Monday, 10 August 2020 00:00

ባለህበት ጽና

Written by  እንዳለ ደምስስ
በደቡብ ኦሞ የቅዱስ ቂርቆስ ቤተ ክርስቲያን ቀዳሽ ካህን የሆኑት ቀሲስ ተውህቦ ይሔይስ ኪዳን አድርሰው ምእመናንን ካሰናበቱ በኋላ ልብሰ ተክህኖአቸውን እንደለበሱ ቤተልሔም መግቢያ በር ላይ ካለው አግዳሚ ወንበር ተክዘው ቁጭ ብለዋል፡፡ ጠይም፣ ቀጭን፣ በግምት በአርባዎቹ የዕድሜ ክልል ላይ የሚገኙ አባት ናቸው፡፡ በአባታቸው አባ ይሔይስ ዘመን የቤተ ክርስቲያኑ አገልጋዮች ቁጥር ስፍር አልነበራቸውም፡፡ ከፊሎቹ ከዚህ ቤተ መቅደስ አልፈው ለሌሎች አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ይተርፉ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ ቤተ ክርስቲያኑ ሲመሠረት ጀምሮ የመጀመሪያው አገልጋይ ቀሲስ ይሔይስ ሲሆኑ ከሰማንያ ዓመታት በላይ አገልግለው ዕድሜ ገድቧቸው ካረፉ ዐሠር ዓመት አልፎታል፡፡  ከልጆቻቸው የአባታቸውን ፈለግ የተከተሉት ቀሲስ ተውህቦ ብቻ ሲሆኑ ከሕፃንነት ጀምሮ በአባታቸው እግር ሥር ሆነው ከፊደል እስከ ፲፬ቱ ቅዳሴያት ተምረዋል፤ ቤተ ክርስቲያኑንም የማስተዳደር ኃላፊነት አባታቸው ካረፉ በኋላ ተረክበው አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ አገልግሎት በመፈጸም ላይ ይገኛሉ፡፡ ነገር ግን ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ አገልጋይ ካህናትና ዲያቆናት ቤተ ክስቲያኑን ጥለው እየወጡ የተሻለ ክፍያ ወዳለበት ወደ ከተማ በመኮብለላቸው ተጨንቀዋል፡፡ የቀሩት እሳቸውና ሁለቱ ዲያቆናት ልጆቻቸው ብቻ በመሆናቸው ለምእመናን ቅዳሴ ቀደሰው ለማቁረብ፣ ቤተ ክርስቲያን በየጊዜው የምታከናውናቸውን ሃይማኖታዊ አገልግሎት ለመፈጸም ተቸግረዋል፡፡

 

በቤተ ክርስቲያኑ ቅጥር ውስጥ ጸጥታ ሰፍኗል፣ ቤተ ክርስቲያኑን ከበው የሚገኙት ሀገር በቀል ዛፎች ቅርንጫፎቻቸው ብቻ የነፋሱን እንቅስቃሴ ተከትለው ይወዛወዛሉ፣ ቀሲስ ተውህቦም እንደ ዛፎቹ ቅርንጫፎች በሐሳብ አንዱን እየጣሉ አንዱን እያነሱ ከራሳቸው ጋር ሙግት ገጥመዋል፡፡

-“እኔም ጥዬ ልሂድ ይሆን? ዲያቆናቱም ሆነ ካህናቱ የተሻለ ኑሮ ፍለጋ ከተማ ናፍቀው ሔደዋል፤ እኔ ብቻዬን እዚህ ምን እሠራለሁ? የአባቴን የአደራ ቃልስ ምን ላድርገው? ቤተሰቤስ፣ እጠብቃቸው ዘንድ ከእግዚአብሔር የተሰጡኝ ምእመናን በጎቼን ለማን በትኜ እሔዳለሁ፣ ለተኩላ አሳልፌ ሰጠኋቸው ማለት አይደል? እግዚአብሔር እንደንፈቀደው ያድረገኝ እንጂ ሌላው አደረገው ብዬስ እኔ አላደርገውም” አሉ ለራሳቸው የእጅ መስቀላቸውን በትካዜ እያገላበጡ፡፡

