ይህ ሁሉ ቢሆንም ግን ቤተ ክርስቲያን ዛሬም የድርሻዋን በመወጣት ኢትዮጵያን የመታደግ ኃላፊነት አለባት። ቤተ ክርስቲያን ከአስተምህሮዋ የሚመነጭና ከዚች ሀገር ፖለቲካ ጋር የማይጋጭ የፖለቲካ መነጽርን በግልጽ ማበጀት አለባት። ከዚህ እይታ የሚመነጭ ትምህርት፣ ምክርና ተግሣጽ መስጠትም ሁልጊዜ የሚጠበቅባት ጉዳይ ነው። ይህም ትምህርት ምክርና ተግሣጽ ለሰው ሁሉ ኅሊና የሚስማማ ሆኖ በሚዲያዎች መስተጋባት ይኖርበታል። ለዚህ የሚከፈል ዋጋ ካለም ለመክፈል ቆራጥ ርምጃ መውሰድ አለባት።
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በኦርቶዶክሳዊነት መነጽሯ በምትሰጠው ትምህርትና ምክር በቅድሚያ የራሷን ልጆች በአንድ ቤት ማሳደር/አንድ ማድረግ/ አለባት። ከዚያም በዘር ሐረግ፣ በቋንቋ፣ በባህል ልዩ ልዩ የሆነውን የውስጧን ኦርቶዶክሳዊ ማኅበረሰብ በኦርቶዶክሳዊ እምነት መነጽር የሀገሩን ፖለቲካ እንዲመለከት በዚያም እንዲግባባና ሀገሩን ከጥፋት እንዲታደግ መሥራት አለባት። ይህ ስለሀገር የምታደርገው ጥረቷ ደግሞ እውን እንዲሆን በኢትዮጵያ የነበረው አንድነትና የእርስ በርስ ማኅበራዊ ትስስርም እንደገና ተመልሶ እንዲጠናከር በመላው ሀገራችን ያሉ ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ድምጽ በመስማት በአንድ መቆም አለባቸው። ቤተ ክርስቲያን እውነተኛ የእምነት ቤት መሆኗን ለዓለሙ ማሳየት የምትችለው በዚህ በዘር ለመባላት ባኮበኮበ ትውልድ መካከል ገላጋይና አስታራቂ ሆና መገለጥ ስትችል ነው። ትናንት የነበራትን ክብርም ማስቀጥል የምትችለው በዚህ ደረጃ ስትሠራ ነው።
የአሁኑ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ኦርቶዶክሳዊ ትውልድ ግን ይህንን ለማድረግ የዘገየ ይመስላል። ይህ ደግሞ ከፍተኛ ዋጋ ሊያስከፍል ይችላል። ሌሎች ይህን በሀገር እየዘነበ ካለ የመከራ ዶፍ አስጠላይ ሆነው ለመታየትና በቀጣዩ የኢትዮጵያ ትውልድ ውስጥ ባለውለታና ክፉ ዘመን አሻገሪ ሆኖ ለመቅረብ መውተርተራቸው ከአሁኑ የቤተ ክርስቲያን ትውልድ መዘግየት የመነጨ ነው። እውነተኛ ሰላም፣ ግብዝነትም ለሌለበት ፍቅር ምንጩ የሆነች ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን የያዘ ትውልድ ኢትዮጵያ ብዙ ሳትጎዳ ኀዘኗም ከልክ ሳያልፍ መፍጠን አለበት።
ለዚህም ደግሞ ወጣቱ ትውልድ መጀመሪያ በሃይማኖት አባቶቹ ላይ የሚያደርሰውን የማይገባ ነቀፌታ እንዲተው የሃይማኖት መሪዎቻችን ሞራል ማደግ ይገባዋል። ትውልዱ መሪዎቹን ብዙ ጊዜ ታዝቧል። ከመታዘብ ባለፈ አቅም ቢስ አድርጎ ሥሏቸዋል። በቅድሚያ ከጥንት ዘመን ጀምሮ የነበረው የሃይማኖት አባቶች ክብር ይመለስ ዘንድ ቤተ ክርስቲያን የመሪዎቿንና አገልጋዮቿን ክብር ለማስለመስ በትጋት መሥራት ይኖርባታል። በዚህም መሠረት አባቶቻችን የጥንቱን በሚመስል ግብር