Wednesday, 24 March 2021 00:00

መፍትሔ ያልተገኘለት የኦሮምያ ክልል ኦርቶዶክሳውያን ሰቆቃ

Written by  ካሳሁን ለምለሙ

Overview

ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች ከሀገር ውስጥና ከውጭ ሀገራት የኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር በመፋለምና የሕይዎት መሥዋትነትን በመክፈል በመሠረቷትና ሀገር አድርገው በቆሟት ሀገራቸው ውስጥ ባይተዋር ሆነው ከመቆየታቸው ባሻገር ሠርተው ለፍተው በሚኖሩባቸው አንዳንድ ሀገራችን አካባቢዎች በአክራሪ ሃይማኖተኞችና በስሑት ትርክት አቀንቃኞች አማካኝነት እየታደኑ መገደል ከጀመሩ ግማሽ ክፍለ ዘመንን አስቆጥረዋል።  ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች በመሆናቸው ብቻ ያለምንም ምክንያት በአሰቃቂ ሁኔታ ይገደላሉ፤ ሀብት ንብረታቸን ይዘረፋል፤ ሆን ተብሎም ከማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ዘርፎች ይገለላሉ፤ እንዲሁም ከአካባቢያቸው ተፈናቅለው ለሥደትና ለርኀብ ይዳረጋሉ። በአክራሪ ሃይማኖተኞችና በስሑት ትርክት አቀንቃኞች አማካይነት የሚደርስባቸው ጥቃት መነሻው ደግሞ ከዚህ ቀደም  በሀገራችን የነበረው የፖለቲካ ድርጅት ቤተ ክርስቲያንንና ምእመናንን ‹‹በጠላትነትና በጨቋኝነት›› ፈርጆ መነሣቱ ነው። ይህ የፖለቲካ ኃይል ላለፉት ሃምሳ ዓመታት ቤተ ክርስቲያንን የትግል ማእከል አድርጎ ሲያጎሳቁላት፣ ሲከፋፍላት፣ ዶግማና ቀኖናዋንም በመጣስ ሊያጠፋት እልህ አስጨራሽ ትግል ሲያደርግ ቆይቷል።  በመላ ሀገራችን ያሉ የዚህ ፖለቲካ ድርጅት የግብር ልጆች አሁንም ድረስ ቤተ ክርስቲያንን መድፈራቸውን ምእመናንን ማሳደድና መግደላቸውን አላቆሙም። ‹‹የፖለቲካ ለውጥ›› መጥቷል ከተባለበት ጊዜ አንሥቶም በተለይ በኦሮምያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ውስጥ የሚገኙ ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች በየጊዜው በአሰቃቂ ሁኔታ ይገደላሉ። ኦርቶዶክሳውያኑ አብዛኛውን ጊዜ በአክራሪ እስላሞች አማካይነት ይገደሉ እንጂ ከጀርባ ሆነው ጥቃቱን የሚደግፉና የሚያስተባብሩ የክልሉ የፖለቲካ አመራሮች እንዳሉ በተለያየ ጊዜ ከተለያዩ ምንጮች ለመረዳት ችለናል። እነዚህ የአካባቢው የመንግሥት ባለሥልጣናት ከዚህ በፊት በሥልጣን ላይ የነበረው ፀረ ኦርቶዶክስ የፖለቲካ ድርጅት ያወረሳቸውን ኦርቶዶክስ ጠልነት ሐሳብ በተግባር ሲፈጽሙ ቆይተዋል። በመሆኑም ላለፉት ሦስት ዓመታት ብቻ በባሌ፣ በአርሲ፣ በምሥራቅና ምዕራብ ሐረርጌ እንዲሁም በሌሎች የኦሮምያ ክልል አካባቢዎች በርካታ ኦርቶዶክሳውያን ያለ ጥፋታቸው በአሰቃቂ ሁኔታ ታርደው ተገድለዋል፣ ከአካባቢያቸው ተፈናቅለዋል፤ ለረኀብና ለእርዛትም ተዳርገዋል።  