ምኖረው አዲስ አበባ ውስጥ ነው። አሁን ከአዲስ አበባ ወጣ ብላ ከምትገኝ አነስተኛ ከተማ ደርሼ እየተመለስኩ መኪና ውስጥ ነኝ። የተሳፈርኩበትን መኪና አንደኛውን የመስኮት ጥግ ይዤ መስታውቱ ላይ ደገፍ ብዬ ተቀምጫለሁ። ስገባም እንደዚሁ ነው የተቀመጥኩት። የተሳፈርኩበት መኪና ጉዞ ከጀመረ ሁለት ሰዓታት ተቆጥረዋል። መንገዳችን በጠቅላላ ፭ ሰዓት ያህል ይፈጃል። ፊቴን እንደ ሐምሌ ሰማይ እንዳከበድኩት ይታወቀኛል። ምንም ነገር ማሰብ አልፈልግም። በጣም ከፍቶኛል። ከማንም ጋር በምንም ጉዳይ ማውራት ፍላጎቱም የለኝም።
፳፮ ዓመቴ ነው። ከልጅነቴ ጀምሮ አብሮኝ ያደገ ያወቅሁትን ነገር ለሌሎች የማካፈል ጉጉቴ እጅግ ከፍተኛ ነው። አዲስ ነገር አውቄ ላላወቁት ስነግር ሳስረዳ እና ሲሰሙኝ ውስጤ የሚሰማኝ ደስታ እንዲህ በቃላት የምገልጸው አይነት አይደለም። ምንም ነገር አላግኝ ግን በቃ ያወቅሁትን ልናገር በተለይ ልብ ብሎ የሚያዳምጠኝ አካል ካለ እጅግ ደስተኛ ነኝ። በማላውቀው ነገር ግን ለመናገር አልቸኩልም። የተማርኩት የምሠራውም መካኒካል ምህንድስና ነው። ሥራየን እወደዋለሁ።
በእያንዳንዱ ቀን አዲስ ነገር ስለማውቅበት እና የልጅነት ስሜቴ ስለነበር በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ ሥራውን መሥራት እችላለሁ። ይህንን ስለሚረዱ ነው መሰለኝ አለቃዬ ብዙ ጊዜ ከአዲስ አበባ ውጭ ላሉ ሥራዎች እኔን የሚመርጡት። እኔም ደስተኛ ሁኜ ነው የምሠራው።
የዛሬው ግን የተለየ ነው። ከዚህ በፊት እንደሚገጥመኝ ዓይነት ሁኔታ አልነበረም። በጣም የተከፋሁበት የመስክ ሥራ የዛሬው ነው። ከሰዓታት በኋላ ራሱ ንዴቴ ስላለቀቀኝ በየመሃሉ በረጅሙ እተነፍሳለሁ። ብቻዬን እያወራሁ እንደሆነ የተረዳሁት “ልጄ?” የሚል ድምፅ ስሰማ ነው። በልዩ ሐሳብ ከመመሰጤ የተነሣ በቦታው ስላልነበርሁ በጥቂቱ ደነገጥኩ። ከጎኔ አብረውኝ የተሳፈሩ ካህን ነበሩ የተናገሩት። እንዴት ይህን ያህል ሰዓት አብረን ስንጓዝ ከጎኔ እንደተቀመጡ እንኳን ማስተዋል አልቻልኩም? ይህን ያህል የለሁም ነበር ማለት ነው?
