Thursday, 21 January 2021 00:00

የጥያቄዎቻችሁ መልስ

Written by  ዲ/ን ዐብይ ሙሉቀን
፭. ሐመር፡- ‹‹ሰው አምላክ ሆነ አምላክ ሰው ሆነ›› ስንል ከላይም እንደ ተገለጸው ልዑለ ባሕርይ መለኮት ትሑቱን ሥጋ ገንዘብ አደረገ ማለት ነው። ይህ ከሆነ ደግሞ ነቢዩ ዳዊት በመዝሙሩ “ሁሉ ተካክሎ በደለ አንድ ስንኳን በጎ ነገርን የሚያደርጋት የለም” (መዝ.፲፫፥፫ ፤ መዝ.፶፪፥፫) እንዳለ አንድም ንጹሕ ሰው አልነበረም። ስለዚህ ‹አምላክ የተዋሐደው ሥጋ ጥንተ አብሶ ነበረበት› አያስብልም ወይ? መምህር ሥሙር፡- እዚህ ላይ መጠንቀቅ የሚያስፈልገው ነገር “ሁሉ” የሚለው ቃል አንጻራዊ ነው። ለምሳሌ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም “እነሆ ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ይሉኛል” (ሉቃ.፩፥፵፰) ብላ ስትናገር አንጻራዊ በሆነ አገላለጽ እንጂ የማያምን እንዳለ የታወቀ ነው። ሁሉ የሚለው ቃል አማኞችን ብቻ የሚመለከት ነው። ስለዚህ ይህ ዳዊት የተናገረው ቃል በተነገረበት ዘመንና ከተነገረበት ዘመን በፊትም የነበረውን ብንመለከት ሁሉም አልበደሉም። ለምሳሌ፡- በብሉይ ኪዳን ጽድቅ የመርገም ጨርቅ ቢሆንም እጅግ በርካታ ደጋግና ቅዱሳን የእግዚአብሔር ሰዎች እንደ ነበሩ መዘንጋት የለብንም። በዘፍ.፬ ስለ አቤል ጽድቅ ተጽፎ እናገኛለን። እንዲሁም በመጽሐፍ ቅዱስ ሄኖክ እንደ ተሰወረ እናገኛለን። ክርስቶስ ከመወለዱ በፊት “አብርሃምም በእግዚአብሔር አመነ፤ ጽድቅም ሆኖ ተቆጠረለት” (ዘፍ.፲፭፥፮)ተብሏል። እንደ አብርሃም ያሉ ጻድቃን እንደ ይስሐቅ ያሉ ታዛዦች፣ እንደ ያዕቆብ ያሉ የእግዚአብሔር ሰዎች ነበሩ። ይህ ሁሉ የነበረው በ፶፻፭፻ ዘመን ውስጥ ነው። በመሆኑም ሁሉ በደለ ከተባለ በሕገ ልቡናም ሆነ በሕገ ኦሪት ብዙ ደጋግ ሰዎች ነበሩና ከመሆናቸው ጋር ይጋጫል። ስለዚህ ሁሉም የሚለው ቃል በደለኞችን ብቻ እንጂ ያልበደሉትን አይጨምርም።

 

ነገሩን በተሻለ መልኩ ግልጽ ለማድረግ እግዚአብሔር አምላካችን ስለ ዳዊት ሲናገር “ኢይጠፍእ ምስፍና ወምልክና እምአባሉ ለይሁዳ፤ መንግሠት ከይሁዳ አይጠፋም፤ ምስፍናም ከአብራኩ” (ዘፍ.፵፱፥፲) በሚለው እኮ ለዘለዓለም አይጠፋም ተብሎ ተነግሮ ግን ጠፍቷል። በእስራኤል ዘንድ አሁን በዘመናችን እንኳ ጥንት በተነገረው መንገድ አይደለም። በሀገራችንም ቢሆን የዳዊት ዘር ነን የሚሉ የነበሩበት ዘመን እንደ ነበር ቢታወቅም በየመሀሉ እጅግ የተቆራረጠበት ዘመን ነበር አሁንም በዚያ መንገድ የለም። ስለዚህ አንጻራዊ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል።

