Saturday, 27 February 2021 00:00

የወደቀው መልአክ

Written by  በመዝሙርና ሥነ ጥበባት አገልግሎት ማስተባበሪያ

Overview

“አብዬ…”  “አንተ…” ትለኛለች። አያቴ ናት። የቤቱ ደጃፍ ላይ ቁጭ ብየ ከራሴ ጋር ብይ እየተጫወትኩ ነበር። ቅዳሜ ከቀኑ አሥር ሰዓት ገደማ ይሆናል። ከቤት ውስጥ መስኮቱ ባለበት ግድግዳ በኩል የተሠራ መደብ ላይ ተኝታ ነው ምትጠራኝ። የመጀመሪያውን ጥሪዋንም ሰምቸዋለሁ… ለምን እንደሆነ አላውቅም ብዙ ጊዜ በሁለተኛው ጥሪ ነው መልስ የምሰጠው። የጠራኝ ሰው አንድ ጊዜ ብቻ ተጣርቶ ካቆመ በቃ እኔም እየሰማሁት  ሳልመልስ እሱም ሳይደግም እንለያያለን። ለዚህ ነው አያቴ ስትጠራኝ መጀመሪያ ስሜን አቆላምጣ ትጠራኝና እንደሰማሁ ስለገባት በሁለተኛው “አንተ..” ትለኛለች። ለምን እንደዚህ እንደማደርግ ለኔም አይገባኝም።  “ኧ ኧ ኧ…” የተለመደ መልሴ ነው። አቤት የምለው ለማላውቀው ሰው ነው። ለምን?  እንደሆነ እኔ እንጃ! “ነገ ጠዋት በተስኪያን ህደህ የቅዳሴ ጸበል እንድታመጣልኝ እኔ አሞኛል እግሬ እሽ አይለኝም።” አለች። “እሽ።” አልኩ። ቀዝቀዝ አድርጌ ህጄ ብይ ማንከባለሉን ሳላቆም። 

 

እግሯን ያማታል። “ቁርጥማት ነው” ስትል እሰማለሁ። እኔ አይገባኝም። ሳስበው እግሯ ውስጥ የሆነ የሚበላት የሚነክሳት ነገር ያለ ነው የሚመስለኝ። ሲያማት ባቷን በእጆቿ እያሸች ጥርሷን ነክሳ የሕመም ስሜት ስታሳይ እና “ኧሁሁሁ…” ስትል የማደርገውን ነገር አቁሜ እግሯን አያለሁ። አንዳንድ ጊዜ በእጆቼ አሽላታለሁ ግን ትንንሽ መዳፎቼ እና ልፍስፍስ ጉልበቴ አያረካትምና ተቀብላኝ ታሸዋለች። 

አያቴን ሳስታውሳት የምትመስለኝ። ድ……..ሮ ጀምሮ ገና ስትወለድ መሀል ላይ አንድ ትልቅ ቁልፍ ያለው ነጫጭ የአበባ ስዕል ያለበት ጥቁር ሹራብ የለበሰች። ድ……ሮ ጀምሮ ቢጫ ቆብ የለበሰች። ድ….ሮ ጀምሮ ከርደድ ያለ ቀሚስ ያላት እና መቍጠሪያዋ በአንገቷ አልፎ እስከ ሆዷ የደረሰ። ድ…ሮ ጀምራ የዋህ….

ዛሬ ባያማት ኖሮ እሁድ በጠዋ…ት ትነሣና “አብዬ…. አንተ…. ተነሣ ልብስህን ልበስ። ንቃ ታጠብ ፊትህን…” ብላ ትቀሰቅሰኝና ወደ ቤተ ክርስቲያን ይዛኝ ትሄዳለች። አንዳንድ ቀን ከእንቅልፌ መነሣት ቢመረኝም ብዙውን ጊዜ ግን አላማርርም። ቤተ ክርስቲያን ደጀ ሰላሙ ላይ ስንደርስ መቋሚያዋን አንደኛዋ የበሩ ጥግ ላይ ታስደግፍና ከበሩ መካከል ፊት ለፊት መካከሉ ላይ ትቆምና ወፍራሙን ነጠላዋን አስተካክላ እጆቿን አንስታ “በስመ አብ…” ስትል እሰማታለሁ። ከዚያ ቀጥሎ ያለው አይሰማኝም። ዝም ብዬ አያታለሁ እስከ ምትጨርስ። ይበርደኛል። አካባቢው ከዛፎች እንቅስቃሴ እና ከወፎች ድምፅ በተጨማሪ ከቤተ ክርስቲያኑ ሄድ መለስ እያለ ከሚመጣው የቄሶች ቅዳሴ ድምፅ ውጭ ምንም አይሰማም።

