በተጨማሪም “ወናሁ ተሠርዐ በተፍጻሜተ ዝንቱ መጽሐፍ ዘይደሉ ለሊቃውንት ከመ ይወስኩ ዲቤሁ ወያንትጉ እምኔሁ፤ ወአልቦ ዘኢኮነ ሎሙ ብውሐ ውስተ ዝንቱ፡- እነሆ በዚህ መጽሐፍ መጨረሻ ላይ ለሊቃውንት የሚገባው ነገር ተጽፏል። በእርሱ ላይ እንዲጨምሩ፣ ከእርሱም እንዲቀንሱ በዚህ ውስጥ ያልተፈቀደላቸው ነገር የለም” (መቅድመ ጉባኤ ዘፍትሐ ነገሥት) ተብሎ እንደተጻፈው ቤተ ክርስቲያኒቱን አኹን ካለችበት ከፍተኛ የሕግና ሥርዓት አለመከበር፣ እንዲሁም ከገባችበት የአስተዳደር ውጥንቅጥ ለማውጣትና አሠራሯን አዘምኖ ሐዋርያዊ ጉዞዋን ማፋጠን ይቻል ዘንድ በሥራ ላይ የሚገኙ ሕግጋት፣ ደንቦችና መመሪያዎች ሐዋርያዊ መሠረታቸውን በጠበቀ ኹኔታና የዘመኑን ተግዳሮት ሊመክቱ በሚችሉበት መልኩ ሊሻሻሉ ይገባል።
በእርግጥ ቤተ ክርስቲያናችን በራሷ ቅዱስ ሲኖዶስ የመንበረ ፓትርያርክ አስተዳደራዊ መዋቅር ዘርግታ የሠራችበት ዘመናዊ ልምድ ከአኃት አብያተ ክርስቲያናት ጋር ሲነጻጸር ገና ከግማሽ ክፍለ ዘመን ብዙ ያላለፈ ነው። አሁን በሥራ ላይ ያሉ ሕግጋትን ውስጣዊ ይዘትና ዘመናዊ አፈጻጸም በጥናት በምርምር ለማሻሻል ያደረገችውን ጥረት፣ ቅድመ ዝግጅትና አደረጃጀት ስንመለከትም ከቀደምትነቷና ከታላቅነቷ አኳያ ሲታይ ብዙ ይቀረዋል። በተለይም ሕግጋቱ ዘመኑን ከመዋጀት አንጻር ሲመዘኑ ገና እጅግ ብዙ መሻሻል እንደሚቀራቸውና በውስጣቸውም ከሠፈሩት መካከል በተግባር የማይፈጸሙ አያሌ ድንጋጌዎች በመኖራቸው ችግሩ ልዩ ትኩረት የሚፈልግ በመሆኑ ኹሉም አካል በባለቤትነት ስሜት ከፍተኛ ጥረት ሊያደርግ ይገባል።
ለዚህ ደግሞ አንዱ በማሳያነት ሊወሰድ የሚገባው እስከ አኹን ድረስ ለረጅም ዓመታት የነበረው የሕግ ማውጣትና ማሻሻል ሂደት ይህን ጥንታዊና ዓለም አቀፋዊ አሠራር አለመከተሉና ኹሉንም የቤተ ክርስቲያኒቱን ልጆች አለማሳተፉ፤ በተለይ ደግሞ በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን በጥልቀትና በስፋት ሳይፈተሽ በጉባኤ ሳይመከርበት እንዲዘጋጅ መደረጉ ለታላቋ ቤተ ክርስቲያን የማይመጥንና በአፈጻጸም ረገድም አስቸጋሪ ኾኖ መገኘቱ ነው።
በአኹኑ ጊዜ በሥራ ላይ የሚገኘው ሕገ ቤተ ክርስቲያንም በጥቅምት ፳፻፲፫ ዓ.ም በተካሔደው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ እንዲሻሻል በተወሰነው መሠረት የማሻሻል ሂደቱ በውስን አካላት ዝግጅት እንደ ተጀመረም ተረድተናል። ነገር ግን ከላይ ደጋግመን እንደገለጽነው ሕገ ቤተ ክርስቲያንን የማሻሻል ሂደቱ በተወሰኑ አካላት ብቻ የሚፈጸም ሳይኾን እንደ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን ሐዋርያዊ ሥርዓት በኹሉም አቅጣጫ የሙያ ብቃት፣ የትምህርት ዝግጅትና የአገልግሎት ልምድ ባላቸው የቤተ ክርስቲያኒቱ ሊቃውንትና በዘርፉ ሙያ ያላቸው ኦርቶዶክሳውያን ሙሉ ተሳትፎ ምክርና ሐሳብ ተሰጥቶበት ሊፈጸም ይገባዋል። ማኅበራችን “ፍኖተ ጽድቅ ወሕይወት ጉባኤ ማኅበራ ለቤተ ክርስቲያን ዓለም አቀፍ ኅብረት” ላለፉት ስድስት ወራት የጉዳዩን አሳሳቢነት ተገንዝቦ ሕገ ቤተ ክርስቲያንንና ቃለ ዓዋዲውን በዝርዝር ከማጥናት ጋር በአራቱም መዐዝነ ዓለም የሚገኙ ካህናትንና ምእመናንን ቤተ ክርስቲያናችን አኹን ስላለችበት ኹኔታ ሐሳብና አስተያየት ሲጠይቅና ሲያጠና፣ቤተ ክርስቲያን ከውጭ ከተጋረጠባት ፈተና በላይ በውስጥ ያለው መንፈሳዊና አስተዳደራዊ ድክመት አሳሳቢ መኾኑን ኹሉም የኅብረቱ አባላት በቁጭት የሚገልጹት ኾኖ ቆይቷል። በሥራ ላይ ያለውን ሕገ ቤተ ክርስቲያን የማሻሻል ሂደቱ አኹን