Saturday, 27 February 2021 00:00

የጥያቄዎቻችሁ መልስ

Written by  ዲ/ን ዐብይ ሙሉቀን
ውድ አንባብያን በጥያቄዎቻችሁ መልስ ዐምዳችን የትዳርንና ትዳር የሚፈርሱባቸውን ምክንያቶች በተመለከተ የሚነሡ ጥያቄዎችን መሠረት አድርገን ምላሽ ይሰጡን ዘንድ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በምሥራቀ ፀሐይ ቀበና መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ስብከተ ወንጌል አገልጋይ የሆኑትን መጋቤ አእላፍ ቀሲስ ፋሲል ታደሰን ጋብዘናል። መጋቤ አእላፍ ቀሲስ ፋሲል ታደሰ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የቴሌቪዥን መርሐ ግብር አዘጋጅም ናቸው። ፈቃደኛ ሆነው ከቦታችን ተገኝተውልን ቆይታችንን እንዲህ አዘጋጅተነዋል፤ መልካም ንባብ። ሐመር፡- መጋቤ አእላፍ ቀሲስ ፋሲል ታደሰን  ትዳርንና በትዳር መካከል የሚነሡ ችግሮችን መሠረት ያደረጉና በማኅበረሰቡ ዘንድ የሚነሡ ጥያቄዎችን መሠረት አድርገን ለምናነሣቸው ሐሳቦች ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ ስለ ሆኑልን አስቀድመን በእግዚአብሔር ስም እናመሰግናለን።  መጋቤ አእላፍ ቀሲስ ፋሲል ታደሰ፡-  እኔም  ስለጋበዛችሁኝ አመሰግናለሁ። ፩. ሐመር፡- ትዳር ማለት ምን ማለት ነው? መጋቤ  አእላፍ ቀሲስ ፋሲል ታደሰ፡-  ትዳር፡- ብዙ አጥኚዎች፣ በጋብቻ ዙሪያ የጻፉና የሰበኩ መምህራንም በተለያየ መልኩ ገልጸውታል። እኔ በአለኝ መረዳት ሁለት ተጋቢዎች አንድ ወንድና አንዲት ሴት በጋብቻ አንድ የሚሆኑበት ተብሎ ሊገለጽ ይችላል። በሌላ አገላለጽ ደግሞ ሀብት ንብረት ማፍራት፣ ልጆች ወልዶ፣ በአንድነት ቤተሰብ መሥርቶ መኖር ትዳር ይባላል። አንዳንድ ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱስ ትዳር ሀብት ንብረት ተብሎ ተገልጾ እናገኛለን። ተጋቢዎች ሀብት ንብረት አፍርተው የሚኖሩበትን ሕይወት ያስረዳል። ለምሳሌ “ከዐሥራ ሁለት ዓመትም ጀምሮ ደም የሚፈስሳት ሴት ነበረች፤ ትዳሯንም ሁሉ ለባለ መድኃኒቶች ሰጥታ ማንም ሊፈውሳት አልተቻለውም ነበር” (ሉቃ.፰፥፵፫) ተብሎ ተጽፎ እንደምናነበው ትዳር ሀብት ንብረት ተብሎ ተገልጾአል። በአጠቃላይ ትዳር አንድ ወንድና አንዲስ ሴት በጋብቻ ተጣምረውና ጎጆ ቀልሰው የሚኖሩበት የአንድነት ኑሮ ማለት ነው።  ፪. ሐመር፡- ትዳር በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን  አስተምህሮ እይታ እንዴት ይገለጻል? መጋቤ አእላፍ ቀሲስ ፋሲል ታደሰ፡- ትዳር (ጋብቻ) በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ቅዱስና ክቡር ነው ተብሎ ይገለጻል። አስቀድሞ መሥራቹ ልዑል እግዚአብሔር ነው። ፈጻሚዎቹ ደግሞ የሰው ልጆች ናቸው። እግዚአብሔር የባረከው፣  የቀደሰውና ሕግ አድርጎ የሰጠው ሁሉ መልካም ነው። አንድ ወንድና አንዲት ሴት በፍቅር ላይ ተመሥርተው የሚመሠርቱት ጋብቻም ቅዱስ ነው። ከአዳምና ከሔዋን ጀምሮ ጋብቻን ባርኮ የሰጠ እግዚአብሔር ነው። የሰው ልጅ ዕድሜው ሲደርስ በቅዱስ ጋብቻ ወይም በምንኵስና እንዲኖር ይመከራል። ሱባኤ ገብቶ፣ ልቡን መርምሮ፣ ካህናትን አማክሮ አንዱን ሕይወት ይወስናል። ስለዚህ በየትኛውም ሕይወት ማለትም በጋብቻም ሆነ በምንኵና ሕይወት መኖር የተቀደሰና የተባረከ ነው።  አስቀድሞ የተመሠረተው በእግዚአብሔር ስለሆነ ዛሬም ራሱን መርምሮ ከካህን ጋር ተመካክሮ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ጠይቆ በትዳር እንዲወሰን መጽሐፍ ቅዱስ ይመክራል ያስተምራል። አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በማስተማር ዘመኑ የመጀመሪያውን ተአምር በቃና ዘገሊላ ተገኝቶ በሰርግ ቤት ማድረጉ ጋብቻ የተባረከ መሆኑን ያሳየናል። እንዲሁም አስቀድሞ “ሰው ብቻውን ይኖር ዘንድ መልካም አይደለም፤ የሚረዳውን ጓደኛ እንፍጠርለት እንጂ” (ዘፍ.፪፥፲፰) በማለት የተናገረውን አምላካዊ ቃል ሕግ አድርጎ እንደሰጠን ሁሉ በማስተማር ዘመኑም ‹‹ሰው አባቱንና እናቱን ትቶ ሚስቱን ይከተላል፤ ሁለቱም አንድ አካል ይሆናሉ። እንኪያስ ሁለት አይደሉም፤ አንድ አካል ናቸው እንጂ፤ እግዚአብሔርም አንድ ያደረገውን ሰው አይለይ” (ማቴ.፲፱፥፭-፮) ብሎ ማስተማሩ ትዳር ቅዱስ መሆኑ ይገልጻል።  እንደ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ትዳር ክብረ ንጽሕናቸውን ጠብቀው እስከ ጋብቻቸው በድንግልና ለኖሩ በተክሊል፣ በልዩ ልዩ ምክንያት ድንግልናቸውን ላልጠበቁ ንስሓ ገብተው፣ በቁርባን በመንፈሳዊ ሥርዓት ሲፈጸም ቅዱስ፣ ክቡር ነው። ልዩ ልዩ ምክንያቶች የተባሉትም በሞት፣ በዝሙትና በመሳሰሉት እንደ ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ ፳፬ ትእዛዝ ድጋሜ ጋብቻ ለሚፈጽሙት በመዓስብ ሥርዓት ይፈጸማል። ማሳረጊያው ግን ቅዱስ ቊርባን ነው። ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን  በንስሓና በመንፈሳዊ ሥርዐት የሚፈጸም ጋብቻ ክቡር ነው፤ ቅዱስ ነው፤ የእግዚአብሔር ፈቃድ ያለበት ነው፤ እያለች ትመሰክራለች።  