Friday, 04 December 2020 00:00

ጾመ ነቢያት

Written by  ዲ/ን ዮሐንስ ጌታቸው
በኢትዮያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ መሠረት ሰባት የአዋጅ አጽዋማት አሉ። እነዚህን የአዋጅ አጽዋማት በተመለከተ ፍትሐ ነገሥት (ፍትሕ መንፈሳዊ) አንቀጽ ፲፭፥፭፻፷፬ ጀምሮ ተጽፏል። በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ ፲፭፥፭፻፷፰ “ከልደት አስቀድሞ የሚጾም ጾም ነው፡ መጀመርያው የኅዳር እኩሌታ፡ ፋሲካው፡ የልደት በዓል ነው።” ተብሎ የጾመ ነቢያት መነሻውና መድረሻው ተገልጿል። ይህ ማለት በሦስቱ ወንጌላውያን ማለትም በዘመነ ማቴዎስ፣ በዘመነ ማርቆስና በዘመነ ሉቃስ ከኅዳር ፲፭ ጀምሮ  ኅዳር ፳፱ የሚፈሰክ ሲሆን በዘመነ ዮሐንስ ደግሞ መነሻው ያው ከኅዳር ፲፭  ጀምሮ ይሆንና ኃዳር ፳፰ ቀን የሚፈሰክ ይሆናል ማለት ነው።     ጾመ ነቢያት በሌሎቹ ኦርቶዶክሳውያን አብያተ ክርስቲያናትም ሆነ በተለምዶ ካቶሊክ እያልን በምንጠራቸው ዘንድ የታወቀ ነው። እኛ ጾመ ነቢያት የምንለውን ሌሎቹ የልደት ጾም (The Nativity Fast) በማለት ይጠሩታል። ይህ ጾም የሚጾምበት ዋና ምክንያት የክርስቶስን ልደት ለመቀበልና ነቢያት አስቀድመው ልደቱን በመመኘት የጾሙትን ጾም ለማስታወስም ነው። ይህን ጾም የግብፅ ቤተ ክርስቲያን የምጽዓት ጾም (The Advent Fast) በማለት ትጠራዋለች። ምክንያቱም አካላዊ ቃል ከቅድስት ድንግል ማርያም ለመወለድ መምጣቱን በማሰብ የሚጾም ነውና። 

 

ይህ ጾም ከክርስቶስ ልደት በፊት ለ፵፬ ቀናት ያህል የሚጾምና የክርስቶስን ልደት ለመቀበል የሚደረግ ጾም ነው። ፵ው ቀናት ሊቀ ነቢያት ሙሴ በሲና ተራራ የእግዚአብሔርን ሕግጋት ለመቀበል የጾመውን የሚያስታውስና ለሐዲስ ኪዳን ክርስቲያኖች ደግሞ የክርስቶስን ልደት መሠረት በማድረግ የሚጾም ነው።  

በዚህ ጾም ውስጥ ከ፵ው ቀናት በተጨማሪ አራት ቀናት ተያይዘው ይጾማሉ። ሦስቱ ጾመ አብርሃም ሶርያዊ ይባላል። በግብፅ ውስጥ በሊቀ ጳጳሱ በአባ አብርሃም ዘመን አሕዛባውያን “የሰናፍጭ ቅንጣትን የሚያህል እምነት ካላችሁ ይህን ተራራ ከዚህ ተነሥተህ ወደዚያ ሂድ ብትሉ ይሆንላችኋል” (ማቴ.፲፯፥፳) የሚለውን በማንሣት ክርስትናን ለመገዳደር ሲሞክሩና ሊቀ ጳጳሱንም ጠርተው ይህን ማድረግ ትችላላችሁን ብለው ጠየቁት። ሊቀ ጳጳሱም አዎን ብሎ መለሰ። ከዚያም ከምእመናኑ ጋር የሦስት ቀን ጸሎት አድርጎ በሥዕለ ቅድስት ድንግል ማርያም ፊት ተማጽኖንም ባቀረበ ጊዜ ይህን ማድረግ የሚችለው በግብፃውያን ቅዱስ ስምዖን ቆዳ ፋቂው  Simon Tanner (በእኛ ትርጓሜ ስምዖን ዘአሐቲ ዐይኑ ይለዋል) ተብሎ የሚጠራው ተራራውን እንዲንቀሳቀስ አድርጎታል። ከ፵ው ቀናት በፊት ሦስት ቀናት የሚጾሙት ይህን ድንቅ ተአምር ለማዘከር ነው። አንዱ ቀን ጾመ ገሃድ ይባላል። ይህም ልደት አርብ ወይም ረቡዕ የሚውልበት ጊዜ ስላለ አባቶች ለዚህ ምትክ እንዲሆን ሲሉ እንዲጾም ወስነዋል።

