መጋቤ ሐዲስ ምሥጢረ ሥላሴ ማናየ፡- አምስቱ አዕማደ ምሥጢር ለእኛ የእምነት መሠረት ወይም ዶግማ ብለን የምንጠራቸው ናቸው። ምሥጢረ ሥላሴ የሥላሴን አንድነት ሦስትነት፣ የስም፣ የግብር፣ የአካል፣ የኩነት ሦትነት፣ የባሕርይ፣ የአገዛዝ፣ የሥልጣን፣ የህልውና ወዘተ. አንድነት የምንማርበት በጠቅላላው ምሥጢረ እግዚአብሔርን ለሰው ልጆች የምንገልጥበት ነው። ሁለተኛው ከሦስቱ አካላት አንዱ አካል እግዚአብሔር ወልድ ሰው መሆኑን የምንማርበት ነው። ለትንሣኤውም መሠረት የሆነው ከሦስቱ አካላት አንዱ አካል ሰው መሆኑ ነው። ሦስተኛው ምሥጢረ ጥምቀት ሲሆን የሥላሴን ልጅነት ስለምናገኝበት ምሥጢር የምንማርበት ነው። አራተኛው ምሥጢረ ቍርባንም እንዲሁ ለድኅነታችን ስለተሰጠን ስለ ክርስቶስ ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደም የምንማርበት ምሥጢር ነው። አምስተኛውና የመጨረሻው ምሥጢረ ትንሣኤ ሙታን ደግሞ ስለ ሰው ልጆች ዳግም መነሣትና ከሞት በኋላ ስላለው ሕይወት የምንማርበት ምሥጢር ነው።
ሁለቱን ማለትም ምሥጢረ ሥላሴንና ምሥጢረ ሥጋዌን እናምንባቸዋለን፤ እንታመንባቸዋለን። ሌሎቹን ግን አምነን እንሳተፍባቸዋለን። ሞቱን በሚመስል ጥምቀቱ እንጠመቃለን። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “በሞቱ ከመሰልነውም በትንሣኤው እንመስለዋለን” (ሮሜ ፮፥፭) በማለት እንደገለጸልን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ተጠምቀን ልጆቹ ለመሆን ትንሣኤውን ተስፋ እያደረግን ጥምቀቱን እንሳተፋለን። በጥምቀታችን ሦስት ጊዜ ብቅ ጥልቅ ስንል ትንሣኤ ሙታንን ተስፋ ማድረጋችንን የሚያስረዳ ነው።
ጌታችን ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት በከርሠ መቃብር እንዳደረ እኛም ሦስት ጊዜ ብቅ ጥልቅ እንላለን። ይህ ማለት እኛም ሞተን፣ ፈርሰንና በስብሰን አንቀርም እያልን በጥምቀታችን ትንሣኤውን መስክረን እንነሣለን። ምሥጢረ ጥምቀት የወደፊቱን ተስፋ ምሥጢረ ትንሣኤ ሙታንን እንገልጽበታለን። ይህም ማለት በሁለቱ ምሥጢራት በምሥጢረ ሥላሴና በምሥጢረ ሥጋዌ እምነታችንን መስክረን በምሥጢረ ጥምቀት ምሥጢረ ትንሣኤ ሙታንን እንገልጽበታለን።
በምሥጢረ ቍርባን ሥጋውን ደሙን ተቀብለን የዚሁ የምሥጢረ ትንሣኤ ባለቤቶች ሆነን ዘለዓለማዊ ሕይወትን ገንዘብ እናደርጋለን። ምሥጢረ ቍርባንን አምነን በመሳተፍ እግዚአብሔር በእኛ ያድራል፤ እኛም ከእግዚአብሔር ጋር እንኖራለን። ሐዲስ ኪዳን የምንለው “ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ በእኔ ይኖራል፤ እኔም ከእርሱ እኖራለሁ።” (ዮሐ.፮፥፶፯) የሚለውን የምንገነዘብበት ነው። ስለዚህ ይህን ስንፈጽም እርሱ እንደተነሣ እኛም ሥጋውን በመብላታችን ሕያው እንደምንሆን አምነን ትንሣኤ ሙታንን ተስፋ አድርገን እንጠብቀዋለን።
