Saturday, 02 January 2021 00:00

የጥያቄዎቻችሁ መልስ ክፍል አንድ

Written by  ዲ/ን ዐብይ ሙሉቀን

Overview

ውድ አንባብያን በጥያቄዎቻችሁ መልስ ዐምዳችን የነገረ ሥጋዌን ጉዳይ በተመለከተ የሚነሡ ጥያቄዎችን መሠረት አድርገን ምላሽ ይሰጡን ዘንድ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በደብረ ነጎድጓድ ቅዱስ ዮሐንስ ቤተ ክርስቲያን የስብከተ ወንጌል ኃላፊና የመጻሕፍት መምህር የሆኑትን መምህር ሥሙር አላምረውን ጋብዘናል። መምህር ሥሙር የመጻሕፍተ ሐዲሳትና የመጻሕፍተ ሊቃውንት ትርጓሜ መምህር ሲሆኑ፡ ፈቃደኛ ሆነው ከቦታችን ተገኝተውልን ቆይታችንን እንዲህ አዘጋጅተነዋል፤ መልካም ንባብ። ሐመር፡- መምህር ነገረ ሥጋዌን መሠረት ያደረጉና በማኅበረሰቡ ዘንድ የሚነሡ ጥያቄዎችን መሠረት አድርገን ለምናነሣቸው ሐሳቦች ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ ስለ ሆኑልን አስቀድመን በእግዚአብሔር ስም እናመሰግናለን።  መምህር ሥሙር አላምረው፡- እኔም  ስለጋበዛችሁኝ አመሰግናለሁ። ፩. ሐመር፡-በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ከሚዘመሩት መዝሙራት መካከል አንዱ ነቢዩ ዳዊት “በኃይል ቀን በቅዱሳን ብርሃን ከአንተ ጋር ነበርሁ” (መዝ.፻፱፥፫) የሚለው ነው። ነቢዩ እንዲህ ሲል ምን ማለቱ ነው? ይህ የኃይል ቀን የተባለውስ መቼ ነው?  መምህር ሥሙር አላምረው፡- ይህ ዕለተ ኀይል የተባለው በርካታ ዝርዝሮች አሉት። የተወሰኑትንና በተለይም ከነገረ ሥጋዌው ጋር ግንኙነት ያላቸውን ብቻ እንመለከታለን። ይህ ዕለተ ኀይል የተባለው፡-  ሀ.የመጀመሪያው ዕለተ ፍጥረት ነው። ማለትም ይህ ዓለም ካለመኖር ወደ መኖር የተፈጠረበት ዕለት ነው። በቅዱሳን ብርሃን የሚለው ደግሞ በቅዳሴሆሙ ለመላእክት ብለው ሊቃውንቱ ይተረጉሙታል። ቅዱሳን መላእክት ‹‹ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ›› እያሉ ያመሰገኑበት ቀን የኃይል ቀን ይባላል። በዚህች ቀን ቀዳማዊ ወልድ ከቀዳማዊ አብ ጋር ነበር ብሎ ነቢዩ ቀዳማዊነትን ለእግዚአብሔር አብም ለእግዚአብሔር ወልድም ሰጥቶ ይናገራል። ተናጋሪው እግዚአብሔር ወልድም እግዚአብሔር አብም ይሆናል። ይህ ዕለት የኀይል ቀን የተባለበት ምክንያት የዚህ ዓለም ጠበብት ምንም ነገር ቢሠሩ ካለመኖር ወደ መኖር አምጥተው ሊፈጥሩ አይችሉም። እግዚአብሔር ግን ይህን ዓለም ካለመኖር ወደ መኖር አምጥቶ ፈጥሮታልና የኀይል ቀን ይባላል። በዚህ ዓለም ጠበብት የተፈጠሩ በርካታ ነገሮች አሉ። ግን ሰዎች የፈጠሯቸው  ከተፈጠረ ነገር ነው። ለምሳሌ- መብራትን ቢፈጥሩ መብራትን ለመፍጠር የሚያስችል ቅንጣት፤ መኪና፣ አውሮፕላን፣ ወዘተ. ቢያዘጋጁ እነዚህን ሁሉ ለማዘጋጀት የሚያስችሉ ቁስ አካላት ያስፈልጓቸዋል። እግዚአብሔር ግን በመጽሐፈ ቅዳሴያችን  “ዘእንበለ እሳት አንደደ ወዘእንበለ ማይ አብረደ፤ ያለእሳት እሳትን ፈጠረ፤ ያለ ውኃ ውኃን ፈጠረ” ተብሎ እንደ ተገለጸው ዓለምን ካለመኖር ፈጠረ። ስለዚህ እንዲህ ያለው ድንቅ ተግባር ተከናውኖበታልና ይህ ቀን የኃይል ቀን ተብሏል። በዚህ በኀይል ቀን እግዚአብሔር ወልድ ከእግዚአብሔር አብ ጋር ነበረ። ለምን ከተባለ በመፍጠር አንድ ናቸውና። ወንጌላዊው ዮሐንስም “በመጀመሪያ ቃል ነበረ፤ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፤ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ። ይህም በመጀመሪያ በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ። ሁሉ በእርሱ ሆነ፤ ከሆነውም ሁሉ ያለ እርሱ ምንም ምን የሆነ የለም።” (ዮሐ.፩፥፩) በማለት እንደ ገለጸው ዓለም ከመፈጠሩ በፊት በአንዲት ህልውና የነበሩ ሥላሴ ይህን ዓለም በአንዲት ሥልጣን፣ በአንዲት ፈቃድ ፈጥረዋል። ስለዚህ ‹‹ዓለምን ካለመኖር ወደ መኖር አምጥቶ ለመፍጠር አብሬው ነበርሁ›› ብሎ እግዚአብሔር ወልድም እግዚአብሔር አብም ይናገራል። ለ. ዕለተ ፅንስ፡- ይህ ዕለት ከሦስቱ አካላት አንዱ አካል እግዚአብሔር ወልድ በተለየ አካሉ ከድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋን ከነፍሷ ነፍስን ነሥቶ በኅቱም ድንግልና የተፀነሰበት ዕለት ነው። ይህ ዕለት የኀይል ቀን ተብሏል ምክንያቱም ፅንሰቱ ያለ ዘርአ ብእሲ ስለ ሆነ ነው። አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫም ይህን ድንቅ ነገር ሲናገር “ለቀዳማዊ ልደቱ አመሥጠሮ ወለደኃራዊ ልደቱ አመንከሮ፤ ቀዳማዊ ልደቱን አረቀቀው፣ ደኃራዊ ልደቱን ደግሞ አስደነቀው” (መጽሐፈ ምሥጢር) በማለት በኅቱም ድንግልና ተፀንሶ በኅቱም ድንግልና መወለዱን በአድናቆት ይገልጻል። ይህ ነገር ለምን ተደነቀ ከተባለ ፅንሱ ከአጋንንት የተሠወረ ነው። እንኳንስ ከአጋንንት ከዮሴፍም የተሠወረ ስለ ነበር ዮሴፍ እጅግ ተጨንቆ ነበር። እመቤታችንም ተደንቃበታለች። እንዲሁ የቅዱስ ገብርኤልን ቃል አልተቀበለችውም። እንዴት ይሆናል ወንድ የማታውቅ አንዲት ድንግል እንዴት ልትፀንስ ትችላለች በማለት ጥያቄ አቅርባ ነበር። ነገር ግን መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል “ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለም” ሲላት “እንደ ቃልህ ይደረግልኝ” ብላ ተቀበለች። ይህንም ምክንያት አድርጎ ከቅዱስ ገብርኤል የሰማችው ቃል በማኅፀነ ማርያም ተፀነሰ። እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው የቅዱስ ገብርኤል ቃል ተፀነሰ ማለት አይደለም። ራሱ ባለቤቱ “ላእከ ኮንኩ ለርእስየ ወአብሠርክዋ ለወላዲትየ በአምሳለ ገብርኤል ላእክ፤ ለራሴ መልእክተኛ ሆንኩ ለእናቴም በገብርኤል አምሳል አበሠርኳት” በማለት ተናግሯል። ስለዚህ በገብርኤል አምሳል እናቱን ያበሥር የነበረው እግዚአብሔር ቃል ወይም በገብርኤል ላይ አድሮ ድንግል ማርያምን ያበሠራት እግዚአብሔር ቃል በኅቱም ድንግልና ተፀነሰ። ይህ ዕፁብ ድንቅ የሆነው ምሥጢር ስለ ተፈጸመበት የኃይል ቀን ተባለ። በዚህ ዕለት ‹‹ከአንተ ጋር ነበርሁ›› የሚለው እግዚአብሔር አብ ለማጽናት፣ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ለጠበቅ እግዚአብሔር ወልድ ደግሞ በተለየ አካሉ ለመፀነስ፣ ከሥጋዋ ሥጋን ከነፍሷ ነፍስን ነሥቶ ለመዋሐድ አድረውባታልና ‹‹ከአንተ ጋር ነበርሁ›› ይላል። ሐ. ዕለተ ልደት፡- ዕለተ ልደት ማለት ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደበት፤ አምላክ ሰው መሆኑ ሰው አምላክ መሆኑ የተገለጠበት ዕለት ነው። በዚህም ጊዜ “ከአንተ ጋር ነበርሁ” ያለው ከእግዚአብሔር አብ የተለየበት ጊዜ አለመኖሩን ያስረዳል። እግዚአብሔር ወልድ በተለየ አካሉ ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ከድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋን ከነፍሷ ነፍስን ነሥቶ ስለ ተወለደ ከባሕርይ አባቱ ከእግዚአብሔር አብ ከባሕርይ ሕይወቱ ከእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ተለየ የተባለበት ጊዜ የለም። ይህ ከባሕርይ አባቱ ከአብ ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ሳይለይ የተወለደበት ቀን እጅግ ድንቅ ስለ ሆነ የኃይል ቀን ተባለ። ሌላው የኀይል ቀን የተባለበት ምክንያት እርሱ በተወለደ ጊዜ ጣኦታት ተሰባብረዋል፣ አጋንንት በጣኦታት ላይ ማደር ተስኗቸው ተጨንቀዋል። እንዲያውም አጋንንት እየሄዱ ለአለቃቸው ለዲያብሎስ ጣኦታቱም ተሰባበሩ እኛም በጣኦታት ላይ ማደር አልተቻለንም ብለው ነገሩት። በዚህ ጊዜ “ያ ኢሳይያስ ‘እነሆ ድንግል ትፀንሳለች፤ ወንድ ልጅንም ትወልዳለች ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች’ (ኢሳ.፯፥፲፬) ብሎ ትንቢት የተናገረለት፣ ሚኪያስም ‘አንቺም የኤፍራታ ምድር ቤተ ልሔም ሆይ አንቺ በይሁዳ አእላፋት መካከል ትሆኚ ዘንድ ታናሽ ነሽ፤ ነገር ግን አወጣጡ ከቀድሞ ጀምሮ ከዘለዓለም የሆነ በእስራኤል ላይ ገዢ የሚሆንከአንቺ ይወጣልኛል’ (ሚክ.