Friday, 06 November 2020 00:00

የተከዜ ምዕራፈ ቅዱሳን ቅድስት ኪዳነ ምሕረት እና መድኃኔዓለም ዘአቡነ ሐዋርያ ክርስቶስ አንድነት ገዳም (ክፍል አንድ)

Written by  በወግደረስ አዳል
መግቢያ በሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ውስጥ ፴፩ ገዳማት የሚገኙ ሲሆን ተከዜ ኪዳነ ምሕረት ምዕራፈ ቅዱሳን አቡነ ሐዋርያ ክርስቶስ ገዳም አንዱ ነው። እግዚአብሔር አምላካችን ለወዳጆቹ በሰጣቸው ቃል ኪዳን መሠረት ምእመናን በቅዱሳኑ ስም ከተመሠረቱ ገዳማት በረከትን ያገኛሉና እኛም ሁሉም ምእመናን ወደ ገዳሙ በመሄድ በረከትን ይሳተፉ ዘንድ በዚህ የእናስተዋውቃችሁ ዐምድ የዚህን ገዳም ታሪክ ከነሥርዐቱ አቅርበናል። መልካም ንባብ።  የገዳሙ መገኛ ገዳሙ የሚገኘው በሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት በላስታ ወረዳ  በዜሮ ሰባት ቀበሌ እና በመቄት ወረዳ ነው።  የአባቶች ገዳም ተከዜን ተሻግሮ ከወንዝ ማዶ የሚገኝ ሲሆን የእናቶች ገዳም ላስታ ወረዳ ውስጥ የሚገኝ ነው።  ገዳሙ የተከዜን ወንዝ በሥሩ እየጠጣ የቅዱሳን መነሀሪያ የሆነ በቆላማው የሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት የተከዜን ወንዝ መሠረት አድርጎ የተሠራ ነው። በስተ ሰሜን የቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት በደቡብ የአቡነ አሮን ገዳም በቅርብ ርቀት የሚያዋስኑት ገዳም ነው። ወደ ገዳሙ ለመድረስ በወልዲያ ወይ በባሕር ዳር በጋሸና አድርጎ ወደ ላሊበላ በሚወስደው መንገድ ላይ በተለምዶ ግራኝ አምባ (አዲስ አምባ) በመባል የምትታወቀው ከተማ ሲደርሱ ወደ ምዕራብ አቅጣጫ ታጥፎ እስከ ገዳሙ ክልል ድረስ በተጠረገው መንገድ በእግር ወይም በመኪና መጓዝ ይቻላል። በገዳሙ ውስጥ ሦስት አብያተ ክርስቲያናት የሚገኙ ሲሆን እነሱም የቅድስት ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን በእናቶች ገዳም፣ የመድኃኔ ዓለም በአባቶች ገዳምና የቀጭን አበባ ሥላሴ ናቸው። አመሠራረትና እስካሁን ያለው ታሪክ የገዳሙ መሥራች በጽኑዕ ተጋድሏቸው የሚታወቁት አቡነ ሐዋርያ ክርስቶስ ሲሆኑ የተመሠረተውም በቅዱስ ገብረ ማርያም (ሐርቤ) ዘመነ መንግሥት በ፲፪ኛው መቶ ክ/ዘመን ነው። የአባታችን አቡነ ሐዋርያ ክርስቶስ ትውልዳቸው ሸዋ ቡልጋ ሲሆን አባታቸው ንዋየ ጽዮን እናታቸው ፍቅርተ ክርስቶስ የሚባሉ ደጋግ  በተለይም ለምጽዋት እና እንግዳ ለመቀበል የተጉ ክርስቲያኖች ነበሩ። በዘመናቸውም እመቤታችን በእንግድነት ተገልጻላቸው ይህን ቅዱስ አባት እንደሚወልዱ አብሥራቸዋለች።  የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ተምረው ዲቁና እንደ ተቀበሉ ወደ ታላቁ የአየለነ (እየላ) ሚካኤል መጥተው በዲቁና እያገለገሉ በጽኑ ተጋድሎ እየተጋደሉ ቆይተው ምንኵስናን ለመቀበል ወደ ደብረ በንኰል አቡነ መድኃኒነ እግዚእ ገዳም ሄዱ። በዛም በብዙ ተጋድሎ ከቆዩ በኋላ በአቡነ መድኃኒነ እግዚእ እጅ ምንኵስናን ተቀብለው በቅዱስ ሚካኤል መሪነት ከእመቤታችን እጅ የተቀበሏትን የቃል ኪዳን መታሰቢያዋ የሆነችውን ታቦተ ኪዳነ ምሕረት ይዘው መሃል ተከዜ ወደሚገኘው ወደዚህ ገዳም መጥተዋል። ወደ ገዳሙ ሲደርሱም በአናምርትና በአናብስት ተከቦ በረድኤተ እግዚአብሔር ሲጠበቅ አግኝተውታል። ለታቦተ ኪዳነ ምሕረት ማደሪያ የሚሆን ቤተ ክርስቲያን ከሠሩ በኋላ ሌሊት ተከዜ ወንዝ ውስጥ ሲጸልዩ እያደሩ ቀን ቀን አሜከላ አንጥፈው ሲሰግዱ በመዋል አብዝተው እየተጋደሉ መኖራቸውን ቀጠሉ። ገዳሙም የብዙ መናንያን መሰባሰቢያና ትልቅ ገዳም ሆነ።  የተከዜ ኪዳነ ምሕረት ገዳም በቅዱስ ገብረ ማርያም (ሐርቤ) ዘመነ መንግሥት የተመሠረተ ሲሆን ገዳሙን ከምሥረታ ጀምሮ ወደ ተሻለ ደረጃ እስከ ማሳደግ ድረስ የደረሱት ታላቁ አባት ሐዋርያ ክርስቶስ ናቸው። እኒህ አባት በእግዚአብሔር ጥሪ የኦሪት መሥዋዕት ይሠዋበት በነበረው ከእየላ ሚካኤል ተነሥተው ወደዚህ ገዳም የተከዜን ወንዝ ተከትለው በመምጣት ዙሪያዋን አንበሶች እና ነብሮች አጥሯን ፤ ቅጥሯን እየጠበቁ አገኟት። ወደ ገዳሙ ሲገቡ ሰማይ ተከፍቶ እግዚአብሔር በዙፋኑ ተቀምጦ ታያቸው። ጌታችን “ወዳጄ ሐዋርያ ክርስቶስ እንኳን ደኅና መጣህ፤ ሁል ጊዜ ከእኔ ጋር ትኖራለህ” አላቸው። ከዚህ ጋር አያይዞም “ይህ ቦታ ምዕራፈ ቅዱሳን ተብሎ ይጠራል” አላቸው። እርሳቸውም ከእመቤታችን በተቀበሉት የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም የቃል ኪዳኗ መታሰቢያ በሆነው በቅድስት ኪዳነ ምሕረት ታቦት ስም የመሠረቱትን ገዳም ምዕራፈ ቅዱሳን ቅድስት ኪዳነ ምሕረትና መድኃኔ ዓለም አንድነጽ ገዳም ብለው ከጌታችን በተነገራቸው ቃል ኪዳን መሠረት መጥራት ጀመሩ። ሐዋርያ ክርስቶስም  በዚህ ገዳም እየጸለዩ እና እየሰገዱ ለዓለም ምሕረትን እየለመኑ ለሕሙማን ፈውስን እያሰጡ የምንኵስና ሕይወት በገዳሙ እንዲሰፋ እና እንዲጠናከር አድርገዋል።  