Wednesday, 07 April 2021 00:00

ዘር ቆጣሪ

Written by  እንዳለ ደምስስ

Overview

የቀኑ ሐሩር አናት ይበሳል፣ ከአስፋልቱ ግለት የሚወጣው ወላፈን ፊትን ከመለብለብ አልፎ ልብ ይሰልባል። በዚያ ጠራራ ፀሐይ እመቤት ከንስሓ አባቷ ጋር ለያዘችው ቀጠሮ በሰዓቱ ለመድረስ እየተጣደፈች ከአራት ኪሎ ቁልቁል በመውረድ፣ በፓርላማ በኩል አድርጋ ወደ ታእካ ነገሥት በአታ ለማርያም ገዳም አቀናች። ቁና ቁና እየተነፈሰች ታእካ ነገሥት በአታ ለማርያም ገዳም ስትደርስ አማትባ ወደ ውስጥ በመግባት በስተቀኝ ካለው ዛፍ ሥር ድንጋይ ላይ ዐረፍ አለች። ቀይ ፊቷ ብስል ቲማቲም መስሏል፤ በነጠላዋ ጫፍ የፊቷን ላብ ጠርጋ በረጅሙ “ኡፍፍፍፍ…” ብላ የድካም አየር አስወጥታ ዛፎቹና ንፋሱ ከሚፈጥሩት ቀዝቃዛ አየር ወደ ውስጥ ሳበች። ጥቂት ዕረፍት አድርጋ አስፋልቱን ይዛ በቀዝቃዛ አየር ታጅባ ወደ ቤተ ክርሰቲያኑ አመራች። የታእካ ነገሥት በአታ ለማርያም ገዳም ግቢ በጥንታዊ ሀገር በቀል ዛፎች እንደተከበበ ግርማ ሞገሱን ተላብሶ ይታያል፣ ነፋሻማው አየር ደግሞ ለነፍስ ሐሤትን ያጎናጽፋል፣ የአዕዋፋቱ ዝማሬ በተመስጦ ሰማየ ሰማያት አድርሶ ይመልሳል። እመቤት ቅዳሴ ከተጠናቀቀ በኋላ ስለደረሰች ግቢው ውስጥ የሰው ዘር አይታይም። ወደ ቤተ ክርስቲያኑ እንዳቀናች በሴቶች መግቢያ በኩል በማምራት ተንበርክካ በመሳለም የልቡናዋን መሻት ይፈጽምላት ዘንድ ፈጣሪዋን፣ እንዲሁም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን በምልጃዋ እንድትረዳት ስትማጸን ቆየች። 

 

የኔታ ወልደ ዮሐንስ ከቅዳሴ በኋላ ጥቂት ዕረፍት ወስደው በቀጠሯቸው መሠረት እመቤትን ለማግኘት በገዳሙ ግቢ ውስጥ ካለው ማረፊያ ቤታቸው በመውጣት ወደ ሥዕል ቤት ኪዳነ ምሕረት በማምራት ከተሳለሙ በኋላ እመቤትን ፍለጋ በዐይኖቻቸው ግራ ቀኝ አማተሩ። 

እመቤት ቀድማ ስላየቻቸው በፍጥነት ወደ ንስሓ አባቷ አመራች። መስቀል ተሳልማ ከዛፎቹ መካካል በመግባት ጠፍጣፋ ድንጋዮችን ፈልገው ተቀመጡ። ሁለቱም ስለ ቤተሰብ፣ ስለ ጤንነት፣ ከተጠያየቁ በኋላ በመካከላቸው ጸጥታ ሰፈነ። የኔታ ወልደ ዮሐንስ እመቤት ልትነግራቸው የፈለገችውን ነገር ለመስማት ከአሁን አሁን ትናገራለች ብለው እየጠበቁ ነው፤ እርሷ ደግሞ ከየት እንደምትነሣ ግራ ገብቷት የምትጀምርበትን ጫፍ ፍለጋ በሐሳብ አንዱን ጥላ አንዱን ስታነሣ ቆየች። 