ሰሞኑንም በዚሁ ክልል በሆሮ ጉድሮ ወለጋ ዞን አቢ ደንጎሮ ወረዳ ዴቢስ ቀበሌ ላይ  ይንቀሳቀስ የነበረ “ታጣቂ ኃይል” በፈጸመው ድንገተኛ ጥቃት በርካታ ኦርቶዶክሳውን ክርስቲያኖች በአሰቃቂ ሁኔታ በጥይት ተደብድበው፣ በስለትም ታርደው ተገድለዋል። ከአካባቢው የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው ጥቃቱን በንጹሓን ኦርቶዶክሳውያን ላይ የፈጸመው ‹‹ኦነግ ሸኔ›› የተባለው በአካባቢው የሚንቀሳቀስ ታጣቂ ቡድን ነው። ይህ “ታጣቂ ቡድን” በቤተ መቅደስ ውስጥ በጸሎት ላይ የነበሩ ካህናትና ምእመናንን ጨምሮ በየቤታቸው የነበሩ ንጹሓን ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖችን ጭምር በስለት አርዶ በመሣሪያ ደብድቦ እንደገደላቸው ታውቋል።  የሆሮ ጉድሮ ወለጋ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ መልአከ ጽዮን ቀሲስ ተፈራ ቢሻሙ ከዝግጅት ክፍላችን ጋር በስልክ በነበራቸው ቆይታ እንዳስታወቁት ‹‹በአካባቢው የሚንቀሳቀሰው ‹‹ኦነግ ሸኔ›› የተባለው ታጣቂ ቡድን በፈጸመው ሃይማኖት ተኮር ጥቃት ቢያንስ ሃያ ዘጠኝ ኦርቶዶክሳውያን ምእመናን ተገድለዋል›› ብለዋል። ካህናትና መምህራንን ጨምሮ እየተመረጡ የተገደሉት በሙሉ ኦርቶዶክሳውያን ብቻ መሆናቸውን የጠቆሙት ሥራ አስኪያጁ  “ከዚህ በፊት በአካባቢው የፀጥታ ሥጋት እንዳለብን ለወረዳውና ለዞን አመራሮች አሳውቀናል” ሲሉም ተናግረዋል። ‹‹በአካባቢው ያሉት የመንግሥት ባለሥልጣናት ‹‹አባቱ ዳኛ ልጁ ቀማኛ›› ዓይነት በመሆናቸው ለታጠቁ ኃይሎች ድጋፍ ከማድረግና ስንቅና ትጥቅ ከማቅረብ ውጭ የንጹሓን ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖችን ደኅንነት ለመጠበቅ ያደረጉት ጥረት የለም” ሲሉም አክለዋል።  በአሁኑ ሰዓት በአካባቢው የተወሰነ የፀጥታ ኃይል ገብቶ የማረጋጋት ሥራ እየሠራ እንደሆነ የተናገሩት ሥራ አስኪያጁ ‹‹ጥቃት ያደረሰው ‹‹ኦነግ ሸኔ›› የተባለው ታጣቂ ቡድን ጥቃት ካደረሰበት አካባቢ ላይ በቅርብ ርቀት በሚገኝ ጫካ ውስጥ መሽጎ ይገኛል›› ብለዋል። በተለያዩ አካባቢዎች የመሸገው ይህ ታጣቂ ቡድን በአካባቢው ዘላቂ ሰላም እንዳይኖርና ሕዝበ ክርስቲያኑ ሥጋት ላይ እንዲወድቅ አድርጎታል፤ በቋሚነት ታጣቂ ኃይሉን ከአካባቢው ማጽዳት እስካልተቻለ ድረስ  ዘላቂ ሰላምን ማምጣት እንደማይቻል አክለው አስረድተዋል።  በሆሮ ጉድሮ ወለጋ ሀገረ ስብከት የአቢ ደንጎሮ ወረዳ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ኃላፊ የሆኑት መልአከ ገነት ቀሲስ ደመቀ ታደሰ በበኩላቸው በወረዳቸው ‹‹ኦነግ ሸኔ›› የተባለው ታጣቂ ቡድን ሃይማኖት ተኮር ጥቃት እንደፈጸመ ተናግረው በጥቃቱም በርካታ ካህናት፣ ዲያቆናት መምህራንና ምእመናን እንደተገደሉ አረጋግጠዋል። ታጣቂ ኃይሉ መጀመሪያ  ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በጸሎት ላይ የነበሩ አገልጋዮች ካህናትንና ምእመናንን ከገደለ በኋላ በየመንደሩ እየዞረ የቀሩትን ኦርቶዶክሳውያን እንደገደለ ኃላፊው አስረድተው አስከሬናቸው የተገኘ ፲፱ ሰዎች ብቻ ተቀብረዋል›› ሲሉ ተናግረዋል። የሟቾች ቁጥር እስከአሁን ድረስ ፲፱ ይባል እንጂ ፳፪ እና ከዚያ በላይ ሊሆን እንደሚችል ኃላፊው ተናግረው ከተገደሉት በተጨማሪም በርካቶች ታፍነው እንደተወሰዱ አስረድተዋል። የምእመናን ሀብት ንብረት እንደተዘረፈና ቤታቸው እንደወደመም ገልጠዋል።  