፭፥፪) ሲል የሰማሁት  ሌሎችም ነቢያት ትንቢት የተናገሩለት ተወልዶ ይሆናል” ብሎ ተናገረ። በዚያም ጊዜ በምናሴ ላይ አድሮ ነቢያቱን አስገደላቸው። መላእክት ከእረኞች ጋር ዘምረዋል፤ እረኛ ዘፈን እንጂ ምስጋና አያውቅም በዚያ ዕለት ግን ከመላእክት ጋር አብረው ዘመሩ። የኃይል ቀን ያስባለው ይህ ሁሉ ነው። በአጭሩ የኀይል ቀን ማለት ዓለም ካለመኖር ወደ መኖር መጥቶ የተፈጠረበት፣ አምላክ ሰው የሆነበት ሰው አምላክ የሆነበት ዕለተ ፅንስ፤ አምላክ ሰው መሆኑ ሰው አምላክ መሆኑ የተገለጠበት ማለትም በኅቱም ድንግልና ተፀንሶ በኅቱም ድንግልና የተወለደበት ዕለተ ልደት ነው። ይህ ብቻ ነው ማለት አይደለም ዕለተ ስቅለቱ፣ ዕለተ ትንሣኤው፣ ዕለተ ዕርገቱ፣ ለሐዋርያት መንፈስ ቅዱስ የወረደበት ዕለት፣ ዕለተ ምጽአቱ ሁሉ የኃይል ቀን ይባላል። በዚህ ሁሉ እግዚአብሔር ወልድ ከእግዚአብሔር አብ ጋር በአንዲት ፈቃድና በአንዲት ሥልጣን አባታዊና አምላካዊ ሥራውን ይሠራልና በኀይል ቀን ከአንተ ጋር ነበርሁ የሚለው እንዲህ ይተረጎማል። ፪.ሐመር፡- ከላይ እንደ ተመለከትነው የኃይል ቀን ከተባሉት መካከል አንዱ አምላክ ሰው የሆነበት ሰው አምላክ የሆነበት ነው ብለናልና ለመሆኑ አምላክ ሰው ሆነ ሰው አምላክ ሆነ ስንል ምን ማለታችን ነው? መምህር ሥሙር አላምረው፡- ‹አምላክ ሰው ሆነ ሰው አምላክ ሆነ› ስንል እንደ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ‹ከኃጢአት ብቻ በቀር አምላክ የእኛን ባሕርይ፣ የእኛን ጠባይ፣ የእኛን አካል ገንዘቡ አደረገ› ማለታችን ነው። በሌላ መንገድ ‹አምላክ ሰው ሆነ ሰው አምላክ ሆነ› ማለት ‹ልዑሉ አምላክ የትሑቱን ሥጋ ባሕርይና አካል ገንዘብ አደረገ፤ ትሑት የነበረው ሥጋ ደግሞ ባሕርየ መለኮትን፣ አካለ መለኮትን ገንዘቡ አደረገ› ማለታችን ነው። ፫. ሐመር፡- አምላክ ሰው መሆን ለምን አስፈለገው? መምህር ሥሙር አላምረው፡- የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ልዩ ልዩ ነጥቦችን ይናገራሉ። የተወሰኑትን ለማየት ያህል ቅዱስ ጎርጎርዮስ ገባሬ ተአምራት “እስመ አሕዛብ አፍቀሩ አርአያ ወአምሳል እምዕፀው ዘፀረብዎሙ ፀረብት ወበእንተዝ ኮነ ሥጋ ወልድከ፤ አሕዛብ የለዘበ ድንጋይ የተጠረበ እንጨት እያመለኩ የሚታይ አምላክ እንጂ የማይታይ አምላክ ማምለክ አልፈለጉም በዚህም ልጅህ ሥጋን ተዋሐደ” (ሃይ.አበው ዘጎርጎርዮስ ፲፭፥፮) በማለት አምላክ ሰው የሆነበትን ምክንያት ያስረዳል። ሰዎች የሚታይ አምላክ ከፈለጉ ብሎ የሚታይ፣ የሚዳሰስ፣ የሚጨበጥ ወዘተ አምላክ ሆኖ መጣ። ስለዚህ አምላክ ሰው የሆነው የሰው ልጅ የማያየውን፣ በእምነት ብቻ የሚከተለውንና የሚያመልከውን አምላክ ማምለክ ስላልቻለ ግዙፍ አምላክ ለግዙፍ አስተሳሰባችን የሚመች ሆኖ መጣ።  