“ትርሲተ ማርያም፣ እስቲ እንደዚያ ያስጨነቀሽን ነገር ከመጀመሪያው ጀምረሽ ንገሪኝ። ምንድነው የገጠመሽ?” አሉ የኔታ ወልደ ዮሐንስ የእመቤት ዝምታ ግራ አጋብቷቸው። ጠዋት በስልክ እንደምትፈልጋቸው እያለቀስች ስትነግራቸው የጉዳዩ አሳሳቢነት አስጨንቋቸው ነበር። አሁን ደግሞ ጣቶችዋን እያፍተለተለች አቀርቅራ ሲመለከቷት መናገር እስክትጀምር በትዕግሥት ለመጠበቅ ወሰኑ።  

እመቤት ካቀረቀረችበት ቀና ብላ የኔታ ወልደ ዮሐንስን ተመለከተች። “እንዴት እንደምነግርዎ ተቸግሬ ነው” አለች።

“ግድ የለሽም ልጄ አባትሽ ነኝ። ከእኔ የምትደብቂው ነገር አይኖርሽም። ብትደብቂ ደግሞ ኃጢአት ነው፤ ስለዚህ ንገሪኝ” አሉ የኔታ ወልደ ዮሐንስ ትኩር ብለው እየተመለከቷት።

ትርሲተ ማርያም ጥቂት ስታሰላስል ቆይታ “ወላጆቼ ከተለያዩ ብሔረ ሰቦች የተገኙ ናቸው። በፍቅር ኖረው ከእነርሱ የተገኘነውን ሦስት ልጆቻቸውን በፍቅር  አሳድገው፣ በሃይማኖታቸው ጸንተው፣ እኛንም በሰንበት ትምህርት ቤት እንድንማር፣ ከመንፈሳዊው ማዕድ እንድናቋደስ፣ የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ጣዕም እንድንቀምስ ያደረጉና ለወግ ለማዕረግ ያበቁ ናቸው። አንድም ቀን ብሔራቸው በመካከላቸው እንቅፋት ሆኖ አያውቅም። የሁለቱንም ቤተሰቦች እኩል ዐውቀን፣ በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ሁለቱም አያቶቻችን ዘንድ እየሔድን ምርቃት ተቀብለን ዛሬ ላይ ደርሶናል። 

እግዚአብሔር ፈቅዶልኝ እኔም ቤተሰብ የመመሥረት ዕድሉ ገጥሞኛልና ምኞቴ ሁሉ ወላጆቼ ባለፉበት መንገድ በማለፍ በፍቅር መኖር ነበር። ምኞቴ ግን በአጭሩ ተጨናገፈ- አባቴ!” በማለት ስቅስቅ ብላ አለቀሰች።

የኔታ ውልደ ዮሐንስ በዝምታ እያደመጧት ነበር። ለማባበል አልሞከሩም። ‘ትንሽ አልቅሳ ይውጣላት’ በሚል ዝምታን መረጡ።

እመቤት ለተወሰኑ ደቂቃዎች እያለቀሰች ከቆየች በኋላ ራሷን አረጋግታ ያስጨነቃትን ሁሉ ለመተንፈስ ተዘጋጀች። “ይቅርታ አባቴ! የደረሰብኝ ነገር ዕረፍት ነስቶኝ ነው። እርስዎም እንደሚያውቁት ከባለቤቴ ጋር በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ወደንና ፈቅደን ከተጋባን ገና ስድስተኛ ወራችን ነው። ነገር ግን ገና ሳንጀምረው ልንለያይ ነው። በዚህ ላይ የሦስት ወር ፅንስ በሆዴ ቀርቷል። አባቴ ትዳሬን ያድኑልኝ!” ብላ እያለቀሰች ከየኔታ ወልደ ዮሐንስ እግር ሥር ተደፋች። 

የኔታ ከተቀመጡበት ተነሥተው እመቤትን ከተደፋችበት ለማንሣት ታገሉ፤ ግን አልቻሉም። “የኔ ልጅ ሁለታችሁም ከእግዚአብሔር የተሰጣችሁኝ ልጆቼ ናችሁ፤ ችግራችሁ ችግሬ ነው። አቅሜ የፈቀደውን ሁሉ አደርጋለሁ፣ እግዚአብሔርም ይረዳናል። በዚህ አጭር ጊዜ ደግሞ ምን ተፈጠረ? ባለፈው ሳምንት ፍቅረ ማርያምን አግኝቼው ነበር ምንም የነገረኝ ነገር የለም። ምንድነው የተፈጠረው ትርሲተ ማርያም?!” አሉ ግራ በመጋባት። 

