Friday, 04 September 2020 00:00

ዓይን የላቸውም ዓይን ያለንን ግን ይመሩናል፣እጅ የላቸውም ያሰሩናል . . .

Written by  ከቆየ እትም የተወሰደ
ክፍል አንድ በዚህ ዓምድ በሕይወታቸው፣ በአገልግሎታቸው፣ በዕውቀታቸውና በሙያቸ ሊያስተምሩ የሚችሉ እንግዶች እንዲሁም ስለ ቤተክርስቲያን ተቋማትና ተያያዥ ጉዳዮች የሚስተናገዱበት ነው፡፡  እንደ ጥንቱ የአብርሃም ቤት እንግዶች የሚስተናገዱበት በመሆኑም ይህን ስያሜውን አግኝቷል፡፡ እስከ ፲፱፻፶፰ ዓ.ም ድረስ በላስታ አውራጃ በዋልድቢት ማርያም ገዳም ይኖሩ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ቀደም ብሎ የጀመራቸው የሥጋ ደዌ በሽታ ስለተባባሰባቸው ለሕክምና ወደ ደሴ ከተማ መጥተው ከ፲፱፻፶፰-፲፱፻፷፫ ዓ.ም ቦሩ ሜዳ ሆስፒታል ሕክምናቸውን ሲከታተሉ ቆዩ፡፡ ይህ ሕመም ሳይሻላቸውም ዓይናቸው ታመመ፡፡ ከዚያም ለከፍተኛ ሕክምና ወደሻሸመኔ ኩየራ ሔዱ፡፡ ሻሸመኔ ሲደርሱ ግን ሐኪሙ ወደሌላ ቦታ በመሔዳቸው ሳይታከሙ ቀሩ፡፡   ከሻሸመኔ ወደ አገራቸው ለመመለስ የነበራቸው ገንዘብ በቂ አልነበረምና ሌላ መፍትሔ ያፈላልጉ ጀመር፡፡ የታመመ ሐኪም መፈለጉን አይተውምና በ፲፱፻፷፫ ዓ.ም ‹‹ሐኪም አለ›› መባልን ሰምተው ወደ አዋሳ ሄዱ፡፡ ከአዋሳ ይርጋዓለም እየተመላለሱ ይታከሙ ጀመር፡፡ መኖሪያቸውም በዚያው ሆነ፡፡ በመጨረሻም ሕመሙ በከፍተኛ ሁኔታ በመባባሱ በ፲፱፻፹፭ ዓ.ም አዲስ አበባ አለርት ሆስፒታል ሁለት እግሮቻቸው ተቆረጡ፡፡ የዚህ ታሪክ ባለቤት አባ ዜና ገብርኤል ይባላሉ፡፡ 

 

አባ ዜና ገብርኤል አሁን እግሮቻቸውን፣ እጆቻቸውንና ዓይኖቻቸውን አጥተዋል፡፡ የሚንቀሳቀሱትም በተሽከርካሪ ወንበር በሌላ ሰው እየተረዱ ነው፡፡ ይህ ሁሉ ቢሆንም ግን ከቤተ ክርስቲያን አገልግሎት አልተለዩም፡፡ እጅ እግርና ዓይን ባይኖራቸውም እግዚአብሔር በሰጣቸው ጸጋ ቤተ ክርስቲያንን ያገለግላሉ፡፡ በዚህም በአዋሳ፣ በይርጋዓለምና በአካባቢው ወረዳዎች ምእመናንን በማስተባበር በየገጠሩ የሚገኙ የተቸገሩ አብያተ ክርስቲያናትን በመርዳት ላይ ናቸው፡፡ አባ ዜና ገብርአል በሚያበረክቱት በዚህ አገልግሎት ለብዙ ጊዜ ተዘግተው የነበሩ፣ የንዋየተ ቅድሳት የዕጣን፣ የጧፍ፣ የመገበሪያ፣ የአልባሳት … ወዘተ ከፍተኛ ችግር የነበረባቸው አብያተ ክርስቲያናት ተከፍተውና የሚያስፈልገው በመጠኑ ተሟልቶላቸው ለምእመናን አገልግሎት ለመስጠት በቅተዋል፡፡ በተጨማሪም በእድሜ ብዛትና በእንክብካቤ ጉድለት የተጎዱ አብያተ ክርስቲያናትን በማስጠገን ላይ ናቸው፡፡ በዚህ የተነሣ በአዋሳና በይርጋዓለም አካባቢ ምእመናን ዘንድ ከፍተኛ ፍቅርን አትርፈዋል፡፡ ልጅ አዋቂ ሳይሉ በማስተባበር ሊስተካከሉ አይችሉም የተባሉ የብዙ አብያተ ክርስቲያናትን የንዋያተ ቅድሳትና የሌሎች ቁሳቁስ ችግር ለማቃለል ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ ነው፡፡ 

