Friday, 04 September 2020 00:00

‹‹አንገቱ ላይ ማዕተብ ያሰረ ኦሮሞ አናውቅም››

Written by  ካሳሁን ለምለሙ

Overview

ክፍል አንድ ቤተ ክርስቲያን በክርስቶስ ደም ከተመሠረተችበት ዘመን ጀምሮ በርካታ ፈተናዎችን አልፋለች፤ወንጌልን ለዓለም ለማዳረስ  ብዙ ዋጋ ከፍላለች፡፡ በየዘመናቱ ለቤተ ክርስቲያን ጠላት ሆነው በተነሱ ከግለሰብ እስከ ገሥታት ድረስ ላደረሱበቸው መከራና ስቃይ አገልጋዮቹ ገፈት ቀማሽ ሆነው ኖረዋል። ቤተ ክርስቲያን፣  ንዋያት ቅዱሳት ሳይቀሩ ተቃጥለው ሲወድሙ ኖረዋል። ዛሬም በአምልኮቷ፣ በእምነቷ፣ በስርዓቷ እየመጡ ተከታዮቿንና እሷን ሲጎዱ ኖረዋል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሀገርን ባቆመች፣ ዳር ድንበርን ባስከበረች፤ በሚዳሰሱና በማይዳሰሱ ቅርሶቿ ሀገርን በዓለም አደባባይ ባስወቀች ውለታዋን መመለስ ሲገባ ሆን ተብሎ በችግር ውስጥ እንድታልፍ ሲደረግ ኖሯል። ለበርካታ ዘመናት ቤተክርስቲያንና ምእመናንዋ ተመርጠው የጥቃት ዒላማ ሲሆኑ ኖረዋል፡፡  አግዚአብሔር እንዳይመለክ፣ ምዕመናን ወደቤተ ክርስቲያን እንዳይሄዱ የተደረጉባቸው ሁነቶች የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ናቸው፡፡ አሁን አሁን እየገዘፈ እና እየበረታ የመጣው ደግሞ በሀገሪቱ ውስጥ የአንድ ሃይማኖት የበላይነትን ለማስፋፋት የሚመኙት የተስፈኞች ሴራ ቤተ ክርስቲያንና ምዕመናን ለምን በየጊዜው የጥቃት ኢላማ ይሆናሉ ለሚለው በቂ መልስ ነው፡፡ እነዚህ ተስፈኞች ሳር ቅጠሉ ሁሉ የእነርሱን ሃይማኖት ብቻ እንዲከተል የሚመኙ፤ ከፍ  ሲልም ከእነርሱ ሃይማኖት ውጪ የሆነ የሰውን ልጅ  ሁሉ ማረድ፣ ሀብት ንብረቱን መዝረፍ፣ ማቃጠል እንዲሁም እንዲሰደድ በማድረግ ቀን ከለሊት እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ በተለይ የኦርቶዶክሳውያንን ደም ካላፈሰሱ የሚረኩ አይደሉም፡፡ ተስፍኛውና አክራሪው ቡድን  ኦርቶዶክሳውያንን በጭካኔ ለመግደልና ሀብት ንብረታቸውን ለማውደም በአብዛኛው በሀገር ውስጥ የሚፈጠር ሁከትና ግርግርን ይመርጣል፡፡ በዚህ ወቅት የኦርቶዶክሳውያንን የአንገት ማዕተብ አስገድዶ ይበጥሳል፤ አስገድዶም ልብን ሳይሆን አካልን ያሰልማል፡፡ የዚህ አክራሪ ጽንፈኛ ኃይል የሃይማኖቴ ትርጓሜ “ሰላም” ነው ይበል እንጂ ከቃል ያልዘለለውን ፕሮፖጋንዳ ሽፋን አድርጎ የብዙ ንጹሓን ኦርቶዶክሳውያንን ሰላም ያናጋል፡፡ የያዝነውን ዓመት ጨምሮ ያለፉት ሁለት ተከታተይ ዓመታት ለዚህ ጽንፈኛ አክራሪ ቡድን የሽብር ወንጀሉን  ለመፈጸም ምቹ የመጫወቻ ሜዳ ሆነውለታል፡፡

 

ከሐምሌ ፳፰ እስከ ፲፱ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም ጅግጅጋን ጨምሮ በሱማሌ ክልል በሚገኙ ዞኖችና ወረዳዎች በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናትና ምእመናን ላይ በዐይን ለማየት የሚሰቀጥጥ አስከፊ ወንጀልን ተፈፅሟል፡፡ በጊዜው በርካታ ምእመናንና አገልጋዮች ያለምንም በደላቸው በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድለው አስከሬናቸው ተቃጥሏል፡፡ አብያተ ክርስቲያናት፣ የምእመናን የንግድ ተቋማት እንዲሁም መንፈሳዊ ተቋማት ለሕዝብ አገልግሎት መስጠታቸው እንደበደል ተቆጥሮ በግፍ ተዘርፈዋል፤ ተቃጥለዋልም፡፡ 

