Thursday, 08 April 2021 00:00

ፍትሕን የተጠሙ ነፍሳት…

Written by  ካሳሁን ለምለሙ
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና በምእመናን ላይ ከሌላው ጊዜ በተለየ መልኩ መጠነ ሰፊ የሆነ የአካል፣የንብረት፣የሥነ ልቡናና የኢኮኖሚ ጥቃት እየተፈጸመባቸው ይገኛል። ጥቃቱን በአብዛኛው የሚፈጽሙት በሃይማኖት ስም የተደራጁ አክራሪ ቡድኖች ናቸው። በተለይም በአንዳንድ የኦሮምያ ክልል ከተሞች በተደራጀና በተቀናጀ መልኩ የማያቋርጥ ውድመትና ጭፍጨፋ ሲያደርሱ ቆይተዋል፤ አሁንም እያደረሱ ይገኛሉ። መረጃዎች እንደሚያመለክቱት እነዚህ ጽንፈኛ አክራሪ ኃይሎች ከሀገር ውስጥና ከውጭ ሀገራት ጭምር ሳይቀር የስንቅና ትጥቅ ድጋፍ ይደረግላቸዋል።  ለአክራሪ ጽንፈኛ ኃይሎች የስንቅና ትጥቅ የሚያቀርቡትም ሆነ የአክራሪዎቹ ዋና ዓላማ ቤተ ክርስቲያንን ማዳክም ሕዝበ ክርስቲያኑን ደግሞ ቢችሉ እነርሱ ወደሚፈልጉት እምነት መውሰድ ካልሆነ ደግሞ መግደል፣መዝረፍ ማፈናቀል እንዲሁም ሕይወታቸውን በስጋትና በሰቀቀን እንዲገፉ ማድረግ ነው። የመጨረሻ ሕልማቸውም ወድቃ የማትወድቀውን ቤተ ክርስቲያንን ገፍተው መጣል ነው። ይህንን ተግባር ላለፉት አርባና ኀምሳ ዓመታት ይፈጽሙት እንደነበረ ቢታወቅም በተለይ ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ መልኩንና ዓይነቱን እየለዋወጡ በቤተ ክርስቲያንና በምእመና ላይ ዘመን የማይሽረው ትውልድ የማይረሳው በደል ሲያደርሱ ቆይተዋል፤ አሁንም እያደረሱ ይገኛሉ።  

 

በኦሮምያ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች በቤተ ክርስቲያንና በምእመናን ላይ እየተፈጸመ ከላው መጠነ ሰፊ ጥቃት ባልተናነሰ መልኩ በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎችም ኦርቶዶክሳውያንን ዒላማ ያደረገ ጥቃት ተፈጽሟል። በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የብዙኃንን ትኩረት እየሳበ የመጣው በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት በተደጋገሚ በኦርቶዶክሳውያንና በቤተ ክርስቲያን ላይ እየተፈጸመ ያለው ግድያና ዘረፋ ነው። በዚህ ሀገረ ስብከት ለበርካታ ዓመታት ኦርቶዶክስ ተኮር ጥቃት ሲሰነዘር ቢቆይም ባለፉት ሦስት ዓመታት አክራሪዎች በተከታታይ የፈጸሙት ጥቃት ግን የተለየ ነው። የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የሰላም ሕዝብ ደኅንነት ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ሲሳይ ዳምጤ በሰሜን ሸዋና በኦሮሞ ብሔረሰብ ዞኖች  መጋቢት ፲ ቀን ፳፻፲3 ዓ/ም በተነሣ የፀጥታ ችግር በሰው ሕይወትና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን መጋቢት ፲፪ ቀን ፳፻፲፫ ዓ/ም ለአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት ተናግረዋል።

ስለሆነም በጥቃቱ ሳቢያ በኦርቶዶክስ  ክርስቲያኖችና በቤተ ክርስቲያን ላይ  የደረሰውን ጥፋት፣ ዓይነትና የጉዳት መጠን ለማጠራት የሀገረ ስብከቱን ሥራ አስኪያጅና የዞኑን አስተዳደሪ መረጃ ጠይቀን የሚከተለውን ጽሑፍ አጠናቅረናል።    

የሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ መጋቤ ሐዲስ ነቅዐ ጥበብ አባቡ ከዝግጅት ክፍላችን ጋር በስልክ በነበራቸው ቆይታ እንዳስታወቁት ከመጋቢት ፲ ቀን ፳፻፲3 ዓ/ም ጀምሮ በሀገረ ስብከታቸው ሥር በሚገኙት ማጀቴ፣ አጣዬ፣ ካራቆሬ፣ ጀውሃና ሸዋ ሮቢት አካባቢዎች ቤተ ክርስቲያንንና ኦርቶዶክሳውያንን ዒላማ ያደረገ ጥቃት በአክራሪ ሃይማኖተኞች መፈጸሙን ተናግረዋል። በጥቃቱም አብያተ ክርስቲያናት ጉዳት ደርሶባቸዋል፤ በርካታ ምእመናንም ተገድለዋል ብለዋል። 

ምእመናን በተፈጸመባቸው ጥቃት ምክንያት ሀብት ንብረታቸው እንደወደመና ከመኖሪያ አካባቢያቸው ተፈናቅለው በጊዜያዊ መጠለያ ውስጥ እንደሚገኙ የተናገሩት ሥራ አስኪያጁ ችግሩ አሁን ብቻ የተከሠተ ሳይሆን ከዚህ በፊት መጋቢት ፳፰ ቀን ፳፻፲፩ ዓ/ም ጀምሮ  ብዙ ምእመናን፣ ካህናት እንዲሁም አንድ ቤተ መቅደስ የዚህ ችግር ሰለባዎች እንደነበሩ አስታውቀዋል። በዚያ ወቅት በተከሠተው ችግር ከኀዘን ሳንወጣ በዚህ ወቅት በተመሣሣይ ሁኔታ መጋቢት ወር ፳፻፲3 ዓ.ም በወርሐ ዐቢይ ጾም አክራሪ ሃይማኖተኞች ከፍተኛ  ጥቃትና ወረራ ፈጽመውብናል ሲሉም አክለው ተናግረዋል። 

በአሁኑ ሰዓትም በሀገረ ስብከታቸው በሚገኙ አንዳንድ አካባቢዎች የተፈጸመውን ጥቃት ለመቀልበስ ከመንግሥት አካላት ጋር ተቀራርበው በመሥራታቸው በአካባቢው  አንፃራዊ ሰላም መኖሩን ያስረዱት ሥራ አስኪያጁ የተፈናቀሉ ምእመናንን ወደ ቀድሞ አካባቢያቸው እንዲመለሱ የማድረግ፣የማጽናናት፣የማረጋጋት፣የማስተማር እንዲሁም አስፈጊውን ዕለታዊ ድጋፍ የማድረግ ሥራ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል። 

በሸዋ ሮቢት ከተማ ብቻ ከጥቃት የተረፉ ከሁለት ሺህ አንድ መቶ በላይ ተፈናቃዮች ይገኛሉ ያሉት ሥራ አስኪያጁ የአካባቢው አጥቢያዎችም ለእነዚህ ተፈናቃዮች ተመድበው  ድጋፍ እያደረጉላቸው መሆኑን ገልጠዋል። ቤተ ክርስቲያን ያለ ምንም የእምነት ልዩነት ለተፈናቃዮች ድጋፍ እያደረገች እንደምትገኝና ድጋፉም ለስድስት ተከታታይ ቀናት የዘለቀ መሆኑን ያስገነዘቡት ሥራ አስኪያጁ  በሞትና በመፈናቀል ከፍተኛውን ቁጥር የያዙት ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲኖች ቢሆኑም የእስልምናና የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮች ጭምር  በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተጠልለው እንደሚገኙ አስረድተዋል። በሀገረ ስብከት ደረጃ ለአጣዬና ለሸዋ ሮቢት ተፈናቃዮች መጠነኛ ድጋፍ መደረጉንም ሥራ አስኪያጁ አክለው ተናግረዋል።  

እስካሁን ድረስ ከአብያተ ክርስቲያናት የካራ ቆሬ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበት ሲሆን የኩሪ ግሪ ቅዱስ ሚካኤል ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን  ደግሞ መጠነኛ ጉዳት እንደደረሰበት ሥራ አስኪያጁ አስረድተው በሌሎች አካባቢዎች ባሉ አብያተ ክርስቲያናት ግን ከሙከራ የዘለለ ጉዳት እንዳልደረሰባቸው አክለዋል። እስካሁን ድረስ ምን ያህል ምእመናን በአክራሪዎች እንደተገደሉ የተጣራ መረጃ እንደሌለና ጥቃቱን ለመመርመር ሦስት አጣሪ ቡድን ተመድቦ በአጣዬ፣ በማጀቴና በሸዋ ሮቢት የማጣራት ሥራ እየሠሩ መሆኑን ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል። 