እመቤት ፈቃደኛ ስለሆኑላት ደስ ብሏት ከወደቀችበት ተነሣች። “ይቅርታ አባቴ፣ ስለጨነቀኝ ነው። ትዳሬን በፍጹም ማጣት አልፈልግም። ግን የብሔርና ቋንቋ ጉዳይ ትዳሬን ሊያፈርስብኝ ነው። እኔና ብርሃኑ የተገናኘነው ገና በለጋነታችን በትምህርት ቤት ውስጥ ነው። በወቅቱ ለመንፈሳዊ ትምህርት ብዙም የቀረበ ስላልነበር በሰንበት ትምህርት ቤት እንዲሳተፍ፣ በተሰጠው ጸጋ ደግሞ ቤተ ክርስቲያንን እንዲያገለግል ገፋፍቼው ተሳክቶልኝ ነበር። ከልጅነት የተመሠረተው ትውውቃችን አድጎ በዩኒቨርሲቲም ቀጥሎ ሥራ ከያዝን በኋላ እግዚአብሔር ፈቅዶ እርስዎም እንደሚያውቁት ለትዳር በቃን። አሁን ግን ትዳሬ አደጋ ላይ ወድቋል። 

ባለቤቴ ብርሃኑ በቅርቡ ጸባዩም፣ ቋንቋውም ተለውጧል፣ አብዛኛውን ጊዜ የሚያናግረኝ ሁለታችን በምንግባባበት ቋንቋ አይደለም። እኔ ደግሞ እርሱ የሚናገረውን ቋንቋ አልችልም። አልፎ አልፎ ደግሞ በአማርኛ “ገና ምን አይተሽ እናጠፋችኋለን!” እያለ ይዝትብኛል። የራሱን ብሔር መርጦ አለማግባቱንና እኔንም በማግባቱ እንደተጸጸተ ይነግረኛል። ሰክሮ ገብቶ በውድቅት ሌሊት ከቤት እያባረረኝ ጎረቤት ለበርካታ ቀናት አድሬ አውቃለሁ። አንድም ቀን በመካከላችን ስለ ብሔራችን አንስተን የተነጋገርንበት ጊዜ አልነበረም። አሳስቦንም አያውቅም ነበር፤ አሁን ግን ምን አዲስ ነገር እንደ ተከሠተ ግራ አጋብቶኛል። መኝታ እንኳን ከለየን ሁለት ወራት ተቆጥረዋል።” 

የተከሠተውን ችግር ለቤተሰቦቼ ባማክራቸውም ትተሽው ነይ እኛ ለአንቺ መሆን አያቅተንም። ወይ እርሱን በይ ወይ እኛን በይ ብለው ርቀውኛል። እኔ ደግሞ የልጅነት ፍቅሬን ትቼ መሄድ አልፈለግሁም። በርካታ ዘመናት በፍቅር ቆይተናል። አሁን ወደ ብሔሩ አደላ ብዬ ልሸሸው አልፈልግም። ከእግዚአብሔር የተሰጠኝ ስጦታዬን፣ በእግዚአብሔርና በቅድስት ቤተ ክርስቲያን በካህኑ ፊት የገባሁትን ቃል አላጥፍም” አለች እመቤት መፍትሔ በመሻት የኔታ ወልደ ዮሐንስን እየተመለከተች።

የኔታ በሰሙት ነገር በጣም ተገርመዋል፣ አዝነዋልም። 

“ልጄ ጊዜ ያመጣው ጣጣ ነው። እግዚአብሔር ተቆጥቶናል፤ ለዘመናት በአባቶቻችን ተጋድሎ፣ በቅዱሳን ጸሎት ተጠብቃ የኖረችን ሀገር ለማፍረስ ዲያብሎስ ጦሩን ሰብቆ፣ ጎራዴውን ስሎ መጥቷል። ይህ ይሆን ዘንድ ግድ ከሆነ ምን እናደርጋለን? የቻለ እግዚአብሔር ቁጣውን በምሕረት እንዲመልስልን እንደ ነነዌ ሰዎች መጾም፣ መጸለይ ነው። ዛሬ ሀገራችን ታማለች፣ ሁሉም ዘር ቆጣሪ ሆኗል፣ አንድ አድርጋ አስተባብራ የእግዚአብሔርን መንግሥት ስትሰብክ የኖረችውን ቤተ ክርስቲያንን ለማጥፋት የማይቆፍሩት ጉድጓድ፣ የማይፈጥሩት አዲስ ታሪክ የለም። የአንድ እግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን፣ መኖሪያችን በሰማይ መሆኑ ተዘንግቷል። ለመሆኑ ለምን እንዲህ እንደሚያደርግ ጠይቀሽው ታውቂያለሽ?” አሉ ውስጣቸው እያዘነ።