በመጨረሻም እግዚአብሔር አምላክ እስከ ዳግም ምጽአት ‘‘ሞት የለብህም’’ ብሎ  ስለ ፍቅራቸውና ስለ ጽኑ ተጋድሏቸው ዐሥራ ሁለት ክንፍ ተሰጥቷቸዋል። ሐዋርያ ክርስቶስም ቃል ኪዳን ተቀብለው በ፲፩፻፲፭ ዓ.ም. ግንቦት ፲፮ ቀን ተሠውረዋል።  አፄ ምኒልክ ለገዳሙ መገልገያ የሚሆኑ የተለያዩ ንዋየ ቅዱሳትን አበርክተዋል። ልጃቸው ንግሥት ዘውዲቱ ከባላምባራስ ጉግሳ ወሌ ጋር በየገዳማቱ እየሄዱ ይረዱና ለሕይወታቸው ይማፀኑ ነበር። ብዙ ተኣምራትንም አድርጋላቸዋለች። ገዳሙ ከተመሠረተበት ዘመን ጀምሮ  በሳቸው እግር በተተኩ አባቶች ፈተናዎችን እያለፈ በጽኑ ገዳማዊ ሕይወትና ሥርዓት ቢቆይም በ፲፱፻፸፯ ዓ.ም. በነበረው ድርቅ ምክንያት ተፈቷል። ከሦስት በማይበልጡ መነኰሳት እየተጠበቀ ያለ ምንም የውስጥ አገልግሎት እስከ ፲፱፻፺፪ ዓ.ም. ቆይቷል። በ፲፱፻፺፪ ዓ.ም. በአባ ኪዳነ ማርያም አማካኝነት በርካታ መናንያን ተሰባስበው ድጋሚ ተጠናክሮ በአሁኑ ሰዓት ፮፻፲፮ መናንያንና ከ፴ የሚበልጡ የአብነት ተማሪዎች የሚገኙበት ገዳም ሆኗል። (ምንጭ በገዳሙ ከሚገኙ አባቶች) ፩. ሥርዓተ ገዳም ፩.፩.አንድነት ገዳሙ የአንድነት ገዳም በመሆኑ ጥብቅ የአንድነት ሥርዓት ያለው ነው። በዚህ ገዳም ቁሪት፣ ዘረኝነት፣ ነገረ ሠሪነት ክልክል ከመሆኑም አልፎ ውጉዝ ነው። ማንም በገዳሙ በምናኔ የሚኖርም ሆነ በእንግድነት የመጣ ሰው የገዳሙን የአንድነት  ሥርዓት የማክበር ግዴታ አለበት ። ምግብንም የገዳሙ መጋቢ ከቆነነው ውጭ መጠቀም ፈጽሞ ክልክል ነው። እንግዳ ወደ ገዳሙ  ለሥራ፣ ለጠበል፣ ለጸሎትና ለሱባኤ ሲመጣ ከመናንያን  በዓት ማረፍ ከተመደበለት ሊቀ አበው ውጭ ያለ ሥራና ያለ መጋቢው ፈቃድ ከሌሎች ጋር መገናኘት ክልክል ነው። ይህ እና ይህን የመሳሰሉት ሥርዓቶች በመናንያኑ ዘንድ (ከሥር በፎቶው እንደሚታየው) የአንድነት ገዳማዊ መንፈሳዊ ሕይወት ቃል ኪዳን ውስጥ ተካትተው የሚታወቁ ናቸው። ፩.፪.