Friday, 16 October 2020 00:00

ጸጸት

Written by  እንዳለ ደምስስ

Overview

ቀኑ ለምሽት ተራውን እየለቀቀ ነው፡፡ ፀሐይ ከወደ መጥለቂያዋ የእሳት አሎሎ መስላ በሰከንዶች ልዩነት ከአድማስ ማዶ ቁልቁል ለመሸሸግ ትጣደፋለች፡፡ አክሊሉ አራት ኪሎ ከሚገኘው መሥሪያ ቤቱ ወጥቶ በቀጥታ ያመራው ሲኤምሲ ቅዱስ ሚካኤል ጀርባ ካለው መኖሪያ ቤቱ ነው፡፡  ጠዋት ከቤት ከመውጣቱ በፊት ልጁ ናሆም የጠየቀው ጥያቄ ጤናማ ጥያቄ ነው ብሎ ማመን ቸግሮት ዕረፍት ሲነሣው ውሏል፡፡ በቂ መልስ ሊሰጠው አለመቻሉም አስጨንቆታል፡፡ የጠዋቱ ሁኔታቸው እየተመላለሰ ይረብሸዋል፡፡ ጠዋት የ፲፪ እና የ፰ ዓመት ልጆቹ ቀድመውት ከእንቅልፋቸው ተነሥተው ወደ ትምህርት ቤት ለመሔድ እየተዘጋጁ ነው፡፡ አክሊሉ ሌሊቱን ጥሩ እንቅልፍ ባለመተኛቱ ድካም ቢሰማውም እየተነጫነጨም ቢሆን ተነሣ፡፡ ቁርስ የመብላት ልምድ ስለሌለው ባለቤቱ እስክታቀርብለት አልጠበቀም፡፡ ወደ ትምህርት ቤት ለመሔድ የሚጣደፉት ልጆቹን ስሞ ወደ በሩ እያመራ ሳለ የመጀመሪያ ልጁ ናሆም ያልጠበቀውን ጥያቄ ጠየቀው፡፡   “አባዬ እኛ ለምንድነው ቤተ ክርስቲያን ሔደን የምንሰግደው?” ሲል ጠየቀው፡፡ ያልጠበቀው ጥያቄ ነበር፡፡ ናሆም ገና የ፲፪ ዓመት ልጅ ነው፡፡ ሁል ጊዜ መጠየቅ ይወዳል፣ ትምህርት ቤት ውስጥ ከጓደኞቹ ጋር ሲጫወት የሚያነሷቸውን ጥያቄዎች ከአእምሮው በላይ ስለሚሆኑበት ወደ ቤት መጥቶ አባቱን ይጠይቃል፡፡ አክሊሉ ከቢሮ ይዞት የመጣውን ሥራ ለማጠናቀቅ በሚል ትኩረቱ ሁሉ ኮምፒዩተሩ ላይ ቢሆንም ለልጁ ጥያቄ በጥቂቱም በተከፈለ ልቡ ለመመለስ ይሞክራል፡፡ በልጁ ጥያቄዎች ብዙ ጊዜ ይገረማል፣ የጓደኞቹም ፈጣን አእምሮ ያስደንቀዋል፣ አንዳንዴም ያበሳጨዋል፡፡ የዛሬው የጥያቄው ጤናማነት ግን አጠራጠረው፡፡  “ማነው ይህን የጠየቀህ?” አለው ምላሹን ከመስጠት ተቆጥቦ፡፡ ሙሴ ነዋ፡፡ አጠገቤ የሚቀመጠው ጓደኛዬ:: ብታይ ምሳ ስንበላ ዓይኑን ጨፍኖ ነው የሚጸልየው፣ እመቤታችንን ደግሞ አይወዳትም፣ ብዙ ጊዜ ይሳደባል፡፡ እኔም ዝም አልለውም ለምን ይሰድባታል ብዬ እንደባደባለን፡፡ ባለፈው እንኳን የአማርኛ አስተማሪያችን ቲቸር በላቸው ገረፈኝ ብዬ አልነገርኩህም?” “አዎ፡፡ ለምን እንደገረፈህ እኮ አልነገርከኝም?” አለ ምክንያቱን ሳይጠይቀው ማለፉን አስታውሶ፡፡ በሥራ እየተጠመደ ልጆቹ የሚገጥማቸውን ችግር ለመፍታትም ሆነ ምን ዓይነት ተማሪዎች እንደሆኑ ለመጠየቅ ከመምህራኖቻቸው ጋር ለመመካከር ጊዜ ሰጥቶ አያውቅም፡፡ ከትምህርት ቤት መልእክት ሲመጣ፣ ስብሰባ ወይም ውጤት ለመቀበል እንኳን ሔዶ አያውቅም፡፡ የልጆቹን ጉዳይ አሳልፎ ለባለቤቱ ሐና ሰጥቷታል፡፡ ልጆቹን መከታተል