Friday, 06 August 2021 00:00

የአክራሪ እስላም እኩይ ድርጊትና የክርስቲያኖች የሕልውና ፈተና ክፍል ሁለት

Written by  ካሳሁን ለምለሙ

Overview

የተወደደዳችሁ አንባብያ የዚህን ጽሑፍ የመጀመሪያ ክፍል ከዚህ በፊት በነበረው እትም ላይ ማቅረባችን ይታወሳል፡፡ ቀጣዩንና ሁለተኛውን ክፍል ደግሞ እነሆ፦ የእንግሊዝ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ባስቀመጠው ትርጒም መሠረት አክራሪ እስላም የሚለው ሐረግ ከሁለት ቃላቶች የተገኙ ሲሆን ትርጒሙም “የኃይል ርምጃንና ጥቃትን እንደ ስልት በመጠቀም የራሱን ሃይማኖትና ፍልስፍና ሌሎች እንዲቀበሉ የሚያስገድድ ኃይል ነው” ይላል።የአክራሪ እስልምና እንቅስቃሴ በዓለም ላይ መቼ እንደተጀመረ በውል የሚታወቅ ባይሆንም ዘመናትን ያስቆጠረ መሆኑን ግን መገመት አያስቸግርም።የአክራሪ እስልምና እኩይ እንቅስቃሴ መላውን ዓለም ያዳረሰ ቢሆንም የመካከለኛው ምሥራቅ ሀገራትን ያህል ግን እንቅስቃሴው የተስፋፋበት የዓለማችን አካባቢ የለም።አንዳንድ የመካከለኛው ምሥራቅ ሀገራት በተለይ ሶርያ፣ ኢራቅ፣ የመን፣ ሳውዲ ዓረቢያ፣ ኢራንና ሌሎች ሀገራት የአክራሪ እስልምና እኩይ ተግባር መዳረሻ ከሆኑ ቆይተዋል። በተለይ በሶሪያና ኢራቅ የሚንቀሳቀሰው ራሱን “አይ ኤስ” ብሎ የሚጠራው እስላማዊ የሽብር ቡድን በአካባቢው በርካታ ውድመት አድርሷል። በነዚህ ሀገራት የሚኖሩ ክርስቲያኖች ለሞት፣ለስደትና ለከፋ እንግልት መዳረጋቸውን የሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን መግለጧን ኦርቶዶክስ ኮግኔት ፔጅ ዘግቧል። እንደ ዘገባው ከሆነም የሽብር ቡድኑ በክርስቲያኖች ላይ በሰነዘረው ተደጋጋሚ ጥቃት በርካታ አብያተ ክርስቲያናት ወድመዋል፣ሀብት ንብረቶቻቸው እንዳልነበረ ሆነዋል፤ ይህ በመሆኑም ሕዝበ ክርስቲያኑ ለከፋ የሥነ ልቡና ጫና ተዳርጓል።በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ክርስቲያኖች ሲገድሉ፤ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩት ደግሞ አካባቢያቸውን ለቀው ተሰደዋል። በአሁኑ ወቅት በአካባቢው አንፃራዊ ሰላም ያለና የሽብር ቡድኑ እንቅስቃሴ የተዳከመ ቢሆንም ከአካባቢያቸው የተፈናቀሉ ክርስቲያኖች ግን ከተሰደዱበት ሀገር ወደ አካባቢያቸው አልተመለሱም፤ የወደመባቸው ሀብትና ንብረትም አልተተካላቸውም።

 

የመካከለኛው ምሥራቅንና አንዳንድ የዓለም ሀገራትን ያካለለው እስላማዊ የሽብር ቡድን እንቅስቃሴ በምዕራብ፣ በመካከለኛውና በምሥራቅ አፍሪካም መከሠቱን ከጣለ ቀላል የማይባል ጊዜያትን አስቆጥሯል። በምዕራብ አፍሪካ የሚንቀሳቀሰው እስላማዊ የሽብር ቡድን ቦኮሐራም ሲባል በምሥራቅ አፍሪካ የሚንቀሳቀሰው ደግሞ አልሸባብ ይበላል። ቦኮሐራም ናይጀሪያን መነሻው አድርጎ የምዕራብ አፍሪካ ሀገራትን የሚያጠቃ ሲሆን አልሸባብ ደግም ሶማልያን መሠረቱ አድርጎ አንዳንድ የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራትን ያሸብራል።