ጥቃቱ የተፈጸመው የካቲት ፲፯ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም ቅዳሜ ከቀኑ ሰባት ጀምሮ እንደሆነ የጠቆሙት ኃላፊው ቤተሰቦቻቸው የተገደሉባቸውንና ታፍነው የተወሰዱባቸውን ሕፃናት ከነ ነፍሳቸው በአቅራቢያ በሚገኝ ወንዝ ላይ እንደጣሏቸው አስረድተዋል። በወቅቱ ግማሽ የሚሆነው የአካባቢው ሕዝበ ክርስቲያን ወደ ገቢያ በመሄዱ ቀሪዎቹ አቅም ኖሯቸው ታጣቂ ኃይሉን መመከት እንዳልቻሉ ያነሡት ኃላፊው የአንድ ቤተሰብ አባላት የሆኑ በርካታ ሰዎች በአሰቃቂ ሁኔታ እንደተገደሉ አስረድተዋል። አስክሬናቸው እስከአሁን ድረስ ያልተገኘ እንዳለም አክለው  ተናግረዋል።  በወረዳው ሥር ፵፮ አጥቢያዎች የሚገኙ ሲሆን በአካባቢው የሚኖረው  አብዛኛው የኅብረተሰብ ክፍሎች የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች መሆናቸው ታውቆ ጥቃቱ እንደተፈጸመ ያስረዱት ኃላፊው ጥቃቱ ከተፈፀመ በኋላ የተረፉ ምእመናን ተሰብስበው ራሳቸውን ለመከላከል ጥረት ቢያደርጉም ‹‹የኦነግ ሸኔ›› ታጣቂ ኃይል ትጥቅ ከሕዝበ ክርስቲያኑ አቅም በላይ በመሆኑ ለከፋ የጸጥታ ችግርና ለሕይወት መጥፋት እንደተዳረጉ ተናግረዋል። የአካባቢው የመንግሥት ታጣቂ ኃይልም ‹‹የኦነግ ሸኔ›› ታጣቂ ኃይል ደጋፊና መረጃ አቀባይ በመሆኑ ለእነርሱ ችግራቸውን ማስረዳትም ሆነ እገዛ መጠየቅ የማይታሰብ መሆኑን ኃላፊው አስረድተዋል።  አንዳንዴ በአካባቢው ችግር እንዳለ መረጃ ደርሷቸው የፌዴራል የፀጥታ ኃይሎች በቦታው ተገኝተው ማጣራት ሲፈልጉ የአካባቢው የመንግሥት ባለሥልጣናት ችግር እንደሌለ ነግረዋቸው እንደሸኛቸው ያረጋገጡት ኃላፊው “ይህም በመሆኑ የአካባቢው ኅብረተሰብ ለከፋ የፀጥታ ችግር ከመጋለጡ ባሻገር ሕይወታቸውን ሙሉ በሥጋት እንዲያሳልፉ አድርገዋቸዋል” ብለዋል። ባለሥልጣናቱም ለታጣቂ ኃይሉ ሽፋንና የስንቅና ትጥቅ አቅርቦት ከማድረግ ውጭ ለንጹሓን የአካባቢው ኗሪ ምንም ዓይነት የሕግ ከለላ አያደርጉላቸውም ሲሉም ተናግረዋል። ታጣቂ ቡድኑ ካህናትንና ምእመናንን እየመረጠ የገደለ ሲሆን “ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ብቻ ካቃጠልን ድጋሜ ሊሠሩ ይችላሉ፣ ካህናትና መምህራንን ቀድመን ካጠቃን ግን የቤተ ክርስቲያን ሕልውና ያበቃል›› በሚል እሳቤ ተነሳስቶ ጥቃት ሲፈጽም እንደነበረም ኃላፊው ተናግረዋል። ጉዳዩን ከወረዳ እስከ ዞን ላሉ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት በሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ናትናኤልና በሥራ አስኪያጁ በኩል እንዳስረዱ ኃላፊው አክለው ገልጠዋል።  የአቢ ደንጎሮ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ብሪሳ ኃይሌ ጉዳዩን አስመልክቶ ለተነሳላቸው ጥያቄ በሰጡት ማብራሪያ በወረዳቸው የሚንቀሳቀሰው ‹‹ኦነግ ሸኔ›› የተባለው ታጣቂ ቡድን በንጹሓን ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች ላይ አሰቃቂ ጥቃት መፈጸሙን ተናግረው “በአካባቢው በቂ ጥበቃ አሰማርተን ንጹሓንን ስንጠብቅ የነበረ ቢሆንም ከአቅም በላይ በሆነ ችግር ምክንያት ግን  ጥቃቱ ተፈጽሟል” ብለዋል። ዕለቱ የገበያ ቀን በመሆኑም በጥበቃ ላይ የነበሩ አንዳንድ የአካባቢው የፀጥታ ኃይላት ወደሌላ አካባቢ መንቀሳቀሳቸውን ተከትሎ የተፈጸመ ጥቃት እንደሆነም ኃላፊው አስረድተው። “ጥቃቱ የተፈጸመበት አካባቢ ከወረዳቸው ርቀው ጫካ አካባቢ በሚኖሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ላይ እንደሆነ የገለጡት አስተዳዳሪው ይህም ከርቀቱ አንጻር ደኅንነታቸውን የመጠበቁን ሥራ አክብዶብናል” ብለዋል። በወቅቱ ጥቃቱን ያደረሰው ታጣቂ ቡድንም የጥቃቱ ሰለባዎች መረጃ እንዳያወጡ በሚል ተንቀሳቃሽ ስልካቸውን እየነጠቀ እንደገደላቸው አስተዳዳሪው ተናግረዋል።  