ተሳልማ ስትጨርስ እና የበራፉን ሁለቱን መቃኖች ስትስም እኔም ሄጄ እስማለሁ። ወደ ውስጥ እንሄዳለን እንደገና የቤተ ክርስቲያኑ መግቢያ በር ላይ ስንደርስ ትሳለማለች እኔ አጠገቧ እቆማለሁ። “የሴቶች መግቢያ” የምትለውን ጽሑፍ እንደተለመደው ደጋግሜ አነባታለሁ። ግን  ቃላቱን ቦታ በማቀያየር ሌላ አዲስ ቃል ለመመሥረት እሞክራለሁ። ገልብጨ ደግሞ አነበዋለሁ። “ያቢግመ ችቶሴየ…” በመካከል አያቴ መሳለሟን ትጨርሳለች። እንገባለን። ሌሎች የተቀመጡ መነኮሳትን ድምጿን ቀንሳ ሰላም ትላለች። “….ችሁ” የምትለዋ ድምፅ ብቻ ናት የምትሰማው። ሰዎቹን በስም አላውቃቸውም እነርሱም እንደ አያቴ መነኵሴ ናቸው። ሁልጊዜ እሑድ እሑድ እዚህ ስለማገኛቸው እዚህ የሚኖሩ ነው የሚመስለኝ። ደግሞ የሚገርመኝ ተሳስተው እንኳን የሚቀመጡበት ቦታ ተቀያይሮ አያውቅም።  ለዚያ ነው እዚህ የሚኖሩ የሚመስለኝ። 

አያቴ የምትቆምበት ቦታ ላይ ስትደርስ እንደገና ትሳለምና ዝቅ ብላ እያየችኝ በጣቷ ወደ መሬት ትጠቁመኛለች  ስለሚገባኝ አንገቷ ላይ ክር የታሰረባትን የጸበል እቃ ክዳኗን ከፍቼ ከፊት ለፊታችን አስቀምጣታለሁ። አያቴ አታወራኝም። ከፊት ለፊቴ ግድግዳ ላይ የተሳሉትን ስዕሎች ማየት እጀምራለሁ። አንዳንዶቹን አያቴ ስለነገረችኝ አውቃቸዋለሁ። በፈረስ ዘንዶ የሚወጋ… ሰው የሚመስል ነገር በራሱ የተሸከመ ከጎኑ የሆነ ወታደር የሚመስል ሰውዬ ሲከተለው… የማርያም (የሆነ ሰው እጁን ደረቱ ላይ አድርጎ ከማርያም እግር ስር ሆኖ “ቅዱስ ኤፍሬምን እንደባረከችው” የሚል ጽሑፍ ያለበት) … ጌታችን ተሰቅሎ በመጋረጃ ተሸፍኖ… ሌላም ብዙ ሳይ እቆይና ይደክመኛል። አያቴን ቀና ብየ አያታለሁ። ፊት ለፊት እያየች ዝም ብላለች። አታየኝም። ቀስስስ ብዬ ወደ ግድግዳው ተጠግቼ አያቴ እግር ስር እቀመጣለሁ። እንቅልፌ ይመጣል። የሆነ ሰዓት ላይ እጀን ነቅነቅ ነቅነቅ ስታረገኝ ብንን እልና ቀና ስል ወዲያው ዲያቆኑ በተቀመጥኩበት ፊቴን በመጽሐፍ ያሳልመኝና ያልፋል። ትንሽ ግራ ይገባኝና ያለሁበት ትዝ ይለኛል። ግራና ቀኝ ያሉትን ሰዎች ትንሽ እቃኝና ተመልሼ አንገቴን ስደፋ እንቅልፍ ይዞኝ ይሄዳል። 