ከዚህ በመቀጠል የተስፋው ፍጻሜ የሆነው በመጨረሻ የሚፈጸም ምሥጢረ ትንሣኤ ሙታን ነው። ይህ ከነባለቤቱ ከነዘርፉ የተገለጸ ነው ነው። ሙታን የሚባሉት ከአራቱ ባሕርያተ ሥጋ ከሦስቱ ባሕርያተ ነፍስ የተፈጠሩት ሦስቱ ባሕርያት ተለይተዋቸው ወደ ተፈጠሩበት አፈር የሚመለሱት ናቸው። ሰው ሞተ የሚባለው ሦስት ነገሮች ማለትም ነፋስ ውኃ እና እሳት ሲለዩት አፈር ብቻ ሲቀር፣ ነፍስ ደግሞ ወደ እግዚአብሔር ሄዳ ተፈርዶላት በገነት ስትኖር ወይም ተፈርዶባት ወደ ሲኦል ስትወርድ ነው። ሰው እሳት ሲለየው፣ ይቀዘቅዛል፤ በእኛ ቋንቋ በድን ሆነ እንለዋለን። ውኃ ሲለየው ደግሞ የደም ዝውውር ያቆማል፤ ነፋስ ሲለየው የሕይወት እስትንፋስ የምንለውን ነገር ያጣል። ስለዚህ በዚህ ሂደት አፈር ወደ አፈርነቱ ይመለሳል።
በመጽሐፈ መክብብ “አፈር ወደ ነበረበት ምድር ሳይመለስ ነፍስም ወደሰጠው ወደ እግዚአብሔር ሳይመለስ በሥጋም በነበረበት ጊዜ መልካም ወይም ክፉ ቢሆን ስለሠራው ሁሉ መልስ ሳይሰጥ ፈጣሪህን አስብ” (መክ.፲፪፥፯) ተብሎ እንደተነገረ አፈር ወደ አፈርነቱ ይመለሳል። ስለዚህ ሞት ማለት የአፈር ወደ ነበረበት ምድር መመለስ ነው። እነዚህ ሙታን አካል ተነሥተው ከመቃብር በመነሣት በእግዚአብሔር ቀኝ ወይም በእግዚአብሔር ግራ የሚቆሙበት ጊዜ ትንሣኤ ሙታን ይባላል። እነዚህ ሙታን መቃብር ክፈቱልኝ፣ መግነዝ ፍቱልኝ ሳይሉ አምላካቸውን ክርስቶስን መስለው ፈጣሪያቸውን ተከትለውና እርሱን የትንሣኤያቸው በኵር አድርገው የሚነሡት ትንሣኤ ትንሣኤ ሙታን ይባላል።
፫. ሐመር፡- ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በከርሠ መቃብር ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት አደረ ይላልና ይህ ሦስት መዓልትና ሦስት ሌሊት እንዴት ተቆጥሮ ነው የሚሞላው?
መጋቤ ሐዲስ ምሥጢረ ሥላሴ ማናየ፡- ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት ተብሎ የሚቈጠረው ጌታችን የሞተው ዓርብ ነው። ስለዚህ ዓርብ አንድ ተብሎ ይቆጠራል። ዋናው ጉዳይ ፱ ሰዓት መሞቱ፣ ፲፩ ሰዓት መቀበሩ አይደለም። የሞተው በዕለተ ዓርብ ስለሆነ ዓርብ ሌሊቱን ጭምር ቆጥሮ አንድ መዓልት አንድ ሌሊት ይባላል። ለምሳሌ አንድ ሰው ዓርብ ጧት ቢወለድ፣ ከሰዓት በኋላም ቢወለድ ዓርብ ተወለደ ነው የሚባለውና የዓርብን ሌሊትም ጨምሮ አንድ ተብሎ ይቆጠራል። ይህን ሊቃውንት መዓልት ይስህቦ ለሌሊት ወሌሊት ይስህቦ ለመዓልት፤ ቀን ሌሊትን ይስበዋል፣ ሌሊትም ቀንን ይስበዋል” በማለት ይገልጹታል። ደግሞም ሌሊት የሌለው ቀን ቀን የሌለው ሌትም ሊኖር አይችልም።
ስለዚህ ዓርብ ዘጠኝ ሰዓት “አጽነነ ርእሶ ወመጠወ ነፍሶ፤ ራሱንም አዘንብሎ ነፍሱን ሰጠ” (ዮሐ.፲፱፥፴) ተብሎ በቅዱስ ወንጌል እንደተጻፈ ዓርብ አንድ ቅዳሜ ሁለት እሑድም የተነሣ ሌሊት ቢሆንም መዓልቱን ስቦ ሦስት ተብሎ ይቆጠራል። ዕለት ማለት የ፲፪ ሰዓት ብርሃንና የ፲፪ ሰዓት ጨለማ ያለው ነው። ዕለት ብሂል ዘያስተዛውጎሙ ለመዓልት ወለሌሊት፤ ዕለት ማለት መዓልትና ሌሊትን አንድ የሚያደርጋቸው ነው” (ምንጭ፡- ብሉይ ኪዳን ትርጓሜ) በማለት ሊቃውንቱ እንደሚነግሩን ሌሊትና መዓልትን አንድ ያደረገ ነው። ዋናው ሰዓት ሳይሆን ድርጊቱ የተፈጸመበትን ዕለት ስለሆነ ከዓርብ ጀምረን እስከ እሑድ ስንቆጥር ሦስት መዓልትና ሦስት ሌሊት ይሆናል።