“አቤት አባ?” አልኳቸው አቀማመጤን እያስተካከልኩ።
“ምን ሆነሃል ልጄ? እንደው ከቅድም ጀምሮ እኮ….. ስትብሰለሰል መንገዱን ጨረስከው።” አሉኝ ረጋ ባለ አባታዊ አንደበት።
“አ…አይ ምንም አባ…እንዲሁ ስለሥራ ጉዳይ እያሰብኩ ትካዜ ገብቶኝ ነው።”
አልኳቸው ብዙም ስለጉዳዩ ለማውራት ባልፈለገ እና ለመናገር ግራ በተጋባ ስሜት።
ምን ብዬ አስረዳቸዋለሁ…. ምኑ እንዳናደደኝ እና እንዳስኮረፈኝስ እንዴት እገልጽላቸዋለሁ? ከየት ብጀምርስ ይገባቸው ይሆን? ተውኩት። አለባብሼ ለማለፍ ወሰንኩ። ከሁለት ቀናት በፊት ዋይ.ሲ.ጅ ከሚባለው ድርጅቴ ለሥራ ወደዚች ቦታ ስለ ማሽን ተከላ(ፕላንቲንግ) ማስገንዘቢያ ሥልጠና ለመስጠት እና የማሽን ተከላውንም ለማገዝ ፱ ቀን ተልእኮ ተሰጥቶኝ ነው የተላክሁት…… ብዬ መጀመር ይኖርብኛል ነገሩን ለማስረዳት። ይህ ደግሞ ለኔ አሰልቺ ሆነብኝ ። ማሽኖች ይተከሉበታል ተብሎ የታሰበው የሥራ ቦታ ስደርስ የገጠመኝ ነገር ግን እንደጠበቅሁት አልነበረም። ለሚመለከተው ሰው ማንነቴን አስረድቼ ወደ ሥራው ለመግባት ያለብኝን ኀላፊነት እና ሥልጣን በዝርዝር ሳስረዳ በቦታው ያሉ አለቆች ነገሩ አልተዋጠላቸውም። ፊታቸው ላይ የንቀት እና የቅያሜ ገጽታ ተነበበ። ወደ ሥራው ስንገባማ ጭራሽ ልንግባባ እና ሊያዳምጡኝ አልቻሉም። የማውቀውን ነገር ሁሉ ረጋ ብዬ ለማስረዳት ሞከርሁ። ሰዎቹ አንድ ዓይነት ሆኑብኝ። ሊያዳምጡኝ ፈቃደኛ አልሆኑም። ሥልጣናቸውን የተቀሙ ያህል ነው እየነደዳቸው ያለው። እንደተረዳሁት ከሆነ በማንም ትእዛዝ ሥር መሆን አይፈልጉም። ግን እኮ እኔ የመጣሁት በማሽን ተከላው ሥራ ላማክራቸውና ልረዳቸው እንጂ አለቃ ልሆንባቸው አልነበረም። ያውም ለ፱ ቀን ብቻ። እንዴት ቢያስቡት ነው? እየተተከለ ያለው ማሽን እኮ….. በትክክል ካልተገጠመ የሠራተኛውን ሕይወት በሙሉ ሊቀጥፍ የሚችል ነገር ነው።
ንዴቴን አምቄ ሊፈጠር ስለሚችለው አደጋ ለማስረዳት ሞከርኩ። ትዕግሥቴ እስኪሟጠጥ ድረስ በቻልኩት መንገድ ሁሉ ለፈለፍሁ። ጭራሽ ይግረምህ ብለው የማሽን ተከላ ሥራውን ጀመሩት። ስለሥራው ስለ ማሽኑ ጠንቅቀው የሚያውቁ ሰዎች ቢሆኑ እኔ ምንም አይገርመኝም ነበር። ነገር ግን ምንም የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ከአነጋገራቸው ራሱ መረዳት ችያለሁ። እነዚህ ሰዎች ገጠምን ብለው በሚሠሩት ስሕተት ነገ ሠርቼ እበላለሁ ያሉ የደኃ ለፍቶ አደር እጆች እየተቆራረጡ ሲወድቁ ማሽኑም ጥቅም ሳይሰጥ በማን አለብኝነት በተሠራ ስሕተት የሰው ሕይወት ሲቀጥፍ ማሰብ ዕረፍት ሊሰጠኝ አልቻለም።
ጉዳዩን ለበላይ አለቆቼ ደውዬ አሳወቅሁ። ከሰዎቹ ጋር ተገናኙ አወሩ ተጨቃጨቁ….ብዙ ብዙ ነገር። ለኔም የመጨራሻ ትእዛዝ ተሰጠኝ። በቻልኩት መጠን ነገሩን አረጋግቼ ችግሩን ለመፍታት እንድሞክር እና ካልሆነ ድርጅታችን ኀላፊነቱን እንደማይወስድና ቦታውን ለቅቄ ወደ ቢሮዬ እንድመለስ ተነገረኝ።
ዕረፍት አደረግሁና በነጋታው ከትናንትና የተራረፈች ጭላጭ ትዕግሥቴን አጠረቃቀምኩና በቦታው የሥራ መሪ ሆኖ የተመደበውን ሰው መናገር ያለብኝን ነገር ለመናገር ስጀምር ባልጠበኩት ሁኔታ በጥ…….ፊ ከደነኝ። በጣም ደነገጥሁ እንዲህ ይሆናል ብዬ አልጠበቅሁም ነበር። የምናገረው ጠፋብኝ። የምለው አጣሁ። በንዴት መንቀጥቀጥ ጀመርኩ።
የውስጤን ስሜት እንኳን ያኔ አሁንም ማሰብ አልችልም። ለራሳቸው ብዬ በረዳኋቸው? ትሞታላችሁ ይህንን አስተካክሉ ባልኳቸው?