ያዕቆብ ዘሥሩግ የተባለው የቤተ ክርስቲያናችንም ሊቅ “መላ ሕዋሳትን ከእኛ ገንዘብ አደረገ” ይልና ይህን ሲያብራራው ለራሱ ደረትን ገንዘብ አደረገ፤ድንግል ትታቀፈው ዘንድ፤ በኋላም ደግሞ የፈጠረውን አዳምን ይታቀፍበት ዘንድ፣ ለራሱ ጀርባን ገንዘብ አደረገ፤ ለጊዜው የጠፋውን በግ ይሸከምበት ዘንድ በኋላም በዕለተ ዐርብ ተገርፎ፣ ቆስሎ፣ መከራን ተቀብሎ፣ በቁስሉ ቁስላችንን ያድን ዘንድ፤ ለራሱ አፍና ምራቅን ገንዘብ አደረገ፤ የዕውራንን ዐይን ያበራ ዘንድ”(ሃ. አበው ፹፰፥፭-፯) በማለት ያብራራል። ስለዚህ በድንግል ማርያም እቅፍ ላይ ተቀምጦ የሚታይ አካል፣ የሚገረፍ ጀርባ፣ በዕውራን ዐይን ላይ እንትፍ ተብሎ ዕውራንን የሚያበራ ምራቅ፣ ያስፈልገው ነበርና አምላክ ሰው ሆነ። ሌላው አምላክ ሰው መሆን ለምን አስፈለገው የሚለውን ስንመለከት ከጥንተ ጠላት ዲያብሎስ ሴራና ተንኮል እንድንመለከት ያስገድደናል። ዲያብሎስ አዳምና ሔዋንን ሲያስታቸው በእባብ ላይ አድሮ ነው። ስለዚህ ‹‹እሾህን በእሾህ” እንዲሉ ስሕተቱን በመጣበት መንገድ ለመመለስ ነበር። ዲያብሎስ በእባብ ገላ አድሮ አዳምንና ሔዋንን እንዳሳተ እግዚአብሔር ወልድም በሥጋ ተገልጦ ዲያብሎስን ድል ያደርግና አዳምን ነጻ ያወጣ ዘንድ አምላክ ሰው ሆነ “ወበከመ ተሀብአ ሰይጣን በጕህሉት ውስተ ሥጋ ከይሲ ከማሁ ኮነ ድኅነትን በተሠውሮተ ቃለ እግዚአብሔር በዘመድነ፤ ሰይጣን በተንኮሉ በሥጋ ከይሲ እንደ ተሠወረ ድኅነታችንም ቃለ እግዚአብሔር በሥጋችን በማደሩ ተፈጸመልን።” (መቅድመ ወንጌል) እንደ ተባለ የእኛ ድኅነት በዚህ መንገድ ይሆን ዘንድ ፈቅዷልና አምላክ ሰው ሆነ። በሌላ መንገድ ሰው መሆን ለምን አስፈለገው የሚለውን ቄርሎስ የተባለው የቤተ ክርስቲያናችን ሊቅና አረጋዊ መንፈሳዊ የተባለ ሊቅ የተባበሩበት “በሕፃን አምሳል ተገለጠ አንተን ሕፃን ያደርግህ ዘንድ”  ይላል። ቅዱስ ጎርጎርዮስ የተባለ የቤተ ክርስቲያናችን ሊቅም እኛ በመጀመሪያ “እግዚአብሔርም አለ ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌያችን እንፍጠር” (ዘፍ.፩፥፳፮) ያለውን ይጠቅስና ‹‹የሰው ልጅ ሁሉ እግዚአብሔርን መስሎ ተፈጥሮ ነበር። ነገር ግን አትብላ የተባለውን ዕፀ በለስ ሲበላ እግዚአብሔርን መምሰሉ ተበላሸ፣ መነሻ ግብራችን ከእኛ ተለይቶን ነበር። ስለዚህ ያ  እግዚአብሔርን የመሰለበት ተፈጥሮ ሲበላሽ ራሱ እግዚአብሔር ሰውን መሰለ›› በማለት ያብራራል። እዚህ ላይ ሁለት መመሳሰሎች ይታያሉ። የመጀመሪያው ‹እግዚአብሔር ሰውን በአርአያውና በአምሳሉ ፈጠረው›ና ‹ሰው እግዚአብሔርን መሰለ›። ሁለተኛው ግን የአምላክ ሰው መሆን ራሱ አምላክ ሰውን ሆኖ መጣ ማለት ነው። ሳዊሮስ የተባለ ሊቅ “ቀዳሚሰ ወሀበነ አርአያሁ ክብርተ ወደኃሪሰ ነሥአ ሥጋነ ህሥርተ፤ በመጀመሪያ ክብርት የሆነች አርአያውን ሰጠን፤ በኋላ ግን የእኛን የጎሰቆለ ባሕርያችንን ከኃጢአት ንጹሕ አድርጎ ገንዘቡ አደረገ።” (ቅዱስ ጎርጎርዮስ)  በማለት ያስረዳል። ስለዚህ ለእኛ ሁለተኛ ልደት ይሰጠን ዘንድ እርሱ ሁለተኛ ተወለደ፤ እርሱ ሁለተኛ ባይወለድ እኛም ሁለተኛ አንወለድም ነበር። እርሱ ፈራሽ በሆነ ሥጋ ተወልዶ እኛ ዘለዓለማዊ የሆነ ልደትን እንድንወለድ አደረገን። አምላክ ሰው የሆነበት ዋናው ምክንያት ይህ ነው። ፬. ሐመር፡- አምላክ ሰው መሆን ያስፈለገው ከላይ የተዘረዘሩትን ነገሮች ለማድረግ ነው። ይሁን እንጂ ከላይ የተዘረዘሩትን ነገሮች በሙሉ ለማድረግ ነው ከተባለ ሁሉን የሚችል አምላክ ሰው ሳይሆን ማድረግ አይችልም ነበር ወይ? መምህር ሥሙር አላምረው፡- ይህን ጥያቄ ከእኛ በፊት የነበሩ ሊቃውንት ጠይቀው መልሱንም መልሰውታል። ኀይለኛ ደካማውን ቢያሸንፍ አይደንቅም። “አኮ መንክር እመ ሞዖ ኃያል ለድኩም መንክርሰ እመ ሞዖ ድኩም ለኀያል፤ ኀይለኛ ደካማውን ድል ቢያደርግ አይደንቅም የሚያስደንቅ ግን ደካማ ኀይለኛውን ድል ማድረጉ ነው። ይህም ደካማ ሥጋ ኀይለኛውን ዲያብሎስ ድል ማድረጉ ነው እንጂ ኀያሉ መለኮት ደካማውን ዲያብሎስ ድል ማድረጉ አያስደንቅም። ስለዚህ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አዳምንና ሔዋንን ከዲያብሎስ ግዞት ነፃ ያወጣቸው በደካማ ሥጋ እንጂ በኀያል መለኮት አይደለም። በእርግጥ ደካማ ሥጋ ከኀያል መለኮት ጋር ተዋሕዷል።  በመሆኑም የዲያብሎስ መሸነፍ የክርስቶስ ማሸነፍ በደካማ ሥጋ መሆኑ ነው እንጂ የሚያስደንቀው በኃያል መለኮት ቢሆን አያስደንቅም ነበር። ስለዚህ በዚህ ድንቅ በሆነ ጥበቡ እኛን ያድነን ዘንድ አምላክ ሰው ሆነ። በሌላ መልኩ ደግሞ ኪዳን ወይም ትምህርተ ኅቡአት በተባለ መጽሐፍ ላይ እንደ ተገለጸው “አርአያ ዘኢይማስን ዘቦቱ በአርአያ ዘይማስን ተነሥተ፤ የማይሞት አካል ያለው ዲያብሎስ በሚሞት ሥጋ ድል ተነሣ” (ትምህርተ ኅቡአት) ይላል። ስለዚህ የማይሞተው መለኮት ዲያብሎስን ድል አድርጎት ቢሆን አይደንቅም ነበር።  እንዲሁም እግዚአብሔር ለሰው ልጅ ያለው ፍቅር አይታወቅም ነበር። ፍቅሩ ድንቅ ይሆን ዘንድ ከሚራብ፣ ከሚጠማ፣ ከሚታመም፣ ከሚሞት ሥጋ ጋር ተዋሐደና ረሀብ፣ ጥም፣ ሕማም፣ ሞት ወዘተ. የማይስማማውን ዲያብሎስን ድል አደረገው። እግዚአብሔር ለሰው ልጅ ያለውን ፍጹም ፍቅር በቅዱስ ወንጌልም “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘለዓለም ሕይወትን እንዲያገኝ እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን ቤዛ አድርጎ እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲህ ወዶታልና” (ዮሐ.