Friday, 04 December 2020 00:00

''በስሜም ሰላም በሉት’’፩ኛ ሳሙ.፳፭፡፭

Written by  ማኅበረ ቅዱሳን

Overview

ለሰው ልጆች ህልውና እጅግ አስፈላጊ ከሆኑ ነገሮች መካከል ሰላም ዋናው ነው። ሕይወትና ኑሮ ሊታሰብ የሚችለው ራሱ ሰላም ሲኖር ነው። ሰላም ከሌለ መምህሩ ማስተማር፣ ተማሪው መማር፣ ነጋዴው መነገድ፣ ሸማቹም መሸመት አይችልም። ሐኪሙ ማከም፣ መሐንዲሱ መገንባት የሚችለው ሰላም ሲኖር ብቻ ነው። ይህ ካልሆነ ግን ሐኪሞ አክሞ የሚያድነው ሟችን፣ መሐንዲሱ የሚገነባውም ፈራሽን ይሆናል። ሰላም ከሌለ ገበሬው ዘርቶ ሀገር መመገብ አይችልም፤ የሃይማኖት አባቶችም ያልተማረውን ለማስተማር የተማረውንም ለማጽናት ፈተናው ይበረታባቸዋል። የሰላም ዋጋው እጅግ ውድ ነው። የትኛውም ሰው የዕለት ግብሩን ለመፈጸም በቅድሚያ ሰላም ሊኖረው ይገባዋል። ለዚህ ነው መዝሙረኛው ‹‹ከክፉ ሽሽ መልካምንም አድርግ፤ ሰላምን ሻት ተከተላትም፤›› ሲል የዘመረው። (መዝ.፴፫፥፲፬)። አብዛኛው የሀገራችን ታሪክ በጦርነት የታጀበ ነው። ብዙ ጠላቶች በየዘመናቱ እየተነሡብን የመከትነውን ያህል፡ እርስ በእርስ የተገዳደልንባቸው ታሪኮቻችንም ትንሽ የሚባሉ አይደሉም። በሁሉም ጦርነቶች ግን ወንድሞች ተገዳድለዋል፣ ሕፃናት በወላጅ እጦት ተርበው አልቀዋል፣ ወገን ተጨፍጭፏል፣ ሀገር ወድማለች። ይህ ሁሉ ክስረት በየዘመናቱ የተከሰተው እርስ በእርስ ወንድማማቾች ተጣልተው መሆኑ ደግሞ ሕመሙን የከፋ ያደርገዋል።

 

ሰላም በጠፋባቸው በእነዚህ የታሪካችን ክፍሎች ሁሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጉዳትም ቀላል የሚባል አልነበረም። እንዲያውም የመከራዎቹ ዋናዋ ገፈት ቀማሽ እርሷ፣ አገልጋዮቿና ምእመናኗ ነበሩ። በመሆኑም የሰላምን መልካም ጣዕምና የጦርነትን መራራነት በተግባርም ጭምር ታውቀዋለች። ስለዚህም የሰላምን አስፈላጊነት በአገልግሎቷ ሁሉ ትሰብካለች። ስለ ሀገር ሰላም ዘወትር ትጸልያለች። በጸሎት ብቻም ሳይሆን ድርሻዋን በተግባር በመወጣትም ዘወትር ግንባር ቀደም ናት። ብዙ አብያተ ክርስቲያናት በተቃጠሉባትና አገልጋይ ካህናቷና ምእመኖቿ በተሠዉበት ባለፉት ቅርብ ዓመታት እንኳን በተለያዩ ሀገር ዐቀፍ የሰላም ጉባኤያት ስለ ሰላም ሰብካለች። ልበ አምላክ ዳዊት ናባል የተባለውን የምስጉኗ የአቢግያ ባልን የማጥፋት ኀይል እያለው ‹‹በስሜም ሰላም በሉት›› ብሎ ብላቴኖችን የላከበት ከዚህ የቤተ ክርስቲያንና የቅዱሳን ባሕርይ የተነሣ ነው።

በሀገራችን እየተካሄደ ያለው ጦርነትም ቤተ ክርስቲያንንና እኛ ልጆቿን በእጅጉ የሚያሳስብ ነው። በዚህ ጦርነት ስለሚጠፉት ነፍሳትና ስለሚወድመው የሀገር ሀብት ማሰብ እጅግ ያስጨንቃል። ቤተ ክርስቲያን ዘወትር ስለ ሰላም ሰብካለች። ይህም ብቻ ሳይሆን በልጆቿ አማካይነት ይህ ጦርነት እንዳይመጣ በተግባርም ብዙ ደክማለች። አሁንም የበለጠ እልቂትና ውድመት ሳይከሰት ይህ ጦርነት በአጭሩ እንዲቋጭ ጸሎቷና ምኞቷ ነው። ይህንን ምኞቷንም ሁሉም አካላት እንዲጋሩላት ትፈልጋለች። የሀገራችን ዜጎች ሁሉ እንደ ገና በሰላምና በመተሳሰብ እንዲኖሩ፣ ምእመኖቿም ያለ ሥጋት ‹‹የሰላም አለቃ›› የተባለ አምላክን እንዲያመልኩ ትፈልጋለች። ለዚህም ደግሞ በየትኛውም ጽንፍ ያለ ወገን የመዝሙረኛውን ቃል በማስተዋል ‹‹በስሜም ሰላም በሉት›› እንደ ተባለ ሁሉም ‹‹ከክፉ ሸሽቶ መልካምንም አድርጎ›› ስለ ሰላም ፈጣሪውን እንዲጠይቅ፣ እርስ በራሱም ሰላም እንዲባባል ትሻለች። በኃጢአት የጎሰቆሉ ልጆቿ በንስሓ ወደ መልካሙ መንገድ ሳይመለሱ እንዳይጠፉ ዘወትር ትጸልያለች።

ወቅቱ የጾም እንደ መሆኑም ካለንበት የክፋት ዘመን ያወጣን ዘንድ ሁሉም ሰው በጾም፣ በጸሎትና በልቅሶ ወደ እግዚአብሔር ሊጮህ ይገባል። ስለ ጠፉት ነፍሳት፣ ስላሉት ወገኖች፣ ስለ ቤተ ክርስቲያን፣ ስለ ሀገርና በአጠቃላይ ስለ ሰላም ሁሉም በአንድነት ከጮኸ፡ እግዚአብሔር የምንዱባንን ጩኸት የሚሰማ አምላክ ነውና ወደ እኛ ይመለከታል። ‹‹ሰላምን እንደ ወንዝ፥ የአሕዛብንም ክብር እንደሚጐርፍ ፈሳሽ እመልስላታለሁ›› የሚል አምላክ ‹‹በጾምና በልቅሶ›› ወደ እርሱ ለሚመለሱ ሁሉ ፊቱን ሊመልስላቸው የታመነ ነው። እርስ በርሳችን ከመወቃቀስና ከመጠፋፋት ይልቅ ሰላምን ልንጠያየቅ፣ ወደ እርሱም በጾምና በልቅሶ ልንመለስ ይገባናል። (ኢሳ. ፷፮፡፲፪ ፣ ኢዩ.፪፡፲፪)።

 

Read 538 times