Saturday, 15 May 2021 00:00

‹‹መመሪያውን ተግባራዊ ከማድረግ አንፃር ማኅበሩና መዋቅሩ ትልቁን ድርሻ ይወስዳሉ›› - (አቶ ውብሸት ኦቶሮ የማኅበረ ቅዱሳን ዋና ጸሓፊ) ክፍል ሁለት

Written by  ካሳሁን ለምለሙ
ማንኛውም አባል በመመሪያው ከተከለከለው የአመራርነት መደብ አገልግሎቱን ከጨረሰ በፈለገው የፖለቲካ ድርጅት ውስጥ ገብቶ የማገልገል መብቱ የተጠበቀ ነው። እንዲህ ዓይነቱን አባል ማኅበሩ የሚገድብበት ወይም የሚከለክልበት ምንም ዓይነት ምክንያት የለውም። ብዙዎች ብዥታ የሚፈጥርባቸውና የማይገባቸው ይሄ ነው።አንዴ አመራር ከሆኑ ዕድሜ ልካቸውን አመራር የሆኑ የሚመስላቸው አሉ። ከዚህ በፊት ማብራሪያ መስጠት ያላስፈለገው እነዚህ ሰዎች ያልተከለከሉ አባላት በመሆናቸውም ጭምር ነው።  መመሪያው ስለአሁን ነው እንጂ ስላለፈው ወይም ስለወደፊቱ ስለማያወራ ነው ከዚህ በፊት መግለጫ ወይም ማብራሪያ መስጠት ያላስፈለገው። በሰነዱም ላይ ይኸው ነው በግልጽ የጠቀመጠው። መመሪያው የማኅበረ ቅዱሳን ሥራ አመራር አባላት ይላል እንጂ የማኅበረ ቅዱሳን ሥራ አመራር የነበሩት አይልም። ብዣታው አሁንም ግልጽ ሊሆን ይገባል መመሪያው የሚከለክለው በአገልግሎት ላይ ባሉበት ጊዜ ብቻ ነው። ለአገልግሎት ተመልሰው ሲመጡ በግልጽ አባል አለመሆናቸውን ገልጸው ወደ አገልግሎት ሊገቡ ሲሉ የተቀመጠ ቅደም ተከተል አለ። ከፖለቲካ አባልነት ወጥተው እና ጨርሰው አገልግሎት ላይ እስከተመደቡ ድረስ በአገልግሎት ላይ እስከቆዩ ድረስ ከዚያ አባልነት ውጪ መሆናቸውን ብቻ ነው ማኅበሩ የሚከታተለው።  ከዚያ በኋላ ያለው የራሳቸው ግለሰባዊ መብታቸው ነው። ይህንንም መመሪያው  መከልከል አይችልም። አባላት ወደ ፖለቲካው ዓለም ሲገቡም ሆነ የመንግሥት ከፍተኛ የሥልጣን እርከን ላይ ሲደርሱ ከማኅበሩ አገልግሎት እንዲርቁ የሚያስገድድ አንዳች ነገር የለም። ሰዎች ወደ ከፍተኛ የሥልጣን እርከን ሲወጡ ባለባቸው የሥራ ጫና እና መደራረብ ምክንያት ከአገልግሎት ሊርቁ ይቻላሉ እንጂ በማኅበሩ አካባቢ ገፊ ነገር የለም።  ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ተከታይ ወይም የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ እርከን ላይ ያለ የማኅበሩ አባል በተከለከሉት የአገልግሎት መደብ ላይ አያገለግልም እንጂ ከዚያ ውጪ ባሉት የአገልግሎት መደቦች ላይ ሊያገለግል ይችላል። በእርግጥ ወደ ማኅበሩ ሲመጣ እንደ ሥልጣኑ ወይም እንደ ፖለቲካ አቋሙ ሳይሆን መንፈሳዊ ሆኖ ነው የሚያገለግለው፤ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ የበላይ እና የበታች ሆኖ ሊያገለግል ይችላል ወደ ማኅበሩ ሲመጣ ግን ሁሉም እኩል ሆኖ ነው የሚያገለግለው። መድረኩም ለዚህ ምቹ አይደለም። በዚህ ምክንያት አባል ሆኖ ስለሚያገለግሉ ብቻ ባላቸው የፖለቲካም ሆነ የመንግሥት ሥልጣን ተጽእኖ መፍጠር አይችሉም በዚህም ስጋት የለብንም። ይህ ልምድ ትላንት ነበረ ፣ዛሬም አለ ነገም በሩ ክፍት ነው።   በእርግጥ ማኅበሩ ብዙ አባል ብዙ መዋቅር እንደመያዙ መጠን ይሄን መዋቅር ለመጠቀም የተለያዩ አካላት ፍላጎት አይኖራቸውም ብሎ ማሰብ አስቸጋሪ ነው። ብዙዎች ሊኖራቸው ይችላል ፍላጎቱን መከልከል አይቻልም። የራሳቸው ፍላጎት ነውና ዓላማቸውን ለማሳካት ፍላጎት ማሳየታቸው ወንጀል አይደለም፤ ማኅበሩ ይህ ፍላጎት እውን እንዳይሆን ነው የሚሠራው፣ የሚከለክለውም።  በመዋቅራችን እንዳስቀመጥነው የማኅበራችን መልካም ስም መዋቅር ዝና ንብረት ሀብት ለዚህ መጠቀም እንደማይቻል መመሪያው ይከለክላል።  ሁለተኛው የማኅበሩን መዋቅር የሚወክሉ ወይም ደግሞ የበላይ ሆነው የሚመሩ እስከታችኛው መዋቅር ድረስ ያሉት አባሎቻችን ከየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ገለልተኛ ስናደርግ ዋና ዓላማው ይሄነው። መዋቅርን ለሌላ ነገር መጠቀም እንዳይቻል ለመከልከል ነው። ከሀገራዊ ምርጫ ጋር ተያይዞ ኦርቶዶክሳውያን በፖለቲካው ንቁ ተሳትፎ እንዳይኖራቸው ማኅበረ ቅዱሳን  በማንም ላይ ተጽዕኖ አላደረሰም ከዚህ ጋር በተያያዘም ምንም የተገደበ ነገር የለም። ሰዎች እንዲህ ሊያስቡ ቢችሉም የማኅበሩ መመሪያ ትላንትም ዛሬም ያለው አንድ ነው።  ማኅበሩ ገለልተኝነቱን ለማረጋገጥ ሲል ከከለከላቸው አባላት ውጪ የከለከላቸው ሌሎች አባላት የሉም። በማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ መሳተፍ የፈለጉትን ፓርቲ መደገፍ የአባላት ግላዊ ምርጫቸው እና መብታቸው ነው። ማኅበሩ እስከዛሬ አባላት በሀገራዊ ጉዳይ ላይ መልካም ነገር እንዲመጣ፣ እንዲፈጠር ንቁ ተሳታፊ መሆን እንዳለባቸው ከጊቢ ጉባኤ ጀምሮ ሲያስተምር ነው የመጣው። አባላት  ለወገናቸው ፣ለቤተ ክርስቲያናቸው ፣ ለሀገራቸው የሚጠቅም ሥራን መሥራት አለባቸው ብሎ ማኅበረ ቅዱሳን በጽኑ ያምናል። ለዚህ ደግሞ አንድ ሰው እንደዜጋ፣ እንደተማረ ሰው ድርብ ኃላፊነት አለበት በማለት በጊቢ ጉባኤ ሲያስተምር ነው የቆየው። ሕዝቡን በታማኝነት በመልካም ሥነ ምግባር ማገልገል አለባችሁ ብሎ ነው ማኅበሩ የሚያስተምራቸው። አባላት በየትኛውም ፖለቲካዊ ጉዳይ አባል ይሁኑ፣ ሀገራቸውን ያገልግሉ ወደማኅበሩ መድረክ ሲመጡ ግን ለአገልግሎት ብቻ ይምጡ ፖለቲካዊ ዓላማቸውን ፣አቋማቸውን እዚያ ያስቀምጡ እዚህ ሲመጡ ለመንፈሳዊ አገልግሎት ብቻ ይምጡ የሚል አቋም ነው ማኅበሩ ያለው። ምናልባት አባላት ወደ ተለያዩ ፓርቲዎች ሲገቡ መዋቅሩን ተጠቅመው ይሆን እንዴ? እነዚህን አባላት ያመጡ የሚል ዓይነት ግምቶችም ሊኖሩ ይችላሉ። ከዚያ ባለፈ ግን  የማኅበሩ መዋቅር በዚህ ቀን በዚህ ቦታ ለፖለቲካ ዓላማ ለፖለቲካ ሥራ እንዲህ አድርጎ ተጠቅሞአል የሚል በተጨባጭ የቀረበ መረጃና ማስረጃ የለም። ከቀረበ ለወደፊቱ ለመያዝ ዝግጁ ነው። ማንኛውም አካል የማኅበሩ መዋቅር ለዚህ አገልግሎት ውሏል ካለ ማኅበሩ አጣርተን ለማስተካከል መልስ ለመስጠት እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ ነው። እስካሁን ድረስ ባለው መረጃ በየትኛውም መልኩ አባላቶቻችን አመራሮቻችን በየደረጃው ያሉት ኃላፊዎቻችን ኃላፊነት የሚሰማቸው ናቸው። ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ቅድሚያ የሚሠጡ ገንዘባቸውን፣ ጊዜያቸውን እውቀታቸውን ለቤተ ክርስቲያን ለመስጠት የመጡ ቁርጠኛ አቁዋም ያላቸው አባላት ናቸው። ከማኅበሩ ሕግና መመሪያ ውጪ ይህን ዓላማ ይጠቀማሉ ብለን አንጠረጥርም።  ሌላው ተጽዕኖ ፈጣሪ የሆኑ ሰዎች ተጽዕኖ ፈጣሪነታቸውን ተጠቅመው መዋቅሩን መጠቀሚያ ሊያደርጉት አይችሉም። በዚህ በኩል የማኅበረ ቅዱሳን አገልግሎት ለዚህ መግቢያ ቀዳዳ አይሰጥም። በመጀመሪያ እንዲህ ዓይነት ሰዎች ሲመጡ በኃላፊነት ወይም በአመራርነት አይመጡም አባል ሆነው በሆነ ክፍል ነው ሊያገለግሉ የሚችሉት። ስለዚህ ተጽዕኖ ፈጣሪነታቸው ዝቅተኛ ነው ማለት ነው። ኃላፊነት ቦታ ላይ ሲሆኑ ነው ተጽዕኖ መፍጠር የሚችሉት። ከዚህ ጋር ተያይዞ በማኅበረ ቅዱሳን የሁሉም ሰው ሐሳብ እኩል ይከበራል። አንድ ሰው ባለ ሥልጣን ስለሆነ የበለጠ ተደማጭ የሚሆንበት መድረክ የለም የሁሉም  ሰው ድምጽ እኩል ነው። ውሳኔ የሚወሰነው እንኳን ሁሉም ሰው ሲስማማ ነው። ስለዚህ ሁሉም አባላት እኩል መብት አላቸው ማለት ነው። በመንግሥት መዋቅር ውስጥ የበላይ እና የበታች ሆኖ ሊያገለግል ይችላል፤ እዚህ ሲመጣ ግን ሁሉም እኩል ሆኖ ነው የሚያገለግለው። መድረካችንም ለዚህ ምቹ አይደለም። ማኅበሩ ስላለው ማኅበራዊ ሱታፌ  በማኅበሩ መመሪያ አንቀጽ ሰባት ላይ ማኅበሩ ያለው ማኅበራዊ ሱታፌ በሚል ወደ ስምንት ነጥቦች ተቀምጠዋል። ባለፉት ዓመታት በሀገራችን  ብዙ አለመግባባቶችና ግጭቶች አይተናል። ተፈጥሮአዊና ሰው ሠራሽ የሆኑ ብዙ ችግሮች በሀገሪቱ ተፈጥረዋል ከዚህ አንፃር በሀገራዊ እና አካባቢያዊ ጉዳዮች የሚከሠቱ ያለመግባባትን በማስታረቅ ሥራ ላይ መሳተፍ እንደ ሃይማኖት ተቋም ሲሠራ ቆይቷል። ከዚህ በፊት በመድረክ መግለጫ ባነንሰጥም በምንቸለው መልኩ እንዲህ አይነት ግጭቶች እንዳይፈጠሩ ስንሠራ ነው የቆየነው።  