Friday, 16 October 2020 00:00

“በፈረሰበት በኩል በፊቴ የሚቆምላትን ሰው ከእነርሱ  መካከል ፈለግሁ።”  (ሕዝ.፳፪ ፥፴)

Written by  ዲ/ን ተስፋዬ አሰፋ

Overview

ይህን ቃል የተናገረው ነቢየ እግዚአብሔር ሕዝቅኤል ነው። ሕዝቅኤል ማለት ጽኑዕ፣ ጽንዐ እግዚአብሔር ማለት ነው። ቃሉን የተናገረውም በኢኮንያን ተማርኮ ባቢሎን ከሕዝቡ ጋር በወረደበት ጊዜ ነው። በዚህ ርእስ ሊተላለፍ የተፈለገው የፈረሰችው ኢየሩሳሌም ለጣዖት ሰገደች፤ ሌባ፣ ቀማኛ በዛብሽ፤ ልጆችሽ ወላጆቻቸውን የማያከብሩ ሆነዋል፤ የንጹሓንን ደም አፈሰስሽ፤ እንደ ነዌ ዝናመ ምሕረት የማዘንብባት የነበረሽው ኀጢአትሽ ከሰዶም በልጧልና ዳግማዊት ሰዶም ተባልሽ፤ ካህናቶችሽ ሕጌን ጣሱ፣ ቤተ መቅደሴን አረከሱ፤ እናም አምባውን አጽንቶ በፊቴ የሚቆም አርበኛ ሰው ከመካከላችሁ ፈለግሁ። ይኸውም እንደ ሙሴ እስራኤልን በንስሓ አድሶ፣ በረድኤት ተካሶ ለማማለድ በፊቴ የሚቆም ጻድቅ ሰው ፈለግሁ። ሕዝቡም ወንበዴዎች ቀማኖች ሆኑ ይህ ሁሉ ሆነ፤ የፈረሰውን ቅጽር የሚሠራ፣ በፈረሰበት በኩል የሚቆምላትን ሰው እፈልጋለሁ አለ እግዚአብሔር። ዛሬም እግዚአብሔር ሰው ይፈልጋል። በዚህ ርእስ ውስጥ አስፈላጊ የሆነ ጻድቅ ሰው እናያለን ስሙም ነህምያ ይባላል። (ሕዝ.፳፪፥፴ አንድምታ) ኢየሩሳሌም በጠላቶቿ ፈርሳ፣ ቋያ በቅሎባት እና አራዊት ሰፍሮባት በተበተነችበት ዘመን ቅጥሯን ሊሠራ የበረታው ነህምያ ነበር። ለመኾኑ ኢየሩሳሌም የተባለች ማን ነች? የፈረሰ ግንቡዋ ምንድን ነው?  እኔ እና እናንተ የፈረሰውን ግንብ ለመሥራት ምን እና በየት በኩል እንድንቆምላት ትፈልጋለች? ምን ልናደርግላት ያስፈልጋል?   ኢየሩሳሌም የተባለች ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ናት። ቤተ ክርስቲያን ዛሬ በብዙ ጉዳዮች ፈርሳለች። ለመሆኑ ነህምያ የተባልን እኛ ምእመናን  የጸናች ግንብ የተባለች ቤተ ክርስቲያን በፈረሰበት በኩል እንድንቆምላት ምን መረዳት ያስፈልገናል?  ፩. በፈረሰበት በኩል ለመቆም የሀገርን ፖለቲካዊ አዝማሚያ ተረድተናል? ነህምያ በቤተ መንግሥት በመጋቢነት የሚያገለግል፣ አምላኩን የሚፈራ፣ ለቤቱ የሚቀና ምእመን ነበር። በሱሳ ግንብ ተቀምጦ ከዚህ በፊት የፈረሰች ኢየሩሳሌምን መፍረስ በሰማ ጊዜ «በሮችዋ ተቃጥለዋል አሉኝ ይህን ቃል በሰማሁ ጊዜ ተቀምጬ አለቀስኩ፤ አያሌ ቀንም አዝን ነበር» እንዳለ የቤተ ክርቲያንን ቀዳዳ ለመሸፈን በፈረሰበት በኩል ለመቆም ካህን አልያም ባለሥልጣን እንዳልነበረ ሁሉ ለሀገርህ እና ለቤተ ክርስቲያን ዘር፣ ቀለም፣ ጎጥ፣ ሀገር፣ ልጅ፣ ወንዝ፣ ሳንል «እኛ ሀገራችን በሰማይ ነውና ከዚያም ደግሞ የሚመጣ መድኃኒትን እርሱንም ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን እንጠባበቃለን» እንደተባለ ወገናችን እግዚአብሔር፣ ወገንተኛነታችን ለቤተ ክርስቲያን መሆን አለመሆኑን ማረጋገጥ ይኖርብናል። (ነህ.፩፥፬፤ ፊል.ጵ ፫፥፳)  ዛሬ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን እያንዳንዱ ምእመን ነህምያ ነው። ለቤተ ክርስቲያን ራእይ ያለው፣ በአንድነት የሚያምን የኢየሩሳሌም ቤተ ክርስቲያን የወደቁ የተቃጠሉ የመቅደስ በሮች ከሌሎች ወንድሞቹ ጋር በኅብረት የፖለቲካ እና የዘር ሽኩቻውን ትቶ ከነገዱ እና ከዘሩ ይልቅ ቤተ ክርስቲያን መቅደሱ የምትበልጥበት፣ በፈረሰበት በኩል የሚቆም ነህምያ ቤተ ክርስቲያን ትሻለች። እኛስ ነህምያ ነን? እርሱ የፈረሰው ግንቡ ብቻ አይደለም፣ የፈረሰው ሥነ ልቦናችንም ነው ብሎ በማመኑ ፶፪ ቀናት ሙሉ ጠላት ግንቡን ሊያፈርስ ቢመጣ እንዴት መጠበቅ፣ እንዴት ማገልገል እንዳለባቸው በቃለ እግዚአብሔር ሠርቷቸዋል። «የሕዝቡም ልብ ለሥራው ጨከነ» እንዳለ ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ደጀን ለመኾን እንጨክን።  (ነህ. ፬፥፮)  ከዚህ ባለፈ አንድ ምእመን ካልጾመ፣ ካልጸለየ፣ ቅዳሴ ካላስቀደሰ፣ ቃለ እግዚአብሔር ካልሰማ፣ ገድላቱን፣ ተአምራቱን ካላዳመጠ፣ እንዴት የጸና ግንብ ነው ማለትስ ይቻላል? «መንፈሳዊ ቤት ለመሆን ተሠሩ» ተብሎ ግንቡ ከፈረሰ ምኑን ጠባቂ ሆንን?   (፩ጴጥ. ፪፥፭) ፪. በፈረሰው በኩል ለመቆም በቤተ ክርስቲያን አንድነት እናምናለን? የወንድሞቹን ሥቃይ የየትኛውም ሀገር ሰው ይሁን እንደ ሰው ማሰብ ጤነኛ እሳቤ ነው። ከቢሮ ሥራችን፣ ከፖለቲካ ድርጅታችን በላይ በነፃ አእምሮ ከማንም ተጽዕኖ ውጭ የተጎዳው ወንድምህን ለመታደግ እተጋለን? ይህን የምናደርገው ለእግዚአብሔር ደስታ እንጂ ጀግና እንድንባል፣ የሆነ አካልን ለማስደሰት አይሁን። ብዙ ጊዜ ሰዎች ስለመደሰታቸው እንጂ እግዚአብሔር በእኛ ስለመደሰቱ ማሰብ ይሳነናል። የእግዚአብሔር ደስታ የበደለ ሲክስ፣ ያጠፋ ሲመለስ፣ በንስሓ ሲታደስ ነው። «ንስሓ በሚገባ በአንድ ኀጢአተኛ በሰማይ ደስታ ይሆናል» እንደተባለ በፈጠራ ታሪኮች ተወስደን ከአጥፊዎች ጋር እንዳንተባበር። (ሉቃ. ፲፰፥፲፭) ቤተ ክርስቲያን አንዱ ባሕርይዋ «አንዲት» የሚል ነው። በቅዱሳን ሐዋርያት፣ በሐዋርያነ አበው የተሰበከች ያለ ምንም ደም መፍሰስ ባኮስ ኢትዮጵያዊ የሰበካት ቅዱስ ፍሬምናጦስ ያስተዋወቃት፣ ተስዐቱ ቅዱሳን ያስፋፉዋት ነች። ሀገርን ከእነሙሉ ክብሩ በአንድነት የጠበቀች ናትና ይቺን አንድነት መጠበቅ አለመጠበቃችንን መፈተሽ አለብን። ፫. በፈረሰው በኩል ለመቆም ፈተና የማይለውጠን ነን? ሰንባላጥ እና ሞዓባዊው ጦቢያ ነህምያን እንደፈተኑት በብዙ ሰዎች እንፈተናለን። ሴራ ይሸርቡብናል፤ የሥነ ልቦና ጦርነት ውስጥ እንወድቃለህ። እንደ ነህምያ ስማችንን ያጠፉትም ይሆናል። ያለንን ነገር ልናጣ እንችላለን። በዚህ ጊዜ ከነቢዩ ዕንባቆም ጋር እንዲህ እንበል «ምንም እንኳ በለስ ባታፈራ፥ በወይንም ሐረግ ፍሬ ባይገኝ፥ የወይራ ሥራ  ቢጎድል፥ እርሾችም መብልን ባይሰጡ፥ በጎች ከበረት ቢጠፉ፥ ላሞች በጋጥ ባይገኙ እኔ ግን በእግዚአብሔር ደስ ይለኛል፤ በመድኃኒቴ አምላክ ሐሴት አደርጋለሁ»  (ዕን.፫፥፲፯) ስንቶቻችን ነን ፈተና የቀየረን? በሚታየው እና በሚሰማው ነገር የተቀየርን? ሞራ ያስገለጥን፣ ስኒ ያስገለበጥን? በፈረሰበት በኩል መቆም አቅቶን ራሳችን የፈረስን ብዙ ነን። ከቤተ ክርስቲያን ይልቅ ዘራችን፣ ከመቅደሱ ይልቅ ስማችን ከበለጠብን እውነትም ፈተና ከለወጣቸው ሰዎች ተራ ቆመናል። ነህምያ የፋርስ ነገሥታትን ልብ ያንበረከከው በእምነቱ ጥንካሬ ነው። እኛስ?  ፬. በፈረሰበት ለመቆም ለሀገር እና ለቤተ ክርስቲያን እንጸልያለን? የነህምያ ተግባር የተጀመረው በጾም እና በጸሎት ነው። እንዲህ ነበር ያለው «የኢየሩሳሌም ቅጥር ፈርሶአል በሮችዋም ተቃጥለዋል አሉኝ። ይህን በሰማሁ ጊዜ ተቀምጬ አለቀስሁ አያሌ ቀንም አዝን ነበረ በሰማይም አምላክ ፊት እጾም እና እጸልይ ነበር» (ነህ.፩፥፫-፬) ስለዚህ ስለ ሀገር አለመጸለይ፣ ስለራስ አለመጸለይ ነው። ወልዶ መሳም፣ ዘርቶ መቃም የሚቻለው ቤተ ክርስቲያን ፣ ሀገር ስትኖር ነው። ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ «አቤቱ ማረን አንተን ተማምነናል ጠዋት፥ ጠዋት ክንድ በመከራ ጊዜም ማዳን ሁነን» ብሎ እንደጸለየ እያሉ ዳዋ ጥሰው፣ ድንጋይ ተንተርሰው፣ ድምፀ አራዊቱን፣ ግርማ ሌሊቱን ታግሰው፣ በበዓት ተወስነው የላመ፥ የጣመ ሳይበሉ ስለ ሀገር የሚጸልዩ አበው ያሉባት ሀገር ናትና በማኅበራዊ ሚዲያው በአጸያፊ ቃላት ከመታኮስ ሰብሰብ ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል።   