አለመቻሉ አሳፈረው “ወይኔ ልጆቼ! ወልጄ ብቻ ተውኳችሁ ማለት ነው?” በማለት ሁለቱን ልጆቹን እያፈራረቀ በጥፋተኝነት ስሜት ውስጥ ሆኖ ተመለከታቸው፡፡    “ሌባና ፖሊስ ስንጫወት ሳሸንፈው ጊዜ እመቤታችንን ተሳድቦ ሲሮጥ ድንጋይ ወርውሬ ጭንቅላቱን መታሁትና አለቀሰ፡፡ የአማርኛ አስተማሪያችን ደግሞ ገረፈኝ፡፡ ከዚያ ደግሞ አስታረቀን” አለ ጣፋጭ በሆነ አንደበቱ፡፡ “ታዲያ ይህን ጥያቄ ሙሴ ለምን ጠየቀህ?” አለው በስጋት፡፡ “ሊያናድደኝ ነዋ፡፡ ስላልመለስኩለት ደግሞ ለጓደኞቻችን አስቆብኛል” አለ እየተሸማቀቀ፡፡ “አየህ ልጄ እሱ የሚልህን አትስማው፡፡ እግዚአብሔር በሁሉም ቦታ አለ፡፡ ነገር ግን ቤተ ክርስቲያን እግዚአብሔር ስሙ የሚጠራበት፣ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን የምንቀበልበት፣ ጸሎት የምንጸልይበትና ጸሎታችንም የሚሰማበት ቅዱስ ቦታ ስለሆነ በእግዚአብሔር በቅድስናው ሥፍራ በቤተ ክርስቲያን እንሰግዳለን፡፡ ሁል ጊዜም ቤተ ክርስቲያን ሔደን እንሰግዳለን፣ እንሳለማለን” አለ፡፡ መልሱ ልጁን አርክቶት ይሁን አይሁን ለማረጋገጥ በትኩረት አስተዋለው፡፡ ግራ እንደተጋባ ሲረዳ ከአቅሙ በላይ በሆነ አገላለጽ ምላሹን እንደሰጠው ተረዳ፡፡ አቅልሎ ለመንገር ቃላት መምረጥ ፈለገ፡፡  ከመጽሕፍ ቅዱስ ጥቅስ ጠቅሶ ሊያስረዳው አሰበ፡፡ ነገር ግን ከአቅሙ በላይ በሆነ መንገድ የባሰ እንዳያደናግረው ስለሰጋ እንዴት ላስረዳው በሚል ተጨነቀ፡፡  አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ትዝ አለው፡፡ “ይኸውልህ ልጄ ነቢዩ ሕዝቅኤል የተባለው እግዚአብሔርን የሚያመልክ ሰው ነበር፡፡ እርሱ ምን አለ መሰለህ “በሰሜኑም በር መንገድ በቤቱ ፊት አገባኝ፡፡ እኔም አየሁ፣ እነሆም የእግዚአብሔር ክብር የእግዚአብሔርን ቤት ሞልቶት ነበር፡፡ እኔም በግንባሬ ተደፋሁ” እያለ ይናገራል፡፡ (ሕዝ.፵፬.፬)፡፡ ሌላው ደግሞ ቤተ ክርስቲያን ስንሔድ ራሳችን አዘጋጅተን መሆን አለበት፡፡ ነቢዩ ሙሴ ቁጥቋጦው በእሳት ሲቃጠል ታየው፣ ነገር ግን ወደ ቁጥቋጦው ቀርቦ ሲመለከት ቁጥቋጦው አልተቃጠለም፡፡ የእግዚአብሔርም መልአክ “ሙሴ ሙሴ ወደዚህ አትቅረብ አንተ የቆምህባት ስፍራ የተቀደሰች መሬት ናትና ጫማህን ከእግርህ አውጣ” አለው፡፡ ይህ ለምን ይመስልሃል? የእግዚአብሔርን ቤት ቤተ ክርስቲያን የተቀደሰች ሥፍራ እንደሆነች ሲያስተምረን ነው፡፡ (ዘፀ.፫.