ቅዳሴው ሊያልቅ እግዚኦታ ሰዓት ላይ ተነሥቼ እቆማለሁ። አብሬ እግዚኦ ለማለት እሞክራለሁ… በትክክል አልለውም። ሲጠናቀቅ ጸበል ጠጥተን አስቀድተን መክፈልት በልተን ከሌሎች መነኰሳት ጋር አያቴ እያወራች ወደ ቤት እንሄዳለን። መንገድ ላይ ቀስስ… እያሉ እያወሩ የሚሄዱት ነገር ትንሽ ያናድደኛል። እኔ ቶሎ ቶሎ በልጅ እግሬ ስሄድ እነሱ አይከተሉኝም። አያቴን ትቼ ወደ ቤቴ መሄድ ደግሞ አልችልም። ትቀየመኛለች። ስለዚህ በየመሀሉ እየቆምኩ መንገድ ላይ ባገኘሁት ነገር ለመጫዎት እሞክራልሁ። 

ዛሬ ግን አያቴ እግሯን ስላመማት ብቻየን ነው የምሄደው። እሑድ ጠዋት ቀድሞ አያቴ ስትቀሰቅሰኝ እነሣበት ከነበረው ሰዓት ረፈድፈድ ብዬ ተነሣሁ። አያቴ ተኝታለች። እንቅልፍ ግን አልወሰዳትም። ፊቴን ታጥቤ ነጠላዬን እሷ ስታለብሰኝ እንደምታደርገው አድርጌ ለመልበስ ሞከርኩ። ዝም ብላ በተኛችበት ታየኛለች። የጸበል እቃዋን ከራስጌዋ አንሥቼ ከቤት ወጥቼ መንገድ ጀመርኩ። ወደ በዓታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን። የጸበል እቃዋ ነጭ ናት። ዙሪያዋን ዳር ዳሯን በጥርሴ ነክሻታለሁ። የጥርሴ አሻራ ታትሞባታል። ለምንድነው የምነክሳት?? ስነክሳት ትምቡክ ትምቡክ ስለምትል ደስ ስለምትለኝ ይመስለኛል።

ከረፈደ ስለ ተነሣሁና በመንገድም ላይ ቀስ እያልኩ ስለሄድሁ ቅዳሴ ገብተው  ደረስኩና ደጀ ሰላሙ አንድ ጥግ ላይ ቆሜ ማስቀደስ ጀመርኩ። ስለተለያየ ነገር ሳስብ ቅዳሴው አለቀና ጸበል አስቀድቼ እሑድ በመጣ ቁጥር እንዲያልፉኝ ለማልፈልጋቸው ሁለት ነገሮች ተዘጋጀሁ። 

የመጀመሪያው ተአምረ ማርያም ሲነበብ ታሪኩን መስማት ነው። መጽሐፉን ገልጠው ከሚያነቡት ቄስ እግራቸው ስር ሔጄ እቆምና ሌላ ነገር ሳላስብ የሚነበበውን ታሪክ እሰማለሁ። እግራቸው ስር ሔጄ የምቆመው ድምፃቸው በደንብ እዲሰማኝ እና ሲጨርሱ መጀመሪያ እኔን እንዲያሳልሙኝ ነው። የተአምረ ማርያም መግቢያውን ዘወትር ከመስማቴ የተነሳ በቃሌ ሸምድጀዋለሁ። አንዳንድ ጊዜ ከሚያነበው ቄስ ጋር አብሬ ለራሴ አነበንባለሁ። የዕለቱ ታሪክ ሲደርስ አዲስ ያልሰማሁት እንዲሆን በልቤ እመኛለሁ። የሰማሁትን ፈጽሞ አልረሳውም።

ሁለተኛው ትልቅ እና ተጠባቂ ነገር ደግሞ ከተአምረ ማርያም በኋላ የሚኖረው መክፈልት ነው። መጀመሪያ ተሳልሜ መክፈልት ወደ ሚበላበት ስፍራ ሔጄ ቁጭ ብዬ እጠባበቃለሁ። ሰዎቹ እስኪሳለሙ ሁሉም ሰው እስኪመጣ መጠበቅ ግድ ነው። ይዘገዩብኛል። ሁሉም ካልመጡ ደሞ የአያቴ ጓደኛ መክፈልቱን መስጠት አይጀምሩም። በጸበል እቃዬ እየተጫወትኩ ጥበቃዬን እቀጥላለሁ። ትልልቅ ሰዎች ተቀምጠው ሲጨርሱ መክፈልት መሰጠት ይጀምራል። ሁልጊዜም እዚያ ጫፍ ላይ ከተቀመጡት ሽማግሌ ሰውዬ ነው የሚጀመረው። “ለምንድነው እኛ ካለንበት ቦታ መስጠት የማይጀምሩት?” የሚል ጥያቄ ይመጣብኛል። ግን አይቀየርም። የአያቴ ጓደኛ ብቻዬን መቀመጤን ሲያዩ 

