቅቶህ ቤተሰቦችህም ስላላስተማሩህ ነው እንበል፡፡ ዛሬ ግን የንስሐ አባታችን የሚጨቀጭቁህ አይበቃም፡፡ እስከ መቼ ቸልተኝነት፡፡ ሞት እኮ ቀጠሮ አይሰጥም፤ እራስን በንስሓ ዝግጁ አድርጎ መጠበቅ አይሻልም”   

‹‹ይልቅ እሱን ተዪና ብሩን ስጪኝ ስሞትልሽ ሚስቴ! … በሜሮኔ ሞት … አንገቱ ላይ ሰንሰለት እንደተደረገበት ውሻ እጥፍጥፍ ብዬ ሳመሽ አላሳዝንሽም?››

‹‹አታሳዝነኝም! … እንደውም ባሌ ካገባሁት ከስንት ዓመት በኋላ ቤቱ ስላመሸልኝ ደስ ብሎኛል … በዛ ላይ በሕማማት …  በዛውም ለአፍህ እና ለጨጓራህ ዕረፍት ስጣቸው ››

‹‹ነው!››

‹‹አዎ!››

‹‹መጨካከን ተጀመረ ማለት ነው?!››

‹‹አዎ አልኩህ አታስፈራራኝ … እንደውም ሜሪዬ ትንሽ ብር እፈልጋለሁ ብላኝ ነበር … ትሰጣታለህ››

‹‹አቤት! ከየት? በአሁን ሰዓት የብብቴን ጸጉር ንጭ ካልሆነ በስተቀር ገንዘብ አምጣ የሚለኝ ደሜን ያፈላዋል … እኔ የምለው እስከአሁን ግን የት ሄዳ ነው ያላየኋት?›› አለ የቤቱን ሁሉንም አቅጣጫ በዐይኑ እየቃኘ የልጁን አለመኖር አስተውሎ፡፡

‹‹ሆ! ሆ! እስቲ አታስቀኝ አንተ … ስለልጅህ ተጨንቀህ የት የምታውቀውን እና ነው የት አመሸች የምትለኝ? … ነው ወይስ ማጣት ከቤትህ ጋር ሲያፋጥጥህ ደርሰህ አባት ሆኜ ልቆጣጠር ልትል ነው?

‹‹ምን እያወራሽ ነው? መቼስ ቢሆን ልጄን መቆጣጠር መብት የለኝም?››

‹‹አላልኩም! ልጅህን መቆጣጠር መብትህ ነው፤ … ግን ጊዜ ሰጥተህ የማትጨነቅላትን ልጅ ዛሬ ደርሰህ የት አመሸች ስትል ምን ላርግ››

‹‹በጣም ጥሩ ልጅቷን አንዘላዝለሻታል ማለት ነው፤ … ሰዓቱ ስንት ነው? … እስቲ ተመልከች አንዲት አሥራ ስምንት ዓመት ያልሞላት የአሥራ አንደኛ ክፍል ተማሪ እንዴት ነው እስከ ሁለት ሰዓት ተኩል የምታመሸው?›› አላት ነጠላዋን አስተካክላ መስቀልኛ በማድረግ እንደወትሮዋ ወደ ቤተ ክርሰቲያን ለስግደት የምትሄደው ሚስቱ ላይ እያፈጠጠ፡፡  

‹‹አመሸች እንግዲህ ምን ታደርገዋለህ … ከአባቷ የወረሰችው አንድ ነገር ቢኖር ይህ ነው፡፡ ገና ሕፃን ሳለች ጀምሮ በአግባቡ እንደ ወላጅ ቤቱ ገብቶ ያላጫወታት አባት፣ ፈሪሀ እግዚአብሔር እንዲያድርባት ያላስተማራት አባት፣ እንኳን እሱዋን እራስን በእግዚአብሔር መንገድ ለማራመድ የማይጥር አባት ሲያጋጥማት የሚያመሽበት ጭለማ ናፍቋት ቤቱ አስጠላት … ምሽቱ ተመቻት!››

