Friday, 16 October 2020 00:00

ዚኖቢስ ወዚኖቢያ፤ ዚኖቢስና ዚኖቢያ

Written by  ዲ/ን ዐብይ ሙሉቀን

Overview

በአውግስጦስ ዘመነ መንግሥትና በወንድሙ በቀላውዴዎስ ቄሣር ዘመን በሉቅያኖስ ሥልጣን በዚያ ወራት ኤጌዎን በተባለች ሀገር የክርስቲያኖች ስደት ሆነ። አንድ ቆስጠንጢኖስ የተባለ ጸሐፊ ንጉሡን አቤቱ ሆይ ባይስ በተባለ ሀገር አንድ ሰው አለ አባቱም ታላቅ ሰው ነው እናቱም እንዲሁ ሥርዓታቸውም የተለየ ነው። ከየት እንደሆኑ አናውቅም ነገር ግን ክርስቲያኖች እንደሆኑ እንገምታለን አለው። ዳግመኛም አረማውያንን ወደ ክርስትና ይመልሷቸዋል፤ ወፍ ሳይጮኽ በሌሊትም ያስወጧቸዋል በዕለቱም ብዙዎች ወደ እነርሱ ይሄዳሉ ክርስቲያንም ይሆናሉ። አሁንም ከግዛታቸው አስረው ያመጧቸው ዘንድ ጠንካራ ሰዎችን ላክ አሉት። ገዢውም አጳርጎሪስን ጥሩት አለ። ወታደሮቹም ከዚህ ቁሟል አሉት ገዢውም ብርቱ ሰዎችን ላክ የሚያሳያቸውን ይያዙና አስረው ወደእኔ ያምጧቸው እንቢ የሚል ካለ እናቱም ካለቀሰች እርሷንም አስራችሁ አምጧት አለ። ወታደሮችም እንደታዘዙት ዚኖቢስንና ዚኖቢያን አመጡለት። ገዢውም ዚኖቢስን ሥርዓትህ ምንድን ነው? ወገንህስ ከማን ነው? ይህን የምታደርግ አንተ ሀገርህስ የት ነው? ዓለምን ታስታለህ በዚህ ሀገር የሚኖሩትን ሰዎችም ክርስቲያንም ታደርጋቸዋለህና አለው። ዚኖቢስም ሃይማኖቴን ማወቅ ከፈለግህ ክርስቲያን ነኝ። በሁሉም የምታወቅበት ስሜም ዚኖቢስ ነው። ገዢ ነበርሁ። ከዚህም በኋላ ስደት ሆነና ተሰደድን ወዳጆችም አሉኝ፤ በሮም ሀገርም የሚያውቁኝ አሉ፤ ከዚህ እንድሄድም አሰብሁ ከዚህ በኋላም መንፈስ ቅዱስ አደረብኝ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም አመንሁ ለዘለዓለሙ ይድኑ ዘንድም ብዙዎች ተሰበሰቡ ሁሉም ክርስቲያን ይሆኑ ነበር። የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ማዕተብ /ምልክትም/ ይወስዱ ነበር። መንፈቀ ሌሊት በሚሆንበት ጊዜም ሂዱ እላቸዋለሁ ይሄዳሉ። ዳግመኛም በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የምታምኑ ምእመናን ሆይ የተቀደሰ ሰማያዊ አክሊልንና መንግሥቱን ለማግኘት ስለ እርሱ እንጋደልና እንሞት ዘንድ ሁላችሁም ኑ በማለት እጠራቸዋለሁ። ለዚህ ከባድ ተጋድሎም ይሰበሰባሉ አለው።  