ከአንድ ወር በፊት አብሮ አደግ ወዳጃቸውና የዚሁ ቤተ ክርስቲያን አገልጋይ የሆኑት ቀሲስ ጥላሁን ከኪዳን ጸሎት በኋላ ከቤተ መቅደስ እየወጡ “አንድ መረጃ ይዣለሁ፡፡ ብንነጋገርበት ጥሩ ነው” በማለት ቀሲስ ተውህቦን እንደሚፈልጓቸው ይነግሯቸዋል፡፡

“በሰላም ነው የፈለግኸኝ?” አሉ ቀሲስ ተውህቦ ከቤተ መቅደስ እየወጡ፡፡

“አዎ፡፡ ካሰብንበት መታደል ነው” አሉ ግቢው ውስጥ ዛፍ ሥር ካለው መቀመጫ አረፍ እያሉ፡፡

“በል ንገረኝ ልስማዋ” አሉ ቀሲስ ተውህቦ ለመስማት ጓጉተው ቀሲስ ጥላሁን አጠገብ እየተቀመጡ፡፡ 

“ዕድሉን ከተጠቀምንበት ሕይወታችን ይቀየራል፡፡ መልካም ዜና ደርሶኛል፤ እንደምንም ተቸግረንም ቢሆን ሌሎች ወንድሞቻችን የደረሱበት መድረስ አለብን፡፡ እኛ የተሻለ ኑሮ አያምርበብንም እንዴ?” አሉ፡፡

“ለምን አትነግረኝም?”  

“ምን መሰለህ፤ ስንት ዓመት እዚህ ገጠር ውስጥ እንዳገለገልን ታውቃለህ? ይኸው አርባ ዓመታ አለፈን፡፡ የተለወጥነው ነገር አለ? ትላንትም ድሃ ነበርን ዛሬም ድሃ ነን፣ ከድህነት ሌላ ምን አተረፍን?” አሉ ቀሲስ ጥላሁን ትላንትን እየረገሙ፡፡

“አልገባኝም፡፡ ለምን ዳር ዳር ትላለህ ተናገረው እንጂ” አሉ ቀሲስ ተውህቦ ለመስማት የነበራቸው ፍላጎት ከስሞ በንዴት እየተመለከቷቸው፡፡

“እዚህ አብረውን ሲያገለግሉ የነበሩ ካህናት ምን ያህል እንደነበሩ የሚያውቁት ጉዳይ ነው፡፡ አንድ አንድ እያሉ ድህነትን ለማምለጥ ወደ ከተማ ገቡ፡፡ ሁሉም ተሳክቶላቸዋል፣ የደብር አለቃም የሆኑ አሉ፣ በየወሩ ከሦስት ሺህ ብር በላይ የሚከፈላቸውም አሉ፡፡ እኛ እዚህ ተቀምጠን ድህነት ውጦናል፣ መቼ ነው ደህና ልብስ የምንለብሰው? መቼ ነው ልጆቻችንን ደህና ትምህርት ቤት የምናስተምረው? እዚሁ ተወልደን እዚሁ ልንሞት ነው?” አሉ ቀሲስ ጥላሁን ቀሲስ ተውህቦን ለማሳመንና ልባቸውን ለማሸፈት እየሞከሩ፡፡

“እና ምን እናድርግ ነው የሚሉኝ?” ሁለቱም አንቱ የሚል የመከባበር ቅጽል ይጠቀማሉ፡፡

“አንድ ታማኝ ሰው አግኝቻለሁ፡፡”

“ምን የሚያደርግ?”

“ከተማ ላይ ካሉ አብያተ ክርስቲያናት የሚያስቀጥር፡፡”

“እኔ ቀዬን ትቼ የትም አልሔድም፡፡ እትብቴ የተቀበረበት፣ ክርስትና የተነሳሁበት፣ ከልጅነት እስከ ዕውቀት ያገለገልኩበትን ቤተ መቅደስ ዘግቼ፣ ግራ ቀኛቸውን የማያውቁ በጎቼን በትኜ፣ ለአውሬ ሰጥቼ የትም አልሔድም” አሉ ቀሲስ ተውህቦ በንዴት፡፡

“ትንሽ ብር ነው የምንጠየቀው፣ መክፈል ያቅተናል ብለው ፈርተው እንዳይሆን፡፡”

