Tuesday, 09 February 2021 00:00

በሙዚቃ ድግስ የታጀቡ የቤተ ክርስቲያን በዓላት ከየት ወዴት?

Written by  በዝግጅት ክፍሉ

Overview

መነሻቸውም ሆነ መድረሻቸው የክርስትና ሃይማኖትና አስተምህሮ የሆኑት፤ በተለይም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መገለጫ የሆኑትንና  በምእመኑ ዘንድ በጉጉት የሚጠበቁ በዓላት በዓለማዊ ኮተት እንዲታጀቡ መደረግ ከጀመሩ ሰንብተዋል።  በቤተ ክርስቲያናችን እና በምእመናን ዘንድ ልዩ ትኩረት የሚሰጣቸው የዘመን መለወጫ፣ ገና፣ ጥምቀት እና የትንሣኤ በዓላት ቀደም ሲል የገበያ ማሻሻጫ አሁን አሁን ደግሞ የዘፈን እና የመዝናኛ ማጀቢያ እንዲሆኑ የተፈረደባቸው ይመስላል።   ቀደም ባሉት ዓመታት የዘመን መለወጫ፣ የገና፣ የጥምቀትም ሆኑ የትንሣኤ በዓላት ሲደርሱ በዓላቱን በማስታከክ  በመስቀል የአደባባይ ኤግዚብሽን ማዕከል ይደረግ የነበረው ዝግጅት ገበያ ብቻ እንደነበር ይታወቃል።  በተለይ ገዢና ሻጭ የሚገናኝበት፤ ከወትሮው በተለየ መልኩ ሌላ ጊዜ እና ቦታ ውድ የሆኑ ነገሮች በርካሽ የሚገኙበት  በየቦታው እንደልብ የማይገኙ የምግብ ዓይነቶች እና ልዩ ልዩ ቁሳቁሶች በአንድ ቦታ ለተጠቃሚው የሚቀርቡበትም ነበሩ።  ከላይ እንደተጠቀሰው ገበያው የሚካሄደው በበዓላቱ ስም መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ማለት ነው።  

 

የቤተ ክርስቲያናችን መገለጫ በሆኑት በዓላት ስም እና በበዓላቱ ወቅት የሚከናወኑት እነዚህ የገበያ ዝግጅቶች ባለቤቶች እነማን እንደሆኑ አይታወቁም፤ ቤተ ክርስቲያንም በበዓላቷ ስም የሚነግዱትን አካላት ማንነት ጠይቃ አታውቅም።  የማያምነውም ሆነ አማኙ ክፍል በሚታደምበት በዚህ በዓል ጠበቅ ንግድ ተሳታፊዎቹ ወይም ባለቤቶቹ ኦርቶክሳውያን ይሁኑ የሌላ እምነት ተከታዮች ጠያቂ ኖሮባቸው አያውቅም።  መድረኩ ፈለጊና ተፈላጊን በቀላሉ የሚያገናኝ ነው ተብሎ በአዎንታዊ መልኩ ቢወሰድም እየዋለ ሲያድር ያስከተለው አሉታዊ ተፀዕኖ ግን ቀላል አይደለም።   

በዓላቱ ዛሬ ዛሬ ታላላቅ የሙዚቃ ድግሶች የሚዘጋጅባቸው መድረኮች ሆነዋል።  ከበዓላቱ ስምና ተግባር በተቃራኒ ለዓለማዊ አገልግሎት ሲውሉ ለምን ባይ ጠያቂ የለባቸውም።  ከቤተ ክርስቲያን ውጪ በሆኑ ሰዎች በገበያ የተጀመረው በዓል ተኮር ትዕይንት ወደ  ኮንሰርትነት (የሙዚቃ ድግስነት) ሲቀየር ለምን የሚል ጠያቂ ሊኖር ይገባል።  በዓላቱ የሚከበሩበት የራሳቸው የትመጣና አስተምህሮ እንዳላቸው ገልጦ ፊት ለፊት ማስተማር አስፈላጊ ነው።  በሙዚቃና በዳንኪራ የታጀቡ የቤተ ክርስቲያንንመ አስተምህሮ በሚያጠለሹ መድረኮች ላይም ባለመገኘት ወይም ባለመታደም ክብሯን ማስጠበቅ ከቤተ ክርስቲያን ልጆች ይጠበቃል። 

በእርግጥ አሁን አሁን በገና ፣ በጥምቀትና በትንሣኤ ዋዜማ ላይ የበዓላቱን ስም ታከው የሚከወኑ ልዩ ልዩ ዝግጅቶች በሌሎች የእምነት በዓላት ስምም መዘጋጀት ጀምረዋል።  ነገር ግን እንደ ገና እና ትንሣኤ የሙዚቃ ኮንሰርት ማጀቢያ ሲደረጉ ግን አይታይም።  ይህ የሚያሳየው ለቤተ ክርስቲያን እና ለበዓላቷ አዘጋጆቹ ወይም ባለቤቶቹ ያላቸውን ንቀት ነው።  በሌሎች ሃይማኖቶች በዓላት ላይ የንግድ ባዛር ሲተዋወቅ እና ሲካሄድ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን በዓላት ግን የኮንሰርት(የሙዚቃ ድግስ) ማድመቂያ፣ አዲስ የዘፈን አልበም እና ዘፋኝ ማስታወቂያ ናቸውና ክርስቲያኖች ልብ ልንለው ይገባል። 

