Friday, 04 December 2020 00:00

“እመኚ እንጂ አትፍሪ”

Written by  ዲ/ን ዐብይ ሙሉቀን
የጽጌ ወቅት አልፎ የበጋው ወራት ከተተካ ሰነባብቷል፣ በዘመነ ጽጌ ፈክተው የነበሩ  አበቦችና ልምላሜ የተላበሱት ዕፅዋት ጊዜ ገድቧቸው ደርቀዋል፣ በአበቦችና ነፋሻማ አየር ታጅቦ ውስጣዊ ስሜትን በሐሤት ይሞላ የነበረው ጊዜ አልፎ ደረቅ ነፋስና የፀሐዩ ግለት ነፍስን ያስጨንቃል። ዕለቱ ሐሙስ እኩለ ቀን ነው፤ ፀሐይዋ አናት ላይ ስታርፍ ከጥንካሬዋ የተነሣ እንደ መርፌ አናት ትበሳለች።  ጽዮን ከማንም ጋር ላለመገናኘት ራሷን አግልላ ከተሸሸገች ሰንብታለች። ዛሬም ውኃ ለመቅዳት ወደ ወንዝ ከሚወርዱ አንዳንድ ልጃገረዶች በስተቀር ማንም በማይንቀሳቀስበት ሰዓት በእኩለ ቀን የፀሐይዋን ሙቀት ተቋቁማ እንሥራዋን በጀርባዋ አዝላ ውኃ ልትቀዳ ብቻዋን ወደ ወንዝ ወረደች። ነገር ግን መንገዱን ከጀመረች በኋላ ተጨናነቀች።  ጽዮን በዲፕሎማ ተመርቃ ካደገችበት ከቢቸና ከተማ  በዐሥር  ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኝ የገጠር ቀበሌ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ባስተማሪነት ትሠራለች። በትዳር ለመወሰን ካላት ጉጉት የተነሣ ጥያቄያቸውን ያለምንም ማንገራገር ብትቀበልም በየተራ የቀረቧት ሦስት ወንዶች ከቀረቧት በኋላ ከድተዋታል። ሦስቱም እሺ እስክትላቸው ድረስ ለእውነተኛና ዘላቂ ትዳር እንጂ ለጊዜያዊ ፍላጎት እንደማይፈልጓት ይነግሯታል። ይሁን እንጂ እሽ እንዳለቻቸውና  የትዳር ጥያቄያቸውን እንደተቀበለቻቸው ሲረዱ ለጾታዊ ግንኙነት ይጠይቋታል። እርሷ ደግሞ በሰንበት ትምህርት ቤት በተማረችው መሠረት ከትዳር በፊት ግንኙነት ኃጢአት እንደሆነ ተረድታለችና እንቢ ትላቸዋለች። በዚህ ምክንያት ከሦስቱም ሳትስማማ ቀርታ ተለያይተዋል። ይሁን እንጂ ከሦስቱም ጋር አብራ ትታይ ስለነበር በማኅበረ ሰቡ ዘንድ እንደዝሙተኛ እየተቆጠረች መገለል ደርሶባታል። ራሷን መደበቅ የፈለገችውም በዚህ ምክንያት ነበር። ውኃ መቅዳት ስታስብም ቀትር ላይ መሄድን የወሰነችውም ከሰው ዐይን ለመራቅ በወሰነችው ውሳኔ ነበር።

 

ጽዮን ቀትር ላይ ወደ ወንዝ ስትወርድ “በእንዲህ ያለ ሰዓት ወጥቼ ጎረምሳ መጥቶ ቢደፍረኝስ?” እያለች ታወጣ ታወርድ ጀመር። በሌላ በኩል የፀሐይዋ ጥንካሬ ነጭ ላብ እያስወጣ ቁና ቁና ያስተነፍሳል፤ ልብስ ሁሉ አውልቃችሁ ራቁታችሁን ሂዱ ሂዱ ያሰኛልና ደረቷ አካባቢ ያለውን የቀሚሷን ክፍል በቀኝ እጇ ይዛ ታርገበግባለች።