“እርስዎ መሄድ ይችላሉ፣ እኔ አደራዬን ትቼ ከዚህ የትም አልንቀሳቀስም፡፡”

“ስንት ብር መሰሎት የጠየቀው ለእያንዳንዳችን ሃያ ሺህ ብር ብቻ ነው፡፡ ካስታወሱ  እነ ቀሲስ ትእዛዙ የዛሬ ሁለት ዓመት ከዚህ ሲሔዱ የከፈሉት ሠላሳ ሺህ ነበር፡፡ ለእኛ ብዙ ቅናሽ ነው ያደረገልን” አሉ ቀሲስ ጥላሁን የወዳጃቸውን መበሳጨት ወደ ጎን በመተው፡፡

“መሄድ ይችላሉ፡፡ እኔ ሳይገባኝ ሥልጣነ ክህነትን የተቀበልኩት አምላኬ የደረሰበትን መከራ መስቀል እንዳስብ፣ በታማኝነት እስከ ሞት ድረስ እንዳገለግል እንጂ ለድሎት አይደለም፡፡ ይቅርታ አድርጉልኝ በሐሳብዎ አልስማማም፡፡”

“በሉ እንግዲህ ከነድህነትዎ ይኑሩ” ብለው ቀሲስ ጥላሁን ተስፋ ቆርጠው ትተዋቸው ከቤተ ክርስቲያኑ ቅጥር ወጡ፡፡

አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ አዲስ አበባ መጥተው የመቀጠራቸውን ዜና ምሽቱን ነበር ሰሙት፡፡ 

ቀሲስ ተውህቦ ከቤተልሔሙ አጥር ጥግ ካለው አግዳሚ ወንበር ላይ እንደተቀመጡ ልቡናቸው በሁለት ጥጋቸውን በያዙና ሊቀራረቡ እንኳን በማይችሉ ተቃራኒ ሐሳቦች ተከፍሎ ቆየ፡፡ 

-“እዚህ ምን ታደርጋለህ? ዘመኑ ተቀይሯል፣ ትንሽ ብር ከፍለህ ብዙ ወደሚገኝበት ከተማ ኮብልል፣ በአንድ ዓመት ተለውጠህ ትመጣለህ፡፡ አደራ አለብኝ እያልክ ወደ ኋላ አትቅር፡፡ ሒድ ሒድ…” ይላቸዋል አንደኛው ጽንፍ ሐሳብ፡፡

-“ይህ የሕይወትህ መሠረት የተጣለበት ቦታ ነው፡፡ እግዚአብሔርን ታገለግል ዘንድ የተሾምክበት ሥፍራ ስለሆነ የገባኸውን ቃል አትጠፍ፤ አባትህ እግዚአብሔር ፈቅዶላቸው ያጸኑት ቦታ ነው፡፡ እግዚአብሔር የሰጠህን መንጋ የት በትነህ ትሔዳለህ? ቆም ብለህ አስብ፣ መንገድህን አትሳት፣ እንደ ኤሳው በረከትህን አታስወስድ፣ ይህንን አገልግሎት ወደ ልጆችህ ለማስተላለፍ ያደረግኸውን ትጋት አስብ፣ ዛሬ ልጆችህ ደርሰውልሃል፣ ለዲቁና አብቅተሃል፣ አባትህ አንተን በመንገዱ እንደመራህ ልጆችህንም ምራቸው፡፡ አገልግሎትህን የሚረከቡ የአብራክህ ክፋይ ያገኘኸው በዚህ ቤተ መቅደስ አገልግሎትህ ነው፣ ይህ ሥፍራ ባለውለታህ እንደሆነ አስብ፣ ለአንተ የተፈቀደ ቦታ ይህ ነው፣ የትም አትሒድ ባለህበት ጽና …” ይላቸዋል፡፡ ተጨነቁ፡፡ 

ቀስ በቀስ ግን ሂድ- ሂድ እያለ ሲገፋቸው የነበረው ስሜት እየበረደ እዚሁ ቤተ ክርስቲያንን እያገለገሉ ከሚወዱትና ከሚወዳቸው ሕዝባቸው ጋር ለመኖር፣ ልጆቻቸውንና ሌሎችን ለማስተማር፣ ተተኪ ለማፍራት ቃል ገቡ፡፡ 

  

 

Read 1632 times