Friday, 04 September 2020 00:00

 መንግሥትና ቅዱስ ሲኖዶስ ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ  ይገባል  

Written by  ረቂቅ መቻል
ሀገራችን ኢትዮጵያ እንዲሁም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በዓለም ደረጃ እንዲታወቁ  ካበቋቸው ዋና ዋና ጉዳዮች መካከል  ታሪኮቻቸው ፣ ለዘመናት ተጠብቀው የቆዩት የሚዳሰሱ እና የማይዳሰሱ የቤተ ክርስቲያኒቱ ቅርሶች ፣  ቤተ ክርስቲያኒቷ  እምነትና ስልጣኔን ለማስተዋወቅ በዘመናት ውስጥ  የአብሪ ኮከብነት ሚናን ተጫውታለች፡፡ ለሀገር ሰላም እና ለሕዝብ አንድነት ብዙ ስትሰራ ቆይታለች። ለዚህ ሁሉ ውለታዋ  በየዘመናቱ የተቃጣባትን የማጥፋት ዘመቻ፣ ይደርሱባት የነበረውን ችግሮችና ፈተናዎች  በትዕግሥት አልፋ  እዚህ ደርሳለች፡፡     ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ያለፉትን የመከራ  እና የፈተና  ዘመናት  እንደየአመጣጣቸው ብትመክትም ሙሉ በሙሉ ከፈተና ነፃ ሆና አታውቅም፡፡ በዚህ በያዝነው ዓመት ብቻ እንኳ በቤተክርስቲያን ላይ የደረሰው ሃይማኖት ተኮር ጥቃት ለዐይን የሚከብድ፣ ለጆሮ የሚሰቀጥጥ ነበረ፡፡ አብያተ ክርስቲያናት ተቃጥለዋል፤ ክርስቲያኖች  በአክራሪዎች በግፍ ተገድለዋል፣ የምእመናን ሀብት ንብረታቸው ተቃጥሏል እንዲሁም ብዙዎች ከመኖሪያ ቀዬያቸው ተፈናቅለዋል፡፡ 

 

በየጊዜው በምዕመናን ላይ በሚፈጸሙ ድርጊቶች  ውስጥ አክራሪ ሃይማኖተኞች፣ የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች  እና  የመንግሥት አመራሮች በቀጥታና በተዘዋዋሪ ተሳታፊዎች እንደነበሩ መንግሥት ባደረገው ምርመራ መገለፁ ይታወሳል፡፡ በዚህ ሆን ተብሎ በሚፈፀም ጥቃት መንግሥት ተጎጂዎችን መልሶ  ከማቋቋም አንፃር  አስቸኳይ መፍትሔ በመስጠት ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት መጠናከር ያለው ሚና አናሳ ሆኖ ታይቷል፡፡ ከመነሻው መንግስት በቤተ ክርስቲያን እና በምዕመናንዋ ላይ የሚደርሰውን ጥቃት መከላከል እንዲሁም ጥበቃ ማድረግ ሲገባው በተለይም የሚመለከታቸው እና በአካባቢው የሚገኙ የመንግስት አካላት ኃላፊነታቸውን በተገቢው መንገድ ባለመወጣታቸው የተነሳ አብያተ ክርስቲያናት ፣አገልጋይ ካህናት እና ተከታይ ምዕመናን ለከፋ ጉዳት ተዳርገዋል፡፡

የምዕመኑን  በነፃነት ኃይማኖቱን የማራመድ   መብቱን ማስጠበቅ፤ ከአቅም በላይ ሆነው  ለተፈፀሙ ጥቃቶች አስቸኳይ ፍትሕን መስጠት፣ ይቅርታ መጠየቅ፣ ካሣ መክፈልና ግልፅ መመሪያዎችን አውጥቶ በጥንቃቄ መተግበር ከመንግሥት ይጠበቃል።  ይህን አለመደረጉ በአንድ  እምነት ተቋም ላይ የሚድርስ  ጉዳት  በዜጎችና በሀገር ኢኮኖሚ ላይ የሚያደርሰውን ተያያዥ አደጋ መገንዘቡ ተገቢ ነው፡፡

የቤተክርስቲያን ትልቁ ተልእኮዋ ምእመናን የቤተክርስቲያንን ትምህርተ ሃይማኖት፣ ሥርዐታቸውን፣ ሃይማኖታዊ ትውፊትንና የቅዱሳንን  ተጋድሎን  አውቀው  በሃይማኖታቸው ጸንተው እንዲኖሩ ፤ በእምነት በምግባር እንዲጎለብቱ እንዲሁም ወደ ክርስትና ሕይወት  ያልመጡ እንዲመጡ ማድረግ ነው፡፡ ሁሉም የእምነት ተቋማት  ያለመድሎ በእኩል ዐይን  ሕግና ርትዕን እንዲያገኙ ማድረግ ደግሞ የመንግሥት ትልቁ ድርሻው ነው፡፡

በየትኛውም የመንግሥት ሥልጣን ላይ የተቀመጡ ግለሰቦች ከእኩይ ተግባራቸው ተቆጥበው ሀገርንና ሕዝብን በአግባቡ እንዲያገለግሉ መንግሥት ትኩረት ሰጥቶና  ችግሮችን በመለየት ረገድ  ኃላፊነቱን በተግባር ሊወጣ ይገባል፡፡ አንዳንድ ጽንፈኛ ግለሰቦች የሀገሪቱን ጤናማ ታሪክና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ለሀገር ያደረገችውና እያደረገች ያለውን አስተዋጽኦ ለማጠልሸት የቤተክርስቲያንን ቅርስ በመዝረፍ፣ የቤተክርስቲያን ዐበይት በዓላትን በማስታጎል፣ ንዋየ ቅዱሳት የአምልኮ መገለጫነታቸው እንዲረሳና ወደ ሀገራችን በሚገቡ ቱሪስቶች በሸቀጥነት እንዲታዩ የሚደረግ የሚዲያ ዘመቻ  ሲከናወንም እያየን ነው ።  

