ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ የቅዱስነታቸውን ሞት ከሰሙበት ዕለት ጀምሮ ታላቅ ኀዘን እንደተሰማቸው ገልጠው በራሳቸውና በቅዱስ ሲኖዶስ ስም እኅት ቤተ ክርስቲያን ለሆነችው የሕንድ ማላንካራ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ፣አገልጋይ አባቶችና ምእመናን ልዑል እግዚአብሔር መጽናናትን እንዲሰጣቸው ተመኝተዋል፡፡
የሕንድ ማላንካራ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማርቶማ ፓውሎስ ፪ኛ ሦስት ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናንን እንደባረኩና ለሀገራችን ፍቅራቸውን እንደገለጡ ያስረዱት ቅዱስ ፓትርያርኩ ቅዱስነታቸው በዚያን ጊዜ ባደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ምእመናን በከፍተኛ ፍቅርና ደስታ እንደተቀበሏቸው ገልጠዋል፡፡
ቅዱስነታቸው አያይዘውም ‹‹በተለይ በ፳፻፲ ዓ.ም በኢትዮጵያ መስቀል ዐደባባይ በተከበረው የመስቀል በዓል ወቅት ቅዱስ ፓትርያርኩ በቦታው ተገኝተው የሰጡት ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ በሁሉም አገልጋዮችና ምእመናን ልብ ውስጥ ሲታወስ ይኖራል›› ብለዋል፡፡
ቅዱስነታቸው ሁለቱ እኅት አብያተ ክርስቲያናት የበለጠ ጠንካራ ግንኙነት እንዲኖራቸው ከመሥራት ባሻገር በአጠቃላይ አኅት አብያተ ክርስቲያናት መካከል መልካም የሆነ ታሪካዊ ትሥሥር እንዲኖር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በደብዳቤው ገልጠዋል፡፡ አክለውም የቅዱሳን አባቶቻችን አምላክ ለዑል እግዚአብሔር የቅዱስነታቸውን ነፍስ ከቅዱሳን አባቶቻችን ከሐዋርያት ጎን በሰላም እንዲያሳርፍልን ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በኦፕን ዶርስ መረጃ መሠረት ክርስቲያኖችን በማሳደድ አፍጋኒስታንን የምትቀድመው ሀገር ሰሜን ኮሪያ ብቻ ስትሆን ይህም በዓለም ክርስቲያኖችን በማሳደድ ከተዘረዘሩት ሀገራት መካከል አፍጋኒስታንን በሁለተኛ ደረጃ ላይ አስቀምጧታል፡፡