ታሪኩ በመጽሐፍ ቅዱስ ተመዝግቦ እንደምናገኘውና ሊቃውንቱም በምሥጢር እንዳስረዱን ዮናስ ወደ ከርሠ አንበሪ የገባው ዓርብ በሠርክ ነው። ከከርሠ አንበሪ የወጣው ደግሞ እሑድ ሌሊት ነው። (ምንጭ፡- ትንቢተ ዮናስ ትርጓሜ) ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምልክት ያሳዩት ዘንድ ለጠየቁት ሰዎች “እስመ በከመ ነበረ ዮናስ ውስተ ከርሠ አንበሪ ሠሉሰ መዋዕለ ወሠሉሰ ለያልየ ከማሁ ይነብር ወልደ እጓለ እመሕያው ውስተ ልበ ምድር ሠሉሰ መዋዕለ ወሠሉሰ ለያልየ፤ ዮናስ ሦስት መዓልትና ሦስት ሌሊት በዓሣ አንበሪ ሆድ እንደ ነበረ እንዲሁ የሰው ልጅም ሦስት መዓልትና ሦስት ሌሊት በምድር ልብ ውስጥ ይኖራልና” (ማቴ.፲፪፥፵-፵፩) በማለት እንደ መለሰላቸው ምሳሌው ሆኖ የቀረበው ዮናስ ዓርብ በሠርክ ወደ ከርሠ አንበሪ (ሆድ) ገብቶ እሑድ በሌሊት እንደ ወጣ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በዘጠኝ ሰዓት ቅድስት ነፍሱን ከቅዱስ ሥጋው ለይቶ በ፲፩ ሰዓት ተቀብሮ እሑድ ሌሊት መነሣቱ ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት በከርሠ መቃብር አደረ እያልን የምንናገረው ይህን ነው።
፬. ሐመር፡- ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤውን በመጀመሪያ የገለጸው ለሴቶች ነው። ለምን?
መጋቤ ሐዲስ ምሥጢረ ሥላሴ ማናየ፡- ሞት በመጀመሪያ ወደ ሰው ልጅ የመጣው በሴቶች ነው። የሞት መርዶ ኀዘን በሴቶች እንደመጣ ትንሣኤውም በእነርሱ በኩል እንደመጣ ለማስረዳት ነው። እንደሚታወቀው ሔዋን ጆሮዋን ከፍታ አእምርሮዋን አንቅታ የዲያብሎስን ምክር በመስማቷ ምክንያት ሞት ወደ ሰው ልጅ መጥቷል። እንዲሁ እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም ጆሮዋን ከፍታ፣ አእምሮዋን አንቅታ የመልአኩን የቅዱስ ገብርኤልን ምክር በመስማቷ ሕይወት ወደ ሰው ልጅ ገብቷል። ይህንም ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬም እመቤታችንን ባመሰገነበት ውዳሴው “ስለሔዋን የገነት ደጅ ተዘጋ ስለ ድንግል ማርያምም ዳግመኛ ተከፈተልን” (ውዳሴ ማርያም ዘሐሙስ) በማለት አስረድቶናል። ስለዚህ ሞትም ሕይወትም የጀመረው በሴቶች ነው ለማለት ትንሣኤውን ለሴቶች ገለጠው።
ሕይወት የሚረጋገጠው ደግሞ በትንሣኤው ነው። አምላክ እኛን ከሞት ወደ ሕይወት ሊያሽጋግረን ወደዚህ ዓለም መጣ፤ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ሞትን ድል አድርጎ ተነሥቶ እኛን ከሞት ወደ ሕይወት አሸጋገረን። ስለዚህ ሞትና ኀዘን በሴቶች በኩል እንደመጣ ሁሉ ደስታና ሕይወት ያለበትን ይህን ምሥጢርም ለእነርሱ ገለጠው።