ታጣቂ ቡድኑ አንድ ቦታ ላይ ሆኖ መዋጋት የማይችልና አሳቻ ሰዓት ጠብቆ ሕዝብን ጨፍጭፎ የሚሠወር ኃይል ነው ያሉት አስተዳዳሪው “ይህም ንጹሓንን ከጥቃት ለመከላከል ፈታኝ አድርጎታል” ብለዋል። ዘላቂ ሰላም በአካባቢው ማስፈን የሚቻለው የአካባቢውን ኅብረተሰብ በዘላቂነት ማደራጀት እንደሆነ አስተዳዳሪው ጠቅሰው “የአካባቢው ኅብረተሰብ ታጥቆ ራሱን እንዲከላከል የማድረግ ሥራ ስንሠራ ቆይተናል፤ ለወደፊቱም አጠናክረን እንቀጥላለን” ሲሉ አስረድተዋል። “በአሁኑ ወቅት በቂ የሚባል የፀጥታ ኃይል በአካባቢው ላይ  በመሠማራቱ አካባቢው የተረጋጋ ሆኗል” ብለዋል”። ጥቃት የተፈጸመባቸው የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች መሆናቸውን አስተዳዳሪው አስረድተው የሟቾች ቁጥርም ሃያ ሁለት ብቻ እንደሆነም ተናግረዋል።   ጥቃቱን ሸሽተው ከተሰደዱ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት አድርገን ወደ አካባቢያቸው የሚመለሱበትን ነገር እያመቻቸን እንገኛለን ያሉት አስተዳደሪው የተሰደዱት ወደ አካባቢያቸው ከተመለሱ በኋላ ውይይቱ ተጠናክሮ የሚቀጥል ሲሆን በቀጣይም ዘላቂ ሰላም በሚመጣበት ዙሪያ አቅጣጫ በጋራ እናስቀምጣለን ሲሉ ተናግረዋል። በታጣቂዎች ታፈነው ከተወሰዱ የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል ሦስት ያህሉን ማስመለስ እንደቻሉም አስተዳዳሪው ለዝግጅት ክፍላችን አስረድተዋል። በአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት ቀርበው በስልክ አስተያየታቸውን የሰጡት የአካባቢው ኗሪ ታጣቂ ቡድኑ ጥቃቱን የጸፈመው የካቲት ፲፯ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም ቅዳሜ ዕለት ከቀኑ ሰባት ሰዓት ጀምሮ እንደሆነ ተናግረው ታጣቂ ቡድን በአካባቢው በሚገኘው መንደር እየዞረ ያገኘውን ሰው ወደ ኋላ በገመድ እያሰረ እንዳረዳቸው አስረድተዋል። በጥቃቱ አረጋውያን ጨምሮ ሕፃናት የታረዱ ሲሆን በተለይ ፲፱ የሚሆኑትን በኋላቸው አስሮ አርቆ በመውሰድ አርዶ እንደገደላቸው ያዩ መሆኑን ለቴለቭዥን ጣቢያው በስልክ ተናግረል።  “ኦነግ ሸኔ” የተባለው ታጣቂ ቡድን በተለየ ሁኔታ ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖችን እያጠቃ መሆኑን ያስረዱት ግለሰቡ የወረዳው የፀጥታ ኃይልም ለታጠቂ ቡድኑ እገዛ እንደሚያደርግለት ተናግረዋል። የአካባቢው ኅብረተሰብ በዚህ ወቅት ወደ መኖሪያ ቀዬው እንዳልተመለሰና ምግብ ለመብላት ብቻ ወደ አካባቢያቸው ዘልቀው ከሰዓት በኋላ ደግሞ ወደ ጫካ ተመልሰው እንደሚሄዱ አያይዘው አስረድተዋል። እስካሁን ድረስም ወደ አካባቢያቸው መመለስ ባለመቻላቸው ሀብት ንብረታቸው በታጣቂ ቡድኑና በተባባሪዎቹ እየተዘረፈባቸው እንደሆነ ግለሰቡ አስረድተዋል።  
Read 452 times