በዚህ ሰዓት ወንዝ ሲወርዱ ወረፋ የለም፤  ሰው አያይም፤ ሹልክ ብሎ ለመሄድና እንደ ልብ ሳይጋፉ ቀድቶ ለመምጣት የተሻለ ጊዜ ነው።  ምንም እንኳን በዚህ ሰዓት የሚያስፈሩ ነገሮች ቢኖሩም ልጃገረዶች ግን እንዲህ ያለውን ሰዓት ይመርጡታል። ብቻቸውን እያንጎራጎሩ፣ የልብ ወዳጃቸውን በእንጉርጉሯቸው እያሞጋገሱ፣ እያሰላሰሉ በአካል አብሯቸው ባይኖርም በመንፈስ ከእርሱ ጋር እየተወያዩና፣ የልብ የልባቸውን እያወሩ በልዩ ተመስጦ ውስጥ ሆነው ውኃቸውን ቀድተው ይመለሳሉ። በመሆኑም ይህን ሰዓት እጅግ ይወዱታል።

ጽዮን ግን እንደ ልጃገረዶች በእንደዚህ ያለ ሐሳብ ለመመሰጥ ሳይሆን ባሳለፈቻቸው የተደራረቡ የሕይወት ውጣ ውረዶች ውስጧ ተሰብሮ ከማንም መገናኘት አትፈልግም፤  በራሷ ዓለም ተንቀሳቅሳ መመለስ ትፈልጋለች፤ ባህሉን፣ ሥርዓቱን፣ የአካባቢውን ማኅበረ ሰብእ ሽሙጥና ምጸት መቋቋም ተስኗታል። ስለዚህ ሰው በማይበዛበትና ውኃ ለመቅዳት ወረፋ በሌለበት ሰዓት ሄዳ እንሥራዋን ሞልታ መመለስ ትፈልጋለች። በዚህ ልማድ ነበር እኩለ ቀን ላይ ውኃ ለመቅዳት ወደ ወንዝ የወረደችው።

በያዘችው መጥለቂያ ከምንጩ እየቀዳች ወደ እንስራዋ ስትገለብጥ ድንገት አንድ ጎልማሳ ከሩቅ አስተዋለች፤ ጨነቃት፤ ሮጣ ማምለጥ አትችልም፤ ልሞክር ብትልም መንገዱ አንድ ብቻ ነው፤ ያውም እርሱ የቆመበት ብቻ። ከእርሱ በተቃራኒ ልሂድ ብትል ገደል ስለሆነ የሚታሰብም የሚሞከርም አይደለም። ታግላ ማሸነፍ አትችልም፤ እጅግ ተጨነቀች፤ በተመሰቃቀለና በተረባበሸ የሐሳብ ውጣ ውረድ ውስጥ ሆና ሳለች ይባስ ብሎ ጎልማሳው ወደ እርሷ እየቀረበ መጣ። ሰውነቷ ከወንዙ ዳር በቅላ ነፋስ እንደሚያርገበግባት ቄጠማ ተንቀጠቀጠ። ምርጫ ስላልነበራት የሚሆነውን ትጠባበቅ ጀመር። 

በአግባቡ ሰላምታ ሳይሰጣት “ውኃ አጠጪኝ?” ሲል ጠየቃት። 

ልትነፍገው ባትፈልግም ሰውነቷ እየተንቀጠቀጠ መፍራቷ አሳበቀባት። ፍርሃቷን ለመቋቋም ጥረት እያደረገች በያዘችው የቅል ዋርማ ውኃ ቀድታ ልትሰጠው ስትል ከመፍራቷ የተነሣ የውኃ መቅጃው ከእጇ አፈተለከና ወደቀ። የውኃ መቅጃው የወደቀው ድንጋይ ላይ ስለነበር ከመሰበር አልታደገችውም። ይህን ሁሉ የምታሰላስልበት አቅምና መረጋጋት ስላልነበራት በያዘው በትር የመታት፣ የውኃ መቅጃዋንም ከድንጋይ ላይ ጥሎ የሰበረው መሰላት፣ እጅግ ስለደነገጠችም ድንጋዩ ላይ ወደቀች።

በእርሷ ልቡና ውስጥ ያለው ስሜት እርሱ ውስጥ ባለመኖሩና እርሷ አስባው ለነበረው መጥፎ ድርጊት የተዘጋጀ ባለመሆኑ ከወደቀችበት እቅፍ አድርጎ አነሣትና