ሌላኛው ምክንያት ወደ መቃብሩ በመገሥገሥና በመመላለስ በፈቅሩ በመቃጠል ሴቶች የመጀመሪያውን ደረጃ ይዘው እናያለን። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአይሁድ እጅ ከተያዘበት ሰዓት ጀምሮ ሁሉ ሸሽተዋል። እኩሌቶቹ ቤት ዘግተው ተደብቀዋል፤ እኩሌቶቹም በየቦታው ሸሽተዋል። ይህ ሁሉ ሲሆን ሴቶቹ ግን በቅዱስ ወንጌል “በሰንበትም ማታ ለእሑድ አጥቢያ ማርያም መግደላዊትና ሁለተኛዋ ማርያም መቃብሩን ሊያዩ መጡ” (ማቴ.፳፰፥፩) ተብሎ እንደተጻፈ ጨለማውን ሳይፈሩ፣ ወደ መቃብሩ ሲገሠግሡ እናያቸዋለን። ስለዚህ የፍቅራቸው ዋጋ የፍቅራቸው መገለጫ ይሆናቸው ዘንድ ትንሣኤውን ለሴቶቹ ገለጸው።
ወደ መቃብሩ የሚሄዱትም ሽቱ ለመቀባት አስበው ነበር። እንዲህ ያለው ልማድ የአይሁድ ልማድ ነበር። አይሁድ ሰው በሞተ በሦስተኛ ቀኑ እንዲሁም በሰባተኛ ቀኑ መቃብሩን እየከፈቱ ሽቱ ይቀቡ ነበር። ዛሬ እኛ ወደ ጸሎትና ወደ ምጽዋት ቀይረን በሠልስት፣ በሰባት፣ በዐሥራ ሁለት ወዘተ. የምናከናውነው በዚያ ልማድ ነው። ለፍቅሩ ከመሳሳታቸው የተነሣ ሽቱ ሊቀቡ በሌሊት ሲሄዱ መልአኩን አገኙት። በዚህም ያልጠበቁትን ነገር አገኙ። ያገኙትም ነገር እነርሱ መቃብሩን ሽቱ ለመቀባት ሲሄዱ ጌታችን ተነሥቷል፤ መልአኩ “እናንተስ አትፍሩ፤ የተሰቀለውን ኢየሱስን እንደምትሹ አውቃለሁና። በእዚህ የለም እርሱ እንደተናገረው ተነሥቷል፤ ነገር ግን ኑና ተቀብሮበት የነበረውን ቦታ እዩ።” (ማቴ.፳፰፥፭) በማለት ነገራቸው። የተሰቀለው ሌላ የሞተው ሌላ የተነሣው ሌላ እንዳልሆነ ለማስረዳት “የተሰቀለውን እንደምትሹ አውቃለሁና እርሱ ግን በዚህ የለም ተነሥቷል” በማለት የሞተው የተነሣው የተሰቀለው ራሱ ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን አስረዳቸው። ይህን ሊቃውንቱ “ወዝ ነገረ መልአክ ያኤምር ከመ ስቅለተ ክርስቶስ ትምክሕተ ሰማያውያን ወምድራውያን፤ ይህ የመልአኩ ነገር የክርስቶስ ስቅለት የሰማያውያንም የምድራውያንም ትምክህት እንደሆነ ያስረዳል” (ምንጭ፡- ትርጓሜ ወንጌል) ብለው ገልጸውታል።
ሌላው ሊቃውንቱ በትርጓሜያቸው ሴቶች መልእክትን (የምሥራችን) ለሰው ሁሉ ለማዳረስ ፈጣኖች ናቸውና የትንሣኤው የምሥራች ለዓለም ሁሉ በፍጥነት ይዳረስ ዘንድ ነው ብለዋል። ይህም ይታወቅ ዘንድ መልአኩ “ፈጥናችሁም ሂዱና ከሙታን ተለይቶ ተነሣ፤ እነሆ ወደ ገሊላ ይቀድማችኋል፤ በዚያም ታዩታላችሁ ብላችሁ ለደቀ መዛሙርቱ ንገሯቸው፤ እነሆም ነገርኋችሁ” ብሎ እንደነገራቸው ፈጥነው እየሮጡ ሄደው ለደቀ መዛሙርቱ ነግረዋቸዋል። “በፍርሃትና በታላቅ ደስታም ከመቃብሩ ፈጥነው ሄዱ፤ ለደቀ መዛሙርቱም ይነግሯቸው ዘንድ ሮጡ” (ማቴ.፳፰፥፯-፰) እንዲል።
በአጠቃላይ የእግዚአብሔር ፈቃድ ሆኖ፣ ሞት በሴቶች በኩል እንደመጣ ሕይወትም በሴቶች በኩል መምጣቱን ለማስረዳት፣ እነርሱም ለፍቅሩ ስለሚሳሱና የትንሣኤው ዜና በፍጥነት ለዓለሙ ሁሉ ይዳረስ ዘንድ ለሴቶች ገለጸው።
፭. ሐመር፡- ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አስቀድሞ ትንሣኤውን የገለጸው ለሴቶች ሲሆን ግን ማርያምን ለምን አትንኪኝ አላት?
