Wednesday, 07 April 2021 00:00

የጥያቄዎቻችሁ መልስ ክፍል ሁለት

Written by  ቀሲስ ዐብይ ሙሉቀን

Overview

ውድ አንባብያን ባለፈው ወር ዕትማችን በጥያቄዎቻችሁ መልስ ዐምዳችን የትዳርንና ትዳር የሚፈርሱባቸውን ምክንያቶች በተመለከተ የሚነሡ ጥያቄዎችን መሠረት አድርገን ምላሽ ይሰጡን ዘንድ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በምሥራቀ ፀሐይ ቀበና መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ስብከተ ወንጌል አገልጋይ የሆኑትን መጋቤ አእላፍ ቀሲስ ፋሲል ታደሰን ጋብዘን አንደነበርና መልሳቸውንም ለእናንተ ማካፈላችን ይታወሳል። ቀጣዩን ክፍል ደግሞ በዚህ ወር ዕትማችን እናቀርባለን መልካም ንባብ። ፭.ሐመር፡-  በአሁኑ ጊዜ የብዙዎች ትዳር ከሚፈርሱባቸው ምክንያቶች አንዱ በሩካቤ ሥጋ ጊዜ የስሜት አለመጣጣም ችግር እየተፈጠረባቸው እንደሆነ ጠቅሰዋል? ለዚህ ምክንያቱ ምን ይሆን መፍትሔውስ? መጋቤ አእላፍ ቀሲስ ፋሲል ታደሰ፡- ለዚህም ጥያቄ በርከት ያሉ ምክንያቶች ሊጠቀሱ ይችላሉ። ዋና ዋና የምላቸውን ለመጥቀስ ልሞክር፡-

 

ሀ. የግንዛቤ ችግር፡- ስለ ሩካቤ የሚኖራቸው ግንዛቤ ምንአልባት ለአንዳንዶች ፍርሃት ሊሆን ይችላል። ሴቶችም ሆኑ ወንዶች የአደጉበት ሁኔታ፣ ባህልና ልዩ ልዩ መንገዶች ምክንያት እየሆኑአቸው ወንድየው ሚስቱን ለመጠጋት ሚስትም ባሏን ለመጠጋት የሚፈሩበት ሁኔታ ይፈጠራል። ውስጣቸው ዝግጁ ስላልሆነ በግዴታ ቢቀርቡም ስሜታቸው ይቀዘቅዝና ለግብረ ሥጋ ግንኙነት ፍላጎት ያጣሉ። 

ለሌሎች ደግሞ ሩካቤ ሥጋን እንደ ስሕተት መመልከት ሊሆን ይችል። እንዲሁ አስቀድመው በንጽሕና በቅድስና እንደቆዩ ሁሉ ሲያገቡም ከባልና ከሚስት ጋር የሚደረገውን ግብር እንደ ኃጢአት ሊቆጥሩት ይችላሉ። ራስን ጠብቆ በቤተ ክርስቱያን አስተምህሮ መሠረት ማደግ ተገቢ መንገድ ነው። ሆኖም ግን በዚህ ሁኔታ ቢያድጉም ወደ ትዳር ሲገቡ ደግሞ “መጋባት በሁሉ ዘንድ ክቡር ነው፤ ለመኝታቸውም ርኵሰት የለውም፤ ሴሰኞችንና አመንዝሮችን 

ግን እግዚአብሔር ይፈርድባቸዋል” (ዕብ.፲፫፥፬) የተባለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ሕግ በመዘንጋት፣ ልጆች የሚተኩበት አምላካዊ ሕግ መሆኑንም ባለመረዳት የስሜት አለመጣጣም ችግር ሊከሠት ይችላል። 

