Saturday, 26 June 2021 00:00

ከመግለጫው ባሻገር ሥራ መሥራት ይጠበቃል

Written by  በዝግጅት ክፍሉ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በተለያዩ ተግዳሮቶች ውስጥ እያለፈች ትገኛለች። በሀገራችን ኢትዮጵያ የብዙ ዘመናት ታሪክ ውስጥ ቅድምና ያላት እንዲሁም በአገልግሎት ተደራሽነቷ የአንበሳውን ድርሻ የምትወስደው ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በሰፊው አገልግሎቷ ውስጥ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ሲፈራረቁበት ቆይታለች። ራሱን የቻለ ሀገር በሆነው አገልግሎቷ ውስጥ ሰው ሠራሽ እና ተፈጥሯዊ ችግሮችን እያሳለፈች  ዛሬ ላይ ደርሳለች። በሀገር ውስጥ ትልቁን የባለቤትነት ድርሻ ይዛ የነበረችው ታላቋና ስመ ገናናዋ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በዘመናት ሂደት ውስጥ ከዚህ ትልቅ ክብር ስትገፋና እንድትርቅ ስትደረግ ቆይታለች። የነበራት መልካም ስምና ዝና ሆን ተብሎ በተለያዩ ምክንያቶች እንዲጠለሽ ሲደርግ ቆይቷል። ሀገር ናት የተባለላት ደግሞም በእውነት ሀገር የሆነች ቤተ ክርስቲያን በክልል ብሎም በመንደር እንድትወሰን ተደርጋለች። ቀስ በቀስ ሥር እየሰደደ የመጣው የጎሰኝነት በሽታ ደግሞ እንደ ሰደድ እሳት ተቀጣጥሎ ዛሬ እየደረሰባት ላለው ችግር ዳርጓት ይገኛል።   

 

በሀገርነቷ የምታካሂደው ዓለማቀፋዊ አገልግሎቷ ተዘንግቶ ወደ መንደርነት  ተገፍታ በሰፈር ስትታጠር፤ ከዘርና ከነገድ ውጪ ሆና ሐዋርያዊ አገልግሎት የምትሰጠው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በአንድ የብሔር ቅርጫት ውስጥ ስትወረወር፣‹‹ከዚህ ክልል ከዚህ አካባቢ ድርሻ የላትም፤ የእነ እከሌ ዘር ሃይማኖት ናት›› ተብላ ስትገፋ በየዘመናቱ በሚለኮሱ የዘረኝነትና የጎጠኝነት ወላፈኖች ስትለበለብ ኖራለች። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ደግሞ ቤተ ክርስቲያን ከዚህ ክልል ትውጣ ስትባል እየሰማን ነው። ዓለማቀፍ ሐዋርያዊ አገልግሎቷ በክልል ከዚያም እጅግ ወርዶ በመንደር እንዲወሰን ሲሠራ ዛሬም እያየን ነው። ከዋናው የወንጌል አገልግሎት ተልእኮዋ ወጥታ ይህን ዓይነቱን በሽታ እንድታስታምም እየተደረገች ነው። 

በመንግሥታት የለውጥ ሂደት ውስጥ መጥፎ ስም እየተሰጣት ለአንዱ ወዳጅ ለሌላው  ጠላት ስትደረግ ቆይታለች። ሀገርን እንደ ሀገር ያቆመች፣ የሀገር ታሪክ ባለቤት፣ የሀገር ዋርካ የሆነች ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሀገርነቷን ለማሳነስ፣ የታሪክ ባለቤትነትዋን ለማጥፋት፣ ከሁሉ ከፍ ብሎ የሚታይ ዋርካነቷን ከሥር ገዝግዞ ለመጣል፣ ከግለሰብ እስከ መንግሥታት ፣ ከትንሽ እስከ ትልቅ ብዙ ጠንካራ መዳፎች ተሰንዝረውባታል። የጀመረችውን ክርስቲያናዊ አገልግሎት ለመምእመናን ለማድረስ በሆደ ሰፊነት ለመጓዝ ብትሞክርም በየዘመናቱ መልካቸውን እየለዋወጡ ከፊቷ የሚደቀኑ እንቅፋቶቿ ከፊት እየተጋረጡ ርምጃዋን እየገቱት ይገኛሉ። 

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ባጠቃላይ ሐዋርያዊ አገልግሎቷን የሚያቀጭጩ ፣ ወደ ፊት አንድ ስትራመድ ወደ ኋላ ሁለት ርምጃ የሚጎትቷትን ውስጣዊና ውጫዊ ተጽዕኖዎችን አሳልፋለች። የጎጠኝነት ካባ የሚደርቡላት፣ የፖለቲካ ታርጋ የሚለጥፉላት ፣ እምነቷ እንዲበረዝ የምንፍቅና መርዝ የሚረጩባት፣ ሀብት ንብረትዋን ለመንጠቅ ቀን ከሌት የሚተጉ ብዙዎች ናቸው። ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በእነዚህ ሁሉ ተግዳሮቶች ውስጥ ቆማ ስለ አስተምህሮዋ መበረዝ፣ስለ ሥርዓቷ መጣስ ፣ ስለ ክብርዋ መደፈር፣ ስለ መብትዋ መነጠቅ ስትጮህ ኖራለች ዛሬም እየጮኸች ነው። ሆኖም ግን ጩኸቱ  ለውጥ የሚያመጣና መከራዋን ሊያስታግሥላት የሚችል  ጩኸት መሆን አለበት።