ሥርዓተ ምንኵስና በገዳሙ ለምናኔ የሚመጣ ሰው ስለ መጣበት ምክንያት ተጠይቆ ያስረዳል። ቤተሰቡን ትዳሩን ልጆቹን በትኖ አለመምጣቱን፣ ወንጀል ሠርቶ ለመደበቅ አለመምጣቱን፣ ገዳሙን በማንኛውም መንገድ ሊጎዳ አለመምጣቱን፣ ማንነቱን የሚገልጽ መታወቂያ  እና መሰል ሁኔታዎችን ተጠይቆ ለ፺ ቀናት (ለሦስት ወራት) ደጅ እንዲጠና ይደረጋል። ከዚያም በሰላም ለኪ ወደ ገዳመ ማኅበሩ ገብቶ ለሦስት ዓመት የአመክሮ ጊዜ ይሰጠዋል።  ከሌላ ገዳም ፈልሶ የመጣ እንደ ሆነ በምን ምክንያት ከነበረበት ገዳም እንደ ወጣ፣ በምግባር ችግርም ተባሮ እንደ ሆነ ይጠየቃል። ‹ነበርኩበት› ወዳለው ገዳም ተደውሎ ስለ እርሱ ይጠየቃል። ፈተና ጸንቶበት የመጣ እንደ ሆነ ይቀበሉታል። በምግባር ብልሹነትና ሁከት በማስነሣት የተባረረም ከሆነ ተለይቶ እንዲመከርና በጥንቃቄ ገዳመ ማኅበሩን በማይበጠብጥበት ሁኔታ እንዲታረም ይደረጋል። ምክንያቱም ሁከት ይፈጥራል በሚል ሥጋት ብቻ እንደ መጣ ቢባረር ወደ ዓለም ተመልሶ ይወድቃልና የመታረሚያና የጽሞና ጊዜ ይሰጠዋል። የማይመለስ ከሆነና ለገዳማዊ ሕይወት እንቅፋት የሚሆን ሆኖ የተገኘ እንደ ሆነ  ገዳሙን ለቆ እንዲወጣ ይደረጋል። ምንፍቅናንና ሁከትን ሊዘራ የመጣ ከሆነ ግን ሳይውል ሳያድር ገዳሙን ለቆ እንዲወጣ ይደረጋል። በገዳሙ ውስጥ የአመክሮ ጊዜያቸውን በጥሩ ገዳማዊ ሕይወት ላሳለፉ አባቶችና እናቶች አቡነ ሐዋርያ ክርስቶስ የልደታቸው መታሰቢያ በሚከበርበት ሐምሌ ፲፮ እና እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከስደት ተመልሳ ደብረ ቍስቋም በገባችበት በኅዳር ፮ የምንኵስና ሥርዓታቸው ይፈጸማል። ሐምሌ ፲፮ የጻድቁ አቡነ ሐዋርያ ክርስቶስ በዓለ ንግሥ ሲሆን በኅዳር ፮ ደግሞ እመቤታችን ከስደት ተመልሳ ደብረ ቍስቋም የገባችበት ዓመታዊ በዓል ነው። ስለዚህ ወደ መርንኵስና ሕይወት ለሚቀላቀሉ አባቶችና እናቶች ከቅድስት ድንግል ማርያም እና ከአቡነ ሐዋርያ ክርስቶስ ቃል ኪዳን ለመቀበል ነው።  በገዳሙ ሥርዓት መሠረት ከወላጅ አልባዎች ውጭ ለምናኔ የሚመጡ ዕድሜያቸው ከ፲፰ ዓመት በታች የሆኑትን አይቀበልም። ይልቁንም ውስጣቸው ያለው መንፈሳዊነት ልምላሜው የማይቋረጥበትን መንገድ አመላክቶና ምክር ሰጥቶ ወደ ቤተሰቦቻቸው ይመልሳል። ፩.፫.