በቀልድ መሰል ንግግር የተጀመረው የባልና ሚስቱ ጨዋታ መጣፈጡን ረስቶ መረረ፡፡ ሚስት በልጅ አስተዳደግ በባል አለመታገዟ ሲያበሳጫት፣ ባል አባትነቱ ዋጋ እንዳጣ ሲያውቅ እጅግ ተበሳጨ፡፡ በተለያየ ፍላጎት ውስጥ ያደገችው ሜሮን ከልካይ ሳይኖራት ዘለለች፡፡ መዝለሏን ያወቀች እናት ብትታገላትም ማሸነፍ ስላልቻለች ተወቻት፡፡ ማምሸት ወንድ በር ድረስ ማምጣት ጀመረች፡፡ በአድራጎቷ ያዘኑ የሰፈሩ ሰዎች በትዝብት ከንፈራቸውን መጠጡ፡፡ የእናት የአባቷ ቤት በር ላይ የሰፈራቸው መተላለፊያ ላይ ይሉኝታዋን አውልቃ ጥላ ልጅነቷን ረስታ ተሳመች፡፡ ነጠላን ከንፈር ላይ አድርጎ አግድም ከማየት ውጪ ብልግናዋን ሊነግራት የደፈረ ጎረቤት ስለጠፋ በረታች፡፡ ለምክር ወንበር የሚስብ አባት፣ ከተጣመመችበት ለመመለስ የሚፈልግ አባት፣ አልፎ አልፎም ቀበቶውን ፈቶ የሚያስፈራራ አባት ስለሌላት እናቷን ናቀቻት፡፡ በጆሮዎቿ አድርጋ እንደምትሰማቸው ራፐሮች የእናቷን ንግግር ደነሰችበት፡፡

‹‹ወይኔ እኔ አላውቅልህም መስዬ … ያለማቋረጥ ማምሸቴ ሳያንስ ጭራሽ ዛሬ ሳድር እናቴ ምን እንደምትል አላውቅም››

‹‹አቦ ባሉበት ይመቻቸው … አንዳንዴም የማደርን ነፃነት ይስጡና … ሁሌ ቀን ይሰለቻል … እንዲች ሾልካ የምትገኝ ምሽትማ ታስፈልጋለች … ይልቅስ ሜሪዬ ፈታ በይ … ሻንጣ ውስጥ ያለውን ጀለቢያሽን አድርጊና ቤቱን ፏ አድርጊው››

‹‹ወይኔ ጉዴ … መስዬ ሙት ፈርቻለው … ለማንኛውም ሺሻ አለን? ሳንገዛ እኮ ነው የመጣነው››

የቅዱሳን ሥዕላት ሳይሆኑ ወጣትነት የሳባቸው የነጮቹ ፎቶዎች በአራቱም የቤቱ ግድግዳ አቅጣጫ ተሰቅለዋል፡፡ እነዚህን ወጣቶችን ለማማለል ሲሳሳሙ፣ ሩብ ጉዳይ እርቃናቸውን ሲላፉ፣ ቢች ዳር አሸዋ ላይ ሲንከባለሉ የሚታዩት ፈረንጆችን ለመምሰል የሳር ፍራሽ ላይ የሚንከባለሉ የሀገሬ ልጆች ብዙ ናቸው፡፡ ሜሮንም የሞቀ የእናትና የአባቷን ቤት ጥላ ፍቅረኛዋ መሳይ ለመቃሚያና ሺሻ ለማጨሻ የተከራያት ሕገ ወጥ ቤት ውስጥ ማደሯን መርጣለች፡፡ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በክብር መዳሩ፣ በሥጋ ወደሙ መታተሙ ቀርቶባት ድንግልናዋ የተወሰደበት ሳር ፍራሽ ላይ ስትቅም መዋሏ ሳያንሳት ዛሬ ቃጢራ ልትቅም ወስናለች፡፡  

በጎረምሳ ፍቀረኛዋ አባባይነት ማደሯን ስትወስን ጀለብየዋን ለብሳ ቤቱን አሞቀችው፡፡ ቡናው እየተቆላ፣ የገዙት ሳር ተጎዝጉዞ፣ ጫቱ ከኮባው ወጥቶ ዕጣኑ ጨሷል፡፡ የተወሰኑ ሰዎችን ብቻ የምታስተናግደው ቤት በጭሱ እፍን ብላለች፡፡ ሁሉን ጨራርሳ ቡናውን ለመቅዳት ስትሰናዳ በቀልድ መልክ ጓደኛዋን እያየች፡፡

‹‹ምርቃትህ ከዚህ የአሜሪካ እርዳታ ስንዴ ከመጣበት የማዳበሪያ ኮርኒስ ባያልፍም መርቅ›› አለችው፡፡ እጁን እያፍተለተለ እና እያፋጨ የተሰጠውን የመራቂነት እድል ለመጠቀም ያክል ጀመረ፡፡

‹‹ያረቢ አትበለን እምቢ … ቱቦ ቱቦ .. ቱቦ .. ሴሳ … ሳ .. ሳቱማ … ቱማ የሌ የሌ … በከቡሽ … ቡሽ” 

