Friday, 04 September 2020 00:00

በኮሮና ወረርሽኝ ወቅት በክርስቲያኖች ላይ የሚፈጸመው ጥቃት ጨምሯል ተባለ

Written by  ካሳሁን ለምለሙ
ዓለም በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እየተፈተነች ባለችበት በዚህ ወቅት በመላው ዓለም በሚገኙ ክርስቲያኖች ላይ እየተፈጸመ ያለው ጥቃትና መገለል እየጨመረ መሆኑን ኦርቶዶክስ ታይመስ ዘግቧል፡፡ በተለይም የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኘ በዓለም መከሠቱ ክርስቲያኖችን ለአካላዊና ሥነልቦናዊ ጥቃት እንዳጋለጣቸው ዘገባው አመልክቷል፡፡  በታዳጊ ሀገራት የሚኖሩ ክርስቲያኖች በተለይም ምግብና የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መከላከያ ቁሳቁስ እየተከለከሉ እንደሆነ የዩሲኤን ዘገባን ዋቢ አድርጎ ኦርቶዶክስ ታይምስ ዘግቧል፡፡  በተለይም በስደት ላይ የሚገኙ ኤርትራውያን ክርስቲያኖች መጠለያና የተባበሩት መንግሥታትን ድጋፍ ለማግኘት በሚያደርጉት ጥረት በአክራሪ ሃይማኖተኞች የሰፋ ጥቃት እየተፈጸመባቸው ነው ሲል ዘገባው አመላክቷል፡፡  የኮረና ቫይረስ ወረርሽኝ በዓለም ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ ለፓኪስታንና ለግብጽ ክርስቲያኖች ሕይወት እንደከበደባቸው ያነሣው የኦርቶዶክስ ታይምስ ዘገባ በእነዚህ ሀገራት የሚገኙ ክርስቲያኖች በከፋ ድህነት ውስጥ ይገኛሉ ብሏል፡፡ ክርስቲያኖቹ የዕለት ምግባቸውን ከማጣታቸው ባሻገር ራሳቸውን ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ለመጠበቅ የሚያግዟቸውን የፊት መሸፈኛ ጭንብልና የእጅ ንጽሕና መጠበቂያ ኬሚካል ጭምር በገንዘብ እጥረት ምክንያት እንዳላገኙ በዘገባው ተመልክቷል፡፡  በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሠተው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በክርስቲያኖች ላይ ለሚፈጸመው መገለልና ጥቃት አባባሽ እንደሆነ ከዘገባው የተገኘው መረጃ አመላካች ሲሆን በአንዳንድ የዓለም ሀገራት የሚገኙ ክርስቲያኖች እንደሁለተኛ ዜጋ እየተቆጠሩ እንደሆነም ታውቋል፡፡ የጥቃቱ ሰላባ እየሆኑ ያሉት ክርስቲያኖች ደግሞ ከእስልምና፤ ከሂንዱና ከቡዲሂስት እምነቶች የተመለሱ ናቸው ተብሏል፡፡  ክርስቲያኖች ከመንግሥታቸው ከሚያገኙት ሁለንተናዊ አገልግሎት በሃይማኖታቸው ምክንያት በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተገለሉ እንደሆነና እንደሁለተኛ ዜጋም እየተቆጠሩ እንደሆነ ያነሣው የኦርቶዶክስ ታይምስ ዘገባ የባንግላዲሽ፤ የማሌዥያ፤ የህንድ፣ የፍሊፕንስ፣ የናይጄሪያ እና የዓረቡ ዓለም ክርስቲያኖች ስለሚደርስባቸው መገለልና አካላዊ ጥቃት እንዲሁም ኢፍትሐዊ አያያዝ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አቤቱታ እንዳቀረቡ ከኦርቶዶክስ ታይምስ ዘገባ ለማወቅ ተችሏል፡፡      
Read 747 times