ስለ ዳዊት የተነገረው ለዘለዓለም የሚለው ቃል የዳዊትን ልጆች ብቻ የሚመለከት እንደ ሆነ ሁሉ “ሁሉ ተካክሎ በደለ” የሚለውም በደለኞችን ብቻ እንጂ ሁሉንም አይመለከትም። ከዚህም በተጨማሪ ምንም በራሳቸው ቅዱሳን ቢሆኑም ጽድቃቸው እንደ መርገም ጨርቅ ሆኖባቸው ወደ ገነት መግባት አልቻሉም ነበር። ክርስቶስ በሥጋ ተገልጦ ነፍሳት እስካዳነበት ጊዜ ድረስ ሁሉም የሲኦል እስረኞች ነበሩ።

በሌላ መልኩ በቀጥታ ወደ ተነሣው ጥያቄ ስንመለስ ልናየው የሚገባው ነገር እመቤታችን ከእነዚህ ንጹሐን ከምንላቸው ሁሉ በተለየ ሁኔታ ንጽሕት ናት። ሌሎቹ ጻድቃን ቢባሉም የአዳም መርገም አይጠፋባቸውም። በራሳቸው ንጹሐን ቢሆኑም የራሳቸው ንጽሕና ገነት መንግሥተ ሰማያት ስለማያስገባቸው የሲኦል እስረኞች ነበሩ። የራሳቸው ንጽሕና የራሳቸው ብቃት የገነትን በር ሊከፍትላቸው ስላልቻለ በአዳም መርገም ምክንያት የገነት በር ተዘግቶባቸዋል።

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ግን የአዳም መርገም በውስጧ ስለሌለ ከሁሉም የተለየች ናት። ቴዎዶጦስ የተባለ የቤተ ክርስቲያናችን ሊቅ “ወኢረኵሰት በምንትኒ እምዘፈጠራ፤ ከፈጠራት ጀምሮ በምንም በምን አልረከሰችም” (ሃ. አበው ፶፫፥፳፪)  በማለት ይነግረናል። ይህ ቃል ሲብራራ አዳም ከወደቀበት በፊት የነበረውን ቅድስና ይዛ ኖራለች ማለት ነው። “ወበከመ ነፍሀ ውስተ ገጹ ለአዳም ከማሁ አንቲኒ ሀሎኪ ወኢረሳህኪ፤ አዳም ከመውደቁ በፊት ንጽሐ ጠባዕይ ሳያድፍበት እንደነበር አንቺም እንደዚያ ነሽ” እንዲል። አዳም በተፈጠረበት ቅጽበት ያገኘውን ጸጋ ይዞ ሰባት ዓመት ይዞት የነበረውን ንጽሐ ጠባዕይ ሳታሳድፍ ይዛ የተገኘች ናት። ይህ ከፍጥረት የምትለይበት አንዱ መገለጫዋ ነው።

ስለዚህ ሁሉ በደለ የሚለው ቃል እመቤታችንን አይመለከትም። እግዚአብሔር የጠበቃት ንጽሕት ናት። “መንረፈስ ቅዱስ ዐቀባ እምከርሠ እማ፣ ከእናቷ ማኅፀን ጀምሮ መንፈስ ቅዱስ ጠብቋታልና” ከአባት ወደ ልጅ የሚመጣው መርገም የለባትም። ስለዚህ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተዋሐደው ሥጋ ጥንተ አብሶ የለበትም።

እመቤታችን ከጥንተ አብሶ ንጹሕ መሆኗን ለማስረዳት ተጨማሪ ምሳሌ ብንጠቅስ ጌዴዎን አሕዛብን ድል ታደርጋለህ ሲባል እርሱ ‹‹እንዴት እችላለሁ›› ብሎ ተከራክሮ ነበር። በዚህ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነው ተባለ። እመቤታችንን ግን መልአኩ ሲያበሥራት እግዚአብሔር ካንቺ ጋር ነው ብቻ አላላትም፤ ‹‹ጸጋን የተመላሽ ነሽ›› የሚለውንም ልዩ ቃል ተናግሯል። እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር የነበሩ ብዙ ሰዎች ነበሩ። ጸጋን የተመሉ ግን አልነበሩም። ስለዚህ በጨለማ ዘመን ጸጋን የተመላች፣ ከተፈጠረች ጀምሮ ንጽሕት የሆነች፣ የእናት የአባት መርገም ካለባቸው እናት አባት ተገኝታ እርሷ ግን መርገም ያላገኛት ንጽሕት ዕንቍዕ ከአዳም አብራክ ጀምራ የምታበራ ሁና ንጽሕናዋ፣ ቅድስናዋ፣ ከፍጥረታት ሁሉ የተለየች ስለ ሆነች ጥንተ አብሶ የሚባል ነገር አያውቃትም። በመሆኑም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተዋሐደው ሥጋም ከጥንተ አብሶ የነጻ ነው።

፮. ሐመር፡- "ከሥጋዋ ሥጋን ከነፍሷ ነፍስን ነሣ" ስንል ምን ማለታችን ነው?