“አይዞሽ አትደንግጪ ለምን ትፈሪያለሽ? ደግሞስ ምንም ሳትባይ ለምን እንዲህ ትጨነቂያለሽ?” አላትና እርሷን አረጋግቶ የውኃ መቅጃው ጨርሶ ባለመሰባበሩ በሰባራውም ቢሆን ውኃውን ቀዳላትና አሸከማት። 

ከነበረባት ድንጋጤ ስትመለስ በስርቆሽ ዐይን ቀና እያለች ማስተዋል ጀመረች። መልከ መልካም ነው፣ አነጋገሩም ለስለስ ያለ ነው።  “ለምን ፈራሁትና እንዲህ ተረበሽኩ” እያለች ራሷን ትወቅስ ጀመረች።

እንስራዋን እንደተሸከመች ጉዟቸውን ቀጠሉ ቀስ እያለ “ስምሽ ማን ነው?” ብሎ ጠየቃት። 

“ጽዮን” አለችው። 

“መልካም ስም አለሽ” አላት። 

“በግብር የማይገለጽ ስም ምን ያደርግልኛል?” አለችው ፍርሃቷ በአግባቡ ከእርሷ ላይ ሳይወገድ። 

“ምን ማለት ነው?” ሲል እርሱም ጥያቄውን አስከተለ። 

“ገና ሕፃን እያለሁ ሰንበት ትምህርት ቤት ስንማር የኔታ መርሐ ጽድቅ ‘ጽዮን ማለት ጸወነ ሥጋ ጸወነ ነፍስ ማለት ነው’ ብለው አስተምረውን ነበር። እኔ ግን የኃጢአት፣ የዝሙት፣ የክፉ ሁሉ ነገር መጠጊያ እንጂ ስሜ እንደሚያመለክተው አይደለሁምና ስለዚህ ነው” አለች ሳታስበው ከውስጧ ያልጠበቀችው ኃይል እየገፋት ተናገረች።

ጽዮን ቀጠለችና “እኔኮ የተጠላሁ፣ የተናቅሁ፣ ማኅበረ ሰቡ ያገለለኝ፤ ለጌታዬ ያልታመንሁ፣ ዝሙተኛ ነኝ እንጂ እንደ ስሜ መልካም ግብር የለኝም” አለች ተስፋ በቆረጠ ድምፀት። 

ጎልማሳውም በተራው “አየሽ ጽዮን፤ የሰው ልጅ መልካሙንም መጥፎውንም ሕይወት ያሳልፋል። አንቺ ደግሞ መንፈሳዊ ትምህርትም ተምረሻል። ጠቢቡ ሰሎሞን በመጽሐፈ ምሳሌ ‘ጻድቅ ሰባት ጊዜ ይወድቃል፣ ሰባት ጊዜ ይነሣል’ (ምሳ.፳፬፥፲፮) ብሏል። ስለዚህ መውደቅ መነሣት ያለ ነው። ግን እንደወደቁ መቅረት ነው አደጋውና ተስፋ ሳትቆርጪ አሁንም ንስሓ ገብተሽ ተገቢውን ሕይወት መኖር አለብሽ”  ደግሞስ መጽሐፍ “እመን እንጂ አትፍራ “ ይል የለ (ማር ፭፥፴፮) እና አንቺም “እመኚ እንጂ አትፍሪ” አላት።

ጽዮን ፈራ ተባም እያለች ያልጠበቀችውን መንፈሳዊ ምክር እያዳመጠች ሳለ ከአጠገቧ እየራቀ፣ እየራቀ፣ እየራቀ፣ ሄደ። በዐይኗ ብትከተለውም ልትደርስበት አልቻለችም። በመጨረሻም ከእይታዋ ተሠወረ። ድንጋጤዋ በትክክል አለቀቃትም፤ በሁለት መንታ ሐሳብ ተወጠረች አንደኛው ምትሐት መሰላት፣ “ቀትር ላይ ክፉ መንፈስ ከወንዝ ዳር ይገኛል” የሚለውን አነጋገር ማሰላሰል ጀመረች። ሰውነቷ መልሶ ተንቀጠቀጠባት። ክፉውን ሁሉ አሰበች፣ “በሰው ተመስሎ ሊያስተኝ ነበርን? ለነገሩማ ከዚህ በላይ ምን ሊያደርገኝ ኑሯል? ከወንዙ ላይ ጣለኝ እኮ” እያለች ከወንዝ ላይ የሆነውን ክሥተት እየመላለሰች ማስታወስ ጀመረች። ነገር ግን የተፈጠረውን ክስተት በደንብ ማስታወስ አቃታት።

