Tuesday, 23 February 2021 00:00

ዓላማውን የሳተው የዐውደ ምሕረት ስብከታችን

Written by  በጋዜጣው ሪፖርተር

Overview

ሠርክ ቃለ እግዚአብሔርን የምንሰማባቸው የቤተ ክርስቲያን ዐውደ ምሕረቶች እንደሰባክያኑ መልካቸው የተለያየ ነው።  ምእመናን ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚሄዱት ቃለ እግዚአብሔርን ሰምተው ሊታነፁበት፣ ወደ ንስሓ ሊመለሱበት ፣ ባጠቃላይ የጽድቅ ሥራ ሊሠሩበት ነው።  ዛሬ ዛሬ በየዐውደ ምሕረቶቻችን የምንሰማቸው አንዳንድ ስብከቶች ዓላማቸውን የሳቱ፣ በግለሰብ ፍላጎት እና ሓሳብ ላይ የተመሠረቱ ሆነዋል።  በተከበረው የእግዚአብሔር ዐውደ ምሕረት ወንጌል መሰበክ ሲገባው ስለኳስ ጨዋታ፣ ስለሰባኪው የግል ዝንባሌና ምኞት፣ስለ ዘረኝነት ፣ ስለ ወቅቱ የሀገሪቱ የፖለቲካ ትኩሳት እንዲሁም ገንዘብ መሰብሰብ ላይ ያተኮረ መልእክት ማስተላለፍ የተለመደ ሆኗል።  ከላይ ባነሳናቸው ሐሳቦች ዙሪያ ትኩረት የሚያደርጉ ምእመናንን ፍጹም የማያንፁ፣ በዓለማዊ ቋንቋና ሐሳብ የተሞሉ ፍጹም ግለሰባዊ ስብከቶች ከየዐውደ ምሕረቱ ሲሰሙ ሃይ የሚላቸውና ስሕተት ነው ባይ የላቸውም።   በአበይት በዓላት፣ በሠርክ ጉባኤና፣ በቅዳሴ ሰዓት የሚሰጡ ስብከቶችን ለመስማት የሚታደሙ ምእመናንም እንዲህ ዓይነት ከዓላማው የተፋታ ስብከት ሲሰሙ ለምን አይሉም።  ነገሩን በውል ተረድተው ልክ አለመሆኑን ቢያውቁም በአብዛኛው ሰምተው እንዳልሰሙ፣ አይተው እንዳላዩ ወይም በይሉኝታና በፍርሃት ተይዘው እግዚአብሔርንም እንደመዳፈር ቆጥረውት ዝም ይላሉ።  ግን እስከመቼ? ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ስብከቱ በመንግሥተ ሰማያት፣ በዘር ፣ በእርሾ እየመሰለ ማስተማሩን መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል።   ዛሬ ዛሬ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ሊቃውንት በተቀመጡበት ዐውደ ምሕረት በእነርሱ ፊት ወጥቶ የሚሰብከው ሰባኪ ከምእመኑ ጋር የማይገናኝ የምእመኑን ዕድሜ፣ የትምህርትና የኑሮ  ደረጃዎች ፣ጾታንና የመሳሰሉትን ሁኔታዎች ያላገናዘበ ትምህርት ሲሰጥ ዝም ሊባል አይገባም።  ምእመኑም የእግዚአብሔር ቤት ነው ብሎ አክብሮ የሚነገረውን ሰምቶ መሄዱ እንደተማረ ተቆጥሮ መታለፍ የለበትም።  ምክንያቱም እንዲህ ዓይነት ስብከቶችን በክርስትናው ባልተለወጡ ምእመናን ሕይወት እያየነው ስለሆነ ነው።  በተከበረው የእግዚአብሔር ዐውደ ምሕረት ላይ ወጥቶ ከምእመናን ልብ የማይደርስ ስብከት ሲሰጥ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ዝም ሊሉ አይገባም።  የጉባኤው ተካፋይ ምእመንም ቢሆን እንዲህ ዓይነት ክፍተቶች ሲያይ ዝም ከማለት ወደ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደር አለዚያም ወደ ስብከተ ወንጌል ኃላፊዎች ቀርቦ እንዲስተካከል ማድረግ ይጠበቅበታል።   