“ምንም የሚመልሰው መልስ የለውም። ስጠይቀው ለመማታትና እኔን ለመርገም ይፈጥናል፣ ቤተ ክርስቲያን ላይ ጸያፍ ስድብ ይሳደባል፣ ይባስ ብሎ ትናንት አምሽቶ መጥቶ ‘መፋታት እፈልጋለሁ’ አለኝ። ሐሳቡን ይቀይር ይሆናል፣ አንድ አድርጎም ያስተሳስረናል ብዬ እርጉዝ እንደሆንኩ ነገርኩት። ነገር ግን የተረፈኝ ዱላ ነው። ‘አልፈልገውም አስወጪው’ አለኝ። አባ እኔ በጣም ተጨንቄያለሁ። ምን ላድርግ?” አለች በሁለቱም ጉንጮችዋ የማያቋርጥ የዕንባ ጎርፍ እየጎረፈ።

የኔታ ወልደ ዮሐንስ በሚሰሙት ታሪክ እንዳዘኑ መፍትሔ ፍለጋ አቀረቀሩ። ከጥቂት ቆይታ በኋላ ካቀረቀሩበት ቀና ብለው “ፍቅረ ማርያምን ወደ እኔ ይዘሽው መምጣት ትችያለሽ?” አሉ በጥርጣሬ።

“አባቴ አልችልም። በተደጋጋሚ ለምኜዋለሁ። እንኳን እርስዎ ዘንድ ለመምጣት ቤተ ክርስቲያንም ላለመሔድ ወስኗል።” 

“ልጄ ይህ እኔ ላይ ለምን ሆነ ብለሽ እግዚአብሔርን እንዳታማርሪ፤ ከአንቺ የሚጠበቀው በሃይማኖት ጸንቶ እግዚአብሔርን በጸሎት መለመን ብቻ ነው። ከክፉ ራቂ፣ ክፉን በክፉ አትመልሺ። አሁን ያለንበትን ዘመን መሻገር የምንችለው በጾም በጸሎት፣ መልካም ነገርን በማድረግ ብቻ ነው። ሀገራችን በዘር፣ በሃይማኖት ተከፋፍላ ሁሉም እኔ እኔ የሚልበት ወቅት ነው። ነገር ግን ዘላቂነትም የለውምና አትረበሺ። ነገ በሌሊት ከቤት ከመውጣቱ በፊት እቤታችሁ እደርሳለሁ፣ ራስሽን ጠብቂ ልጄ” አሉ እመቤትን እያጽናኑ።

“አባቴ ይህንን ጊዜ በጽናት አልፈው ዘንድ ጸልዩልኝ። እኔ ፈርቻለሁ፤ ወይ ከትዳሬ አልሆንኩ ወይ ከቤተሰቦቼ አልሆንኩ ተጨንቄ ነው” አለች በውስጧ ፍርሃት እንደ ነገሠ።

“አይዞሽ እግዚአብሔር ይረዳናል” ብለው ጸሎት ጸልየው አሰናበቷት።

 

የኔታ ወልደ ዮሐንስ ከሌሊት ጀምሮ ከካህናቱ ጋር ስብሐተ እግዚአብሔር ሲያደርሱ ቆይተው ኪዳን እንደተጠናቀቀ አራት ኪሎ ወደሚገኘው ብርሃኑና እመቤት ቤት አመሩ።

