Friday, 04 September 2020 00:00

መንግሥት ለምእመናን አፋጣኝ የደኅንነትና የኑሮ ዋስትና እንዲሰጥ ቤተክርስቲያን አሳሰበች

Written by  ካሳሁን ለምለሙ
የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳን ድንገተኛ ሞት ሽፋን በማድርግ በአንዳንድ የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች በአክራሪ ሙስሊሞች ጥቃት ከተፈጸመባቸው ምእመናን የቀሩትን  መንግሥት አፋጣኝ የደኅንነትና የኑሮ ዋስትና ሊሰጣቸው እንደሚገባ  ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ነሐሴ ፳ ቀን ፳፻፲፪ ዓ/ም ባወጣችው መግለጫ አሳሰበች፡፡  ተጎጂዎች በእምነታቸው ምክንያት ከደረሰባቸው የተቀናበረ ስልታዊ ጥቃት በኋላ የደኅንነት ስጋት ላይ እንደሚገኙ ቤተክርስቲያን ያረጋገጠች ሲሆን ምእመናኑ በአሁኑ ሰዓት ያሉበት ሁኔታም ለኮሮና ቫይረስ እና ለሌሎች ተላላፊ በሽታዎች በሚያጋልጣቸው ሁኔታ እንደሆነ ታውቋል፡፡ በመሆኑም የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥትና የፌደራል መንግሥት የኦርቶዶክሳውያንን በሕይወት የመኖር፤ ሀብትና ንብረት የማፍራት ፤ ሰብአዊ እና ዜጋዊ መብታቸውን እንዲሁም የደኅንነት እና የመኖር ዋስትናቸው በአፋጣኝ እንዲከበርላቸው ቤተክርስቲያን በመግለጫዋ ጠይቃለች፡፡ መንግሥት ጥቃቱን ያቀዱትን፤ የፈጸሙትንና ያስተባበሩትን ኃይሎች እንዲሁም የተጣለባቸውን መንግሥታዊ ኃላፊነት ወደጎን ትተው የተፈጸመውን ጥቃት በዝምታ የተመለከቱ በመንግሥት በመዋቅር ውስጥ ያሉ ሹማምንቶችንና የፀጥታ አካላትን በሙሉ በቁጥጥር ሥር በማዋል እና በሕግ ተጠያቂ በማድረግ እስከመጨረሻው ድረስ በአካባቢው ፍትሕ እንዲሰፍን የማድረግ ተግባር  እንደሚጠበቅበትም አስገንዝባለች፡፡  በአሳዛኝ ሁኔታ በደልና ግፍ የተፈጸመባቸው ኦርቶዶክሳውያን ምእመናን ሆነው እያለ፤ ነገር ግን በጥቃቱ ምንም ሱታፌ ሳይኖራቸው  የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ በመሆናቸው ብቻ በእስር  እየተንገላቱ የሚገኙ ንጹሓን ምእመናን ጉዳያቸው በጥንቃቄ ታይቶ ከእስር እንዲፈቱ ቤተ ክርስቲያኒቱ መንግሥትን አሳስባለች፡፡ አንዳንድ የመንግሥት ባለሥልጣናትና የፖለቲካ ፓርቲዎችም በግፍ በተገደሉ ምእመናን ላይ ከመሳለቅ እንዲቆጠቡና መንግሥትም ክትትል አድርጎ በእነዚህ አካላት ላይ አስፈላጊውን ሕጋዊ ርምጃ እንዲወስድ ቤተ ክርስቲያን አጥብቃ ጠይቃለች፡፡    መንግሥት በዚህ ዓመት በጥቅምት፣ በጥር እንዲሁም በሰኔ ወራት በምእመናን ላይ ከተፈጸመ ግድያ፣ ዘረፋ እና በአብያተ ክርስቲያናት ላይ  ከደረሱ ጥቃቶች ጀርባ  ያሉትን አጥፊዎች አጣርቶ  ለፍርድ እንዲያቀርብ እና ውጤቱንም በይፋ ለሕዝብ እንዲገልጽ በመግለጫው አጽንኦት ሰጥታ አሳስባለች፡፡    
Read 847 times