መጋቤ ሐዲስ ምሥጢረ ሥላሴ ማናየ፡- አትንኪኝ ያለበት በዋናነት ሁለት መሠረታዊ ምክንያቶች አሉ። እነርሱም፡-
በመጀመሪያ ደረጃ አለማመኗ ነው። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አስቀድሞ እንደሚሞት፣ እንደሚቀበር እንዲሁም ሙስና መቃብርን ድል አድርጎ እንደሚነሣ ደጋግሞ አስተምሮ ነበር። ይህን ትንሣኤ አምና ብትቀበል ኖሮ አትንኪኝ አይላትም ነበር። አለማመኗ የሚረጋገጠው ደግሞ ከመቃብሩ አጠገብ ስትደርስ፣ መቃብሩ ባዶ ሆኖ ስታገኘውና ራሱን ጌታንም ስታገኘው ምንም እንኳን እርሱ መሆኑን ባታውቅም “ጌታዬን አይሁድ ወስደውታል መሰለኝ፣ አንተም ወስደኽው እንደሆነ ንገረኝ” እያለች ስትናገር ነበር። ይህ የአይሁድ ሐሳብ ነው። እርሷ ቃሉን የሰማች፣ እሞታለሁ፤ እነሣለሁ፤ ብሎ ሲያስተምር አብራ የተማረች ናትና “ወስደውታል መሰለኝ፤ አንተም ወስደኽው ከሆነ ንገረኝ” እያለች ባልተናገረችም ነበር። ስለዚህ አትንኪኝ ያላት ገና ያላመነችበት ስለነበር ነው። ከጌታችን ጋር ለመኖር ማመን የግድ ነው። ላላመኑት አጠገባቸው ሁኖም ይረቅባቸዋልና ይህን ለማስረዳት ነው።
በሁለተኛ ደረጃ ሥርዐት ሊሠራ ፈቃዱ ስለነበር ነው። ይህም ሥርዐት የማጥመቅ፣ ቀድሶ ሥጋ ወደሙን የመፈተትና ለምእመናን የማቀበል፣ በአጠቃላይ የክህነት አገልግሎትን የማከናወን ድርሻ ለወንዶች መሆኑ ነው። ይህም ይታወቅ ዘንድ ቶማስን “ጣትህን ወዲህ አምጣና እይ፤ እጅህንም አምጣና ወደ ጎኔ አግባ፤ እመን እንጂ ተጠራጣሪ አትሁን።” (ዮሐ.፳፥፳፯) ማለቱን እንመለከታለን። ባለማመን ሁለቱም እኩል ናቸው ነገር ግን ቶማስን “ዳሥሠኝ” ማለቱ ማርያምን ደግሞ “አትንኪኝ” ማለቱ የክህነት አገልግሎት ለወንዶች ብቻ የተሰጠ የአገልግሎት ድርሻ መሆኑን ለማስረዳት ነው።
ሥልጣነ ክህነትን ለወንዶች ብቻ ያደረገውም በሴቶች ያለ ልማድ ስላለ ነው። ይህ ልማድም በየወሩ የሚመጣ ደም (የወር አበባ)፣ እንዲሁ በወሊድ ጊዜ የሚኖሩ ሁኔታዎች ተጠቃሾች ናቸው። የወር አበባ በሚመጣ ጊዜ እንኳንስ ከቤተ መቅደስ ገብቶ መቀደስ ማስቀደስም አይቻልም። በወሊድ ጊዜም እንዲሁ ነው። አንዲት እናት ወንድ ብትወልድ እስከ አርባ ቀን ሴት ብትወልድ እስከ ሰማንያ ቀን ቤተ ክርስቲያን አትገባም። በዚህ ጊዜ ደግሞ ቅዳሴ መቋረጥ የለበትም። በዚህና በመሳሰሉት ምክንያቶች መድኃኔዓለም ክርስቶስ ክህነትን የሰጠው ለወንዶች እንጂ ለሴቶች አይደለም። የሚገርመው ግን ይህ ልማደ አንስት ልጆች የሚገኙበት መንገድ መሆኑ ነው። በዚህ ተፈጥሯዊ ማንነት የሚገኙት ልጆች ደግሞ ወንዶች ቢሆኑ ካህን ሊሆኑ ይችላሉ። ስለዚህ ሴቶች ራሳቸው ካህን መሆን ባይችሉም የክህነት ምንጭ በመሆን ታላቅ አገልግሎት ያከናውናሉ።
፮. ሐመር፡- ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ማርያምን አትንኪኝ ስላላት ሴቶች በቤተ ክርስቲያን ወይም በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ቦታ የላቸውም ወይም እኩል አይደሉም የሚል ጥያቄ ይነሣልና ይህ እንዴት ይታያል?