በቤተ ክርስቲያናችን ካሉት አሳሳቢ ችግሮቹ አንዱም ለመገናኛ በማይመቹ አካባቢዎች ያሉ በዕድሜ ብዛት እና በእንክብካቤ እጦት በመፈራረስ ላይ የሚገኙት፣ በውስጣቸው ብዙ ንዋያተ ቅድሳትንና ብርቅና ድንቅ ታሪካዊ ቅርሶችን የያዙት አብያተ ክርስቲያናት ችግር ነው፡፡ ከዚህ አንጻር አባ ዜና ገብርኤል በማድረግ ላይ ያሉት እንቅስቃሴ አበረታችና አስተማሪ ነው፡፡ ስለዚህ ከአባታችን ልንማር ይገባል በሚል የወሩ የ‹‹የአብርሃም ቤት›› እንግዳችን ሆነዋል፡፡ አባ ዜና ገብርኤል የሚኖሩት በአዋሳ ደ/ምሕረት ቅ/ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ ቤት ለእንግዳ…፡፡  

ዓይን የላቸውም ዓይን ያለንን ግን ይመሩናል፣ እጅ የላቸውም ያሠሩናል …

ስምዐ ጽድቅ፡- ስለትውልድዎ፤ ስለአስተዳደግዎና እስከአሁን ስላለው ታሪክዎ ቢገልጹልን?

አባ ዜና ገብርኤል፡- ሊጠቀስ የሚችል ብዙም ታሪክ የለኝም፡፡ ብዙውንም ሥራ ራሴን ደብቄ በስውር ሳከናውን ነው የኖርኩት፡፡ ስለዚህ እዚህ መጥቀሱ ተገቢ አይመስለኝም፡፡ 

ስምዐ ጽድቅ፡- የገጠር አብያተ ክርስቲያናትን መርዳት የጀመሩት መቼና እንዴት ነበር?

አባ ዜና ገብርኤል፡- /ከዚያ በፊት ያለውን ትተነው/ በ፲፱፻፸ ዓ.ም ሐምሌ ፲፫ ቀን ቤተ ክርስቲያን ቆሜ ጸሎት ሳደርስ አንዲት ሴት ተንበርክከው እያለቀሱ እመቤታችንን ይመጸኑ ነበር፡፡ /ሴትየዋ ወ/ሮ ሙሉ እመቤት ይባላሉ፡፡ በቅርቡም አርፈል/ በወቅቱ ወ/ሮ ሙሉ እመቤት ‹‹እንግዲህ መዘንጋቱን አንቺም ወደሽዋል…›› እያሉ ያለቅሱ ስለነበርና ስላሳዘኑኝም ጸሎታቸውን ሲጨርሱ ‹‹ምን ሆነው ነው?›› ብዬ ጠየቅኋቸው፡፡ እርሳቸው ከሚኖሩበት ከአለታወንዶ እየተመላለሱ የሚረዷትና ለፍልሰታም ለካህናትና ለመቀደሻ የሚያስፈልገውን ወጪ ሁሉ እየሸፈኑ የሚያገለግሏት ቤተ ክርስቲያን ካህን ጠፍቶ ለማስቀደስ እንዳልቻሉና ያሳዘናቸውም ይኸው እንደሆነ ነገሩኝ፡፡ ቀደም ሲል ቤተ ክርስቲያኒቱ በባላባቶች ተከባ በአካባቢውም ምእመናን እየተረዳች ትኖር ነበር፣ ከደርግ መምጣት በኋላ ግን ተከትሎ በመጣው ችግር ያለረዳት በችግር ኖራለች፡፡ 