‹‹ቡሽ ነገር ነህ … ከዚህ ውጪ ምንም ምርቃት እንደማታውቅ ታወቀብህ … እስቲ ይህ አሁን ምርቃት ነው እርግማን?››

‹‹እስቲ ዝም በይ ሜሪ … ዋናው ሐሳቡ ነው … ምርቃት ነው ብለሽ ካሰብሽ ይሆንልሻል” አላት በኮባ ተጠቅልሎ የተቀመጠውን ጫት እየፈታ 

“ይልቅስ ልነዳው ነው?››

‹‹ንዳው!››

‹‹ያዥ ይህንን ምግብ የሆነ በርጫ ቃም ቃም አድርጊና ስትፈልጊ አሜሪካ ስትፈልጊ ገነት ግቢ … ብቻ እንጨቱን መጣልሽን እንዳትረሺ … አሜሪካም ሆነች ገነት የጫት እንጨት ይዞ መገኘት ያስጠይቃል››

ጫቱ ሲቃም ቡናው ሲጠጣ ሺሻው ሲሳብ ሰዓቱ ሄደ፡፡ በረባውም ባረባውም የምትስቀው ሜሮን አይኗ ቁልጭ አለ፡፡ በምርቃና የወረዛ ግንባሯን እያየ የሚያፈጠው መሳይ እንደገባላት ስሜቷ እንደተለወጠ ተረዳ፡፡ ደጋግሞ የሚነካካውን ሞባይል አሁንም አንሥቶ መልእክት ነገር ጻፈና ላከ፡፡ የምትሠራውን የምትናገረውን በአግባቡ የማታውቀው ሜሮን በተቀመጠችበት ትቁነጠነጣለች፡፡ ደጋግማ የምትከተው ጫት አፍታም ሳይቆይ ውጣው ሌላ ለመውስድ እጇን ትሰዳለች፡፡ 

ሁኔታዋን እያየ በድል አድራጊነቱ የተደሰተው መሳይ ያጣመረውን እግሩን በተለያየ አቅጣጫ እየለቀቀ ያፍታታል፡፡ ውጥኑ የሰመረለት፣ ነግዶ ያተረፈ ነጋዴ፣ ዘርቶ የበቀለለት ገበሬ ይመስል ልቡን ይነፋል፡፡

ከወዲያ መልእክት የላከላቸው ጓዶቹ የግብዣው ጥሪ ደርሷቸው ከቤቱ ደረሱ፡፡ ተንኳኳ … ወትሮ ፈሪ የነበረችው ሜሮን ከሌሊቱ ስድስት ሰዓት ያቺ ጠባብ ክፍል ስትንኳኳ የሥጋ ቤት አምፖል የመሰለ ዐይኗን ሰደደች እንጂ አልፈራችም፡፡ መሳይ በዐይኑ ምልክት ሲሰጣት ልትከፍት ተነሣች፡፡ የተቀረቀረውን በር ስትከፍት የሦስት ጎረምሶች ዐይን ተሰካባት፡፡ ጥሪያቸው የራት ብፌ ነው እና መዘጋጀቱን ሲያውቁ ፍሪዳቸው ሜሮንን ተከትለው ገቡ፡፡ የጓደኛቸውን ግብዣ ሊቀበሉ፡፡ ጓደኛቸው መሳይም ከዚህ በፊት ያበሉትን የፍስክ ብፌ ውለታውን ሊከፍል በፈገግታ ተቀበላቸው፡፡ 

በአባቱዋ ያልተገራችው ወጣትም ለፍቅረኛዋ ጓደኞች መሥዋዕት ልትሆን ተሰናዳች፡፡ ኢትዮጵያዊነት ወግ ባልገባበት፣ ሃይማኖት፣ ምግባር ባላየው ሁኔታ፤ ባልገው ሊያባልጉዋት ወንድነታቸውን ፈተሹ፡፡ ከሰው የማይካፈሉትን ተካፈሉ፡፡ ሰዶማውያን በረከሱበት መንገድ ሊረክሱ ወጣትነታቸውን ሊያስረጁ ግብግብ ገጠሙ፡፡ የሀገሬ ሰዎች ፈጣሪያቸውን “አቤቱ ይቅር በለን” ብለው ጉልበታቸውን መሬት እያመላለሱ በሚጠይቁበት ወቅት እነሱ የራሳቸውን የእርኩሰት ዓለም ፈጥረው በጠባቡዋ ቤት ሰሚ የሌለው ጩኸት አሰሙ፡፡ 

Read 1318 times