በሕንድ ማላንካራ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የሚመራውና ክርስቲያናዊ ክሥተቶችን በመዘገብ የሚታወቀው ኦርቶዶክስ ኮግኔት ፔጅ እስላማዊ የሽብር ቡድን በአፍሪካ አህጉር የተለያዩ ሀገራት እየፈጸመ ያለውን የሽብር ተግባር በቅርቡ ዘገባው በትንታኔ አስፍሮታል።በአፍሪካ አህጉር በተለያዩ ሀገራት እስላማዊ የሽብር ቡድን በክርስቲያኖች ላይ ተደጋጋሚ ጥቃት እንደሚፈጸም በመግለጽ ዘገባው ይጀምራል። በመቀጠልም “በመካከለኛው ምሥራቅ የሚንቀሳቀሰው እጅግ አውዳሚና አደገኛው “አይ ኤስ” የተባለው እስላማዊ የሽብር ቡድን ህልውናው ሊያበቃለት ተቃርቧል” ሲል ዘገባው ያክላል።በመካከለኛው ምሥራቅ ያጣውን ተቀባይነትና ማሳካት የተሳነውን የሽብር ተግባር ለማካካስ በአፍሪካ በተለያዩ ሀገራት ከፍተኛ እንቅስቃሴ ማድረግ መጀመሩን ዘገባው አስረድቷል። በምዕራብ አፍሪካና በሌሎች ሀገራት በተለይም በናይጄሪያ፣ በቡርኪናፋሶ፣ በሞዛምቢክ፣ በኡጋንዳ፣ በኮንጎና በሶማልያ ዘላቂ የሆነ መሠረቱን እየጣለ መሆኑን ዘገባው አስገንዝቦ በተለይ በናይጄሪያ ባለፉት ሦስት ተከታታይ ዓመታት ቦኮሐራም የተባለው እስላማዊ የሽብር ቡድን ለቁጥር የሚያታክቱ ክርስቲያኖችን መግደሉንና በርካታ አብያተ ክርስቲያናትን ማውደሙ ተገልጿል።

በፈረንጆች ዘመን አቆጣጠር ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ በናይጄሪያ ብቻ ከዐሥራ አምስት ሺህ በላይ ክርስቲያኖች በዚሁ እስላማዊ የሽብር ቡድን እኩይ ሥራ ሲገደሉ ከሁለት ሺህ በላይ አብያተ ክርስትያናትና ሌሎች የማምለኪያ ማእከላት መውደማቸውን ዘገባው አመልክቶ የሞቱ ክርስቲያኖችና የወደሙ የማምለኪያ ማእከላት ቁጥር ከተጠቀሰው ቁጥር በላይ ሊሆን እንደሚችል ታሳቢ ተደርጎ የወጣ መረጃ እንደሆነ ዘገባው አስገንዝቧል።ከዚህ በተጨማሪም እስላማዊ የሽብር ቡድኖችና ተከታዮቻቸው በበርካታ የአፍሪካ ሀገራት ራሳቸውን እያደራጁ መሆናቸው ከስድስት መቶ ሰማንያ አምስት ሚሊዮን በላይ የአፍሪካ ክርስቲያኖች ከፍተኛ የደኅንነት ሥጋት ላይ መውደቃቸው ተነግሯል።ዘገባው የWST ጥናትን ዋቢ አድርጎ እንዳስረዳው አይ ኤስ የተባለው እስላማዊ የሽብር ቡድንና የማእከላዊ አፍሪካ ተባባሪዎቹ ከዚህ ቀደም በአንጎላና በሞዛምቢክ ከፍተኛ ጥቃት መፈጸማቸውን አስረድቷል። በቡርኪናፋሶም ከሚሊዮን በላይ ክርስቲያኖች ከአካባቢያቸው እንደተፈናቀሉ አስገንዝቦ ሌሎች ደግሞ ለአካል ጉዳትና ለህልፈተ ሕይወት እንደተዳረጉ በዘገባው ተመላክቷል። 