መምህር ሥሙር አላምረው፡- ይህን በአጭሩ በሁለት መንገድ እንመልከተው። ከሥጋዋ ሥጋን ከነፍሷ ነፍስን ነሣ ስንል “ከ” የሚለውን በትኩረት መመልከት የተሻለ ግልጽ ያደርገዋል። እመቤታችንን ‹ሥጋዋን ነፍሷን ነሣ› ማለትና ‹ከሥጋዋ ሥጋን ከነፍሷ ነፍስን ነሣ› ማለት እጅግ የተለያዩ ናቸው። ሥጋዋንና ነፍሷን ነሣ ብንል ራሷን እመቤታችንን ተዋሐደ ማለት ይሆናል። ይህ ደግሞ እርሷም አምላክ ሆነች ያሰኛል። ይህም የእግዚአብሔር እናት ሳይሆን እግዚአብሔር ናት ወደ ማለት ይወስደናል። እንዲህ እንዳይሆን ከሥጋዋ ከፍሎ ከነፍሷም ከፍሎ ተዋሐደ ማለት እንጂ እርሷን ተዋሐደ ማለት አይደለም። 

አምላክ ሰው የሆነው ከነፍሷ ነፍስን ከሥጋዋ ሥጋን ከፍሎ ነው። ሰው ከእናቱና ከአባቱ ከፍሎ የሚነሣው አለ። በቤተ ክርስቲያን አስተምህሮም ሰው ሲወለድ ከአባቱ ዘርን ከእናቱ ደምን ነሥቶ ነው። ይህ የአባት ዘር በክርስቶስ ዘንድ የለም። ይሁን እንጂ ከድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋን ከነፍሷ ነፍስን ከፍሎ ተዋሐደ።

በሁለተኛ ደረጃ “ህየንተ ነፍስ ኮኖ መለኮቶ፤ በነፍስ ፈንታ መለኮቱ ነፍስ ሆነው እንጂ ነፍስን አልተዋሐደም”  የሚሉ መናፍቃን ለምሳሌ እንደ አቡሊናርዮሳውያን ያሉ አሉ። ለእነዚህ በአጭሩ መልስ የሚሆነው የእነ ሳዊሮስ መልስ ነው። ሳዊሮስ እንዲህ ብሎ ይጠይቃል “እኛ ክርስቶስ በሥጋ ሞተ እንላለን በሞተም ጊዜ ነፍሱ ወደ ሲኦል ወረደ፤ ሥጋው በመቃብር ነበር እንላለን። እናንተ ነፍስን አልነሣም የምትሉ ከሆነ መለኮት ከሥጋ ተለይቶት ነበር። ያንጊዜ ወደ ሲኦል የሄደው ከሥጋ ጋር አልነበረም ማለት ነውን? እንዲህ ከሆነ ሩቅ ብእሲ ነው ያስብላል። ዕሩቅ ብእሲ ከሆነም ውላጤ ያለበትን አምላክ እንዴት ልናመልከው እንችላለን?” በማለት ይጠይቃል። ይህ ደግሞ ቤዛነትን አያመጣም። እንዲህ ዓይነት በተከፍሎ አንድ ጊዜ አምላክ ሌላ ጊዜ ሰው የሚሆን መለኮት የሚለየው እንደ ገና የሚዋሐደው ከሆነ ቤዛነታችንም ፍጹም አይሆንም። ነገር ግን ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ መሆኑን የሚያስረዳን መለኮት ሥጋንም ነፍስንም ተዋሐደ የሚለው ነው።

በሌላ መልኩ ምሥጢረ ሥጋዌን ይንደዋል። ምክንያቱም አንድ ሰው ‹ሰው ነው› የሚባለው ነፍስም ሥጋም ሲኖረው ነው። ከዚያ ውጭ በደማዊት ነፍስ እንስሳ ነው የሚሆነው። በደማዊት ነፍስ ደግሞ እንስሳትም ሕይወት አላቸው። ክርስቶስ ግን እንዲህ እንዳልሆነ “ወኢኮነ ካልዐ እንስሳ ዘበአንትጎ አላ ምሉዕ ውእቱ ወፍጹም ምስሌነ ዘበ ሕላዌ፤ በማጉደል ሌላ እንስሳ የሆነ አይደለም። በሕልውና ከእኛ ጋር ምሉዕና ፍጹም ነው እንጂ” (ሃ.አበው ዘቅዱስ ኤፍሬም ፵፯፥፴፪) እንስሳት በደም ሙቀትና በደም ዝውውር ሕይወት አላቸው እንጂ ሕያዊት ነፍስ የላቸውም ። ክርስቶስ አምላካችን ግን እንደዚያ አይደለም። ስለዚህ ነፍስንም ሥጋንም ባይነሣ ፍጹም ሰው ልንለው አንችልም።