መጋቤ ሐዲስ ምሥጢረ ሥላሴ ማናየ፡- ይህ ማለት ሴቶች የበታች ናቸው ማለት አይደለም። ለምሳሌ፡- በአንድ አካል ውስጥ ብዙ ብልቶች አሉ። የየራሳቸውን የሥራ ድርሻ ይሠራሉ እንጂ አንዱ የሌላውን ካልሠራሁ ሊል አይችልም። ባለመሥራቱም የበታች ነው ሊባል አይችልም። ዐይን እንደ ዐይንነቱ ያያል እንጂ እንደ ጆሮ ባለመስማቱ የበታች ነው አይባልም። ጆሮም እንደ ጆሮነቱ ይሰማል እንጂ እንደ ዐይን ባለማየቱ፣ እንደ አፍንጫ ባለማሽተቱ የበታች ነው ሊባል አይችልም። በቤተ ክርስቲያን የሴትና የወንድ የአገልግሎት ድርሻም እንዲሁ ነው።
ቤተ ክርስቲያን ለሁሉም ቦታ አላት። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤውን ለሴቶች ሲገልጥ ወንዶቹ የበታች ናቸው አልተባሉም። ወዳጁ ዮሐንስ ያውም እስከ መስቀል ድረስ ያልተለየው እያለ፣ የሐዋርያት አለቃ ቅዱስ ጴጥሮስ እያለ ለሴቶች ሲገለጥ ወንዶች የበታች ናቸው እንዳልተባለ ሁሉ የክህነት አገልግሎት ደግሞ የወንዶች ብቻ ስለሆነ ሴቶች የበታች ናቸው አያስብላቸውም። በክህነት አገልግሎት አይሳተፉ እንጂ በቤተ ክርስቲያን የየራሳቸው ድርሻ እንዳላቸው መገንዝብ ያስፈልጋል። ለምሳሌ፡- በጸሎተ ቅዳሴ ይበል ካህን፣ ይበል ዲያቆን፤ ይበሉ ሕዝብ የሚል አለ። በዚህ ውስጥ ይበሉ ሕዝብ በሚለው ላይ ሕዝብ ሲባል የወንዶችም የሴቶችም ድምር ማለት እንጂ ወንዶቹ ብቻ አይደሉም። ስለዚህ የበታችነትን የሚያሳይ አይደለም። ይልቅ በቅንነት መመልከት ያስፈልጋል።
ዓለም የሴቶች እኩልነት እያለ ሴቶች የበታች ተደርገው እንደሚታዩ እና የበላይ መሆን እንዳለባቸው ያቀነቅናል። ይሁን እንጂ ዓለም ስላቀነቀነ የበላይ ሊሆኑ አይችሉም። ቤተ ክርስቲያን ወንዶች የበላይ ናቸው ብላ ሳታስተምር ዓለም ወንዶች የበላይ ሁነዋል ስላለም የበላይ ናቸው ማለት አይደለም። ሲጀመር ወንድና ሴት እኩል ናቸው ወይስ አይደሉም? የሚለውን ጥያቄ ማንሣትም ተገቢ አይደለም። ምክንያቱም ከተፈጥሮ ጋር በተያያዘ የየራሳቸው ድርሻ ቢኖራቸውም ሁለቱም አስፈላጊ ናቸው። ከላይም እንደተገለጸው ዐይንና ጆሮ የየራሳቸው የሥራ ድርሻ አላቸው፤ የየራሳቸውንም ሥራ ይሠራሉ እንጂ አንዱ በሌላው ሥራ ጣልቃ አይገባም፤ ልግባም ቢል አይችልም። የየራሳቸው ድርሻ ያላቸው አካላት መሆናቸውና አንዱ የሌላውን ማከናወን አለመቻላቸው ደግሞ የበላይና የበታች ናቸው የሚያስብላቸው አይደለም።
ከነገረ ድኅነት አንጻርም ስንመለከተው በወንዶች ያልተመለሰ በሴቶች ማለትም በእመቤታችን በቅደስት ድንግል ማርያም በኩል ተመልሷል። ይህ ሲኖር ሴቶች ከወንዶች የበላይ ናቸው አያስብላቸውም። እንዲሁ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋውን ቆርሶ ደሙን አፍስሶ ሲያድነን ወንዶች ከሴቶች የበላይ ናቸው አያስብላቸውም። በነገረ ድኅነት ሴቶችም ወንዶችም እጅግ የጎላ ድርሻ አላቸው። ስለዚህ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ወንዶች ይበልጣሉ ሴቶች ያንሣሉ ብላ አስተምራ አታውቅም። ወደ ፊትም አታስተምርም።
ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የወንዶችንና የሴቶችን እኩልነት የምታረጋግጠው ተጋድሏቸውን የፈጸሙ ወንዶችንም ሆነ ሴቶችን ጽላት ቀርጻ፣ ገድል ጽፋ፣ ቤተ ክርስቲያን አንጻ፣ በስማቸው ዝክር ትዘክራለች፣ አማልዱን እያለች ትጸልያለች፣ በዓል ታከብርላቸዋለች። ጻድቁን አቡነ ተክለ ሃይማኖትን እንደምታከብር ሁሉ ቅድስት ክርስቶስ ሠምራንም ታከብራለች። ምክንያቱም ቤተ ክርስቲያን የምታከብረው ሰውነትን እንጂ ጾታን አይደለም። ሰው የሚባለው ደግሞ ከአራቱ ባሕርያተ ሥጋ ከሦስቱ ባሕርያተ ነፍስ የተፈጠረ ሴትም ወንድም ሁሉ እንጂ ወንድ ብቻ አይደለም።
፯. ሐመር፡- ከላይ ከተገለጸው በመነሣት የሴቶች በቤተ ክርስቲያን የሚኖራቸው አገልግሎት እስከምን ድረስ ነው የማያገለግሉበትስ የተገደበ አገልግሎት አለ ወይ?