እስላማዊ የሽብር ቡድኑ አይ ኤስ በአሁኑ ወቅት ክርስቲያን በሚበዛባቸው የአፍሪካ ሀገራት ላይ በርካታ አባላትን በመልመል ላይ እንደሆነም ዘገባው አስረድቷል። የተመለመሉ ወጣቶችም የሽብርና የአጥፍቶ ጠፊ ሥልጠናዎች እየተሰጣቸው መሆኑ ታውቋል። አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎችን ጠቅሶ ዘገባው እንዳስረዳው “አይ ኤስ” የተባለው እስላማዊ የሽብር ቡድን በአፍሪካ እስላማዊ መንግሥት የመመሥረት ዓላማ ይዞ እንደሚንቀሳቀስ ለማወቅ ተችሏል። ከአክራሪ የሱኒ ሙስሊሞች በተጨማሪ በርካታ የሽዓ አክራሪ ሙስሊሞች ጭምር በኢራን እገዛ የአፍሪካ የሽብር ቡድኑን ተፋለሚዎች እየመለመሉ ነው ተብሏል። ታዋቂ የዓረቡ ዓለም የእስልምና እምነት መምህራን  በአፍሪካ ምድር በአብዛኛው መታየታቸው ደግሞ የሽብር ሥራቸውን ያሳያል ብሏል ዘገባው። የእነዚህ መምህራን ዓላማ በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ለእስላማዊ የሽብር ቡድን አይ ኤስ ይፋለማሉ ተብሎ ለተመለመሉ ወጣቶች መመሪያ መስጠት ሲሆን እስላማዊ የሽብር ቡድኑም ለማንም የማይራራና ጨካኝም እንደሆነ ዘገባው አስታውሷል።

ዘገባው “እገታ፣ አስገድዶ መድፈርና ማሠቃየት የሽብር ቡድኑ መገለጫዎቹ ናቸው። እነዚህ የተጠቀሱት የሽብር ቡድን ተግባራት ሌላው ዓለም ካለው ልምድ አንጻር ምንም ላይሆን ይችላል “ካለ በኋላ  “ለአፍሪካውያን ግን ተግባሩ አዲስና ፈታኝ የሕይወት ልምድ ነው” ሲል ይገልጸዋል።እስላማዊ የሽብር ቡድን የአፍሪካ ክርስቲያኖችን ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት ያቀደው በአፍሪካ ምድር እስላማዊ መንግሥት ለመመሥረት ‹‹እንቅፋት ይሆኑኛል›› ብሎ በማመኑ እንደሆነና በዚህም ምክንያት በአሁኑ ወቅት የአፍሪካ ክርስቲያኖች ደኅንነት የተጠበቀ እንዳልሆነ ዘገባው አስረድቷል። ክርስቲያኖችን በዘላቂነት ከሥጋት፣ ከመፈናቀልና ከጥቃት ለመታደግ የሚመለከታቸው የየሀገራቱ የመንግሥት ባለሥልጣናት በቂ ሥራ እየሠሩ አይደለም። የሽብር ጥቃት የተፈጸመባቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች የተሻለ ደኅንነት እየተሰማቸው እንዳልሆነም ከዘገባው መረዳት ይቻላል። በእስላማዊ የሽብር ቡድን የሚደርሰው ጥቃት የሚቀጥል ከሆነ ክርስቲያኖች ያለማቋረጥ እንደሚሰደዱ፣ የአካልና የመንፈስ ጉዳት እንደሚደርስባቸው፣ ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር እንደሚበራከት ዘገባው ሊኖር የሚችለውን ስጋት ጭምር አብራርቷል።

ይህ ዘገባ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ቀንድ ወሳኝ ሀገር መሆኗን ይጠቅስና እንደሌሎች የአፍሪካ ሀገራት የአክራሪ እስላም ጥቃት ሰለባ እንደሆነች ያስረዳል። እስላማዊ አክራሪነት በተለይ በኦሮምያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ጎልቶ እንደሚታይም ይተነትናል።