እንደደረሱም “እንደ ምን አደራችሁ ቤቶች?” አሉ የኔታ ወልደ ዮሐንስ።

እመቤት ቀድማ ተነሥታ ሳሎን ውስጥ ሆና ትጠባበቅ ስለነበር “እግዚአብሔር ይመስገን፤ ይግቡ” አለች የሳሎኑን በር እየከፈተች። 

“ደኅና አደራችሁ ልጆች? በሌሊት መጥቼ ቀሰቀስኋችሁ?” አሉ ወደ ሳሎን ገብተው እመቤትን መስቀል እያሳለሙ።

“አይ አባቴ ከተነሣሁ ቆይቻለሁ። ዐረፍ ይበሉ” አለች ሶፋውን እንደማስተካከል ብላ እንዲቀመጡ እያመለከተቻቸው።

“ትርሲተ ማርያም አልቀመጥም። እስቲ በጣሳ ውኃ አምጪ ጸሎት ላድርስ። ፍቅረ ማርያም አልተነሣም እንዴ? ቀስቅሺው እንጂ።”

“እሺ” ብላ ወደ መኝታ ቤት ልትገባ ስትል ብርሃኑ ከነ ሌሊት ልብሱ ዓይኑን እያሸ ብቅ አለ።

“እንዴት አደርክ ልጄ?” ብለው ሊያሳልሙት መስቀላቸውን ወደ ግንባሩ ሲያስጠጉ ብርሃኑ ለመከላከል ሞከረ።

“ምነው ልጄ? መስቀል አትሳለምም እንዴ?” አሉ መስቀላቸውን እየመለሱ።

“አይ ዝም ብዬ ነው።” ብርሃኑ አመነታ።

“ምን ማለትህ ነው? ከመቼ ወዲህ ነው መስቀሉን መሸሽ የጀመርከው? በመስቀሉ አምላካችን ስለ ሰው ልጆች የከፈለውን ዋጋ ምነው ዘነጋህ? በል ና ተሳለም” አሉት ትእዛዝ ባዘለ ድምፀት።

ብርሃኑ እያመነታም ቢሆን መስቀሉን ተሳለመ።

እመቤት በጣሳ ውኃ አቀረበች።

የኔታ ወልደ ዮሐንስ ብርሃኑን ካሳለሙ በኋላ ጸሎታቸውን ቀጠሉ።

ብርሃኑና እመቤት የኔታ ወልደ ዮሐንስን ተከትለው ለጸሎት ቆሙ። ብርሃኑ በስርቆሽ እመቤት ላይ ከንፈሩን በጥርሱ እየነከሰ “እሠራልሻለሁ!” የሚል ዛቻ በምልክት እያሳያት ለማስፈራራት ሲሞክር ቆየ።

የኔታ ጸሎታቸውን አጠናቅቀው ሁለቱንም ጸበል ከረጩ በኋላ ቤቱንና ደጁን ሁሉ ረጭተው ተመለሱ።

“በሉ ኑ እስቲ ዐረፍ እንበልና ጥቂት ቃለ እግዚአብሔር እንማማር” ብለው ሁለቱንም እንዲቀመጡ ጋብዘው ከመጽሐፍ ቅዱስ “መጋባት በሁሉ ዘንድ ክቡር መኝታውም ንጹሕ ይሁን”(ዕብ.፲፫፥፬) በሚል ቃል ማስተማራቸውን ቀጠሉ። በትምህርታቸውም ባልና ሚስት በፍቅር ሊኖሩ እንደሚገባቸው፣ከእግዚአብሔር ፍቅር እንዳይወጡ በጊዜያዊ ስሜትና ፍላጎት እግዚአብሔርን እንዳያሳዝኑ፣ ከዘመኑ ብሔር አቀንቃኞችና ጦርነት ናፋቂዎች እንዲጠበቁ  ምክር አዘል ትምህርታቸውን አስተላለፉ።

ከትምህርቱ በኋላ የኔታ ወልደ ዮሐንስ ቁጭ ብለው “እሺ ትዳር እንዴት ነው?” ብለው ሁለቱንም ጠየቁ። እመቤት ዝምታን ስትመርጥ ብርሃኑ ከአንገቱ አቀረቀረ።

“ተናገሩ እንጂ!” አሉ ወደ ብርሃኑ እየተመለከቱ።

“ጥሩ ነው” አለ ብርሃኑ እንዳቀረቀረ።

“ጥሩ ነው ብቻ ማለት በቂ ነው?” አሉት በእርጋታ እየተመለከቱት።

“አይ አባቴ አሁንም የቆየሁት እርስዎን በማክበር ነው እንጂ በትዳሬ ደስተኛ አይደለሁም። መፋታት እፈልጋለሁ” አለ ካቀረቀረበት ቀና እያለ።

“ምን ማለት ነው። ትዳር ዝም ብለው የሚያፈርሱት የመንገድ አጥር ነው እንዴ ልጄ? የመንገድ አጥርም እኮ ባለቤት አለው፤ ያለ ምክንያትም አይፈርስም። ለመሆኑ ምክንያትህ ምንድነው? ትርሲተ ማርያም አስቀይማሃለች እንዴ?”