መጋቤ ሐዲስ ምሥጢረ ሥላሴ ማናየ፡- ሴቶች የተከለከሉበት የአገልግሎት ድርሻ ማጥመቅ፣ ቀድሶ ማቍረብ፣ መባረክ፣ በዐውደ ምሕረት ወጥቶ መስበክ፣ ወዘተ. እነዚህን በመሳሰሉ የክህነት አገልግሎቶች ላይ አይሳተፉም። ከዚህ በቀር ከላይም እንደገለጽነው በማኅበር ጸሎት ይሰተፋሉ። በዚህ ጉባኤ ላይ ሴቶች ወጥተው አያስተምሩም እንጂ ተቀምጠው ይማራሉ። ጉባኤ በተዘረጋበት ጳጳሳት፣ ካህናት፣ ዲያቆናት በአጠቃላይ ከምእመናን በማዕረግ የሚበልጡ አካላት የሚገኙበት ነው። በዚህ ጊዜ ደግሞ ሴቶች ብቻ አይደሉም የተከለከሉት፤ ማንኛውም ሰው ተነሥቶ ሊያስተምር አይችልም። ሊያስተምሩ ፈቃድ ያላቸው፣ የተሾሙ መምህራን ያስተምራሉ እንጂ ማንኛውም ሰው አያስተምርም።
አገልግሎት ማለት ማስተማር ብቻ አይደለም ተቀምጦ የእግዚአብሔርን ቃል የሚሰማውም አገልጋይ ነው። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በማርታና በማርያም ቤት በገባ ጊዜ ማርታና ማርያም ያከናወኑትን አገልግሎትና የትኛው የተሻለ እንደነበር ወንጌላዊው ሉቃስ ሲገልጽ ማርታ ምግብ በማብሰል ትደክም እንደነበር ማርያም ግን ከጌታ እግር ሥር ተቀምጣ ትምህርቱን ትከታተል እንደነበር በዚህም የማርያም አገልግሎት እንደተመሰገነላት አስረድቷል። (ሉቃ.፲፥፴፰-፵፪)
ሴቶች ከላይ ከዘረዘርናቸው የክህነት አገልግሎቶች በቀር በሌላው ሁሉ ይሳተፋሉ። ለምሳሌ በሰበካ ጉባኤ ይሳተፋሉ፤ በሰንበት ትምህርት ቤት ውስጥ ባሉ የአገልግሎት ክፍሎች ኃላፊ እየሆኑ ማገልገል ይችላሉ። ከምንም በላይ ግን ከጥንት ጀምሮ ሴቶቹ በራቸውን ከፍተው ማዕድ አዘጋጅተው ነቢያትን፣ ሐዋርያትን፣ ሊቃውንትን፣ መምህራንን፣ ወዘተ. እየተቀበሉ ያስተናገዱ በርካታ ሴቶች ነበሩ። ለምሳሌ፡- በኤልያስ ዘመን መበለቲቱ ኤልያስን ከነበረበት ጽኑ ረኀብ የታደገችው፣ በሐዋርያትም ዘመን የሐዋርትን ምግብ በማዘጋጀት ያገለግሉ የነበሩ በርካታ ሴቶች ነበሩ፤ ዛሬም አሉ። አገልግሎት ማለት ደግሞ ይህ ሁሉ ተደምሮ ነው። አገልጋዮች ካልበሉ ሊያገለግሉ አይችሉም። ስለዚህ አገልጋዮች በአግባቡ ያገለግሉ ዘንድ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ደግሞ ዐውደ ምሕረት ላይ ወጥተው ከሚያስተምሩት ከመምህራኑ እኩል በረከትን የሚያስገኝ አገልግሎት ነው።
በአጠቃላይ ቤተ ክርስቲያን ሴቶች የሌሉበት አገልግሎት የላትም። ለምሳሌ፡- በዝክረ ቅዱሳን ማለትም ቅዱሳንን በምንዘክርበት በዓመታዊ በዓላትም ይሁን በወርኃዊ በዓላት ሴቶች አሉ። የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት በአግባቡ እንዲከናወን ለአገልጋዮቹ ሴቶች ምግባቸውን በማዘጋጀት ያስፈልጋሉ፤ ጥንቱንም ወንጌል የተዳረሰው በሐዋርያት ብቻ ሳይሆን ሐዋርያትን እየተከተሉ ለሐዋርያት ያገለግሉ በነበሩት ቅዱሳት አንስት ጭምር እንደሆነም መገንዘብ ያስፈልጋል።
፰. ሐመር፡- በመጨረሻ ከነገረ ትንሣኤው ጋር በተያያዘ ቀረ የሚሉት ሐሳብ ካለ ቢገልጹልን?