ጾመ ነቢያት መሠረቱ የሙሴ ጾም ነው።  ሙሴ ፵ ቀንና ፵ ሌሊት ጹሞ በጽላት  ላይ የተጻፈን የእግዚአብሔር ቃል ተቀብሏል። (ዘፀ.፳፬፥፲፪-፲፰) ከዚያም ነቢያት የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ልደት ተስፋ በማድረግ ጹመውታል። አስቀድመው ነቢያት የጌታችንን የልደት ዕለት ተስፋ በማድረግ ልደቱን በጉጉት ለማየት የጾሙትን የልደት ጾም ከግብዝነት ሕይወት ራሳችንን ለይተን ሰውነታችንን ለእግዚአብሔር አስገዝተን ብንጾም ነቢያት ያገኙትን በረከት እናገኛለን። ጾመ ነቢያት ለሐዲስ ኪዳን ክርስቲያኖች ከነቢያት በጎ ምኞት ጋር መገናኛ መሥመር እና ወደ እነርሱ ትንቢት ፍጻሜ መጓጓዣ ነው። ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በነቢያትና በሐዋርያት መሠረት ላይ የተመሠረተች እንጂ፣ በሐዋርያት መሠረት ላይ ብቻ የታነጸች አይደለችም። ጾመ ነቢያት የሐዲስ ኪዳኗ ቤተ ክርስቲያን ከነቢያት ጋር ያላትን አንድነት የሚገልጽ፣ የነቢያትም የሐዋርያትም ጉዞ ወደ ንጉሥ ክርስቶስ የልደት ስፍራ መሆኑን እንድንረዳ የሚያግዝ ምርኩዝ ነው።  

ሰባቱ የአዋጅ አጽዋማት ክርስቲያኖች የግድ ይጾሟቸው ዘንድ የታዘዙ ናቸው እንጂ በቸልታ የሚታለፉ አይደሉም። አንዳንድ ወንድሞች የአዋጅን ጾም “የቄሶች ጾም” ብለው በራሳቸው ለራሳቸው ምክንያት አበጅተው ከጾም ሲርቁ ይታያሉ። ጾመ ነቢያት ለኦርቶዶክሳውያን በሙሉ የታወጀ የግድ ሊጾም የሚገባው እንጂ በሰበባ ሰበብ ሊዘነጋ ፈጽሞ አይገባም። ይህን ጾም “የቄሶች” ብሎ አለመጾም ማለት በአንድ በኩል ለጾም ያለን ውስጣዊ ፍላጎት እጅግ የደከመ መሆኑን ሲያሳይ በሌላ በኩል ደግሞ ከዚህ ጾም የሚገኘውን በረከት አለመረዳትም ነው። በጥልቀት ከተመረመረ ደግሞ የሌለን ሥርዓት ሠርቶ ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን ጋር መጋጨትም ነው። 

የሰማይና የምድር ንጉሥ ሰው ሆኖ የሚወለድበትን ቀን ለማየትና በዚያ ቀን ከሚገኘው ፍጹም ደስታ ለመሳተፍ አስቀድሞ በጾምና በጸሎት መትጋት ያስፈልጋል። የክርስቶስን ሕማም ሳናስብ ትንሣኤው ጋር ዘልለን መሄድ እንደ ማንችለው የክርስቶስን የልደት ዕለት ለማግኘት በነቢያት ትንቢትና ጾም በር በኩል ማለፍ ግድ ይለናል። የክርስቶስን የልደቱን በዓል ለማክበር ለበዓሉ የሚሆን ዝግጅት ማድረግ በእጅጉ አስፈላጊ ነው። አንድ ታላቅ ወዳጅ የምንለው ሰው ወደ ቤታችን መጥቶ ያርፍ ዘንድ ካወቅን አስቀድመን ቤታችንን አስተካክለንና አሳምረን ወዳጃችንን ለማስደሰት የምንሻ አይደለንምን? ሌላው ቀርቶ የእኛን የልደት ዕለት ለማክበር እንኳን ከልደታችን ዕለት አስቀድመን የምንዘጋጅ መሆናችን ይታወቃል። እንግዲያው ዓለማትን በእጁ የያዘ እርሱ ከቅድስት ድንግል ማርያም ሥጋና ነፍስን በፍጹም ተዋሕዶ ነሥቶ ሰው ሆኖ በቤተ ልሔም የተወደበት ዕለት  በመንፈሳዊው ደስታ ደስ ለመሰኘት አስቀድመን ፍጹም ጥንቃቄና ዝግጅት ልናደርግ ያስፈልገናል።