በኦሮምያ ክልል ባለፉት ሦስት ዓመታት ሲካሄድ የቆየው የብሔር ግጭት ለአክራሪ እስላሞች እኩይ የሽብር ተግባር ጥሩ ዕድል እንደፈጠረላቸው ዘገባው ካስረዳ በኋላ ባለፉት ሦስት ዓመታት ብቻ በኢትዮጵያ ከ30 በላይ አብያተ ክርስቲያናትና ሌሎች ተቋማት መውደማቸውን ያነሣል። እንደ ኦርቶዶክስ ኮግኔት ፔጅ ዘገባ በእስላማዊ የሽብር ጥቃት የተነሣ በርካታ ክርስቲያኖች ለአካል ጉዳትና ለኅልፈተ ሕይወት ተዳርገዋል። በሚሊዮኖች የሚቆጠሩት ደግሞ ከአካባቢያቸው ተሰደዋል ይላል። በኢትዮጵያ ለበርካታ ዘመናት የአፅራረ ቤተ ክርስቲያን እንቅስቃሴ የታየ ቢሆንም በተለይ ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ ግን የተለየ መሆኑን መርዳት እንችላለን። አፅራረ ቤተ ክርስቲያን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሚያደርሱት መከራ ከኢትዮጵያውያን አልፎ ጉዳዩ ለሌላው ዓለም እጅግ አስደንጋጭ ሆኗል።እኛ ኢትዮጵውያንን ሌላው ዓለም የሚያውቀን  የሃይማኖት ልዩነት ቢኖረንም ተቻችለንና ተፋቅረን እንደምንኖር ነው። ነገር ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሃይማኖታዊ አክራሪዎች በሚፈጽሙት ኢሰብአዊ ተግባር የሀገራችን መልካም ዝናና ገጽታ በሌላው ዓለም ዘንድ እየተበላሸ መጥቷል። በተለይ እስላማዊ አክራሪ ቡድን በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች በቤተ ክርስቲያንና በምእመናን ላይ በተደጋጋሚ የሚፈጽመው የሽብር ጥቃት የሀገርን አንድነት የሚንድና ለባሰ ትርምስና ሁከት የሚዳርግ ተግባር መሆኑን መርዳት እንችላለን።እስላማዊ የሽብር ቡድን ኦርቶዶክሳውያን በሰቀቀን ኑሯቸውን እንዲገፉ ከሚደረጉባቸው የሀገራችን አካባቢዎች መካከል ምዕራብና ምሥራቅ ሐረርጌ፣ ባሌ፣አርሲ፣ጅማ ዙሪያ፣ ደቡብ ወሎ፣ስልጤ እና የመሳሰሉት አካባቢዎች ይጠቀሳሉ። ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች በእነዚህ አካባቢዎች በሚደርስባቸው ጫና የተነሣ ተወልደው ያደጉበትን አካባቢ ለቀው የተሻለ ሰላም ወደሚያገኙበት አካባቢ ተሰደዋል።ሀብት ንብረቶቻቸው ተዘርፈዋል፤ተቃጥለዋል፤ እንዲሁም ያለምንም ወንጀላቸው ለኅልፈትና ለአካል ጉዳት ተዳርገዋል። በተጠቀሱት አካባቢዎች ያሉ የመንግሥት ባለሥልጣናትም የዜጎችን ሰብአዊ መብት ከማስጠበቅ ይልቅ ለግፈኞች ተባባሪ ሲሆኑ ተስተውለዋል። ለሽብር ጥቃት ተጋላጭ የሆኑ የአፍሪካ ክርስቲያኖችን ጉዳይ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በጥንቃቄ በመመልከት የክርስቲያኖችን ፍላጎትና ደኅንነት ሊያስጠብቅ ይችላል ያለውን ተግባር ሁሉ ሊያከናውን ይገባል ሲል ዘገባውም አጠቃሏል። 

 

Read 467 times