“አንተ አያትህ ምን ሆነው ቀሩ ዛሬ?” አሉኝ ይተዋወቃሉ። ጓደኛ ናቸው። 

“እግሯን አሟት ተኝታለች።” አልኩ።

“አዬዬዬ…ያ ቁርጥማት ተነሣችባቸው ደግሞ?” አሉ። መልስ አልሰጠሁም። ዐይኔም ልቤም በሰፊ ሰፌድ ከያዙት ዳቦ ላይ ነው። 

“በል እንካ ከመክፈልቱ ውሰድላቸው….” ብለው ፫ የዳቦ ቁርሥራሾች እቅፌ ላይ አደረጉልኝ። በጣም ውስጤ ፈነደቀ። ደስታዬን ፊቴ ላይ ላለማሳየት ሞከርኩ። አልቻልኩም ፈገግ አልኩ ሳላውቀው። ከዚያ በኋላ የተናገሩትን አልሰማሁም እንጂ የሆነ ነገር ተናግረዋል። መክፈልቱን በፍቅር አየሁት። ቀስ አድርጌ በትክክል በአራት ማዕዘን የተቆረሰውን መክፈልት አንደኛውን ጎን ቆረስ አድርጌ ወደ አፌ አልኩት። ሁሌም እንደተገረምኩ ነው። እጅግ በጣም ነው ሚጣፍጠው። ሽታው ብቻ ለኔ ልዩ ነገር ነው። ስበላው ምንም ነገር አላስብም እሱን ብቻ ነው በአፌም በልቤም የማላምጠው። ጥያቄዎቼን አስከትላለሁ። “ምን ቢያደርጉበት ነው እንዴህ የሚጣፍጠው?... ለምንድን ነው እኛ ቤት የሚጋገረው መክፈልት እንደዚህ የማይጣፍጠው?... መጋገሪያው ቤት ውስጥ ስንት መክፈልት ይኖር ይሆን…” ተደጋጋሚ ናቸው ጥያቄዎቼ። አይሳካም እንጂ ሁልጊዜም እንዲደግሙኝ እፈልግ ነበር። ግን አይደግሙኝም። እኔም ድገሙኝ ብዬ አላውቅም። “ምናለበት ከቤት ፮ ሙሉ ሙሉ መክፈልት አምጥቼላቸው እዚህ ባለው መክፈልት ቢቀይሩኝ…” እያልሁ አስባለሁ።  

ሳላውቀው እማሆይ ከሰጡኝ መክፈልት ሁለቱን በላሁት። ሦስተኛውንም ብደግመው ደስታዬ ነበር ግን ለአያቴ መውሰድ አለብኝ። እጄ ላይ የቀረውን አንድ መክፈልት አፌን እያጣጣምኩ አየሁት። እንዳልሳሳት በነጠላዬ ሸፈንኩት። ወደ ቤቴ መሄድ ብፈልግም ትልልቅ ሰዎች ጨርሰው ሳይነሡ መነሣት ስለማይቻል ተቀምጨ መጠበቁን ተያያዝኩት። ልክ ከትልልቆቹ አንደኛው ከመቀመጫው ብድግ ሲል እኔም ላጥ ብዬ ተነሣሁ ። ለካ ሰውየው የተነሣው ለተሰበሰበው ሰው የሆነ ነገር ሊናገር ነበር እንጂ ሊሄድ አልነበረም። ከጎኔ የተቀመጡት ሰውዬ ሲያዩኝ ትንሽ እፍረት ቢጤ ያዘኝና ተመልሼ ቁጭ አልኩ። 