፪-፭)፡፡ ስለዚህ ጫማችንን እናወልቃለን፣ እንሰግዳለንም፡፡ አሁንስ ገባህ?” አለ ልጁ በመልሱ ይርካ አይርካ መገመት አቃተው፡፡ ከአእምሮ በላይ ሌሎችን ጥቅሶች እየደረደረ ሊያስጨንቀው አልፈለገም፡፡ ሰዓቱን ሲመለከት ለልጆቹም ሆነ ለእርሱ እንደረፈደ ተረዳ፡፡ “በቃ ማታ በደንብ እንነጋገራለን፡፡ ሁለተኛ ከማንም ጋር እንዳትጣላ” ብሎ ሁለቱንም ልጆቹን ስሞ ቅር እያለው ወጣ፡፡ አክሊሉ ለስሙ መሥሪያ ቤቱ ይሂድ እንጂ ቀኑን ሙሉ ለልጁ እንዴት ማስረዳት እንዳለበት ቃላት እየመረጠ አንዱን እየጣለ ሌላውን እያነሣ በሐሳብ ሲባዝን ውሎ ነው የተመለሰው፡፡  ጎጃም ከቤተሰቦቹ ጋር ሳለ በልጅነቱ ከፊደል አንስቶ እስከ መዝሙረ ዳዊት በአጥቢያቸው ካሉት የኔታ ዘንድ ይማር እንጂ ጠለቅ ብሎ እንደ ሌሎቹ የሠፈሩ ልጆች የአብነት ትምህርት የመማር ዕድል አልገጠመውም፡፡ አዲስ አበባ የሚኖሩት አጎቱ በልጅነቱ ወደ አዲስ አበባ ወስደው ዘመናዊውን ትምህርት አስተማሩት፡፡ ዛሬ በአንድ መንግሥት መሥሪያ ቤት በኃላፊነት በመሥራት ላይ ነው፡፡ ልጆቹን ሰንበት ትምህርት ቤት ውስጥ አለማስገባቱ ጸጸተው፣ ቤትም ውስጥ እርሱ ያወቀውንና የተማረውን ትምህርት ለልጆቹ የሚገባቸውን ዕውቀት ባለማስጨበጡ ራሱን እንደ ባለ ዕዳ ቆጠረ፡፡  ገና ወደ ቤት ከመግባቱ በጉጉት ሲጠብቀው የዋለው ልጁ ዘሎ አንገቱ ላይ ተጠመጠመ፡፡ “አባዬ እ- እ- ጠ- ጠ- ዋት የ- የነገረከኝን ሁሉ ለሁሉም ጓደኞቼ ነገርኳቸው፡፡ ሙሴ መልስ መመለስ አቃተው፣ እንዳበሸቀኝ አናደድኩትና ጓደኞቼ ሳቁበት” አለ ናሆም በድል አድራጊነት ፈንድቆ፡፡ “ጎበዝ የኔ ልጅ፡፡ መጣሁ ልብሴን ልቀይር” ብሎ ወደ መኝታ ቤት ገባ፡፡ ናሆም ለረጅም ጊዜ ለአእምሮው ጥያቄ የፈጠረበትና መልስ ያጣለት ተጨማሪ ጥያቄ ለአባቱ ለመጠየቅ ተዘጋጀ፡፡ ማታ ለጠየቀው ጥያቄ በሰጠው መልስ ጓደኛውን ድል ስላደረገ ተጨማሪ ማብራሪያ አልፈለገም፡፡ ለዛሬው ጥያቄ ደግሞ ተዘጋጀ፡፡ አክሊሉ ከመሥሪያ ቤት ሆኖ ሲሠራ ውሎ አላልቅ ያለውን የጽሑፍ ሥራ እቤቱ ሆኖ ለመጨረስ ፍላጎት ቢኖረውም ከዚያ በፊት ልጁን ማረጋጋት እንዳለበት ስለተረዳ ልብሱን ቀይሮ ለጥቂት ደቂቃዎች ከልጆቹ ጋር ማሳለፍ ውስጡን አሳምኗል፡፡ የልጆቹን ኃላፊነት በሚስቱ ሐና ላይ ጥሎ ስለነበር ኃላፊነቷን በአግባቡ ባለመወጣቷ አጉረመረመ፡፡ ናሆም ዛሬ ደግሞ ሲከነክነው የዋለውን ጥያቄ ለአባቱ ይዞ መጥቷል፡፡ ሳሎን እንደተቀመጡ ጥያቄውን ለማንሣት ፈለገ፡፡ “አሁን ጠዋት ለጠየቅኸኝ ጥያቄ መልሱን ላብራራልህ” አለ አክሊሉ ሁለቱን ልጆቹን ግራና ቀኝ አስቀምጦ፡፡  “ገብቶኛል አልፈልግም፡፡ ሌላ ጥያቄ ደግሞ አለኝ” አለ ናሆም አባቱ ይመልስለት ዘንድ ዓይኖቹን እያቁለጨለጨ፡፡ “ደግሞ ምንድነው ጥያቄህ?” ስጋት ገባው፡፡ “እ- እነ ሙሴ ለምንድነው ዓይኖቻቸውን ጨፍነው የሚጸልዩት? ብታይ እ- እሱ ዓይኖቹን ጨፍኖ ሲጸልይ ጓደኞቼ ምሳውን ይሰርቁበታል፣ ከዚያ ይደባደባሉ፡፡ ጋሼ በኃይሉ ደግሞ እየሮጡ መጥተው