ዛሬ በዓላቱን ጠብቀው ዘፈን መልቀቃቸው፣ ኮንሰርት (የሙዚቃ ድግስ) ማዘጋጀታቸው ብቻ አይደለም መታየት ያለበት።  በጊዜ ሂደት ትውልዱ አዲስ ዓመት ሲመጣ ራሱን በንስሐ ከማደስ ይልቅ በዘፈን ስለመታደስ እንዲያስብ እየተደረገ ነው።  ገና ሲመጣ ስለ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መወለድ ሳይሆን ስለሚዝናናበት ኮንሰርት (የሙዚቃ ድግስ) እንዲናፍቅ እየተደረገ ነው።  ጥምቀት ሲመጣ ትውልዱ ስለተከበረው የሰው ልጅ መንፈሳዊ ድኅነት ከማሰብ ይልቅ በዓሉን ጠብቆ አዲስ ስለሚለቀቀው የዘፈን አልበም እንዲያስብ እየተጋበዘ ነው።  የተከበረውን በዓል ሳይሆን በዓሉን ታኮ ስለሚመጣው የሥጋ ደስታ ላይ ዓይኑ እንዲያማትር የልምምድ መድረክ እየተመቻቸ ነውና የቤተ ክርስቲያን ልጅ የሆነው ሁሉ ከዚህ ወጥመድ መሸሽ ተገቢ ነው ሌሎችንም ከወጥመዱ እንዲሸሹ ማድረግ ይኖርበታል። 

የነገውን ጥፋት በጥልቀት አይቶ ከክፉው ጋር ላለመተባበር ከመራቅ ውጪ ቤተ ክርስቲያን በዓላቷን አጉልታ የምታሳይበትን መድረክ መፍጠምር ይጠበቅባታል።  የዘፈን ማድመቂያ የሆኑትን በዓላት ዝማሬ የሚሰማባቸው ሳምንታት በማድረግ ትክክለኛ ገጽታቸውን መመለስ ከእምነቱ ተከታዮች ይጠበቃል።  በዓላቱን የሚገልጹ መንፈሳዊ ነገሮችን ለገበያ በማቅረብ በሰው ልብ ታትመው እንዲቀሩ ሰፊ ሥራ መሥራትም ይኖርበታል።  

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተጀመሩት በቤተ ክርስቲያን አካባቢ ብቻ ተወስነው የሚታዩት ትናንሽ የንግድ እንቅስቃሴዎች በደንብ ተደራጅተው ትልቅ ሥራን ወደ መሥራት እንዲሸጋገሩ ቢደረግ በተለይ በዘፈንና በማስታወቂያ ከሚያደነቁሩት የገበያ ማዕከላት ልጆቿን አውጥታ የበዓላቱን ክብር በምትገልጥባቸው ትምህርትና መንፈሳዊ ዝማሬዎች የደመቁ የገበያ ማዕከላትን በየአጥቢያው ብትከፍት ከላይ ለተዘረዘሩት ችግሮች መፍትሔ ማግኘት ይቻላል ብለን እናምናለን።  በሌላም አገላለጽም በዓላቱን ጠብቀው እና በኅብረት ሆነው ትልቅ መንፈሳዊ ባዛር በማዘጋጀት ከየሰው አእምሮ ሊጠፋ የተዘጋጀውን የቤተ ክርስቲያን ዕሴት በቀላሉ መመለስ ይቻላል፡፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዘማርያን እንዲሁም ሰባክያን በሕብረት በመሆን በኮንሰርት (በሙዚቃ ድግስ) የተወሰደውን ሰው መመለስ ይጠበቅባቸዋል። ኦርቶዶክሳውያን ነጋዴዎች በመተባበር በበዓላቸው ላይ ምርቶቻቸውን ለምእመናን የሚሸጡበትን መድረክ ቢያመቻቹ ራሳቸውን ብሎም የምእመኑን ሥጋዊና መንፈሳዊ ሕይወት መጥቀም ጭምር ነው።  

የቤተ ክርስቲያንን በዓላት ጠብቀው የሚዘጋጁ ኢ-ክርስቲያናዊ ተግባራት በቀጣይ ወዴት ሊያመሩ እንደሚችሉ መገመት አያዳግትም።  ከኤግዚቢሽን ማዕከል ወደ ሆቴሎች የተዛመተው በበዓላት ስም የሚዘጋጀው የመሙዚቃ ኮንሰርት ቀስ በቀስ በግለሰቦች ስም ላለመዘጋጀቱ ምን ዋስትና አለ? የእስከዛሬው የሚያሳየን ይህን ነውና።  ‹‹ሳይቃጠል በቅጠል›› እንዲሉ ነገ ከፍቶ የሚመጣውን ዛሬ ላይ በመቅጨት ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን የነገ ክብር እና ህልውና ዛሬ ላይ አጥብቀን እንሥራ እንላለን።

Read 655 times