ምን እናድርግ? ፩. ግንቧ የፈረሰባት የተባለች ቤተ ክርስቲያን ናትና ሳንታክት የፈረሰውን እንጠግን የምእመናን ኅብረት እንዳይፈርስ፣ ጉባኤያት እንዳይበተኑ፣ አብነት ተማሪው ነገን እንዲረከብ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በፈረሰው በኩል ቁሙልኝ ትላለች። ሕፃናት ሃይማኖታቸውን እንዲያውቁ አዕማድ የተባሉ ምሥጢረ ሥላሴ፣ ምሥጢረ ሥጋዌ፣ ምሥጢረ ጥምቀት፣ ምሥጢረ ቍርባን፣ ምሥጢረ ትንሣኤ ሙታንን እንዲማሩ የወላጅነት ድርሻህን ተወጣ። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ «ስለዚህ አንታክትም ነገር ግን የውጭው ሰውነታችን ቢጠፋ እንኳ የውስጡ ሰውነታችን ይታደሳል» እንዳለ (፪ቆሮ. ፬፥፲፮)  ብዙዎቻችን ለአውሮፓዊ አእምሮ ስለተማረክን፣ ለሚታየው እና ለጠፊው ዓለም ስለተገዛን፣ ከቤታችን ይልቅ በጠርሙስ ብርጭቆ ውስጥ፣ በአልባሌ ተራ ቦታ መደበቅ ስለምንሻ ፈርሰናል። የፈረሰው ውስጣችን የሚታደሰው በቅዳሴው፣ በኪዳኑ፣ በማኅሌቱ ነው። ክርስትና መሓሪውን አምላክ የምናመልክበት ሃይማኖት ነው። ፈርሰናል ስንል በንስሓ የምንመለስበት፣ ከተኛንበት አዚም የምንቀሰቀስበት መንገድ ሰፊ ነው። «አንተ የምትተኛ ንቃ ከሙታንም ተነሣ ክርስቶስም ያበራልሀል» እንዲል መጽሐፍ። (ኤፌ. ፭፥፲፬)    ፪. ግንብ የተባለች ቤተ ክርስቲያን በእጁ ተቀርጻለችና እንሳለማት ቤተ ክርስቲያን የተመሠረተችው በጌታችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ይህቺውም በመልዕልተ መስቀል ላይ በደም ዓላባ በተመቱ፣ በችንካር በተቸነከሩ በእጆቹ ትርትራት መሃል የተቀረጸች፣ የተሳለች ናት። ምድራውያኑን ከሰማያዊው ዓለም የምታገናኝ ድልድይ ነች። በዐጸደ ነፍስ ያሉት ቅዱሳኑ በዐጸደ ሥጋ ካለን ከእኛ ጋር ኅብረት የሚፈጥሩባት የእግዚአብሔር ንድፍ ዲዛይን ናት። አሁን፣ አሁን የሥርዓት ድንበር እያፈረስን ነው። በቅዱሳት መጻሕፍት የተገለጠውን ደጋግመን ስናደርግ አይስተዋልም። ቅዱሳት ሥዕላትን፣ በሩን፣ ጉበኑን፣ መሬቱን ስንሳለም በእምነት ስለሚደረግልን ነገር ማሰብ ስለሚያቅተን በጥርጥራችን ደጁን