“ለመሆኑ ማን ነው እርሱ በእንዲህ ያለው ሰዓት ውኃ አጠጪኝ ያለኝ? እርሱ ማን ነው? ብወድቅ ያነሣኝ፣ ብደነግጥ ያረጋጋኝ፣ እንስራዬን የሞላልኝ፣ አንሥቶስ ያሸከመኝ እርሱ ማን ነው? ምን ዓይነትስ ቸር ቢሆን ነው? እኔ እንዲህ ስፈራው እርሱ ፍርሃቴን ያራቀልኝ እርሱ ማን ነው?” እያለች ውስጧን ጥያቄ በጥያቄ አጨናነቀችው። 

አንድ ነገር ግን መገመት ቻለች። በልጅነቷ ከሰንበት ትምህርት ቤት ስትማር የኔታ መርሐ ጽድቅ ያስተምሯቸው የነበረውን ታሪክ አስታወሰች። የእነ ርብቃን፣ የእነ ሲፓራን ታሪክ አስታወሰች። “ምን አልባት እግዚአብሔር ኃዘኔን አይቶና ተመልክቶ አጋር ሊሰጠኝ ይሆን” እያለች በመንታ ልብ ተጨናንቃ መልካሙንም፣ ክፉውንም እያፈራረቀች ታወጣ ታወርድ ጀመር። 

የኔታ መርሐ ጽድቅ በእነማይ ወረዳ ከቢቸና ከተማ ወጣ ብሎ ከሚገኘውና በተለምዶ አሮጌው ጊዮርጊስ እየተባለ ከሚጠራው ጥንታዊ ደብር የመጽሐፍና የቅኔ መምህር ናቸው። ደብሩ ጥንታዊና በርካታ ሊቃውንት የፈለቁበት ቢሆንም ስብከተ ወንጌሉን ለምእመናን ከማዳረስ አንጻር ግን ብዙም ያልተሠራበት ቦታ ነው።

“ቃለ ወንጌልን ለምእመናን ለማድረስ የሰንበት ትምህርት ቤት መስፋፋት አለበት” ብለው ያምናሉ። 

በዚህም ምክንያት ቅዳሜና እሑድ ቍጥራቸው አናሳ ቢሆንም የሚመጡ አንዳንድ ሕፃናትንና የእርሳቸውንም የመጽሐፍ ተማሪዎችን እየሰበሰቡ ያስተምራሉ። ራሳቸው መዝሙር ያስጠናሉ፤ አንዳንዴ ተማሪዎቻቸውን መርሐ ግብር እንዲመሩ እያደረጉ በዕድሜያቸውም ሆነ በትምህርታቸው ያልበሰሉ ሕፃናትንም የሚያካትት ትምህርት ያስተምራሉ። ተማሪዎቻቸውም ከትርጓሜው በተጨማሪ የስብከት ዘዴውን እንዲለማመዱት የስብከት ተራ እየሰጡ እንዲያስተምሩ ያደርጋሉ። ጽዮን በሕይወት ዘመኗ የመጣባትን ፈተና ሁሉ በጽናት እንድታልፍ የረዳት ይህ የየኔታ መርሐ ጽድቅ ትምህርት ነበር። 

ከምንም በላይ ግን አንድ ቀን የኔታ መርሐ ጽድቅ ስለ ሰማዕቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ የተናገሩትን አንድ ታሪክ አስታወሰች። “ከዕለታት አንድ ቀን አንዲት ልጃገረድ ቀትር ላይ ብቻዋን ወደ አንድ ቦታ ስትሄድ አንድ ጎረምሳ አገኛትና አስገድዶ ሊደፍራት ሞከረ። እርሷም እንዲተዋት ብትማፀነው “እንቢ” አላት። በዚህ ጊዜ ‘እባክህ ሰማዕቱ፣ ፈጥኖ ደራሹ ድረስልኝ’ ብላ ስትለምነው በነጭ ፈረስ ተጭኖ ከየት መጣ ሳይባል ደረሰላትና ሊደፍራት ከነበረው ጎረምሳ ታደጋት። ስለዚህ እናንተም በጨነቃችሁ ጊዜ ሰማዕቱን አምናችሁ ጥሩት ፈጥኖ ደራሽ ነውና ይደርስላችኋል።” ብለው አስተምረዋቸው ነበር። 