የሚነገረው ነገር ተነግሮ ሰዎቹም ተነሥተው መንገድ ስንጀምር ከኋላ ተነሥቼ ከፊት እገኛለሁ። ቤት ልደርስ ትንሽ ሲቀረኝ ለአያቴ የያዝኩትን መክፈልት አየሁት … ተቀነጣጥቦ ግማሽ ደርሷል። አያቴ እንደምትታዘበኝ ገባኝ። ያም ሆኖ የቀረውን ይዤ ቤቴ ስገባ አያቴን በረንዳ ላይ ተቀምጣ ፀሐይ ስትሞቅ አገኘኋት። የጸበል እቃውን እና ከመቀነጣጠብ የተረፈ መክፈልቱን እሰጣታለሁ። ትመርቀኝና ከጸበሉ ጠጥታ መክፈልቱን ትበላለች። በልታ ስትጨርስ አፍ አፏን አያታለሁ። አንድ ነገር እንድትጠይቀኝ እፈልጋለሁ። ካልጠየቀችኝ ቅር ይለኛል። እንደ ሁል ጊዜው እያጣጣመች ትጠይቀኛለች።

“ዛሬ ምን ዓይነት ታምር ተነገረ ንገረኝ እስኪ..?” ስትለኝ ከአፏ ነጠቅ አድርጌ 

“ዛሬማ ታምር ላይ … የሆነ አገር ላይ አዲስ የማርያም ቤተ ክርስቲያን እየተሠራ ነበር። ከዚያ እዚያ ሰፈር ግመል የሚጠብቅ አንድ እስላም ሰውዬ ነበረ። ግመሉን ሲጠብቅ ሳያያት አንዷ ግመል ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ገባችበት። ከዚያ ደንግጦ ሔደና ሊያስወጣት ቢል እምቢ አለችው። ከዚያ ቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ እንዳልገባ ብሎ ከውጭ ሆኖ ወደ ውስጥ ድንጋይ መወርወር ጀመረ። ከዚያ በድንጋይ ግመሏን አስወጣት። አንድ ቀን ሲሞት ሰማይ ቤት ሊኰነን ሲል ማርያም ደግሞ መጥታ ጌታችንን “ይሄን ሰው ማርልኝ” አለችው። ከዚያ “አልምርልሽም በሥላሴ አላመነም አልተጠመቀም” አላት። ከዚያ “ቤተ መቅደስሽን ያሠራውን እምርልሻለሁ ብለኸኝ አልነበር። ይህም ሰው ግመል ለማባረር ብሎ የወረወረው ድንጋይ አዲስ ከሚሠራው ቤተ መቅደሴ ላይ አርፎ ሕንጻው ተሠርቶበታል።” ስትለው “እሽ እምርልሻለሁ” ብሎ ማረላት። ሰውየውም ዳነ።”

አያቴ ዐይን ዐይኔን በዝምታ እያየች ነው የምታዳምጠኝ። ታሪኩን በገባኝ መንገድ ስለሆነ የምነግራት ግማሹን አልነግራትም። አያቴ ግን ይገባታል። ታሪኩን ስለምታውቀው ይሁን ዐላውቅም። በጭንቅላቴ ውስጥ ያለውን ሁሉ አልነግራትም አንዳንዱን እዘለዋለሁ ዋና ዋና የመሰለኝን ነው ምነግራት። 

ስጨርስ “ጎሽ” ትለኝና ቁርሴን እንጀራ በሽሮ ትሰጠኛለች። ከመክፈልት የጎደለውን በሽሮ እሞላና ወደ ጨዋታዬ እወጣለሁ። አያቴ ከቤት አትወጣም። ተመልሼ ስመጣም በረንዳ ላይ ተቀምጣ ጥጥ እየፈተለች በእግሯ ደግሞ ጠርዝ ጠርዙ የተጨማደደ ደብተሬን እንዲስተካከል ረግጣ ይዛ አገኛታለሁ። ደብተሬን እየተኮሰችው ነው። አያቴ የአስኳላ ትምህርት ስላልተማረች ነው እንጂ ብታስጠናኝ ደስ ይላታል። ግን… ያላት አማራጭ የተጨማደደ ደብተሬን ማስተካከል ብቻ ነው። 

የሆነ ቀን አያቴ ሌላም ተጨማሪ ሕመም አሟት ብዙ ቀን ከተኛች በኋላ  ከጨዋታ ስመለስ እቤታችን ሰው ሲንጫጫ ደረስኩ። አያቴ ሞታለች። አላለቀስኩም። የምር አልመሰለኝም ነበር። እየቆዬ ሲመጣ ግን አያቴ ስለምትናፍቀኝ ብቻዬን ማልቀስ ጀመርኩ። 