ጋብቻ ቅዱስ የሚሆነው በመንፈሳዊ ሥርዐት ሲፈጸም  ብቻ ነው። ሰው ሁሉ የሥላሴ ፍጡር ነው። ሰው ሁሉ ግን ቅዱስ ነው ማለት አይቻልም። ይህም ቅድስና የተለየ ተጋድሎ ስለሚጠይቅ ነው። ተራሮች ሁሉ የእግዚአብሔር ፍጥረታት ናቸው። ግን ተራሮች ሁሉ መሥዋዕት አይሠዋባቸውም። ቦታዎችን ሁሉ ቅዱሳት መካናት፣ አድባራትና ገዳማት አንላቸውም። ታቦተ ሕጉ ያለበትን፣ ሥጋ ወደሙ የሚፈተትበትን ቅዱሳን ከሰብአ ዓለም ተለይተው ዕድሜ ልካቸውን የጸለዩበትን፣ ሱባኤ የገቡበትን፣ ቃል ኪዳን የተቀበሉበትን፣ ወዘተ ቅዱሳት መካናት፣ አድባራትና ገዳማት እያልን እንጠራቸዋለን። ከተራራ መርጦ በገዳመ ቆሮንቶስ ጾምና ጸሎት እንደያዘ፣ በደብረ ሲና ጽላተ ኦሪትን እንደሰጠ፣ በደብረ ታቦር ብርሃነ መለኮቱን እንደገለጠ ሁሉ በምክረ ካህን በፈቃደ ካህን፣ በንስሓ ሕይወት፣ በመንፈሳዊ ሥርዐት በቅዱስ ቊርባን የተፈጸመ ጋብቻ ቅዱስ ነው፤ ክቡርም ነው።    ፫. ሐመር፡- እንደ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ባልና ሚስት እንዴት ይገለጻሉ? በምንስ ይመሰላሉ? መጋቤ አእላፍ ቀሲስ ፋሲል ታደሰ፡- ባልና ሚስ በቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ እንዴት ይገለጻሉ በምንስ ይመሰላሉ? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ መሠረቱ መጽሐፍ ቅዱስ ነው። ለምሳሌ፡- በኦሪቱ ነቢያት የእስራኤልንና የእግዚአብሔርን ግንኙነት እንደባልና ሚስት መስለው አስተምረውበታል። እስራኤል ከሕገ እግዚአብሔር ፈቀቅ ባሉ ጊዜ ጋለሞታ ተብለው ተሰድበዋል። በድንቅ አጠራሩ ጠርቶ፣ በቸርነቱ ረድቶ ከብዙ መከራ የታደጋቸው ሲበድሉ ግን እግዚአብሔር በነቢዩ በኤርምያስ ላይ አድሮ የተናገረውን እንመልከት። ከዳተኛይቱ እስራኤል ያደረገችውን አየህን ወደረዘመው ተራራ ሁሉ ወደለመለመ ዛፍም ሁሉ በታች ሄደች፤ በዚያም አመነዘረች። ይህንም ሁሉ ካደረገች በኋላ ወደእኔ ተመለሽ አልኋት፤ ነገር ግን አልተመለሰችም፤ አታላይ እህቷ ይሁዳም አየች ከዳተኛይቱ እስራኤል እንዳመነዘረች አየሁ። የፍችዋንም ደብዳቤ በእጅዋ ሰጥቼ ሰደድኋት ጎስቋላ እህቷ ይሁዳ ግን በዚያ አልፈራችም፤ እርሷም ደግሞ ሄዳ አመነዘረች ዝሙቷም ከንቱ ሆነ፤ እርሷም ከድንጋይና ከግንድ ጋር አመነዘረች በዚህም ሁሉ ከዳተኛይቱ ይሁዳ በሐሰት እንጅ በእውነት ወደእኔ አልተመለሰችም። (ኤር. ፫፥፮-፱) ጋለሞታ ማለት ባል ፈትታ የምትኖር ሴት ማለት ነው። እስራኤል ከአምልኮተ እግዚአብሔር ወጥተው በአምልኮተ ጣዖት ወይም ከፈቃደ እግዚአብሔር ውጭ ሆነው መኖር በጀመሩ ጊዜ ባሏን የፈታች ሴት ተብለዋል። ባልና ሚስት አይለያዩም፤ የሰው ልጅም ከአምልኮተ እግዚአብሔር ሊወጣ አይገባውም። አለዚያ ግን ጋለሞታ ወይም ባል አልባ ወይም ሚስት አልባ ይባላል። ስለዚህ እስራኤል ከአምልኮተ እግዚአብሔር በወጡ ጊዜ እግዚአብሔር አምላካችን በነቢዩ በኤርምያስ ላይ አድሮ “ጋለሞታ” በማለት ገሠጻቸው። ነቢዩ እግዚአብሔር በእስራኤል ስለመገለጡ፣ በእስራኤል ድንቅ ምሥጢር ስለማድረጉ እነርሱን እየመገበ በእነርሱ እየተመሰገነ መኖሩን እግዚአብሔር እንደ ባል እስራኤል እንደሚስት ሆነው ቅርርባቸውን የሚያሳይ ነው። ይህም ትዳር መንፈሳዊና ሰማያዊ ምሥጢር ያለው መሆኑን ነው የሚያሳየው።  በሐዲስ ኪዳን ደግሞ የበለጠ ይልቅም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ባልና ሚስትን ይልቁንም በፍቅር የሚዋሐዱ አንድ ወንድና አንድ ሴትን በክርስቶስና በቤተ ክርስቲያን መስሎ አስተምሯል። ይህንም በኤፌሶን መልእክቱ ‹‹ዐቢይ ውእቱ ዝ ነገር፤ ወአንሰ እብሎ ላዕለ ክርስቶስ ወላዕለ ቤተ ክርስቲያኑ፤ ይም ምሥጢር ታላቅ ነው፤ እኔም ይህንኑ ስለክርስቶስና ስለ ቤተ ክርስቲያኑ እናገራለሁ›› (ኤፌ.፭፥፴፪) በማለት የምሥጢሩን ታላቅነትና ባልና ሚስት ሊኖሩበት የሚገባውንም ልዩ የአኗኗር ምሥጢር በክርስቶስና በቤተ ክርስቲያን መስሎ አስተማረ። ከላይም እንዲሁ “ወንዶችም ክርስቶስ ቤተ ክርስቱያንን እንደ ወደዳት ራሱንም ስለ እርስዋ ቤዛ አድርጎ እንደሰጠላት ሚስቶቻቸውን ይውደዱ” ይላል። (ኤፌ.፭፥፳፭) ይህ ማለት ሴትም ለባሏ ትገዛ ባልም ሚስቱን ይውደዳት በማለት ነው።  ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን የወደዳት እስከሞት ድረስ ነው። ባልም ሚስቱን እስከሞት ድረስ ሊወዳት ይገባል። ሚስትም ለባሏ ትገዛ ሲል ቤተ ክርስቲያን ለክርስቶስ በፍቅር እንዳምትገዛ ሁሉ ሚስት ለባሏ በፍቅር ትገዛ ሲል አስተምሯል። ቤተ ክርስቲያን ስንል ማኅበረ ምእመናንን ማለታችን ነው። ማኅበረ ምእመናን የሚጾሙት፣ የሚጸልዩት፣ ንስሓ የሚገቡት ተገደው አይደለም። ካህናቱ አስገድደዋቸው ገዝተዋቸው አይደለም። በራሳቸው ፈቃድ ነው። ደስ ብሏቸው የሚያደርጉት ነው። አጽዋማቱ መጡ፣ ብለው ሊጾሙ የሚዘጋጁት፣ በዓላቱ መጡ ብለው ገንዘባቸውን አውጥተው ሊያከብሩ የሚዘጋጁት፣ ዐሥራት በኩራታቸውን የሚያወጡት እግዚአብሔርን ወደው ነው። ስለዚህ ሴት ለቧሏ የምትገዛ በፍቅር ነው። ባልም ከመውደድ አልፎ ይሙትላት ተብሏል። እንግዲህ ክርስቶስ ራሱን አሳልፎ እንደሰጠ ባልም ራሱን አሳልፎ እስኪሰጥ ድረስ የሚወዱትና ሁለቱም በጽኑ ፍቅር የሚኖሩበት ስለሆነ ባልና ሚስት በክርስቶስና በቤተ ክርስቲያን ተመስለዋል።  