ሁላችንንም ይገርፉናል” አለ በችኮላ፡፡ “አንተ ግን በእንደዚህ ዓይነት መጥፎ ድርጊት ውስጥ መሣተፍ የለብህም፡፡ ጥል፣ ተንኮል መሥራት፣ መሳደብ ኃጢአት ነው፣ እግዚአብሔርን ማሳዘን ነው ብዬ ከዚህ በፊት ነግሬህ የለም?” “አዎ፡፡ ግን እኔ የምጣላው በቤተ ክርስቲያን ነገር ሲሳደቡ ብቻ ነው፡፡ አሁን የጠየቅሁህን ጥያቄ አትመልስልኝም?” አለ አንገቱን ሰበር አድርጎ መሬት መሬት እያየ፡፡ “እመልስልሃለሁ፡፡ ዓይንን ጨፍኖ መጸለይ ትክክል አይደለም፡፡ እግዚአብሔር የጨለማ አምላክ አይደለም፣ የብርሃን እንጂ፡፡ ጨለማ የሰይጣን ምሳሌ ነው” አለ እንዴት ማስረዳት እንዳለበት እየተቸገረ ሳለ ባለቤቱ ወ/ሮ ሐና ከቢሮ ወደ ቤቷ ተመለሰች፡፡ “እንዴት ዋላችሁ?” ብላ ሦስቱንም ስማ ወደ ውስጥ ገባች፡፡ “እንዴ አባዬ ጨለማንና ብርሃንን፣ ሁሉንም ነገር የፈጠረው እግዚአብሔር ነው ብለህ አልነገርከኝም? እንዴት እግዚአብሔር የብርሃን አምላክ ብቻ ይሆናል?” ናሆም ሌላ ጥያቄ አባቱ ላይ ጫነ፡፡ አክሊሉ በልጁ ፈጣን ጥያቄዎች ተደናገጠ፡፡ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንደማደጉ ዘመናዊውን ትምህርት ብቻ ሲያሳድድ ለመንፈሳዊው ዕውቀት ባዕድ እየሆነ መምጣቱን እነዚህን ቀላል የሚመስሉ ጥያቄዎችን መመለስ ባለመቻሉ በራሱ አዘነ፡፡ መልሶ ደግሞ የሚያውቀውንም ለማስረዳት ለልጁ ከአቅሙ በላይ እንደሚሆንበት ተረዳ፡፡  “አየሽው ልጅሽ የሚጠይቀው ጥያቄ? በደንብ ብትከታተይው ኖሮ እንዲህ ጠያቂ ብቻ አይሆንም ነበር” አለ አክሊሉ ሐና ከመኝታ ቤት ወደ ሳሎን ስትወጣ ደካማ ጎኑን በሚስቱ ለማሳበብ እየሞከረ፡፡  “ምነው ገና ከመግባቴ ነገር ይዘህ ቆየኸኝ፡፡ ልጆቹ እንደሆነ የእኔም የአንተም ናቸው፡፡ ያለን ኃላፊነት እኩል ነው፡፡ ከቢሮ እያመሸህ ትመጣለህ፣ ቤት መጥተህ ለቤተሰብህ ጊዜ መስጠት ሲገባህ ሥራ ይዘህ ከኮምፒዩተርህ ጋር ትፋጠጣለህ፡፡ እኔ ብቻዬን ምን አድርጊ ነው የምትለኝ?” ሐና ፊት ለፊቱ መጥታ እጆቿን ወገቧ ላይ አድርጋ በንዴት ቁልቁል እየተመለከተችው፡፡ “የልጆቹን ኃላፊነት የወሰድሽው አንቺ ነሽ፡፡ ምን በሉ፣ ምን ለበሱ ብቻ ሳይሆን ውሎአቸውንም መከታተል አለብሽ፡፡ እኔ ጊዜ እንደሌለኝ ታውቂያለሽ” አለ ሚስቱን እንዳስቆጣት ሲረዳ ንግገሩን በማለዘብ፡፡ “እኔም እኮ መሥሪያ ቤት ስለፋ ውዬ ነው የምመጣው፡፡ ቤት መጥቼ ደግሞ የቤት ውስጥ ሥራው ይጠብቀኛል፡፡ አንተ እንደሆንክ የወደቀ ዕቃ እንኳን ቀና አታደርግም፡፡ ውለህ፣ አምሽተህ፣ እንደገና ኮምፒዪተር ላይ ታፈጣለህ፡፡ ጊዜ ወስደህ የቤት ሥራቸውን እንኳን ለመከታተል አትሞክርም፣ እኔ ስንት ቦታ ልድረስ?” ሶፋው ላይ ተቀምጣ ቁጭ ብላ  አለቀሰች፡፡ አባትና ልጆች ተደናገጡ፡፡ ልጆቹ ሮጠው እናታቸው ላይ ተጠመጠሙ፡፡ የእናቷን ማልቀስ የተረዳችው ኤፍራታ እናቷን እንዳቀፈች አለቀሰች፡፡ አክሊሉ የሚይዘውን፣ የሚጨብጠውን አጣ፡፡ የፈጠረውን ችግር መልሶ ለመጠገን ተቸገረ፡፡ ለቅሷቸውን እስኪያቆሙ ጠብቆ “ይቅርታ እናቴ ሳላስበው አስቀየምኩሽ” ብሎ ሐናን አቅፎ ለማባበል ሞከረ፡፡ “ለምን ታሰቃየኛለህ? ሁሉን ችዬ ዝም ስላልኩህ ነው? ለምን አታግዘኝም? የቢሮ ሥራህን ቢሮ ውስጥ ጨርሰህ ሠርተህ ወደ ቤትህ መምጣት፣ ባትጨርስ እንኳን በማግስቱ ትደርስበታለህ፣ ቤት ውስጥ ደግሞ ለቤተሰብህ ጊዜ ስጥ፡፡ ሁሉን ነገር እኔ ላይ ጥለህ እንዴት እችላለሁ? አላሳዝንህም? ለልጆችህስ አታዝንምን?” አክሊሉ የልጁ ብቻ ሳይሆን የባለቤቱ ያልተመለሱ ጥያቄዎችን መመለስ ተሳነው፡፡ ምን ያህል ቤቱን እንደበደለ ሲያስበው ለፀፀት እጁን ሰጠ፡፡ ይህን ያህል ችግር ያመጣል ብሎ ያላሰበው ጉዳይ ቤተሰቡን መጉዳት መቻሉ አሳፈረው፤ ቀና ብሎ ባለቤቱንና ልጆቹን ለማየት አቅም አጣ፡፡ ሳሎኑ በዝምታ ድባብ ተዋጠ፡፡ ሁሉም ዝም . . . ፡፡  የቤቱ ራስ የሆነው አክሊሉ የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት ግዴታ መሥዋዕትነት መክፈል እንዳለበት ተረዳ፡፡ ጭቅጭቁ በዚሁ ከቀጠለ አቅጣጫው እንደሚቀየር ገብቶታል፡፡ “ይቅርታ የኔ ውድ! እውነትም በድያለሁ፡፡ ነገር ግን ይህን ያህል እስክትጎጂ ለምን ጠበቅሽ? እስከ ዛሬ ለምን አልነገርሽኝም?” አለ ባለቤቱን ቀና ብሎ ለማየት እየተሸማቀቀ፡፡   ልጆቹ በየተራ አንድ ጊዜ አባታቸውን፣ መልሰው ደግሞ እናታቸውን እያዩ ዓይኖቻቸውን ያቁለጨልጫሉ፡፡ ላስተዋላቸው ፊታቸው ላይ ፍርሃት ይነበባል፡፡  “እንዴት አይገባህም? እኔ ስንት ቦታ ልበጣጠስ?” አለች በቁጣ እያፈጠጠችበት፡፡ “ይቅርታ አልኩሽ እኮ፡፡ አሁንም ቢሆን አልረፈደምና የተፈጠረውን ችግር በጋራ እንፍታው፡፡ ተጨቃጭቀን አንዘልቀውም፡፡ ቤታችንን ለማፍረስ የሚታገለንን ዲያብሎስ ማሳፈር አለብን፡፡ እኔ እኮ በኢኮኖሚ እንዳንጎዳ፣ ነገ የተሻለ ኑሮ እንኖራለን በሚል ነው ያለ ዕረፍት የምሠራው፡፡ በቅንነት እንጂ አንቺን ወይም ቤተሰቤን ለመጉዳት አስቤ ያደረግሁት አይደለም፡፡” “ስለ ነገ እያሰብኩ ዛሬን አላበላሽም፡፡ እየኖርን ያለነው ዛሬን ነው፣ ነገ ምን እንደሚፈጠር አናውቅም፡፡ ለምን ራስህንም ቤተሰቦችህንም ትጎዳለህ? ትዳራችን በሚመጣ ገንዘብ ብቻ አይደለም የሚቆመው፡፡ ስንተሳሰብ፣ ስንረዳዳ፣ አንዳችን ለአንዳችን ስንጨነቅ ነው፡፡ በውድቅት ሌሊት ትተኛለህ፣ የጎሕ መቅደድ ተከትለህ ትወጣለህ፣ ለምን? እሑድ እንኳን ቅዳሴ አለቀ አላለቀ እያልክ ስትቁነጠነጥ ትጨርሳለህ፣ በቃ ቤትህ ውስጥ አትታይም፡፡ መንፈሳዊ ሕይወታችን ምን ያህል ባዶ እንደሆነ አስተውለሃል? ከተጋባንበት ጊዜ አንስቶ ምን ያህል ጊዜ እንደቆረብን ታውቃለህ? ስጠይቅህ ነገ ነገ እያልክ ጊዜውን ገደልክ፡፡ የንስሓ አባታችንን መቼ ነው ያገኘናቸው? መቼ ነው ንስሓ የገባነው? መንፈሳዊ ሕይወታችን አያሳስብህም? ያ ሁሉ ጥንካሬህ የት ሔደ?” አክሊሉ ጥፋቶቹን ሲያስባቸው ሊሸከመው የማይችለው ፀፀት ውስጡን በላው፡፡ የልጁን ጥያቄ መመለስ ተስኖት ጭራሽ የባለቤቱን፣ የግማሽ አካሉን ብሶት ቀሰቀሰ፡፡ ምንም መከራከሪያ ነጥብ በአእምሮው ሊመጣ አልቻለም፡፡ ሐና ትክክል እንደሆነች ውስጡን አሳመነ፡፡ ንግግራቸው ወደ ጭቅጭቅ ሳይሆን ወደ ውይይት መውሰድ እንዳለበት ተገነዘበ፡፡ ሳሎኑ አሁንም ዝምታውን ተረከበ፡፡ አክሊሉ በኃፍረት አቀርቅሯል፣ ሐና ገንፍሎ የመጣውን ብሶት ያዘለ ንዴቷን ለማብረድ፣ ለቅሶዋን ለማቆም ትታገላለች፣ ናሆምና ኤፍራታ በዝምታ ወላጆቻቸውን ይመለከታሉ፡፡ ከደቂቃዎች ቆይታ በኋላ “ወደ ኋላ መመለስ አንችልም፡፡ የሆነው ሆኖ አልፏል፡፡ ጥፋቴን አምኛለሁ! ሁሉንም በይቅርታ እንለፈው፡፡ ይቅር ማለት የሚችሉ ልቦች የታደሉ ናቸው፡፡ ይቅር በይኝ ውዴ! ያለፈውን እንርሳ፣ ቤታችንን በይቅር ባይነት ደግመን እንሥራው” ብሎ በባለቤቱና በልጆቹ መካከል በግንባሩ ተደፍቶ “ይቅር በሉኝ!” አለ፡፡ ሐና ደነገጠች፡፡ በአንድ ጊዜ እንዲህ ውስጡ ይሰበራል ብላ አላሰበችም፡፡ ባለቤቷን ትወደዋለች፣ ታከብረዋለች፣ ከትምህርት ቤት ጀምሮ ማንነቱን ታውቃለች፣ ስላመነበት ነገር ይሞታል፡፡ ለእሷ ያለውን ፍቅር ወሰን እንደሌለው ትረዳለች፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ጭልጥ ብሎ ሥራው ላይ ብቻ መጠመዱ እያሳሰባት፣ ፍርሃት እየገባት ሁሉን ተሸክማ ዛሬ ላይ ደርሳለች፡፡  ፊት ለፊቷ ተደፍቶ ይቅርታ ሲጠይቃት ንዴቷ ከላይዋ ላይ እንደ ጢስ ተነነ፡፡ አዘነችለት፡፡ የፍቅር ትኩስ ዕንባ እያነባች ከተደፋበት ብድግ አድርጋ አቀፈችው፡፡ ሁለቱም ተያይዘው ተላቀሱ፣ ልጆቹ ወላጆቻቸውን አቅፈው በዕንባ ተከተሏቸው፡፡ የፍቅር፣ የፀፀት፣ የጭንቀት፣ የደስታ ዕንባ፣ ድምፅ አልባ የዕንባ ዘለላዎች ጎረፉ፡፡ “ይቅርታ አድርገሽልኛል?” አለ አክሊሉ ከእቅፏ ወጥቶ ግንባሯን በፍቅር እየሳመ፡፡ “አዎ፡፡ እኔንም ይቅር በለኝ” አለች ዕንባዋን እየጠረገችና ሶፋው ላይ ቁጭ እያለች፡፡  “አዎ ውዴ! አንቺ ምንም አላጠፋሽም፣ እኔ ነኝ ኃላፊነቴን የዘነጋሁት፡፡ ወደፊት በዚህ ሁኔታ መቀጠል የለብንም፡፡ መተጋገዝ አለብን፡፡ እኔ የልጆቻችንን ኃላፊነት በአግባቡ እወጣለሁ፡፡ ተጨማሪ ኃላፊነቶች ካሉ ልትሰጪኝ ትችያለሽ፡፡ ይህንን ስል አንዳችን