Thursday, 08 April 2021 00:00

በመጪው ሀገራዊ ምርጫ የምእመናን ተሳትፎ

Written by  በጋዜጣው ሪፖርተር
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ  ክርስቲያን ሀገርን በሚመለከት ማንኛውም ጉዳይ ላይ ዘርፈ ብዙ አገልግሎት ስትሰጥ ቆይታለች። ተደጋግሞ እንደሚጠቀሰው የትምህርት ሚኒስቴር፣ የገንዘብ ሚኒስቴር የማስታወቂያ ሚንስቴር፣ የመንፈሳዊ ፍርድ ቤት ሆና ሀገርን እና ሕዝብን ስታገለግል ኖራለች። ኦርቶዶክሳውያን ልጆቿም ከቤተ መንግሥት ጀምሮ እስከታችኛው የአስተዳደር መዋቅር ድረስ በሀገራችን በተለያዩ መሥሪያ ቤቶች ውስጥ በከፍተኛ ኃላፊነት፣ በአማካሪነት እንዲሁም በዲፕሎማትነት ሲያገለግሉ ኖረዋል። እነዚህ ሁሉ ቤተ ክርስቲያን በሀገር ላይ ለነበራት ከፍተኛ ሥፍራ እና ተሰሚነት ማሳያዎች ናቸው። በሀገራችን ውስጥ የሚገኙ ተቋማትም ሆኑ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች የኋላ ታሪካቸው ሲታይ የቤተ ክርስቲያን አሻራ ያረፈባቸው ናቸው። በእምነት ተከታዮቿ ብዛት የሀገራችን ሕዝብ ከግማሽ በላይ የሚሸፍን ምእመን ያላት ክርስቶሳዊት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ታላቅ ክብርና  ተሰሚነት የነበራት፣ ታላቅ ቦታም የሚሰጣት  ተቋም ነበረች። እንደዛሬው ሳይሆን በዚህ ወቅት በታላቁ የጾመ ሁዳዴ የመገናኛ ብዙኃኑ ሳይቀር ስለመንፈሳዊ ነገር የሚሰብኩ፣ በዘፈን ፈንታ የበገና መዝሙር የሚሰማባቸው ነበሩ። 

 

የዘውዳዊው ሥርዓት ሰፍኖ እስከቆየበት እስከ ፲፱፻፷፯ ዓ.ም ድረስ ቤተ ክርስቲያን በሀገሪቱ ውስጥ ሢሶ መንግሥት ነበራት፤ ንግሥናውም ተዋረዳዊ (ሰሎሞናዊው ሥርዓተ መንግሥት) በመሆኑ ነገሥታቱን በቅብዐ መንግሥት የምታነግሥው እንዲሁም ለንግሥናው ቡራኬ የምትሰጠው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ነበረች። በአጠቃላይ በሀገር የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴ ውስጥ ቤተ ክርስቲያን ነበረችበት። በቤተ ክርስቲያን በሚደረጉ ታላላቅ ክብረ በዓላት ላይ ሁልጊዜ ነገሥታቱ ከቅዱስ ፓትርያርኩና ከሊቃነ ጳጳሳቱ ጎን ነበሩ። ፓትርያርኩና ሊቃነ ጳጳሳቱም በተመሳሳይ በቤተ መንግሥቱ በነበሩ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የነበራቸው ንቁ የአብሮነት ተሳትፎ እንደዚያው ነበር። 

በእነዚያ ዘመናት ቤተ ክርስቲያን በአንጻራዊነት ለራስዋ አስተዳደራዊ አገልግሎት የምትጠቀምባቸው የእርሻ መሬቶች ነበሯት። በዚህም መሠረት ሌሎች አዳዲስ አብያተ ክርስቲያናትን ለመትከልም ሆነ መንፈሳዊ አገልግሎትን ለመፈጸም ብዙ ችግር አልነበረባትም። ምክንያቱም ነገሥታቱ ራሳቸው የቤተ ክርስቲያንን ሥርዓት የማይጋፉ ክብርና መብትዋንም አስጠብቀው የሚሠሩ ስለነበሩ ተሰሚነትዋ ከፍ ያለ ነበር። በ፲፱፻፷፯ ዓ.ም የዘውዳዊውን ሥርዓት መንበረ ሥልጣን በኃይል የነጠቀው የደርግ መንግሥት ሥልጣኑን ሲረከብ የቤተ ክርስቲያን ዕጣ ፈንታና ክብር ከዘወዳዊው ሥርዓት ጋር አብሮ ወደቀ። በውጭ ወራሪ ሳይሆን በሀገር ልጆች ፓትርያርኳን በሞት ተነጠቀች። አድሃሪ ናት ተብላ የምትተዳደርበት ንብረት ሳይቀር እንዲወረስ ሲደረግ ወደ ድህነት አሽቆልቁላ በዐውደ ምሕረቷ ላይ ቆማ እንድትለምን ተገደደች። እስከ ዛሬም ጠባሳው አልጠፋም።

ደርግ ወድቆ የኢሕአዴግ መንግሥት ቦታውን ቢይዝም የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ከድጡ ወደ ማጡ ሆነ እንጂ የተሻለ ነገር አልታየበትም። ቤተ ክርስቲያን በዘመናት ውስጥ ስትገፋ፣ ያላትን ሁሉ ስትነጠቅ፣ ስታጣ ኖራለች። ለዚህ ሁሉ ዓይነተኛው ምክንያት በሀገሪቱ ውስጥ ባሉ ታላላቅ ተቋማት የሚቆረቆርላት፣ ለምን ብሎ የሚጠይቅላት፣ የተበላሸውን የሚያስተካክልላት ሰው አለመኖሩ ነው። በሌሎች እምነቶች ዘንድ በዓላማ የሚገባባቸው የተለያዩ ፖለቲካ ቀመስ ሀገራዊ ተቋማት በቤተ ክርስቲያን ልጆች ግን የሚፈሩና ‹‹ፖለቲካን በሩቁ›› ተብለው የሚራቁ መሆናቸው ነው። ገፍተው የሄዱት እና በከፍተኛ የሥልጣን እርከን ላይ ያሉ የቤተ ክርስቲያን ልጆችም ቢሆኑ ለተቀመጡበት ወንበር ከማገልገል ውጪ እንደ ቤተ ክርስቲያን ልጅነታቸው ጎን ለጎን የቤተ ክርስቲያንን ክብር ለማስጠበቅ አልታደሉም። ብዙዎቹ ሥልጣን በክርስትናቸው ላይ አጥልቶባቸው ተሸፍነው ቀርተዋል፤ ሰማያዊውን ሳይሆን ምድራዊውን ብቻ ሲያገለግሉ ኖረዋል።  

በዘመነ ኢሕዴግ ተጠናክሮ በመጣው የምርጫ ሥርዓት ላይ ለመሳተፍም የቤተ ክርስቲያን ልጆች ቸልተኝነትን ማሳየታቸው ዛሬ ዋጋ እያስከፈለን ይገኛል። ሀገር የሁሉም፤ ሁሉም በእኩልነት የሚኖርባት እንዲሁም ሁሉም በእኩልነት የሚመራት መሆኑ እሙን ቢሆንም ድርሻችንን አሳልፈን መስጠታችን የበይ ተመልካች ብቻ ሳይሆን ነፃነታችንን አሳልፈን እንድሰጥ አድርጎናል። እኛ የጣልነውን መብት ሌሎች አንሥተው ራሳቸውን ሲጠቅሙበት እኛንም ሲጎዱበት ለምን ብሎ መጠየቅ ከእያንዳንዱ ክርስቲያን ይጠበቃል። ‹‹ሀገር ናት›› የተባለች ኦርቶዶክስ ሀገር አልባ ሆና በብዙ ስትገፋ ሀገር መሆንዋን የሚያሳዩ ብርቱ ልጆች ሊሆኑ ይገባ ነበር። ዛሬ ግን ከመቼውም ይልቅ  ወቅቱ የሚጠይቀው ጉዳይ ራስን በሁሉም ሀገራዊ ጉዳዮች ተሳታፊ ማድረግ ነው። 