በተያዘው መንገድ በጥቂት አካላት ብቻ ሳይኾን ኹሉም የቤተ ክርስቲያናችን ፍሬዎች ማለትም የየጉባኤ ቤቱ ሊቃውንት፣ ዘመናውያን የዘርፉ ምሁራን እንዲሁም በሀገር ቤትም ኾነ በውጭ ሀገር በተለያየ ደረጃ ቤተ ክርስቲያንን የማገልገል ልምድና ዕውቀት ያካበቱ የቤተ ክርስቲያናችን ልጆች በአንድነት ኾነው በሀገር ቤትም ኾነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያጋጠሙ ችግሮችንና እንደ አስፈላጊነቱም የአኃት አብያተ ክርስቲያናትን ልምድ ባካተተ መልኩ በጉዳዩ ላይ በስፋትና በጥልቀት ለመወያየት ኹሉም የሚገኙበት ዐቢይ ጉባዔ ተጠርቶ በጥንቃቄ ሊመከርበት ይገባል።
ዐቢይ ጉባኤውም ጥንታዊና ሐዋርያዊ መሠረት ካላቸው ቀኖናትና ሕግጋት ጋር በማገናዘብ በጥንቃቄ አጥንቶ በሚያሳልፈው ውሳኔና የአሠራር መመሪያ መሠረት አኹን ያለው ሕገ ቤተ ክርስቲያን እንዲሻሻል ማድረጉ አማራጭ የሌለው ብቸኛ መንገድ መኾኑን በአጽንኦት እናሳስባለን። ይኽ ሳይኾን ቀርቶ አሁን በጥቂት አካላት የሚደረገው የማሻሻል ሥራ በተጀመረው መንገድ የሚቀጥል ከኾነ ግን ተቋማዊ ችግሩን ከድጡ ወደ ማጡ የሚወስድና በእናት ቤተ ክርስቲያን ላይ ከፍተኛ አደጋ የሚያስከትል መኾኑን መረዳት ያስፈልጋል። ይኽንንም የምንለው እስካሁን ከደረስንበት ጥናት፣ በመላው ዓለም የሚገኙ ካህናትና ምእመናን በተመሳሳይ ኹኔታ ከሚያንጸባርቁት የቁጭት ሐሳብ በመነሣት ነው።
ስለዚህም ይህ ችግር ልዩ ትኩረትንና አፋጣኝ ምላሽ ሊሰጠው ይገባል። ነገር ግን ይኽ ማሳሰቢያችን እንደ ቀላል ታይቶና ቸል ተብሎ በዚሁ ከቀጠለ የካህናቱና የሕዝበ ክርስቲያኑ ብሶትና ቁጭት ወዳልተፈለገ አቅጣጫ የሚያመራ በመኾኑና ይኽን ታላቅ ችግር በዝምታ ማየት ደግሞ ከህሊና ወቀሳም አልፎ በሃይማኖትና በታሪክ ተወቃሽ የሚያደርግና እንደ ተባባሪም የሚያስቆጥር ስለሚኾን፤ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ከተጨማሪ ውርደትና ውድቀት ለመታደግ ስንል ከእኛ የሚጠበቀውንና ልናደርግ የሚገባንን ኹሉ ለማድረግ የምንገደድ መኾኑን አስቀድመን ልናሳውቅ እንወዳለን።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ውስጣዊ የአሠራር ችግሮችንና ውጫዊ ፈተናዎችን ተረድቶ የመፍትሔው አካል ለመሆን ጉለበትን፣ገንዘብን፣ዕውቀትን እንዲሁም ጊዜን መስጠት ተገቢ ነው። ለዚህ ተግባር ደግሞ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር በይፋ በቤተ ክርስቲያን ስም ከተቋቋሙ ማኅበራት ጀምሮ እስከ ተራ ምእመን ድረስ የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባል። በተለይ በዚህ ዘመን ቤተ ክርስቲያናችን በሁለንተናዊ ፈተናዎች እንደ ቆዳ ተወጥራ የምትገኝበት ወቅት በመሆኑ ሁሉም አካል ተረባርቦ የአባቶቻችንን አደራ በመወጣት ቤተ ክርስቲያንን ለቀጣዩ ትውልድ ማሻገር ካልቻልን የታሪክ ተጠያቂ የምንሆነው በዚህ ዘመን ያለን ትውልዶች ነን።
ይህ የቤተ ክርስቲያናችን ውስጣዊ የአሠራር ግድፈት ቤተ ክርስቲያንን ለማትወጣው ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮች እየዳረጋት መሆኑን መርዳት አስፈላጊ ነው። በተለይ ውስጣዊ ችግሮቻችንን ቶሎ ያለማረማችን ቤተ ክርስቲያንን ሊውጣት ላሰፈሰፈው የውጭ ጠላት ሰርግና ምላሽ ሆኖለታል። ስለሆነም አንድነታችንን አጠናክረን ውስጣዊ ችግሮቻችንም አርመን ውጫዊ ጠላቶቻችንን መመከትና አሳፍሮ መመልስ የሚያስችልና በቀላሉ የማይቀለበስ አቅም መገንባት ያስፈልገናል።