ማኅበሩ ከላይ እስከታች ያሉትን መዋቅሮች እየተጠቀመ ከአጋርና ከተባባሪ አካላት ጋር እየሆነ ግጭቶች መቅረት የሚችሉበትን፣ አለመግባባቶች የሚያስከትሉትን ጦርነቶች፣ የሚያመጡትን ጉዳት እያሳየ  የሰላምን ጥቅም ደግሞ ሲያስተምር ቆይቷል በመመሪያው ላይ የተካተተውም አጽንኦት እንዲሰጠው ነው። ወደፊትም ግጭቶችን ስለማስቀረት አለመግባባትን ስለማስወገድ በሰፊው የምንሠራ ነው የሚሆነው። በመመሪያው ላይ አጽንኦት እንዲያገኝና በተለይ ሀገራች አሁን ካለችበት ሁኔታ አንፃር ጉዳዩ አድርጎ መሥራት ስለአለበት አንድ ዋና ጉዳይ አድርገን አስቀምጠናል።  ሌላው ማኅበራዊና ሰብአዊ ልማት ለማስፋፋት ሌሎች ድጋፎችን በማድረግ ረገድም  በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች በተፈጠረው ችግር ለረኃብ፣ለእርዛት የተዳረጉ ወገኖቻችን ከመደገፍ ዝም ብለን አልተቀመጥንም። የምንችለውን ድርሻ መወጣት አለብን ብለን ከሀገር ውስጥ እና ከሀገር ውጪ ያሉትን ምእመናንን በማስተባበር በሁሉም አቅጣጫ ላሉ ለችግር ለተጋለጡ ወገኖች፣ ተቋማት ድጋፍ ለማድረግ ስንሞክር የምችለውንም ስናደርግ ነበር፤ አሁንም እያደረግን ነው ያለነው። የወረርሽኝ፣ የሰው ሠራሽ እና የተፈጥሮ አደጋ ሰለባ የሆኑትን የማኅበረሰብ ክፍሎች በመርዳት ረገድ ከማኅበረሰብ ጤና አገልግሎት ጋርም የምንሠራቸው ሥራዎች አሉን። በተለይ  መዋቅሮቻችንን በመጠቀም  ከቤተ ክርስቲያን መዋቅር ፣  ከአጥቢያዎች ጋር በመሆን ስንሠራ ቆይተናል። አሁንም እንዲህ ያሉ ሥራዎችን አጠናክረን እንደምንሠራ ለመግለጽ ነው መመሪያችን ውስጥ ያካተትነው። መዋቅሮቻችንም ይህንን ትኩረታችንንና ጉዳዮቻችንን አውቀው እና ትኩረት ሰጥተው ነው እንዲሠሩ ለማሳሰብ የምፈልገው። ከላይ በዝርዝር ያናቸውንና የወጣውን መመሪያ ተግባራዊ ከማድረግ አንጻርም ማኅበሩ እና መዋቅሩ ትልቁን ድርሻ ይወስዳሉ። በማኅበሩ ሁሉም መዋቅር ላይ ያሉ አካላት ይሄን መመሪያና ሌሎችም መመሪያዎችን በአግባቡ የመተግበር፣ የመጠበቅ ፣የማስጠበቅ ድርሻ ይኖርባቸዋል። ከዚህ አንፃር ሙሉ በሙሉ ወስደው አባላት እንዲረዱት በማድረግ  ካልተፈለገ ተጽዕኖ ነፃ በማድረግ መጠበቅ ይኖርባቸዋል። ይህን ትልቁን ድርሻ የሚወሰዱት ማኅበሩ እና በመዋቅሩ ላይ ያሉ ኃላፊዎች ናቸው። መመሪያን ለሁሉም መዋቅር አውርደናል ሁሉም መዋቅር ያውቃሉ የግንዛቤ መፍጠሪያ ሥራዎችን ሠርተናል። ይህን ለወደፊቱ በሰፊው ማብራሪያ የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮችን ከአባላቱ ጋር እየተወያዩ ግልጽ እያደረጉ እንዲሄዱ እናደርጋለን። ሁለተኛ አባላቱ ናቸው አባላቱ ኃላፊነት የሚሰማቸው ያላቸውን ጊዜ ያላቸውን ጉልበት ዕውቀታቸውን ለቤተ ክርስቲያን እናውል በረከት እናግኝ ብለው የመጡ አባላት ናቸው እና እነዚህ አባላት እንኩዋን ተነግሯቸው ሳይነገራቸውም ምን ማድረግ እንዳለባቸው ያውቃሉ። ስለዚህ አባላት ትልቅ ድርሻ አላቸው ማለት ነው።  የሀገራችንን አሁናዊ ሁኔታና እየደረሠ ያለውን ምርጫ በተመለከተ ሀገራችን አሁን ያለችበት ሁኔታ ሁሉም የሚያውቀው ሲሆን ይህንን ታሳቢ ያደረጉ ሥራዎች ሊሠሩ ይገባል የሚል አቋም ነው ያለን። የሚመለከተው አካል ይህንንን ግጭት፣ አለመግባባት ባጠቃላይ የሰው ሕወት የሚቀጥፉ ነገሮችን እንዴት ማስቀረት እንችላለን? የሚለው ላይ ትኩረት ሰጥተው መሥራት አለባቸው። ከሁሉም ሕይወት ይቀድማል ፣ሰው ይቀድማል ምርጫ ቢደረግ ለሰው ሰውን ለማስተዳደር ነው ሰው ከሌለ ሕዝብ ከጠፋ የሚመረጠው አካል ምንድነው የሚመራው? የሚያስተዳድረው? ስለዚህ ከሁሉ ነገር በፊት የሰው ልጅ ደኅንነት መቅደም አለበት፤ የሰው ልጅ ሕይወት ክቡር ነው ክቡር የሆነውን የሰው ልጆችን ሕይወት የሚያጠፋ ነገር ሁላችንም በመጠንቀቅ መጠበቅ አለብን። ሕገ እግዚአብሔርን ጠብቀን ግንዛቤ እንፈጥራለን ስንልም ይሄንን ነው የሚወቀድመው ነገር መቅደም አለበት። ቅድመ ምርጫ፣ ጊዜ ምርጫ፣ ድኅረ ምርጫ ከግጭት ካለመግባባት መለያየቶች ሊኖሩ ይችላሉ ነገር ግን አለመግባባቶችን በውይይት ከመፍታት አንፃር በሐሳብ ብልጫ የመሸናነፍን ባህል ማዳበር አለብን። አሁንም ያሉ ችግሮች በሙሉ በሰከነ አእምሮ ሊታዩ ይገባል ሽግሌዎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ፣የሚመለከታቸው የሃይማኖት አባቶችም ይህንን ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል። ሁሉም ነገር የሚሆነው ሰላም ሲኖር ነውና። ግጭቶች፣ አለመግባባቶች ቦታ ስለወሰዱ ትኩረት ማግኘት ያለባቸው ነገሮች ትኩረት እያገኙ አይደለም።  በቅርብ ጊዜ እንኳን ያለውን ብናይ አሰቦት ገዳም ላይ የተነሣው እሳት ሀገርን ያጠፋ፤ በ፳ እና በ፴ ዓመት የማንተካቸውን ቅርሶች አገር በቀል የሆኑ ዛፎች በሙሉ ወድመዋል። ይህ የሚያሳየው ግጭቶች ሁሉ ትኩረታችንን እየወሰዱብን እንደሆነ ነው። ስለዚህ ትኩረት መስጠት ካለብን ነገሮች ላይ መረባረብ ቸል ማለት አይገባም። ሁሉም ነገር የሚሆነው ሰላም ሲሆን ነውና ለሰላም ቅድሚያ መስጠት ያስፈልጋል። ስለዚህ ደግሞ ሁሉም  ድርሻውን ሊወጣ ይገባል የሚለው መልእክታችን ነው።  
Read 718 times