“አይ። በቃ እኔ ዘሬን ነው ማግባት የምፈልገው። ተሳስቼ ነበር።”

“ዘር ስትል ምን ማለት ነው?”

“በቃ ከብሔሬ ነው ማግባት የምፈልገው።”

“ክርስቲያን ብሔሩ ወዴት ነው? ዘሩስ ከወዴት ነው? ዳግመኛ የተወለዳችሁት ከሚጠፋ ዘር አይደለም፣ በሕያውና ለዘለዓለም በሚኖር በእግዚአብሔር ቃል ከማይጠፋ ዘር ነው እንጂ” ይላል የእግዚአብሔር ቃል በሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ ላይ አድሮ። (፩ኛ ጴጥ.፩፥፳፫)። እኛ ክርስቲያኖች የእግዚአብሔር ልጆች ነን። “እኛ የእግዚአብሔር ልጆች እንደሆን ለልቡናችን ምስክሩ መንፈስ ቅዱስ ነው። እኛ የእግዚአብሔር ልጆች ከሆንን ወራሾቹ ነን” የሚልም ቃል በሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ሮሜ ሰዎች መልእክት ላይ ተጽፎ እናገኛለን። (ሮሜ.፰፥፲፮):: ስለዚህ ከሰማያዊ አባቱ ሸሽቶ ምድራዊው ብልጭልጩን ዓለም ሽቶ ወዴት ሊሄድ ይገባዋል? የአባቱ ርስት ተካፋይ ይሆናል እንጂ አይኮበልልም። ተጠንቀቅ ልጄ። ዘመኑ ባነፈሰው ንፋስ አትወሰድ፣ ቆም ብለህ አስብ። ወደ ጥፋት ጎዳና እያመራህ እንደሆነ አስብ። የዘመኑ ፖለቲከኞች በሚነዙት ወሬና አሉባልታ ተሸብረህ ከአባትህ ቤት፣ እስከ ሞትም ድረስ ከታመነ አምላክ ፊት አትኮብልል። መጨረሻው ጥፋት ነው። ሉቃስ ፲፭ ላይ ከአባቱ ቤት እንደ ኮበበለው ልጅ የእሪያዎች ጠባቂና የእነርሱንም ትርፍራፊ የምትለቃቅም አትሁን። እግዚአብሔር መርጦ ከሰጠህ ትዳርህ አትኮብልል።

ዘር፣ ብሔር የምትለው ነገር አያዛልቅህም። በባዶ ትርክት ትዳርህን በትነህ በነፍስም እንዳትጠየቅ አሁንም ቆም ብለህ አስብ። ሀገርን ለመበተን ልትተባበር ትችል ይሆናል፣ ዛሬ አይዞህ የሚሉህ ሁሉ ገንዘብ ሊሰጡህ ይችሉ ይሆናል፣ ንብረት ሊያካፍሉህ፣ ሥልጣን ሊሰጡህ ይችሉ ይሆናል። እንዳንተው እግዚአብሔር በአምሳሉና በአርአያው የፈጠረውን የሰው ልጅ ልታጠፋ ትሮጥ ይሆናል፤ እግዚአብሔር ስላጠፋኽው ነፍስ ከእጅህ ይቀበላል፣ እግዚአብሔር መልሶ አንተን እንደሚያፈርስህ ዕወቅ። የቀደመውን ፍቅርህን ትተሃልና ልተፋህ ነው እንዳይልህ እግዚአብሔር በሰከነ መንፈስ ራስህን ጠይቅ፣ ጎዳናው ወዴት እንደሚወስድ ሳታውቅ እርምጃ አትጀምር። ተጠንቀቅ!” አሉ የኔታ ወልደ ዮሐንስ በስሜት ተውጠው።