ወገኔንና አባቴን ማን እንደሆነ ለማወቅ ከፈለግህ የአባቴ ስም ሜኖፊሎስ የእናቴ ስምም ዚኖቢያ ይባላል የወንድሜ ስምም ኔዎን ይባላል እርሱም አናጉንስጢስነት ተሹሟል፤ ክርስቶስንም አመስግኗል፤ እርሱም ከእኛ ጋር አለ የወደድከውንም አድርግ አንተ በአጋንንት ዘንድም ትመራመራለህ  አለው። ገዢውም ሽማግሌ ነህና አፍርሃለሁ፤ እናትህ ታላቅና ባልቴት ናትና አፍራለሁ አለው። መንፈስ ቅዱስ ያደረባቸው ዚኖቢስና ዚኖቢያም እኛስ ስላንተ እናዝናለን ለዘለዓለሙ ትጠፋለህና አሉት። ገዢውም ፈጽሞ ተቆጣ፤ ልብሷን አውልቁና በራስ ፀጉሯ ስቀሏት፤ ይህንም ልብሱን አውልቁና ራቁቱን ስቀሉት፤ ዛሬም አያፍሩም እሺም አይሉምና አለ። በብትር ይመቷቸው ዘንድም አዘዘ። ሲመቷቸውም ምንም አልተናገሩም ዚኖቢስና ዚኖቢያም እንዲህ እያሉ ጸለዩ ለሁሉም ክብርን የምታጎናጽፋቸው አቤቱ የሰማይና የምድር አምላክ ሆይ እኔንም አልብሰኝ አለች ያን ጊዜም ዚኖቢያ ሰፊ የሆነ ወርቀ ዘቦ ልብስን ተጎናጽፋለች ራሷም እንደንግሥት ተሸለመች የዚኖቢስ ልብስም ነጭ ነበር ገዢውም እንደ አገልጋይ ወንበር ተሸክሞ በዚኖቢስ ኋላ ይከተል ነበር ሕዝቡን በተመለከተ ጊዜም ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ አምላካችን እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ አበራልን፤ የእርሱን ስምም ወደማወቅ አመጣን እያለ ጮኸ። ከዚህም በኋላ ገዢው ወደ ዙፋኑ በተመለሰ ጊዜ ፈጽሞ ተቈጣ። እነዚህን ምን ታደርጋቸዋለህ የክርስቲያኖች አምላካቸው ብርቱ ነውና። ዚኖቢስና ዚኖብያም በአማልክትህ ምክንያት እንዴት ትስታለህ ዓለምንና የሚክዱትን ሁሉ ማጥፋት የሚቻለው እግዚአብሔርን ክደኸዋል አሉት። ከዚህ በኋላም ገዢው ፈጽሞ ተቈጣ ለየራሳቸው ትሰቅሏቸው ዘንድ ሁለት መስቀሎችን አዘጋጁ። አንዱ አንዱን እንዲያየውም እስከ ሁለት ሰዓት ተያዩ፤ እንደሚተያዩ አድርገውም  ሰቀሏቸው፤ ከሰማይም ደመና መጣና ጋረዳቸው ምግብም ሰጣቸው። በነጋተውም ገዢው መጣ ተቀምጠው የእግዚብሔርን ቃል እያስተማሩም አገኛቸው። የሚሰሟቸውና አምነው የሚድኑትም ብዙዎች ነበሩ። ያላመኑትም ለዘለዓለሙ ጠፉ፤ እነዚህን ምን ላድርግላቸው እነሆ ታላላቅ ተአምራትን ያደርጋሉና አለ። ዚኖቢስም አጋንንት እንዴት እንደሚያስቱህ አስተውል አለው። ገዢውም እንዴት እንደሚያሳስቱኝ ንገሩኝ አላቸው። ዚኖቢስና ዚኖቢያም ኃያልና ጽኑ የምትሆን እግዚአብሔር አምላክ ሆይ የአምላክነትህን ጸጋ በሰዎች የምታሳድር፤ ውኃውን ለውጠህ ወይን የምታደርገው አንተ ነህ። ሰውንም ወደ ሃይማኖት ትመልሳለህ። አምላካችን