አንዳንዱ ሰባኪ እንደ ተከበረው የእግዚአብሔር ቤት ዐደባባይ ሳይሆን እንደራሱ ቤት በሚቆጥረው መድረክ ላይ የመጽሐፍ ቅዱሱን ቃል ሳይሆን የራሱን ሐሳብ ብቻ ተናግሮ  ይወርዳል።  ምእመኑ ዘንድ ስለሚደርሰው የእግዚአብሔር ቃል ሳይሆን እርሱ በዚያች ሰዓት ስለሚያስተላልፈው ሐሳብ ብቻ ተጨንቆና ተጠቦ በመምጣት ያንኑ አስተላልፎ ሲወርድ ልክ አይደለህም ሊባል ይገባል።  እንዲህ ዓይነቱ ሰባኪ ሲያጠፋ ስላልተነገረው ብቻ ራሱን ትክክል አድርጎ በየሄደበት ዐውደ ምሕረት ከምእመናን ሕይወት ያልተገናኘ ስብከት ሲሰብክ ይኖራል።  በተሳሳተበት ቀንና ቦታ ስላልተነገረውም ከመንገድ የወጣ ትምህርቱ ሥር እየሰደደ ይሄድና ለመመለስ ይቸግራል።  ‹‹ ሳይቃጠል በቅጠል›› እንዲሉ አባቶች ገና ከመነሻው ያልተነገረ ጥፋት በአድራጊው ዘንድ እንደ ትክክል ይቆጠራልና ሰባኪውም ሆነ ምእመኑን ወደ ፍጹም ስሕተት  ሳይገቡ እርምት ሊሰጥ ይገባል።  የዐውደ ምሕረቱ አስተባባሪ ወይም ፕሮግራም መሪ ‹‹እከሌ የተባሉት መምህር አሁን ያስተምሩናል›› ብሎ ለወንጌል ትምህርት የተፈቀደለትን መድረክ ተጠቅሞ እግዚአብሔርን ሳይሆን ራሱን የሚያስተዋውቀውን፣ቃለ ወንጌልን ሳይሆን ይዞት የመጣውን መጽሐፍ ወይም ሲዲ አስተዋውቆና በረከት የሚገኘው ከመጽሐፉና ከሲዲው ነው በማለት የወንጌሉን ቃል ወደ ጎን ሲተው ሃይ ባይ የሚገሥፅ ያስፈልጋል።  ዐውደ ምሕረቱ ለቃለ ወንጌሉ ነው በማለት ከስሕተቱ እንዲታረም ማድረግ ካልተቻለ ‹‹ቤቴን የንግድ ቤት አደረጋችሁት . . . ›› እንዳለው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዐውደ ምሕረቱ ወደ ንግድ ማዕከልነት ሳይለወጥ በጊዜ መላ ሊበጅለት ይገባል።    ትናንት ያየውን ዜናና ዓለማዊ ፊልም ለስብከቱ ማዳመቂያ አድርጎ መድረክ ላይ የሚወጣውም ሰባኪ መንፈሳዊ ዕውቀትን ለመገብየት የመጣውን ምእመን ስላየው ዜናና ፊልም ዳግም እየነገረ የቤተ ክርስቲያንን ክብር ስለሚያዋርደው ሰባኪ አንድ ነገር ሊባል ይገባል።  በዐውደ ምሕረቱ ያልተለመደ ፌዝና ስላቅ እያስተላለፈ ምእመኑን ‹‹ይሄ ነው ትክክለኛው›› እንዲሉ መንገድ የሚጠርገውን ሰባኪ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ከዐውደ ምሕረቷ ዘወር ልታደርገው ይገባታል።  የቤተ ክርስቲያን ልጆችም ቢሆኑ እንዲህ ዓይነት ቀልድና ፌዝ ከቃሉ ጋር ተቀላቅለው ሲነገሩ፤ ዓለምን ከነኮተቷ ወደ ቤተ ክርስቲያን ቅጽር ሊያስገቡ ሲሞክሩ ‹‹ይህ የአባቶቻችን ትምህርት አይደለም›› በማለት ለቤተ ክርስቲያናቸው ክብር ሊቆረቆሩ ይገባል።   