ይህ ጽንፈኛ አክራሪ ኃይል በወቅቱ ንጹሓን ኦርቶዶክሳውያንን በመግደል ብቻ አላቆመም፤ ይልቁንም ከጨቅላ ሕፃናት ጀምሮ እናቶችንና መነኮሳትን ሳይቀር በጭካኔ ደፍሯል፡፡  በጊዜው ሰማይ ምድር ለተደፋባቸው ኦርቶዶክሳውያን የሕግ የበላይነትን የሚያከብር ጠፋ፣  ሕግ አስከባሪው ሳይቀር  ሕግን ጣሰ፣  ክቡሩ የሰው ልጅ ሕይወት እንደዋዛ ጠፋ፡፡ ሕፃናት ሲደፈሩ፣ እናቶች ሲታረዱ የአባቶች ደም በከንቱ ሲፈስ “ፀጥታን አስከብራለሁ” የሚለው ኃይል መከራቸውን ቁሞ እየተመለከተ በእነርሱ ሥቃይና ሰቆቃ ሐሴት ያደርግ ነበር፡፡ 

ይህ ጽንፈኛና ቀቢፀ ተስፋን ያነገበ የጥፋት ቡድን በሃይማኖት እኩልነት የማያምን በመሆኑ የተለመደውን ከጥቅምት ፲፪ እስከ ፲፬ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በሚገኙ በርካታ ሀገረ ስብከቶች የጥፋት ድግሱን ደገሰ፡፡ አክራሪው በወቅቱ እንደመነሻነት የተጠቀመው አቶ ጀዋር መሐመድ የተባለው ግለሰብ ያስተላለፈውን የፌስቡክ የተከብቤአለሁ ጥሪ ነበር፡፡ ይህ የተከብቤአለሁ ጥሪ ኦርቶዶክሳውያኑን ዒላማ ያደርገ ስለነበር በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ ዞኖች፣ ወረዳዎችና ቀበሌዎች በኦርቶዶክሳውያንና በአብያተ ክርስቲያናቱ ላይ ከፍተኛ ወረራ ተካሄደ፡፡ በወቅቱ በርካታ ኦርቶዶክሳውያን ታርደው ሕይወታቸው በከንቱ እንዲያልፍ ተደረገ፡፡ በርካቶችም ለአካልና ለሥነ ልቡና ጉዳት ተዳረጉ፡፡ አብያተ ክርስቲያናትም ከነቅርሶቻቸው ወደሙ፤ የኦርቶዶክሳውያኑ መኖሪያ ቤቶችና የንግድ ተቋማት እንዳልሆኑ ሆነው ወደሙ፡፡ በሺዎች የሚቆጠሩ ምእመናን ቀያቸውን ጥለው ተሰደዱ፡፡ የመሰደድ ዕድሉን ያላገኙ ሌሎች ምእመናን ደግም በአረመኔው እጅ በጭካኔ አገዳደል የእሳት እራት ሆኑ፡፡ አጥፊው ሳይጠየቅ እንዳላየ ታለፈ፡፡ ፍትሕ በዚህ  መልክ በመዛባቱ የተከብቤአለሁ ጥሪ ያስተላለፈው ግለሰብም ሆነ አጋፋሪዎቹ ምንም ነገር እንዳልፈፀሙ ተቆጥሮ በነፃነት እየሸለሉና ለሌላ ጥፋት ዝግጅት እያደርጉ ኑሯቸውን ቀጠሉ፡፡ ነገር ግን የፍጥርታት ሁሉ አምላክ እግዚአብሔር አንድ ቀን የምእመናኑን ዕንባና ጸሎት ተመልክቶ የተሻለ ጊዜ ይዞ እንደሚመጣና ገዳዮቹ በፍርድ አደባባይ እንደሚቆሙ ይጠበቅ ነበር፡፡ እግዚአብሔር ቢዘገይ እንጂ የሚቀድመው የለምና ገዳዮቹና እስገዳዮች በተወሰነ ደረጃ በፍርድ አደባበይ መቆም ጀመረዋል፡፡ 

የአክራሪ ቡድኑ የበላይ ጠበቂዎች ወደፍርድ አደባባይ ከመቅረባቸው በፊት ሦስተኛውንና የመጨረሻቸው ይሆናል ተብሎ የማይጠበቀውን ሃይማኖታዊ የሽብር ድግስ በተለመደው ሕግና ሥርዓት ባልተከበረበት አንዳንድ ኦሮሚያ ክልል አደረጉ፡፡ በዚህ ክልል ባለፉት ጥቂት ዓመታት ለተፈጸመው ኢሰብአዊ ሃይማኖታዊ ጭፍጨፋ ክልሉ የሕግ የበላይነትን ባለማስከበሩ የልብ ልብ የተሰማው አክራሪው የጥፋት ኃይል ሰኔ ፳፪ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም ከምሽቱ ሦስት ሰዓት ጀምሮ የተለመደውን ጥፋት በነዚያ ጠባቂና መከታ በሌላቸው ኦርቶዶክሳውያን ላይ አካሄደ፡፡ 

ግርግርን እንደ አዒላማው ማስፈፀሚያ የሚጠቀመው አክራሪው ቡድን የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳን ድንገተኛ ኅልፈት ተከትሎ ‹‹ኀዘኔን ለመግለጥ ነው የወጣሁት›› በሚል ሰበብ እንደተለመደው ኦርቶዶክሳውያኑን በደም ጎርፍ አጠበ፡፡ ሀብት ንብርታቸውን ዘረፈ፤ አቃጠለ!! 

የተደራጀው አክራሪ ጽንፈኛ ቡድን በOMN (በኦ መ,ኤም ኤን)፣ በTigray TV (በትግራይ ቴሌቭዢኝ)፣ እንዲሁም እንዲሁም DW (በድምፀ ወያኔ የቴሌቭዥን ጣቢያዎች)  የተለመደ የወንጀል ድርጊቱን ለመፈፀም የክተት አዋጅ ነጋሪት ከጎሰመ በኋላ ከምሽቱ ሦስት ሰዓት ጀምሮ የሰው ልጅ በሥራ የደከመ ጎኑን ባሳረፈበት ሰዓት ጭፍጨፋውና እልቂቱ ጀመረ፡፡ ከታማኝ ምንጭ በተገኘው መረጃ መሠረት ጽንፈኛው አክራሪ ኃይል የተደራጀ ጥቃቱን ለዒላማ በተዘጋጁ በአስር ዞኖች፣ በሁለት ከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም በአምስት ወረዳዎችና ከተማዎች በጭካኔ ፈጸመ፡፡ በስም የተለዩ ሃምሳ ሁለት ንጹሓን ኦርቶዶክሳውያንን በማረድ፣በመስቀል፣ በድንጋይ በመውገርና በጥይት በመደብደብ ሕይወታቸው እንዲያልፍ አደረገ፡፡ እጅግ በርካቶች ደግሞ ለከፍተኛ የአካልና ለሥነልቦና ጉዳት ተዳረጉ፡፡ ኦርቶዶክሳውያኑ በኢኮኖሚ እንዲዳከሙና ተስፋ ቆርጠው ሀገር ጥለው እንደሄዱ ደግሞ  አሉ የተባሉ የኦርቶዶክሳውያንን ዓለም አቀፍ ሆቴሎች፣ የምግብና የመጠጥ ቤቶች፣ ማከፋፈያዎች፣ ማሽኖች፣ በርካታ ተሽከርካሪዎች እንዲሁም ክርስቲያናዊ ሐውልቶች በሙሉ ተመልሰው በማይተኩበት በሆነ ሁኔታ አወደሙ፡፡ 

አክራሪው የሽብር ቡድን ኦርቶዶክሳውያንን ለማጥቃት ብሔር አይመርጥም፡፡ ከየትኛው ብሔር ይምጣ ብቻ ኦርቶዶክስ ከሆነ ይገደላል፤ ይዘርፋል እንዲሁም ይፈናቀላል፡፡ በዚህ ሁኔታም  ኦርቶዶክሳዊነት ኃጢአት ይመስል በርካታ የሸዋ ኦሮሞዎች ከሌሎች የሃይማኖት እህት ወንድሞቻቸው ጋር አበረው ተሠውተዋል፡፡ ከሞት ለመዳን ለአክራሪው ቡድን ኦሮሞ መሆናቸውን በተደጋጋሚ ቢገልጡም ‹‹አንገቱ ላይ ማዕተብ ያሰረ ኦሮሞ አናውቅም›› በማለት ገደለዋቸዋል፤ ቤት ለቤት እየዞሩም የአንገታቸውን ማዕተብ አውልቀዋል፡፡ እያስገደዱም አስልመዋል፡፡ ለዚህ የወንጀል ድርጊት ማሳያዋ ደግሞ የሀረሯ ሚኤሶ ከተማ ነች፡፡ ኦርቶዶክሳዊነት ወንጀል የሆነባቸው ይመስላል በከተማዋ ውስጥ የሚኖሩ የጋሞ፣ የየም፣ የጉራጌ፣ የወላይታ፣ የትግሬ እንዲሁም የአማራ  ኦርቶዶክሳውያን የሽብር ጥቃቱ ሰለባ ሆነዋል፡፡ ተገደው ሰልመዋል፤ ሞተዋል፤ ተደብድበዋል እንዲሁም ቤታቸውን ጨምሮ የንግድ ተቋሞቻቸው በግፍ ወድመዋል፡፡ 

ይቆየን

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

Read 638 times