በሌላ አንቀጽ እንደ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ እንደ ነፍስና ሥጋ ተዋሕደው የሚኖሩ ናቸው። ነፍስና ሥጋ ተዋሕደው ሰው የሚለውንና በሰብእና የሚገልጸው ነገር  እንደሚያስገኙት ሁሉ ባልና ሚስትም በአንድነት ተዋሕደውና ተስማምተው የመኖር ድንቅ ምሥጢር እንዳለው በልዩ ልዩ የሊቃውንት መጽሐፍ እንረዳለን። ክብር ይግባውና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም አንድ አካል ናቸው በማለት ድንቅ ቃል ተናገረ። አንድ አካል ናቸው ሲልም ለምሳሌ፡- ማንም አካሉን እንደሚወድ ሁሉ ከአካሌ ላይ ይቆረጥ፣ ከእግሬ ላይ ይቆረጥ እንደማይል ሁሉ በሌላ አገላለጽም ቅዱስ ጳውሎስ “ሚስቱንም የሚወድ ራሱን ወደደ” (ኤፌ.፭፥፳፰) እንዳለ ሁሉ ባል የሚስት አካል ነው ሚስትም የባል አካል ናት። ማንም ሰው ለዐይኑ እንደሚሳሳ እንዲሁ አንዲት ሴት ለእጇ፣ ለእግሯ፣ ለሰውነቷ ሌላው ቀርቶ ለጌጣጌጧ እንደምትሳሳ ሁሉ ባሏንም እንደሰውነቷ እንደ አካሏ እንድታይ ጌታችን መድኃኒታችን አንድ አካል ናቸው ያለውን መሠረት አድርገው ሐዋርያትና ሊቃውንት ተንትነውታል።  ለምሳሌ፡- ቅዱስ ጳውሎስ በ (፩ቆሮ.፯፥፬) ላይ “ሚስት በራስዋ አካል ሥልጣን የላትም፤ ሥልጣን ለባልዋ ነው እንጂ፤ እንዲሁም ባል በራሱ አካል ሥልጣን የለውም፤ ሥልጣን ለሚስቱ ነው እንጂ” ሲል በእርሱ አካል ላይ ሚስት ሥልጣን አላት። በሚስት አካል ላይ ባል ሥልጣን አለው። ይህም አንድ አካል ናቸው የሚለውን ይበልጥ እንድንረዳው የሚያስገነዝበን ነው። ራስ ወዳድነት የሚጠፋበት፣ መዋደድ፣ መተሳሰብ፣ ባል ለእኔ ሳይሆን ለእርሷ የሚልበት፣ ሚስትም ከራሷ ይልቅ ለባሏ የምታስብበት፣ የባል ችግር ለሚስት፣ የሚስትም ችግር ለባል፣ የባል ደስታ ለሚስት፣ የሚስትም ደስታ ለባል፣ የሚሆንበት ነው። በአንድ  የሰውነት ክፍል መታመም የትኛውም የሰውነት ክፍል ምቾት አይስማማውም። ለምሳሌ፡- እግር ቢታመም መላውን ሰውነቱን እንደ ሕመም ይሰማዋል። ይህ ሁሉ የማይነጣጠል ጽኑ አንድነት ያለበት በእስራኤልና በእግዚአብሔር በክርስቶስና በቤተ ክርስቲያን፣ በነፍስና በሥጋ የተመሰለ መሆኑን ያስረዳናል።  ፬. ሐመር፡- በዚህ ዘመን የትዳር መፍረስ እየተስፋፋ እንደሆነ ይስተዋላል። ለትዳር መፍረስ ምክንያቶች ናቸው ብለው ከሚያስቧቸው መካከል የተወሰኑትን ቢገልጹልን? መጋቤ አእላፍ ቀሲስ ፋሲል ታደሰ፡- ለትዳር መፍረስ ምክንያት የሚሆኑ ብዙ ነገሮች አሉ። አንዳንዶች እንደ እግዚብሔር ፈቃድ በሽምግልና ከመፍረስ ሲድኑ አንዳንዶቹ ደግሞ በየፍርድ ቤቱ ሰማንያችን