የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ይዞታዎቿን በሕግ አግባብ የማስከበርና የማልማት ውስንነቶች እንዳሉባት የቤቶችና ሕንጻዎች አስተዳደር ልማት መምሪያ ኃላፊ አፈ መምህር ቆሞስ አባ ገ/ሥላሴ ገለጡ።
ኃላፊው ይህንን የገለጡት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጠቅላይ ቤተ ክህነት ግቢ ውስጥ እየተሠሩ ያሉ የልማት ሥራዎችን የማኅበረ ቅዱሳን መደበኛ አገልጋዮች በጎበኙበት ወቅት ባደረጉት ገለጻ ነው።
በርካታ የቤተ ክርስቲያን ይዞታዎች በግለሰቦችና በመንግሥት እጅ መሆናቸውን የጠቀሱት ኃላፊው እነዚህን ቦታዎች አስመልሶ ይዞታቸውን በማረጋገጥ ማልማት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
ኃላፊው አያይዘውም ከዚህ ቀደም በአዲስ አባባ ከተማ አስተዳደር በመንግሥትና በግለሰቦች እጅ ተይዘው ከነበሩ ሕንጻዎች የተወሰኑትን ማስመለስ ቢቻልም ሌሎች ያልተመለሱ በርካታ ሕንጻዎችና ሌሎች ይዞታዎች እንዳሉ አስታውቀው ይዞታዎቹን ለማስመለስም ቤተ ክርስቲያንም ሆነች ልጆቿ አስፈላጊውን ሙያዊ እገዛ ማድረግ እንዳለባቸው አስረድተዋል።
ለቤተ ክርስቲያን የተመለሱ ይዞታዎችን ለማልማትና ለማስመለስ በሂት ላይ ያሉትንም በፍጥነት እንደሚለሱ ባለድርሻ አካላት በሙሉ ጥረት ሊያደርጉ እንደሚገባ ኃላፊው አስረድተው የቤተ ክርስቲያን ልጆች የሆኑ ባለሙያዎች ሁሉ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ መልእክት አስተላለፈዋል።
በዚህ ወቅት እየለሙ ያሉ የቤተ ክርስቲያን ይዞታዎች በሙሉ የልማት ሥራዎቻቸው በሙያቸው በተመሰከረላቸው የቤተ ክርስቲያን ልጆች እየተመሩ መሆናቸውን ያስታወቁት ኃላፊው ይህም የቤተ ክርስቲያን ልጆች ጥበበኛ እጆች እንዳሏቸውና ሃይማኖታዊና ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን የመምራት አቅም እንዳላቸው ማሳያ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
በመጨረሻም በአሁኑ ወቅት ቤተ ክርስቲያን በልማት እንቅስቃሴ ላይ መሆኗን ኃላፊው ገልጠው በተሻለ ሁኔታ የልማት ተጠቃሚ እንድትሆን ሁሉም የቤተ ክርስቲያን ልጆች የበኩላቸውን እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።