እግዚአብሔር ሆይ ርኩስና ክፉ መንፈስን አስወግደው። ለሰው ልጆችም አንተ ብቻ እንደሆህ ከአንተ ብቻ በስተቀርም ሌላ አምላክ እንደሌለ ግለጥ አሉ። ዚኖቢስና ዚኖቢያ ከጸለዩ በኋላም ይህ መንፈስ ርኩስ እንደ ሰው ሆነ፤ ፊቱም ሁለት ነበር። በአፉ ውስጥ እሳት ይወጣ ነበር፤ ከዚህ በኋላ ይህ ርኩስ መንፈስ ተወገደ፤ ገዢውንም ለቀቀው፤ ገዢውም ጮኸ። አጋንንት እንደሚያስቱኝ አውቃለሁ አለ። አሕዛብም በአንድነት የክርስቲያኖች አምላክ ታላቅ እንደሆነ እናምናለን፤ የሚያምኑበትም ሁሉ እንደሚድኑበት እናምናለን እያሉ በአንድ ድምፅ ጮኹ። ገዢው ተቆጣ። ከዚህ በኋላም ሁለት የብረት ወንበሮችንና ሁለት የብረት ጦሮችን አምጡ፤ አስራችሁም ከእሳት ጨምሯቸው ስትመቷቸውም ለአማልክት ሠዉ በሏቸው የአደሮ ማርና ዘይቱ ሲፈላም በእነርሱ ላይ ጨምሩት አላቸው። ዚኖቢስና ዚኖቢያም እግዚአብሔር ኃያል ብርቱም ነው። አሁንም ቅዱስ ሆይ ጠብቀን ይቅርም በለን፤ በቅዱስ መንፈስህም ሥቃይን ሁሉ ከእኛ አስወግድ አሉ። ዚኖቢስና ዚኖቢያ ከጸለዩ በኋላም ይህ የብረት ጦር እንደ ደረቅ የእንጨት በትር ሆነ። የእግዚአብሔር ቅዱሳንም በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም ፊታቸውን አማተቡ፤ ተነሡና ተቀመጡ፤ ጳውሎስ እንዳስተማረውም የእግዚአብሔርን ቃል ያስተምሩ ጀመር። አሕዛብም ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የተመሰገነ ነው ዛሬም በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ ዚኖቢስንና ዚኖቢያን ከዚህ ሁሉ ሥቃይ ያነሣ የእግዚአብሔር ልጅ ጌታን እናመስግነው አሉ። ዚኖቢስም ቆሞ ያመናችሁ ሁላችሁ ኑ፤ ከእኔ ጋርም ለእግዚአብሔር እንጋደል በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም በማመንም ሰማያዊውን አክሊል እናገኝ ዘንድ እንጋደል እያለ ይጣራ ነበር። የሰሙና በቅዱሳኑ ላይ እግዚአብሔር ያደረገውን ተአምር የተመለከቱ ሁሉም እየሮጡ ይመጡ ነበር። በአብ በልድና በመንፈስ ቅዱስም ያመኑ ነበሩ ዳኑም። ገዢውም ከመመለስ ይልቅ በክፋቱ እየጸና ሄደ። ዐሥር ክንድ ያህል ከፍታ ያለው እሳት አስነድዶም በዚያ እንዲጣሉ አደረገ። ዚኖቢስና ዚኖቢያም ዘመናትን ዓመታትን የምታፈራርቅ አንተ ነህ። ለሰው ልጆች ተአምርህን ግለጥ፤ ይህን እሳት ነበልባሉንም አቀዝቅዘው ገዢውንም መልሰው በማለት ወደ እግዚአብሔር ጸለዩ። ዚኖቢስና ዚኖቢያም