ለ. ግልጽ አለመሆን፡- ይህ ከፍቅር ማነስም የሚከሠት ሊሆን ይችላል በፍቅር ውስጥ ፍርሃት የለም። በፍቅር ውስጥ ሊኖር የሚችለውን ጉዳይ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ “ፍቅር ያሳታግሣል፤ ፍቅር ያስተዛዝናል፤ ፍቅር አያቀናናም፤ ፍቅር አያስመካም፤ ፍቅር ልቡናን አያስታብይም፤ ብቻየን ይድላኝ አያሰኝም፤ አያበሳጭም፤ ክፉ ነገርንም አያሳስብም፤ ጽድቅን በመሥራት ደስ ያሰኛል እንጂ ግፍን በመሥራት ደስ አያሰኝም፤ በሁሉ ያቻችላል፤ በሁሉ ያስተማምናል፤ በሁሉም ተስፋ ያስደርጋል፤ በሁሉም ያስታግሣል።” (፩ቆሮ.፲፫፥፫-፯) በማለት ይዘረዝርልናል። ከልብ መዋደድ ሲኖር ይሉኝታ የለም፣ መተፋፈር የለም፣ ስሜትን በግልጽ አለመነጋገር አይቻልም። ይህ ሳይሆን ሲቀር ግን መተፋፈር፣ መደባበቅ፣ በግልጽ አለመወያየት እየጠነከረ ይህድና በመጨረሻም ለፍች ይዳረጋሉ። 

ሐ.ራስን አለመጠበቅ፡- መንፈሳዊ ተግባራት ወሳኞች ናቸው። ይሁን እንጂ በሚያስፈልገው ወቅት ደግሞ የሚገባውን ምግብ መመገብና ዐቅምን ማጠናከር ሲገባ በጾም ወቅት በለመዱት መንገድ መጓዝና በምግብና በልዩ ልዩ መንገድ ዐቅምን አለመጠበቅ ለድካም ያጋልጣል። የአቅም ማነስ፣ ተደጋጋሚ ሊድን በሚችል በሽታ መያዝና መዳከምን ከዚህም ሲያልፍ ስሜት አልባ መሆንን፣ ሙሉ በሙሉ ስሜት አልባ ባይሆኑም ድካም ሊኖር ስለሚችል የፍላጎት አለመጣጣምን ያስከትላል ። 

መ. የጤንነት ችግር ሊኖር ይችላል። አንዳንድ ጊዜ በተፈጥሮም ሆነ በሕመም ምክንያት፣ በሕክምናም ከመገናኛ (ከመራቢያ) አካላት ጋር በተገናኘ በወንዱም ሆነ በሴቷ ላይ የጤና ችግር ሊኖር ይችላል። የሚታይና አካላዊ የሆነ የጤና ችግር ባይኖርም የሥነ ልቡና ውድቀትም ሊከሠት ይችላል። በወንዱም ሆነ በሴቷ በኩል ራስን እንደ ዝቅተኛ ማየት ራስን እንደጤነኛ ሰው አለመቁጠር፣ የበታችነት ስሜትን አስቀድሞ ወደ አእምሮ መላክ፣ ወዘተ ሁሉ በግብረ ሥጋ አለመጣጣም ላይ የራሱ የሆነ ተጽእኖ ይኖረዋል። ይህ እንዳይፈጠር አስቀድሞ የጤናን ሁኔታ ማወቅ ያስፈልጋል። 

መፍትሔ

ከላይ የተጠቀሱትን በአግባቡ መረዳት፡- በማንኛውም ጉዳይ አስቀድሞ ችግሩንና የችግሩን መንሥኤ በአግባቡ መረዳት ያስፈልጋል። ከላይ የተዘረዘሩት ደግሞ ለችግሩ መንሥኤዎች ናቸው። ስለዚህ ከላይ የተዘረዘሩትን በአግባቡ መረዳት ቀዳሚው ጉዳይ ነው።ከላይ የተዘረዘሩትን በአግባቡ ከመረዳት በተጨማሪ የሚከተሉትን ጉዳዮች ልብ ማለትም ያስፈልጋል።

ሀ. በፍቅር መመሥረት አለበት፤ 

ለ. ሥነ ልቡናዊ ውድቀትን ማስተካከል፤ 

ሐ. መታገሥ በትዕግሥት ብናልፈው ሊስተካከል እንደሚችል ማመን፤ 

መ. አጉል ፍርሃትን ማስወገድ በተገቢው ጊዜ የሚደረግ ግንኙነት የተፈቀደ ስለሆነ ከይሉኝታና ከሃፍረት መውጣት፤

ሠ. መመካከር (መወያየት)፤

ረ. ለባለሙያ ወይም ለመምህረ ንስሓና  በዕድሜ ለሚበልጡን፣ ማማከር።

፮. ሐመር፡- በባለ ትዳሮች መካከል አለመተማመን ይፈጠራል፤ ከፍ ሲልም መፋታታቸውን ሳያውጁ (በትዳር እያሉ) ወንዱ ከሌላ ሴት ሴቷም ከሌላ ወንድ ጋር አላስፈላጊ ግንኙነት ይፈጥራሉ። ይህ በትዳራቸውም ላይ ከሚያስከትለው ጉዳት፣ ከቤተ ክርስቲያን አስተምህሮም አንጻር እንዴት ይታያል?

መጋቤ አእላፍ ቀሲስ ፋሲል ታደሰ፡-  በመጀመሪያ አለመተማመን ደረጃ ላይ ለምን ደረሱ የሚለውን ከችግሩ ልነሣ ባልና ሚስት ከላይም በተደጋጋሚ እንደተገለጸው አንድ አካል ናቸው። ይህ ሆኖ ሳለ ግን አይተማመኑም። ምክንያቱም፡-

፩.  በፍቅር አለመጋባት፡- ጋብቻቸው በእውነተኛ ፍቅር ላይ የተመሠረተ ከሆነ ባልም ሆነ ሚስት ሌላ ሊታያቸው ሊታሰባቸውም አይችልም። ግን እንዲሁ አፍአዊ በሆነ መስፈርት የተመሠረተ ጋብቻ ልክ ሰርጉ እንዳበቃ ወደ ሌላ አቅጣጫ ይቀየርና ከትዳርነት ይልቅ የጭቅጭቅ ቤት መሆን ይጀምራል። 

፪. ሳይለወጡ ማግባት፡- እዚህ ላይ ለውጥ ማለት መንፈሳዊውን ለውጥ ነው። በሁለቱም በኩል ካወቁበትና ከተረዱት ጋብቻቸው ፍጹም ከሆነው የቅድስና ደረጃ ላይ ያደርሳል። ለዚህ ግን ቀደሞ የነበረ መጥፎ አመልን አስወግዶ ፍጹም የሆነ መንፈሳዊ ለውጥን ገንዘብ አድርጐ መግባት ያስፈልጋል። የቀድሞ ግብርን ሳይተውና መንፈሳዊ ለውጥ ሳይኖር ቢጋቡ ከጋብቻ በኋላም ወደ ቀደመ ማንነታቸው እየሄዱ በውስጣቸው አለመተማመናቸው እየሰፋ ይህዳል። 

፫ ፈሪሀ እግዚአብሔር ሲጠፋ፡- ማንኛውም ሰው እግዚአብሔርን መፍራት የሕይወት መሠረቱ ሊያደርግ ይገባዋል። ዮሴፍ በዘፍ.፴፱ ላይ ታሪኩ ተጽፎ እንደምናገኘው ሰው በሌለበት ጊዜና ቦታ የዝሙት ጥያቄ ቀርቦለት ነበር። ያውም ከእመቤቲቱ በዚህ ጊዜ ዮሴፍ “ሰው ባያይ እግዚአብሔር ያያል” በማለት አይሆንም አለ። የጲጥፍራ ሚስት ባል እያላት፣ ሌላ ተመኘች ዛሬም ሰዎች በተለያየ ምክንያት ለምሳሌ በሥራ፣ በትምህርት፣ ወዘተ በተለያየ ቦታ ሲኖሩ ሰው ባያይ እግዚአብሔር ያያል ብለው ለትዳራቸው ለገቡት ቃል ኪዳን ለኅሊናቸው ይልቁንም ለእግዚአብሔር መታመን አለባቸው። ሚስት ባትኖር እግዚአብሔር ያየኛል ባል ባይኖር እግዚአብሔር ያየኛል በማለት ቸልተኝነትንና ግዴለሽነትን ማስወገድ ያስፈልጋል። 