ምንም አልተናገርኩም። ወዲያውኑ ሻንጣዬን አንሥቼ ከቦታው ጠፋሁ። አሁን ወደ መጣሁበት ለመመለስ መንገድ ከጀመርኩ ሁለት ሰዓት ተኩል ገደማ ሆኖኛል። … ይህን ሁሉ ነገር ከጎኔ ለተቀመጡት ካህን ልነግራቸው አሰብኩና ….ለኔ ራሱ እንደገና ሕመሜን መቀስቀስ ንዴቴን ማባባስ ይሆንብኛል ብዬ አጠር አድርጌ በግርድፉ
“ አባ…… ሥራ ቦታ…. እንዳትጎዱ እንርዳችሁ ያልናቸው ሰዎች …. መልሳቸው ክፋት ሆኖብኝ….. በሱ ቅሬታ ተሰምቶኝ ነው።” አልኳቸው እና ትንሽ ስለተሸማቀቅሁ ሸረፍ አድርጌ አየኋቸው። እስክመልስላቸው ዐይን ዐይኔን እያዩኝ ነበር። ሳልመልስላቸው ቆዬሁ እንዴ? አልኩ ለራሴ። በየመካከሉ መኪናው እንደመንገጫገጭ ይላል።
ጥቂት ቆይተው እንዲህ አሉኝ
“ልጄ …. አሁን ወቅቱ የጾመ ነቢያት ወቅት ነው። ነቢያት የጌታን መወለድ እየተጠባበቁ እንደጾሙት እኛም በዓለ ልደቱን ለማክበር የምንዘጋጅበት፣ ለእኛ ሲል የተቀበለውን ሥቃይና መከራ የምናስብበት ወቅት ነው። ይህንን ወቅት ስታስብ ጌታ ለድኅነተ ዓለም ለሰው ልጅ ጥቅም ሲመጣ ሲወጣ ሲወርድ ሰው በተቃራኒው የደረሰበትን መከራ ታስባለህ። እና አንተም መልካም ስላደረግህ በመልካም ፋንታ ክፉ ቢመለስልህ አይግረምህ። የሰው ልጅ መድኃኒቱን መቃወም ልማዱ ነው። ‘አውቀውትስ ቢሆን የክብርን ጌታ ባልሰቀሉት ነበር’ ይላል መጽሐፍ።” አሉኝና ወደ ፊት እያዩ ዝም አሉ።
እኔንም ወደ ሌላ አንክሮ ወሰዱኝ። ከልጅነት እስከ ዕውቀት በየቦታው የተማርኩት የነገረ ሥጋዌ ትምህርት በሐሳቤ ተመላለሰ። እንዴት ግን ክርስቶስን የሚያህል መድኃኒት በሰው ልጅ ዘንድ ተናቀ? ለዓለማት ሁሉ ፈጣሪ የሰው ልጅ ቦታ ነፍጎት በበረት ሲያስተኛው መታገሥ እንዴት አይነት ትዕግሥት ነው? ሰው ግን እንዴት ደፋር ቢሆን ነው ክፉና ደጉን ላሳይህ ያለውን ጌታውን በጥፊ የመታው?
ጌታስ እንዴት ትዕግሥተኛ ቢሆን ነው ለእርሱ አንዳች በማይጨምርለት ጉዳይ ላይ የሰውን ልጅ ያን ያህል የታገሠው። መከራ ሲያደርሱበት እንዴት ዝም አለ? የሰው ልጅ በሞት እንዳይወሰድ እስከመቃብር ድረስ መከራን የታገሠለት እንዴት ዓይነት ፍቅር ቢኖረው ነው?