የአመጋገብ ሥርዓት አመጋገብን በተመለከተም ገዳሙ ሥርዓት አለው። በበዓለ ሃምሳ በቅዳሜና እሑድ ከጧቱ  ሦስት ከሃያ እና ዘጠኝ ሰዓት ከሃያ ላይ፣ ሥራ በማይሠራባቸው በዓላትና በፍልሰታ በቀን አንድ ጊዜ ዘጠኝ ሰዓት ፣ በሰሙነ ሕማማት ከዋክብት ሲታዩ፤ በሌሎች ቀናት ለአረጋውያንና ለካህናት ዘጠኝ ሰዓት በቀን አንድ ጊዜ ሲሆን ለሚወጡት ለሚወርዱት (ሥራ ለሚሠሩ) አርድእት በሰባት ሰዓት የመቁንን ሥርዓት ተሠርቷል። በገዳሙ አንድነት በ፳፻፰ ዓ.ም. በተወሰነው ውሳኔ መሠረት ዐበይት በዓላትንና ዓመታዊ የቅዱሳን መታሰቢያ በዓላትን ጨምሮ በየትኛውም ጊዜ በገዳሙ ውስጥ አስካሪ መጠጥ አይዘጋጅም፤ ሥጋ አይበላም፤ ከውጭም ይዞ መግባት ፈጽሞ ክልክል ነው። በገዳሙ ሕመምተኞች የሚረዱበት በአባቶችም በእናቶችም ቤተ ሕሙማን ያለ ሲሆን እነሱን የሚንከባከቡ ትራስ ቀና የሚያደርጉ የሚያጎርሱ ልብሳቸውን የሚያጥቡ አረጋውያንንም የሚጦሩ ሊቀ አበው አሉ። በገዳሙ ውስጥ አእምሮውን ላጣ፣ ሂድ ሂድ ለሚለው ሰው ለ፫ ቀን፣ ለ፯ ቀን ጸሎተ ማርያም ይደረግለታል በሁሉም ጸሎቶች ያታሰባል፤ የንስሓ አባቱ እንዲጎበኙትና እንዲመክሩት ይደረጋል። የማይተወው ከሆነና የሚጸናበት ከሆነ እግረ ሙቅ ይደረግለታል። ከዚህም በተጨማሪ የምክርና የሕክምና እርዳታ የሚያገኝበት በገዳሙ አባቶችና እናቶች የሚገለገል መለስተኛ ክሊኒክም አለ። ፩.፬.የቤተ ሰብ ጉብኝት ሥርዓት ዘመድ ጥየቃንም በተመለከተ ገዳሙ ሥርዓት አለው። ማንኛውም የመናኝ ቤተሰብ ዘመድ ‹በዚህ ገዳም ይገኛልና ልጠይቀው መጥቻለሁ› ካለ የገዳሙን ህልውና የሚፈታተን ሰው አለመሆኑን ለማረጋገጥ የሚጠቅሙ መሠረታዊ ጥያቄዎችን እንዲሁም ስለ መናኙ ማንነትና ስም ይጠየቅና “የተባለው ሰው በገዳሙ ስለ መኖሩ እናጣራለን” ተብሎ በእንግዶች ማረፊያ እንዲያርፍ ይደረጋል። ከዚያም የተባለው ሰው በገዳሙ ያለ ከሆነ እከሌ የሚባል ሰው ያውቅ እንደ ሆነ ተጠይቆ “አውቀዋለሁ” ካለ “ሊጠይቅህ መጥቷልና ልታገኘው ትፈልጋለህ ወይ” ተብሎ ይጠየቃል። “አዎ አግኝቸው ስለ ደኅንነቴ እንዲያውቅና ስለ ሁሉም ነገር ልነግረው እፈልጋለሁ” ካለ እንዲገናኙ ይደረጋል። “አይ ላገኘው አልፈልግም ደኅና መሆኔን ነግራችሁ ሸኙት” ካለ ወይም “አይ ለምናኔ ሕይወቴ ፈተና ስለሚሆንብኝ ላገኘውም አልፈልግም እዚህ መኖሬንም አትንገሩት በጥሩ የእንግዳ አሸኛኘት አስተናግዳችሁ ሸኙት” ካለ በጥሩ ሁኔታ ተስተናግዶ ይሸኛል። ፪.