፯. ሐመር፡- እግዚአብሔር ሰማይና ምድር የማይወስኑት አምላክ ነው። ግን አንዲት ብላቴና ወሰነችው፤ እንዲህ ከሆነ ማለትም በአንዲት ብላቴና የሚወሰን ከሆነ አምላክ ነው ማለት እንዴት እንችላለን?

መምህር ሥሙር አላምረው፡- ይህ የአባ ሕርያቆስም ጥያቄ ነው። አባ ሕርያቆስ “መንበር ኪሩባዊ ዘያንጸበርቅ ወዘየዐውዶ ነደ እሳት አይቴኑ ተደለወ ወአይቴኑ ተተክለ  በውስተ ከርሥኪ እንዘ ንእስት መርዓት አንቲ፤ የሚያንጸበርቅ ነደ እሳት የሚከበው ኪሩቤል የተሸከሙት ዙፋን በሆድሽ ውስጥ ወዴት ተዘጋጀ? ወዴትስ ተተከለ? አንቺ ታናሽ ሙሽራ ስትሆኚ” (ቅዳሴ ማርያም) እንዲል። አባ ሕርያቆስ ጠይቆና አድንቆ ብቻ አልቀረም። እልፍ ይልና “ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እንበል” ብሎ ከዚህ በላይ ሊባል እንደማይቻል ያስረዳል። በእርግጥ ሊቃውንቱንም እጅግ ያስደነቃቸው እንዲህ ያለው ልዩ ምሥጢር ነው።

ከላይም እንደ ተገለጸው አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫም እንዲህ ያለውን ምሥጢር ሲያደንቅ “ለቀዳማዊ ልደት አመሥጠሮ ወለደኃራዊ ልደት አመንከሮ፤ የመጀመሪያውን ልደት ረቂቅ አደረገው ሁለተኛውን ልደት ደግሞ ድንቅ አደረገው” (መጽሐፈ ምሥጢር) በማለት ያስረዳል። እጅግ ድንቅ የሚያደርገው በዓለም ሁሉ ምሉዕ የሆነ መለኮት በዓለም ምሉዕ ካልሆነች አንዲት ብላቴና ማኅፀን ተወስኖ ማደሩ ነው።

ይሁን እንጂ ተወሰነ ስንል መላእክትን ሳይቀር እንዳስደነቀ በታች በምድር በእመቤታችን ማኅፀን ሆኖ ያዩታል፤ ቀና ሲሉ ደግሞ በላይ በሰማይ በኪሩቤል ዙፋን ተቀምጦ ያዩታል። እዚህ በእመቤታችን እቅፍ ያዩታል በላይ በሰማይ ደግሞ ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ዕሪና ሳይለይ የኪሩቤልን ምስጋና ሲቀበል ያዩታል። ስለዚህ ተወሰነ ስንል በዚህ መንገድ እንጂ የሰማይ ዙፋኑን ትቶ፣ ምሉዕነቱን፣ አምላክነቱን፣ ወዘተ ትቶ ማለት አይደለም። እንደ ሰውነቱ ተወሰነ እንደ ምላክነቱ ደግሞ ዓለምን ሞልቷል።

በሌላ መልኩ ‹ሰማይና ምድር የማይወስኑት አምላክ በአንዲት ብላቴና እንዴት ተወሰነ?› የሚለውን ሊቃውንቱ በዐይን ብሌንና በፀሐይ ብርሃን ይመስሉታል።  እንደሚታወቀው የዐይን ብሌን ጠባብ ነው። የፀሐይ ብርሃን ደግሞ አንጻረዊ በሆነ መልኩ ምሉዕ ነው። ይህም ሆኖ ዐይናችን ከፀሐይ ብርሃን ሙሉ በሙሉ አይቀበልም። ብርሃን የሚቀበለው የተወሰነው የዐይናችን ክፍል ነው። ይህ ግዙፍና ሰፊ የሆነው የፀሐይ ብርሃን ከጠባቧ የዐይናችን ብሌን ጋር በተዋሐዱ ጊዜ ብዙ ነገር ማየት ይችላል። የሰው ዐይን የፍጡር ዐይን በመሆኑ ጠፈር ደፈር ቢከለክለውም ብዙ ነገር ማየት ይችላል። እመቤታችን በዐይን ብሌን ትመሰላለች። መለኮት ደግሞ “እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ” እንዳለ በፀሐይ ብርሃን ይመሰላል። ስለዚህ ምሉዕ የሆነው መለኮት በዐይን ብሌን ከተመሰለችው ከእመቤታችን ከሥጋዋ ሥጋን ከነፍሷ ነፍስን ነሥቶ ተዋሐደ። ምሉዕ መለኮት ተወሰነ፣ ውስኑ ሥጋ መላ እንላለን።