እነዚህ ጽንፈኛ ግለሰቦች ክርስቲያኖች በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፍ ያላቸውን ጉልህ ድርሻ በማዳከም በእምነቱና የእምነቱ ተከታዮች ላይ የሚደረገው  የሥነ ልቡና ቁማር ቤተ ክርስቲያንም ሆነች ምእመናንዋ  ለሀገር ያበረከቱትን አስተዋጽኦ በሐሰት ትርክት ብቻ አሉታዊ ገጽታ በማስያዝ ክርስትናንና ቤተክርስቲያንን ጠል የሆነ ትውልድ እንዲፈጠር እየተደረገ ነው፡፡

በእርግጥ  ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ላይ መሥራት ለሀገር መሥራት  ነው፡፡ በአንጻሩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶን ክብር አለመጠበቅ ኢትዮጵያን ማዋረድ ነው፡፡ ስለሆነም ይህች ሀገር የሆነች ሐዋርያዊት  ቤተክርስቲያን  ለኢትዮጵያ ዕድገት ያበረከተቻቸውን በርካታ አስተዋፅዖዎች ተዘርዝረው የሚያልቁ አይደሉም። ያሏትን ታላላቅ ገዳማት አድባራት፣ እንዲሁም የሀገሪቷን ታሪክ ሰንደው የያዙትንም ጭምር  ደኅንነታቸውን ከማስጠበቅ አኳያ መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ ሊሠራ ይገባል፡፡ 

 አሁን አሁን ‹‹ቤተ ክርስቲያን የማን ናት?  ቤተ ክርስቲያን የኛ  ወይስ የነሱ? የየትኛው ብሔር? የየትኛው ጎሣ? ›› ወዘተ የሚሉት ጥያቄዎች በብዙዎች የሚነሡ፤ በአንዳንድ አካባቢዎች በምእመናን መንፈሳዊ ሕይወት ላይ ትልቅ እንቅፋት እስከመሆን የደረሱ ጉዳዮች ናቸው፡፡ ነገር ግን ቤተክርስቲያን የሁሉም እናት፣  ሰው የሆነውን ፍጡር ሁሉ አቃፊና ደጋፊ  መሆኗን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ በአንዳንድ  አካባቢዎች ላይ በቸልተኝነት ጥቃት እየደረሰ ያለውም  ይህንኑ ማንነቷን በግልጽ ባላወቁና ባልተገነዘቡ ግለሰቦች፣ የመንግሥት ባለሥልጣን ፣የፖሊስ አካላትና የጸጥታ ኃይሎች  መሆኑ እሙን ነው፡፡

ቤተ ክርስቲያን ከአንድ ዘርና ከአንድ አካባቢ የመጣች ወይም የአንድ ቋንቋ ተናጋሪ ብቻ አይደለችም ፡፡  ከዚህ ጋር በተያያዘም በቤተክርስቲያን መዋቅር ውስጥ ያሉ አካላት  በቤተ ክርስቲያን ላይ በዘር፣ በጎሳ፣ በቋንቋ፣ከባህል ጋር በተያያዘ  እየደረሰ ያለውን ጥቃትና አስተያየት ለመገምገምና በተግባር ጭምር መልስ ለመስጠት ያለው አመለካከት የላላ በመሆኑ  ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ 

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ አንድነት ከጥንት ጀምሮ ጠንካራ መሠረት ያለው  መሆኑ ቢታወቅም በአሁኑ ወቅት ይህ አስተዳደራዊ አንድነቷን አደጋ ላይ የሚጥሉ አንዳንድ ምልክቶች መታየት ጀምረዋል፡፡ ስለዚህ ከላይ የተነሡት ጉዳዮች በመንግሥት፣ በሚመለከታቸው አካላት ብሎም በቤተክርስቲያን አመራሮች ትኩረት የሚሹ የቤተ ክርስቲያን ጉዳዮችና ችግሮች መሆናቸው ይታወቃል፡፡ በቃለ ዓዋዲው መሠረት የቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ አሠራር መጠናከር አለበት፡፡ ከመንፈሳዊው አገልግሎት ጎን ለጎን አስተዳደራዊ የሥራ ጥራትን ለመፍጠር በተገቢው ሥፍራ ተገቢውን ሰው በመመደብ በአስተዳደር ላይ ያሉ አባቶችን በተገቢው  የአስተዳደር ዕውቀት ማጎልበት ያስፈልጋል፡፡ መንግሥትም ኦርቶዶክሳውያን ላይ  በሕግ ሽፋን ስም በካህናትና ምእመናን  ላይ የሚደርሰውን እንግልት ማስቆም፣ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታይ ያልሆኑ የመንግሥት ባለ ሥልጣናት በኦርቶዶክስ ምእመናን ሕይወትና አስተምህሮ ላይ የሚያርጉትን ጥላቻና  በአንዳንድ መገናኛ ብዙኃን  አማካኝነት በቤተክርስቲያንና በምእመናንዋ  ላይ  ጥቃት እንዲደረግ የሽብር ቅስቀሳ  በሚያደርጉት ግለሰቦች የፖለቲካና  የሐሰት ትርክት አራማጆች ላይ መንግሥት አስተማሪ ርምጃ ሊወስድ ይገባል እንላለን፡፡   

 

Read 557 times