ሳሎኑ በዝምታ ማዕበል ተመታ። ዝምታ ሰፈነ፣ ሁለቱም የትዳር አጋሮች ካቀረቀሩበት ቀና ማለት ተሳናቸው። እመቤት እግዚአብሔርን እየተማጸነች ዕንባዋን ታጎርፈዋለች፤ ብርሃኑ አንደበቱ ተለጉሞ መልስ ፍለጋ ቢሽከረከርም ጠብ የሚል ነገር በማጣቱ ዝምታን መረጠ።

“ትርሲተ ማርያም እስቲ ንገሪኝ፣ ምንድነው የተፈጠረው?” አሉ ከብርሃኑ መልስ በማጣታቸው።

እመቤት እያነባች “አባቴ እኔ ትዳሬን ከማክበር፣ እንደ አቅሜም እግዚአብሔርን በመፍራት በታማኝነት ከመኖር ውጪ ምንም አላውቅም። ባለቤቴን ከልጅነት ጀምሮ ስወደው ኖሬያለሁ፣ ሳስብለትና ስጨነቅለት፣ ሳፈቅረውም ኖሬያለሁ፤ አሁንም እወደዋለሁ። ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ ግን ዓይንሽን ለአፈር ብሎኛልና ትዳሬን እንዲታደጉልኝ ነው የምፈልገው” አለች በነጠላዋ ጫፍ ዕንባዋን እየጠረገች።

“በል እስቲ ፍቅረ ማርያም ምንም ሳትደብቅ ንገረኝ። ዘር፣ ብሔር ስትል ምን ማለትህ ነው? ከእግዚአብሔር ይበልጥብሃልን? ሁላችንም የእግዚአብሔር ልጆች አይደለንም እንዴ? እስቲ መልስህን ልስማው?” አሉ የኔታ ወልደ ዮሐንስ።

ሲያመነታ ቆይቶ “የምትሉት እውነት እንደሆነ አውቃለሁ። እስከ ዛሬም ይህንን አምኜ ነው የኖርኩት። አሁን ግን በየሚዲያው የምሰማው፣ የቤተሰቦቼና የጓደኞቼ ግፊት ያለፈውን ሕይወቴን እንድጠላ፣ አዲስም ሰው እንድሆን ውስጤ ገፋፋኝ። እውነቱ የቀደመው እንደሆነ ብረዳም አሁን በዘመኑ ላለው አስተሳሰብ ተሸነፍኩ። እኔ ባለቤቴን ጠልቻት አይደለም ግን አዳዲስ ትርክቶችን በሰማሁ ቁጥር ውስጤን ፍቺ እንድፈጽም እየገፋፋኝ ያደረግሁት ነው” አለ ብርሃኑ ጸጉሩን አሥር ጊዜ እያሸ።

“እንግዲያውስ እውነቱን ተጋፈጥ ልጄ። ለምን እንዲህ አደረግህ ብዬ ለሌላ ጥፋት እልህ ውስጥ እንድከትህ አልፈልግም። ወደ ራስህ ተመለስ። ይህ ጊዜ የወለደው ትርክትና ፉከራ አንድ ቀን ያበቃል፣ ዛሬ ያፈረስከው ትዳርህን፣ የካድከው የአብራክህ ክፋይን ግን ታጣለህ። ከሁሉም በላይ ደግሞ እግዚአብሔርን ታጣለህ። ስለዚህ ወደ ትዳርህ ወደ እግዚአብሔርም ተመለስ። ዘር የሚያስፈልገው ገበሬው ነገ ለሚያመርተው ምርት ነው። ሳይገባህ ያለ ሥራህ ዘር ቆጣሪ አትሁን። በኋላ ታዝናህ። በል እኅትህን፣ የትዳር አጋርህን አሳዝነሃታልና ይቅርታ ጠይቃት።” አሉት በአባትነት ተግሣጽ።

ብርሃኑ ከዚህ በላይ መጓዝ አልቻለም። በእመቤት እግር ሥር ይቅርታን ፍለጋ ወደቀ። ሁለቱም ተቃቅፈው ተላቀሱ። የኔታ ወልደ ዮሐንስ በቀላሉ ስለተመለሰላቸው ልቡን ከፍቶ እንዲራራና ወደ ቀደመ ማንነቱ እንዲመለስ ያደረገውን እግዚአብሔርን አመሰገኑ። ሁለቱንም አስታርቀውና ቀኖና ሰጥተው ወደ በኣታ ለማርያም ገዳም ተመለሱ።   

Read 1306 times