የአንዳችንን ጉድለት ከመሙላት ጀምሮ እየተነጋገርን እንረዳዳለን፡፡ አይመስልሽም?” አለ አክሊሉ ባለቤቱን በፍቅር ዓይኖቹ እያስተዋላት፡፡ “ደስ ይለኛል፡፡ የተጠራቀመ ብሶቴን በአንድ ጊዜ አራገፍኩብህ አይደል? ለዚህም ይቅርታ! በዋናነት በቅድሚያ ትኩረት የምናደርገው መንፈሳዊ ሕይወታችን ላይ ቢሆን እመርጣለሁ፡፡ እሑድ ከቅደሴ መልስ የንስሓ አባታችንን እናነጋግራለን፡፡ እርሳቸው በሚሰጡን አቅጣጫ በጸሎት እየበረታን ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ግንኙነት እናጠናክራለን፡፡ ጎን ለጎን የልጆቻችንም፣ የቤታችንም ኃላፊነት በጋራ እንወጣለን፡፡ አይመስልህም?” በፈገግታ ባለቤቷንና ልጆቿን ተመለከተች፡፡ “እስማማለሁ፡፡ እናደርገዋለንም፡፡ እስከ አሁን ብዙ ተጎድተሻልና አንዲት ረዳት ብትኖረን ደስ ይለኛል፡፡ በሥራ ደክመሽ ውለሽ እንደገና ወደ ጓዳ ማለቱ እጅግ አድካሚ ነው፡፡” “እያሰብኩበት ነው፡፡ ጥሩ ሰው ከተገኘ አጠያይቃለሁ፡፡” “መልካም፡፡ ኑ ልጆች እናታችሁን እናመሰግናለን! ብላችሁ ሳሟት” አለ አክሊሉ እየሳቀ፡፡ ሁለቱም እናታቸው አንገት ላይ ተጠመጠሙ፡፡ እቅፍ አድርጋ ስትስማቸው ቆይታ “አሁን ተራው ለአባታችሁ ነው ሒዱና ሳሙት” አለች ፈገግታ እየመገበቻቸው፡፡  ልጆቹ በእናታቸው ትእዛዝ መሠረት አባታቸውን አቅፈው ከሳሙት በኋላ ኤፍራታ ከአባቷ ጋር መጫወት ፈለገች፣ ናሆም ደግሞ ለጠየቀው ጥያቄ መልስ ፈለገ፡፡ ሐና ባለቤቷንና ልጆቿን በፍቅር ዓይኖች እያስተዋለች “በሉ እናንተ ተጫወቱ፡፡ እኔ እራታችንን ላዘጋጅ” ብላ ወደ ጓዳ ገባች፡፡ ከላይዋ ላይ ትልቅ ሸክም ተነሣላት፡፡ ለብዙ ጊዜ ሲያስጨንቃት የቆየው ጉዳይ ባልጠበቀችው ጊዜ መፈታት መቻሉ አስገረማት፡፡ እፎይታ በውስጧ ነገሠ፡፡ ቤቱ በአንድ ጊዜ ከዝምታ ድባብ ወደ ፍቅር ጨዋታ ተለወጠ፡፡ ቤቱ ውስጥ ሲያንዣብብ የነበረው ዳመና ተገፈፈ፡፡ ጥቂት ሲጫወቱ ቆይተው ናሆም ዓይኖቹን እያቁለጨለጨ “የቅድሙ ጥያቄ እኮ አልመለስክልኝም” አለ፡፡  “እኔ መጫወት ነው የምፈልገው” አለች ኤፍራታ እያኮረፈች፡፡  አክሊሉ “ቆይ ለወንድምሽ አሁን ጠይቆኝ ለነበረው ጥያቄ መልስ ልስጠውና ከአንቺ ጋር ደግሞ እንጫወታለን፡፡ እሺ?” አላት ዐይን ዓይኗን እየተመለከተ፡፡ ኤፍራታ እንዳኮረፈች ተቀመጠች፡፡ አክሊሉ የልጁን ምላሽ አልጠበቀም ከናሆም ጋር ጀምረውት ወደ ነበረው ጥያቄና መልስ አመሩ፡፡ አክሊሉ ለልጁ እንዴት በቀላሉ ሊያስረዳው እንደሚችል ማሰብ ጀመረ፡፡  “ቅዱስ ዳዊት ምን ይላል መሰለህ ልጄ? “እግዚአብሔር ያበራልኛል፣ ያድነኛልም” ይላል (መዝ.፳፯.