ጾመ ነቢያት ከሰባቱ የአዋጅ አጽዋማት መካከል መሆኑን የሚሰሙ አንዳንድ ተቃዋሚዎች ደግሞ የአዋጅ የሚል ጾም የለም ብለው ሲሞግቱ ይሰማል። ይህ ሐሳባቸው ሌላው ቀርቶ ራሳቸው እናምናለን ብለው ከሚያስቡት መጽሐፍ ብቻ (Scripture alone) ከሚለው ጋር የሚጋጭ መሆኑን ቢረዱት መልካም ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ በአዋጅ የመጾምን ጉዳይ በተደጋጋሚ ዘግቦ ያስቀመጠልን ስለሆነ በእንዲህ ዓይነቱ ጉዳይ መወዛገብ የለብንም።  መጽሐፍ እንዲህ ይላል “... የእግዚአብሔርን ቃል በጾም ቀን በእግዚአብሔር ቤት በሕዝቡ ጆሮ በክርታሱ አንብቡ፤ ... በኢየሩሳሌም የተቀመጡ ሕዝብ ሁሉ ከይሁዳም ከተሞች ወደ ኢየሩሳሌም የመጡ ሕዝብ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ለመጾም አዋጅ ነገሩ።” (ኤር. ፴፮፥፮-፱)። ነቢዩ በግልጽ “በጾም ቀን” ማለቱ የታወቁ የጾም ቀናት መኖራቸውን ያስረዳል። ከዚህም ጋር አያይዞ “በኢየሩሳሌም የተቀመጡ ሕዝብ ሁሉ ከይሁዳም ከተሞች ወደ ኢየሩሳሌም የመጡ ሕዝብ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ለመጾም አዋጅ ነገሩ።” ማለቱ ደግሞ ነገሩን የበለጠ ግልጽ ያደርገዋል። 

ነቢዩ ኢዩኤል “ጾምን ቀድሱ፣ ምህላንም አውጁ፣ ሽማግሌዎችንና በምድር የሚኖሩትን ሁሉ ወደ አምላካችሁ ወደ እግዚአብሔር ቤት ሰብስቡ፣ ወደ እግዚአብሔርም ጩኹ” በማለት ሲገልጽ (ኢዩ. ፩፥፲፬) ። ነቢዩ ዘካርያስ ደግሞ “የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የአራተኛው ወር ጾም፣ የአምስተኛውም፣ የሰባተኛውም፣ የዐሥረኛውም ወር ጾም ለይሁዳ ቤት ደስታና ተድላ የሐሤትም በዓላት ይሆናል።” በማለት የበለጠ ጉዳዩን አጠንክሮ ገልጿል።   (ዘካ. ፰፥፲፱)። ነቢዩ ዘካርያስ አጽዋማትን ወይም የአጽዋማት ወቅቶችን የደስታ ጊዜያት ሲያደርጋቸው ከጾም ሕይወት ፈጽመው የራቁ ሰዎች ደግሞ በራሳቸው ስሜት ሐሳቡን ገልብጠው የጾም ወቅቶችን የኀዘንና የትካዜ ያደርጓቸዋል። ገና ጾም ሳይገባ እንዳይገባ በር በመዝጋት ላለመጾም ጥብቅና ይቆማሉ። ይህ በእጅጉ መጎዳት መሆኑን ልብ ብለው ያስተውሉ ዘንድ ከላይ የተገለጹትን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሐሳቦች መቀበል ግድ ይላቸዋል። ምናልባት ከላይ የተገለጹትን የአዋጅ አጽዋማትን ሰምተው ‹‹እነዚህማ በብሉይ ኪዳን የተገለጹ እንጂ በሐዲስማ እንዲህ ያለ ሥርዓት የለም›› እንዳይሉ ቅዱስ ሉቃስ “የጦም ወራት አሁን አልፎ ስለ ነበር . . .”  በማለት ገልጿል። (ሐዋ. ፳፯፥፱) ። ይህ ሁሉ የሚያሳየው ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ምን ያህል በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረትነት የምትመራ መሆኗን ነው። እንግዲህ የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ መሠረቱ መጽሐፍ ቅዱስ መሆኑንና ማንኛውም ዓይነት ኢ-መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሐሳብ ሊያነዋውጻት አለመቻሉን ምእመናን በአግባቡ ልንረዳ ይገባል።