አያይዘውም “በሀገረ ስብከታችን የፀጥታ ችግር በነበረበት ወቅት  አክራሪ ሃይማኖተኞች ዒላማ ያደረጉት ቤተ ክርስቲያንና ምእመናንን ከአካባቢው ለማጥፋት ነበር፤ ነገር ግን ምእመኖቻችን ራሳቸውን መሥዋዕት አድረገው ብዙ አብያተ ክርስቲያናትን ከጥፋት ታድገዋል፤ የደረሱ ጥፋቶችን በአኀዝ በተደገፈ መረጃ ለመናገር ጥናት የሚያስፈልግ ቢሆንም በጥቃቱ ከፍተኛ የሆነ ጉዳት የደረሰው ግን አጣዬ ላይ ነው። በአጣዬ ከተማና አካባቢው የከፋ ውድመት ደርሷል። በማጀቴም እንደዚሁ መለስተኛ ጉዳት ቢደርስም የከፋ ጉዳት እንዳይደርስ ሕዝቡ ተደራጅቶ የመጣውን አክራሪ ኃይል መመከት ችሏል” በማለትም አስረድተዋል። ሥራ አስኪያጁ አክለውም “ከዚህ ቀደም የችግሩን ስፋትና ጥልቀት የሚያስረዳ ደብዳቤ ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽፈናል። በቀጣይም በጥናት ላይ የተመሠተ የተጣራ መረጃ ለመንግሥት እናቀርባለን” ካሉ በኋላ ለወደፊትም ቢሆን አክራሪዎች በአካባቢው ተመሳሳይ ችግሮችን ሊፈጠሩ እንደሚችሉ በመቆም “ቤተ ክርስቲያንም ሆነች መንግሥት የየድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል” ብለዋል። 

ቤተ ክርስቲያን አንድነቷን ጠብቃ የመጣባትን ወራሪ ጠላት መመከት ያስፈልጋታል ያሉት ሥራ አስኪያጁ “ባልሆነ ነገር ጊዜያችን በከንቱ የምናሳልፍበት ወቅት ላይ አይደለም፤ በሀገራችን በአራቱም አቅጣጫ ቤተ ክርስቲያንና ምእመናንን ማዕከል ያደረገ  አደጋ ከፊታችን መቷል፤ ስለዚህ ከአባቶቻችን ጀምሮ ሁላችንም በመደራጀትና በመናበብ የመጣብንን አደጋ መቀልበስ ያስፈልጋል” ብለዋል። መረጃ ከመለዋወጥና ከማደራጀት አንስቶ ቤተ ክርስቲያን የተለየ ሥራ መሥራት እንዳለባት ሥራ አስኪያጁ ጠቁመው በሰሞኑ ጥቃት ምክንያት የተፈናቀሉ ምእመናንን መደገፍ፣ ማፅናናትና ማስተማር እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል። 

የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታደሰ ገ/ጻድቅ በበኩላቸው “በዞኑ በተለይ በአጣዬ፣ በማጀቴና በሸዋ ሮቢት አካባቢ ከፍተኛ  የፀጥታ ችግር በመከሠቱ ምክንያት በርካታ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተገድለዋል፤ ቤታቸው ተቃጥሏል፤ ሀብት ንብረታቸው ተዘርፏል፤ እንዲሁም አብያተ ክርስቲያናትም ተቃጥለዋል፤” በማለት ተናግረዋል። ጥቃት ያደረሰው ይሄው የተደራጀ አክራሪ ቡድን ጥቃቱን የብሔርና የሃይማኖት  ለማድረግ እንቅስቄሴ ማድረጉንም  አክለው አስረድተዋል። 

አክራሪዎች በተለያየ ቦታ በፈጸሙት ጥቃት ሦስት ያህል አብያተ ክርስቲያናት መቃጠላቸውን ያስታወቁት አስተዳደሪው “በአብያተ ክርስቲያናቱ ላይ የተፈጸመው ጥቃት ሆን ተብሎ ሃይማኖትን ከሃይማኖት ጋር ለማጋጨት የተደረገ ሴራ ነው። በተፈጸመው ጥቃትም የእስልምና እምነት ተከታይ ወገኖች የተገደሉ ቢሆንም ጥቃቱ ይበልጥ የክርስትና እምነት ተከታዮችን ዒላማ ያደረገ መሆኑን የሚያመላክቱ ታላላቅ የኦርቶዶክስ አባቶች በጥይት ተደብድበው መገደላቸው ነው” ሲሉ ተናግረዋል። 

ዋና አስተዳዳሪው አያይዘውም “አካባቢው ሁልጊዜም የሥጋት ቀጠና መሆኑ ቢታወቅም ሕዝቡን አደራጅተን ራሱን እንዲከላከል ባለማድረጋችን ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ይህ የታጠቀና የተደራጀ አክራሪ ኃይል ሕዝባችን በመደበኛ እንቅስቃሴ ላይ እያለ ከፍተኛ ጥቃት ፈጽሞበታል” ካሉ በኋላ “የአካባቢው ማኅበረሰብ ሰላምና ደኅንነቱ እንዲጠበቅ ባለፉት ጊዜያት በርካታ ሥራዎችን የሠራን ቢሆንም በአካባቢው የሚንቀሳቀሰው “የኦነግ ሸኔ” ኃይል ባልታሰበ ጊዜ ጥቃት መፈጸሙን አስገንዝበዋል። 

ሰላምን አማራጭ አድርጎ በተቀመጠና ምንም ዓይነት ቅድመ ዝግጅት ባላደረገ ማኅበረሰብ ላይ የተፈጸመውን ጥቃት በቀላሉ ለመቀልበስ አስቸጋሪ እንደሆነ አስተዳደሪው ገልጠው “ማኅበረሰቡን በስንቅና ትጥቅ ማደራጀት ብንችል ደግሞ  የአካባቢውን ሰላም ከመጠበቅ አልፎ የአጎራባች አካባቢዎችንም ሰላም መጠበቅ የሚችል አቅም አለው” ብለዋል። በአካባቢው ሕዝቦች መካከል  ቁርሾና መጠራጠር እንዳይፈጠርም በጥንቃቄ ሲሠሩ እንደነበር አስተዳደሪው አክለው አስረድተዋል።

ለኦሮሞ ብሔረሰብ ዞንና ለሰሜን ሸዋ ዞን ሲያገለግል የነበረውን የፀጥታ ኃይል ለተልእኮ ወደ ሌላ አካባቢ መዛወሩን እንዳጋጣሚ ተጠቅመው አክራሪ ኃሎች ጥቃቱን እንደፈጸሙ የገለጡት አስተዳደሪው ከዚህ ቀደም በአካባቢው የተፈጸሙ ጥቃቶችን ከግምት ውስጥ ያስገባ ዘላቂ መፍትሔ ለማበጀት ተደጋጋሚ ጥፋቶችንም ለማስቀረት የተቀናጀ ወጥ ሥራ መሥራት እንደሚያስፈልግ በማመን ሥራዎችን እየሠራን ነው ያሉት አስተዳደሪው “በተፈጸመባቸው ጥቃት የተፈናቀሉትና ሀብት ንብረታቸው የወደመባቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች በሥነ ልኑና የማረጋጋትና የመደገፍ ሥራዎችንም በተጓዳኝ እየሠራን እንገኛለን” ብለዋል። 

አስተዳዳሪው ከዚሁ ጋር በማያያዝም የዞን አመራሮች በየአካባቢው ተሠማርተው እና መድረኮችን ፈጥረው ከማወያየት ጀምሮ በአካባቢው ተጨባጭ ለውጥ የሚያመጡ ሥራዎች እየተሠሩ እንደሆነ፤ የዓይነትና የጥሬ ገንዘብ ድጋፍ ለማሰባሰብ ኮሚቴ ተቋቁሞ እንቅስቃሴ መጀመሩንም አስታውሰው አስተዳደሪው በአካባቢው የዞን፣ የክልልና የፌዴራል የምርመራ ቡድን ገብቶ ምርመራ መጀመሩንና ከምርመራው በኋላም የችግሩ ምንጪ ምን እንደሆነ በመለየት የተጣራ መርጃ ለሕዝብ ይፋ እንደሚሆን እንዲሁም ለችግሩ የሚመጥን መፍትሔ እንደሚቀመጥለት ተናግረዋል። 

ለአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት በስልክ አስተያየታቸውን የሰጡ አንድ የአጣዬ ከተማ ኗሪ እንደገለጡት በአካባቢያቸው እጅግ የሠለጠነና ዘመናዊ ትጥቅ ያለው ኃይል ጦርነት ከፍቶ ብዙ ንጹሓንን እንደገደለና ሀብት ንብረት እንዳወደመ ተናግረዋል።

Read 455 times