በልጆቻቸው ዘንድ ከልብ ሊታዩ ከተጣሉአቸውም ሁሉ ከልብ ሊታረቁ ፣ በውስጣቸው ያለውን የዘር፣ የባህል፣ የቋንቋ፣ የጎጥ፣ የጥቅም ግጭትም ወዘተ እርም አድርገው ከውስጣቸው ሊያስወግዱ ይገባል። ብፁዓን አባቶች የሚደፍሩትን ይቅር መባባል ልጆቻቸው ቀሳውስትና ዲያቆናት ይደፍሩታል። ከዚያ ደግሞ ምእመናን እርስ በርሳቸው ይቅር ይባባላሉ። ይህንንም ሁሉ በማየት ትውልድ ሁሉ እርስ በርሱ ይቅር ለማባባል አቅም ያገኛል። በመጽሐፍ ‹‹ክፉ ከምትሠሩ ይልቅ መልካም ሥራ እየሠራችሁ የእግዚአብሔርንም ፈቃድ እየተከተላችሁ መከራ ብትቀበሉ ይሻላልና።›› (፩ኛ ጴጥ ፫ ፥ ፲፯) ተብሎ እንደተጻፈ። በዚህ ሂደት ውስጥ የሚመጣ እስራት፣ ስደት፣ ሞት፣ እንግልት፣ የስም መጥፋት፣ ወዘተ መከራ ቢኖር እንኳን መከራውን መቀበል አስደሳች ይሆናል።
ቅደስት ቤተ ክርስቲያን ከአስተምህሮዋ የሚመነጨውን ይህን መልካም ተግባር በትጋት ለመፈጸም ሀገርን ከሚመሩ የፖለቲካ ኃይሎች ጋር ያለቸልተኝነት በምክክርና በትብብር አብራ ልትሠራ ይገባል። ከዚያ ያለፈ ነገር ሲመጣ ደግሞ ለምን ብላ ልትጠይቅ ልትገሥጽም ይገባታል። ከኢትዮጵያ ጥፋት በላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ሊያስተክዛት የሚችል ነገር አይኖርምና። ኢትዮጵያን አስከብራ እንደኖረች ሁሉ በኢትዮጵያ የሚመጣውን መከራ ዛሬም በመቀበል ላይ ናት።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሕዝብን ሁሉ በጥላቻ ከመተያየት ማትረፍ ይጠበቅባታል። የቤተ ክርስቲያ አምላክ ሀገራችንንና ሕዝቦቿን ከሰይጣን ክፉ ሥራዎች ሁሉ እንዲጠብቃቸው ዘወትር መጸለይ ያስፈልጋል። ለዚህ ግን የቤተ ክርስቲያን ልጆች ዘግይተዋል። በመሪዎቻችንም ላይ ሰይጣን ከልክ ያለፈ የሚያዘገይ አዚም የጫነባቸው ይመስላል። ከዚህ አዚም በመውጣት የቤተ ክርስቲያንን መከራ ማቅለል ከመሪዎቿም ከልጆቿም ዘመኑ የሚጠይቀው ጉዳይ ነውና ይህንን ከማድረግ መዘግየት የለብንም።
በቅርብ ዘመን ታሪክ ውስጥ እንኳን በመከራ ውስጥ አልፎ ሀገርና እምነትን ስለማስከበር ምሳሌ የሚሆኑ አባቶች ነበሩ። በኢትዮጵያ የእነ አቡነ ጴጥሮስ፣ የእነ አቡነ ሚካኤል መልካም ሥራ በእኛም የዘመኑ ኦርቶዶክሳዊ ትውልድ ደም ውስጥ መኖር ይገባዋል። በግብጽ ጨካኝ እስላማዊ መንግሥት ሥር የወደቀች የግብፅ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን ህልውና ለመጠበቅ ተጋድሎ ሲፈጽሙ የነበሩትን አቡነ ሺኖዳ ሣልሳዊን ማሰብ እና ምን ላይ እንዳለን በግልጽ ያመለክተናል።
ሀገር ከፈረሰ፣ ወገን ከደከመ፣ መላም ከጠፋ በኋላ፣ በስንፍናችንም መባስ ፈጣሪ ቸል ካለን በኋላ ብንነቃ ምን ዋጋ አለው? ዛሬ እንዳናጣው የምንመኘውን ክብርና ጥቅም ሁሉ ብቻችንን ሆነን በምንቀበለው መከራ እናጣዋለን። ስለዚህ ለመልካም ሥራ ዘግይተናል፤ አሁንም ግን ጊዜ አለ፤ እንዳንቀር እንጠንቀቅ።