ይቀደድልን ብለው ሲሄዱና ትዳራቸውንም ሲያፈርሱ ይስሠተዋላል። ለዚህ ሁሉ ችግሮችና የችግሮቹን ምንጮች ስናነሣ እንደ ቤተ ክርስቲያን አስተምሮ ከመጀሪያው ለመነሣት፡- ፩. በጠላት ዲያብሎስ ፈተና፡- ጠላታችን ዲያብሎስ በዙሪያችን ሆኖ የእኛን መሰናከልና መውደቅ ይጠባበቃል። በመሆኑም በሥጋ ወደሙ፣ በንስሓ ሕይወት፣ በአጠቃላይ በጥሩ መንፈሳዊ ሕይወት ከብረው የኖሩትን ባልና ሚስቶች ሳይቀር መርዙን እየረጨ ሊፈትናቸው ይችላል። ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ “እንግዲህ ዐዋቂዎች ሁኑ ትጉም፤ ጠላታችሁ ጋኔን የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሳ አንበሳ ይዞራልና” (፩ጴጥ.፭፥፰) በማለት እንደገለጸው ዲያብሎስ እኛን ለመጣል ስለማያርፍ በዚህ ምክንያት ሊፈርስ ይችላል።  ፪. በራስ ደካማ ጐን ፡- ይህ ሲባል በባል ወይም በሚስት በኩል ባለ ድክመት፣ ራስን ለይቅርታ ባለማዘጋጀት በማይረባ ምኞት በመጠለፍ ፈተናቸው እየጠነከረ ሲሄድ ይስተዋላል። ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ “የሚፈተን ሰው ቢኖር እግዚአብሔር ይፈትነኛል አይበል፤ እግዚአብሔር ለክፉ ነገር አይፈትንምና፤ እርሱ ማንንም አይፈትንም። ነገር ግን እያንዳንዱ በራሱ ምኞት ሲሳብና ሲታለል ይፈተናል። ምኞት ከፀነሰች ኃጢአትን ትወልዳለች፤ ኃጢአትም ከተፈጸመች ሞትን ትወልዳለች” (ያዕ.፩፥፲፫-፲፭) በማለት እንደተናገረው ክፉ ምኞታችን ለራሳችን የሕይወት መሰናክል ይሆናል።  እንዲሁ ይህው ሐዋርያ ‹‹በእናንተ ዘንድ ጥልና መጋደል ከወዴት ይመጣሉ? በሰውነታችሁ ውስጥ የሚሠራውን ዝሙት ከመውደድ የተነሣ ከዚህ አይደለምን? ትመኛላችሁ እንጂ አታገኙም፤ ትቀናናላችሁ፤ ትገዳደላላችሁ፤ በብርቱም ትፈልጋላችሁ፤ ልታገኙም አትችሉም፤ ትጣላላችሁ፣ ትዋጉማላችሁ፤ ነገር ግን አትለምኑምና የምትፈልጉትን አታገኙም፤ ትለምናላችሁ ለፍትወታችሁ ትከፍሉ ዘንድ ለክፉ ትለምናላችሁና አታገኙም” (ያዕ.፬፥፩-፫) በማለት እንደተናገረ ከራሳችን ክፉ ምኞት፣ ጸሎት አለማድረግ፣ ብናደርግም እንኳን ለመልካም ነገር ሳይሆን ለክፉው ነገር ስለምንለምን መልካሙን አታገኙም ተባልን። ስለዚህ ራሳችን ያለመገንዘብ፣ ራሳችን ለትዳራችን በአግባቡ ካለመጸለይ፣ ወዘተ ከመሳሰሉት ሁሉ ለትዳር መፈታት ምክንያት ሊሆኑ የሚችሉ ነገሮች ይኖራሉ። ሌሎቹንም ብዙ ጊዜ ለትዳር መፍረስ ምክንያት የሚሆኑትን የተወሰኑትን ለመጥቀስ ልሞክር፡-   ፫. ሳይተዋወቁ መጋባት፡- ቀድሞ በሁለቱም በኩል ያለውን ጠንካራና ደካማ ጐን ሳይጠናኑ በችኮላና በአንዳንድ ጊዜያዊ ስሜቶች ወስኖ የሚገቡበት ትዳር በኋላ ለሚፈጠረው የሐሳብ መለያየት “ሳላውቀው ነው፤ ሳላውቃት ነው” መባባል ላይ ስለሚደርሱ የፍች ምክንያት ሲሆን ይታያል።  