በኅሊናችን ውስጥ ስለ ጾም መልካም ስፍራ ማዘጋጀች አለብን። በውስጣችን ለጾም ያዘጋጀነው ቦታ ጠባብ ከሆነ እንኳን “አይ ይህ ጾም ቢጾምም ባይጾምም አይጎዳም” ልንል ቀርቶ እንዲህ ዓይነቱ ሐሳብ በውስጣችን እንዲመላለስ አንፈቅድም። አንድ ሊቅ  “ጸሎትና ጾም በሌለበት ሰው ውስጥ ሰይጣን አለ ብለን ማሰብ እንችላለንን?” ብሎ ይጠይቅና ሲመልስ “አዎ፣ አጋንንት ወደ ሰው ውስጥ ሲገቡ መግባታቸውን በገሃድ አያሳውቁም፣ መግባታቸው እንዳይታወቅባቸው ለማድረግ ሲሉ ግን ራሳቸውን ይደብቃሉ እንጂ፤ ሆኖም የገቡበትን ያን ሰው ክፉውን ነገር ሁሉ በስውር ከውስጥ ያስተምሩታል፣ መልካም የሆነውን ነገር ደግሞ ያስጠሉታል። ያ ሰው የሚፈጽመው የጠላትን ፈቃድ ሆኖ ሳለ እርሱ ግን ራሱ እያደረገው እንደ ሆነ ያስባል። ጠላት  የሚወጣውና ሌላ መመለሻ አጋጣሚ እስኪያገኝ ድረስ ከእርሱ ርቆ የሚጠባበቀው ጸሎትና ጾምን ሲታጠቅ ብቻ ነው። ጸሎትና ጾም ከተተው ግን እንደ ገና ተመልሰው ይመጣሉ።” በማለት የጾም ጥቅሟን ይገልጻል። 

ጾም ኃይሏን ባልተረዷት ሰዎች ዘንድ ተራና የማትጠቅም ተደርጋ ልትወሰድ ትችላለች፤ ነገር ግን የሰዎቹ አለማወቅ የጾምን ታላቅነት ሊያስቀር ፈጽሞ አይችልም። ጾምን ለመረዳት ከጾም ውጭ መሆን የለብንም፤ አንድን ምግብ ጣዕሙን በመስማት ሳይሆን የምንለየው በመቅመስ ነውና። ጾምም ባልቀመሷት ዘንድ ጣዕሟ አለመታወቁ አይደንቅም። አንዳንዶች ደግሞ ጠቃሚነቷን ሳይቀበሉ ሊያጣጥሏትና ምንም ረብና ጥቅም እንደ ሌላት አድርገው ሊያሳምኑም ይሻሉ። ጥንቱን በበሽተኛ ሰው የተቀመሰ ጣፋጭ ምግብ መች ጣፍጦ ያውቅና ነው! ምግቡ ጣፋጭ ስላይደለ አይደለም፤ ቀማሹ በሽተኛ ስለ ሆነ ነው እንጂ። የውጫዊ ዐይን ዕውርነት የውስጣዊ ዐይንን ብሩህነት አይከለክልም። የውስጣዊው ዐይን ዕውርነት ግን የውጫዊውንም ዐይን የማሳወር ኃይል እንዳለው መገንዘብ ይኖርብናል። ጾም በሆዳሞች ዘንድ ብትጠላም፤ ሆዳምነታቸውን ዐውቀው እንደ መድኃኒት ቢጠቀሟት ኖሮ በሽታቸውን የማራቅ ኃይል እንዳላት ይረዷት ነበር። 