ተዳፍረነዋል። «ወደ ማደርያዎቹ እንገባለን፤ እግሮቹ በሚቆሙበት ስፍራ እንሰግዳለን» መባሉን እንረሳዋለን። አንዳንድ ጊዜ መጥፎ አርአያ የሚሆኑ ሰዎችን አርአያ ከማድረግም ይመነጫል። ወደ ቤተክርስቲያን ስንገባ በልባችንም፣ በአካላችንም ጉልበትን በማስነካት መስገድ ያስፈልጋል። ሌላኛው የፈረሰንበት ሐሳብ በሰማያዊት ኢየሩሳሌም በእርሷ አምሳል ውስጥ በጎጥኛ በሀገር ልጅ ተካፍለን መባላታችን ነው የሚያስገርመው። ቢሆንልንማ መንግሥተ ሰማያት የእኛ ዘር ወገን ብቻ እንዲገባልን የምንፈልግ ሳይሆን አይቀርም። ሠዓሊ ቀለማትን ተጠቅሞ በቡርሽ ሥዕልን እንደሚሥል የቅድስት ሥላሴ አርአያ እና አምሳል በነፍሳችን ተሥሎብን እያለ ስለምን ነፍሳችንን በዘረኝነት አሳመምናት? «እኔ ቅጥር ነኝ» እንዳለ የነፍሳችን ቅጥር ጠባቂ ቅድስት ሥላሴ ከሣሉብን ተሥዕሎተ መልክእ አንውጣ። መኃ. ፰፥፲  ፫. ግንብ የተባለች ቤተ ክርስቲያን ጠላትን ማምለጫ ምሽግ ናትና እንጠለልባት ግንብ፣ ምሽግ ፣ መደበቂያ ጠላትን ማጥቂያና መዳኛ ነው። «የጸናች ከተማ አለችን ለቅጥር እና ለምሽግ መድኃኒትን ያኖርባታል» እንደተባለ (ኢሳ. ፳፮፥፩) ። ዲያብሎስን ከእነሠራዊቱ የምትጥል ናት። ሌሊቱን ሙሉ እንደ መላእክት ማኅሌት የሚቆሙ ካህናት ማደሪያ ናት ተጠለልባት። ዕቀብ ሕዝባ ወሠራዊታ ለሀገሪትነ ኢትዮጵያ እያለች የምትጸልይ፣ ብራና ፍቃ፣ ቀለም በጥብጣ የድንቁርናን ጨለማ የገለጠች ከማንም በፊት ፋና ወጊ እናት ናት ተጠለልባት። ሀብተ ወልድና ስመ ክርስትና የሰጠችህ፣ የዳረችህ፣ የሸለመችህ፣ ወንጌል ግታ ያሳደገችህ፣ በሞት ስትያዝ ሰው ሁሉ ሲጸየፍህ ፍትሐት ፈትታ፣ በጸሎት በዕጣን አክብራ፣ አጸያፊ ሽታህን በጉያዋ ታቅፋ የምትቀበልህ ናትና ተጠለልባት። ጠባቂዋ የማይተኛ «እኔ በዙሪያዋ የእሳት ቅጥር እሆንላታለሁ በውስጧም ክብርን እሆናለሁ» ያላት ለምን ትፍረስ? ለምን ትጎዳ? (ት.ዘካ ፪፥፭)  ፬. ግንብ የተባለች ቤተ ክርስቲያን መስፈርቷ ሰማያዊ ነውና አንጠራጠራት ሰማያዊ ኩነቶች መለኪያቸው ሰማያዊ መስፈርቱም ሰማያዊ ነው። ወንጌላዊ ቅዱስ ዮሐንስ «ከእኔም ጋር የሚነጋገረው ከተማይቱንና  በሮቿን ቅጽሮቿንም የሚለካበትን የወርቅ ዘንግ ይዟል። ከተማይቱም አራት ማዕዘን ነበረች፤ ርዝመቷም እንደ ስፋቷ ልክ ነበረ፤ ከተማይቱንም በዘንግ ለካት ዐሥራ ሁለት ሺህ ምዕራፍ ሆነች፤ ርዝመቷና ስፋቷ፣ ከፍታዋም ትክክል ነው። ከዚህም በኋላ ቅጽርዋን ለካ፤ በሰው ክንድ መቶ አርባ አራት ነው፤ ይህውም  በመልአኩ ክንድ አንድ ክንድ ነው» ብሏል። ራእ. ፳፩፥፲፭-፲፰ ይህች ርዝመቷ፣ ስፋቷ፣ ከፍታዋ ትክክል ነበር ያላት ቤተ ክርስቲያን ነች። ያስቀመጠችውን ቀኖና ትክክል መሆኑን ለሚጠይቁህ ንገራቸው። ዶግማዋ፣ ሥርዓቷ፣ ቀኖናዋ ለረጅም ዘመናት የተሻገረ ስለመሆኑ አስተምር ፤ ዝም አትበል። አንተም ጠበሉን፣ ውኃ፥ እምነቱን አፈር ማለት ከጀመርህ የፈረሰ ነገር አለ ማለት ነው። ጠበል መስፈርቱ፥ መለኪያው ሰማያዊ ስለኾነ ሲፈውስ፥ ሲቀድስ ትመለከታለህ፤ ውኃ ይህን ማድረግ አይችልም በራሱ የተለየ የማዳን ኃይል አልተላበሰም። ለምሳሌ አንድ ቁስ  በቤተ ሙከራ ሲለካ የራሱ ውጤት አለው እንበልና ፍቅርን በቤተ ሙከራ መለካት ብንፈለግ መለኪያ መስፈርቱ ከዚህ ስለሚለይ እና በዚህ ስለማይለካ ውጤት አናገኝም። ስለዚህም ከጠበል ይልቅ ሆስፒታል መመላለስ ይቀለናል። ብዙ ጊዜ ለእኛ ቤተ እግዚአብሔር የመጨረሻ አማራጭ ነው። ነገር ግን እግዚአብሔርን የመጀመሪያ አማራጭ ለማድረግ አትጠራጠር። ማጠቃለያ ነህምያ የተባለ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ነህምያ የጸሎት ሰው ነበር። (ነህ. ፩፥፬)   አማናዊ ነህምያ ኢየሱስ ክርስቶስ ጸሎትን ያስተማረ ጸሎታችንን የሚሰማ አምላክ ነው። (ማር. ፩፥፴፭) ነህምያ ከሰንባላጥ እና አሞናዊው ጦብያ ተቃውሞ ገጥሞት ነበር። (ነህ. ፭፥፬)   አማናዊው ነህምያ ኢየሱስ ክርስቶስ ከአይሁድ፣ ከጸሐፍት ፈሪሳውያን ተቃውሞ ደርሶበታል። ማቴ. ፲፪፥፲፬)     ነህምያ መቅደሱን አጽድቶ ለአገልግሎት ምቹ እንዳደረገ (ነህ. ፲፫፥፯-፱) አማናዊው ነህምያ ኢየሱስ ክርስቶስም በመቅደስ ውስጥ የነበሩ ነጋዴዎችን በጅራፍ ገርፎ አስወጥቷል። (ማር. ፲፩፥፲፭-፲፱) ነህምያ ግብዞችን ገሥጿል። (ነህ. ፲፫፥፲፭) አማናዊው ነህምያ ኢየሱስ ክርስቶስ ግብዝ የነበሩ አይሁድን በቃሉ ገሥጿል። ማቴ.፳፫ ፥፲፫) ነህምያ የፈረሰች ኢየሩሳሌምን ገንብቷል፤ አማናዊው ነህምያ ኢየሱስ ክርስቶስ ቋያ በቅሎብን የመዳን በራችን ተዘግቶብን፣ ግንባችን ተደርምሶ የነበርን የሰው ልጆች ከሲኦል ሞት ከባርነት ቀንበር ነፃ አውጥቶናል። እኛም እንደ ነህምያ በፈረሰው በኩል ቆመን የሚጠበቅብንን መልካም ሥራ ሠርተን በሃይማኖት ጸንተን የመንግሥቱ ወራሾች የስሙ ቀዳሾች እንድንሆን እግዚአብሔር ይርዳን አሜን፡፡   ወስብሐት ለእግዚአብሔር  
Read 1210 times