በዚህ መነሻነት በጣም አዝኜ በወቅቱ ወደነበሩት የወረዳው ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ ሔጄ ጉዳዩን አስረዳኋቸው፡፡ እርሳቸውም ችግሩን ተረድተው ከሻሸመኔ ካህን እንዲመጣ አስደረጉልንና ያቺ ቤተ ክርስቲያን ፍልሰታን ተቀደሰባት፡፡ ወ/ሮ ሙሉ እመቤትን ስለ ቤተ ክርስቲያኒቱ በጠየቋቸው ጊዜ የዕጣን፣ የጧፍ፣ የአልባሳት፣ የመገበሪያና ሌሎችም ችግሮች እንዳሉ ነገርውኝ ስለነበረ ከዚያ ቀን ጀምሮ የተለያዩ ሰዎችን በመጠየቅ የሚሰባሰበውን በየዓመቱ ለሴትዮዋ እየሰጠሁ፣ ካህናትንም ቀደም ብዬ በመፈለግና በማዘጋጀት ይህችን ቤተ ክርስቲያን በስውር ስረዳ ቆየሁ፡፡ እንግዲህ የመጀመሪያ መነሻ ይኼ ነው፡፡ 

ስምዐ ጽድቅ፡- ይህ አገልግሎትዎ አሁን ወዳለበት ደረጃ ያደገውስ እንዴት ነው?

አባ ዜና ገብርኤል፡- በእርግጥ አሁን አገልግሎቱ አድጓል፡፡ በ፲፱፻፹፭ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ ሔጄ እግሮቼ ተቆርጠው ወደ አዋሳ ከተመለስኩ በኋላ ልጆች ሊጠይቁኝ ይመጡ ነበር፡፡ ቤትም ጽዋ ይጠጡ ነበር፡፡ በዚህም መሠረት ግንቦት ፳፩ ቀን በነበረ ማኅበር ላይ አንድ መምህር ስለጽዮን ማርያም በሰፊው ካስተማረ በኋላ ገንዘብ አዋጥተን አክሱም ጽዮንን ብንረዳና ብንጎበኝ የሚል ሃሳብ አቀረበ፡፡ 

በነገሩ ላይ ስንወያይም አክሱም ጽዮንን ሔዶ መሳለም በረክቷንም ማግኘት ተገቢ እንደሆነ ተነጋገርን፡፡ ከዚሁ ተጓዳኝ ግን በአቅራቢያችን በየገጠሩ ያሉትን አብያተ ክርስቲያናትንም ማስታወስና መርዳት እንደሚገባ ተስማማን፡፡ ለዚህም ብዙ ቅርሳቅርስ የሚገኝባቸው፣ ታሪካዊ የሆኑ ነገር ግን የንዋየተ ቅድሳት፣ የዕጣን፣ ጧፍ እና ሌሎችም ችግሮች ያሉባቸው፣ በመፈራርስ ላይ የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት መኖራቸውን አስታውሼ የአቅማችንን እንርዳ የሚል ሐሳብ አቀረብኩ፡፡ ለመነሻ እንዲሆነንም የሲቄ ማርያም ቤተ ክርስቲያንን አስተዋወቅኋቸው፡፡ ሲቄ ማርያም በአለታ ወንዶ ወረዳ የምትገኝ ቤተ ክርስቲያን ነች፡፡ 

በሐሳቡ በመስማማታችን በእኔ አስተባባሪነት ርዳታ ማሰባሰቡን ጀመርን፡፡ እኔ እንደ ድሮው ተዘዋውሬ ለመለመን ባልችልም ልጆቹ ያሰባሰቡትን ፭፻ ብር ሐምሌ መጨረሻ ላይ አምጥተው ሰጡኝ፡፡ እኔም ብሩን ለወ/ሮ ሙሉ እመቤት ሰጥቼ ልጆቹ ቦታዋን አይተው እንዲመጡ ላኳቸው፡፡ 

የስቄ ማርያም ቤተ ክርስቲያን ሁኔታ በጣም አሳዛኝ ነበር፡፡ በመንግስት ለውጥ ጊዜ /፲፱፻፹፫/ በተፈጠረው ሁኔታ የመቃብር ቤቶቹ ቆርቆሮ ሳይቀር እየተነቀሉ ተወስደዋል፡፡ ደጀ ሰላሙም ፈራርሷል፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱ አጥር ስለሌላትም ከብቶች የቤተ ክርስቲያን ሕንፃ እየታከኩ አፈራርሰውታል፡፡ ይህ ሁሉ ያዩት ልጆች በየወሩ መዋጮ ለማዋጣትና የሲቄ ማርያምን  ቤተ ክርስቲያን ብቻ ሳይሆን ሌሎች የገጠር  አብያተ ቤተ ክርስቲያናትንም ለመርዳት ወሰኑ፡፡ ሥራውን የማስተባብረውም እኔ ነበርኩ፡፡ 

በዚህም መሠረት መስከረም ፳፩/፲፱፻፹፮ ዓ.ም በአሥራ ዘጠኝ ፈቃደኛ ሰዎች በተጀመረው እንቅስቃሴ በዚያው ዓመት የሲቄ ማርያም ቤተ ክርስቲያንን አጥር አሳጥረን፣ የቤተ ክርስቲያኑን ሕንፃ ግድግዳና ደጀ ሰላም አጠናክረን አሠራን፡፡ አሸዋ ከይርጋዓለም በማስመጣት ወለሉንና ግድግዳውን በሚገባ ለማሠራት ቻልን፡፡ ከዚህ በኋላ አገልግሎቱ እየሰፋ፣ የሚሳተፉትም ምእመናን ብዛት እየጨመረ ሔደ፡፡

ስምዐ ጽድቅ፡- ምእመናንን ሲያስተባብሩ ዋና ዓላማዎ ምን ነበር? 

አባ ዜና ገብርኤል፡- ዋና ዓላማችን ከመገናኛ እጥረት ከቦታ ርቅት የተነሣ ረዳት ያጡ አብያተ ክርስቲያናትን መርዳት ነው፡፡ በተለይ ከ፲፱፻፷፯ ዓ.ም ጀምሮ የአካባቢያቸው ሰዎች በመፈናቀላቸው ለከፍተኛ ችግር የተዳረጉ፣ ዙሪያቸውን በመናፍቃን የተከበቡ፣ ተንከባካቢ አጥተው በመፈራረስ ላይ ያሉ ብዙ ቅርሶችን የያዙ አብያተ ክርስቲያናት ቁጥር ጥቂት አይደለም፡፡ ስለዚህም ሁላችንም ባለብን የሃይማኖት ግዴታ መሠረት ያለፍላጎታቸው ወደመናፍቃን የሚፈልሱትን ምእመናን ለመመለስና በተያዩ ችግሮች የተነሣ ሳይቀደስባቸው የሚቆዩ አብያተ ክርስቲያናትን ለመርዳትና ባሉበት ለማጠናከር አቅማችን የፈቀደውን እየረዳን ነው፡፡ በአጠቃላይ ምእመናንን በማሰባሰብ ሰባኪ መድቦ ወንጌል እየተሰበከላቸው፤ ቅዳሴ እየተቀደሰላቸው በንስሓ እየተመለሱ ቤተ ክርስቲያንን እንዲያገለግሉ ማድረግ ነው ዓላማችን፡፡ 

ስምዐ ጽድቅ፡- በእርስዎ አስተባባሪነት የረዷቸውን አብያተ ክርስቲያናት ጥቂቱን ቢጠቅሱልን? 

አባ ዜና ገብርኤል፡- ብዙ ናቸው፡፡ የማስታውሳቸውን ብቻ ልንገርህ፡፡ የመጀመሪያዋ የሲቄ ማርያም ቤተ ክርስቲያን ነች፡፡ ይህች ቤተ ክርስቲያን የምትገኘው በሸበዲኖ ወረዳ ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሕንፃ በጣም ተጎድቶና ፈራርሶ ስለበረ በሚገባ አሠርተናል፡፡ 130  ቆርቆሮ የሚፈጀውንም ጣራ በአዲስ መልክ አሠርተናል፡ በተጨማሪም አዲስ መንበርና የእንግዳ መቀበያ ቤት ሠርተናል፡፡ ቀድሞ በወር አንድ ጊዜ እንኳ የማይቀደስበት ቢሆንም ልዑካኑን በማሟላት በየሳመንቱ እሑድ እንዲቀደስ አድርገናል፡፡ የአንዱን ካህንና የአንዱን ዲያቆን አበል የምንከፍለውም እኛ ነን፡፡ በተጨማሪም በአካባቢው ቋንቋ የሚያስተምሩ መምህራንን አስፈላጊ ወጪ በመሸፈን ምእመናን እንዲማሩ ጥረት እያደረግን ነው፡፡ 

ይቆየን

Read 604 times