ከጸለዩ በኋላ እንደ ትንሽ መታጠቢያ ቤት ሆነ፤ ገዢውም የመታጠቢያ ቤት ጠባቂ ሆነ። ውኃን የመላ ማሰሮ ይዞ ነበር። ዚኖቢስና ዚኖቢያም እግአብሔርን ፈጽመው ያመሰግኑት ጀመር። በቅዱሳን አድሮ ተአምራትን የሚያደርግ እግዚአብሔር ቡሩክ ነው አሉ። ገዢውም ወደቤቱ ሄደ፤ በዚያም ፊቱ ሁለት የሆነ ሰው አገኘ። ይህም ክፉ ርኩስ መንፈስ ነው። ገዢውም በአንተ ምክንያት እንሳሳታለን እንጠፋለንም አለው። ጠራውና ተፋበት። ከዚህም በኋላ ገዢው ዳግመኛ ከዙፋኑ ተቀመጠ። እነዚህን ጎስቋሎች ጥሯቸውና አስቀምጧቸው አለ። ወታደሮቹም አቤቱ እነሆ በፍርድ አደባባይህ ፊት አሉ አሉት። ከዚህ በኋላ ሁሉም ሰዎች የእግዚአብሔር ኃይሉ ታላቅ ነው እያሉ ጮሁ። ገዢውም ለታላቁ አምላክ ለባኪና ለዲዮንስዮስ ቅረቡና ሠዉ አለ። ዚኖቢስም እነዚህ አማልክት ምንም እንዳልሆኑ እንደሚሰጠሙም አታውቅምን አለው። ዚኖቢስና ዚኖቢያም ጸለዩ ሁለት የምስል አማልክትም ተሰጠሙ የነበሩበት ቦታም ምድረ በዳ እንደሆነ የአትክልት ቦታ ሆነ። ዚኖቢስና ዚኖቢያም አሰምተው ተናገሩ ገዢውንም አማልክቶችህ የት አሉ አሉት እነሆም እርሱ ብቻ አምላክ የሆነ እግዚአብሔርን ክደኸው እነርሱም እነሆ ጠፉ ምን ትላለህ ከእንግዲህ ወዲህ በምን አምላክ ታመልካለህ አሉት። ሕዝቡም አሰምተው ተናገሩ፤ እነሆ ዛሬ የክርስቲያኖች አምላክ እውነተኛ አምላክ እንደሆነ ተረድተናል አሉ። ገዢውም ተናደደ፤ ውሰዷቸውና ግደሏቸው አርቃችሁም ጣሏቸው። ነገ በእሳት አቃጥላቸው ዘንድም በድናቸውን ጠብቁ አላቸው። ይዘውም ገደሏቸው፤ በሚገድሏቸው ጊዜም ነጎድጓድና መብረቅ ብልጭታም ሆነ። በመደንገጥም አምስት መቶ ሰዎች ሴቶችም ወንዶችም ሞቱ። ሲመሽም ከምእመናን ወገን በሌሊት መጡ በድናቸውንም  ወሰዱ ሁለት መቃብርም ቆፍረው በሰቀሉባቸው ቦታ ሁለቱንም ጎን ለጎን ቀበሯቸው። በማግስቱም ገዢው በአደባባዩ ተቀመጠ። በእሳት እናቃጥል ዘንድ የእነዚያን ሰዎች በድን አምጡ አላቸው ወታደሮችም አቤቱ ምሽት በሆነ ጊዜ ነጎድጓድ ብልጭልጭታ፣ መብረቅና ብዙ ጎርፍም ሆነ። ዳግመኛም በመንፈቀ ሌሊትም እንደ መብረቅ ያለ ተመለከትን በቤታችንም ድምፁን ሰማን አሉት። ገዢውም ይህን ተአምር በሰማ ጊዜ እኔም ክርስቲያን መሆን እሻለሁ አለ ይህ ገዢና ወታደሮቹም ሁሉ አመኑ።  ተጋድሏቸውም በኤጌዎን ሀገር ሉቅያኖስም የአሕዛብ አለቃ ሳለ፤ አውግስጦስ በተባለው በቀላውዴዎስ ዘመን ነው። የቅዱሳኑ በረከት ከሁላችን ጋር ይሁን አሜን። (ምንጭ ገድለ ሰማዕታት ቅጽ ፩)  
Read 542 times