ሁልጊዜም እሑድ በመጣ ቁጥር አያቴ በምትቀሰቅሰኝ ሰዓት ወደ ቅዳሴ እየሄድኩ በአያቴ የጸበል እቃ ጸበል እያመጣሁ ማስቀመጡን ሥራ ብዬ ተያያዝኩት። ዝምታዬ ግን እየበረታ መጣ ብዙ ነገር አላወራም። ውዳሴ ማርያም ተምሬ ዳዊት ደግሜ ከድርገት በፊት ቅኔ ማሕሌት ላይ ሃይማኖተ አበው ማንበብ ጀመርኩ። ከትምህርቴ ባሻገር ከቤተ ክርስቲያን ደጃፍ አልጠፋም። ዕድሜዬ እየጨመረ ዝምታዬ ቦታውን ሳይለቅ አደግሁ። 

ልጅነቴ አልፎ ሃያዎቹ ዕድሜ ውስጥ ከገባሁ በኋላ የልጅነት አመሌ እየተለወጠ የተለያዩ አዳዲስ ነገሮችን መሞከር ጀመርኩ። የሥጋዊ ስሜቴ እየፈተነኝ ያንገዳግደኝ ጀመር። ከዕለታት አንድ ቀን በአጋጣሚ ከአንድ በዓለማዊ ትምህርት ከገፋና የፍልስፍና ባለሙያ ነኝ ከሚል ሰው ጋር ተቀምጠን በምናወራበት ጊዜ ከወሬ ወሬ ተነሣና 

“ግን ለምንድን ነው ሰው የሚያስፈልገውን ነገር እንደፈለገ መፈጸም የማይችለው?” 

በመባባል ረጅም ሰዓት አወራን። አብሮ ከሚያወራኝ ሰውም በርከት ያሉ የፍልስፍና አመለካከቶችን አነሣን።

ከዚያን ቀን ጀምሮ አመለካከቴ ተቀየረ። “ሰው እንዴት ከራሱ ስሜት ጋር ጦርነት ይገጥማል?” ለምን አያስተነፍሰውም? የሚል አስተሳሰብ አደረብኝ። አዋዋሌ ተቀየረ። ጓደኞቼ በዙ። ያላደግሁበትን ከሴቶች ጋር መዋል ማደር መጫወት መቃለድ ጀመርኩ። ስለ ቅዳሜ ያለኝ አመለካከት ተለወጠ። እንደተሰማኝ እንዳየሁት ዘና ማለት ጀመርኩ። ያደግሁ የተለወጥኩ መሰለኝ። ውስጤ ደስተኛ ሆነ። ባለኝ ነገር እዝናናለሁ። ከሌለኝ ደግሞ አብረውኝ ከሚውሉ ጓደኞቼ ጋር በተገኘው ነገር እዝናናለሁ። እንደተለመደው ቅዳሜ ዕለት ስልኬ ጠራ ሔድኩ፤ ተሰባሰብን፤ ተቃለድን፤ ተጫወትን፤ ሳቅን፤ በላን፤ ጠጣን፤ እየመሸ ሲሄድ ሥጋዊ ስሜት አሸነፈ። መጋረጃ ተዘጋ ከሰው ዐይን በግድግዳ ተከለልሁ “ሰው እንዴት ሥጋዊ ስሜቱን ሊቋቋመው ይችላል?” የምትለዋ አመለካከቴ እንደ መፈክር በድርጊቴ ወደፊት እንድሰግር አደረገችኝ። ጋለብሁ….ጋለብሁ… ሰይጣን በማላውቀው ሜዳ እንደ ፈረስ አስጋለበኝ…. አዲስ ደስታ በመሰለኝ ነገር ሁሉ ደረስሁ።  በአግራሞት ለእኔ ደስታ በሚመስለኝ ግን ወደ ቁልቁለት ወረድሁ….ወረድሁ… አዲስ ጥበብ እንዳገኘ ፈላስፋ አዲስ ቀለም እንዳገኘ ፀሐፊ…  ባየሁት በነካሁት ነገር ሁሉ በደስታ ባሕር እየዋኘሁ ልጓሙን እንደፈታ ባዝራ ፈረስ ደስ ባለኝ እየረገጥሁ ልቤ መፈክሩን እየደጋገመ ልክ ነህ እያለኝ ሄድኩ ሄ….ድኩ… ሄ….ድ…..ኩ።