መጋቤ ሐዲስ ምሥጢረ ሥላሴ ማናየ፡- ያላነሣነው በዙ ነገር ይኖራል። ምሥጢረ ትንሣኤን ያህል ሰፊ ሐሳብ እንዲህ በአንድ ጊዜ አንሥተን ልንጨርሰውም አንችልም። ይሁን እንጂ ትንሣኤ ሙታን ከብሉይ ኪዳን ጀምሮ በትንቢትም በምሳሌያዊ ትንቢትም የተነገረ ነው። ይህ በትንቢትም ሆነ በምሳሌያዊ ትንቢት የተነገረው የጌታችን የመድኃኒታችንም የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤም የሙታን ትንሣኤም ነው። የጌታችንን ትንሣኤ የሚመለከት ምሳሌያዊ ትንቢት ማለት “ዮናስ ሦስት መዓልትና ሦስት ሌሊት በዓሣ አንበሪ ሆድ እንደ ነበረ እንዲሁ የሰው ልጅም ሦስት መዓልትና ሦስት ሌሊት በምድር ልብ ውስጥ ይኖራልና” (ማቴ.፲፪፥፵-፵፩) ተብሎ በዮናስ አንጻር የተነገረው ነው። ቀጥተኛ ትንቢት ደግሞ ነቢየ አግዚአብሔር ዳዊት “እግዚአብሔር ይነሣ ጠላቶቹም ይበተኑ” (መዝ.፷፯፥፩) በማለት የተናገረውን የሚመስል ነው።
የሙታንንም ትንሣኤ በተመለከተ ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ “ሙታን ይነሣሉ፤ በመቃብርም ያሉ ይድናሉ።” (ኢሳ.፳፮፥፲፱) በማለት ቀጥተኛ በሆነ ትንቢት ሲናገር ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደግሞ “እውነት እውነት እላችኋለሁ የስንዴ ቅንጣት በምድር ላይ ካልወደቀችና ካልሞተች ብቻዋን ትኖራለች፤ ከሞተች ግን ብዙ ፍሬን ታፈራለች” (ዮሐ.፲፪፥፳፬) በማለት ምሳሌያዊ በሆነ ትንቢት ተናግሯል።
ይህ የትንሣኤ ሙታን ጉዳይ በሐዲስ ኪዳን የትንሣኤያችን በኵር የሆነው ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጎ በመነሣት የእኛን ተስፋ ትንሣኤ አለምልሞታል። ሐዋርያትም ይህንኑ አምልተውና አስፍተው አስተምረውታል። ለምሳሌ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ “ጌታ ራሱ በትእዛዝ በመላእክትም አለቃ ድምፅ በእግዚአብሔርም መለከት ከሰማይ ይወርዳልና፣ በክርስቶስም የሞቱት አስቀድመው ይነሣሉ። (፩ተሰ.፬፥፲፮) በማለት የተናገረውን እንመለከታለን።
በአጠቃላይ በኵራችን ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጎ ተነሣ፤ እኛም እርሱን መስለን፣ እርሱን ተከትለን እንነሣለን። የእኛ ትንሣኤ ግን አማናዊው ትንሣኤ ይሆንልን ዘንድ አስቀድመን ትንሣኤ ልቡና መነሣት ያስፈልጋል። ካልሆነ ትንሣኤያችን ለክብር ሳይሆን ለኀሳር ሊሆንብን ይችላል። ይህን በተመለከተ ነቢየ እግዚአብሔር ዳንኤል “በምድርም ትቢያ ውስጥ ካንቀላፉት ብዙዎቹ እኩሌቶቹ ለዘለዓለም ሕይወት እኩሌቶቹም ለእፍረትና ለዘለዓለም ጕስቁልና ይነሣሉ።” (ዳን.፲፪፥፪) በማለት የተመለከተውን ራእይ ጽፎልን እናገኛለን። የክብር ትንሣኤ እንጂ የኀሳር ትንሣኤ ደግሞ ትንሣኤ ሊባል አይችልም። ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት “ስለዚህ ዝንጉዎች በፍርድ፣ ኃጥአንም በጻድቃን ምክር አይቆሙም” (መዝ.፩፥፮) በማለት እንደተናገረው እግዚአብሔር በሚመጣበት በፍርድ ቀን እናንተ የአባቴ ቡሩካን ከሚላቸው ጻድቃን ጋር በቀኝ መቆም ስለማይችሉ መነሣታቸው ባይቀርም ትንሣኤያቸው ግን የኀሳር ስለሆነ እንደ ትንሣኤ አይቆጠርም። ይህ እንዳይሆንና በቀኙ ከሚያቆማቸው ጋር ለመቆም እንድንበቃ ዛሬ ትንሣኤ ልቡና ተነሥተን በእግዚአብሔር ፈቃድ ተመላልሰን መኖር ያስፈልጋል። ትንሣኤ ልቡናን ተነሥተን በመጨረሻዪቱ የፍርድ ቀን በቀኙ እንዲያቆመን የእግዚአብሔር ቸርነት የድንግል ማርያም አማላጅነት የቅዱሳን መላእክት ጥበቃ የቅዱሳን ሁሉ ምልጃና ጸሎት አይለየን አሜን።
ሐመር፡- ላነሣናቸው ጥያቄዎች ተገቢውን መልስ ስለሰጡን በእግዚአብሔር ስም እናመሰግናለን።
መጋቤ ሐዲስ ምሥጢረ ሥላሴ ማናየ፡- እኔም አመሰግናለሁ።