ነገ እና ከነገ ወዲያ ቅድስት የሌቦችና የወንበዴዎች የግፈኞችም መናኸሪያ ሳትሆን በቀደመ ክብርዋና ልዕልናዋ የኦርቶዶክሳውያን ቤት ሆና እንድትቀጥል ዛሬ ላይ ልጆቿ ተግተው ሊሠሩ ይገባል። የትላንቱ ቸልተኝነት ዛሬ ቤተ ክርስቲያን ስጥቃጠል፣ ስትዋረድ፣ ስትሰደድ ቆመን እንድናይ እያደረገን  ነውና ልብ ብለን የነገ የቤት ሥራችንን ልንሠራ ይገባል። ትላንት ደፍረው ወደ ፖለቲካው መድረክ የመጡ የቤተ ክርስቲያን ልጆች ሲገፉ፣ ሲዘበትባቸው ‹‹ክርስቲያንና ፖለቲካ›› በሚል ሽፋን በፍርሃት እንዲኖሩ መደረጋቸው ወደዚያም የሚገባ ኦርቶዶክሳዊ አማኝ  እንዳይኖር፤ የገቡትም ሐሜትና ስድብን ሽሽት ከቤተ ክርስቲያን እንዲርቁ እንቅፋት ሆኖ ዘልቋልና ትናንትን ላለመድገም ዛሬ ላይ ልጆቿ ጠንክረው መሥራት ይጠበቅባቸዋል።

ሀገርም ሆነች ቤተ ክርስቲያን የሁላችን ናትና ነገ በጠንካራ መሠረት ላይ የቆመች የማትነቃነቅ እንድትሆን የድርሻችንን ልንወጣ ይገባል። ሀገር ከፍ ብላ እንድትታይ በውስጧ የሚኖሩ ሁሉም ዜጎች መብቶቻቸው ይከበሩላቸው ዘንድ አጥብቆ የሚሠራ እንዲሁም የተሻለ ርዕዮተ ዓለም ያለውን የፖለቲካ ድርጅት መምረጥ ችላ የማይባል ትልቅ ጉዳይ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ሀገርን ለመምራት ራስን ማዘጋጀት፤ ቤተ ክርስቲያንን ከተጋረጠባት ፈተና ለመታደግ፤ እንዲሁም በፈረሰው በኩል ለመቆም ራስን ለዕጩነት ማቅረብ፣ ለዚያ መዘጋጀት ሁለት አፍ ያለው ሰይፍ መሆን ነውና በእጅጉ ሊታሰብበት ይገባል።

ሀገር የእነ እገሌ ብቻ ሳትሆን የኛም ናት በሚል የተቆርቋሪነት ስሜት ነገን ዛሬ መሥራት ከእኛ ከክርስቲያኖች የሚጠበቅ ነው። ቤተ ክርስቲያን እና ልጆቿ ሀገርን ጠብቀው ማቆየታቸውን የትላንት ብቻ ታሪክ አድርጎ ማለፍ አይገባም። ነገን በተሻለ ለመሥራት ዕድሉ ዛሬ በእጃችን ነውና ልንጠቀምበት ይገባል። መመረጥም ሆነ መምረጥ ለሌሎች የምንተወው ጉዳይ ሳይሆን ጠበቅ አድርገን ልንይዘው የሚገባ  ነውና ለዚያ መዘጋጀት ተገቢ ነው እንላለን።

 

Read 448 times