እያልኩ መልስ በማላገኝላቸው የመገረም ጥያቄዎች ስወጣ ስወርድ ቆየሁና ድንገት የኔ ጉዳይ ትዝ አለኝና ውስጤ ድንግጥ አለ። ምን ያህል ከንቱ ሰው እንደሆንኩ እየተገለጠልኝ መጣ። ሰውነቴ መሸማቀቅ የጀመረ መሰለኝ። ጌታ እስከመስቀል ሥቃይን ሲቀበል፣ ለገዳዮቹ በፍቅር ሲጸልይ፣ ለወጉት መልካምን ሲያደርግ ከነበረ እኔ ስናገር አልሰሙኝም ብሎም በጥፊ መቱኝ ብዬ እንዴት ይህን ያህል እቀየማለሁ? እንዴት ወደ ስሕተት ጎዳና ሲሄዱ ወደ ጉዳት ሲገሠግሡ እያየሁ ጥያቸው መጣሁ? ምንስ ቢያደርጉኝ እና ቢበድሉኝ የኔ ጉዳት ከእነርሱ ጉዳት በልጦ ነው? እንዴት ዓይነት ከንቱ ሰው ነኝ?
በሚደርስብኝ ነገር ሁሉ ክርስቶስን መምሰል ካልቻልኩ የኔ ክርስትና ምኑ ላይ ነው? የልቤ ላይ እምነት አንሳ አንሳ እጅ….ግ ኢምንት ሆነችብኝ። ወደ ሥራ ቦታው ልመለስ ፈለግሁ። ብዙ ርቀት መጥቻለሁ። እንደሚታየኝ ሁሉ አንገቴን አዙሬ በመኪናው የጀርባ መስታወት ወደኋላ ተመለከትሁ። አካባቢው ከዐይኔ ተሠውሯል። በረጅሙ ተነፈስኩ።
ድጋሚ ስሜቴ ተቀይሮ ከፋኝ። አዲስ አበባ እንደደረስኩ ተመልሰህ ሂድ ብባል እና ብመለስ ደስተኛ ነኝ። የዛሬውን ፈተና ወድቄያለሁ። ለወደፊት ፈጣሪዬ እንደገና ዕድል ከሰጠኝ ለማስተዋል እሞክራለሁ። በእነዚህ ሁሉ ዓመታት ባሳለፍኩት የክርስትና ጉዞዬ መንፈሳዊነት አልገባኝም። ቢገባኝ ባስተውል ኖሮ እነዚያ ሰዎች አውቀውም ይሁን ሳያውቁ ለኔ ጥሩ የትሕትና ትምህርት እየሰጡኝ መከራንም እያለማመዱኝ ነበር። ምን ያደርጋል….. አልቻልኩበትም።
አወይ የኔ ክርስትና ….. እኔም ክርስቲያን ቅዱስ እስጢፋኖስን ቅዱስ ዮሴፍን የመሰሉ ብርቱና አስተዋይ ወጣቶችም ክርስቲያን…… አልኩና በራሴ እጅግ ተናደድኩ ራሴን ታዘብኩት። ድንገት ከጎኔ የተቀመጡት አባት ትዝ አሉኝና ቀስ ብዬ በኃፍረት አንገቴን በግማሽ አዙሬ አየኋቸው። ፊት ለፊት እያዩ በራሳቸው ሐሳብ የተወሰዱ ይመስላሉ። ዳዊታቸውን በእጃቸው ይዘው እያንሰላሰሉ ከጎናቸው መቀመጤን የረሱ ይመስላል።
እውነታቸውን ነው… ምኔ ይታወሳል ደግሞ እኔ። እንደገና በራሴ ሁኔታ በመከፋት አዲስ አበባ ለመድረስ የሁለት ሰዓት ያህል ጉዞ የሚቀረውን መኪና መስኮት ተደግፌ በራሴ እምነተ ቢስነት ላይ ትካዜዬን ቀጠልሁ።
ለካ ክርስቶስ በየዕለቱ እየተወለደ በየዕለቱ በልባችን ግርግም ይተኛል። ለካ በየዕለቱ በሕይወታችን አደባባይ ይገረፋል፤ ይገፈፋልም። ለካ “ኑ ሕይወትን ታገኙ ከሞት ትድኑ ዘንድ ሥጋዬን ብሉ ደሜንም ጠጡ” እያለ ለሚጣራው ጌታ መልሳችን መከራ እና ክፋት ሆኗል ። የእኝህ ካህን እጅግ ያነሠች እና ያልተዝረከረከች ንግግር እንደነፋስ ሽውታ ውልብ ሽው… ብላ ነገሬን ሁሉ መረመረችው ራሴንም ለራሴ ገለጠችልኝ። ምን ጊዜም ቢሆን ጾመ ነቢያትና የጌታ ልደት ለእኛ ሕይወት እንደ መስታወት ነው። ራስን መመልከቻ የነፍስ መስታወት ስለሚያገለግል ልንጠቀምበት ይገባል።