ጉዳቱን እናንሣ 

፩. ኀጢአት ነው፡- እግዚአብሔር አምላክ ለሙሴ ከሰጠው ዐሠርቱ ትእዛዛት መካከል አንዱ “አታመንዝር” (ዘፀ.፳፥፲፬) የሚለው ነው። ስለዚህ የእግዚአብሔርን ቃል ተላልፎ እንዲህ ያለ ሥራ መሥራት ኃጢአት ነው። የኃጢአት ደሞዝ ደግሞ ሞት ነው። ወንጌላዊው ዮሐንስ በራእዩ “የነፍስ ገዳዮችም፣ የሴሰኞችም፣ የአስማተኞችም፣ ጣዖትንም የሚያመልኩ የሐሰተኞችም  ሁሉ ዕድላቸው በዲንና በእሳት በሚቃጠል ባሕር ውስጥ ነው፤ ይኸውም ሁለተኛ ሞት ነው” (ራእ.፳፩፥፰) በማለት እንደተናገረው። ከሥጋ ፍሬዎቹም አንዱ ነው። (ገላ.፭፥፲፱) ስለዚህ የነፍስ ሞትን የሚያመጣ ኃጢአት ነው። ኃጢአተኛን ኃጢአቱ ትቀጣዋለች እንደሚል ሁሉ ቅጣት ያደርስበታል። 

፪. በሽታን ያስከትላል።  በሽታ አስተላላፊ ከሆኑት ነገሮች መካከል አንዱ ዝሙት ነው። በዝሙት ምክንያት የሚመጣ በሽታ ደግሞ በሰው ሰውኛው እስከማይድን በሽታ ይደርሳል። ይህ ደግሞ ለራስም ለጋብቻ አጋርም፣ እልፍ ሲልም ለቤተሰብ ሁሉ ጠንቅነው። 

፫. የሥነ ልቡና ጉዳት ያስከትላል፡- ባለመተማመን ወደ ሌላ በመወስለት የሥነ ልቡና ጉዳት ይደርስበታል። ሚስቱ ሳታየው ከሌላ ጋር ዝሙት የፈጸመ ሰው መቼም ቢሆን ውስጡ ጤነኛ ሊሆን አይችልም። ታወቀብኝ አልታወቀብኝ በማለት ውስጡ ይጨነቅበታል። ኅሊናው ይካሰስበታል። ከምንም ባለይ ሰው ያላየኝ ቢመስለው ከኅሊና ዳኝነት ሊያመልጥ ወይም ሊሠወር አይችልምና በመጨረሻ የሥነ ልቡና ጉዳት ያስከትልበታል።

፬. ትዳር ይፈርሳል፡- ከላይ የተዘረዘሩት ሁሉ ባለመተማመን የሚከሠቱ ናቸው። በዚህ ምክንያት ከሁለቱ አንዱ በትዳራቸው መኖርን አልፈልግም ቢል ይችላልና ትዳራቸው ሊፈርስ ይችላል። እንደ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮም በዝሙት ምክንያት ከሆነ ትዳር እንዲፈርስ ይፈቀዳል። መድኅነ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ስለፍቺ በተጠየቀበት ወቅት “ያለዝሙት ምክንያት ሚስቱን የሚፈታ ሁሉ አመንዝራ ያደርጋታል፤ የተፈታችውንም ያገባ ያመነዝራል” (ማቴ.፲፱፥፱) በማለት የመለሰው መልስ በዝሙት ምክንያት ከሆነም መፋታት ኃጢአት እንዳልሆነ ያስረዳናል። ስለዚህ ለነፍሳቸውም ሆነ ለሥጋቸው በማይጠቅም የዝሙት ሥራ ትዳርን ማፍረስ ትልቅ ጉዳት ስለሆነ መጠንቀቅ ያስፈልጋል።

፭. የልጆች አሉታዊ ጠባይ መውረስ፡- ልጆች የሚቀረጹት እናት አባቶቻቸው በሚያሳዩአቸው ነገር ነው። ልጆች ክፉውንም በጎውንም ከቤተሰቦቻቸው ይማራሉ። በቃል ከምንሰብካቸው በላይ የአባትና የእናት ተግባር ያስተምራቸዋል። ስለዚህ ባልና ሚስት አለመተማመን የሰፈነበት ኑሮ የሚኖሩ ከሆነ ልጆችም በውስጣቸው ተቀርጾ የሚያድጉት አሉታዊ የሆነው የእናትና የአባቶቻቸው ጠባይ ነው። 

፯. ሐመር፡- ትዳራቸው የተባረከና ፍጹም ፍቅር የሰፈነበት እንዲሆን ባለትዳሮች ምን ማድረግ አለባቸው?