በመሠረቱ ተወሰነ ብቻ አይደለም የምንለው ምሉዕ መለኮት በሥጋ ማርያም ሲወሰን በኪሩቤል ዙፋን ተቀምጦ ይመሰገን ነበር። ነቢዩ ኢሳይያስ “ከዚህም በኋላ ንጉሡ ኦዝያን በሞተበት ዓመት እግዚአብሔርን በረዥምና ከፍ ባለ ዙፋን ተቀምጦ አየሁት። ምስጋናውም ቤቱን ሞልቶት ነበር። ሱራፌልም በዙሪያው ቆመው ነበር…አንዱም ለአንዱ ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ምድር ሁሉ ከክብሩ ተሞልታለች እያለ ይጮኽ ነበር” (ኢሳ.፮፥፩-፫) በማለት እንደ ገለጸው እግዚአብሔር በዙፋኑ ሆኖ ሳለ ምስጋናው ቤቱን (መቅደሱን) ሞልቶት ነበር ይላል።

መቅደስ የተባለችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ናት። መቅደሱን የሚያየው በሰማይ ነው። ሰማይ ተከፍቶ በመቅደሱ ውስጥ ምስጋናው ሞልቶ ይመለከታል። በታች በምድር ደግሞ በእመቤታችን ማኅፀን ሲመሰገን ያያል። ስለዚህ እግዚአብሔር በፈቀደ ለእናትነት መርጦ ከባሕርይ አባቱ ከአብ ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ሳይለይ በሥጋ ተወሰነ ተባለ ይህ እጅግ የሚደንቅ ስለ ሆነ ሊቃውንቱም ዕፁብ ዕፀብ ብለውት አልፈዋል።

ሐመር፡- መምህር በመጨረሻ ቀረ የሚሉት ነገር ካለ?

መምህር ሥሙር አላምረው፡- ነገረ ሥጋዌን በዘመናችን ሙሉ ብንናገረው እንዳልተናገርነው ይቆጠራል እንጂ ገልጸን ልንጨርሰው አንችልም። በመሆኑም ይህኛው ተባለ ይህኛው ደግሞ ቀረ የሚባል ነገር አይኖርም። ነገር ግን ምሥጢረ ሥጋዌ (ምሥጢረ ተዋሕዶ) ከትምህርተ ሃይማኖቱ በዘለለ የሰው ልጆችን ማሕበራዊ አንድነት፣ ኅብረትም የሚያስተምር ነው። ምክንያቱም በባሕርይ የማይመሳሰሉ አካላት  አንዱ ሌላውን ሳያጠፋው በተዋሕዶ ከሁለት አካል አንድ አካል ከሁለት ባሕርይ አንድ ባሕርይ ሆነ። እንዲሁ ሰዎችም ምንም ብዙ የሚያለያዩ ነገሮች ቢኖሯቸውም አንዱ ሌላውን ሳይጎዳ በኅብረት፣ በአንድነት እንዲኖሩ የሚያስተምር ነው። ስለዚህ እርስ በእርሳችን ተቻችለን፣ ተከባብረን፣ በአንድነት ኖረን የማያልፈውን ርስት መንግሥተ ሰማያት እንድንወርስ በዚህ ልክ መዘጋጀት አለብን። ለዚህም እግዚአብሔር ይርዳን።

ሐመር፡- መምህር ጥሪያችንን አክብረው ስለ ተገኙልን፣ ላነሣናቸው ጥያቄዎችም ተገቢ ምላሽ ስለ ሰጡን በእግዚአብሔር ስም እናመሰግናለን።

መምህር ሥሙር፡-እኔም አመሰግናለሁ፤ ማኅበሩንም እግዚአብሔር ይጠብቅልን አሜን። 

 

Read 851 times