፫፥፲፮) ተብሎ እንደ ተገለጸው እንዲሁ መውደዱን ይገልጽልን ዘንድ ዋጋ ከፈለልን። ስለ ወደደን ተወለደልን፣ ስለ ወደደን ተገረፈልን፣ ስለ ወደደን ተሰቀለልን፣ ዋጋ ከፍሎ መውደድና ዋጋ ሳይከፍሉ መውደድ የተለያየ ስለ ሆነ እጅግ የሚያስደንቅ ዋጋ ከፈለልን። ይህን በተመለከተ አባ ሕርያቆስም በቅዳሴው “ፍቅር ሰሀቦ ለወልድ ኀያል እመንበሩ ወአብጽሖ እስከ ለሞት፤ ኀያል ወልድን ፍቅር ከዙፋኑ ሳበው እስከ ሞትም አደረሰው” (ቅዳሴ ማርያም) በማለት እንደ ገለጸው የጽንዐ ፍቅሩ መገለጫ ይሆን ዘንድ የማይሞት መለኮት ከሚሞት ሥጋ ጋር ተዋሐደ፤ የማይራበው መለኮት በሚራብ ሥጋ ተራበ፣ የማይሞተው መለኮት በሚሞት ሥጋ ሞተ። ቄርሎስ የተባለ የቤተ ክርስቲያናችን ሊቅ ደግሞ  “ወረደ ከመ ያዕርገነ ለነ ኀበ ሀገሩ አርያማዊ ኀበ ሀሎ አቡሁ፤ የባሕርይ አባቱ ካለበት ሰማያዊ ሀገሩ ያገባን ዘንድ እርሱ ወደ እኛ ወረደ” (ሃ/አበው) በማለት ተናገረ። ይህን ደግሞ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ስብከቱ “ልባችሁ አይደንግጥ በእግዚአብሔር እመኑ፤ በእኔም እመኑ። በአባቴ ቤት ብዙ ማደሪያና ማረፊያ አለ” (ዮሐ.፲፬፥፩) በማለት ለደቀ መዛሙርቱ እንደ ነገራቸው ሰማያዊውን ርስት ያወርሰን ዘንድ ሰው ሆነ። እንግዲህ ጽንዐ ፍቅሩን ይገልጽልን ዘንድ በሚደክም፣ በሚታመም፣ በሚራብ ሥጋ ተገለጠ፣ በተዋሐደው ሥጋ ተራበ፤ ተጠማ፤ ተገረፈ። መለኮት የሚራብ፣ የሚጠማ፣ የሚታመም፣ የሚሞት ባሕርይ የለውም ስለዚህ ሰው ሆነ የሚታመም፣ የሚገረፍ፣ የሚራብ፣ የሚጠማ፣ የሚሞት አካል ያለውን ገንዘብ ሁሉ ገንዘቡ ለማድረግ አምላክ ሰው ሆነ። በዚህ ክፍል ‹አምላክ ሰው ሆኖ ያደረጋቸውን የማዳን ሥራዎች ሁሉ ሰው ሳይሆን ማድረግ አይችልም ነበር ወይ?› ለሚለው ጥያቄ መልሱ ‹ይችላል› ነው። ነገር ግን ከላይ በዘረዘርናቸው ምክንያቶች ሰው ሆነ እንዳልን ሁሉ ለመጨረሻ አረአያነቱን ሊያድለን ሰው ሆነ። አረአያነት በተግባር የሚገለጽ ነው። መለኮት የሚራብ፣ የሚጠማ፣ የሚቸገር፣ የሚታመም፣ የሚሞት ባሕርይ የለውም። ጹሞ ‹‹ጹሙ›› ሊለን፣ ተርቦ ‹‹ተራቡ›› ሊለን፣ ተጠምቶ ‹‹ተጠሙ›› ሊለን ሰው ሆነ። በቅዱስ ወንጌልም “ቀንበሬን በላያችሁ ላይ ተሸከሙ፤ ከእኔም ተማሩ፤ እኔ የዋህ ነኝና፤ ልቤም ትሑት ነውና ለነፍሳችሁም ዕረፍትን ታገኛላችሁ።” (ማቴ.፲፩፥፳፱) እንዳለን እኛ እንድንጠቀምበት የምንሠራውን ሁሉ አስቀድሞ እርሱ ፈጽሞልናል። ስለዚህ ጹሞ ‹‹ጹሙ›› ለማለት ተርቦ ‹‹ተራቡ›› ለማለት፣ ተሰዶ ‹‹ተሰደዱ›› ለማለት፣ ተገርፎ ‹‹ተገረፉ›› ለማለት የሚራብ፣ የሚጠማ፣ የሚሰደድ፣ የሚገረፍ፣ የሚሞት ሥጋ ያስፈልገው ስለ ነበር አምላክ ሰው ሆነ።
Read 1841 times