ቅደስት ቤተ ክርስቲያን ትላንት ባለፈችበት መከራ ውስጥ ዛሬም ሆነ ነገ ማለፍ የለባትም። ባለፉት ዘመናት የደረሰባሰትን ዘርፈ ብዙ በደል በዝምታ ማለፏ ዛሬ ደግሞ ከዚያ በከፋ መከራ ውስጥ እንድትወድቅ እያደረጋት ነው። ስለሆነም ቤተ ክርስቲያንን ከዚህ በዘመናት ከተፈራረቀባት ጽኑ መከራ ውስጥ እንድትወጣ ለማድረግ ከቃል ያለፈ ሥራን መሥራት ወቅቱ የሚጠይቀው ጉዳይ ነው። ከዚህም የተነሣ ጉዳዩ የአንድ ሰሞን ጩኸት፣ የአንድ ሰሞን መግለጫ፣ የአንድ ሰሞን ሰላማዊ ሰልፍ መሆን የለበትም። ይልቁንም ሥር ነቀል ለውጥ በሚመጣበት መልኩ ሳይቋረጥ የሚሠራበትና ጠንካራ መሠረት የሚጣልበት መሆን ያለበት።

ለዚህ ደግሞ ቅድስት ቤተ ክርስቲን ትላንት የነበራትን ልዕልና ዛሬ ላይ እንዴት ልታጣ ቻለች? የሚለውን ጥያቄ ከግንዛቤ በማስገባት ቤተ ክርስቲያንን ለማዳከም ከስም ማጥፋት ጀምሮ እንድትከፋፈልና የነበራትን የገናናነት ኃይልና ጉልበት እንድታጣ የተደረገባትን የዘመናት ሰንኮፍ በመንቀል፣ ጠላት ያስቀመጠውን የፀረ ኦርቶዶክሳዊነት ወጥመድም በመበጣጠስ በጥንቃቄ ማለፍና ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሥርዓትና ትውፊቷን ከነቅርሶቿ ለተተኪ ትውልድ ማሻገር በሚቻል መልኩ ጠንክሮ መሥራት በእኛ ዘመን ካለው ኦርቶዶክሳዊ ትውልድ የሚጠበቅ ታላቅ ኃላፊነት ነው። ቤተ ክርስቲያን ያጣችውን ሁሉ መልሳ ታገኝ ዘንድ፣ ነገንም ያለ ችግር ወደፊት መራመድ ትችል ዘንድ ከመመሪያና ከመግለጫ፣ ከአንድ ሰሞንም ሰላማዊ ሰልፍ በዘለለ መሬት የወረደ እና ኦርቶዶክሳዊ ኅብረት ያለበት ሥራን ተቀናጅቶ መሥራት የግድ አስፈላጊ ነው። ለዚህ ተግባራዊነት ዕለት ዕለት የሚተጋ ተቋማዊ አሠራርን መዘርጋትም ከቤተ ክህነቱ መዋቅር የሚጠበቅ ነውና ይህም ትኩረት ተሰጥቶት ሊሠራ ይገባል።

ከቤተ ክርስቲያን ልጆች የሚጠበቀው እየተሰደደች ያለችውን ቤተ ክርስቲያን ዳግም በማትሰደድበት መልኩ መሥራት፣ ለደረሰባት ግፍና በደል ያቀረበቻቸው የመብት ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ እንድያገኙ ተግቶ መሠራት ነው። ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ትላንት በደረሰባት መከራ ከተወጣው ሰላማዊ ሰልፍና ከተሰጠው  መግለጫ ባሻገር በመግለጫው እና ሰላማዊ ሰልፉ የቤተ ክርስቲያንን ልዕልና ስለሚጋፋ ፀረ ኦርቶዶክሳዊ ተግባራትና እንቅስቃሴዎች የቀረበው የመብት ጥያቄና ተቃውሞ ምን ያህል አዎንታዊ ተፅዕኖ መፍጠር  የሚለውን በትኩረት መመልከት ይገባል። ይህም ተፅዕኖ ምናልባት ኦርቶዶክሳውያኑ ስለ ቤተ ክርስቲያናቸው ልዕልናና ስለ ሃይማኖታዊ መብቶቻቸው መሞገትና አወንታዊ ተፅዕኖ መፍጠር እንዳይችሉ ያደረጓቸውን መሠረታዊ ችግሮች በውል ለመረዳትና አቋምን ለማስተካከል ይረዳል። ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ አባቶቻችን በተለያዩ ጊዜያት ለሚያወጧቸው መግለጫዎችና ለሚሰጧቸው አባታዊ ማሳሰቢያዎች ሁላችንም የቤተ ክርስቲያን ልጆች እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ እንደ አንድ ልብ መካሪ በመሆን ልንሠራ ይገባል።

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ትላንት የቆሰለችው ዛሬ ይሽር ዘንድ፣ ከትላንት መሰደዷ ዛሬ ታርፍ ዘንድ፣ የትላንት መገፋቷ ዛሬ ላይ ይቆም ዘንድ ሁሉም የቤተ ክርስቲያን ልጅ የድርሻውን ሊወጣ ይገባል። እስከዛሬ ከሆነብን ሁሉ በባሰ መልኩ ዋጋን እንዳንከፍል ስለቤተ ክርስቲያናችን ጊዜ ሰጥተን መነጋገር፣ ከዚያም ባሻገር አጥብቀን ለጠየቅናቸው የመብት ጥያቄዎች እንዲሁም በየጊዜው ለወጡት መግለጫዎች እና ማሳሰቢያዎች መሬት የወረደ እና በተግባር ላይ የዋለ መልስ በሚገኝበት ነገር ላይ በትጋትና በጽኑ አንድነት መሥራት ተገቢ ነው እንላለን።  

 

Read 550 times