መጋቤ አእላፍ ቀሲስ ፋሲል ታደሰ፡- 

ሀ. ፍቅርን ገንዘብ ማድረግ፡- ፍቅር ለባለትዳሮች ከምንም በላይ አስፈላጊ ነው። ‹‹ዘአፍቀረ ብእሲቶ ርእሶ ፈፍቀረ፤ ሚስቱንም የሚወድ ራሱን ወደደ›› (ኤፌ.፭፥፳፰) በማለት ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንደተናገረው እንደራሱ አካል የመውደድን ጥበብ ተላብሶ መኖር ይገባል። የትዳር ሕይወት ማስተዋልን፣ ፈሪሀ እግዚአብሔርን፣ ፍቅርን ወዘተ ገንዘብ አድርገው ሲኖሩበት የሚታወቅና የሚለመድ እንጂ በትምህርት የሚማሩት፣ በሥልጠና የሚያዳብሩት አይደለም። ፍቅርን ገንዘብ አድርገው ሊኖሩ ይገባል። ከውጫዊው ይልቅ በውስጣዊው ማንነታቸው እየተደሰቱ እንዲኖሩ እንጂ ባልም ሆነ ሚስት ለልጄ ስል ነው የምኖረው እንዲሉ አይመከርም። ልጅ ማሳደግ ግዴታቸው ነውና። 

ለ. ዘወትር ስለ ትዳር ማወቅ፡- በትዳር ውስጥ ሁል ጊዜ ደስታ ላይኖር ይችላል። ስለዚህ ምንም እንኳን አስቀድመው ከመግባታቸው በፊት ስለትዳር ማወቅ አለባቸው ቢባልም በየጊዜው የሚፈጠሩ ጉዳዮች የተለያዩ ሊሆኑ ስለሚችሉ ሁሌም ስለትዳር መማርና ማወቅ ይኖርባቸዋል። ትዳር “ትንሿ ቤተ ክርስቲያን ናት” ተብሏልና ብዙ ነገሮችን የምንማርበት ትምህርት ቤትም ነውና ስለሕይወትም ስለ ትዳርም ስለ ብዙ ነገር እንማራለን። 

ሐ. ጊዜ መስጠት፡- ጊዜ መስጠት ማለት አንድ ላይ መቀመጥ ብቻ አይደለም። አንዳንድ ሰዎች “በጊዜነው ቤቴ የምገባው” ይላሉ። በጊዜ ገብቶ አንድ ላይም ተቀምጠው አንድ ላይ የማይሆኑበት ሁኔታ ይስተዋላል። የሚወያዩበት፣ እርሱ ስለ እርሷ እርሷም ስለ እርሱ የሚነጋገሩበት የጋራ ጊዜ ያስፈልጋቸዋል። አብሮነት “እንዳይታጐል” እንደሚባለው መሆን የለበትም። ኅሊናቸውን የሚጠልፍ ነገር ካለ እርሱን አስወግደው በግልጽ የሚወያዩበትና የሚመካከሩበት ጊዜ መመደብ ይኖርባቸዋል።

መ. ይቅርታ መደራረግ፡- ምንም አንድ አካል ናቸው ቢባልም ይህን በጥልቀት ያልተረዱ ባልና ሚስት ሁል ጊዜ እርሱም ስለራሱ እርሷም ስለ ራሷ የሚጨነቁበት ጊዜ ይኖራል። በዚህ ጊዜ አንዱ ሌላውን ሊያስቀይም ይችላል። እንዲህ የመቀያየም ሁኔታ ሲፈጠር በቶሎ ይቅርታ መጠያየቅ ያስፈልጋል። ጠላቶቻችሁን ውደዱ የተባለው ሰው በሚስቱ ላይ ቂም መያዝ የለበትም። 