፩)፡፡ በብርሃንና በጨለማ እኩል አንጓዝም፣ በጨለማ ውስጥ ሆነን የምናየውን ነገር መለየት ያቅተናል፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር የተሰወረውን እንደሚገልጥልን እያመንን ዓይኖቻችንን ገልጠን እንጸልያለን፡፡ በቅድስናው ስፍራ በቤተ ክርስቲያን፣ እንዲሁም በቤታችን ሆነን እንጸልያለን፡፡ ሌላው ደግሞ “የዓለም ብርሃን እኔ ነኝ፣ የሚከተለኝ የሕይወት ብርሃንን ያገኛል እንጂ በጨለማ ውስጥ አይመላለስም” በማለት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አይሁድ የሚሠሩትን ክፋትና ተንኮልን በጨለማ መስሎ ነግሯቸዋል፡፡(ዮሐ.፰.፲፪)፡፡  “በተጨማሪም “ሕይወት በእርሱ ነበረ፣ ሕይወትም የሰው ብርሃን ነበረ፣ ብርሃንም በጨለማ ያበራል፣ ጨለማም አላሸነፈውም” በማለት ወንጌላዊው ዮሐንስ ይነግረናል፡፡ እኛም በብርሃን ልንመላለስ ይገባል፡፡ (ዮሐ.፩፥፭)፡፡ “እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ” ብሎ የተናገረውንና እርሱ ብርሃን ሆኖ ብርሃንነቱን የገለጠልን የአምላካችን የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ቃል ማመንና መቀበል፣ እንዲሁም እንደ ቃሉም መኖር ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ እኛ ዓይኖቻችንን ጨፍነን አንጸልይም፡፡ ሌሎችም ማስረጃዎች ማቅረብ ይቻላል፡፡ ለጊዜው ይበቃናል፡፡ አንተ በሆነው ባልሆነው አትደናገጥ፣ አትከራከር፡፡ በዚህ ዕድሜህ ማወቅ ያለብህን እንጂ ከአቅምህ በላይ መጓዝ የለብህም፣ መጀመሪያ መማር ይቀድማልና፡፡ ከቅዳሜ ጀምሮ ሰንበት ትምህርት ቤት ሁለታችሁንም አስመዘግባችሁና በየሳምንቱ የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ትከታተላላችሁ” አለ አክሊሉ በትክክል መግለጹንና ልጁ የተናገረውን ይረዳ አይረዳ ለማወቅ በትኩረት እየተመለከተው፡፡  “ገብቶኛል፡፡ እኔ እኮ ሲከራከሩ አላስችልህ እያለኝ ነው” አለ፡፡ “እኔ ነገ ትምህርት ቤት ሄጄ ከኃላፊዎቹ ጋር እነጋገራለሁ፡፡ በተረፈ የእናንተ ግዴታ መማር ብቻ ነው፡፡ ገና ሕፃናት ስለሆናችሁ ስለ ሃይማኖት መከራከር አይገባችሁም” ብሎ አስጠነቀቀው፡፡ “እሺ! አመሰግናለሁ” አለ ናሆም በመልሱ ተደስቶ፡፡ “ራት ደርሷል፣ እጃችሁን ታጠቡ” አለች ሐና ከጓዳ ውስጥ ሆና ድምጿን ከፍ አድርጋ፡፡ ናሆም የእጅ ውኃ ከሰጠ በኋላ በአንድ ላይ የተዘጋጀውን ማዕድ መቋደስ ቀጠሉ፡፡  አክሊሉ ተፀፅቶ፣ ለቤተሰቡ የነፈጋቸውን ጊዜ በመስጠቱ፣ የልጁንና የሚስቱን ጥያቄ መመለስ በመቻሉ፣ ከሚስቱንም ጋር በመወያየቱና መግባባት በመቻላቸው ተደሰተ።                     
Read 1300 times