Friday, 06 August 2021 00:00

ዓለም አቀፍ ሰላም አስከባሪዎች ከአፍጋኒስታን መውጣታቸውን ተከትሎ የአፍጋኒስታን ክርስቲያኖች ዓለም በጸሎት እንዲያስባቸው ጠየቁ

Written by  ካሳሁን ለምለሙ
ዓለም አቀፍ ሰላም አስከባሪዎች ከአፍጋኒስታን ለመውጣት በዝግጀት ላይ መሆናቸውን ተከትሎ በሀገሪቱ የሚኖሩ ክርስቲያኖች በአክራሪ ሙስሊሞች ሊደረስባቸው የሚችለውን ጥቃት በማሰብ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በጸሎት እንዲያስባቸው ጥሪ ማቅረባቸውን የቪዥን ክርስቲያን ሬዲዮን ዘገባ ጠቅሶ አዓም አቀፍ ክርስቲያን ኮንሰርን ዘገበ፡፡   በአፍጋኒስታን የሚኖሩ አብዛኛዎቹ ክርስቲያኖች ዓለም አቀፍ የሰላም አስከባሪ ኃይሎች ከሀገሪቱ መውጣት ለታሊባን እስላማዊ የሽብር ቡድን የጭቆና አገዛዝ መመለስ እና ለክርስቲያኖች ስደት በር እንደሚከፍት ገልጸዋል ሲል ዘገባው አስታውቋል፡፡  የአሜሪካ እና የኔቶ ሰላም አስከባሪ አባል ሀገራት እስከ ነሃሴ ፳፻፲፫ ዓ.ም ድረስ ሙሉ በሙሉ ከአፍጋኒስታን ለመልቀቅ መወሰናቸውን ዘገባው የገለጸ ሲሆን በታሊባን እና አሁን ባለው የአፍጋኒስታን መንግሥት መካከል የሰላም ስምምነት ባለመኖሩ ታሊባን ሀገሪቱን መልሶ እንዲቆጣጠር ያደርገዋል ተብሏል፡፡

 

ዓለም አቀፍ የሰላም አስከባሪ ኃይሎች የመልቀቂያ ጊዜ እየቀረበ ባለበት በዚህ ወቅት ታሊባን በመላ ሀገሪቱ ቁጥጥሩን እያሰፋ ወደ ፻፬ ወረዳዎች ያህል እንደደረሰ ዘገባው አስታውሶ፤ በተለይ የሀገሪቱ ክርስቲያኖች ላይ ያነጣጠረ ግድያዎችን እየፈጸመ መሆኑ ታውቋል፡፡  

የአፍጋኒስታን ክርስቲያን ማኅበረሰብ በአብዛኛው ከእስልምና ወደ ክርስትና እምነት የተቀየረ ሲሆን በተለይ እነዚህ ተመላሽ ክርስቲያኖች በአፍጋኒስታን  በግልጽ በሚንቀሳቀሱት ታሊባን እና አይ ኤስ ፅንፈኛ የሽብር ቡድኖች ተደጋገሚ ጥቃት ይፈጸምባቸዋል ሲል ዘገባው አስረድቷል፡፡

እንደ ኦፕን ዶርስ መረጃ ከሆነ ደግሞ “በአፍጋኒስታን ውስጥ አንድ ሰው ክርስቲያን ሆኖ በግልፅ መንቀሳቀስና መኖር እንደማይችል ነው፡፡ ዕምነትን ከእስልምና ወደ ክርስትና ሃይማኖት መቀየር ነውር ተደርጎ የሚቆጠርባት አፍጋኒስታን፤ ክርስትናን የተቀበሉ ሰዎች ከተገኙ አስከፊ ቅጣት እንደሚጠብቃቸው ዘገባው አስረድቶ ወይ ከሀገር መሰደድ አለባቸው፣አለበለዚያ ደግሞ ይገደላሉ ሲል አክሏል፡፡ 

በኦፕን ዶርስ መረጃ  መሠረት ክርስቲያኖችን በማሳደድ አፍጋኒስታንን የምትቀድመው ሀገር ሰሜን ኮሪያ ብቻ ስትሆን ይህም በዓለም ክርስቲያኖችን በማሳደድ ከተዘረዘሩት ሀገራት መካከል አፍጋኒስታንን በሁለተኛ ደረጃ ላይ አስቀምጧታል፡፡

 

Read 444 times