ሌሊት አንዳች ነገር ውስጤን አስበርግጎኝ አፈፍ ብዬ ከተኛሁበት ተነሣሁ። ያለሁበትን አየሁ ስሜቴ ተደበላለቀ። ከእንቅልፌ ብቻ ሳይሆን ከአዚማም ሕይወት የባነንኩ መሰለኝ። ልጅነቴና የቀድሞ ሕይወቴ ፊቴ ላይ ተዘረጋ። ድንጋጤ ከበበኝ። ይህ ሰዓት አያቴ ከእንቅልፌ የምትቀሰቅሰኝ ሰዓት ነበር። ልብሴን ለባብሼ በር ከፍቼ ወጥቼ ስሮጥ በባዶ እግሬ እንደሆንኩ ያስታወስኩት ሻፎ ድንጋይ እንቅፋት ሆኖ የእግሬን አውራ ጣት ሲያወልቀኝ ነው። አመመኝ ደማ። ባለቅስ ደስ ባለኝ ነበር ግን መሄድ አለብኝ። በመንገድ ላይ የሰው ዘር አይታይም። ጥርሴን ነክሼ አውራ ጣቴን መሬት እንዳይነካት ወደ ላይ አንከርፍፌ እግሬን ጎተት እያደረግሁ መንገዴን ቀጠልሁ። አውራ ጣት ሲመታ ለምንድን ነው እንደዚህ ሰውነት ሁሉ የሚነዝረው ግን? ዑራኤል ቤተ ክርስቲያን ደረስኩ። የቤተ ክርስቲያኑ መብራት ብቻ ነበር የሚታየኝ ትልቁ በር ስለተዘጋ እያነከስኩ ወደ ትንሹ በር ለመግባት ስሄድ…

“ወዴት ነው!?” አለኝ። ጥበቃ ሠራተኛው ነው። 

በጣቴ ወደ ቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ ጠቆምኩት። ትንፋሼ ይቆራረጣል።

“አይቻልም!”

“ለ…ምን?”

“አይቻልም። በወረርሽኙ ምክንያት መግባት ተከልክሏል።… ምነው ባገር አልነበርክም እንዴ ጌታው?”

ምንም አልተናገርኩም። ሸርተ…ት ብዬ በሩ ሥር ተቀመጥኩ። እግሬ እየደማ ነው። ሰውዬው ዐይኑን ሳይነቅል ያየኛል።  “አዬዬዬ… ባገር ብኖርማ…” ትንፋሼ ተቆራረጠ… ልቤ ተሰበረ። ከንቱነቴ ተሰማኝ። ውድቀቴን የምገልጽበት ቃል ሞቴን የምስልበት ቀለም አጠረኝ። አያቴ በአካል ቆማ በትዝብት ዐይን የምትመለከተኝ መሰለኝ። ከእፍረቴ የሚሸሽገኝ ነገር አጣሁ። ፊቴን ወደ ቤተ ክርስቲያኑ ዞሬ ማዬት አልቻልኩም። አጥሩን ተደግፌ እግሬን ዘርግቼ በተስፋ መቁረጥ ስሜት ተቀምጬ አይኖቼን ጨፍኜ ውስጤን ሳዬው ቆሽሾ ለማየት የከፋ፣ ለማሽተት የከረፋ ሆነብኝ። እንባዬ ፈሰሰ። ንጽሕናዬን አጣሁት። ልጅነቴ ሻከረብኝ። ያበላሸሁት እኔነቴ አስጠላኝ። ሐሳቤን ሰብሰብ ለማድረግ ሞክሬ የቅዳሴውን ድምፅ ለማዳመጥ ሞከርሁ።

“… ባርክ እግዚኦ ነገረ ዘእምወንጌለ ማቴዎስ ረድኡ ወሐዋርያሁ ለእግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ ወልደ እግዚአብሔር ሕያው ሎቱ ስብሐት ወትረ እስከ ለዓለመ ዓለም አሜን።

የማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ ፳፭ ከቍጥር ፩ እስከ ፲፫፡-

በዚያን ጊዜ መንግሥተ ሰማያት መብራታቸውን ይዘው ሙሽራውን ሊቀበሉ የወጡ አሥር ቆነጃጅትን ትመስላለች።  ከእነርሱም አምስቱ ሰነፎች አምስቱም ልባሞች ነበሩ። ሰነፎቹ መብራታቸውን ይዘው ከእነርሱ ጋር ዘይት አልያዙምና፤ ልባሞቹ ግን ከመብራታቸው ጋር በማሰሮአቸው ዘይት ያዙ። ሙሽራውም በዘገየ ጊዜ ሁሉ እንቅልፍ እንቅልፍ አላቸውና ተኙ። እኩል ሌሊትም ሲሆን። እነሆ፥ ሙሽራው ይመጣል፥ ትቀበሉት ዘንድ ውጡ የሚል ውካታ ሆነ። በዚያን ጊዜ እነዚያ ቆነጃጅት ሁሉ ተነሡና መብራታቸውን አዘጋጁ። ሰነፎቹም ልባሞቹን። መብራታችን ሊጠፋብን ነው፤ ከዘይታችሁ ስጡን አሉአቸው። ልባሞቹ ግን መልሰው። ምናልባት ለእኛና ለእናንተ ባይበቃስ፤ ይልቅስ ወደሚሸጡት ሄዳችሁ ለራሳችሁ ግዙ አሉአቸው። ሊገዙም በሄዱ ጊዜ ሙሽራው መጣ፥ ተዘጋጅተው የነበሩትም ከእርሱ ጋር ወደ ሰርግ ገቡ፥ ደጁም ተዘጋ። በኋላም ደግሞ የቀሩቱ ቈነጃጅት መጡና። ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ፥ ክፈትልን አሉ። እርሱ ግን መልሶ፦ እውነት እላችኋለሁ፥ አላውቃችሁም አለ። ቀኒቱንና ሰዓቲቱን አታውቁምና እንግዲህ ንቁ።

ሰማይና ምድር ያልፋል ቃሌ ግን አያልፍም አለ ጌታ ለደቀ መዛሙርቱ።…”

ልቤ ጸጸቱ በእጥፍ ጨመረ። ለእኔ ብቻ ተብሎ የተነገረ ወንጌል መሰለኝ። እውነት ነው… ዛሬ ስዘናጋ በስህተት ጎዳና ሳዘግም በሩ ቢዘጋብኝ ይሔ በር ነገ ይከፈታል። የመንግሥተ ሰማይ በር ግን ከተዘጋ እጣ ፋንታዬ ሲኦል ነው። ዛሬ ለንስሓ የማይመች ለኑዛዜ የማይሆን ጊዜ ላይ ልቤ ቢነቃም ይህ ክፉ ጊዜ እስኪያልፍ እጠብቀዋለሁ። አምላኬ እያዬኝ ነው። ውኃ እና ንስሓ የማያጸዳው ቆሻሻ የለም። እንደ ልጅነቴ የሥጋም የነፍስም ድንግልናዬን መመለስ ባልችል በኑዛዜ ፈጽሞ ንጹሕ መሆን እችላለሁ። እንደ ቀልድ በወሬ መካከል የተነገረች አንዲት ቃል ሕይወቴን ዘውራው ወደ ገደል ብትመራውም የሥጋ እስትንፋሴ እስካለች ድረስ መመለስና ወደ ቀናው ጎዳና ለመገስገስም ጊዜው አልረፈደም። ነገ ይሁን ዛሬ ሞታችን በማይታወቅበት ጊዜ በእሳት ጨዋታ ደቂቃ ለማይቆይ ደስታ መሳይ ሳቅ በጀርባው እልፍ ስፍር ጸጸትን ባዘለ ቡረቃ መሮጥ መጨረሻው የሞት ሞት ነው።

በልጅነቴ ከቤተ ክርስቲያን ጉያ ስር ተቀምጨ የማገኘውን ውስጣዊ ደስታ እና ሰላም የሚወዳደር ነገር እንደሌለ አይቻለሁ። ግን ተጎድቶ ከመማር፣ ከመስማትና ከመተግበር እጅጉን የተሻለ ነበር። 

ቅዳሴው በተቀመጥኩበት አለቀ። ነጋ። የእግሬ ደም ደርቆ አውራ ጣቴ ማበጥ ጀምሯል። ከቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ እንደወትሮው አስቀዳሽ ምዕመናን አይታዩም። እንዴት ዓይነት ክፉ ዘመን ቢሆን ነው ሰውን ከፈጣሪው ደጅ እንዳይደርስ ያደረገው?... መቼ ነው የንስሓ አባቴ የሚዳስሱኝ?... ድጋሚ ማንባት ብፈልግም እንባዬ ደርቆ ነበር። 

 

Read 1417 times