በእርግጥ ሰው ተጠንቶ አያልቅም። ይሁን እንጂ መሠረታዊ የሆኑ ጉዳዮች ላይ ግን መሠረታዊ የሆነ ግንዛቤ በሁለቱም በኩል ሊኖር ይገባል። ይህ ሳይሆን ይቀርና መጋባታቸው ከመሰማቱ መፋታታቸው የሚሰማ ባልና ሚስቶች እየተበራከቱ መጥተዋል።  ፬.  ስለ ሦስተኛ ወገን ሳያስቡ መጋባት፡- ይህ ማለት ስለ ልጅ፣ ስለ እናትና አባት፣ ስለ ቤተ ሰብ፣ ስለማኅበራዊ ኑሮ ወዘተ ሳያስቡ መጋባት የሚያስከትለው ችግር ነው። ለምሳሌ ከተጋቡ በኋላ ልጅ እንውለድ አንውለድ ተባብለው የሚጋጩ አሉ። በሥራ ጠባይ፣ በሀብት እጥረት፣ በትምህርት ወዘተ ሰበብ ሲሉ ለመውለድ አንዱ ሲፈልግ ሌላኛው ሳይፈልግ ግጭት ይፈጠራል። ይህ ደግሞ ገና መጀመሪያ ሲጋቡ “ሰነፈች፣ ደከመች፣ መከነች፣ ጠቆረች፣ ከሳች፣ ወዘተ” ብዬ ላልፈታት የሚለውን ቃል ኪዳን ልብ አለማለትን ያስረዳል። ከጋብቻ በኋላ ገንዘቡ ሲቀንስ፣ ውበቱ ሲቀንስ፣ ታዋቂነቱ ሲቀንስ ወዘተ የጠባይ መለዋወጥ የፍቅር መቀነስ ይከሠታል። “ራስን መተው፣ ራስን መካድ” የሚለውን ይዘነጉትና በሐሳብ ለመለያየታቸው መሠረታዊ ጉዳይ ባልሆነው ሁሉ ሲጋጩ ይስተዋላሉ። ይህ ሁሉ ትርጉም ሲያጣ ፍቺ ይከሠታል።  ፭. ሀብትን መሠረት አድርጐ መጋባት፡- በዚህ ዓለም ሲኖሩ ሀብት ንብረት ያስፈልጋል። ነገር ግን ቀዳሚ ጉዳይ መሆን የለበትም። ሀብትን መሠረት አድርጐ መጋባት ሀብቱ እየጐደለ ሲሄድ ቤት ላይ በሚጐድሉ ነገሮች መለያየት፣ መጨቃጨቅ ይጀምራሉ። ይህ ብቻ ሳይሆን ሀብት ቢኖርም ሀብት ለጊዜው እንጂ ዘላቂ ፍቅርን አይሰጥም። ሲያውቁበት እንጂ ሳያውቁበት መንግሥተ ሰማያትንም ለመውረስ ፈተና ይሆናል። መድኅነ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ “ገንዘብ ላለው ሰው ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት እንዴት ጭንቅ ነው?” (ማር.፲፥፳፫) በማለት ያስተማረው ወደ ሰማያዊውና ወደ ዘለዓለማዊው ዓለም ለመግባትም መሰናክል የሞሆንበት አጋጣሚ ስላለ ነው። ደግሞም በገንዘቡ እናገኘዋለን ብለው የጠበቁት ነገር አልገኝላቸው ሲል ትዳራቸውን ይፈታሉ።  ፮. አለመተማመን፡- በመካከላቸው አለመተማመን፣ ካለ ትዳራቸው ሊፈርስ ይችላል። በሆነ ባልሆነው መጨቃጨቅ ከእገሌ ጋር አየሁህ፤ ከእገሌ ጋር አየሁሽ ወዘተ መባባል የጭቅጭቃቸው መጠን እየሰፋ ይሄዳል። በባልም ሆነ በሚስት በኩል በድብቅ የሚፈጸም ነገር ካለ በጎም ቢሆን መቆም አለበት። በበጎው ላይ መደባበቅ ካለ በመጥፎውም ላይ ሊኖር ይችላል በማለት እርስ በእርሳቸው እንዲጠራጠሩ ይገፋፋቸዋል። አለመተማመን ለወንዶች ወይም ለሴቶች ብቻ ተለይቶ የሚሰጥ አይደለም። ጥርጣሬ የሚፈጥሩ ነገሮችን ማስወገድ አለመቻል ነው።   ፯. ግልጽ አለመሆን፡- በአንዳንዶቹ ዘንድ የሚበሉ፣ የሚጠጡትን፣ የሚለብሱትን ብቻ መናገራቸው ግልነት ሊመስላቸው ይችላል። ከዚህ ውጭ ግን የውስጥ ስሜታቸውን በተክክል አይናበቡም። በይሉኝታ ተደብቆ፣ በራስ ማንነት ሳይሆን ሚስት ከሆነች ባሏን ባልም ከሆነ ሚስትን ደስ ያሰኙ እየመሰላቸው በትክክለኛ ማንነታቸው መገለጥ አለመቻል ሊገለጡ የሚገባቸውን ጉዳዮች አለመግለጥ፤ ግልጽ የገንዘብ ዝውውር አለመኖር፣ በድብቅ ቤተሰብን መርዳት ወዘተ ለግጭት መንሥኤ ሊሆን ይችላል።  ፰. በሩካቤ ሥጋ አለመጣጣም ነው፡- ከጋብቻ በፊት ጤንነታቸውን፣ የውስጥ ስሜታቸውን በሚገባ ማጤን ይኖርባቸዋል። በቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ከጋብቻ በፊት ባለ የቆይታ ጊዜ ከአላስፈላጊ መነካካት፣ ከመዳራት ከግብረ ሥጋ ግንኙነት መቆጠብ ያስፈልጋል። ይሁን እንጂ በስነ ልቡና ችግር፣ በፊት በነበራቸው የብቸኝነት እሳቤ በፍርሃት ወዘተ… ባለመነጋገር (ባለመወያየት ወዘተ በሚፈጠር አለመጣጣም ጋብቻ ሲፈርስ ይታያል) ፱. የሌሎች አሉታዊ ጣልቃ ገብነት፡- ይህ በቤተሰብ፣ በጓደኛ፣ በሥራ ባልደረባ ወዘተ አማካኝነት ትዳራቸውን ከሚያጸና ይልቅ የሚያፈርስ ሐሳብ ሊያመጣ ይችላልና የሦስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት ካለ ትዳር ሊፈርስ ይችላል። የአንዳንዶቹ ጣልቃ ገብነት በውስጣቸው የሐሳብ መለያየትን ከመፍጠር አልፎ ፍታት ወይም ፍቺው ብለው እስከ መወሰን ድረስ የሚደርስ ነው። በዚህ ጊዜ ባለትዳሮቹ በብሉይ ኪዳን “ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፤ ሚስቱንም ይከተላል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ” (ዘፍ.፪፥፳፬) እንደተባለ በሐዲስ ኪዳንም ‹‹ስለዚህ ወንድ አባቱንና እናቱን ይተዋል ከሚስቱም ጋር አንድ ይሆናል፤ ሁለቱም አንድ አካል ናቸው›› (ኤፌ.፭፥፴፩) ተብሏል። ስለዚህ ሰዎች ይህን በአግባቡ በመረዳት ለትዳራቸው ዋስትና ማበጀት ይኖርባቸዋል። ባል የሚስቱን ሐሳብ ሚስት የባሏን ሐሳብ አክብራ ለትዳራቸው እንቅፋት የሚሆነውን የሦስተኛ ወገን ሐሳብ በመተው ዘላቂ የሆነውን ኑሯቸውን መቀጠል ይኖርባቸዋል። ከዚህ በተቃራኒው ግን ከእናትና ከአባቴ አትበልጥብኝም /ጭብኝም በመባባል ትዳራቸው ሲፈርስ ይስተዋላል።    
Read 2584 times