ጽዮን የየኔታ መርሐ ጽድቅን ትምህርት ከሰማችበት ዕለት ጀምሮ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ያላት መንፈሳዊ ፍቅር ጨመረ፣ የቅዱስ ጊዮርጊስ ስም በልቧ ታተመ፣ በአንደበቷም ከመመስከር አልተቆጠበችም። በወር በወርም ጸበል ጸዲቅ እያዘጋጀች ትዘክራለች፤ ገድሉን በየወሩ ታነባለች።

ጽዮን ዛሬ የሰማዕቱ የቅዱስ ጊዮርጊስ ወርኃዊ የመታሰቢያ በዓል እንደሆነ ረስታለች። ሥራም በዝቶባት ስለነበር ያስለመደችውን ጸሎት አላደረገችም፤ ለዝክሩ የሚሆነውንም ጸበል ጸዲቅ አላዘጋጀችም። ይሁን እንጂ እንዲህ ያለ ሁኔታ ቢፈጠርም  ምክንያቱ ትዝ አላላትም። የሆነውን ነገር ብቻ ግራ በተጋባ መንፈስ እያሰላሰለች ጉዞዋን ቀጥላለች። 

ብቻዋን እያወራች አንዳንዴ ከሰው ጋር ያለች ሁሉ እየመሰላት ድምፅዋንም ጎላ አድርጋ እየተናገረች ቤቷ ደረሰች። እንስራዋን አውርዳ ካስቀመጠች በኋላ የጸሎት መጽሐፏን ያዘችና ወደ ጸሎት ቤቷ ገባች። የጸሎት ቤቷ በሥዕለ አድኅኖ ዙሪያዋን የተከበበች ለእርሷ ብቻ ለመስገድም እንድትመቻት አድርጋ ያዘጋጀቻት ናትና እጅግ ጠባብ ናት። ነገር ግን ዕለት ዕለት ሽቱ ስለምትረጫት በመዓዛዋ እጅግ ታውዳለች። 

ጸሎት ቤቷ ስትገባ በልዩ ተመስጦ ውስጥ የመሆን ልምድ አላት። እንደ ልማዷም ቤቷን ዘጋችና የጸሎት መጽሐፏን ይዛ ድምፅዋን በተወሰነ መጠን ከፍ አድርጋ ዕንባዋን እንደ ጎርፍ እያወረደች የሰባቱን ቀን ውዳሴ ማርያም፣ አንቀጸ ብርሃን፣ ከሰማዕቱ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ገድል ውስጥ ሦስት ምዕራፍ፣ ከተአምሩ ሦስት ምዕራፍ  አድርሳ ስትጨርስ አንድ ድምፅ ሰማች።

ቀና ስትል በአካል አይታይም ግን አሁንም ድምፁ ይሰማታል፣ ተረጋግታ የሚሆነውን ለመከታተል ወሰነች። “አይዞሽ ከክፉ ሁሉ የምጠብቅሽ እኔ ሰማዕቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ ነኝ፤ አትፍሪ፣ ፈተናሽ ከባድና ውስብስብ ቢሆንም ከጎንሽ ነኝና አትፍሪ፣ ጸሎትሽን ወደ እግዚአብሔር አደርስልሻለሁ”  አለና ድምፁ ተሠወራት። 

ጽዮን የሆነውን ሁሉ ነገር በፍርሃትም፣ በጭንቀትም፣ በደስታም አሰበችው። “የማልጠቅም፣ እጅግ ታናሽ ስሆን እግዚአብሔር አሰበኝ፣ በሰማዕቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ አማላጅነት ጎበኘኝ። ቅዱስ ጊዮርጊስ በዕለተ ቀኑ አሰበኝ” በማለት የደስታ ዕንባ እያነባች ረስታው የነበረውን ጸበል ጸዲቅ አዘጋጀችና ዝክሩን ዘከረች።

ይህ ሁሉ የሆነው “ዝክሬን እንድትዘክሪ፣ ገድሌን እንዳታስታጉዪ” የሚል መልእክት ለማስተላለፍ እንደሆነና ሁሌም ከጎኗ መሆኑን ለማስረዳት፣ መከራ ቢመጣባትም እንደማይለያት መሆኑን ተገነዘበች።

 

Read 1148 times