ቃለ እግዚአብሔርን ለመስማት ፣ መንፈሳዊ ዕውቀቱን ለማሳደግ በቤተ ክርስቲያን ቅጽር ውስጥ ለተሰበሰበ ምእመን የተነሣበትን ርእሰ ጉዳይ ትቶ ከርእሱ ወጥቶ ወይም የሆነው ያልሆነውን ሲዘባርቅ የዕለቱንም በዓል አስመልክቶ አንድም ሳያስተምር የጉባኤውን ሰዓት የሚጨርስ ራሱን እንዲያስተካክል መንገር ከቤተ ክርስቲያን አባቶችም ሆነ ከምእመናን ይጠበቃል።  ጊዜውን ተጠቅሞ ለምእመኑ ማስተላለፍ ያለበትን መንፈሳዊ መልእክት ሳያስተልልፍ ፤ ምእመኑን መጀመሪያ ላይ የሰማው ርዕሰ ጉዳይ እስኪጠፋበት እና አንድም ፍሬ ነገር የማያገኝበትን እንቶ ፈንቶ ሲያወራ ቆይቶ ከመድረክ ላይ የሚወርደውን ሰባኪ ተብዬ ‹‹ ቃለ ሕይወት ያሰማልን›› ማለት ሳይሆን ከሕስተቱ ተምሮ እንዴት ማስተማር እንዳለበት አቅጣጫ መስጠት ተገቢ ነው።    ታላላቅ በዓላት በሚከበሩባቸው አብያተ ክርስቲያናት ዐውደ ምሕረት ላይ ምእመኑን ‹‹ ዕልል በሉ፤ አጨብጭቡ›› ከማለት ያለፈ ስለ ዕለቱ አንድም ነገር ሳይናገሩ ከመድረኩ ለሚወርዱ ሰባኪዎቻችን አስቀድሞ ርእስ እና አቅጣጫ መስጠት ተገቢም ነው።  የዕለቱን ክብረ በዓል ምንነት ለምእመናን ከማስተማር ይልቅ ገንዘብ ስለመለመን ብቻ አውርተው የሚወርዱ ሰባኪዎቻችን በምእመኑ አንደበት ሳይቀር ‹‹ ምን እነሱ ብር መለመን ብቻ ነው›› እስከመባል ደርሰዋልና ቤተ ክርስቲያን ይህን ልታስብበት ይገባል።    የቤተ ክርስቲያን አምባሳደር ሆነው በቆሙበት መድረክ ላይ የወንጌልን ቃል ሳይሆን ዘረኝነትን የሚዘሩ፤ ዘለዓለማዊ የሆነውን የእግዚአብሔር ቃል ከማስተላለፍ ይልቅ ሰሞነኛ የፖለቲካ ትኩሳት ማቀንቀን የሚቀናቸው ሰባክያንን ‹‹ቦታው እዚህ አይደለም›› በማለት ወደ ትክክለኛው መሥመር እንዲገቡ ማድረግ ከቤተ ክርስቲያን ልጆች ይጠበቃል።  ሞልቶ ከተረፈው የእግዚአብሔር ቃል ይልቅ ከዓለም በቃረሙት ቃላትና ምሳሌ ወደ ዐውደ ምሕረት አምጥተው ምእመናንን የሚያደነቁሩ ሰባክያን ልክ አይደለም ሊባሉ ይገባል።  ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የአለባበስ ሥርዓት በመጣስ ያልተፈቀደላቸውንና የማይገባቸውን የቤተ ክርስቲያን ልብስ በመልበስ ወደ መድረክ ብቅ የሚሉ ሰባኪዎቻችንን ቤተ ክርስቲያን ችላ ልትላቸው አይገባም።   ዐውደ ምሕረቱን ተጠቅመው የእግዚአብሔርን ቃል የሚሸቃቅጡትን፤ ‹‹ በነፃ የተሰጣችሁን በነፃ ስጡ ›› የሚለውን ቃል ዘንግተው ኪሳቸውን ለመሙላት ብቻ የምእመኑን ኪስ የሚያራግፉትን (ዋጋ ተምነው ይህን ያህል ሊከፈለኝ ይገባል በማለት በድርድር ዐውደ ምሕረት ላይ የሚቆሙ) ሰባክያን ቤተ ክርስቲያን ለይታ ልታወጣቸው ይገባል።  በዚያው ልክ ለቤተ ክርስቲያን ክብር የቆሙ ጨዋ የወንጌል ሰባክያንን (ቤተ ክርስቲያን የሊቃውንት ደሃ አይደለችምና) ወደ መድረክ ልታመጣ ፣ ልትጋብዝ፣ እንዲያስተምሩ ልታደርግም ይገባል።  ባጠቃላይ ምእመኑ ጥሎት የመጣውን ዓለም በቤተ ክርስቲያን ዐውደ ምሕረት ላይ በድፍረት የሚያስተዋውቁ የወንጌል ነጋዴዎች ቤተ ክርስቲያንንም ሆነ ምእመኑን እየጎዱ ነውና ቤተ ክርስቲያን ዐውደ ምሕረቷን  በትኩረት ልታየው ይገባል።
Read 648 times