ሠ. በመንፈሳዊ ምግባራት መትጋት፡- ከመምህረ ንስሓ ጋር ዕለት ዕለት እየተመካከሩ፣ እየጾሙ ንስሓ እየገቡ ሥጋውን ደሙን እየተቀበሉ በመንፈሳዊ ሕይወትና በመንፈሳዊ ምግባራት ጸንተው ሊኖሩ ይገባል። በቃና ዘገሊላ በተዘጋጀው ሰርግ የወይን ጠጁ ማለቅ ችግር ነበር። ችግሩ ግን አልዘለቀም። ምክንያቱም ባለቤቱን ጠርተውታልና፣ የባለቤቱ የጌታ እናት ድንግል ማርያምና ደቀ መዛሙርቱም በዚያ አሉና። ባለትዳሮችም በጾም፣ በጸሎት፣ በምጽዋት፣ በንስሓ፣ በቅዱስ ቁርባን ሕይወት ጸንተው ሲኖሩ፣ እግዚአብሔርን በትዳራቸው ሲይዙት ትዳራቸው የአማረ ይሆናል። ይህ ሲሆን ትዳር መፍረስ አይደለም ለሌሎችም ማስተማሪያ የሚሆን አርአያነት ያለው የእነከሌን ትዳር ተመልከቱ የሚባል ይሆናል። 

፰. ሐመር፡- በመጨረሻ ቀረ የሚሉት ነገር ካለ ዕድሉን እንስጥዎት፡-

መጋቤ አእላፍ ቀሲስ ፋሲል ታደሰ፡- ተጋቢዎቹ ቅድመ ጋብቻ የትዳርን ምንነት፣ በረከቱን፣ በትዳር ውስጥ የሚኖረውን ፈተና ወዘተ የመሳሰለውን ሁሉ አስቅድመው መረዳት አለባቸው። ምንም እንኳን ሰውን ማጥናት ከባድ ቢሆንም መሠረታዊ የሆኑ ነገሮችን አስቀድሞ ማጥናት ያስፈልጋል። መኪና በሙከራ የሚለመድ ቢሆንም መሠረታዊ የሆነውን ዕውቀት ግን አስቀድመው ይይዙታል። ዛሬ ዛሬ ትዳርን የመንጃ ፈቃድ ያህል እንኳን ቦታ ሲሰጡት አይስተዋሉም። ስለዚህ ቅድመ ጋብቻ በጥንቃቄ ተመልክተው ማወቅ ያለባቸውን መሠረታዊ ነገር ዐውቀው ሊገቡ ይገባል። 

በትዳር ውስጥ ያሉትም ብዙ ነገሮች በጊዜ ሂደት በልምምድ የሚስተካከሉ መሆናቸውን መረዳትና ማመን ይኖርባቸዋል። ለምሳሌ መንፈሳዊ ጉዳዮች በመንፈሳዊ ልምምድ፣ የገቢ ጉዳይ ቀስ እየተባለ በጊዜ ሂደት፣ የጤና ችግርም ካለ እንዲሁ ይስተካከላል የሚለውን ማመን ይኖርባቸዋል። አንድ ተማሪ ተምሮ ያሰበው ላይ እስኪደርስ ብዙ ደብተር ሊጨርስ ይችላል። ግን “ለበጐጎ ነው” ብሎ በትዕግሥት መጠበቅ ያስፈልጋል። ‹‹ችኩል ለመጉደል ይቸኩላል›› ይባላልና በችኮላ የሚሆን ነገር ስለሌለ ትዳርንም በትዕግሥት መምራት ያስፈልጋል። የእርስ በእርስ ውይይትንም ማዳበር፣ ሁል ጊዜም በግልጽ በመካከር ለችግሮች ሁሉ መፍትሔ ማምጣት ይቻላል።

ሐመር፡- ውድ ጊዜዎትን ሠውተው ላነሣናቸው ጥያቄዎች ሁሉ ተገቢውን ማብራሪያ ስለሰጡን በእግዚአብሔር ስም እናመሰግናለን።

መጋቤ አእላፍ ቀሲስ ፋሲል ታደሰ፡-  እኔም አመሰግናለሁ።    

  

 

Read 937 times