ላለመጾም ሆን ተብለው የሚቀርቡ ምክንያቶች በሙሉ ካለመጾሙ የበለጠ ጎጂዎች ናቸው። ይህ እኮ ብዙ ሰዎች የማይጾሙት ጾም ስለ ሆነ “አይካበድም” እያሉ በታወቀ ቸልተኝነት አልጋ ላይ በምግብ ፍቅር በጾም ጥላቻ ከመተኛት ጥቅሟን በማሰብ እውነተኛውን ጾም መጾም አለብን። ይህ የሽማግሌ ወይም የቄስ ጾም ነው ተብሎ ሳይገለጽ አንዳንዶች ባለመጾማቸው ከመጣባቸው የኅሊና ክስ ለማምለጥ ከሚያቀርቡት ተራ ምክንያታዊነት መላቀቅ አለብን። ኢትዮጳያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ ጾምን አስመልክቶ እንዲህ ይላል “ጾም ትፌውስ ቁስለ ነፍስ ወታጸምምኵሎ ዘሥጋ ፍትወታት ትሜህሮሙ ለወራዙት ጽሙና፤ ጾም የነፍስን ቁስል ታድናለች፤ የሥጋን ፍላጎት ታስታግሣለች፤ ለወጣቶችም ጽሙናን ታስተምራቸዋለች”። እንግዲህ ይህን ያህል ለመንፈሳዊነታችን የምትጠቅመውን ጾምን አለመውደድ እንዴት ያለ ጉዳት ይሆን! እንዲሁም ሊቁ ቅዱስ ያሬድ “እስመ በጾም ወበጸሎት ይሠረይ ኵሉ ኃጢአት በጾም ድኅኑ አበው ቀደምት ኤልያስ ዐርገ ውስተ ሰማያት፤ በጾምና በጸሎት ኃጢአት ሁሉ ይሠረያል፤ ቀደምት አባቶች በጾም ዳኑ፤ ኤልያስም በጾም ወደሰማያት ዐረገ” በማለት ያስረዳል። (ጾመ ድጓ) ይህ ሁሉ የሚያመለክተው ጾም ምን ያህል አስፈላጊና ሁልጊዜም ልንመርጠው የሚገባ መሆኑን ነው። ስለዚህ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በሠራችልን ሥርዓት ውስጥ ሆነን ጾምን እጅግ በመውደድ ልንይዛትና ልንኖራት ይገባናል። በኅሊናችን ውስጥ የሚመጡትን የጾም ተቃራኒ ሐሳቦች በሙሉ እንሸሽ ዘንድ ጾምን በራሱ መሸሸጊያ አድርገን እንግባባት። በውስጣችን የሚቀጣጠሉትን እኩያት ፍትወታት እናስወግድ ዘንድ በጾም ቤት ውስጥ ገብተን እንኑር። ይህን የነቢያት ጾም በመጾም እንደ ነቢያት የክርስቶስን የልደት ዕለት ለማክበር ከልባችን ልንፈልግ፣ ልንመኝ፣ በጉጉት ልንጠብቅ ይገባናል። 

በአጠቃላይ ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ የልደትን በዓል አስመልክቶ የተናገረውን ማወቅ አስቀድሞ ተጠንቅቆና ተዘጋጅቶ መጠበቅ እንደሚያስፈልግ ለመረዳት እጅግ ይጠቅማል። እንዲህ ይላል “ከበዓላት ሁሉ ይልቅ እጅግ የተከበረውና የተወደደው በዓል እየደረሰ ነው። አንድ ሰው ይህን በዓል “ርእሰ በዓላት” ብሎ ቢጠራው የተመቸ የቀና ነው። ለምን ቢሉ ወልደ እግዚአብሔር በሥጋ የተወለደበት ዕፁብ ድንቅ በዓል ነውና።” በማለት የልደትን በዓል ታላቅነት ገልጿል። (ገብረ እግዚአብሔር ኪደ (ተርጓሚ)፡ አምስቱ የንስሓ መንገዶች (፳፻፲፩ ዓ.ም. ገጽ ፴፮) ። እንግዲህ ይህን በዓል ለማግኘት በነቢያት ጾም በኩል በጥልቅ መመኘት መጓዝ ያስፈልጋል።  አንድ ሰርግ በሚኖርበት ጊዜ የሰርጉ ዕለት ከመድረሱ አስቀድሞ ዝግጅቶችን ማድረግና ለዋናው የበዓል ቀን ራስን ማመቻቸት እንደ ሚያስፈልግ፣  ይህን ታላቅ በዓል በሐሤት ለማክበር በጾም ቅድመ ዝግጅታችንን ማመቻቸትና ለበዓሉ ዕለት የተገባን እንድንሆን በጾም መጓጓዣነት ተግተን መድረስ አለብን። አምላካችን እግዚአብሔር ላለመጾም ከምናቀርበው ምክንያት ጠብቆ ጹመን እንድንጠቀም ይርዳን አሜን።

 

 

Read 1101 times