የገዳሙ አስተዳደር የአገልግሎት መዋቅር ገዳሙን የተመለከተ ማንኛውም ሕግና ሥርዓት ሲወጣና ሲወሰን ሁሉም የገዳሙ አንድነት በተገኙበት ነው። ከዚህ ጠቅላላ ጉባኤ ቀጥሎ የገዳሙን የትኛውንም እንቅስቃሴ የሚቆጣጠርና የገዳሙ ሥርዓተ ገዳም በትክክል እየተተገበረ መሆኑን የሚከታተል ውይይት አድርጎ ለችግሮች የመፍትሔ አቅጣጫ የሚያስቀምጥ የአበው መማክርት አስተዳደር ጉባኤ የሚባል ፲፫ አባላት ያሉት አበ ምኔቱ፣ እመ ምኔቷ፣ አፈ መምህሩ፣ ጸሓፊው፣ መጋቢው፣ ሊቀ አርድእቱ እና የሰባቱ ዘርፎች ተጠሪዎች ያሉበት ነው። ፪. የሥራ ዘርፎች ሀ.የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ዘርፍ፦ ይህ ዘርፍ የቤተ ክርስቲያን የውስጥ አገልግሎት፣ የስብከተ ወንጌል አገልግሎት እና የአብነት ትምህርት ክፍሎችን በውስጡ የያዘ ነው። ለ.የቤተ እግዚአብሔር አገልግሎት ዘርፍ፦  በዚህ ዘርፍ ውስጥ የማኅበር መቁነን ዝግጅት ክፍል እና የቁሳቁስ አቅርቦት አገልግሎት ክፍል ይገኛሉ። በውስጡ እንጨት ፈላጮች፣ አህያ ጫኞች ፣ ሊቀ አበው ፣ ባለ ተስፋዎች፣ እጓል መጋቢዎች እና አረጋውያንን ያካተተ ነው። የአገልግሎት ዘርፉ ሥያሜ (የቤተ እግዚአብሔር አገልግሎት) የሚለው በገዳሙ ውስጥ ያለውን ሁሉ የሚያካትት ቢሆንም  ሥያሜው ግን በዚህ ክፍል ለተጠቀሱት የአገልግሎት ዘርፎች ብቻ ስተለተሰጠ እኛም ሥያሜውን እንዳለ ወስደነዋል።  ሐ.የእጅ ሥራ ዘርፍ፦  በውስጡም የጥሬ ዕቃና ምርት ማደራጃ፣ የሽመና፣ የሹራብ ሥራ፣ የጥልፍ ሥራና የኅትመት ሥራ ክፍሎችን በሥሩ የያዘ ነው። በእደ ጥበብ ሥራ ያለውን ከምርት እስከ ጥራት ፍተሻና ቁጥጥር ያለው በዚሁ ዘርፍ ሥር ነው።  መ.የግብርና ልማት ዘርፍ፦ በውስጡም የእርሻ፣ የደንና የአትክልት ልማት እና የርባታ ክፍሎችን የያዘ ነው። ሠ.የግንባታ ልማት ዘርፍ፦  የቤቶች ግንባታ፣ የመንገድ ሥራና የውኃ ሥራ ክፍሎችን በውስጡ የያዘ ዘርፍ ነው። ረ.የቴክኒክና የኢንዱስትሪ ዘርፍ፦ የተሽከርካሪ አገልግሎት፣ የወፍጮና ሌሎች የሞተር ነክ አገልግሎቶች እና የብረታ ብረትና የእንጨት ሥራ ክፍሎችን የያዘ ዘርፍ ነው። ሰ.የሥነ ጽሑፍና ቅንብር ሥራዎች ዘርፍ፦ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች፣ የድምፅና የምስል ቅንብር ሥራዎች እና የድምፅና ምስል ቀረጻ ክፍሎችን የያዘ ዘርፍ ነው። ሁሉም የገዳሙ ማኅበረሰብ ከላይ ከተጠቀሱት የሥራና የአገልግሎት ዘርፎች ውስጥ የተካተተ ነው። የዘርፎቹም ተጠሪዎች የአበው መማክርት ጉባኤ አባላት ናቸው።
Read 1376 times