Saturday, 15 May 2021 00:00

የአፍሪካ  ክርስቲያኖች ለከፍተኛ ጥቃት ተጋላጭ መሆናቸውን የሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን  አስታወቀች

Written by  ካሳሁን ለምለሙ

Overview

በአሁኑ ወቅት የአፍሪካ ክርስቲያኖች ለከፍተኛ አካላዊና ሥነ ልቡናዊ ጥቃት ተጋላጭ መሆናቸውን የሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በሪፖርት ማስታወቋን ኦርቶዶክስ ታይምስ ዘገበ፡፡  በተለይ በናይጀሪያ ክርስቲያኖች ላይ እተፈጸመ ያለው ጥቃት የዓለምን ትኩረት እየሳበ መምጣቱን ያነሳው ዘገባው ሀገሪቱም በክርስቲያኖች ላይ ከፍተኛ ጥቃት ከሚፈጸምባቸው የዓለም ሀገራት መካከል ቀዳሚ መሆኗን አስታውሷል፡፡ እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር በ2012 ዓ.ም በናይጀሪያ ክርስቲያኖች ላይ የተፈጸመው ጥቃት ከ2011 ዓ.ም ጋር ሲነጻጸር በአንድ ሦስተኛ እንደጨመረ ዘገባው አስረድቶ ከዓለም በአሰቃቂ ሁኔታ ከሚገደሉ ክርስቲያኖች መካከል ዘጠና በመቶ ያህሉን እንደሚይዙ አስታውቋል፡፡  በመላው ዓለም በግፍ ከተገደሉት አራት ሺህ ሰባት መቶ ስልሳ አንድ ክርስቲያኖች መካከል አራት ሺህ ሦስት መቶ ሠላሳ ሦስት ያህሉ ናይጀሪያውያን ክርስቲያኖች እንደሆኑ ያነሳው ዘገባው ለክርስቲያኖች የሞትና የስጋት ምክንያት የሆነው ደግሞ “ቦኮሐራም” የተባለው የሽብር ቡድን መሆኑን በዘገባው ተገልጧል፡፡ የሽብር ቡድኑም እንደ እኤአ ከ፳፻፲፩ ዓ.ም ጀምሮ በናይጀሪያ ጥቃት እንሚፈጽም ከዘገባው ለመረዳት ተችሏል፡፡   በሶማሊያ፣ በኬንያ እንዲሁም በሌሎች የአፍሪካ ሀገራት “አልሸባብ” የተባለው የሽብር ቡድንም  በክርስቲያኖች ላይ ከፍተኛ እልቂት እየፈጸመ እንደሚገኝ የገለጠው ዘገባው የሽብር ቡድኑ በአብዛኛው የከተማ አውቶብሶችን በማስቆም ክርስቲያኖችን ከሙስሊሞችና በመለየት በክርስቲያኖች ላይ አሰቃቂ ጥቃት እንደሚፈጽም ተመላክቷል፡፡  በሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አማካይነት ተዘጋጅቶ የቀረበው ሪፖርት ‹‹የአፍሪካ ክርስቲያኖች ሁኔታ›› በሚል ርእስ  ሲሆን በዋናነት በቤተ ክርስቲያኗ ቅዱስ ሲኖዶ የውጭ ግንኙነት ክፍል በኩል ተዘጋጅቶ በሞስኮ መንበረ ፓትርያርክ ጽ/ቤት በይነ መረብ በኩል እንደወጣ ዘገባው የስረዳል፡፡  በተለያየ ጊዜ በአክራሪዎች ጥቃት ለተፈጸመባቸው የኢትዮጰያና የናይጄሪያ ክርስቲያኖች አስቸኳይ ሰብአዊ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ያስረዳው ዘገባው የአፍሪካ ክርስቲያኖችን ጥቃት በመረጃ በማስደገፍ ችግሩ በዓለም አቀፍ ደረጃ ትኩረት እንዲያገኝ ማድረግ ያስፈልጋል ተብሏል፡፡   
Read 530 times